“የዋዜማ አቋም እና ጥሪ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ” በሚል ርዕስ የዋዜማ ሬዲዮ ይፋ ያደረገውን መግለጫ የጎልጉል ኤዲቶሪያል ቡድን ተወያይቶበታል፡፡ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ከተቋቋመበት ዓላማና ከሚከተለው የአስተሳሰብ መስመር አንጻር የዋዜማ መልዕክት አብሮት የሚሄድ በመሆኑ የቀረበውን ወቅታዊ ጥሪ ከነሙሉ ዓላማ ከዚህ በታች አትመናል፤ በቀጣይ ለሚደረጉ ሥራዎችም እንደ ሚዲያ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች መሆናችንን እና ሌሎችም በተመሳሳይ ተግባር ላይ ያላቸውን ትብብር እንዲያሳዩ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበት ፖለቲካዊ ቀውስ ከወትሮው በተለየ አስጊና አስከፊ አደጋን ያረገዘ ሆኖ ይታያል። የፖለቲካ ቀውሱን “የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዴሞክራሲ አለመዳበር” እያሉ መግለጽ ከፊታችን የተደቀነውን አደጋ አቅልሎና የተለመደ አስመስሎ የሚያቀርብ አሳሳች መነሻ ነው። ምክንያቱም፣ ስለ መልካም አስተዳደርም ሆነ ስለዴሞክራሲ መዳበር ለመነጋገር በቅድሚያ መሟላት የሚገባቸው ነገሮች ስላሉ ነው። እነርሱም በሰላም የምትኖር አገር፣ ቢያንስ በሕይወት የመኖርና መሠረታዊ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የማድረግ መብታቸው የተከበረላቸው ዜጎች፣ እና እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚችል አስተዳደር ናቸው። በአሁኑ ወቅት እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ከመቼውም ጊዜ በባሰ መልኩ ከአገሪቱ እየጠፉ ነው ወይም ጠፍተዋል።
አገሪቱ አሁን ያለችበትን አደገኛ ሁኔታ በአጭሩ ለመግለጽ፣
ሀ. መንግሥት በመላ አገሪቱ ዜጎች ዘንድ ያለው ሕጋዊ ተቀባይነትና ታማኝነት ወትሮም ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ወርዶ ፈጽሞ ተሸርሽሯል፤
ለ. ገዢው ድርጅት (ህወሓት/ኢሕአዴግ) እና የሚመራው መንግሥት የአገሪቱን ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፣ ጥያቄዎች፣ አማራጭ መፍትሔዎችን እና ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ለመረዳት አልቻሉም። መንግሥት ዝቅተኛ የሚባለውን አቀራራቢ የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ እንኳን አቅምም ሆነ ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳለው የሚጠቁም ምልክት ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።
ሐ. ቅሬታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ በሚሞክሩ ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መወሰዱ በስፋት ቀጥሏል። በዚህም በርካታ ወገኖች እየተገድሉ ነው። ሌሎች ደግሞ መታሰራቸው፣ መደብደባቸው፣ ለስቃይ መዳረጋቸው እንደቀጠለ ነው። ይህ ሁኔታ በፍጥነት ካልቆመ በብዙዎች ዘንድ አደገኛ እልህና ቂም መፍጠሩ አይቀርም።
መ. መንግሥት በሚከተለው ሁሉንም ድምጾች በጉልበት የማፈን አካሄድ የተነሣ የፖለቲካ ምህዳሩ ጨርሶ ተዘግቷል። ቁጥሩ በፍጥነት እየጨመረ የሚገኝ ሕዝብ በመንግሥትና በሰላማዊ ትግል ተስፋ እየቆረጠ ነው። ይህ ወዴት እንደሚጎትተን የቅርብ ጊዜ ታሪካችን አስተማሪ በሆነን ነበር።
ሠ. የብሔረሰቦችን ማንነትና መብት በማስከበር ስም በአገራችን ሕዝቦች መካከል ሲዘራ የሰነበተው የእርስ በርስ መጠራጠር፣ በመንግሥት በራሱና በሌሎችም ቡድኖች ቀስቃሽነት እጅግ ተባብሷል። የትብብርና የመተማመን ምልክቶች አሁንም አሉ ማኅበራዊና ባህላዊ ትስስሮች አልጠፉም። ሆኖም አሁን በሚገኙበት ሁኔታ ለጋራ የፖለቲካ መፍትሔ የሚያበቁ መሆናቸው የሚፈተንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ረ. በተለይ በማወቅም ባለማወቅም የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ የተገለለ ሆኖ እንዲታይ የሚያደረግ አደገኛ ቅስቀሳ ይታያል። የዚህ መነሻ በዋናነት የህወሓት አመራር ተግባርና ፕሮፓጋንዳ ቢሆንም፣ ሌሎችም እሳት ላይ ነዳጅ መጨመሩን ተያይዘውታል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ የብሔሩ ተወላጆች ከሁለት ያጣ መስለው በፍርሃት ተሸብበው ይታያሉ። የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦችና የፖለቲካ ልሂቃን እንዳይተማመኑ የሚደረገው ሙከራም ቀጥሏል። እነዚህን መዘዘኛ አዝማሚያዎች በጋራ መቀልበስ ይኖርብናል።
ሰ. ህወሓት/ኢሕአዴግ የአገሪቱን ተጨባጭ ፖለቲካዊ እውነታ ከመካድ አዙሪት ወጥቶ እውነታውን ሊጋፈጥ አልቻለም። እውቅና ላልሰጠው ችግር መፍትሔ ያመጣል ብሎ መጠበቅ ቂልነት ይሆናል። ድርጅቱ አገሪቱን በጊዜ ከጥፋት ለመታደግ ወደሚያስችል እውነተኛ የፖለቲካ ድርድር እንዲመጣ መገፋትና መገደድ እንዳለበት የሚያከራክር አልሆነም።
ሸ. በተመሳሳይ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በሚገቡ አገሮች፣ ከቀውሱ የመውጫው ወሳኙ ቁልፍ የሚገኘው ሥልጣን በያዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ዘንድ ነው። ሌሎች የፖለቲካ እና የሲቪክ ቡድኖች ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር የማይተካ አስተዋጾ ማበርከት ይችላሉ። ሆኖም ሥልጣን የያዙ ወገኖች የለውጡን ተፋሰስ መሠረታዊ አቅጣጫ የመወሰን አቅም አያጡም። ኢሕአዴግ አገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ ወደሚያስከፍለን የመጠፋፋት፣ የመለያየትና የእርስ በርስ ጦርነት መንገድ እንዳይወስዳት መከላከል የሁላችንም የግልና የጋራ ሐላፊነት ነው።
ቀ. “ኢትዮጵያ አትፈራርስም፤ በድጋሚ ወደ እርስ በርስ ጦርነት አንገባም፤ በኢትዮጵያ በብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠረ የተደራጀ ጥቃት ሊፈጸም አይችልም፤ ወዘተ” ብሎ ራስን ማታለልና ማዘናጋት ብዙ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል።
የእነዚህ ሁኔታዎች ድምር ውጤት አገሪቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁላችንንም ሊጎዳ ወደሚችል ቀውስ ሊያሸጋግራት የሚችልበት ዕድል አለ። ይህ ከመሆኑ በፊት በግልና በቡድን በመንቀሳቀስ አደጋውን ማስቀረት ይገባል። ከዚያም ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የሚያስተናግድ፣ ሕግ የበላይ የሆነበት፣ የዜጎች መሠረታዊ መብቶች የሚከበሩበት ሥርዓት የመገንባት ዕድል ሊኖረን ይችላል።
እነዚህ ኹኔታዎች ሁላችንንም ሊያሳስቡ የሚችሉ እንደሆኑ እንገነዘባለን። ይህን መሰሉ ወቅት ሐላፊነታችንን ሌሎች እንዲሰሩልን የምንጠብቅበት አይደለም። አሳሳቢና አስከፊ ሁኔታዎችን የመቀየር የመጀመሪያ እርምጃ ስጋቱን ራሱን፣ እንዲሁም መፍትሔ የሚሉትን ማሰማት እንደሆነ እናምናለን። በዚህ መነሻነትም፣ የዋዜማ ሬዲዮ ኤዲቶሪያል ቡድን የሚከተሉትን ጥሪዎች በትህትና ለወገኖቻንን ሁሉ ያቀርባል። ሐሳቦቹ መልካም ሆነው ካገኛችኋቸው ተከተሏቸው። ስሕተት ከሆኑ አርማችሁ ተግብሯቸው። ጥሪያችንና ተማጽኗችን በጎ ሕሊና ላላቸው ሁሉ ይድረስ።
1. በየትኛውም መንገድ በምናውቃቸውና በምናገኛቸው የኢሕአዴግ አመራሮችና አባላት ላይ ግፊት ማድረግ። ይህም ስጋታችንን፣ ፍላጎታችንን እና አደጋውን ያለመሸፋፈን በግልጽ ማስረዳትን፣ መከራከርን፣ የበኩላቸውን እንዲያደርጉ መገፋፋትን ሁሉ ያካትታል።
2. በየትኛውም መንገድ በግል በምናውቃቸውና በምናገኛቸው የክልልና የፌደራል ፖሊስ፣ የመከላከያ እና የደኅንነት አመራሮችና ተራ አባላት ላይ ግፊት ማድረግ። በተለይም ጅምላ እስሩ፥ ግድያው፣ አፈናው፥ ማሰቃየቱና ማሳደዱ እንዲቆም በግላቸውም ሆነ ከባልደረቦቻቸው ጋራ ጥረት እንዲያደርጉ ማስረዳት፥ ማሳመንና መገፋፋት ያስፈልጋል።
3. የሃገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ውይይትና ድርድር ለማድረግ መቀመጥ አለባቸው። በዚህ ሒደትም መሠረታዊ አቅጣጫ የሚጠቁም፣ አገሪቱ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስኪረከባት የሚኖረውን ሒደት የሚያሳይ ዝቅተኛ የጋራ የድርጊት መርሃ ግብር (Road map) ነድፈው ከወዲሁ ለሕዝብ ያሳውቁ። ይህ ውይይትና ድርድር በተቻለ መጠን ማንንም ያላገለለ ቢሆን ይመረጣል። በአገር ቤትም በውጭም በሚቻለው መንገድ ሊከናወን ይገባዋል። የተለያዩ ድርድሮች የየራሳቸውን አማራጮች ለሕዝብ ማቅረብም ይችላሉ። ቁም ነገሩ ለሕዝቡ መጪውን ጊዜ የሚጠቁሙና ተስፋ የሚሰጡ አማራጮች መቅረባቸው ነው።
ይህ ሲደርግ ሦስት መሠረታዊ ጭብጦች ሊዘለሉ አይገባም ብለን እናምናለን። እነርሱም:-
(ሀ) ሁሉንም ነገር ከዜሮ መጀመር የለብንም፤
(ለ) የምንገነባው ሥርዓት መሠረታዊ የዴሞክራሲ መርሆችን በተግባር የሚያከብር መሆን አለበት፤
(ሐ) ፌደራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ቁልፍ መነሻ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።
4. የሃገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሲቪክ ቡድኖችና ድርጅቶችም በበኩላቸው የራሳቸውን የተናጠልና የጋራ ሐላፊነት መወጣት አለባቸው። እነዚህ ሲቪክ ድርጅቶች ራሳቸውን ከፖለቲካ ድርጅቶች አላስፈላጊ ተጽእኖ መጠበቅ አለባቸው። እንዲያውም የፖለቲካ ሃይሎቹን የመምከር፥ የመገሰጽ ሚናቸውን ከወዲሁ ማጠናከር ይኖርባቸዋል። እነርሱም ለአገር ይበጃል የሚሉትን የጋራ ምክረ ሐሳብ ለሕዝብ ቢያቀርቡ ትልቅ አስተዋጾ ይሆናል። ይህ አገር ቤትም ሆነ በውጭ ያሉትን ሁሉ የሚመለከት ነው። ሁሉም አካባቢያቸው በሚፈቅድላቸው ሁኔታ ተቀራርበው መመካከር፥ ግንኙነቶችን መፍጠር ይችላሉ። (ይህ በተለያየ ቅርጽና ዓላማ የተቋቋሙ ቡድኖችንና ማኅበራዊ ተቋማትን ማለትም የእምነት ተቋማት/ስብስቦች፣ የሞያ ማኅበራት/ስብስቦች ሁሉ የሚጨምር ሆኖ፥ ለዚሁ ዓላማ የሚፈጠሩ ስብስቦችንም የሚመለከት ነው።)
5. የፖለቲካ አመለካከት፣ የብሔርም ይሁን የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን፣ ሁኔታው በሚፈቅድልን መልኩ ከወትሮው በበለጠ መገናኘት፣ የኖረውን ማኅበራዊ ትስስርና የወንድማማችነት መንፈስ ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ ይታያል። ይህ እንቅስቃሴ ለሁሉም ወገን መተማመንን የበለጠ ያሰርጻል፣ የተዘራውን የመጠራጠር ዘር ያከስማል፤ ምናልባት ግርግር ቢፈጠር እንኳን በቀላሉ ለመረዳዳት ያስችላል።
6. ኢትዮጵያውያን የጋራ ህመማቸውን እና ተስፋቸውን የሚነጋገሩባቸውን የጋራ መድረኮች ሁኔታው በሚፈቅድ መጠን ማስፋፋት። ዜጎች አንዱ ስለሌላው እንደሚያስብ፥ እንደሚጨነቅ መናገርም መስማትም ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያውያን የወገኖቻቸውን የፍቅር፥ የመተማመን እና የተስፋ ድምጾች መስማት ይሻሉ። ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ጋራ መታረቅ ይፈልጋሉ፤ ለወገኖቻቸው የጋራና የተናጠል ህመም ያላቸውን ሃዘን መግለጽ ይሻሉ። ልዩነቶቻቸውን ጥላቻና እልህ ባልተጫነው መንፈስ መወያየት ይሻሉ። ማንንም ሳንጠብቅ ድምጻችንን እንሰማማ።
7. የጥላቻ ንግግር የጥፋት መጀመሪያ ነው። በግልም ሆነ በአደባባይ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ በአንድ ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም ሌላ አይነት የሰዎች ስብስብ ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮችን ማስወገድ የሰላም ሁሉ መጀመሪያ ነው። የጥላቻ ንግግሮችንና ቅስቀሳዎችን ማስወገድ ግዴታ ነው። ተደርጎ ሲያጋጥመንም ስሕተት መሆኑን ማስረዳት የሁላችንም ግለሰባዊ ሐላፊነት ነው። የፖለቲካ ልዩነትን ለማሳየት የሌላኛውን ወገን ሰብአዊነት መካድና እንደሌላ ፍጥረት መሳል፣ ግለሰቡንና የመጣበትን ቡድን እንደሰው እንዳይቆጠሩ መቀስቀስ ሁሉ ከአደገኛ የጥላቻ ንግግር የሚቆጠሩ ናቸው። በጥላቻ ንግግሮች የሚያተርፍ አገር የለም።
8. ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታና እያንዣበበ ያለውን ተጨባጭ አደጋ በትክክል እንዲረዳ በስልትና በትጋት መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው። ይህ ሰላማዊ ሰልፎችን ከማድረግ የዘለለ፣ እልህና ቁጭትን ከመግለጽ የጠለቀ ተልዕኮ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
9. በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ መገናኛ ብዙኀንና ጋዜጠኞ አገራችን ይህንን አስጊ ወቅት አልፋ ወደተሻለ ምእራፍ እንድትሸጋገር ተመሳሳይ ጥሪዎችንና መልእክቶችን ያስተላልፋሉ ብለን እናምናለን። የሚቻል ከሆነም፣ ተመሳሳይ ርእሰ አንቀጾችን በተመሳሳይ ወቅት በማሰራጨት፣ ወይም በሌላ በሚመቻቸው መንገድ የጋራ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ እንማጸናለን።
ጥሪያችንና ተማጽኗችን ያለምንም ልዩነት በጎ ሕሊና ላላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይድረስ።
ዋዜማ ሬዲዮ
ሐምሌ 2008
መልዕክቱን በኦሮምኛ ቋንቋ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
Lemma says
Tebareku!!!!
Ebakachihu yihinin girum melikt lehizbu beyekuankuaw endisemaw degagmachihu bedimst asemu.
Tehahitoch, bekachihu.
Lemma
koster says
Federalism and fascism does not work, federalism under democracy is not based on ethnicity and with a wall to exclude or evict other ethnic groups.