መክሸፍ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፤ መገለባበጥ እንደ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ
ዛሬም እንዳምናና ታቻምናው፤ ታጋዩን ክፍል ወደ አንድ ለማስባሰብ የሚሯሯጡ ሞልተዋል። ዛሬም የሃሳብ እና የተግባር አንድነት ብቻ ሕዝቡን ለድል እንደሚያበቃ መሰበኩ አላቋረጠም። የነበረው ተመክሮ ሳይፈተሽ፤ በፍላጎትና በምኞት ላይ ብቻ በመመርኮዝ፤ አዲስ ተዋንያን አዲስ ቅኝት ይዘው ወደ መድረኩ ብቅ ይላሉ። አሁንም ከመልሱ ይልቅ ብዙ ጥያቄዎችን ያነገበ ሂደት ቦታውን ወርሷል። ነበርኩበት። አልፌበታለሁ። እስካሁን ቦታውን ይዞ የነበረው፡ “ምንም ይሁን ምንም፤ ኢትዮጵያን እናድን!” በሚልና፤ “ሁላችሁም የያዛችሁትን እርግፍ አድርጋችሁ በመተው፤ እኛ በምንላችሁ ተሰባሰቡ!” የሚል ነበር ጥሪው። የዛሬው ግን ለየት ያለ ነው።
የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል ሆነና፤ በሥልጣን ላይ ባለው የትግሬዎች ገዥ ቡድን የተቀነባበር እስኪመስል ድረስ፤ “የዘር ፖለቲካ አታንሱ፤ እኛ ግን ደስ ባለን መንገድ እንወረውራለን!” “ታሪክን አታውቁም እኛ እናስተምራችኋለን!” “የትግራይ ሕዝብ ተበድሏል፤ አትንኩት፤ ያው የፈረደበትን ዐማራ በመውቀጥ፤ ቅኝቱን ቀይሩት!” የሚል ሆነብኝ። በዚህ “አንድነትን እናመጣለን!” “አዲሲቷን ኢትዮጵያን እንመሠርታለን!” አሉን። እናም ወደሚቀጥለው ባለተረኛ ተዋንያን በሩን በው አድርገው ከፍተው፤ ይሄው፤ “አለቀ በቃ! ድል መጣ! አንድነት ተፈጠረ! እንግዲህ ከዚህ የወጣ፤ ውጉዝ ከመ አርዮስ! ጠላት ነው!” የሚለውን የተለመደ ዘፈን እያቀነቀኑልን ነው።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን የዛሬ ፵፮ ዓመት የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆኜ፤ በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፤ የኢትዮጵያ ጂዖግራፊ መምህሬ ሆነው ነው ያወቅኋቸው። ያን ጊዜ ስለ ቤጌምድርና ስሜን አንድ አውራጃ፤ ስሜን አውራጃ ሲነግሩን፤ “የደንጋይ ክምር፤ ሰው ምንም ነገር የሌለው ደሃ፣ ለምድ ለባሽ! . . . ” ብለው ሲገልጹ፤ ከተጨባጩ ሀቅ ይልቅ፤ የኔ የሆነው ክፍል ተነካ በሚል ብቻ፤ “አይደለም፤ ቦታው እንደገለጡት አይደለም . . . ” ብዬ ስነሳ፤ በሚያስደነግጥ ቀፋፊ በሆነ ንቀትና እብሪት፤ “ተቀመጥ! ስለማታውቀው አትቀባጥር!” በማለት፤ እንደመምህር ከማስረዳት ይለቅ፤ ሰድበው አስቀመጡኝ። ያን ጊዜ፤ ቦታውን ሄጄ እንደማይና፤ ስህተታቸውን እንደማጋልጥ፤ ለራሴ ቃል ገባሁ።
ከዚያ ከአንድ ዓመት በፊት፤ የበዕደ ማርያም ትምህርት ቤት (ላብስኩል) ተማሪ ሆኜ፤ የተማሪው እንቅሳቃሴ ንቁ ተሳታፊዎች ከነበሩት ጋር አብሬ እሯሯጥ ነበርና፤ የአሁኑን ዶክተር አረጋዊ በርሄን ያወቅኋቸው ያኔ ነበር። ያኔ ከነዋለልኝ፣ ጥላሁን ግዛው፣ ጎይቶም፣ ተስፉ ኪዳኔ፣ መለስ ተክሌ፣ ፀጋዬ ገብረመድሕን፣ ማርታ መብራቱ፣ ፀሎተ፣ ዮሐንስ፣ ዳዊትና ሌሎችን በመከተል፤ ጠበብ ያለ አንድ ቡድን ነበር። በነበረው ቅኝት፤ ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ “የዐማራው መንግሥትይውደም!” በማለት፤ ዘለግ ባለው ቁመታቸውና ጎላ ባለ ድምጻቸው፤ መፈክር ያስተጋቡ ከነበሩት መካከል አንዱ ነበሩ። ያኔ የዐማራው መንግሥት የተባለውን አሁን ሳስበው ይገርመኛል። አብሬ ማጨብጨቤንና ያንን ማራገቤን አልክድም። ምንም ገና የሃያ ፈሪ እንኳን ያልሞላው ዕድሜ ውስጥ ብገኝም፤ ነበርኩበት። ወጣትነቴን ምክንያት አድርጌ ማምለጥ አልፈልግም። ዐማራውን ተጠያቂ ማድረጉን ተሳትፌበታለሁ።
ከዚያ በቀጥታ አሁን ወዳለንበት ወቅት እንምጣ። ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የትግሬዎች ገዥ ቡድን ሳይሆን፤ ከሁሉም የተውጣጣ አዲስ መደብ ነው አሉን። ይገርማል! ይሄ አዲስ መደብ ነው የትግራይን ክልል ከሌሎች ለይቶ የሚያለማው! ይሄ አዲስ መደብ ነው የኤፈርት ባለቤት! ይሄ አዲስ መደብ ነው ወታደሩን ከላይሆኖ የሚቆጣጠረው! ይሄ አዲስ መደብ ነው ከትግራይ ክልል አንድም ዐማራ ግለሰብ፤ ንብረት ማፍራት፣ በፖለቲካው መሳተፍ እንዲያው ባጠቃላይ መኖር የለበትም በማለት፤ በዐማራው ክልል ግን ገዥ፣ ፈላጭ ቆራጭ አሁንም ትግሬዎቹ እንዲሆኑ ያደረገው! በአኙዋክ መሬቱን ዘርፎ ሕዝቡን እየጨረሰ ያለው! በደቡብም እንዲሁ። ይሄ አዲስ መደብ ነው ወልቃይትን፣ ራያን፣ ጠለምትን የትግሬ እንጂ የዐማራ ክፍል አይደለም። ሕዝቡም ትግሬ እንጂ ዐማራ አይደለም ያለው! ይሄ አዲስ መደብ ነው መተከልና የዐማራ አይደለም ብሎ ለቤንሻንጉል የለገሰው። እስኪ ላስታውሳቸው፤ እሳቸው ይመሩት የነበረውና በወታደራዊ አዛዥነት ያሰለፉት ጦር ነበርኮ፤ ወልቃይት ወሮ፤ ከዛሬ ጀምሮ ትግሬዎች ናችሁ ብሎ ያወጀው። ከረሱት ይሄ የሆነው የዛሬ ፴፰ ዓመት ነበር። እንደፒላጦስ እጃቸውን እያጠቡ ይሆን!
እስኪ አሁንም ዶክተር አረጋዊ በርሄን ልጠይቃቸው። ያኔ ዐማራው ለብቻው መንግሥቱን እንደያዘና ዐማራው እንደ ሕዝብ ለብቻው እንደተጠቀመ ይገልጹ ነበር። ያኔ የመገዘዝን አፈር ገፊ፤ ከልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም በላይ ተጠቅሟል! ብለው የዐማራ መንግሥት ብለው የወነጀሉትና፤ ዛሬ ትግሬዎች አልተጠቀሙም፤ የትግሬዎች መንግሥት ሳይሆን ያለው ከሁሉም የተውጣጣ መደብ ነው የሚሉን፤ ማጠፊያው የት ላይ አጠራቸው? ወይስ ለኔ ሲሆን አይሠራም የሚለው ተገለባባጭነት ነው!
ወደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ስመጣ፤ የት ጀምሬ የት እንደምጨርስ ይጨንቀኛል። መነሻና መድረሻው፤ ተጨባጩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀቅ ሳይሆን፤ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ማንነትና በአዕምሯቸው የሰነቁት አባዜ ነው። ዐማራን ይጠላሉ፣ ይፈራሉ፣ ይንቃሉ፣ አዕምሯቸውን አስጨንቆ የያዛቸው እስኪመስል ድረስ፤ በዐማራዎች ላይ የማያባራ ወርጅብኝ አልተለያቸውም። እስኪ የዘር ፖለቲካ አያስፈልግም ለሚል ምሁር፤ “በላይ ዘለቀ ኦሮሞ ነው!” የሚለውን ምን አዘባረቀው! የበላይ ዘለቀን የትውልድ ማንነት ከዚህ መጣል ለምን ጉዳይ ነው። በፖለቲካ፤ ምልክቶች፣ ናሙናዎችና ቃላት፤ ከሌላው ጊዜ በጣም በተለየ መልክና ክብደት፤ መልዕክት ማስተላለፊያ ይዘት ይጎናጸፋሉ። ይሄን ጉዳይ ስለመጣላቸው የወረወሩት አይደለም። መልዕክት አለው። ዐማራ የለም የሚሉት ምሁር፤ ኦሮሞ አለ ብቻ ሳይሆን፤ እሳቸው ዐማራ ብለው ማሞገስ ( እውነትም በላይ ዘለቀን እያሞገሱ ከሆነ! ) ያልፈለጉትን፤ ኦሮሞ ብለው መሰየም ወደዱ! ለምን ይሆን!
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፤ ቀጥለው አፄ ቴዎድሮስን የሚችሉትን መጥፎ ቀለም ሁሉ ለቅልቀው፤ ከሃዲ ሆነው ከእንግሊዝ ጋር ያበሩትን፤ የሀገር ተቆርቋሪ፣ ጭቆናን ተቃዋሚ አድርገው አቀረቡልን። መክሸፍ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ብል፤ የሚረዳልኝ ይኖር ይሆን!
ልቀጥል።
ሀገር ካጅ የሆኑ ወገኖቻቸው፤ እንግሊዝን በማምጣት፤ አፄ ቴዎድሮስ ላይ አብረው፤ በመሪነት ዘመቱ። እኒህ ባገራችን ታሪክ ወራዳዎች ናቸው። ስለ አፄ ቴዎድሮስ ማንነት፤ ከስድሳ ስድስቱ ሕዝባዊ መነሳሳት ወዲህ፤ ትልቅ አክብሮትና መታወቅ ስለሰፈነ፤ እዚህ ላይ ማንሳቱ ድሪቶ ማከል ይሆናል። ነገር ግን፤ አሁን የሳቸውን የመጨረሻ ወቅት ማንሳት፤ በዐማራና በትግሬዎች መካከል ያለውን የተዳፈነ ረመጥ መቆስቆስ ነው። በርግጥ የምሁር ሚና፤ በሕዝቡ መካከል ያለውን ታሪካዊም ሆነ ተጨባጭ አራራቂ ሁኔታ፤ ምክንያታዊ ገለጻዎችን በማቅረብ፤ ሕዝቡን ለበጎ ግንዛቤ ማቀራረብ ነው። የከሸፈ ከሆነ ግን፤ በቁስል ላይ ስንጥር በመስደድ፤ ያባብሳል። ይህን ነው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እያደረጉ ያሉት። ለምን ይሆን!
በድምሩ የሲያትል ስብሰባ ሲታይ፤ ጥረቱና መዘጋጀቱ ይበል የሚባል ነው። ነገር ግን፤ ዐማራውን የጠቀጠቀ በመሆኑ፤ እኔ አዝኜበታለሁ ብቻ ሳይሆን፤ እውነት የትግል ማዕከል የተፈጠረበት፤ የሕዝቡን ፍላጎት ያዳመጠ ነበር ወይ? የሚለውን ለጥያቄ አቅርቤበታለሁ። የታጋዩን ክፍል ወደ አንድ ለማምጣት የሚደረገው ሙከራ፤ መጀመር ያለበት፤ ለምን የሚለውን በመመለስ ነው። ቀጥሎ ደግሞ ማን ይሰበሰባል፤ ማን የስብስቡ አካል ነው። ማንስ የስብስቡ ዒላማ ነው። የሚለው ነጥሮ መውጣት አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ የዚህ ባለቤትና፤ ብሎም የስብስቡ አካል ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ጠላት ነው። ይሄን በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት፤ ለምን እንደሚጠላና ለምን መወገድ እንዳለበት መግለጥ ያስፈልጋል። ማንነቱንም የግድ ማሰቀመጥ ያስፈልጋል። ጅግራን ጅግራ ብለን ነው ማደንም፤ መብላትም የምንችለው። ጅግራን አሞራ፤ አሞራን ደግሞ ጅግራ ካልን፤ የምንሠራውን አናውቅም። አሁን በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም። የመደብ ጉዳይ አይደለም። አሁን በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለው፤ የትግሬዎች መንግሥት ነው።መዘርዘሩ ባያስፈልገኝም፤ ይሄን ለማለት፤ እያንዳንዱን ትግሬ በዙፋን ላይ ማስቀመጥ የለብኝም። የዚህ መንግሥት አባላት ስብጥርና ይሄ መንግሥት እየሠራ ያለው፤ የማንነቱ መግለጫ ነው። አፌን ሞልቼ የትግሬዎች መንግሥት ነው ስል፤ ትግሬዎችን ስለምጠላ አይደለም፤ ሀቁን መናገር ስለፈለግሁ እንጂ!
ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በተጨማሪ፤ የዶክተር አረጋዊ በርሄው ታንድ፤ የአብረሃ ደስታው አረና፤ ትግሬዎች ተጨማሪ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው ድርጅት ያስፈልጋቸዋል ብለው የተቋቋሙ ናቸው። ከላይ እስከታች ግን፤ ዐማራው መደራጀት የለበትም እየተባለ ይደሰኮራል። ለምን? ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ሲታጩ፤ ከላይ እስከታች የተንጫጩት፤ ትግሬዎቹ ናቸው። በቀንደኝነት አብረሃ ደስታ። በምግባራቸው የተቃወምን ሌሎች ኢትዮጵያዊያን፤ ዘረኛ ተብለን ተወቀስን። የኛ ፖለቲካ፤ እንደ ቁጥራችን ጥንቅርቅሩ የበዛ ነው!
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ሆኑ ዶክተር አረጋዊ በርሄ በንግግራቸው ውስጥ፤ባሁኑ ሰዓት አደጋው፤ የትግሬዎች መንግሥት ሳይሆን፤ በውጪ ሀገር በትግራይ ሕዝብ ላይ ወቀሳ የሚያቀርቡት ታጋዮች ናቸው በማለት፤ የትግሉን መሪ ሊጠመዝዙት ሞክረዋል። ከላይ ከተዘረዘረው ይሄን ሳክልበት፤ “ደሮን ሲያትልሏት በመጫኛ ጣሏት!” ሆነብኝ። አንዱን የሀገሪቱን ጉምቱ ክፍል፤ ማለትም ዐማራውን ያላካተተው ይሄ የሲያትሉ ስብሰባ፤ ለአንድ እኔን ለመሰለ ዐማራ፣ ምን ትርጉም ያስተላልፍልኛል? እኔንስ ያላካተተ ከሆነ፤ ባለጉዳይ ነኝ ወይ? አጠቃላይ መልዕክቱ፤ የትግሬዎችን ገዥ ቡድን ካልተጠቀመው የትግራይ ሕዝብ ለይታችሁ ዕዩልን ጩኸት፤ በሀገሪቱ ያለው የትግሬዎች መንግሥት አይደለም የሚለው ማደንቆሪያ ታክሎበት፤ በትልቁ ማስተጋቢያ መለከት ይስተጋባል። ወዴት ኮተት ኮተት!
እዚህ ላይ፤ ትግሬዎች፤ የትግሬዎች መንግሥትና ትግራይን አታውቁም እየተባልን ነው። ድንቅ! አስተማሪዎቻችን በዛችሁ! እኔ በዐማራነቴ የምለው፤ የናንተ ፖለቲካ የቅንጦት ነው። ለኔኮ፤ የዐማራው በሕልውና መቆየት ነው አንገብጋቢ ጉዳዬ! ተውኝ፤ “ራሴን በሕልውና ልጠብቅ!” ካለው ወገኔ ጋር አሰልፌ መታገሌ፤ የተፈጥሮ ግዴታዬ ነው! እኮ ነው እያልኩ ያለሁት። የኔን ትግልና በዚህ የተሰለፈውን ልታውቁ እንደማትችሉ እገነዘባለሁ። አይጎዳኝም። የለም ግን አትበሉ። የናንተ አለማወቅ፤ የዐማራውን ታጋይ ብን ብሎ እንዲጠፋ አያደርገውም። ዐማራው ታጋዮቹ፤ በውጪም ሆነ በውስጥ፤ በከተማም ሆነ በገጠር፤ በሰላማዊም ሆነ በታጠቀ አመጽ እየተፋለሙ ናቸው። ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው ዐማራው ነው። ይህ የማንንም ዕውቅና አይጠይቅም። ትግሉ ያብባል። ዐማራው ለሕልውናው የሚያደርገው ትግል በአቸናፊነት ይጠናቀቃል። ይልቅስ ተረዱትና ለአብሮነቱ ጥረት አድርጉ። በኛው በዐማራዎች በውስጣችን ለሚካሄደው ጉዳይ፤ እኛው እንጨነቅበት። አስተካክለን ወደፊት እንጓዛለን።
በሳሞራ የኑስም ሆነ ስብሃት ነጋ እሳቤ፤ ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ህወሓት ነው። አዎ! የትግራይ ሕዝብ ተጠቅሟል። ይሄን ለመከራከር የሚፈልግ፤ ሄዶ ገዥዎቹን ይከራከራቸው። ከነሱ በላይ ስለትግራይ ሕዝብ አውቃለሁ ብሎ የተነሱት፤ አረናና ታንድ ናቸው። እኒህ ለትግሬዎች የቆሙ ድርጅቶች ናቸው። ማለትም ከትግሬዎች ገዥ ቡድን ተጨማሪ ነው። እና ከኒህ ጋር ክርክር አልገጥምም። ሆን ብሎ የተኛን መቀስቀስ አይቻልምና!
አንዱዓለም ተፈራ (eske.meche@yahoo.com)፤ ሐሙስ፣ ግንቦት ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓመተ ምህረት
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply