በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን፣ በቦረናና ጉጂ ዞኖች አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና የምርጫውን ሒደት ለማስተጓጎል በተንቀሳቀሱ 26 ታጣቂዎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ታወቀ፡፡ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 20ዎቹ ታጣቂዎች ከጅማ ዞን ናቸው፡፡
ጅማ ዞን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት በጎማ 2 የምርጫ ክልል ዕጩ ሆነው የቀረቡበት አካባቢ ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጥላሁን አመንቴ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢ ይንቀሳቀሱ የነበሩና በፓርላማ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ታጣቂ ቡድኖች በምርጫው ሒደት ላይ መስተጓጎል ለመፍጠር በመሞከራቸው ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በምርጫው ሒደት የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን ለመከላከል፣ ቀደም ብሎ የሥጋት ልየታና የመካላከያ ዕቅድ አውጥቶ እንደነበር በማስታወቅ፣ ለፖሊሶችም የምርጫ ሒደትን የተመለከቱ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ግን፣ ምርጫው እንዳይካሄድ አስቀድመው ለማስተጓጎል ሲጥሩ የነበሩ ኃይሎች አሉ በማለት፣ በእንቅስቃሴ ላይ ሳሉ ታይተው ዕርምጃ የተወሰደባቸው አሉ ብለዋል፡፡ ይሁንና በክልል ደረጃ የነበሩ የፀጥታ ሁኔታዎች፣ የተወሰዱ ዕርምጃዎችና መሰል ጉዳዮችን የሚያካትት የተጠቃለለ ሪፖርት ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ከታጣቂዎች መካከል ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም እጅ የሰጡና የተማረኩ እንደሚገኙበት፣ ከስድስት በላይ ሰዎችም በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ምክትል ኮሚሽነር ጥላሁን፣ አክለዋል፡፡
በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች የሚንቀሳቀሰውን የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን እና ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ሕወሓት) በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወቃል፡፡ (ብሩክ አብዱ)
Leave a Reply