
ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ሕገ-መንግስቱ የፀደቀበት ቀን ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በመንግስት አሳሳቢነት እልፍ ሲልም አስገዳጅነት ህዳር 29 በየዓመቱ ከተለያዩ ጎሳ የተወጣጡ ሰዎች ተሰባስበው በመንግሰት ሹማምንቶች ፊት በአደባባይ ከበሮ የሚደለቅበት ቀን ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን መልካም ፍቃድና ተሳትፎ ባልታየበት የፀደቀው ህገ መንግስት በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከቃሉ አጠቃቀም ጀምሮ እስከ አከባበሩ ክብረ በዓል አብዛኛዉ ሰው እኔንም ጨምሮ ግድ አይሰጠንም፡፡
‹‹ይህ ህገ-መንግስቱን የመነዳ ተግባር ነው!!!›› ከገዢው መንግስት ተደጋግሞ የሚሰማ ለመፈረጅ ወይም ለመከሰስ የሚጠቀሙበት ቃል ነው፡፡ አንድ ወዳጄ እንዲህ አለኝ ‹‹ይህ ህገ መንግሰት ዝም ብሎ የተደረደረ ብሎኬት ነው እንዴ የሚናደው?›› በማለት ሲተች ሰምቸዋለው፡፡ በመናድ እና ደግፎ በማቆየት ላይ የተመሠረተሁን ህገ መንግስት እጅግ በጣም ብዙ ነገር ተብሎለታል፡፡
እየተንገዳገደ ያለው ህገ መንግስት ከአፀዳደቁ ጀምሮ የሚቀሩት ድንጋጌዎች መኖራቸው ለማንም ግልፅነው፡፡ ቢሆንም ፀድቆ በተግባር ላይ የሚገኘው ህገ መንግስት ዋጋ እንዳይኖረው እያደረገ ያለው የገዢው መንግስት አካሄድና ተግባር መሆኑ በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለው፡፡
1ኛ. መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገባም የሚለው በሕገ መንግስት አንቀጽ 11 ንዕሱ አንቀፅ 3 ተደንግጎ የሚገኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ገዢው መንግስት በሃይማኖት ላይ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት እየፈፀመ ይገኛል፤ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በእስልምና አይማኖታ እየተፈፀመ ያለው በደል ነው፡፡ በደሉ በይፋ የወጣ ሲሆን በተለይ ለእምነታችን እንቢኝ ያሉ ለሞት፣ ለእስርና ለእንግልት ተዳርገው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪ በኦርቶዶክስ እምነት ውስጥም ጣልቃ ገብነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ ገዳማትና አድባራት በልማት ስም ፈርሰዋል የተቀሩት ቦታቸው ተጎምዶ ተወስዶል በዚህም ምክንያት የሀይማኖት አባቶችና ጥቂት የማይባሉ የእምነቱ ተከታዮች ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ በሁሉም በተለይ በኦርቶዶክስና በእስልምና የሀይማኖቱ መሪዎች (አባቶች) ሹመታቸው ከሚያመልኩት አምላክ እና ከምዕመናኖ የመነጨ ሳይሆን በመንግስት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የተፈፀመ ነው፡፡
2ኛ. የመንግስት አሠራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ በሕገ መንግስት አንቀጽ 12 ንዕሱ አንቀፅ 1 ተደንግጎ የሚገኝ ነው፡፡ ቢሆንም ከታችኛው የስልጣን እርከን ከሆነው ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይኛው የመንግስት ባለስልጣናት አማከኝነት የሚከናወኑ የመንግስት አሰራሮች ግልፅነት እጅግ በጣም ጠባብ ነው፡፡ በመሆኑም ህብረተሰብ በአገሩ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን በመንገስት አሠራር ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አልተደረገም፡፡
በዚህም ምክንያት የመንግስት አሠራር ለሙሱና የተጋለጠ ነው፤ሙሱና በአሁን ወቅት በአገራችን ህጋዊ እስከመሆን ደርሷል፡፡ በመሆኑም ማናኛውም የመንግስት ኃላፊ ኃላፊነቱን ወይም ስልጣኑን መሠረት አድርጎ ሲበድል እንጂ ለበደሉ ተጠያቂ ሲሆን አልታየም፡፡ስለዚህም የመንግስት አሠራር በየትኛውም ደረጃ ለህዝብ ግልፅ አይደለም ይህ ደግሞ የህገመንግስቱ ድንጋጌ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡
3ኛ. ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡ ተብሎ በህገመንግስቱ አንቀፅ 14 ተፅፎ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የሰው ደህንነትን ለመጠበቅ የተቋቋመው የደህንነት መስሪያ ቤት በየደኑና በየጫካው የስንቱን ሰው ህይወት እንዳጠፋና የአካል ጉዳት እንዳደረስ የሚያውቀው ያውቀዋል፡፡ በተጨማሪ ይህ የነፃነት መብት ገዢው መንግስት በችሮታ ወይም በፍቃዱ የሰጠን እንጂ ሰው በመሆናችን ያገኘነው መብት እንዳልሆነ በሚያሳብቅ መልኩ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት በገዢው መንግስት መልካም ፍቃድ ላይ የተመሠረተ እስከሚመስል ደረስ ተደርሷል፡፡
4ኛ. ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡የሚለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 18 ላይ ይገኛል፤ ይህ የህገመንግስት ድንጋጌ መሸራረፍ ሳይሆን መገርሰስ የሚጀምረው በህገመንግስቱ በተቋቋመው በህግ አስፈጻሚው አካል ነው፡፡
በመሆኑም ክብርን ለማወረድና ጭካኔን ለማሳየት የሰለጠኑ አሰቃዮችና ማሰቃያ ቦታዎች መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ነገሩን ለማነፃፀር እንዲረዳ ፖለቲከኛ ወይም በህግ ጥላ ስር ያለ ሰውን ይቅርና ስታዲዮም እግር ኳስ ለመመልከት ወራፋ የሚጠብቅ በወረፋ ምክንያት ለተነሳ አለመግባባት ፖሊስ እንዴት አድርጎ እንደሚቀጠቅጥ ዱላውን የቀመሰ ያውቃል፡፡
5ኛ. በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቅ መልኩ የመያዝ እና ከሰዎች ወይም ከጠያቂዎቻቸው የመገናኘት መብት አላቸው፡፡ በማለት በህገመንግስቱ አንቀፅ 21/1እና2 ተፅፎ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ነፃ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች አያያዛቸው ክብርን ከመንካት አልፎ በህይወታቸው ላይ አደጋ የሚያስከትል ነው፡፡ በተጨማሪ ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ መጠየቅ የማይሞከር ነገር ነው፤ የመጠየቅ እድል ያላቸው እስረኞች እድላቸው በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
6ኛ. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የአመለካከት እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ የመግለፅ ነፃነት አለው፡፡የሚለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 29 ተፅፎ ይገኛል፡፡ በእርግጥ ይህ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል በህገ መንግስቱ ላይ ተገልፆ የተቀመጠ ሲሆን ገደብ ግን መሠረታዊ የሆነውን መረጃን የመስጠት እና የማግኘት እንዲሁም አስተሳሰብ ላይ ወይም አመለካከት ላይ ውጤት እንደማይኖረው በህገመንግስቱ ተገልፆ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ አሳብን በነፃ ማሰብና ማንሸራሸር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ ነፃ አሳብ የሚንሸራሸርባቸው ነፃ ጋዜጦችና መፅሔቶች ምን ያህል አሉ? እርግጥ ነው ገብያውኑ መሰረት ያደረጉ መዝናኛ ላይ ያተኮሩ መፅሔትና ጋዜጣ ለቁጥር በዝተው ይሆናል፡፡ ግን ሁሉ ነገር በአገር ነው የሚያምረው! ታዲያ ስለ አገር በነፃ አሳብ የሚንሸራሸርበት መፅሔትና ጋዜጣ ምን ያኸል ነው? ጋዜጠኞችን በማሰቃየት፣በማሰር እና እንዲሰደዱ በማደረግ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ መጥፎ ሪከረድ አስመዝግባለች፡፡ መንግስትን ተችቶ የፃፈና ፁሁፉ የወጣበት ጋዜጣ ወይም መፅሔት ጨምሮ ሁሉም ተጠራርጎ ቃሊቲ የሚገባበት ወይም አደገኛ ዛቻና መስጠንቀቂያ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
7ኛ. ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ ሠላማዊ ሠልፍ እና ስብሰባ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ተብሎ በህገመንግስቱ አንቀፅ 30/1 ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን የቅርብ ጊዜ አይን ያወጣ የህገመንግስት ጥሰት ማቀረብ ይቻላል፡፡ በሳውዑዲ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደል ይቁም፣ይህንንም የፈፀሙ ለፍርድ ይቅረብ በማለት አቤቱታ ለማቅረብ የተጀመረው ሠላማዊ ሠልፍ በፖሊስ ዱላ እና እስራት ነው የተጠናቀቀው፡፡ በተጨማሪ በመንግስት እየታየ ያለው የአስተዳደር ብሉሹነት ለማመልከት እና ምላሽ ለማገኘት የተጠሩ የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች እና ስብሰባዎች በመንግስት ቀጥተኛ ትእዛዝ ተከልክሏአል፡፡ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ እና አቤቱታ ማቅረብ መብት ነው! በማለት ክልከላውን ወደ ጎን በመተው አደባባይ ለመውጣት የሞከሩ ለእስርና ለድብደባ ተዳርገዋል፡፡ በመሆኑም የተቃውሞ ሠልፍና ስብሰባ በማድረግ አቤቱታ በኢትዮጵያ ማድረግ የሞት ሽረት ትግልና ጥያቄ ከሆነ ሰንብቷል፡፡
8ኛ. የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ሆነ አካል ተፅዕኖ ነጻ በመሆን በሙሉ ነፃነት ከህግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም፡፡በማለት በህገመንግስቱ አንቀፅ 79 እና በተከታዮቹ ንዑስ አንቀፅ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ዳኞች የመንግስት አስፈፃሚ አካል ከሆነው ነው ሹመታቸውን የሚያገኙት፡፡ በመሆኑም ከመንግስት ጋር ቀጥተኛ ግኝኙነት ያላቸው የፍርድ ውሳኔዎች ምንያኽሉ በህግ እና በህሊና ላይ የተመሠረቱ ናቸው? በተለይ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች የፍርድ ሂደታቸው ምን ይመስል ነበር? እነዚህን እና መሰል ዳኝነቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በህገመንግስቱ የሰፈረው ነጻ ዳኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡
9ኛ. የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የጎሳዎች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል፡፡ ተብሎ በህገመንግስቱ አንቀፅ 87/1 ተደንግጎ ይታያል፡፡ ነገር ግን በየድንበር እና በተልኮ ጭዳ ከሚሆነው ውጪ አብዛኛው የሠራዊቴ አባል እና አዛዥ የአንድ ጎሳ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህም ሠራዊቱ የማነው የኢትዮጵያ ወይስ ወደሚል ጥያቄ እያመራ ይገኛል፡፡
10ኛ. በየደረጃው ትክክለኛ ምርጫ እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፡፡ የሚለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 102 ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎች ሹመታቸው ከመንግስት መልካም ፍቃድ የመነጨ ሲሆን አሰራራቸውም ለገዥው መንግስ በእጅጉ በጣም ያደላ ነው፡፡ስለዚህም ምርጫ ቦርድ ህገመንግስቱን መሠረት አድርጎ ነጻ እና ገለልተኛ ነው ለማለት ከበድ ድፍረትን የሚጠይቅ ነው፡፡
በመሆኑም እነዚህ እና መሰል የህገመንግስቱ ድንጋጌዎች ጥሰት ወይም በእነሱ ቋንቋ የመንድ ተግባር እየተፈፀመ ያለው በህገመንግስቱ በየወንዙ ዳር የሚማማለው ገዥው መንገስት ነው፡፡ ህገመንግስት የበላይ ህግ ነው፡፡ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣን አሰራር ከህገመንግስቱ የሚቃረነረ ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ የሚለው አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 1 የገዥው መንግስት ደራሽ ዉሃ ጠራርጎ ወስዶታል፡፡ ስለዚህም የብሔሮ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚለውን መጠሪያ ስም በመስጠት ከበሮ ተይዞ የሚደለቅለት እና የሚከበረው ህገመንገስት መልሶ ካላስከበረ ፌሽታው እና ቀረርቶው ከምን የመነጨ ነው?
የህወአት ማኒፌስቶ (ህገመንግስት) በኮከብ ባንዲራ ታጅቦ *ተከብሮና ተፈርቶ የሚስፈራና የሚስፈራራ በለው!..
**በመንግስት አሳሳቢነት እልፍ ሲልም አስገዳጅነት ህዳር 29 በየዓመቱ ከተለያዩ ጎሳ የተወጣጡ ሰዎች ተሰባስበው በመንግስት ሹማምንቶች ፊት በአደባባይ ከበሮ የሚደለቅበት ቀን…ዘንድሮ በጅጅጋ በፍርሃትና በሽብር ቀለጠ አሉ…እንዳውም ሽጉጥ የታጠቁ አላፊ አግዳሚውን ምን ትሰራላችሁ?በቄአቸውና በአጥራቸው ጥጋት የት ልትሔዱ ነው? ሲባሉ ሌሎችም መሳሪያ ለመፈተሽ የተደበቀ አሸባሪ በዚህ አልፏል ሲሉም በእየሰው ቤት እየገቡ የድሃ ቤተሰብ ጥሪት በመሥረቅ ሥራ ከፍተው ለበዓሉ ድምቀት ሲሰጡት ከርመዋል፡፡ ዓላማው ምን? ለማን? የማን? እንደሆነ ያልታወቀው ጭፈራና ግርግር ሽብር…የአካባቢውን ጸጥታ ለማስከበር ተሠማርተናል የሚሉም ወጠጤ ካድሬና የሥርዓቱ አሸባሪ ቡድኖች የተለያዩ ሞባይል ቴሌፎናችን በድብቅ እየተጠቀሙ መኪና ውስጥ ተደብቀው በሚጠብቋቸው ግብረህይል በመታገዝ “መንግስት ምሳና አራት ገንዘብ ከአካባባው ሕዝብ እንድንወስድ አዞናል ይህም እንደገቢያችሁና እንደቤተሰባችሁ ብዛት ለለደህንነታችሁ ጥበቃ ፶ እና ፻ ብር ክፈሉ ተብላችኃል” እያሉ ገንዘብ ሲቀበሉ መኪና ውስጥ ለሚጠብቃቸው የዝርፊያው ስምሪት ኀላፊ “ወ/ሮ እከሊት ወይንም አቶ እከሌ ይህንን ያህል ገንዘብ ለምሳችን በፍቃደኝነት ሰጥተውን ለብሔር ብሔረሰብ ክብረበዓል ደስተኛነታቸውንና ሕገመንገስቱ የሰጣቸውን ማንንት ተጠቅመው ለዝግጅታችንና ለአካበቢው ሠላም ሙሉ ተሳታፊነታቸውን አሳይተዋል ይመዝገብላቸው እያሉ ሲያጭበረብሩ ሰንብተዋል በእርግጥ ብሔር ብሔረሰብ ብዝበዛ ወይስ እገዛ? ከህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ሕገ-መንግስቱ ከፀደቀበት ቀን በፊት ያልጨፈሩ ሁሉ አልኖሩም ማለት ነው። “የብሔር ብሔረሰብ ሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች!? ህወአት የክርስትና ልጆች መሆናቸው ነው!?
*ይህ የደርግ እርዝራዥ ከዳተኖች፣ የሶሻሊስት ሀገር ደንቆሮዎችና ዛሬ ጸሐይ የበራላቸው አውርቶ አደሮች፣ሙሰኞች በማህበር ተደራጅተው በጥቅም ተቃቅፈው የሚያንቆለጳጵሱትና እኛ ከሌለን ይፈርሳል፣ደግፉት እንጂ አትደገፉት ይናዳል፣ አከብሩት እንጂ አትጠይቁት የሚሉት ፸፪ከመቶ ማንበብና መጻፍ የማይችል መሀይምና ድሃ ህጻናትን የሚያጃጅሉበት ቃላትና የምሁር ተብዎዬች ማሽቃበጥ ይገርማል። ፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ የህግ ተንታኝ፣ የትግል በታኝ ኢኮኖሚ አቀንቃኝ ሆኖ ሲሞላፈጥ ማየት በጣም ያሳዝናል በእርግጥም ትውልዱን አጃጅለውታል አፍዝዘውታል አምክነውታል እንደበቀቀን ያልገባው እንደወረደ ሳይሸራረፍ ሲደግም ፳፪ዓመት አሯል።
*ይህ ጭንቅላቱ ከካናዳ፣እግሩ ከሕንድ፤እጁ ከአውሮፓ፣ልቡ ከጫካ የተገጣጠመ ጽሑፍ ያስፈራራል ያሸብራል!
1ኛ/ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም:
– በአንድ ሃይማኖት ተከታዮች በውስጣቸውም ይሁን ከሌላው ሃይማኖት አማኝ ጋር በተናጠልም ይሁን በጋራ ሲጋጭ መንግስት ጣልቃ አይገባም በእጅ አዙር ግን ይረዳል ሕገመንግስታዊ መብት ይባላል። ለመንግስት ተገዢ ያልሆነና በምርጫም በገንዘብም በሐሳብም የተለየ አመለካከት ያለው ማናቸውም የሃይማኖት ተቋምና ሀይማኖተኛ ላይ መንግስት በቀጥታ ይገባል፣እስር ቤትም ያስገባል!ሁሉም በህወአት የተፈጠረና በአንድ ጥላ ሥር ለመኖር ምሏልና!
2ኛ/ የመንግስት አሠራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡
-ሕዝብ ማለት? ያው የፈረደበት ብሔር ብሔረሰብ አደለምን?በአዳራሽ ከሰበሰበውና ካስጨበጨበው ፣መስቀል አደባባይ ካስጨፈረው፣ቤተመንግስት ገብቶ ንፍጥና ለሀጩን ካስዝረከረከ፣ አባይን ወንዝ በደቦ ለሱዳንና ለግብፅ ቦንድ ሸጦ ከበሮ ካስደለቀው ፣ለጅቡቲ ኬንያና ሱዳን መብራት አብርቶ ለራሱ ሻማና ጣፍ ካበራ፣አረብ ቻይና ህንድ ቱርክ ሀገሩን ተከራይቶ በነፃ እያሰራ ካኖረው፣ ህወአት ባለሥልጣናት በሙስና በበሉት አብዛኛው በርሃብ ካገሳ፤ የሀገር ሉዓላዊነት፣ወደብ፣ ሰንደቅ ዜግነት፣ቋንቋና ሃይማኖት ባሕልና ታሪክ ያለገደብ እያጠፋ ካስፈነጠዘው፣ ትውልድ እያባከነና እያመከነ ያለው የባንዳ ቡድን ከሀገር እየገፋፋ ወጣቱን በሕጋዊ ፍቃድ ሲሸጠው፣ የመሰለፍ፣ መሰብሰብ፣ መጻፍና መጠየቅ በመብቱን ከገፈፈው፤ ዛሬም በሰው ሀገር ተደብድቦ፣ ተፈንክቶ፣ ተዋር፣ዶ ተደፍሮ፣በሜንጫ እኢጀአ ግር አንገቱን ካስቀነጠሰው፣ ወደሀገሩ ሲመጣ እየለመነበት፣ለመሆኑ ከዚህ የበለጠ ግልጽ ጥፋታዊ አሠራር የት ሀገር አለ? እረ እባካችሁ ህወአትን ብዙ አትጠይቁ ገና በፋውንዴሽን ትመራመራላችሁ!በግልፅ በመሆነ አሠራር መረመር የሚጨምሩህ በውጭው ዓለም ተምረው ጨርሰዋል የበይ ተመልካች ሆነህ ትሞታላህ ወይ ይገባኛል ትላላህ!? አብልቶ በልቶ ከሚያባላ አድርባይ፣ብሔርተኛ፣ተከልልው የተቀመጡ የቁም እንስሶች መች ይሆን የሚፈቱት?ይህ ግልጽ የሆነ የመንግስት ተብዬ የጥፋት ተልዕኮና ተግባር የግድ በሕገመንግስት መደገፍ አለበትን??
3ኛ/ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው፡
-“ሰው ሰብኣዊ” ሆኖ ከተፈጠረ በኋላ ማንነቱን የሚያጣውም የሚያሳጣውም መንግስትና ፓርቲ ነው ማለት ነው!? ህወአት/ወያኔ/ኢህአዴግ ፀሐዩ መንግስት የምድር ገነት የብሔር ብሔረሰብ አባት ሆነ ማለት ይህ አደለምን!?
5ኛ/ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቅ መልኩ የመያዝ እና ከሰዎች ወይም ከጠያቂዎቻቸው የመገናኘት መብት አላቸው፡፡
– ሰብዓዊ ክብር የህይወት አባታቸው ህወአት/ወያኔ ብቻ እነደሆነ ማማን፤በህወአት መፈጠራቸውን በቃለመሐላ ማረጋገጥ፣ያልሰሩትን ሁሉ አምነው ይቅርታ መጠየቅ፣መንግስት መርጦ ለሚልክላቸው ጠያቂዎች፣ ሽማግሌዎች፣ የእምነት ሰባኪ ካድሬዎችን ተቀብሎ ማስተናገድና ቢቻል ተመልሰው በማናቸውም የህወአት/ወያኔ የጥቅም የፖለቲካና ኢኮኖሚ የገቢ ምንጭ በሆኑ ተቋማት አካባቢ እንዳይደርሱ፡ ማናቸውንም ጥያቄዎች እንዳያነሱ፣ ተመልሰውም ተሳትፎ ቢያደርጉና ሚስጠር ቢያወጡ በህይታቸው መፍረዳቸውን በቃለ መሀላ ለንስሃ አባቶቻቻው በማሳመን ይፈታሉ። ሳይሞቱ ፍታትና በመንግስት ተወካዮች መገናኘትና መጎብኘት ሕገመንገግስታዊ መብት ማለት ይህ አደለምን?
6ኛ/ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የአመለካከት እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ የመግለፅ ነፃነት አለው፡
-ማታ ኢቲቪ ያወራውን ጠዋት ሪፖርተር ጋዜጣ ያስነብበዋል፤ምሳ ላይ የታወቁና የታጠቁ የኤፍ ኤም አውርቶ አደሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ህዝብ ችንቅላት አዙረው ተዟዙረው በቀን አበል ቢራ ሲጠጡ ክትፎ ሱበሉ ውለው፤ ማታ ታላላቅ ምሁራን በእየ ቡናቤትና አንዳንዶችም በቲቪ መስኮት ሆዳቸውን እያሹ ንበረት እያሸሹ ትውልድ እያበላሹ፣ በሙስና ዕድገት ሲምነሸነሹ፣በውሸት ትንታኔ ህዝብ ሲያደናቁሩ በነጻ ሀሳባቸውን የሚያንሸራሽሩና ሀገር የሚሸረሽሩ አሉ።ለመሆኑ በሀገሪቱ ስንት ጋዜጣ፣የቲቪ ጣቢያ፣ ድረገፀች፣መጽሔቶች፤አሉ የማን ናቸው?ያስተምራሉ?ያማርራሉ?
7ኛ/ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ ሠላማዊ ሠልፍ እና ስብሰባ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡
-የት? ጃንሜዳ ብቻ ለብሔር ብሔረሰቦች ሲሆን: እንዴት? ለጭፈራና ለመዳራት ከሆነ ቲሸርት ባርኔጣና አንገት ልብስ ኢህአዴግ አቅርቦ መሸጥ ከቻላ ብቻ። መቼ? በማስፈቀድ፣ በማሳሰብና በመማፀን፣ በመለመንና ሙስና በመስጠት፣በአዋቂና ታዋቂ፣ አድናቂና ተመጻዳቂ ልዩ ባለሥልጣናት አማላጅነት ሚፈጸም(የሚፈቀድ) ለምን? ነጻ አውጭው ፓርቲ(አውራው)ብቻ የሞተለትና የሚገድልባት ልዩ የዜግነት መብትና ሥልጣን ለጥቂቶች ብቻ ነውና!?
8ኛ/ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ሆነ አካል ተፅዕኖ ነጻ በመሆን በሙሉ ነፃነት ከህግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም፡፡
-እንኳንም በጥብቅና፣ በዓቃቢ ሕግና፣ዳኝነት የተቀመጡ ብቻ አደለም ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ነፍሳት ሁሉ በኢህአዴግ ሳንባ ብቻ ሊተነፍስ በማኒፌስቶ በረጅሙ ታስሯልና፤ የፍትህ አካሉ ፖለቲካዊ አመራር ተሰጠው ማለት ተጽኖ አደረበት ተብሎ አይጠቀስም!በሙሉ ነጻነት ላይ ተመርኩዞ ሥራ የተባለውን ብቻ ሊሠራ በፍቃደኝነት ገሊ የገባ የታጋይ አኗኗሪ የኮንትራት ነዋሪና ተቀጣሪ ያልተማረ የተማረረ ያልኖረ ግን ለመኖር ያሰበ ተብሎ ይጠቀሳል።
9ኛ/ የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የጎሳዎች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል፡፡
-ብሔር፩ ብሔረሰብ፪ እና ህዝቦች፫ ለመሆኑ ማ ማነው? አንዳንዶች ከሰኞ እስከ ዕረቡ (ትግሬ)ህወአት ሓሙስና አርብ ኦሮሞ፣ ቅዳሜ የብሔር ብሔረሰብ፣ እሁድ አማራ ይሆናሉ፡፤ ማታ ማታ ግን ኤርትራዊ ይሆናሉ። አቶ ስብሃት በዋስንግተን ዲሲ ሀገርፍቅር ሬዲዮ ላይ እንደአስተማሩት “ከትጥቅ ትግል ጀምሮ አሁንም በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ አትዮጵያን የሚመሩት ኤርትራውያንና ትውልደ ኤርትራውያን ናቸው እኔም ኤርትራዊ ነኝ።አራት ነጥብ።ለመሆኑ ተገንጥለናል?ለምን?ለጥቅም ሲባል! ከማን?ጌታና ባሪያ!የተገነጠልነው ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ብቻ?
10ኛ/ በየደረጃው ትክክለኛ ምርጫ እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል: -ግን ሁሉን ውሸት እውነት አድርገን እንዴት ልንዘልቀው ነው ለማናቸውም ፳፪ኣመት እንደቀልድ አጥፍተን ጠፋ! ምርጫው ትክክል ነው። ኮሮጆው የት ሔደ? ማን አየው? ማን ቆጠረው? በአበል የተላከ ምራጭ ካድሬና ከልብ ለሀገሩ የወጣ መራጭ የትኛው ይበልጣል?ለመሆኑ የምርጫ ቦርድ ወይንስ የምርጫ ቦንድ!?
**ነሐሴ ፲፭ ቀን ፲፱፻፹፯ በመፈቃቀድና በነፃ ፍላጎት በአንድ የፖለቲካ ጥላ ሥር ተሰባስበን ኢትዮጵያ የምትባል(ፎርጅድ) ሀገር ላይ ለመኖር ተስመምተናል ይላል። የህወአት (ማኒፌስቶ) ህገመንግሰት ከዚያ በኋላማ ብሔር ብሔረሰብ ለባሕላዊ ጭፈራና ለባሕላዊ ለቅሶ አለገደብ ሆነ መድብለ ፓርቲ ቀርቶ ደብል ፓርቲ (አውራ ፓርቲ) ሆኖ የተነሳውን ሁሉ እየቀናነሰ በላው!። “የተጨፈረለት መሬት ላራሹ” “መሬት ለኢህዴግ መራሹ መንገስት ” ሆነ እንኳንም ልትኖርበት ልትቀበርበትም በፍቃድ ሆነ፤ ጭሰኛው ጨሰ!
**”በእኛ ያመናችሁና የተፈጠራችሁ ሁሉ ብሉና አብሉ ተባሉና “በምረቃ ተጀመረ….በ“ፎርጅድ” ሙያ የሚያሰለጥን “ስውር ተቋም” እራሱ ህወአትሻቢያ ሆነ። (ከሽብርተኝነትም ፎርጅድ እራሱ እያፈነዳና እየገደለ እያሰረ የሚጮህና የሚያጯጩህ ሆነ!)ህገመንግስት የበላይ ህግ ነው፡፡ማንኛውም ህግ፣ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣን አሰራር ከህገመንግስቱ የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም።የብሔሮ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚለውን መጠሪያ ስም በመስጠት ከበሮ ተይዞ የሚደለቅለት እና የሚከበረው ህገመንገስት መልሶ ካላስከበረ ፌሽታው እና ቀረርቶው በሕዘብ ማላገጥ በትውልድ ማፌዝና ማፍዘዝ ነው። በሕግ አምላክ በለው!በቸር ይግጠመን!
አንደ መልእክት አለኝ ለኢትዮጵያ መንግስት
እባካችሁ ዝም ብላችሁ ስራችሁን ስሩ አዲስ አባን አሳምሩ ኢትዮጵያን አሳምሩ ለእንደዚህ ከላይ እንደጻፈዉ ሰዉ አይነት አሉባልታ ጆሮአችሁን ደፍናችሁ አገሪቷን አድሱ ወደፊት ታሪክ ያስታዉሳችሃል እንደነዚህ ያሉትን ስራ ፈቶች ከዚህም በላይ እንደሚዘባርቁ አትጠራጠሩ
እነዚህን ሰዎች ግን አትጥሏቸዉ ምክንያቱም ወደዉ ሳይሆን ስራ ስለሌላቸዉና ጊዚአቸዉን በከንቱ እያሳለፉ ስለሚጨነቁ ነዉ በእናንተ በኩል ጥቂት ጥፋት እንዲገኝ ነዉ የሚፈለገዉ እስኪ ይግረማችሁ የአባይን ግድብ የሚቃወም በታሪክ የአገሩን እድገት የሚቃወም ሰምተንም አይተንም አናዉቅም አንድ ምሳሌ አቅርቤ ልቌጭ በአንድ ወቅት የኑሮ ዉድነቱ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ የጎዳዉ እለት እነዚህ ሰዎች መንግስት አንዳችም መፍትሄ አላደረገም በማለት እንዳልተጮሀ በጉዳዩ ላይ መንግስት ጣልቃ ሲገባ መልሰዉ መንግስት ነጋዴዉን አስገደደ መንግስት ጣልቃ መግባት የለበትም በማለት ሲገለባበጡ ለታዘበ ሰዉ ለዚህ ጽሁፍም የሚሰጠዉ ግምት ያዉ መሆኑን ነዉ ለዚህ ይመስለኛል መንግስትም የተሰላቸዉ እና ዝምታን የመረጠዉ