ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ መንግሥት ዐማራ በተባለው ኅብረተ-ሰብ ላይ ብዙ ግፍና ዐመፅ እንደፈጸመና እንዳስፈጸመ በገፍ ይነገራል። በኅብረተሰቡ ላይ ተፈጸሙ ከተባሉት ድርጊቶች አብዛኞቹ በሥዕል የተቀረጹ፣ ለሰው መብት በቆሙ ባስተማማኝ ብሔራዊና ዓለም-ዐቀፍ ድርጅቶች ከነማስረጃቸው የተጠናቀሩ፣ እሙን በሆኑ ያይን ምስክሮች የተደገፉ ስለሆኑ ማስተባበሉ ከመደናቈርና የአተካራ ግብግብ ከመግጠም ውጭ ሌላ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። የግፎቹ ኢሰብኣዊነትና የፈጻሚዎቻቸውም አውሬነት ለሚሰማ ሁሉ ከመዘግነን አልፎ፣ ሰው ሁኖ መፈጠሩን ራሱን የሚያስጠላ ከመሆኑ የተነሣ፣ ልቦና ያለው ተመልካችም ሆነ ሰሚ፣ መንግሥት ነን ባዮቹ የወያኔ ገዢዎች በጀርመንና በኢጣሊያን ምድር ከታዩት ከናዚና ከፋሽስት መንግሥታት መሪዎች በምን ይለያሉ ብሎ ለመጠየቅ ይገደዳል።
በበኩሌ ጥላቻው ከየት መጣ ብዬ አውጥቼ አውርጄ ማሰላሰል ከጀመርሁ ዓመታት ቈጥሬአለሁ። ዕድል ቀንቶኝ ከብዙ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጋር ኑሬአለሁ፤ አድጌአለሁም። ስለዚህ ፍንጭ ይሰጠኝ ይሆናል ስል ወደልጅነት ሕይወቴ ወደኋላ ተመልሼ በዐይነ-መነጽሬ ሳይና ሳሰላስል፡ ሁሌዬ ተመላልሰው እፊቴ የሚደቀኑብኝ ሁለት ገጠመኞች ናቸው። አንደኛው በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ከምትባል ከተማ በሠላሳ ኪሎሜትር ያህል ርቀት የሚገኝ መንዲዳ የተባለ መንደር አለ። ባንድ የኢጣሊያን መሐንዲስ ለሕንፃ ሥራ ተቀጥረው ከሰሜን የመጡ ሠራተኞች ባካባቢው ዘመናዊ ምግብ ቤት ስለሌለ፣ ሁሌዬ የሚበሉት ከተማሪዎቹ ጋር አብረው ነበር። የቀረውን ምግብ ሁሉ በልተው፣ ጠላዉን ብቻ መተው ልማዳቸው ሁኖ ስለነበር፣ አስተናጋጁ ገርሞት አንድ ቀን ምክንያቱን ሲጠይቃቸው አላንዳች ማፈር “ዐማሮች ናችሁ አሉን፤ ዐማራ ቂጥኝ አለውና እንዳይተላለፍባችሁ ምንም ዐይነት መጠጥ ቢሰጣችሁ እንዳትጠጡ ተብለን ስለተመከርን ፈርተን ነው” ብለው በጨዋነት መልስ ሰጡ። ሌላው በአሥመራ ከተማ በአንዳንድ አስተማሪዎች አነሣሽነት፣ ተማሪዎቹ እነዚህን ዐማሮች አታናግሯቸው ተብለው ስለተመከሩ፣ ከደቡብ የመጣነው በመጀመርያው ዓመት ምንም ብንጥር ጓደኛ ማፍራት ከባድ ሆነብን። እምብዛም ባይሆን ጥቂት ከምንቀርባቸው ጋር ችግሩ ምን እንደሆነ ለማወቅ ተሰባሰብን። መልሱ እውነትም ‘ዐማሮች’ ስለሆነን እንደነበር ለማወቅ ብዙም አልፈጀንም። ከሁሉም የከፋብን ግን ዐማሮች አይደለንም ስንል፣ ቀጥሎ የመጣው ልውውጥ ነበር። “ዐማሮች ካልሆናችሁ፣ ታዲያ ጋላ ናችሁ እንዴ!” ተባልን። ለዚህም በአሉታ ስንመልስ፣ “ታዲያ ከጋላ በታች ሰው አለ እንዴ!” ሲሉን ክው አልን። እንግዴህ እነዚህ የልባቸውን የሚናገሩ ላቅመ አዳም እንኳን ያልደረሱ ልጆች ናቸው፤ በጭንቅላታቸው ውስጥ የሚያንሸራሽሩት አሳቦች ግን የአካባቢውን ስሜት የሚያንፀባርቁ ሊሆኑ አይችሉም ብዬ መከራከሩ የሚያዋጣ ስለማይመስለኝ አልፈዋለሁ። ሁኖም የገጠመኙ ወቅት የወያኔ መሪዎች ልክ ወደጫካ ያመሩበት ጊዜ ስለነበር፣ የዛሬውን ሥራቸውን እያየሁ የለም እነሱ በዚህ ዐይነት አስተሳሰብ የተበረዙ ሰዎች አልነበሩም ብዬ ማሰቡ ያዳግተኛል። በአፍሪቃ ቅኝ ገዢዎችና በፋሽስቶች እጅ ባካባቢዎቻቸው ይካሄድ የነበረው ኀይለኛ ስብከት፣ በዐማራ ላይ ጥላቻ፣ በተቀረው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ንቀት እንዳሳደረባቸው አይጠረጠርም ብል በሐሰት የምወነጀል መስሎ አይታየኝም።
በሁለተኛ ደረጃ መታወቅ ያለበት ወያኔዎች የቀዝቃዛ ጦርነት ፍጻሜው ውጤት መሆናቸው ነው። በዚህ ጦርነት ሕይወት ወቅት እንደመዥገርት የሕዝባቸውን ደም እየመጠጡ የደነደሱ መንግሥታት እምብዛም ሳይቈዩ ወዲያው ፈረጡ:: የሁለተኛው ዓለም መሪዎች ተራ በተራ ከሥልጣናቸው ሲወድቁ፣ ያልታደሉት ታረዱ፤ በለስ የቀናቸው ደግሞ ለፍርድ ቀርበው ሰለባቸው ከነበሩት ጋር ተፋጠጡ። በሦስተኛው ዓለም የሁለቱ ኀያላን ባላንጣዎች መንግሥታት ማለትም የአሜሪቃና የሶቭየት ኅብረት ቱኪዎቻቸው የነበሩት ገዚዎች ግን፣ እንደሁለተኛው ዓለሙ መሪዎች በያመዳቸው አልቀሩም። እንደኢትዮጵያው መንግሥቱ ኀይለማርያም፣ የሱማሌው ሲያድ ባሬና፣ የድሮዋ ዛይር የዛሬዋ ኮንጎ ሞቡቶ ሴሴኮ የመሳሰሉት፣ ያን ሁሉ የድሎታቸውና ያምባገነንታቸው ወቅት ድንፋታና ጉራ ረስተው ይሰብኩ ለነበሩት ለናት አገር ፍቅር እንደመቆም፣ ሁላቸውም ነፍሴ አውጭኝ እያሉ በደንገለላ ሳይሆን በሽምጥ አፈረጠጡ። በጦርነቱ ድልና የበላይነት ያገኘችው አሜሪቃም በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥቱ ኀይለማርያምና ጀሌዎቹ እጣር ላይ መሆናቸውን ሲታይ፣ ዕድሉ ሳያመልጣት በራሷ ተላላኪዎች ሊትተካቸው እንደተሟሟተች፣ ከደርግ መንግሥት ፍጻሜ ዋዜማ በተደረገው በአስችኳይ ስብሰባ ላይ ጥርት ብሎ ይታያል። በስብሰባው፣ አሜሪቃ ሥልጣን ቋማጩቹን ገለልተኛ አገላጋይ መስላ ቢታደራደራቸውም፣ ኳሱንም ሜዳውንም ሙሉ በሙሉ በወያኔ እጅ እንደተወች ለመረዳት አብዛኛውን ተመልካች አያዳግትም ነበር ቢባል ሐቅ ይመስለኛል። ባሜሪቃና በዐረቦች ትብብር፣ የኅበረተሰባዊነትና የመደብ ጦርነት አንጋቢው ደርግ በመስኮት ሲሸመጥጥ፣ የጐጥና የጐሣ አንጋቾቹ ወያኔዎች በበር አድርገው ብቅ አሉ። በአንድ አስተዋይ ጓደኛዬ አባባል፣ ጅሎቹ የሩሲያን አምባገነን ቡችሎች፣ ባሜሪቃ አፋኝ አደንዝዝ ማጅራት መቺዎች ተበሉ።
በጫካ ኑሮ ዘመናቸው ወያኔዎች የተራማጅነት ጨንበል እንዳጠለቀ ወረተኛ ሁሉ፣ በኅብረተሰብአዊነት የተኰተኰቱ፣ የቻይናው ማኦ ቲሰቱንግ ታማኝ ደቀመዛሙርት፣ የአልባኒያው ሆችሚኒ አድናቂዎችና አጨብጫቢዎች ሲሆኑ፣ አሜሪቃ ግን የበዝባዦች ቊንጮና ደመኛቸው ነበረች። ሁኖም በደማስቆ መንገድ ክርስቲያኖችን ድምጥማቸውን ሊያጠፋ ሲጓዝ እንደነበረው ሐዋርያዊው ጳውሎስ፣ እነሱም ባንዴ ከአሜሪቃን ጥልቅ ጥላቻ ወደጥብቅ ፍቅር ተለወጡ። ሥልጣን ላይ እንደወጡ የተገበሩትም ልክ የአሜሪቃ መንግሥት ዋና ጸሓፊ የነበረው ክሲንጀር ጥቂት ቀደም ሲል ስለኢትዮጵያ አረቀቀ የተባለውን ነው ማለት ይቻላል። በቀዝቃዛ ጦርነትና በዐረብ-እስራኤል ግጭት ሰበብ ከ፲፱፻፷ዎቹ መጨረሻ ላይ ጀምሮ፣ አሜሪቃ ስለኢትዮጵያ የነበራት መምርያ ከድሮው ከቅኝ ገዢዎቹ ከአውሮጳውያን መርህ ብዙም የማይለይና የማይራራቅ ነበር ማለት ይቻላል። የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያ ካልተበታተነች የአፍሪቃን ክፍለ አገር በዘለቄታ ከሥልጣናቸው ሥር ለመያዝ አስተማማኝ ዋስትና አይኖረንም ይሉ እንደነበር ሁሉ፣ አሜሪቃም በቀይ ባሕር አካባቢ ያላትን ጥቅሟን እስከሚቻል ጊዜ ድረስ ለማስከበር፣ ኢትዮጵያ እንደ ዐረብ አገሮች ተከፋፍላና ተነጣጥላ ካልጠፋች በስተቀር አይሳካም ወደሚል አቋም የደረሰች ይመስላል። ቅኝ ገዢዋ ኢጣልያ ኢትዮጵያን ለመቈጣጠር “የዐማራን አከርካሪ በማያዳግም ሁናቴ መስበር አለብን” ትል የነበረውን አባባል፣ የወያኔም ባለሥልጣኖች በየጊዜው አስተጋብተውታል [1]። ስለዚህም የወያኔና የአውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች ሕልም አንድ ነው ማለት ይቻላል። እንግዴህ አሜሪቃ የ“ትግራይን ረፓብሊክ” መፍጠር ዋና ግቡ ያደረገውን ወያኔን ለሥውር ዓላማዋ ቢትመርጥ ምንም የሚገርም አይመስለኝም። አሜሪቃም እንደአውሮጳውያኖች ቅኝ ገዢዎች ዐማራ ቢጠፋ ደንታቢስ ቢትሆን ምን ይገርማል።
እንደተለመደው የወያኔ መንግሥት ሥራ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጽሑፎቼ እንዳነሣሁ፣ በጥላቻና በድንቁርና ላይ የተመሠረተ ሁኖ ነው እንጂ እነሱና እነሱን የመሳሰሉ የጐጥና የጐሣ ምሁራንና ልሂቃን የሚነበንቡት ዐማራ በሕይወት ኑሮም አያውቅም ማለት ይቻላል[2]። ዐማራ [በግእዝ ቋንቋ አምሐራ] ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስሙ የሚነሣው፣ በተለያየ ስም “ድግናጃን፣” “ደጋዛን”ና “ግዳዣን” በመባል በሚታወቀው በአክሱም ንጉሥ የሓዋርያነት ሥራ በተያያዘ ጉዳይ ነው። ንጉሡ ከመናገሻ ከተማው ወደመቶ ዐምሳ ሰባኪዎችን “ደብተራ” ብሎ ከሠየማቸው በኋላ፣ ሕዝቡን እንዲያከረስትኑ ወደ “ዐማራ” ምድር እንደላካቸው ሰነዱ ይገልጣል። እንግዴህ በዚህ ሰነድ መሠረት “ዐማራ” የሚያመለክተው፣ የተወሰነ የመሬት ክልል መሆኑ አይካድም። የተለያዩና በየጊዜው የመጡት የውጭ አገርና ያገር ቤት ጸሓፊዎች አላንዳች ማዛባት እንደሚናገሩ፣ ክልሉ በምዕራብ በኩል በአባይና እሱን በሚመግበው የበሽሎ ወንዝ፣ በሰሜን በአንጎትና ላስታ፣ በደቡብ በወንጭት ወንዝ፣ በምሥራቅ ደግሞ ወደደንከል በረሃ በሚደርሰው ሰፋፊ ገደላንገደል የተከበበውን ምድር ይዋሰናል። ይኸ ዝርዝር እንደማስረጃ ካገለገለን እንግዴህ፣ ዛሬ የወያኔ መንግሥት ዐማራ ብሎ የሚጠራቸውን እንደነጐጃም፣ በጌምድር፣ ሸዋ እንዲሁም የወሎን ከፊሉን አያካትትም።
የዚህ ክልል ነዋሪዎች አፈታሪክ የሚነግረን፣ “ዐማሮች” ምንጫቸው በቀጥታ ከአክሱም ሲሆን፣ “ዐማራ” የሚለው ቃል ትርጒሙ “ነፃ ሕዝብ[3]” ማለት እንደሆነ ነው። ሁኖም ዐማራ በሰፊውና በገነነ መልኩ በመቈራኘት የሚታየው ከገዢው መደብ ጋር በመያያዙ ይመስለኛል። የአክሱማውያን መንግሥት ከብዙ የጨለማና የድብልቅልቅ ዘመን በኋላ የተተካው፣ በታሪክ ዟጐ በመባል በሚታወቀው ሥርወመንግሥት ሲሆን፣ ከሱም ቀጥሎ የመጣው “ሰለሞናዊ’” እያልን የምንጠራው ነው። የዛጐ መንግሥት በአገዎች እንደተቋቋመ ሁሉ፣ በታሪክ መሠረት የሰለሞኖች ሥርወ መንግሥት ቈርቋሪ ደግሞ ግእዙ “ንጉሠ አምሐራ[4]” በሚለው በአፄ ይኩኖአምላክ እንደሆነ ይታወቃል። እዚህ በጣም መጠንቀቅ የሚገባን ነገር አለ። “ንጉሠ አምሐራ” የሚል ስያሜ ይኑራቸው እንጂ፣ ጐንደር የነገሥታቱ ቋሚ መናገሻ ከተማ ሁና እስከተቈረቈረችበት ማለትም እንደአውሮጳ አቈጣጠር [አ.አ.] እስከ ፲፮፻፴፪ ዓ. ም. ጊዜ ድረስ፣ ምናልባትም ከመጀመርያው “ንጉሠ አምሐራ” ውጭ፣ በዐማራ ምድር ውስጥ የነገሠ ሌላ ንጉሥ ነበር ማለት ያዳግታል። ግዛታቸው ሰፊ፣ ተራራማና ገደላገደል የሞላበት ስለነበር፣ ለቊጥጥር እንዲያመቻቸው ሲሉ፣ ነገሥታቱ የሚኖሩት በየጊዜው ሰፈር እየቀያየሩ “በዟሪ” ወይንም “በተሽከርካሪ ከተማ፡” ነበር። ሥልጣናቸውን በየጊዜው በመፈታተን እከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥሉት ሁናቴዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጠሩት በአገራቸው ደቡብና ምሥራቅ ባሉት የእስላሞች ባላባቶች በኩል ስለነበር፣ ይኸንን በመገንዘብ የዟሪ ከተማቸው ዋና ዋናዎቹ ግዛቶች በደቡብ እንደነይፋትና ሸዋ፣ ደዋሮና ፈጠጋር የመሳሰሉት አገሮች ነበሩ። ከዘመነ-መሳፍንት በኋላም ቢሆን፣ በዐማራ ምድር ውስጥ የነገሠ ንጉሥ እንደሌለ ስለምናውቅ ወደዝርዝሩ መሄድ አስፈላጊ ሁኖ አይታየኝም።
ዐማራ የተባለው ክልል የ”ዐማራ” የነገሥታት መቀመጫ ሁኖ እንደማያውቅ ግልጽ ከሆነ፣ አገሩን የሚገዙት ነገሥታቱስ ከዐማራ ቤተሰብ ወይንም ክልል የተወለዱ ነበሩ ወይ ብሎ መጠየቁ ተገቢ መስሎ ይታየኛል። አፄ ይኩኖ አምላክ “ንጉሠ አምሐራ” ቢባሉም፣ በመከታተል አልጋቸውን የወረሱት ነገሥታት ግን፣ ምናልባትም ከመጀመርያዎቹ ጥቂቶቹ በስተቀር፣ የአብዛኞቹን የቅርብ ወላጆቻቸውን [ማለትም አባትና እናት] ብንመለከት፣ ሙሉ በሙሉም ሆኑ፣ በከፊል ከዐማራ ዘር ወይንም ምድር መሆናቸው እጅግ በጣም አጠያያቂ ነው ማለት ይቻላል። ለማንኛዉም እስኪ ወደጥልቅ ሳንገባ ለማስረጃ ያህል የሚከተሉትን እንያቸው። በ፲፮ኛ ዘመን የነገሡት ነገሥታት፣ ካፄ ልብነድንግል ባለቤት ከጐጃሜዋ[5] ከእቴጌ ሰብለወንጌል በስተቀር፣ የሁሉም ሚስቶቻቸው የትግራይ ወይንም የሐዲያ ተወላጆች ነበሩ ማለት ይቻላል። የቄንጠኛዋ የጐንደር ከተማ መንግሥት ነገሥታት፣ የአፄ ሱስንዮስ ዝርያ ናቸው። እርሳቸው ደግሞ በእናታቸው ከቤተእስራኤል ሲሆኑ፣ ወልድ ሠዓላ ይባሉ የነበሩት ሚስታቸው እቴጌ ሥልጣን ሞገሳ በበኩላቸው ከኦሮሞ ብሔረሰብ መሆናቸው ይነገራል። እናታቸውም እስላም ነበሩ ይባላል። ከዚህ የምንማረው ነገር ቢኖር፣ ጐንደርን ከቈረቈረው ከልጇ ፋሲለደስ ጀምሮ እስከ ዘመነ-መሳፍንት ድረስ በኢትዮጵያ ዙፋን ይቀመጡ የነበሩት የኦሮሞ፣ የቤተእስራኤል ደም ካላቸው ብሔረሰብሶች የተወላለዱ ልጆችና የልጅ ልጆች ነበሩ ማለት ነው።
የዘመነመሳፍንቱ ነገሥታት በደምገንቧቸው የነበረው ደም በግልጥ የቋራና የኦሮሞ ድብልቅ ነው። የገዛራሳቸውን “ርእስ መስፍን ዘኢትዮጲያ[6]” በሚል የማዕርግ ስም ሠይመው፣ ነገሥታቱን በዘፈቀደ እንደጉልቻ እየቀያየሯቸው በበላይነት የሚመሩት ፈላጭቈራጮቹ መሪዎች ደግሞ ከመላ ጐደል የየጁ ኦሮሞች[7] ነበሩ። ዘመኑም የሚታወቀው በሥርወመንግሥታቸው የ“ወረሼኮች[8]” በመባል ነው። ዘመነ መሳፍንት ማለት እንግዴህ የኦሮሞ ዝርያ ናቸው የተባሉት የየጁ መኳንንት ላንድ መቶ ዓመት ያህል የጐንደርን መንግሥት ሙሉ በሙሉ የተቈጣጠሩበት የኢትዮጵያ ታሪክ ዘመን ነው ማለቱ እውነትትን ያንፀባርቃል ብዬ አምናለሁ።
ከዘመነመሳፍንት ባሻገር፣ ወደዛሬዋ ወደዘመናዊት ኢትዮጵያ ብንመጣ ሁናቴው ብዙም አይቀየርም። ሦስቱ አጼዎች (ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ[9]ና ምኒልክ) ከገዛ ራሳቸውም ሆኑ ከሚስቶቻቸው መካከል አንድም ጭንጩ ዐማራ በርግጥ የለም ማለት ይቻላል። አፄ ቴዎድሮስ[10] ከቋራ፣ አፄ ዮሐንስ ከትግራይ፣ አፄ ምኒልክ ከተለያየ ብሔረሰብ ናቸው። ልጅ ኢያሱና አፄ ኀይለሥላሴ[11] ደግሞ ያማራ ደም አለባቸው ቢባልና ቢለካ በርግጥ ካሥር የአንድ ግማሽ እጅ እንኳን ላይሞላ ይችላል ብል ሐሰት አይደለም።
ከነገሥታቱ ወረድ ብለን በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙትን ባለሥልጣናት ብናይ፣ ደረጃው ሁሉንም አካባቢና ብሔረሰብ ያካተተ ሁኖ እናገኘዋለን። ሁኖም በገዢዎች ትውልድ አካባቢ ለሚመራመር ግለሰብ ታላቁ ችግር፣ ታሪክ ጸሓፊው በግልጥ ካልተናገረ በስተቀር በስም ብቻ ተመሥርቶ ባለሥልጣኑ ከየትኛው ብሔረሰብ ወይንም አካባቢ እንደመጣ መንገር በጣም ያዳግታል። ምክንያቱም በኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ ውስጥ አንድ ግልጥ ሁኖ የሚታይ ጉዳይ ቢኖር፣ ሥልጣንና ሹመት የግለ-ሰቡ የአገልግሎት ብቃትና ትጋት ፍሬ ውጤት እንጂ በትውልዱ ዘርና አካባቢ የተገደበ አይደለም ማለት ይቻላል። ሿሚው በመጀመርያ ደረጃ እንደመስፈርት የሚጠቀማቸው የተሿሚውን ችሎታና ታማኝነት እንጂ ከየትኛው ቤተሰብና ብሔረሰብ ወይንም ቀዬ መምጣቱን አይደለም። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ አንድ በጥብቅ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር፣ ብዙ ጊዜ በተሳሳተ የአውሮጳውያን ታሪክ በመመሥረት ስለኢትዮጵያ የጉልተኛ ባላባት[12] ሥርዐት የሚናገሩ በርካታ ጸሓፊዎች ቢኖሩም፣ ሐቁ ግን እውነትን ለማዛባትና ለማወናበድ ካልሆነ በስተቀር ሥርዐቱ ባገራችን በግልጥ የታየበት ጊዜ የለም። መደብ፣ ወገንና አካባቢ ጠቃሚነታቸው በሁለተኛ ደረጃ ሊሆን ይችላል። ግን እንደችሎታና ታማኝነት ወሳኝ መስፈርቶች አይደሉም። ስለዚህም ነው እንግዴህ ከላይ እንደተባለው ስለባለሥልጣኖቹ ማንነትና አካባቢ ብዙም የማናውቀው። ሁኖም አንዳንዴ ካንድ ጉዳይ ጋር በማማያያዝ፣ የጥቂቶች ማንነታቸው ሲጠቀስ ይታያል። እስኪ ከነዚህ መካከል ለወጉ ያህል ጥቂቶቹን እንመልከት። በአፄ ሱስንዮስ ዘመን ከሁሉም ታላቅ ሹመት ሁኖ የሚገመተውን የጐጃምን ግዛት፣ “ጐጃም ነጋሽ” የሚለውን ያገሩን ገዢ ማዕርግ ተከናንቦ ለብዙ ዓመታት ያስተዳደረው የጉራጌው ተወላጅ “ጐጃም ነጋሽ ክፍሎ” ነበር። ያፄ ሠርፀድንግልን ሁለት ልጆች አግብቶ፣ መላ ኢትዮጵያን በበላይነት ያስተዳድር የነበረው በጊዜው የመንግሥት ፈላጭ-ቈራጩ መኰንን፣ የወለጋው ተወላጅ ራስ ዘሥላሴ[13] ነበር። በ “ዳሞት ጸሓፊላምነት” ማዕርግ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብም ሆነ፣ ወሰንና ድንበር ለማስጠበቅ ሲል ብዙ ጦርነት በጀግንነት በመዋጋት፣ ንጉሠነገሥቱን እንደአ.አ. ከ፲፮፻፲፯ እስከ ፲፮፻፳፯ ዓ.ም. በታማኝነት አገልግሎ፣ በመጨረሻም የዳሞት ግዛቱን ከኦሮሞ ወረራ ሊከላከል ሲል በጦር ሜዳ ላይ ሕይወቱን የሠዋው ደጃዝማች ቡኮ፣ ከመጀመርያዎቹ የኦሮሞች ታላላቅ ገዢዎች አንዱ ነበር። እንዲሁም ንጉሠነገሥቱ “እንደልቤ ታማኝ” ይሉት የነበሩት፣ ዋናው አማካሪያቸውና፣ ከቁመታቸው ዕጥረት የተነሣ በኦሮሞኛ ቃል “ጢኖ” በመባል የሚታወቁት፣ ጸሓፈ ትእዛዙ አዛዥ ተክለሥላሴ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ነበሩ። ጽሑፋቸው እንደሚያመለክተው፣ አዛዥ ጢኖ ከኦሮሞ ቋንቋና ባህል በተጨማሪ፣ ዐማርኛና ግእዝ አሳምረው የሚያውቁ፣ ቅኔ የሚቀኙ፣ አንደበታቸው የተባ፣ ብዕራቸው የሰላ ጸሓፊ ናቸው። እነዚህ ለእንደዚህ ዐይነት ወግና ማዕርግ ሊበቁ፣ ዕውቀትንም ሊገበዩ የቻሉት፣ “ጋላ” በኢትዮጵያ ፈጸመ የተባለው ወረራ ግማሽ ዘመን ማለት ዐምሳ ዓመት እንኳን በማይሞላው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፣ እስከኛ ጊዜ ድረስ ባሉት ዐራት መቶ ዓመታት ውስጥማ ምን ያኽል መቀራረብና መዋሐድ እንደተካሄደ መገንዘብ የሚያዳግት አይሆንም።
ከላይ ስለልጅ ኢያሱና አፄ ኀይለሥላሴ አንሥቻለሁ። ከነዚህ ሁለቱ ጋር በተያያዘ፣ በቅርብ ጊዜ ባነበብሁት ባንድ ሊቅ ሕዝቅኤል ኢብሳ በተባሉ ያንድ ዩኒቬርሲቲ መምህር ተደርሶ በበርካታ የኢትዮጵያ ድረ-ገጾች በወጣ ጽሑፍ ላይ አንዳንድ ኂሶች መሰንዘሩ ተገቢ መስሎ ይታየኛል። ሊቁ “ኢትዮጵያ፤ የኦሮሞ እውከት፤ ስለብሔራዊ ጥያቄና ወደሕዝበ መንግሥት ሽግግር[14]” በሚል ድርሰታቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር [ኢ.ሕ.ዴ.ግ] በመባል የሚታወቀው የወያኔ መንግሥት በዐዋጅ ኦሮሞ ብሎ በሠየመው ሕዝብ ላይ የጐሣው አቀንቃኞች ደርሶበታል የሚሉትን ግፍና ሰቈቃ ይተርካሉ። ታሪክን በገለልተኛነት ለሚመራመርና የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ ለሚያውቅ ምሁር፣ የሊቁ ንግግር የተለመደውን ደጋግሞ ከመወሸከት ውጭ ምንም አዲስ ነገር ስለማያፈነጭ ጊዜ ላለመፍጀትና የጽሑፌን አቅጣጫ ላለመለወጥ ስል አልፈዋአለሁ። ሁኖም ላነሣ የፈለግኋቸው ሁለት አውራ ነገሮች አሉ።
አንደኛ፣ እንዴት ሁለቱ የሴማውያን ዘሮች ማለትም ትግሬዎችና ዐማሮች፣ ኦሮሞችን አገልለውና ካስፈለገም የሥልጣን ፍርፋሪ ብቻ በመወርወር ያስተዳደሩን ሥልጣን የግላቸው ሀብት እንዳደረጉ፣ ምሁሩ አበክረው ይናገራሉ። እንዲህም ሲሉ፣ ሊቁ በጽሑፋቸው የሚጠቅሱትን የእንደነጆን ማርካኪስ [John Markakis[15]] ዐይነቶቹን የግራዘመም ጸሓፊዎችን አሳብ ከማንሸራሸር በስተቀር፣ ከማንም ታሪክ ጸሓፊ የሚጠበቁትን አመዛዛኝ ልቡናና የማያዳላ አእምሮ በመጠቀም የኢትዮጵያን ታሪክ ያገናዘቡት አይመስሉም። በመጀመርያ ደረጃ ከላይ ያየነው በዘመነ መሳፍንት አገሩን ይገዛ የነበረው የወረሼኮቹ ሥርወ መንግሥትም ሆነ፣ ነጋሾቹ መሳፍንት እንደፍላጎታቸው የሚለዋዉጣቸው ነገሥታት በስም ሰለሞናውያን ይሁኑ እንጂ፣ ከመላ ጐደል የኦሮሞ ዝርያ መሆናቸውን አይተናል። ስለዚህም በኢትዮጵያ እየተፈራረቁ ከፍተኛ ሥልጣን ይዘው የነበሩት ትግሬዎችና ዐማሮች እንጂ ኦሮሞች ለዚህ አልበቁም ማለት በጠራራ ቀን ፀሐይ የለችም ብሎ እንደመሟገት የሚቈጠር መስሎ ይታየኛል።
በሁለተኛ ደረጃ የገረመኝ ነገር ቢኖር፣ ምሁሩ በምዕራባውያን ኀይሎች አነሣሽነትና በሥልጣን ሽኩቻ፣ ባንድ በኩል በልጅ ኢያሱና በአባታቸው ንጉሥ ሚካኤል፣ በሌላው ደግሞ በልጅ ተፈሪና (ኋላ አፄ ኀይለሥላሴ) በደጋፊዎቻቸው መካከል፣ እንደኢትዮጵያ አቈጣጠር [ኢ.አ.] በመስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፱ ዓ.ም. የተካሄደውን የሰገሌን ጦርነት በሚያስደንቅ ሁናቴ በመተርጐም፣ በወሎ ኦሮሞችና በሸዋ ዐማሮች እንደሆነ አድርጎ ማቅረባቸው ነው። በሁለቱም በኩል የሚዋጉትም ሆነ፣ ጦሩን በበላይነት የሚመሩት፣ አብዛኞቹ ኦሮሞች ወይንም የኦሮሞ ደም ያላቸው ሲሆኑ፣ ምሁሩ እንዴት አድርገው እንደዚህ ለመደምደም እንደበቁ አይናገሩም። ምናልባት ኦሮሞ ሲሉ፣ እንደነፃ አውጪ ነን ባዮቹ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ የተወሰነ መስፈርት ካላቸው ደግሞ ምሁሩ በጽሑፋቸው ውስጥ ይኸንን ግልጥ አያደርጉም። አባባላቸው ደግሞ ኦሮሞች እርስበርሳቸው አይዋጉም የሚል ከሆነ፣ በጣም ሩቅም ሳይሄዱ የእረኝነትን ሥርዐት ትተው፣ በኦሞ ወንዝ አካባቢ በመንግሥትነት ተቋቁመው የነበሩትን፣ የጅማ አባጅፋርን፣ የጉማንና የጐማን ከዚያም ባሻግር የለቃ-ነቀምትንና የለቃ-እናርያን ንጉሦች፣ እንዲሁም በወሎ ውስጥ የየጁዎች ባላንጦች የነበሩትን የማመዶችን ሥርወ መንግሥት ማየት ይበቃል። በአገዛዛቸው ጨካኝነት፣ በኦሮሞም ሆነ መሬታቸውን ከነጠቁ በኋላ “ባዕዳን” ብለው በፈረጁባቸው ባገሩ ተወላጆች ላይ ያደርሱባቸው የነበረው ግፍና ሰቈቃ፣ የጐሣው ልሂቃን ’የአበሻ” ነገሥታት በሕዝባችን ላይ ፈጸሙበት ከሚሉት እጅግ ይከፋል እንጂ በምንም ረገድ አያንስም ብዬ እገምታለሁ። ሊቅ ሕዝቅኤል በዚህ ድርሰትና በሌሎችም ጽሑፎቻቸው ይልቁንም በጀርመን አገር ታትሞ በወጣው በEncyclopedia Aethiopiaca ኦሮሞ-ነክ ዐምዶች [vol. 4 O-X] ላይ ከፖለቲከኞች እንጂ ካንድ ገለልተኛ የታሪክ ምሁር የማይጠበቁ አያሌ የተዛቡ አስተያየቶች አስቀምጠዋል። እንደዚህ ዐይነቱ የታሪክ አተረጓጐም ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ምሁራን ታሪክን የፖለቲካ ደንገጡር እንዳደረጓት ነው ብል ሐሰት አይመስለኝም። በዚህ ረገድ ሊቅ ሕዝቅኤል ብቸኛ አይደሉም[16]፤ እንደጊዜው ፖለቲካ የሚቀያየሩ የወረት-በላ ምሁራን የበዙበት ዘመን ስለሆነ፣ ነገሩ የሚገርም መስሎ አይታየኝም በማለት አሳቤን ልቋጭና ወደዛሬው ጥያቄዬ ልመለስ።
ዐማራን በተመለከተ በቂ ያልሁ ስለሚመስለኝ፣ ልቀጥልና ወደዐማርኛ ልሻገር። የዐማርኛ ቋንቋ ምንጩና መነሻው ዐማራ ከተባለው ክልል እንደሆነ አይካድም። ልክ እንደዐማራ እሱም በዘተለምዶ ተቈራኝቶ የሚገኘው ከገዢው መደብ ጋር ቢሆንም፣ ሐቁ ግን ቋንቋው በደምቡ ያደገውና የዳበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ያልተቈጠበና ሰፊ አስተዋፅኦ ነው ማለት ይቻላል። ስሙ ከተወለደበት ምድር ጋር ተያይዞ ቢቀርም፣ እውነቱ ግን በየአካባቢው የሚገኙትን የተለያዩ ቋንቋዎች ቃላትንም ሆነ አገባብ በመከለስ፣ በማዳበልና በማቀያየጥ አዋህዷቸውና አመሳስሏቸው ይገኛል። የቋንቋ ጥናት ምሁራን ሴማዊ ብለው ፈርጀውታል። በኔ አመለካከት ይኸ ዐይነቱ አከፋፈል በርካታ ታሪካዊ ጥላሸት የለበሰ በመሆኑ እንደአስተያየት እንጂ እንደዐምደ ሃይማኖት ሁኖ መወሰድ የለበትም። ያም ሁኖ ግን፣ ሐቁ ዐማርኛ በኩሳውያንና በሌሎችም ባካባቢው ካሉት ቋንቋዎች ቃላትና አገባብ በሰፊው ከመደባለቁ የተነሣ ሴማዊ ብሎ መጥራቱ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። የራሱን ስያሜ ሰጥቶ፣ “ኢትዮጵያዊ” ወይንም “አፍሪቃዊ” ማለቱ የሚቀል ይመስለኛል። በፊደልም ሆነ በአነባብ ከማንኛውም ያለም ቋንቋ የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ። ብዙዎች ቋንቋዎች ንባባቸው በጽሑፍ ተቀርጾ ካለው ፊደል ጋር በፍጹም አይጣጣምም። ለምሳሌ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሰበብ ባለም እየተሰራጨ በመጣው የእንግሊዝኛ፣ አንድ ቊጥር ወይንም “One” ሲነበብ “ዋን” ብሎ እንጂ እንደጽሑፉ “ዖንእ” አይደለም። እንዲሁም ከአውሮጳዉያን ቋንቋዎች መካከል ጽሑፉና አነባቡ አገባቡን ተከትሎ ይሄዳል ከሚባሉት ቋንቋዎች መካከል ኢጣሊያንኛ አንዱ መሆኑ ይታወቃል። አባባሉ እውነትነት ቢኖረውም፣ ሐቁ ግን እሱም ቢሆን መጠነኛ ሕገወጥነት ያጠቀዋል። ለምሳሌ ያህል ኢጣሊያንኛ የዐማርኛ “ሸ” የሚል ፊደል ስለሌለው፣ የሚጻፈው ቢያንስ ሦስት ፊደላትን በማቈራኘት ነው። “ሻ-ካሎ[17]” ለማለት “scia-callo” መጻፍ ይኖርበታል። በዚህ መልክ ስናየው ያማርኛ ፊደል የተራቀቀና ዘመናዊነትን ያሟላ ነው ማለት ይቻላል። ፊደሎቹ በዛ በማለታቸው፣ ለጥናት መጠነኛ ጊዜ ቢፈጁም፣ አንዴ ጠንቅቋቸው ላወቀ ግን በቅልጥፈት፣ በቀላልነትና በይዘት ደረጃ ወደር የሚገኝለት ቋንቋ አይደለም ሊባል ይችላል። በኮምፑቴር አገላለጽ “የሚነበበው እንደተጻፈው ነው[18]” የሚለው አባባል የሚገባው ከማንኛዉም ቋንቋ ይልቅ ለዐማርኛ ነው ቢባል እውነትነት አለው::
ዐማርኛ ባገሪቷ ውስጥ ያሉትን የልዩ ልዩ ብሔረ-ሰቦችን ድምፅ ሊያስተናግድ ሲል ጥንት ከአባቱ ግእዝ በወረሳቸው ፊደላት ላይ እንዳስፈላጊነቱ አዳዲስ ፊደል ሊፈጥርና ሊጨምር በቅቷል። አብዛኛውም የቋንቋው ተናጋሪ የሚገኘው ከጥንት ትውልዱ ክልል ውጭ ነው። የተለያዩ ማስረጃዎች እንደሚገልጹ ከሆነ፣ በሁሉም ዘንድ ባይሆን እንኳን በተወሰኑት በዛሬዎቹ ሱማሌዎችም አካባቢ ተስፋፍቶ እንደነበር አል-ፋቂህ በመባል የሚታወቀው የግራኝ ታሪክ ጸሓፊ እስላሙ ዐረብ በ“የአበሻ ወረራ” በሚል መጽሐፉ ከመዘገበው ፍንጭ እናገኛለን። አፄ ልብነድንግልን በድንገት በሰፈሩበት ዐምባ ላይ ለመያዝ ዐቅዶ፣ ግራኝ ለወታደሮቹ በዐማርኛ ብቻ እንዲናገሩ ጥብቅ ትእዛዝ ሰጠ። ወታደሩም እንደታዘዘው አድርጎ፣ ሳይጠረጠር የደኅንነቱን ጠባቂዎች ዐልፎ ንጉሥ ነገሥቱን ለመያዝ ምንም አልቀረውም ነበር። አፄውን ሊያስመልጣቸው ያበቃው ምናልባት ግራኝ ራሱ ሳይታወቀው በራሱ [አደርኛ?] ቋንቋ መናገሩ ይመስላል።
ዐማርኛ ለተለያየ ብሔረሰብና አካባቢ የኢትዮጵያዊነቱ መግለጫ መሆኑ አይካድም። ከላይ የጠቀስናቸው እንደነጐጃም ነጋሽ ክፍሎ፣ ጸሓፈላም ቡኮና ራስ ዘሥላሴ የዐማራ ተወላጆች እንዳልሆኑ ይታወቃል። አጭር በመሆኔ “ጢኖ” የሚል የኦሮሞኛ ስም ተስጥቶኛል ባዩ ጸሓፌ ትእዛዝ አዛዥ ተክለሥላሴም በጽሑፋቸው ስለቋንቋው ሲገልጡ፣ “ዐማርኛ ቋንቋችን” እያሉ ኩራት በተሞላበት ስሜት ሲናገሩ ይታያሉ። በላስታና በሸዋ፣ በበጌምድርና በወሎ፣ እንዲህም በጐጃም ግዛቶች አማርኛ የኩሳውያንን ቋንቋዎች ተክቶ ይገኛል። በአርጐባና ጋፋት በመሳሰሉት አገሮች ደግሞ የሴማውያንን ቋንቋዎች ቦታ ወስዷል።
አማርኛ ያፋቸው መክፈቻ ቋንቋቸው ቢሆንም፣ እነዚህ እላይ የተጠቀሱ አገሮች እንደአ.አ. በ፲፱፻፺ዎቹ ዓ.ም. ላይ፣ ዐማሮች ናችሁ የሚል ስያሜ በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት በግድ በላያቸው ላይ እስከተለጠፈባቸው ጊዜ ድረስ “ዐማራ” በመባል አይታወቁም። ራሳቸውን ይጠሩ የነበሩት በሚኖሩበት አገርና ቦታ ስም ጐንደሬ፣ ጐጃሜ፣ መንዜ በመባል እንጂ በፈጠራ በተሰጣቸው ዐማራ በሚል ብሔረሰብነታቸው አልነበረም። ታሪክም ራሱ የሚያመለክተው ይኸንኑ ሐቅ ነው። ከ፲፬ኛ እስከ፲፰ኛ አዝማን ድረስ በተከትታይ ድረስ የተጻፉት የነገሥታቱ የታሪክ ሰነዶች ዐማራ የሚለውን ቃል ከቦታ እንጂ ከብሔረሰብ ጋር አያቈራኙም። እንዲሁም እስከ፲፱ኛ ዘመን ድረስ በተጻፉት የክርስቲያኖቹም ሆኑ የእስላሞቹ ዜና መዋዕል ውስጥ “ዐማራ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በአሁን ጊዜ በወሎ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የቦታ ስም እንጂ ብሔረሰብን አይደለም[19]።
ጽሑፌ የሚያስረዳው አንድ መሠረታዊ ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያውያን ከገዢው መደብ ጀምሮ እስከ ተራው ሕዝብ በጋብቻና በአምቻ የተሳሰሩ መሆናቸውን ነው። ያገሩ አስተዳደሩም ሆነ ቋንቋው በተለምዶ ዐማራና ዐማርኛ ቢባልም ሁሉም ኅብረተሰብ በባለቤትነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጎባቸው ያስመዘገባቸውና የገነባቸው መሆኑን የታሪክ ሰነዶች ይመሰክራሉ። ዐማራ የሚያመለክተው የዚህ አስደናቂ ግንብ አሳቡንና መሠረቱን የጣለው ሕዝብ የሚኖርበትን በጣም የተወሰነ ክልል እንጂ አሁን በሥልጣን ያለው መንግሥት ለጥቅሙ ሲል አብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በገፍ በማግለል ጭብጥ የማይሞሉና ማንንም የማይወክሉ መሰሎቹን ብቻ አሰባስቦ የፈጠረውን ኅብረተሰብ አይደለም።
[1] የወያኔ መሪዎች ስለዐማራ ተናግረዋል ከሚባሉት ንግግሮች አንዳንዱ ለጠላትም ጆሮ እንኳን ይቀፋል። እዚህ ጥቂቶቹን ከነተናጋሪያቸው ጋር ልጠቅስ እወዳለሁ።
“ ዐማራ ጠላት ነው” (የሕ.ወ.ሃ.ት. ማእከላዊ አቋም – ሰነድ)።
“ዐማራ መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ ሲለምን ማየት እፈልጋለሁ” (መለስ ዜናዊ)።
“ዐማራን እንደ ሲጋራ ረግጠን ጥለነዋል” (ስዬ አብርሃ)።
“ገድለን የቀበርነውን ዐማራ አታንሱብን” (ሳሞራ ይኑስ)።
“ዐማራውንና ኦርቶዶክሱን ሰብረን ጥለነዋል” (አቦይ ስብሃት)።
“ዐማራ ትምክሕተኛ ነው” (ገብረኪዳን ደስታ)።
[2] . መጥሌነትና ድንቁርና ብዙውን ጊዜ ተያይዘው ናቸው የሚሄዱት። ኢጣሊያን አገር ተማሪ ሳለሁ፣ አንድ ከደቡቡ [በሥልጣኔ ወደኋላ ከመቅረቱ የተነሣ “mezzo-giorno” ወይንም “መንፈቀ-ዕለት” ይሉታል] በኩል የመጣ የደስደስ ከፊቱ ያለው ጓደኛችን ካገር ቤት የተላኩልንን የውብ ቤቶች ሥዕል (ፎቶግራፍ) እያየን ሲንጯጯህ ሰምቶ መጣና፣ ሥዕሎቹን ሲያይ ገርሞት፣ “እናንተ ጥቁርች፣ሥዕሎቹ ከየት ናቸው” ሲል ጠየቀን። “ካገራችን” ስንለው፣ ደጋግሞ ያየው የታርዛን ፊልም ትዝ ብሎት ነው መሰለኝ፣ “አፍሪቃ ውስጥ ሁሉም እዛፍ ላይ የሚኖር መስሎኝ! ታዲያ ቤትም አለ እንዴ” ሲለን ከኛ አንዱ፣ “እውነትህን ነው ሁላችንም የምንኖረው በዛፍ ላይ ነው። የኢጣሊያን አምባሳደር ደግሞ የሚኖረው ከሁሉም በረዘመው ዛፍ ላይ ነው” ብሎ ባሽሙር ሲያሽማጥጥበት ነገሩ ያነውኑ ገባው።
[3] . ቃሉ መሻዘር “ዐም (ዕብራይስጥ)= ሕዝብ”፣ “ሐራ = ነፃ”
[4] . ትርጒሙ “የዐማራ ንጉሥ” ማለት ነው።
[5] . የጐጃም ነዋሪ አማራ እንዳልነበረ ዝቅ ብሎ ይታያል።
[6] . ትርጉሙ “የኢትዮጵያ የበላይ ገዢ”።
[7] . ትንሹ ራስ አሊ በመባል የሚታወቀው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተፈራረመው የንግድ ውል የንጉሡንና የራሱን ማኅተም በሰነዱ ላይ ቢያኖርም፣ ራሱን “የኢትዮጵያ ንጉሥ” ብሎ ነው የፈረመው።
[8] ቃሉ ሙሻዘር ሲሆን ከኦሮሞኛ “ወረ = ቤተሰብ”፣ ከዐረብኛ “ሼኽ/ሸይኽ = ሼኽ”፣ ከአማርኛ “ኦች = የብዙ ምልክት” የተወጣጣ ነው። ባንድጋ ሲጋጠም “የሼይኽ/ሼኽ ቤት/ቤተሰብ” ሲሆን፣ ስሙ የሚያመለክተው ሥርወመንግሥታቸው የኦሮሞ፣ የአማራ ወይንም የአርጐባና የእስላም ቅልቅል መሆኑን ነው።
[9] . የአፄ ዮሐንስ ባለቤት እቴጌ ምሥጢረ ሥላሴ የአፋር ተወላጅ ነበሩ። አፄ ዮሐንስን ያገቡት ከከረስተኑ በኋላ ነው።
[10] . አፄ ቴዎድሮስ የቋራ ብሔረሰብ ሲሆኑ፣ ባለቤታቸው እቴጌ ተዋበች የታናሹ ራስ አሊ ልጅ ናቸው።
[11] ልጅ ኢያሱ የወሎው ገዢ የንጉሥ ሚካኤልና የወይዜሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ልጅ ናቸው። አፄ ኀይለሥላሴ ባያታቸው ኦሮሞ ሲሆኑ እናታቸው ጉራጌ ናቸው ይባላል፣ ባለቤታቸው እቴጌ መነን አስፋው የልጅ ኢያሱ የእኅት ልጅ ናቸው።
[12] . በ እንግሊዝኛ ፊውዳሊዝም [feudalism] በመባል የሚታወቀው ሥርዐት ነው።
[13] . ጸሓፊው የራስ ዘሥላሴ አባቱ ከወረብ እናቱ ከጐናን ምድር ሲሆኑ የተወለደው በመጤነት በደርኀ ምድር ነው ይላል። አንዳንድ ጸሓፊዎች ቦታዎቹ በወለጋ ውስጥ ይገኛሉ ቢሉም የተረጋገጠ ነገር የለም።
[14] . Ethiopia: An Oromo Dilemma. The National Question and Democratic Transition”
[15] . ጆን ማርካኪስም ሆኑ ብዙዎች እሳቸውን የመሰሉ የውጭ አገር ጸሓፊዎች እንደሊቅ ሕዝቅኤል በኢትዮጵያ ምድር አልተወለዱም ብቻ ሳይሆን ቋንቋውንም አይናገሩም፤ ላገሩና ለባህሉ ባዳ ናቸው፤ ግንኙነታቸው ደግሞ ከተማሪዎቻቸውና እንደነሱ በአውሮጳውያን ተቋማት ከተማሩት ኢትዮጵያውያን የማያልፍ ስለሆነ ሕዝቡንም በቅርብ አያውቁትም። ስለዚህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ታሪክና ባህል ያላቸው ግንዛቤ የሚያንፀባርቀው በትርጒም ካነበቡትና በአካባቢያቸው ካሉት የቀሰሙት መሆኑ መካድ ያለበት አይመስለኝም።
[16] . በጣም የሚገርመው አብዛኞቹ የኦሮሞ ምሁራን ነን ባዮች እንደፖለቲካ ልሂቃኖቻቸው በታሪክና ተረት መካከል ያለውን ልዩነት የተገነዘቡ አይመስሉም። በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ ብዙ ምናቦች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የቦረንና የበርይቱማ ዝምድና እንደሐቅ አድርጎ መውሰድ ሮማውያን ገናናዋን የሮም ከተማ የቈረቈሩት ሮሙሉስና ረሙስ በጤግሮስ ወንዝ ከተጣሉ በኋላ ተኲላ እያጠባቻቸው አሳደገቻቸው የሚለውን ምናብ ሐቅ አድርጎ እንደመቀበል ነው። በሌላው ደግሞ በኦሮሞ ላይ የተፈጸመውን ግፍና ሰቈቃ ሲወሽክቱ፣ ኦሮሞች በሌሎቹ ላይ የፈጸሙትን አያነሡም። አፄ ምኒልክ የገባር ሥርዐት በሕዝባችን ላይ ጣሉብን እያሉ ንጉሠነገሥቱን በግፍ ሲወቅሱ፣ “ሕዝባቸው” በየወረረበት ሰፋሪውን ያገሩን ተወላጅ በአረመኔ መልክ እንደጨፈጨፈ፣ ለባርነት እንደዳረገ፣ የባላይነቱን በተቀበለው ደግሞ የሃበታ፣ ጠለታ፣ ሞጋሳ/ⶁአሳ፣ ገበሮ እያለ የተለያዩ የጭቆና ሥርዐቶች እንደጫነባቸው ሊናገሩ አይፈልጉም።
[17] . ‘Sciacallo = ቀበሮ”
[18] . የእንግሊዝኛው፣ “What you read is what you see.”
[19] . እንዲሁም ከዚሁ ጋር በማያያዝ የምጨምር ነገር ቢኖር፣ ባሁኑ አጠራር ኦሮሞ፣ ድሮ ደግሞ ጋላ በመባል የሚታወቀው ሕዝብ ሁናቴም ልክ ይኸንኑ የዐማራን ይመስላል። ጥንት ቦረን፣ ሜጫ፣ ቱለማ፣ ኢቱና ጉጂ በመሳሰሉት ስሞች ራሳቸውን ይጠሩ የነበሩትን ብሔረ-ሰቦች ፣ ኦሮሞ በሚባል በጋራ መጠርያ ስም ሥር እንዲካተቱ አስገድዷቸዋል[19]። ጉዳዩ ራሱን የቻለ ሰፋ ያለ ጽሑፍ ስለሚፈልግ ቦታው ስላልሆነ፣ አሁን ልለፈው። ሁኖም አንድ መሰመር የሚገባ የማይካድ ሐቅ አለ።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply