የሀገር ውስጥ ምሁራን በፊደሎቻችን ላይ ብዙ ዓይነት ቅሬታዎችንና ጥያቄዎችን ሲያነሡ ቆይተዋል አሁንም በየ ብዙኃን መገናኛው ማለትም በየነጋሪተ ወጉ(Radio) በየ ምርአየኩነቱ (Television) እና በየ መጣጥፉ በማንሣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለውጦችንም ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም እንዲመቻቸው ይመስላል የፊደሎቻችን ባለቤት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መሆኑን ልቦናቸው እያወቀ እንደፈለጉ ያለከልካይ እና ጠያቂ ለውጥ ለማድረግ እንዲመቻቸው ከፊደላቱ ባለቤት ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተቃውሞ እንዳይነሣባቸው የፊደላቱን ባለቤት ለባዕድ ይሰጡታል ወይም የደቡብ ዓረቢያ ነው ብለው ይሰብካሉ፡፡ ፻ ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ ጀምሮ ምሁራኑ በፊደሎቻችን ላይ ጥያቄ ሲያነሡ ቆይተዋል፡፡ የቀድሞዎቹ በተለየ ያነሡት የነበረ ጥያቄ እንደዛሬው መቀምር (Computer) ባልነበረበት ሰዓት የአማርኛ መጻፊያ መሣሪያ (typewriter) ለማሠራት የአማርኛ ፊደሎች በጣም ብዙ በመሆናቸው በሚል ሰበብ በእነሱ አባባል አላስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን በርካታ ፊደላት ማስወገድ ወይም መቀነስ ግዴታ ነው ብለው ይከራከሩ ነበር፡፡
ነገር ግን የፊደላቱ መበርከት ታይፕራይተሩን ከመሠራት ሳያግደውና አማርኛን በታይፕራይተር መጻፍ እውን መሆን እንዳይችል ሳያደርገው ሁሉንም ፊደላት ባካተተ መልኩ ተሠርቶ በመምጣቱ በዚህ ምክንያት ተነሥቶ የነበረው የጦፈ ክርክር ለመዘጋት ቻለ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው እና እጅግ የሚገርመው ደግሞ ጥቂቶቹ ዚኖሜኒክ ምሁራን በገዛ ፊደሎቻችን መጠቀማችን ለእድገት እንቅፋት ሆኖናል፡፡ መጠቀም ያለብን በላቲኑ ነው ይህን ብናደርግ እድገት እናመጣለን የሚሉ መገኘታቸው ነበር፡፡ በራሳችን ፊደላት መጠቀማችን እንዴት ሆኖ ለእድገት እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ግን አሳማኝ አይደለም እንዲያው የሚመስል እንኳን ማስረጃ አመክንዮ ወይም ሎጂክ ማቅረብ አልቻሉም ነበር፡፡ እግዚአብሔር መቼም በየዘመኑ ሰው አያሳጣምና በአንዳንድ ልበብርሃን ምሁራን በእነ አብዬ መንግሥቱ ለማ የማያዳግም ምላሽ ማለትም የራሷን ፊደል ጥላ በምዕራባዊያኑ እየተጠቀመች ያለችውን ቱርክን የትም አለመድረስ የራሷን ፊደል መጠቀሟ ከእድገት ያልተገታችውንና አስደናቂ ስኬት ያስመዘገበችውን ጃፓንን እና የደረሰችበትን የስኬት ወይም የእድገት ደረጃ በማንሣት በራስ ፊደላት መጠቀም ሊያግዝ ወይም ሊረዳ ቢችል እንጂ እንቅፋት ሊሆን እንደማይችልና መረጃም ሊቀርብበት እንዳልቻለ ወይም እንደሌለ በማሳየትና በመርታት ፊደሎቻችንን ሊታደጓቸውችለዋል፡፡
ነገር ግን ሌሎች ያኔም ሲነሡ የነበሩ አሁንም እየተነሡ ያሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለእነኝህ ጥያቄዎች በእግዚያብሔር ፈቃድ ከዚህ በኋላ ሌላ ጥያቄ ሊነሣ በማይችልበትና አጥጋቢ በሆነ መልኩ ለምሁራን አይደለም ለማንኛውም ሰው ሊገባ በሚችል ግልጽና ጥርት ባለ መልኩ ለጥያቄዎቻቸው መልስ እሰጣለሁ፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ ምላሹ ምሁራኑን እንደሚያረካ፡፡ እስከሁንም ጥያቄዎቻቸውን ከመቶ ዓመታት ጀምሮ እስከ ዛሬ የሚያነሡትና በቂ መልስ ያልተሰጣቸውም አንዱና ዋነኛው ምክንያት መልስ ሊሰጡ የሚገባቸው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ምሁራኑ ጥያቄዎችን የሚያነሡት ባልገባቸው ነገር ላይ በመሆኑ ጥያቄዎቻቸው የትም የማያደርሳቸው መናኛዎች መሆናቸውን በማየትና በመናቅ ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጧቸው ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን እነዚህ ሰዎች በየዩኒቨርስቲው (ወይም መካነትምህርት) ከያዙት የወሳኝነት ሥልጣንና በፊደላቱ ዙሪያ ላሉ ነገሮች ሁሉ የሚመለከታቸው ወይም ተጠያቂዎች እነሱ እንደሆኑ ተደርጎ ከመታመኑ የተነሣ ያለ እውቀት ሳይገባቸው ትክክል መስሏቸው የሚወስኑት የተሳሳተ ውሳኔ ሥራ ላይ ሊውል የሚችልበት አገጣሚና ስጋት ወይም አደጋ በግልጽ እየታየ በመሆኑ ዝምታውንና ንቀቱን ወደ ጎን በመተው በቂና አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በማመን ከእናት ቤተክርስቲያን የገኘሁትንና የማውቀውን ያህል ተገቢውን ምላሽ ሰጥቻለሁ፡፡መልካም ንባብ በቀጥታ ወደ ጥያቄዎቹ ልሒድና ጥያቄዎቻቸው በራሳቸው አገላለጽ የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡
፩. የፊደላቱ ብዛት ከሚገባው በላይ ተንዛዝቶና ገዝፎ እንዲታይ በመደረጉ በመማር ማስተማር ተግባር ላይ አላስፈላጊ ችግር ማለትም መሰላቸትን፣ መታከትን፣ መወሳሰብን፣ አስከትሏል፡፡
፪. ሞክሼ ፊደላት መኖራቸው በሥነ ጽሑፎቻችን ላይ የተዘበራረቀ የፊደላት አጠቃቀም እንዲከሰት አድርጓል፡፡
፫. የአናባቢ ወይም የድምጽ ሰጪ ምልክቶች ወጥ አለመሆን ወይም የተዘበራረቁ መሆናቸው እነእርሱን በቀላሉ ለማጥናት እንዳይቻል አድርጓል የሚሏቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ነገር ግን ምሁራኑ ያልተረዱት ነገር ቢኖር አባቶቻችን ያለበቂና አጥጋቢ ምክንያት ያደረጉት አንድም ነገር እንደሌለ ያለማወቃቸውን ነው፡፡ አሁን ጥያቄዎቻቸውን በተናጠል ከበቂ መልሶቻቸው ጋር እንይ፡-
ወደ መጀመሪያው ጥያቄያቸው ወይም ቅሬታቸው ስናልፍ ማለትም የፊደላቱ ብዛት ከሚገባው በላይ ተንዛዝቶና ገዝፎ እንዲታይ በመደረጉ በመማር ማስተማር ተግባር ላይ አላስፈላጊ ችግር ማለትም መሰላቸት መታከት መወሳሰብ አስከትሏል ላሉት ችግር መፍትሔ አድርገው ያቀረቡት ነጥብ ሞክሼ ፊደላትን፣ ፍንድቅ ፊደላትን፣ የግዕዝ ዲቃላ ፊደላትን በአጠቃላይ ከ፺፩ በላይ ፊደላትን ማስወገድ ሲሆን አንዳንዶቹ ሻል ያሉቱ ደግሞ ፍንድቅ ፊደላትንና የግዕዝ ዲቃላ ፊደላትን በምልክት መተካት ይላሉ፡፡ ይህን ጥያቄ ያነሡ ሰዎች ያልተረዷቸው ነገሮች ቢኖሩ፡-
ሀ/ ቋንቋችን አቡጊዳዊ (syllabary) ማለትም አናባቢንና ተነባቢን በአንድ ፊደል የወከለና ፎነቲክ ማለትም በቋንቋው ውስጥ ላሉ ድምፆች ሁሉ ለእያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ፊደል የሰጠ ወይም የቀረጸ ቋንቋ መሆኑን፡፡ በመሆኑም የፊደላቱ መበርከት ጨርሶ በጥያቄ መልክ ሊነሣ ባልተገባ ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ መሆኑ በዓለም ውስጥ ካሉ ቋንቋዎች እንዲደነቅ ያደረገውና ከማንኛውም ቋንቋ በተሻለ መልኩ ለብዙ ድምፆች ፊደል የቀረጸ በመባል በባዕዳን ምሁራን ሳይቀር ተደናቂ ያደረገው የቋንቋችን ባሕርይ መሆኑ ነውእና፡፡
ለ/ አሁንም ያልተረዱት ነገር ቢኖር ፊደላቱ በዝተዋል በሚል ከ፳፬ በላይ ፍንድቅ ፊደላትንና ፳ የግዕዝ ዲቃላ ፊደላትን ይወገዱ ሲሉ የሚያስወግዷቸው ፊደላቱን ብቻ ሳይሆን በፊደላቱ የተወከሉትን በንግግሮቻችን ውስጥ ያሉ ድምፆችን ጭምር ይወገዱ ማለታቸው እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ቢሆን ደግሞ የቋንቋውን ባሕርይና ምድቡንም ማለትም ከየትኛው የቋንቋ ዘር ውስጥ መሆኑን የሚገልጹትን ድምፆች እንዲያጣ ሊያደርገው መሆኑን፣ቋንቋው ማለት የሚፈልገውን በቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ማለት እንዳይችል ወይም እንዳይገልጽ ሊሆን መሆኑን፣ በጽሕፈት ላይም ከነዚያ ከተወገዱት ፍንድቅ ፊደላትና የግዕዝ ዲቃላ ፊደላት አንዷ የምትገልጸውን ድምፅ በመወገዳቸው ምክንያት ይወክሉት የነበረውን ድምፅ ለመግለጽ ከዚህ በኋላ እንደ አልፋቤቲካዊ ወይም ተናጠላዊ ቋንቋዎች በሁለት ፊደላት መግለጽ ግዴታ በመሆኑ በአንድ ገጽ የሚያልቅ የነበረው ጽሑፍ ከአንድ ገጽ በላይ እንዲገልጽ ሊያስገድደን እንደሆነ ነው፡፡ ይህም በደራሲው በሐዲስ ዓለማየሁ መጽሐፍ በፍቅር እስከ መቃብር ታይቷል፡፡ እራሳቸው ሐዲስ ዓለማየሁም ቢሆኑ የዚህ ዓላማ አራማጅ ሆነውም ጨርሶ ችግር አያመጣም አላሉም፡፡ የሚያስከትለው የንባብ ችግር ወይም የምሥጢር መፋለስና መሰወር ችግር ይህን ያህል አይደለም አሉ እንጂ፡፡ ነገር ግን ትንሽም ቢሆን በትክክሉ ማስቀመጥ ሲቻል አንዲትስ ብትሆን ለምን አግባብ ያልሆነ እንከን እናስቀምጥ?፡፡
አባቶቻችን ያንን ያህል እርቀው በንግግር ላሉ ድምፆች ሁሉ ፊደል በመቅረጽ ያለችግር ማለት የተፈለገን ነገር በትክክል እንዲባል እስከማድረግ ድረስ ርቀው በመሔድ ያደራጇቸውን ፊደላት በመቀነስ ቀደም ሲል ያየነውንና ቀጥሎ የምናያቸውን ችግሮች እንዲከሰቱ ማድረግ ማንም ሊረዳው እንደሚችለው የቋንቋውን እድገትና ብቃት ወደ ኋላ መመለስ ወይም ማንሸራተት እንጂ እድገት ወይም ችግር መቅረፍ ሊሆን አይችልም፡፡
አጥንቶ ለመያዝ ከአንድ ሰሞን በላይ የማይጠይቁትን ፊደላት ሲፈለጉ ብቻ ካልሆነ በስተቀር በፊደል ገበታቸው ቦታቸውን ይዘው አርፈው የተቀመጡትን ፊደላት አቀለልን በማለት ሲያስወግዷቸው ከዚያ በኋላ እነሱ ችግር ነው ከሚሉት በላይ መጽሐፍ ለመጻፍ ተጨማሪ ገጾችን መጠየቃቸው ይህም ደግሞ አንዳች ነገር ለመጻፍ በተፈለገ ጊዜ ሁሉ የግድ መሆኑ ከግለሰብ አልፎ በሀገር ጥሪት ወይም ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው አላስፈላጊ ወጪ ወይም ኪሣራ ጨርሶ አልታያቸውም፡፡ የዚህ ዓላማ አራማጅ የነበሩት ሐዲስ ዓለማየሁ መጽሐፋቸውን እንደዚህ አድርገው ይጻፉት እንጂ በንግግራቸው ግን ጨርሶ ሊተገብሩት አልቻሉም ነበር፡፡ ሊተገብሩትም አይችሉም ምክንያቱም ቋንቋችን ፎነቲክ ነውና ማለትም ለእያንዳንዱ ድምፅ የየራሱን ፊደል የቀረጸና እንደ ፎነቲክነቱም ለእያንዳንዱ ድምፅ ፊደል የመቅረጽ ግዴታ ስላለበት፡፡ ቋንቋችን ፎነቲክ የሆነው በምርጫ ወይም ተፈልጎ አይደለም ነገር ግን ተፈጥሯዊ ባሕርይው ስለሆነ እንጂ፡፡ ቋንቋችን በተፈጥሮው አቡጊዳዊ ወይም ሲላቢካዊ መሆኑ ነው ፊደሎቻችን አቡጊዳዊ ወይም ሲለበሪ ማለትም አናባቢና ተነባቢን በአንድ ፊደል የሚወክሉ እንዲሆኑ የተገደዱት፡፡ ፊደሎቻችን ሳይፈጠሩ በፊትም የቋንቋችን ድምፆች በተፈጥሯቸው ስንናገራቸው አናባቢና ተነባቢ በአንድ ላይ ተቀላቅለው ወይም ተደምረው ነው የሚወጡት፡፡ ለምሳሌ በበ ድምፅ ውስጥ “ብ”ና “ኧ” ድምፆች ተቀላቅለው ነው የሚወጡት ቡ ስንል ደግሞ “ብ”ና “ኡ” ፣ ቢ ስንል ደግሞ “ብ”ና “ኢ” በዚሁ መልኩ ሁሉንም ሆሄዎች ስንጠራ በውስጣቸው የአናባቢ ድምፆች አብርው ይኖራሉ፡፡ ይሄ በቋንቋ ምሁራን የሚነገረን ነው እኔ ግን የየፊደሎቹ የሳድስ ድምፅ ከአናባቢዎች ጋር ሆነው ነው ድምፆቹ የሚወጡት የሚለው አባባል አይስማማኝም፡፡ እንደኔ እንደኔ ድምፆቹ ከሳድስ ድምፅ ጋር ብቻ በመሆን ሳይሆን በየቤታቸው ያሉ ድምፆች ከአናባቢዎች ጋር ሆነው ድምፆቹ እንደሚወጡ ነው የማምነው ለምሣሌ በ ስንል እራሱ “በ” እና “ኧ” ቡ ስንል “ቡ” እና “ኡ” ቢ ስንል “ቢ” እና “ኢ” ሌሎቹንም እንደዛው፡፡ ምክንያቱም
1ኛ. ለምሣሌ “ባ” ስንል አፋችን እንደተከፈተ ሆኖ አገጫችን ካለበት ቦታ ሳይንቀሳቀስ ከንፈር እና ከንፈራችን በመጋጠም ነው ድምፁ የሚፈጠረው በመሆኑም “ባ” እና “ኣ” ድምፆች ነው የሚወጡት እንጂ የላይኛውና የታችኛው ጥርሳችን የመጋጠም ያህል ተቀራርበው የሚወጣው “ብ” ድምፅና አናባቢው “ኣ” አይደሉም የአፍ አከፋፈታችንን ድምፆቹ በሚወጡበት ጊዜ ያየን እንደሆነ ቅርብ ሆኖ የምናገኘው የየድምፅ ቤቶቹ እና አናባቢዎቹ እንጂ የሩቁ የሳደስ ቤትና አናባቢዎቹ አይደሉም፡፡ በተለይም ይህ መሆኑን በግልጽ የምንረዳው በግዕዝ ዲቃላ ፊደላት ድምፆች ላይ ያለውን የድምፅ አፈጣጠር ወይም ጥምረት ስናይ ነው፡፡ በመሆኑም የሳድስ ቤት የሚወክለው የራሱን ቤት ብቻ እንጂ የሁሉንም ቤት አይደለም፡፡
2ኛ. የድምፆቹን ፊደል ውክልና ያየን እንደሆነ የሳድስ ቤት ፊደላት የአናባቢ የድምፅ ሰጪ ምልክት ያለበት እንጂ እንደ ግእዝ ቤት ፊደላት ወጥ ወይም የድምፅ ሰጪ ምልክት አልባ አይደሉም፡፡ ወይም ደግሞ የምሁራኑ አባባል ትክክል እንዲሆን ፊደሎቹ ባሉበት ሆነው የሳድስ ቤት ድምፅና የግእዝ ቤት ድምፅ ድምፆቻቸውን ብቻ መቀያየር ይኖርባቸዋል፡፡ ይሄ ከሆነ ብቻ እነሱ የሚሉት ማለትም የሳድስ ቤት ድምፅ የነበረው አሁን የግእዝ ቤት ድምፅ ደደረግነው ድምፅ ካናባቢዎች ጋር እየሆነ የየቤቱን ድምፅ ይፈጥራል ቢባል ትክክል ይሆናል፡፡ ከተሰጣቸው የፊደላት ውክልና ጋርም የተስማማ ይሆናል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን ወደኋላ ተመልሶ የአናባቢ ቅጽል ያለበት የሳድስ ቤት የአናባቢ ቅጽል የሌለባቸውንና መሠረታዊያን ወጥ ፊደላት የሆኑትን የግእዝ ቤቶች ድምፅ ይፈጥራል ማለት አይቻልም አመክንዮአዊም አይደለም፡፡ ወደቀደመው ነገራችን ስንመለስ እንግዲህ አናባቢ እና ተነባቢ ድምፆች አብረው ያሉ በመሆናቸው ነው ፊደል ሲቀረጽላቸውም አናባቢንና ተነባቢን በአንድነት የሚገልጹ ሆነው የተገኙት፡፡ ይሄ እንግዲህ ምንም ልናደርገው የማንችለው ተፈጥሯዊ ባሕርይው ነው፡፡ ይህንን ከላይ የገለጽኩትን የቋንቋችንን ተፈጥሯዊ ባሕርይ የሚያውቅና የተረዳ ሰው በምንም ተአምር ቋንቋችን ለእያንዳንዱ ድምፅ ፊደል መቅረጹን ሊቃወም ወይም ላይቀበል አይችልም፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ቋንቋችን ለብዙ ድምፆች ለየራሳቸው ፊደል በመቅረጹ የሚያክለው ወይም የሚስተካከለው ቋንቋ የለም በዚህም እጅግ ተደናቂ አድርጎታል፡፡
በመሆኑም ምሁራኑ ይህንን ጥያቄ ሲያነሡ እኔ የሚገባኝ ምንድ ነው? ሰዎቹ ምን ያህል የገዛ ቋንቋቸውን ባሕሪ በጥልቀት ያለመረዳታቸውንና ባልተረዱት ነገር ላይ ለውሳኔ መቸኮላቸውን ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ሰዎች በቋንቋ ጥናት የዶክትሬትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡
ሐ/ የቋንቋው የድምፅ ሥርዓት የሚበላሽ መሆኑን ማለትም አዳዲስና ከአማርኛ ቋንቋ የልሳን ድምፆች ውጭ የሆኑ ወይም ያልነበሩ የተንሻፈፈና የተወላገደ የአፍ አከፋፈት፣ የምላስ መተሣሠር የሚያስከትሉ አዳዲስ ድምፆች የሚከሠቱ መሆናቸውን፡፡ ለምሳሌ ባሏ ለማለት ባልዋ፣ ሲሟሟ ለማለት ሲሙዋሙዋ፣ ሲሯሯጡ ለማለት ሲሩዋሩዋጡ፣ እሷ ለማለት እሱዋ፣ ሿሚ ለማለት ሹዋሚ፣ ቋንቋ ለማለት ቁዋንቁዋ፣ ቧልት ለማለት ቡዋልት፣ ፊቷ ለማለት ፊቱዋ፣ ወንድሞቿ ለማለት ወንድሞቹዋ፣ ኋላ ለማለት ሁዋላ፣ ኗሪ ለማለት ኑዋሪ፣ እንኳን ለማለት እንኩዋን፣ ዟሪ ለማለት ዙዋሪ፣ አንዷ ለማለት አንዱዋ፣ እጇ ለማለት እጁዋ፣ጓደኛ ለማለት ጉዋደኛ፣ ጧሪ ለማለት ጡዋሪ፣ ጯሂ ለማለት ጩዋሂ፣ ፏፏቴ ለማለት ፉዋፉዋቴ ወ.ዘ.ተ እየተባሉ ሲጻፉ ሲነገሩ ሲነበቡ ማንም እንደሚገነዘበው ለአንደበት ካለመመቸታቸውም ባሻገር ለጆሮ የሚሰጡት የድምፅ ቃና ጥሩ ባለመሆኑ የቋንቋችንን የጥራት ደረጃ የሚያወርድ የሚያጎል እንጂ እሴት የሚጨምር አለመሆኑን፡፡
መ/ሞክሼ ፊደላት ቢወገዱ የሚከሰቱትን የምሥጢርና የትርጉም መፋለስን፡፡ ሞክሼ ፊደላትንም አባቶቻችን ያለጥቅምና ያለበቂ ምክንያት እንዳልፈጠሯቸው መረዳት አልተቻላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የሞክሼ ፊደላት አጠቃቀም የራሳቸው የሆነ ዶግማዊ አይዶሎጂያዊ ወይም ርእዮተ ዓለማዊ እና መለያዊ ምክንያቶች ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን ፫ ምክንያቶች በምሳሌ እንይ፡- በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ፭ አዕማደ ምሥጢራት አሉ ከእነዚህ ፫ቱ በፊደላት አጠቃቀም የታሠሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ እና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡ ወደ ምሥጢረ ሥላሴ ስንሔድ ፫ ቁጥር በፊደል ሲጻፍ በንጉሡ ሠ ወይም በሠራዊቱ ሠ ሳብዑ ነው፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃልም ሲጻፍ በንጉሡ ሥ ነው፡፡ ሥላሴና ሦስት በአንድ የሠ ቤት መጻፋቸው ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸው የሚለውን ዶግማዊ አስተምህሮ እንዲገልጽና እንዲይዝ በማሰብ ነው፡፡ ከዚህ ወጥቶ ግን በእሳቱ ሳ ቢጻፍ የሚገልጹት ቃል ወይም ትርጉም ሌላ ይሆናል፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌ ሲጻፍም በንጉሡ ወይም በሠራዊቱ ሠ ሳድሱ ነው፡፡ ሥጋ ሲጻፍም በዚያው ሥ ነው፡፡
የዚህ ምክንያቱ ሥጋ በተጻፈበት ሥጋዌ መጻፉ መለኮት ሰው ሆነ ሥጋ ለበሰ የሚለውን ዶግማዊ ምሥጢር እንዲይዝ ታስቦ ነው፡፡ ትንሣኤ ሲጻፍ የሚጻፈው በንጉሡ ሥ ራብዑ ነው፡፡ ትንሣኤ ማለት መነሣት ማለት ነው፡፡ በዚሁ ሣ መጻፉ ቀርቶ በእሳቱ ሳ ቢጻፍ መነሣት የሚለው ትርጉም ይቀርና አከላከል ወይም መከልከል የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ይህም በመሆኑ ምሥጢር ይፋለሳል መባል የተፈለገው ሳይባል መባል ያልተፈለገው ይባላል ማለት ነው፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ ፊደላቱ ቢለዋወጡ ችግር የሚያመጡ ኅቡአት የእግዚአብሔር ስሞች ብዙ አሉ፡፡ ከዶግማዊ ምክንያቶች እነዚህን ካነሣን ይበቃል፡፡ ወደ አይዶሎጂያዊ ወይም ርእዮተ ዓለማዊ ምክንያቶች ስንሔድ ደግሞ ክቧ ዐ ዐይኗ ዐ በመባል ትታወቃለች ዐይን ሲጻፍም የሚጻፈው በዚህችው ዐ ነው፡፡ ዐይኗ ዐ የተባለችበት ምክንያትም የዐይን ቅርጽ በመያዟ ወይም ዐይን በመምሰሏ ምክንያት ነው፡፡ ወደመለያዊ ምክንያት ስንሔድ ደግሞ በአል የሚለው ቃል በአልፋው አ ሲጻፍ አይሁድ ያመልኩት የነበረን ጣዖት ስም ያመለክታል፡፡ በዓይኑ ዐ ራብዑ ሲጻፍ ደግሞ ልዩ ቀን የተከበረ ቀን የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ዓመት የሚለው ቃል በዐይኑ ዐ ራብዑ ሲጻፍ ፲፪ ወራት ከ፭ ወይም ከ፮ ቀናት ማለት ሲሆን አመት የሚለው ቃል በአልፋው አ ሲጻፍ ደግሞ አገልጋይ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ አኅያ ማለት የእግዚአብሔር ኅቡእ ስሙ ነው፡፡ ሲነበብም ላልቶ ነው የሚነበበው አህያ ደግሞ ከእንስሳት አንዱ የበቅሎ አባት ወይም የፈረስ አጎት ማለት ነው፡፡ ሠዓሊ የሚለው ቃል በንጉሡ ሠ እና በዓይኑ ዐ ራብዑ ሲጻፍ ሥዕል የመሣል ሙያ ያለው ማለት ሲሆን ሰአሊ የሚለው ቃል በእሳቱ ሰ እና በአልፋው አ ሲጻፍ ደግሞ ለማኝ፣ ተማጻኝ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ አራት በአልፋው አ ሲጻፍ ከሦስት ቀጥሎ የሚገኝን ቁጥር ሲያመለክት በዐይኑ ዐ ሲጻፍ ደግሞ መኝታ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ሠረቀ የሚለው ቃል በንጉሡ ሠ ሲጻፍ ወጣ፣ ታየ፣ ተገለጠ፣ ብቅ አለ፣ በራ የሚል ትርጉም ሲኖረው በእሳቱ ሰ ሲጻፍ ደግሞ ለበየ፣ ወሰደ፣ አጠፋ፣ ደበቀ፣ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ምሁር የሚለው ቃል በሀሌታው ሀ ሲጻፍ የተማረ ያወቀ የመጠቀ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ በሐመሩሐ ካዕቡ ሲጻፍ ደግሞ ምሕረት ያገኘ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ቃላት አሉ፡፡ እንግዲህ በግልጽ እንደሚታየው አባቶቻችን ይህን ያደረጉበት ወይም ሞክሼ ፊደላትን የፈጠሩበት ምክንያት የቃላት መመሳሰል ሲያጋጥም በፈደላቱ በመለያየት የየራሳቸውን ትርጉም እንዲይዙ እና አሻሚ እንዳይሆኑ ለማድረግ ነው፡፡
የሞክሼ ፊደላት አገልግሎት ይሄ ነው እንጂ ቀድሞ የተለየ ድምፅ ኖሯቸው ያድምፃቸው አሁን ጠፍቶ ወይም ተረስቶ አይደለም ይህ አስተሳሰብ የተለየ ድምፅ ከነበራቸው አሁን ላይ ያ ድምፃቸው ጠፍቷልና ወይም ተረስቷልና ፊደላቱ ጥቅም የላቸውም ማለት ነው ስለዚህም ይወገዱ ለማለት የተፈጠረ ሰበብ ነው፡፡ እውነቱና የፊደላቱ አገልግሎት ግን ከላይ በምሣሌዎች እንዳየናቸው ነው፡፡ ምሁራኑ ግን ፊደላቱ ያላቸውን አገልግሎት እና ቢጐሉ የሚያስከትሉትን ችግር ባለማጤን ወይም ባለማወቅ እንደ ትርፍና አላስፈላጊ ቆጥረዋቸዋል፡፡ እነኚህ ምሁራን በእንደነዚህ ዓይነት ማብራሪያዎች ወገባቸው ሲያዝ አሁን አሁን ደግሞ ምን ማለት ጀምረዋል? እሺ ለግዕዝስ ይሁን ሞክሼ ፊደላት ለአማርኛ ግን አይጠቅሙም እና ከአማርኛ ይወገዱ ማለት ጀምረዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን እንደለመዳቸው አንድ ያልተረዱት ጉዳይ አለ፡፡ እሱም አማርኛ ቋንቋ በራሱ የቆመ ቋንቋ አለመሆኑን ወይም ያለግዕዝ ድጋፍ ቋንቋ ሆኖ ማገልገል የማይችል መሆኑን፣ ከግሶቹ እና ቃላቶቹ የሚበዙቱ ግዕዝ መሆናቸውን አለማወቅ፣ ከግዕዝ ፈጽሞ መነጠል የማይችል ወይም እራሱን የቻለ ቋንቋ አለመሆኑን ያለመረዳታቸው እና በዚህ ምክንያትም የሞክሼ ፊደላቱን አገልግሎት የግዱን የሚጋራ መሆኑን ካለማወቅ የተነሣ ይህንን ሲሉ ይደመጣሉ በአጠቃላይ ችግር ነው ብለው የሚገልጹትና መፍትሔ ነው ብለው የሚያቀርቡት አራምባና ቆቦ እንደሚባለው የማይገናኙ ብቻ ሳይሆኑ በተቃራኒው አቅጣጫ ሲነጉዱ ይታያል፡፡ ከእነዚህኞቹ የተሻሉ ናቸው የተባሉት ፍንድቅ ፊደላትንና የግዕዝ ዲቃላ ፊደላትን ከማስወገድ ይልቅ በምልክት መተካት የሚሉቱ ለእንዲህ አይነት ውሳኔ የዳረጋቸው ምክንያትና ድርጊታቸው ወይም ውሳኔያቸው ፈጽሞ የሚጣጣም አይደለም እነሱ እንዲህ እንዲሆን የፈለጉበትን ምክንያት ሲገልጹ ፊደሎቹ በጣም ከመብዛታቸው የተነሣ ለጀማሪ ፊደል ቆጣሪ የተወሳሰበ አድርጎታል ብለው ሲያበቁ ለመፍትሔአቸውም ሲሉ የፊደላቱን ቁጥር መቀነስ ላይ ብቻ ሲያተኩሩ መወሳሰብን ለማስወገድ ያሉትን የመፍትሔ መንስኤያቸውን እረስተውት ከአርባ በላይ ፊደላትን በወረቀት ላይ ግዘፈ አካል ነስተው የሚታዩና የሚታወቁ የነበሩትን ፊደላትን በአንዲት ምልክት ተክተው የማይታዩ አደረጓቸው ይሄም መሆኑ ጭራሽ እንኳን ለጀማሪ ፊደል ቆጣሪ ይቅርና ፊደል ለለየውም እንኳን ከአርባ በላይ የተለያዩ ድምፆችና የተለያዩ የድምፅ ቅላጼ ወይም ፎኒም ያላቸውን ፊደላት አንድ ምልክትን ከሀ ለ ሐ መ ው ካሉት አምሳያ ፊደሎቻቸው ጋር በማቀናጀትና በመጠቀም ከአርባ በላይ የፍንድቅ ፊደላትንና የግዕዝ ዲቃላ ፍደላትን እንዲፈጥሩ ማድረግ በጣም የተወሳሰበና ከባድ አደናገሪም እዲሆን ማድረጋቸው ጨርሶ ሳይታወቃቸው ቀርቶል፡፡
ልብ በሉ ይህንን ያደረጉት ግን መወሳሰብን ለማስወገድ በሚል ነው፡፡ ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ችግር ነው ብለው የሚያወሩትና መፍትሔ ነው ብለው የሚያቀርቡት ሐሳብ ጨርሶ ባለመጣጣሙ እነዚህ ሰዎች ደኅና የነበረውን መፍትሔ ነው እያሉ ጭራሽ የተወሳሰበ ችግር የሚፈጥሩበት እንዲህ የሚያደርጋቸው ፊደላቱን የሚያስጠላቸው ዐይነ ጥላ ይሆን ያሰኛል፡፡ ወደ ሁለተኛው የፊደል ገበታችን አለበት ወደ አሉት ችግር ስናልፍ ፡-
፪. በሥነ ጽሑፎቻችን ላይ የተዘበራረቀ የፊደላት አጠቃቀም መከሰቱ ላሉት ችግር መፍትሔ ነው ብለው ያቀረቡት ሐሳብ አሁንም ሞክሸ ፊደላትን ማስወገድ የሚል ነው፡፡ በእውነቱ ከሆነ ይሄ የመፍትሔ ሐሳብ ከአንድ ያልተማረ ሰው ቢሰነዘር ኖሮ አይደንቀኝም ነበር ነገር ግን ምሁራን ከተባሉና የችግሮች መፍትሔ መማር ወይም ማወቅ የሕይወት መርሐችን ነው ከሚሉ ሰዎች ግን ይሄ መሰንዘሩ እጅግ የሚያሳዝንና እነርሱንም ለትዝብት የሚዳርግ ነው፡፡ እንደ ምሁር መፍትሔ ሊያደርጉት የሚገባው እስከ አሁንም ድረስ አዋቂዎች ሲያደርጉት እንደቆዩት ሁሉ የፊደላቱን አጠቃቀም በማጥናት እንደሚገለገሉበት ሁሉ መፍትሔው አጠቃቀማቸውን ማጥናት ነው ብለው ይላሉ ብዬ እጠብቅ ነበር በቀላሉ በዚህ መንገድ ችግሩን መፍታት ሲቻል የፊደላቱን አጠቃቀም እንደ ርእሰ ኃይል መጣቅ (Nuclear Science) አክብደው በማየት መፍትሔው መሆን ያለበት ፊደላቱን ማስወገድ አድርገውት ዐረፉ፡፡ ሌላው ቢቀር ፊደላቱ ቅርሶችም ናቸውና ስለ ቅርስነታቸው ብለው እንኳን ሊሳሱላቸው አልቻሉም፡፡ በጣም የሚገርመው እንዲህ ሞክሸ ፊደላት የሚለይላቸው ቃላት በዙሪያችን ከምናውቃቸው ሰወች ስሞች የማይበዙ ወይም የማይበልጡ መሆናቸው ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ከሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እነኝህን ፊደላት የሚለይባቸውን ቃላት ከሚለይባቸው ምክንያት ጋር ሰብስበው በመጽሔት ቢገልጿቸው ይህ ጥያቄ እንዳይነሣ ከማድረግ አኳያ ጥቅሙ ከፍተኛ ነውና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲያስቡበት ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
ወደ ፫ኛው የፊደል ገበታችን አለበት ወዳሉት ችግር ስናልፍ የአናባቢ ወይም የድምፅ ሰጪ ምልክቶች ወጥ አለመሆን ወይም የተዘበራረቁ መሆን ለማጥናት አስቸጋሪ ስላደረገው ወጥና ተመሳሳይ ድምፅ ሰጪ ምልክቶች ለካዕቡ አንድ ዓይነት ለሣልሱ እስከ ሳብዑ ድረስ ለየቤታቸው አንድ አንድ ዓይነት የድምፅ ሰጪ ምልክቶች መኖር አለበት የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰው በፊደሎቻችን ላይም እንዳሉት የቅርጽ ለውጥ አድርገውባቸው ለማሳየት ሞከሩ፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ የተቀየረው የፊደል ገበታ ጭራሹን በችግር የተሞላ ሆኖ ይታያል፡፡
አባቶቻችን ምሁራኑ እንዳሉት ለየፊደላት ቤቶች ወጥና አንድ ዓይነት የድምፅ ሰጪ ምልክት እንዳያደርጉ ያደረጋቸው እና ፊደላቱን አሁን ባሉበት ሁኔታ የቀረጹበት ምክንያቶች ወይም መለኪያዎች መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሀ.ፊደላቱን ለመጻፍ ከሚጠይቁት የቦታና የጊዜ ፍጆታ ቁጠባ አንፃር ለምሳሌ ሃ፣ ላ፣ ሓ፣ሳ፣ሻ፣ባ፣ኣ፣ካ፣ኻ፣ዛ፣ዣ፣ጣ፣ጳ፣ጻ ወ.ዘ.ተ እንደ እነ ቃ፣ታ፣ቻ፣ያ፣ጋ፣እና ፓ ግራ እግራቸውን ወይም ቀኝ እግራቸውን ወደ ግራ በማጠፍ የራብዕ ድምፅ ቤት እንዲፈጥሩ ያላደረጉበት ምክንያት አሁን ካሉበት ሌላ ተጨማሪ የቦታ ፍጆታ እንዲወስዱ ስለሚያደርጋቸውና ያ ደግሞ እነሱን ለመጻፍ ተጨማሪ የጊዜ ፍጆታ እንዲጠይቁ ስለሚያደርጋቸው ይህ እንዲሆን ደግሞ ስላልተፈለገ፡፡
ለ.ውበታቸውን ከመጠበቅ አንፃር ለምሳሌ ከላይ በእነ ሃ፣ላ፣ ሓ፣ሳ፣…ተርታ የተጠቀሱት ፊደላት ከእነሱ በታች እንደተጠቀሱት ማለትም እንደነ ቃ፣ታ፣ቻ፣…የግራ ወይም የቀኝ እግራቸውን ወደ ግራ በማጠፍ የራብዕ ድምፅ እንዲፈጥሩ ያላደረጉበት ምክንያት አሁን ካሉበት የሚያምር ቅልብጭ፣ ቅልጥፍ፣ ቅልል ያለው አካላቸው ተበላሽቶ ኮተታም የሚያደርጋቸውና ውበታቸውን የሚያበላሽ ሆኖ ስላገኙት፡፡
ሐ.የእራሳችንን ብዙ አማራጮች የመፍጠር ክህሎትን ወይም ችሎታን ከማሳየትና የዚህም ባለቤቶች መሆናችንን ከማሳየት አንፃር፣
መ.ፊደሎቻችን ያላቸውን አካለ ሰለጣዊ ወይም ጅምናስቲካዊ የመተጣጠፍ ተፈጥሯአዊ ክህሎት ወይም ችሎታቸውን እምን ድረስ እንደሆነ ከማሳየት አንፃር፣
ሠ.መመሳሰልን ከማስወገድ አንፃር ለምሳሌ የኮ፣ ጎ፣ ቆ እና ኆ ከጐናቸው እዝል ወይም ቀለበት በማድረግ የሳብዕ ድምፅ እንዲፈጥሩ ያልተደረገበት ምክንያት ከግዕዝ ዲቃላ ፊደላት ከሚባሉት ፊደላት ጋር የሚመሳሰሉ ሆነው በመገኘታቸው ምክንያት የተለየ የሳብዕ ድምፅ የሚፈጥር ምልክት እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡
እናም አባቶቻችን እነዚህን ፭ መለኪያዎች እያዩና እየለኩ እየመዘኑ ፊደላቱን በምናውቃቸው መልኩ ሊቀርጿቸው ችለዋል፡፡ ምሁራኑ ግን እነኚህን ቁምነገሮች ሳያውቁ ትዝብት ላይ ሊጥላቸው ከሚችል ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ቻሉ፡፡ በአማራጭነት ያቀረቧቸው የተለያዩ የፊደል ገበታዎችም ካሏቸው ችግሮች የተነሣ ዓይን የሚስቡ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ለምሳሌ ለውጥ የተደረገበትን የፊደላቱን የራብዑን ቤት ስናይ ሁሉም ፊደሎች ልክ እንደ ቀ፣ ተ፣ ቸ፣ የ፣ ገ እና ፐ ቤቶች እግሮቻቸውን ወደግራ በማጠፍ የራብዕ ድምፅ መፍጠር አለባቸው ብለው በመነሣታቸው ፊደሎቹ በነባሩ የፊደል ገበታ ሲጻፉ ይወስዱ ከነበረበት ቦታ እንደገና ሌላ ተጨማሪ የቦታ ፍጆታ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ደግሞ በፊት እነሱን ለመጻፍ ይጠይቁ ከነበረው የጊዜ ፍጆታ ተጨማሪ የጊዜ ፍጆታ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል፡፡
ከውበት አንፃር ሲታዩም ደግሞ ከነበራቸው አካልና መልክ ተጨማሪ ጭረት እንዲሸከሙ በመደረጋቸው ጭረት የበዛባቸውና ቡቱቷም፣ ተመሳሳይ ከመሆናቸው አንፃርም አሰልቺ አድርጓቸዋል፡፡ አባቶቻችን ያሳዩትን ብዙ አማራጭ የመፍጠር ችሎታንም ጠርጐ በማስወገድ ፊደሎቹ በሙሉ በየቤታቸው ተመሳሳይ በመሆናቸው ፊደላቱ በነባሩ የፊደል ገበታ ላይ የነበራቸውን አጫዋችነትንና አመራማሪነትን እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡ የተለያዩ አካለ ሰለጣዊ ወይም ጅምናስቲካዊ የመተጣጠፍ ችሎታቸውንም አስወግዶ አቅመ ደካማ ውሱንና የተቀየዱ አድርጓቸዋል፡፡ በነዚህም ምክንያቶች እንኳን ለመገልገል ለማየትም ትዕግስትን የሚፈታተን የፊደል ገበታ ሊሆንባቸው ችሏል፡፡ በተለይም ደግሞ አንድ የሳቱት ትልቅ ቁምነገር ቢኖር እነኚህ እነሱ አሻሻልን ካሏቸው ሁለት ሦስት የፊደል ገበታዎች አንዱ በአገልግሎት ላይ ቢውል ከዚህ በፊት በነባሮቹ ፊደሎቻችን በተጻፉት የሀገራችን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶቻችን እና መጻሕፍት ላይ ሞት መፍረድ ወይም ተደራሽ ተነባቢ እንዳይሆኑ ማድረጋቸው እንደሆነ የተረዱት አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ቀጣዩ ትውልድ እነዚህ የሥነ-ጽሑፍ ቅርሶቻችን የተጻፉበትን ፊደል የማያውቅ ይሆናል እና፡፡ በአጠቃላይ ቋንቋችን ሲላቢካዊ ወይም አቡጊዳዊ መሆኑ እንደላቲኑ አልፋቤቲካዊ ወይም ተናጠላዊ አለመሆኑ ከብዙ ዓይነት ጣጣዎች እንዲድን አድርጐታል፡፡
ለምሳሌም እንግሊዝኛ ቋንቋ አልፋቤቲካዊ ወይም ተናጠላዊ በመሆኑ እንደእኛ ሲላቢካዊ ወይም አቡጊዳዊ ባለመሆኑ ማለትም አናባቢንና ተነባቢን በተከታታይ በመደርደር የሚጻፍ በመሆኑ ለአላስፈላጊ የገንዘብና የጊዜ ብክነትና ኪሣራ እንዲዳረጉ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ ይህንኑ Alphabetical የሚለውን ቃል በላቲን ፊደላት ሲጻፍ ፲፪ ፊደላትን ማስፈር ግዴታ ነው፡፡ ነገር ግን የላቲኑን ትተው ማለትም አንዲትን ድምፅ ለመግለጽ ከሁለት እስከ አራት ፊደላትን መደርደር የሚገደደውን አጻጻፍ ትተው በእኛው ሲላቢካዊ ወይም አቡጊዳዊ በሆነው ማለትም አናባቢንና ተነባቢን በአንዲት ፊደል ብቻ በሚገልጸው ፊደላችን ቢጽፉት ፯ ፊደላት ብቻ በማስፈር ማለት የፈለጉትን ቃል መግለጽ በቻሉ ነበር፡፡
ብዙዎች ቃላቶቻቸው በነሱ አጻጻፍ ሲጻፉ የሚዎስዷቸው የፊደላት ብዛት በኛ ሲጽፉት ከግማሽ በታች የፊደላት ብዛት መግለጽ የሚቻሉ ናቸው ፡፡ ሌላም አንዲት አጭር ቃል ብናይ thickness የሚለው ቃል በላቲኑ ሲጻፍ ፱ቃላትን ማስፈር ግዴታ ነው፡፡ በእኛ ፊደላት ሲጻፍ ግን ፬ ፊደላትን ብቻ በማስፈር የ፭ቱን ፊደላት ቦታ በማትረፍ ማለት የተፈለገውን ቃል ማስፈር እና መቆጠብ በቻሉ ነበር፡፡ ይህም ማለት ከግማሽ በላይ የሆነ ኪሳራን ማስወገድ ወይም ፍጆታን ማዳን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ገምቱት ከዚህች አንዲት ቃል ብቻ የአምስት ፊደላትን ቦታ ማትረፍ ከተቻለ ከመጽሐፍ ሲሆን ደግሞ አስቡት ከግማሽ ላላነሰ ለገንዘብ ለጊዜ እና ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ብክነት ተዳርገዋል ማለት ነው፡፡ በ፶ገጽ ማለቅ የሚችለው መጽሐፍ በ፻ እና ከዚያም በላይ ገጾች እንዲያልቅ ይገደዳሉ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም በላቲኑ የአጻጻፍ ዘዴ አንድ ፊደል ሁለትና ከዚያ በላይ የተለያዩ ድምፆችን እንዲወክል በመደረጉ የቋንቋውን ባለቤቶች ሳይቀር አገልግሎት ላይ ሲቸገሩ በየፊልማቸው(በየምትርኢታቸው) ከአስቂኝ ሁኔታዎች ጋር ሲቸገሩ የሚገልጹትና የምናስተውለው ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ G ፊደል ከአናባቢዎች ጋር በመሆን እንደ ጀ፣ ጃ፣ ገ፣ ጉ፣ ጊ፣ ጋ፣ ግ፣ ጎ እንዲነበብ መደረጉ፡፡ C ፊደል ከአናባቢዎች ጋር በመሆን እንደ ሰ፣ ሳ፣ ሴ፣ ከ፣ ኩ፣ ካ፣ ክ እና ኮ እንድትነበብ፡፡ U ደግሞ እንደ አ፣ ኡ፣ ዩ እንድትነበብ በመደረጉ ሌሎችም እንደዚያው፡፡ በተጨማሪም ተጽፈው ሲያበቁ የማይነበቡ ወይም ሳይለንት ፊደላት መኖር ይሄንን እንዲደርጉ ያስገደዳቸው ደግሞ እንደኛ ሞክሼ ፊደላት ስለሌሏቸውና የቃላት መሳሰል ሲፈጠር ለመለያየት ከፊቱ ወይም ከመሀሉ ሌላ ባዕድ ፊደል ይደነቅሩበታል፡፡ ለምሳሌ rite እና write ሲነበቡ ሁለቱም ራይት ተብለው ነው የሚነበቡት ሲጻፉ ግን የግድ አንዱን ከሌላው ለመለየት ከድምፁ ውጪ ባዕድ ቃል እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም አንዳች ነገር ለመጻፍ በፈለጉ ጊዜ እራሳቸው ተወላጆቹ መዝገበ ቃላትን ጨብጠው ካልሆኑ በስተቀር የማይሆን መሆኑ፡፡ እንግዲህ ከእነዚህና ከሌሎችም ጣጣዎች ሁሉ የእኛ ቋንቋ የተረፈው ወይም የዳነው ቋንቋችን ፎነቲክ እንዲሆን ወይም ለእያንዳንዷ ድምፅ የየራሱ ፊደል እንዲኖረው በመደረጉና አቡጊዳዊ ወይም ሲላቢካዊ በመሆኑ ነውና የፊደላቱ መበርከት ለጥቅምና በአጥጋቢ ምክንያት የተደገፈ በመሆኑ ምሁራኑ እንደሚሉት ለማታከት እንዳልሆነ ተረድተው ይህንን ያደረገልንን አምላክና ምክንያት የሆኑትን አባቶቻችንን ማመስገን ይኖርባቸዋል ብዬ እመክራለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እግዚአብሔር ይመስገንና የአባቶቻችንን ድካም በሚገባ የተረዱ ብዙ ምሁራንም አሉን፡፡
ቅሬታ ያለባቸው ምሁራንም ቢሆኑ ሁሉም ያነሧቸው ነጥቦች ሁሉም ውድቆች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ትክክለኛ የሆኑ
ቅሬታም እንዳላቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌ በጽሑፍ ላይ የሚጠብቀውና የሚላላውን የሚለዩ ምልክቶች ስለሌሉ ብዙ ቃላት በአነባበብ ሒደት ላይ አሻሚ ሲሆኑ እንደ አውዳቸው (Contextually) እንድናያቸው ሲያደርጉን ይታያሉ በሚል ያነሱት ቅሬታ ትክክል ነው፡፡ ከሌላ ቦታ ሌላ ምልክት ማምጣት ወይም መፍጠር ሳያስፈልገንም ቅዱስ ያሬድ ለዜማ ምልክትነት የፈጠራቸውን ምልክቶችን በመጠቀም ይህንን ችግር መቅረፍ ይቻላል ይኖርብናልም፡፡ መላው ዓለም የቅዱስ ያሬድን የዜማ ምልክቶች በመውሰድ ለየቋንቋቸው በሥርዓተ ነጥብነትና በድምፅ ምልክትነት እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እድሜ ለ ኪነብጀታ (Technology) የተለያዩ ድረ ገጾችን ስናይ ምን ያህል እንደተዘረፍን ተገንዝበናል፡፡ እናም የፊደል ገበታችን ከሌሎች ቋንቋዎች አንጻር ሲታይ የጎላ አይደለም እንጅ የራሱ ውስንነት እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው እኔ ከነበረው የሚጨመሩና ያለበትን ውስንነት የሚቀርፉ ከነትርፉ 182 አዳዲስ ፊደላትን፣ በመላው ዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝለትና የምዕራባዊያኑን የመጨረሻ ስም ያለው ቁጥር ጎግልፕሌክሲያን (ዐሥር ሽ ዚሮ ወይም ባዶ ያለውን) ስምንት መቶ ሽህ ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ ቁጥርና የቁጥር ስሞች ሠራዊት፣ እንዲሁም ዓለም አሁን እየሠራበት ያለው “የዓረብ ቁጥር” በጣም ለማጭበርበር የተመቸና ዓለም እየተቸገረ ያለ በመሆኑ ፈጽሞ ሊጭበረበሩ የማይችሉ ቁጥሮችን የፈለሰፍኩት፡፡ ለማየት ይሄን ይጫኑ፡፡
ዕንቁ መጽሔት ቅጽ 4 ቁጥር 67 ግንቦት 2004 ዓ.ም.
ናሆም አሰግድ says
ትሰክክል ነህ ከዚ በተጨማሪ ፊደላት የቃላት ፍቺ ልዩነቶችን ያመጣሉ ፈጽሞ ሊቀየሩ አይገባም ሊጠኑ ነው የሚገባው
Abraham says
ቋንቋ የህዝብ እንጂ የቤተ ክርስትያን ሆኖ ያቃል እንዴ?
bayya yekideyea says
ፈጣሪዋ እኮ ቤትክርስቲያን ወይም አባቶቹዋ ናቸው