ከክሮሺያ እና ከቦስኒያ ጋር በሁለት ጦርነቶች ተሸንፎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያደቀቀው የሚሎሶቪች መንግስት በህዝቡ ዘንድ ይሁንታን ባጣበት ሁኔታ ላይ እያለ እ.አ.አ በ1996 ዓ.ም በተካሄደው የክልል ከተሞች ምርጫ በስርቢያ አጠራር ዛየኖ ወይም ቱጌዘር የተሰኘው ፓርቲ በ40 የክልል ከተሞች ውስጥ ማሸነፍ ችሎ ነበር። ሚሎሶቪች ግን ለምርጫ ቦርዳቸው ውጤቱን እንዳያጸድቅ ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፉ። በዚህም ሳቢያ ተማሪዎች ለ55 ቀናት እለት በእለት ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ተቃውሞ የመንግስት ተወካይ ከተማሪዎች ተወካይ ጋር ባደረጉት ስምምነት ለዛየኖ ወይም ቱጌዘር ለተባለው ፓርቲ በማን አለብኝነት ተነፍጎ የነበረውን 40 መቀመጫዎች መልሶ ማግኘት ቻለ።
በተገኘው ድል መጠነኛ የስነልቦና ጥንካሬን ያገኙት እኚሁ ሰልፈኛ ተማሪዎች ለሚሎሶቪች ውድቀት ዋና ተዋናይ ለሆነው ኦትፖር ለተሰኘው ድርጅት መፈጠር መሰረት ጣሉ። የሰርቢያው ፕሬዝዳንት ሚሎሶቪች እራሳቸውን በስልጣን ለማቆየት በርካታ አረመኔያዊ ተግባራት እንደፈጸሙ ይነገራል። ከዚህም መካከል ሀገሪትዋን ከሁለቱ ጎረቤት ሀገራት እና ከኔቶ ጋር አላስፈላጊ የሆነ ጦርነት መግጠማቸው ለብዙሃን ዜጎች እልቂት ምክንያት እንደሆኑም ይታወቃል። በተጨማሪም የስራ አጡ ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ በደረሰበት ሁኔታ ስለ ህዝብ ከመጨነቅ ይልቅ ከባድ የሆነ ህዝባቸውን የመጨቆኛ ዘዴ ላይ ጊዜ እና ገንዘባቸውን መስጠታቸው ይነገራል።
እ.አ.አ በ1998 ዓ.ም የሰርቢያ ተማሪዎች አምባገነኑን የስሎቦዳን ሚሎስቪች ስርዓት በሰርቢያ አጠራር ‘’ኦትፖር’’ ወይም በእንግሊዝኛው ሬዝስታንስ የሚል ድርጅት አቋቋሙ። ኦትፖር በተቋቋመ በ2 አመቱ በርካታ የትግል ዘዴዎችን በመንደፍ እራሱን በሀገሪቱ ላይ አንሰራፍቶ የቆመውን የሚሎሶቪችን ስርዓት በ2000 ዓ.ም ከስልጣን አውርዶ ሄግ ለሚገኘው አለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱን አሳልፎ መስጠቱ ይታወቃል።
ኦትፖር በመጀመሪያ ሲቋቋም በ1998 ዓ.ም በቤልግሬድ ዩኒቨርስቲ የነበረውን የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ለማድረግ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማስከበር ነበር። ብዙም ሳይቆይ እቅዱን በኣዲስ በመንደፍ ትኩረቱን ወደ ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች አዞረ! የነደፉት እቅድም በተሳካ ሁኔታ ሚሎሶቪችን ከስልጣን ሊያወርድ ቻለ። ስልታዊ አተገባበሩም ቅድሚያ የሰጠው በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ላይ ለውጥ ለማምጣት አንደነበር ይነገራል። በወቅቱ ከነበሩት ስራጃ ፖፖቪች የተባለው አንደኛው የንቅናቄው መስራች እንዳስቀመጠው ፍላጎታችን በህዝቡ ላይ የፖለቲካ ንቃትን መፍጠር ነበር ሲል ተናግሯል።
በሴፕተምበር 24 2000 ዓ.ም በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ የስሎቦዳን ሚሎሶቪች መንግስት በህዝብ ድምጽ የተሸነፈ ቢሆንም ስልጣን እንደማይለቅ አስታወቀ። የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽኑም የተቃዋሚ ቡድኑን አሸናፊነት እንደማይቀበል ገለጸ ። በዚህ ጊዜ በተቃዋሚ ጎራ የመሪነት ስልጣኑን በያዙት ቮጅስላቭ ኮስቱኒካ እና በሚሎሶቪች መካከል ከባድ ፍጥጫ ነገሰ። በወቅቱ የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ የነበሩት ፓቭለ ከህዝብ ጋር በመቆም ሚሎሶቪች ስልጣኑን እንዲለቅ ቢያግባቡትም በጄ አልል አለ። ይህን ተከትሎ በቤልግሬድ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ የተቃዋሚ መሪው ኮስቱኒካ የመንግስት ፖሊስ ሃይሎች ህዝቡን እንዳይጎዱ፣ የሚድያ ሰዎችም አድማ እንዲመቱ ፣ በኮሉባራ በምትባል ከተማ የስርቢያን ግማሽ ያህል የኤሌክትሪክ ፍጆታ በሚሸፍነው የከሰል ማእድን ቦታ ተሰማርተው የሚገኙ ሰራተኞችም የስራ ማቆም አድማ እንዲመቱ ኣሳመኑ።
በኦክቶበር 2፣ 2000 ዓ.ም በአጠቃላይ የሀገሪቱ ግዛቶች የሚሎሶቪችን መንግስት ለማሽመድመድ አድማ የተመታ ቢሆንም በመጀመሪያው አካባቢ በሰርቢያ ርእሰ መዲናዋ ቤልግሬድ ውስጥ ውጤታማ መሆን አልቻለም ነበር። ነገር ግን በሌሎች ከተሞች እና አውራጃዎች ከፍተኛ የሆነ መንገዶችን በአውቶሞቢሎች፣ በአውቶብሶች፣ በከባድ መኪናዎች እና በህዝብ በመዝጋት እንዲሁም የግብይት ስፍራዎች እና ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ መንግስቱን አዳከሙ።
በኦክቶበር 5 በአድማው የተዳከመውን መንግስት የነውጥ አልባ ሰልፈኞች ቤልግሬድ ከተማን ወረው በመያዝ ደረታቸውን ነፍተው የሚሎሶቪችን ከስልጣን የመውረጃ ቀን ቆርጠው አሳወቁ። መንግስትን የሚጠብቁ ተሽከርካሪዎች ከተማዋን አጨናንቀው እና እንዲሁም የሰልፈኛውን አንቅስቃሴ የሚገታ አጥር በመንግስት ጠባቂዎች ተሰርቶ ነበር። በዚህ ጊዜ የተወሰኑ የሰልፉ አባላት በመንግስት ጠባቂዎች የተሰራውን አጥር በቡልዶዘር አፈራረሱት። ቀጥሎም የፓርላማውን ህንጻ እና የሰርቢያ ብሄራዊ የራድዮ እና የቴሌቭዥን ማሰራጫዎች በነውጥ አልባ ሰልፈኞች ተከበበ። የነውጥ አልባ ንቅናቄው መሪዎች ከመንግስት ልዩ የፖሊስ ሀይላት ጋር መግባባትን መስርተው የቆዩ በመሆኑ ከበላይ አካል ይመጣ የነበረውን በሰልፈኞቹ ላይ እርምጃ ይወሰድ የሚል ትእዛዝ ተፈጻሚ አያደርጉም ነበር። በስተመጨረሻም የማእከላዊ ፖሊስ እዝ መምሪያው ሙሉ በሙሉ በሰልፈኞች እጅ ወደቀ። አምባገነኑ የሚሎሶቪች ስርዓትም እዚህ ጋር አበቃለት። ቀደም ብሎ በተደረገው ምርጫም አሸናፊነታቸው የተገለጸው የቃዋሚው መሪ ኮስቱኒካ አዲሱ የሀገሪቱ 4ኛ ፕሬዝዳንት በመሆን ኦክቶበር 7፣ 2000 ዓ.ም ቃለ መሃላቸውን ፈጸሙ።
ወደ ሀገራችን ስንመለስ ሚሎሶቪች እና የቅርብ ዘመዶቻቸው የሰርቢያ ፈላጭ ቆራጭ እንደሆኑት ሁሉ ኢትዮጵያችን በጥቂት የህወሃት ባለስልጣናት ፈላጭ ቆራጭነት ስር ትገኛለች። ገዥው ቡድን እስካሁን በስልጣን የቆየበትን ያህል አልፍ ሀገራዊ በደሎችን ፈጽሟል። የህዝብ እሮሮ በጥይት አረር ታፍኗል። በሀገራችን ኣቆጣጠር በ1997 በተደረገው ብሄራዊ ምርጫ የህዝብ ድምጽ በሀይል ተነጥቋል። የበርካታ የሁለቱን ሀገራት ወጣቶች ህይወት የቀጠፈው የዘመቻ ጸሃይ ግባት ጦርነት በወጣት ደም ላይ የተቆመረ ክፉ ቁማር ነበር። እንዲሁም እስካሁን ድረስ አላስፈላጊ በሆነ ጦርነት በሶማሊያ ምን ያህል ወጣቶች ህይወት እንደተገበረ ቤት ይቁጠር። ስራ አጥነት፣ ረሃብ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ስደት በነገሰባት ሀገራችን መልካም አስተዳደርን አስፍኖ ህዝብን ከመታደግ ይልቅ መንግስት የመረጠው የተለያዩ የመጫወቻ ካርዶችን እየሳበ ህዝብን ረግጦ በመግዛት የስልጣን እድሜውን ማራዘም ብቻ ነው።
ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ፣ የህግ የበላይነትን ፣ ፍትህ እና ደሞክራሲን ለማስፈን እኛስ በሀገራችን “ኦትፖር’’ አያስፈልገንምን? በጥቂቱ የሰርቢያን ነውጥ አልባ ትግል ካየን ብዙ መማር እንችላለን የሚል ግምት አለኝ። እራሱን መንግስት ብሎ የሚጠራው ቡድን የተቃወመውንና የተቸውን ሁሉ አሸባሪ የሚል ታፔላ እየለጠፈ የሰላማዊ ተቃውሞ መንገዶችን በሙሉ ዘግቷል። ብሶት የወለደው የአሁኑ የህዝብ እንቅስቃሴ ብዙ ሊያስኬድ የሚችል ሆኖ ሳለ ቅንጅት በማጣቱ ብዙ ዋጋን አስከፍሏል። ውጤቱ መንግስትን ማስደንገጡ ባይካድም በለመደው ጥያቄ ማስቀየሻ (ጆሮ ኣደንቋሪ) ፕሮፓጋንዳ አንዴ ማስተር ፕላኑ በረቂቅ ደረጃ ላይ ነው፣ አንዴ ደግሞ ለሚድያ በማይመጥን ቋንቋ ጠንቋዮች የጠሩት ጋኔል በመኖሩ ነው አንጂ ነገሩ ይሄን ያህል የሚካበድ ኣልነበረም፣ ኣልፎ ኣልፎ ደግሞ በህበረተሰቡ ውስጥ በቂ የግንዛቤ ስራ ባለመሰራቱ ነው፣ በሌላ ግዜ ደግሞ በማስተር ፕላኑ ፕሮጀክት ስም የሚንቀሳቀሱ ህገ ወጦች በመኖራቸው ነው፤ ካሉበት ኣድነን ለጥያቄም አናቀርባለን ወ.ዘ.ተ። አንግዲህ….. የህዝብ ደም ላይ ነው አንዲህ የተቀለደው። ብቻ!! ወያኔ የሚይዘው የሚጨብጠው ሲጠፋው ተስተውሏል። በሰርቢያ ግን አንዲት ደም ጠብ ሳትል በተቀናጀ መልኩ የነውጥ አልባ ትግል ስልቶችን በመጠቀም አምባገነን መንግስታቸውን ድል ነስተዋል። ይህም የሆነው በቅንጅት የትግል ስልቶችን በመተግበራቸው ነው!
አዲስ አበባን በዙሪያዋ ከሚገኙ የኦሮሚያ ክልል መሬቶች ጋር በማስተር ፕላን ስም በማጣመር ነዋሪውን ህዝብ አፈናቅሎ የህወሃት ሹማምንቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሴራ በገዥው ቡድን በመጠንሰሱ የዛሬ አመት ገደማ ወደ 78 ንጹሃን ዜጎችን በመንግስት ታጣቂ ሃይሎች ለህልፈት መዳረጉ ይታወሳል። የዛሬ ወር ገደማ ጀምሮ ከ80 በላይ የሚሆኑ ህጻናት ፣ ወጣት ተማሪዎች እና እናቶች በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ከወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተቀጥፈዋል ግድያው ኣሁንም አየቀጠለ አንደሆነም ይታወቃል። ይህም ማለት እስካሁን ያለው የጭቆና አገዛዝ መላውን ኢትዮጵያዊ እረፍት የነሳ ቢሆንም ይህ ማስተር ፕላን የመጨረሻ የህልውና ጥያቄ በመሆኑ ህዝብም ከመሬቱ አስቀድሞ ደረቱን የሰጠበትን ሁኔታ እንድናይ አድርጎናል። እንዲሁም በተጨማሪ ነዋይ ያወረው የህወሃት ጉጅሌ ከኢትዮጵያ ሰሜን ምእራብ ክፍል መሬት ቆርጠው ለሱዳን ለመግጠም በዲሰምበር 2015 ከሱዳን መንግስት ተወካዮች ጋር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተከትሎ ከአያት ቅድመ አያት መሬቱ በፊት ደረቱን ለጥይት አረር የሰጠበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል። (ህዝቡ መፈናፈኛ ሲያሳጣቸው ይህን ጉዳይ መንግስት የካደው ቢሆንም ሱዳን ትሪቢዩን በኖቨምበር 23 2015 እትሙ መዘገቡ ይታወሳል)። የሆነው ሆኖ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ ግን ቀደም ብሎ ጭቆናው አንገሽግሾት የቆየ ህዝብ እንዳለ እና እንዲህ በአንድ የሚያነሳው አጋጣሚ ይፈልግ እንደነበር ሁኔታዎች አስረድተዋል። ነገር ግን ህዝባዊ አመጹን በአንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ቅንጅት ይጎድለው ነበር ለማለት ያስችላል።
ቅንጅቱ ሲኖር ደግሞ በቅድሚያ ከየትኛውም ተቃውሞ ሰልፍ በፊት መጠነ ሰፊ የማደራጀት ስራ በህቡዕ ሊሰራ ይገባዋል። በዚህም መሰረት አንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ህብረተሰብ ሲነካ ለሌላውም ጉዳዩ እንደሆነ ማሳመን አንዱ ይሆናል ።ለምሳሌ የሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ሲነሳ መላው ኢትዮጵያዊ ነግ በኔ ብሎ ከሙስሊሙ ጎን እንዲቆም፣ የማስተር ፕላኑ ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን፣ በስሜን ምእራብ ኢትዮጵያ በድንበር ማካለል ስም ለሱዳን ሊሰጥ የታሰበው ለም መሬት ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆን አንዲችል ህዝቡ መሃል ከፍተኛ መናበብ አንዲኖር ግድ ይላል። በዚህ ጊዜ መንግስት ከፋፍሎ መርገጥ ይሳነዋል። በተጨማሪም ወታደሩም፣ የእምነት አባቶችም፣ የሚድያ ሰዎችም መብቱን ከተነፈገው ህዝብ ጋር ይቆሙ ዘንድ በህቡዕ የተደራጀ ቅንጅትን ስራን ይፈልጋል። ህዝብ አንድ ከሆነ ህወሃት ኢምንት ይሆናል። ምንም አይነት የመጨቆኛ በር አይኖረውም። አመሰግናለሁ !
በግፍ ለተገደሉት እህትና ወንድሞቸ ነፍስ ይማር ፣ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናት ይስጥልን ! ድል ለጭቁኑ ህዝብ !
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply