ይህ ቃለመጠይቅ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ተስፋዬ ጋር (19 April, 2014) ካደረጉት ቃለምልልስ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡፡
አዲስ አድማስ፤ ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በሬዲዮ ፋና ላይ በነፃው ፕሬስ ዙሪያ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ እርስዎም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በውይይቱ ላይ “ዶ/ር ዳኛቸው ስሜታዊ ሆነው ነበር” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የሚል ትችትም ተሰንዝሮቦታል፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
ዶ/ር ዳኛቸው፤ የስሜታዊነቱን ነገር ያመጡት እንኳን እነሱ ናቸው፡፡ ስድብና ዘለፋውን በመጀመር እነሱ ይቀድማሉ፡፡ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” ለሚለው በእውነቱ በናፍቆት ደረጃ ፍትህ ናፋቂ ነኝ፡፡ ዴሞክራሲና የህዝባችንን ነፃነት ናፋቂ ነኝ፡፡ የዱሮ ሥርዓት ናፋቂ የሚሉኝ “አሁን ያለንበት ወርቃማው ጊዜ ነው” የሚሉ ዜጎች ናቸው፡፡ “ያለፈው ስርዓት ናፋቂ” የሚለው አባባል ሆን ብሎ ሰዎችን ለማሸማቀቅ የተፈጠረ ቃል ነው፡፡ በሌላ መልኩ የአሁኑ ስርዓት እኮ በጣም የተሻለ ነው ለማለት ነው፡፡ እኔ የዛሬ 40 ዓመት ወደ ኋላ ሄጄ ለማወዳደር የፈለግሁት አጠቃላይ ሥርኣቱን ሳይሆን የመናገር ነጻነትን በተመለከተ ርዕስ ብቻ ነበር፡፡ ይህንንም ለመናገር የዕድሜ ባለጸጋም ነኝ፡፡ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” በሚባልበት ጊዜ አንድ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ተምሬያለሁ፡፡ ያኔ የተሻለ የመናገር ነፃነት ነበር ብያለሁ፡፡ ይህንን አባባሌን አሁንም እደግመዋለሁ፡፡ “በአፄው ጊዜ የፈለግነውን ለመተቸት የዩኒቨርሲቲው ህግ ይፈቅድልናል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ መዲና ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተነስተሸ አንድ ፖለቲካዊ የሆነ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ አስተያየት ብትሰነዝሪ ከጸጥታ ኃይሉ የሚጠብቅሽ ችግር ይኖራል፡፡” ስላልኩኝ ነው “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የተባልኩት፡፡ ይሄ አይነተኛ የሆነ የካድሬዎች ማስፈራሪያና በነፃነት የሚናገሩ ሰዎችን ማሸማቀቂያ መንገድ ነው፡፡ እኔ እኮ የድሮ ትዝታ አለኝ፣ ልናፍቅም እችላለሁ፡፡
አዲስ አድማስ፤ ለምሳሌ ከድሮው ስርዓት ምን ምን ይናፍቅዎታል?
ዶ/ር ዳኛቸው፤ ለምሳሌ የእንግሊዝ ፈላስፋ ኤድመን በርክ “Familiarity” የሚል ስለ ትዝታ ያነሳው ሀሳብ አለ፡፡ “ፋሚሊያሪቲ” ምንድነው? መተዋወቅ፣ ያሳለፍነው ትዝታ፣ትውስታ ማለት ሲሆን፤እንደ አርሱ አቀራረብ በአንድ ጉዳይ ላይ ስለተዋወቅን ብቻ መናፈቅ፣ የሰው ልጅ ባህሪና ፀጋ ነው ይላል፡፡ ገባሽ? እኔ የጥንቱን የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ እናፍቃለሁ፣ የፖሊስ ኦርኬስትራንም እንዲሁ፡፡ ዛሬ አንድ ኪቦርድ አስቀምጠው የሚዘፍኑትን ከምሰማ የእነዚያን ኦርኬስትራዎች ሥራ ብሰማ እናፍቃለሁ፡፡ የፈረሱትን የድሮ ሲኒማ ቤቶች— እነ ሲኒማ አድዋን እናፍቃለሁ፡፡ የድሮውን የመድረክ ተውኔት እናፍቃለሁ፡፡ የድሮው የክብር ዘበኛ አለባበስ ከፈረሳቸውና ከነማዕረግ ልብሳቸው ትዝ ሲለኝ እናፍቃለሁ፡፡ እንዴ ብዙ ብዙ የምናፍቀው ነገር አለኝ— እሱን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ በሰፈሬ ሳልፍ አሁን የደረቀው ቀበና ወንዝ ከነሙላቱ ይናፍቀኛል፣ ድሮ ለምሳሌ ሆቴል ገብተን ክትፎ በ75 ሳንቲም “ቅቤ ይጨመር?” እየተባለ የምንበላው ይናፍቀኛ…..እንዴት ያለ ነገር ነው! ድንች በሥጋ ወጥ 15 ሳንቲም የነበረበት ጊዜ ይናፍቀኛል፡፡ የድሮዎቹ አስተማሪዎቼ ይናፍቁኛል፡፡ ታዲያ የድሮውን መናፈቅ ምን ነውር አለው? ምንስ አድርግ ነው የምባለው?
Leave a Reply