የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ራዛክ የግል የባንክ ሒሳብ ውስጥ 675 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህም ገንዘብ ከየት እንደተገኘ የአገሪቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በምርመራ እንዲያጣራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተፅዕኖ እያደረጉ ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ ባለፈው ሰኞ እንደገለጸው፣ 675 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ራዛክ የግል ሒሳብ ተዛውሯል፡፡ ይህም ገንዘብ በዕርዳታ የገባ እንጂ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመራው የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ፈንድ የወጣ አለመሆኑን አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ውዝግብ ያስነሳውና የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንግሥት ያንቀጠቀጠው ይኼ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ፣ በአገሪቱ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዕርዳታ የመጣ ነው ቢባልም፣ ኮሚሽኑ ዕርዳታውን የሰጠውንም ሆነ በባንክ አካውንቱ ያስቀመጠውን ግለሰብ ወይም አካል አላሳወቀም፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ ሊያድበሰብስ የፈለገው ጉዳይ አለ ተብሎ እየተጠረጠረ ነው፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ሕዝቡ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካውንት የገባው ገንዘብ ከማሌዥያ ኢንቨስትመንት ዴቨሎፕመንት ነው በማለት ቢወነጅሉም፣ ከፈንዱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ገንዘብ ተሰጥቶም ሆነ በአካውንታቸው ገብቶ እንደማያውቅ የፈንዱ ቢሮ አሳውቋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ እ.ኤ.አ. በ2009 የተመሠረተው የማሌዥያ ኢንቨስትመንት ፈንድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሽመድመዱንና ወደ 11 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር እንዳለበት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ግልጽ አሠራር የለውም እየተባለም ይተቻል፡፡
እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2015 መጀመርያ ላይ የዎል ስትሪት ጆርናል ሪፖርት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ራዛክ አካውንት ውስጥ 700 ዶላር ገቢ መሆኑን አትቶ ነበር፡፡
ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሚኒስትሩ ለአገሪቱ ልማት የሚውለውን ፈንድ ለግል ጥቅም እንዳላዋሉ፣ በስማቸው የተቀበሉት ገንዘብ እንደሌለና ጆርናሉን በስም ማጥፋት ወንጀል እንደሚከሱ ሲናገሩ ከርመዋል፡፡
ውንጀላው ከተሰነዘረባቸው ጀምሮም በጉዳዩ ዙርያ የሚሞግቷቸውን ሁሉ ከሥልጣን ማስወገድ ይዘዋል፡፡ ባለፈው ሳምንትም የአገሪቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሃይዲን ያሲን፣ እንዲሁም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አብዱል ጋኒን ከሥልጣን አስወግደዋል፡፡
በጠያቂነታቸውና ተሟጋችነታቸው የሚታወቁትን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን ጨምሮ አራት የካቢኒ አባላት ከሥልጣን ማስወገዳቸውን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫም፣ የካቢኒ አባላት በመሉ በአገሪቱ መከፋፈልን ሊያመጣ የሚችልና ከመንግሥት አጀንዳ የተቃረነ ሐሳብ በግልጽ መወያየት እንደማይችሉ አሳውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጋኒ የማሌዥያ ኢንቨስትመንት ዴቨሎፕመንት ፈንድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካውንት ገብቶ እንደሆነ ከሚያጣራው ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከማሌዥያ ማዕከላዊ ባንክ፣ እንዲሁም ከፖሊስ ጋር እየሠሩ ነበር፡፡ ከሥራ ከመታገዳቸው አስቀድሞም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አካውንት ውስጥ የገባው ገንዘብ ከአገሪቱ ልማት ፈንድ ጋር ግንኙነት እንደነበረው የሚያስረዳ ዶክመንት ደርሷቸው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አራት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከሥራ ሲያስወግዱ የሁለት መገናኛ ብዙኃንን የሥራ ፈቃድም አግደዋል፡፡
የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ፈንድ ላይ የተሠራ ሽፍጥ አለ በመባሉ ምክንያት፣ ተከትሎ በማሌዥያ ዋና ከተማ ኳላላምፑር ውጥረት ነግሷል፡፡ የታቃውሞ ሠልፍም ተካሂዷል፡፡ ተቃውሞ አድራጊዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥራ ይልቀቁ ብለው መጠየቃቸውን ዘ ጋርድያን ዘግቧል፡፡
ከተቃውሞ ሰልፍ ጋር በተያያዘ 29 ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፣ ክስ የተመሠረባቸውም በአገሪቱ እስከ 20 ዓመት እስራት በሚያስፈርደው ያልተፈቀደ ተቃውሞ ላይ በመሳተፍ ተብሎ ነው፡፡
በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ፈንድና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አካውንት ላይ ምርመራ እየተደረገ ቢሆንም፣ የኮሚሽኑ ውጤት ሚስተር ራዛክን ከጥፋተኝነት የሚያድን ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬን ፈጥሯል፡፡
ከምርመራው ጋር ተያይዞ የዴሞክራቲክ አክሽን ፓርቲ አባልና የፓርላማው መሪ ሚስተር ሊም ኪት ሲያንግ፣ የዚህን ድርጊት ውጤት ማሌዥያውያንና የዓለም ሕዝቦች በትኩረት እየተከታተሉት ነው ብለዋል፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ራዛክ የማሌዥያ መሪ ሆነው ለመቆየት ከፈለጉ ከእንዲህ ዓይነቱ ሙስና የፀዱ ለመሆናቸው ማሌዥያውያንን ማሳመን ይጠበቅባቸዋል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለግል ጉዳያቸው ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳልወሰዱ ገልጸው፣ ውንጀላው ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ሆን ተብሎ የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ባለቤታቸው ሮዝማህ ማንሱር በጣም አባካኝና የተደላደለ የቅንጦት ሕይወት የሚወዱ በመሆናቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ጋር ተያይዞ ስማቸው እየተብጠለጠለ ነው፡፡
ሒዩማን ራይት ስዎች የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ሐምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በኳላላምፑር የሚካሄደውን ስብሰባ ለመሳተፍ መምጣታቸውን አስመልክቶ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ራዛክ ጋር በጉዳዩና በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ እንዲነጋገሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)
Leave a Reply