ቻይናዎች “አንድ ሀገር መበልፀግ ከፈለገ መንገድ መገንባት አለበት” የሚል አባባል አላቸው። በዚህ መሰረት ሀገሪቱ በየብስና ባህር ላይ “የሀር መንገድ” (Silk Road & Silk Maritime) ለመገንባት አንድ (1) ትሪሊዮን ዶላር በጀት መድባለች። ይህ የሀር መስመር በሚያልፍባቸው 68 ሀገራት ውስጥ 900 የሚሆኑ ትላልቅ የአስፋልት መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የባህር ወደቦች፣ የመብራት ማመንጫ ግድቦችና ማሰራጫዎች፣ የጋዝ (ነዳጅ) ማስተላለፊያ ትቦዎች ለመገንባት ወይም ለመዘርጋት የተመደበ ከፍተኛ በጀት ነው።
ይህ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚገኘው ከቻይና ልማት ባንክ (China Development Bank CDB), ከቻይና ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ (China Ex-Im Bank)፣ ከኢሲያ መሰረተ-ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ (Asia Infrastructure Investment Bank – AIIB), ከሀር መንገድ ፈንድ (Silk Road Fund-SRF)፣ የቻይና ግንባታ ባንክ (China Construction Bank – CCB)፣ የቻይና ግብርና ባንክ (Agricultural Bank of China – ABC)፣ እንዲሁም ከቻይና መንግስት ኢንቨስትመንት ፈንድ (State owned Investment Fund) እና ከቻይና ግል ባንኮች ናቸው።
በዚህ መልኩ ከሚገኘው ውስጥ የተወሰነው በቻይና መንግስት ድጋፍ ወይም ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) የሚውል ነው። የተቀረው ግን እንደ ሁኔታው በአነስተኛ ወለድ ወይም በገበያ ላይ ካለው መጠን ትንሽ ዝቅ ባለ የወለድ መጠን በሀር መስመር ላይ ላሉ ሀገራት በብድር መልክ የሚሰጥ ነው። የቻይና መንግስት በድጋፍ መልክ ከገነባቸው ወይም በቀጥታ ኢንቨስት ካደረገባቸው ውስጥ፤ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ዋና ፅ/ቤት፣ የጥሩነሽ-ቤጂንግ ሆስፒታል፣ እንዲሁም በቻይና መንግስት ድጋፍ የተሰሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ትምህርት ቤቶች እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ። የተጠቀሱት የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚከናወነው በቻይና ድጋፍ ወይም እርዳታ ብቻ ሳይሆን በቻይና ተቋራጭ ድርጅቶች አማካኝነት ነው። በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ደግሞ የድርጅቱ አመራር ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ሰራተኞች ቻይናዊያን ናቸው።
ሌላው ከቻይና ባንኮች በተገኘ ብድር የሚሰሩ ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚሰጡት ለቻይና ተቋራጭ ድርጅቶች ነው። እነዚህ ተቋራጭ ድርጅቶች ከባለሙያዎች ባለፈ አንዳንዴ የጉልበት ሰራተኞችን ጭምር ከቻይና ያስመጣሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታን እያከናወነ ያለው የቻይና ተቋራጭ ድርጅት (CCCC) ሰራተኞች ከሞላ-ጎደል ሁሉም ቻይናዊያን ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩት የቻይና ተቋራጭ ድርጅቶች የሚጠቀሙት የግንባታ ግብዓቶች በዋናነት ከቻይና ኢንዱስትሪዎች የተገዙ ናቸው።
በመጨረሻም የቻይና መንግስት የሚገነባቸው 900 የሚሆኑ ትላልቅ የአስፋልት መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የባህር ወደቦች፣ የመብራት ማመንጫ ግድቦችና ማሰራጫዎች፣ የጋዝ (ነዳጅ) ማስተላለፊያ ትቦዎች በዋናነት የቻይና የውጪ ንግድን ለማቀላጠፍና ለማስፋፋት ዓላማ ያደረጉ ናቸው። በመሆኑም ከቻይና መንግስት በሚሰጥ ድጋፍና ብድር የሚሰሩት የመሰረተ ልማት አውታሮች በሙሉ የሀገሪቱን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት በሟሟላት እና ለኢንዱስትሪ ምርቶች ተጨማሪ ገበያ በማግኘት ላይ ማዕከል ያደረጉ ናቸው።
በዚህ መሰረት የቻይና መንግስት በባህርና የብስ ላይ ለሚገነባው የሀር መስመር ከመደበው አንድ ትሪሊዮን ዶላር ውስጥ አብዛኛው ተመልሶ ወደ ቻይና ይሄዳል።
አንደኛ፡- በቻይና ተቋራጭ ድርጅቶች የግብዓት ግዢ፣ ለሰራተኞች በሚከፍሉት ደሞወዝ፣ ለቻይና መንግስት በሚከፍሉት ግብር እና ከሥራው በሚያገኙት ትርፍ፤
ሁለተኛ፡- ለቻይና ባንኮች በሚከፈለው ብድርና ወለድ አማካኝነት ዶላሩ ተመልሶ ወደ ቻይና ይሄዳል።
በሌላ በኩል የቻይና ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃዎችን በአንስተኛ ዋጋ ስለሚገዙ የምርት ወጪያቸው ይቀንሳል እና ለምርቶቻቸው ደግሞ ተጨማሪ ገበያ ያገኛሉ። በዚህ ምክንያት ቻይና ከውጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ በብዙ ቢሊዮን ዶላር ይጨምራል።
ከላይ በተገለጸው መሰረት ቻይና ለሀር የንግድ መስመር ግንባታ የመደበችው አንድ ትሪሊዮን ዶላር ከመመለሱም በላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፍጥነት እንዲያድግ ያስችለዋል። በአንፃሩ የሀር መንገድ ፕሮጀክት አካል የሆኑት ሀገራት ደግሞ ትላልቅ አስፋልት መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ የአየር ማረፊያዎች፣ የመብራት ማመንጫ ግድቦች፣ የነዳጅ ማስተላለፊያ ትቦዎች እና የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች ይኖሯቸዋል። ሁለተኛ እነዚህን መሰረተ ልማቶች ለመገንባት ከቻይና መንግስት ባንኮች የወሰዱት ብዙ ቢሊዮን ዶላር ብድርና ወለድ ይከመርባቸዋል።
በመሰረቱ ታዳጊ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት አገልግሎት እጥረት አለባቸው። በመሆኑም ከቻይና መንግስትና ባንኮች ባገኙት ብድር የገነቧቸው መሰረተ ልማቶች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ከማቀላጠፍ አንፃር አዋጭ ከሆኑ ሀገራቱ የዕዳ ጫና ውስጥ አይገቡም። በብድር የተገነቡት የመሰረተ ልማት አውታሮች አዋጭ ካልሆኑ ግን ሀገራቱ የዕዳ ጫና ውስጥ ይወድቃሉ። የመሰረተ ልማት አውታሮች አዋጭነት እንዲኖራቸው የኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነት እና የሀገሪቱ የውጪ ንግድን ማደግ አለበት።
በሀር መንገድ ፕሮጀክት የሚሰጠው ብድርና ድጋፍ ከቻይና ጋር የሚደረገውን ንግድ ለማቀላጠፍ ነው። ስለዚህ ሀገራት ከቻይና መንግስት በሚሰጣቸው ፈንድና ብድር አዳዲስ እንዱስትሪዎችን ለመገንባት ወይም ነባር ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት አያገለግልም። በፕሮጀክቱ መሰረት የሚገነቡት የመሰረተ ልማት አውታሮችም ቢሆን የቻይናን የውጪና ገቢ ንግድ ለማሳደግ እንጂ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ዓላማ ያደረገ አይደለም። በዚህ ምክንያት የሀገራቱ ምርትና ምርታማነት አያድግም፣ በውጪ ንግዱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ አይመጣም። ስለዚህ የሀገራቱ የብድር ወለድ እየጨመረ ሄዶ በዕዳ ጫና ውስጥ ይወድቃሉ።
ከዚህ አንፃር በቻይና የሀር መንገድ ፕሮጀክት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላት ሲሪላንካ አይነተኛ ማሳያ ነች። በአምባገነንነታቸው የሚታወቁት የቀድሞ የሲሪላንካ ፕረዜዳንት በአብዛኛው በአነስተኛ ብድር ከቻይና መንግስትና ባንኮች 4.8 ቢሊዮን ዶላር ተበድረዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በ1.8 ቢሊዮን ዶላር በአመት አንድ ሚሊዮን መንገደኞች የሚያስተናግድ የአውሮፕላን ማረፊያ በፕረዘዳንቱ የትውልድ ሰፈር ገነቡ። “Mattala Rajapaksa International Airport” በሚል በአምባገነኑ መሪ ስም የተሰየመው እጅግ ዘመናዊ የሆነ አውሮፕላን ማረፊያ ተመርቆ ሥራ የጀመረው እ.አ.አ. በ2013 ነው።
ከሦስት አመት በኋላ በአመት አንድ ሚሊዮን መንገደኞች ያስተናግዳል የተባለው አውሮፕላን ማረፊያ በሳምንት አንድ አውሮፕላን ብቻ ማስተናገድ ጀመረ። ምክንያቱም ማረፊያው የተገነባው በፕረዘዳንቱ ልዩ ፍላጎት እንጂ በገበያ አዋጭነቱ አይደለም። በዚህ ምክንያት የአውሮፕላን ማረፊያው በየአመቱ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አለው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሳምንት አንድ በረራ እንኳን ማስተናገድ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ብዛት ያላቸው የዱር እንስሳት በአውሮፕላን ማረፊያ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመግባታቸው ነው።
አስገራሚው ነገር በአውሮፕላን ማረፊያው ከገቡት የዱር እንስሳት ውስጥ አንዱ ዝሆን ነው። በዚህ መልኩ ያለ በቂ የአዋጭነት ጥናት በ1.8 ቢሊዮን ዶላር የተገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ በመጨረሻ የዝሆን ማረፊያ ለመሆን በቅቷል። ከአውሮፕላን ማረፊያው በተጨማሪ ወደዚያ የሚወስደው ትልቅ አስፋልት መንገድ ጭምር ባዶ ነው። ከዚያ በተጨማሪ በሲሪላንካ ዋና ከተማ የተገነባው የኮሎምቦ ወደብ ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር የተሰራ ነው። ይህም ወደብ ልክ እንደ አውሮፕላን ማረፊያው ባዶ ነው።
ከላይ በተገለጸው መሰረት ስሪላንካ ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር የገነባቻቸው መሰረተ ልማቶች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እሴት የሚጨምሩ አይደሉም። በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ወድቃለች። ይህን ተከትሎ የቻይና መንግስት በሰጠው ብድር የተሰራውን ወደብ በ99 ዓመት ሊዝ ገዝቶታል። ለዚህ ደግሞ የቻይና መንግስት የገዛውን ወደብ ለመጠበቅ በሚል የባህር ሰርጓጅ መርከቦቹን እና ወታደሮቹን በስሪላንካ ባህርና መሬት ላይ ማንቀሳቀስ ጀምሯል።
እ.አ.አ. በ2015 አምባገነኑ መሪ ከስልጣን ተወግዶ በአዲስ ፕረዜዳንት ቢተካም በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠው የዕዳ ጫና ፈቀቅ አላለም። አዲሱ ፕረዜዳንት ወደ ስልጣን እንደመጣ የወሰደው የመጀመሪያ ተግባር የሀገሪቱ አየር መንገድ ወደ “Mattala Rajapaksa International Airport” የሚያደርገውን በረራ ለማቋረጥ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ማፅደቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የቻይና ኩባንያዎች በሀገሪቱ የንግድና ግንባታ ሥራዎች ላይ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርቧል። አንድ የቻይና ዲፕሎማት እንደተናገሩት ስሪላንካ ያላት አማራጭ ፊቷን አዙራ ቻይናን ማቀፍ ነው። ምክንያቱም የቻይና መንግስትና ባንኮች በሰጡት ብድር ምክንያት የተፈጠረው የዕዳ ጫናው በስሪላንካ ላይ የሉዓላዊነት አደጋ ጋርጧል። ይህ የቻይና ጅብ ነው!
(ምንጭ፤ Ethiopian Think Thank Group by Seyoum Teshome; (የመግቢው ፎቶ ከኢንተርኔት የተወሰደ ነው፤ ሌሎቹ በጸሃፊው የተመረጡ ናቸው)
ተመስገን መላኩ says
ሀገራችን ከዚህ አኳያ ለቻይና ያላት አመለካከት በስሜት የጋመ ሳይሆን በማስተዋል የበሰለ መሆን አለበት ባይ ነኝ ፡፡ እጅ ለማጉረስ ብቻ ሳይሆን ለመደቆስም እንደሚሰነዘር ታሳቢ ማድረግ አለባት፡፡
Delta Tango says
የቻይና ጅማሮ ዉጤት እንዳያስገኝ-ሀገራችን ከወድሁ በሙሰኞች በመራቆቷ, በእዳዋ ምክንያት እንደ ስሪላንካ መሆናችን መች ይቀራል?