
የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካል የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ማክበር ካልቻለ ሥርዓት ተሰብሯል ማለት እንደሆነ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ተናገሩ። ላለፉት አራት ዓመታት ሪፖርት ሊያቀርቡ ባለመቻላቸው አፈጉባዔውን ወቅሰዋል።
ፕሬዚዳንቷ ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ፣ ከፍተኛና ጠቅላይ፣ እንዲሁም የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን፣ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ ክንውን ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት ነው።
ምክር ቤቱ ባካሄደው የአንድ ቀን የፍርድ ቤቶች ግምገማ ከምክር ቤት አባላትና ከሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች፣ ፍርድ ቤት ከወሰነላቸው በኋላ ውሳኔ የማይከበርላቸውን አካላት በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
የሕግ ባለሙያው አቶ በፍቃዱ ድሪባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ድርጅት በመወከል የተገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሦስቱ የመንግሥት አካላት አንዱና ትልቁ ዜጎች የመጨረሻ የመብት ጥሰት ሲገጥማቸው መብታቸውን ሊያስከብሩበት የሚችሉበት ተቋም በመሆኑ፣ በማንኛውም መንገድ ይህ ተቋም የሚወስነው ውሳኔ አጠያያቂ መሆን እንደሌለበትና ቀይ መስመር መቀመጥ እንዳለበት ተናግረዋል።
በመሆኑም የአንድ ዳኛ ውሳኔ ለማስከበር እስከየትኛውም ርቀት ድረስ መሄድ እንዳለበት የገለጹት አቶ በፍቃዱ፣ ለአብነት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አንድ ዳኛ የወሰነውን ውሳኔ እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ የተሰጠው ፖሊስ ጉዳዩን ባለማስፈጸሙ ምክንያት፣ ፖሊሱ ላይ ማዘዣ እንደወጣ፣ ፖሊሱ አልታዘዝ በማለቱ ደግሞ የፖሊሱ አለቃ ላይ ማዘዣ የወጣበትን ክስተት አውስተዋል።
በመሆኑም ዳኞች በዚህ ደረጃ ቆራጥ መሆን እንዳለባቸው በመጥቀስ አንድ ዜጋ ያለ አግባብ አንድ ሰዓትም ቢሆን መታሰር እንደሌለበት ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ በበኩላቸው፣ ፓርላማው የመስክ ምልከታ በሚያደርግበት ወቅት ያጋጠሙ በርካታ ቁልፍ የሆኑ ችግሮች ያሏቸውን በመጥቀስ፣ ለምሳሌ ያህል፣ “በውሳኔ መዘግየት ምክንያት እስር ላይ የሚቆዩ ሰዎች ማየት በጣም ውስጥን የሚነካ ነገር ነው፤” ብለዋል።
በዚህም ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እየተጣሰ እንደሆነና እንዲህ እየሆነ ያለው በእስር ላይ ባሉ ዜጎች ችግር ሳይሆን፣ በተለያዩ ተቋማት ተቀናጅቶ ባለመሥራት የተነሳ መሆኑን ጠቁመዋል። ለምሳሌ ፖሊስ በወቅቱ ጉዳይ ባለማጣራቱ ምክንያትና በመሰል ሰበቦች የሚቀርቡ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቶች በዚህ ውሳኔ ሳያገኙ እንዲቀሩ በሚደረጉ ሰዎች ላይ ምን ትላላችሁ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
የውሳኔ አፈጻጸምን በተመለከተ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ ምላሽ ሲሰጡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ሁልጊዜም ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። ለአብነት በፍርድ ቤቶች በዓመት 200 ሺሕ ጉዳዮች እንደሚታዩና ከዚህ ውስጥ ችግር ያጋጠመው ከአምስት ወይም ከስድስት እንደማይበልጥ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ያም ሆኖ ጉዳዩ ሁልጊዜ ጎላ ብሎ ሲጠየቅ እንደሚሰማ በመጥቀስ፣ “የፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጥቶ መፈጸም ያቃተን ካለ ግን፣ መዝገቡ ይምጣልን ክትትል እናደርጋለን፤” ብለዋል። “ከዚያ አልፎ አስፈጻሚው ይህንን ማክበር ካልቻለ፣ ሥርዓት ተሰብሯል ማለት እንደሆነ፣ ይህ ከፍተኛና ከፍርድ ቤትም ያለፈ ችግር በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነት ጉዳይ ያለው አካል ማስረጃ ይዞ ይምጣ እኛ ክትትል አድርገን እስከ መጨረሻው ድረስ እንሄዳለን፤” ብለዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ማጉላላት እንዳለ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ አልተፈጸመም የሚል አካል ካለ ግን አሁንም ማስረጃ ይዞ ይምጣ ብለዋል።
“በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኃላፊነት ከተሰጠን አራት ዓመት ቢቆጠርም፣ የፍርድ ቤቶችን አፈጻጸም ሪፖርት ሙሉውን ለፓርላማው እንድናቀርብ ዕድል አላገኘንም፤” ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል።
“ሪፖርት ባለማቅረባችን ክቡር አፈ ጉባዔውን በግል እወቅሳቸዋለሁ፤” ሲሉ የተናገሩት ወ/ሮ መዓዛ፣ “ወቅቱን ጠብቀን ከሥር ከሥር መረጃ ባለማቅረባችን ምክንያት መቅረብ የነበረባቸው ጉዳዮች ይበዛሉ፤” ሲሉ አክለው ተናግረዋል። ሆኖም ሙሉ ፓርላማው ላይ ሪፖርት ለማቅረብ ዕድል ባይገኝም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመውሰድ አሁናዊ የፍርድ ቤቶች ሪፖርት በሚል መረጃ እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
የፍርድ ቤት ሪፎረም መሬት ላይ ያለው አተገባበር ዝቅተኛ ነው ተብሎ ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ “ቁጭ ብዬ አንዳንድ ጊዜ ሪፖርት ሳነብ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ስንነጋገር፣ እውነቱን ልንገራቸሁ፣ ራሴን ማመሥገን አይሁንና ይህ ሁሉ ሥራ እንዴት ተሠራ ብዬ እጠይቃለሁ፤” ብለዋል። አሁን በሥራ ላይ ያለው አመራር ትልቁ ጥንካሬ ከዚህ ቀደም ታስበው ያልተሠሩ ሥራዎችን ለመሥራት ማሽኑን በማንቀሳቀስ፣ ወደ 30 የሚደርሱ መመርያዎች ማዘጋጀት መቻሉ ቀላል አለመሆኑን፣ ነገር ግን የፍርድ ቤት ሥራ ሰፊ በመሆኑና ፍርድ ቤት ሲሶ መንግሥት በመሆኑ ሥራው ተጀመረ እንጂ አላለቀም ብለዋል።
ለረዥም ዓመታት በዕቅድ ላይ የነበረውን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዘመናዊ ሕንፃ ግንባታ፣ ፍርድ ቤቱ ምንም እንኳ መሬት ተቀብሎ ዲዛይን አውጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊዙን በማቋረጥ ካርታውን እንዳመከነው፣ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መስቀል ዋቅጋሪ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የሕንፃ ግንባታ ጨረታ ለማውጣት ያልመከነ ካርታ ስለሚያስፈልግ፣ “ፓርላማው በጀት እንደመደበልን ሁሉ፣ ቦታውን አግኝተን ሕንፃውን መገንባት እንድንችል ዕገዛ ያድርግልን፤” በማለት ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply