የኢቢሲ “ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ” “መንግሥት ታላላቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየሰራ ለትላልቅ ኢንቨስተሮች ይሰጣል። እነዚህ ከባባድ ኢንቨስተሮች ምርቱን በሞኖፖል ከያዙት፣ ይኸ ነገር በሃገራችን “እየተሰፋፉ የመጡትን መካከለኛ ኢንቨስተሮች” ሊያፈናቅላቸው ይችላል ተብሎ ይሰጋል። ይህንን እንዴት ይመለከቱታል።
¼ኛ ጠ/ሚ ደሳለኝ “ትክክል ነው ልማታዊው መንግሥታችን ታላላቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየሰራ ለትላልቅ ኢንቨስተሮች ይሰጣል። ይህን ነገር እኮ እኛ የፈለሰፍነው አይደለም። ከሌሎች ሃገሮች ተመክሮ (ኮርጀን – ባግባቡ ወይም ባላግባቡ) ወስደን፣ ለምሳሌ ከደቡብ ኮርያ፣ ቬትናምና ቻይና አይተን ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የምንሰራበት ምክንያት ኢንቨስተሮች እንዳይቸገሩ ነው። ለምሳሌ መብራት እንዳይቋረጥባቸው። እነሱ ለምን ይቸገሩ? እ? ጨርቁን ቀለም እየቀቡት እያለ መብራት ቢቋረጥ እኮ በቃ ያ ሁሉ ጨርቅ ተበላሸ ማለት ነው። ባለም ገበያ ላይ እኮ ተወዳድረው ነው የሚሸጡት…እ!” (ይሄ የመጨረሻው አረፍተ ነገር ቃል በቃል የተወሰደ ነው [1] ከ 4ኛው ደቂቃ ጀምሮ።
እንግዲህ የትልልቅ ኢንቨስተሮች መብዛት አነሥተኛ ኢንቨስተሮችን ያፈናቅላል አያፈናቅልም ለሚለው ጥያቄ መልሱን አልሰማሁም። ዎልማርት አንድ ቦታ ሲከፈት ያካባቢውን ትንንሽ ነጋዴዎች እንደሚያፈናቅለው ማለት ነው። ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ነው መልሱ። እኔ ደግሞ ይህንን መልስ ሰምቼ ደሳለኝ ደበረኝ። (ወፍጮ ቤቶችና ሱቆች እየፈረሱ መሬት ለሌሎች እየተፈለገ እያለ ማለት ነው።)
የኢቢሲ “ጋዜጠኛ” “ሶቨሪን ቦንድ የሚባለው ነገርስ ለሃገራችን ትልቅ ጫና ይሆናል የሚባለውስ?”
¼ኛ ጠ/ሚ ደሳለኝ “እሱማ ምንም ችግር የሌለበት ብድር ማለት እኮ ነው።ከቻይናና ከወርልድ ባንክ ስትበደሪ ጣጣ አለው። ለምሳሌ ለምን እንደምትፈልጊው፣ ምን ፕሮጄክት ላይ ማዋል እንደምትፈልጊ በዝርዝር ጽፈሽ፣ ፈርመሽ ነው የምትቀበይው። ሶቨሪን ቦንድ ግን በቃ ብር ሥጡኝ ብለሽ መበደር ነው። በሶስት ቀናት የሚገኝ ብድር ነው። ለፈለግሽው ጉዳይ ማዋል ትችያለሽ። እኛ ግን ዝም ብለን ልንበላው አይደለም የምንበደረው … ለሜጋ ፕሮጄክቶች እንዲሆን ነው”
“በሶስት ቀን የሚገኝ ብድር?” … እንዴ ከማን ነው የምትበደሩት? ከማፍያ? “ዝም ብለን ልንበላው አይደለም? ሜጋ ፕሮጄክቶች? ለምሳሌ የብአዴን 35ኛ አመት ማክበሪያ ሜጋ ፕሮጄክት … እየጨፈረን፣ ዝም ሳንል የምንበላው?” ብለን እንጠራጠር የሚል ሃሳብ ውል ባይልብኝም የደሳለኝ መልስ ግን ደበረኝ።
የኢቢሲ “ጋዜጠኛ” “ግብጽ በአባይ ግድብ የተነሳ በጣም ከማሥጋቷ የተነሳ መሳሪያ እያጠራቀመች ነው ይባላል። ይህንን እንዴት ያዩያል?”
¼ኛ ጠ/ሚ ደሳለኝ “ግብጽ ከፈለገች ሃገሩን በሙሉ መሳሪያ ታድርግ። የሚዋጋው መሳሪያ አይደለም አስተሳሰብ ነው”
ደሳለኝ አሳቀኝ። የሚዋጋው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል አስተሳሰብ ነው?
ማርቲን ዴኒስ ከአልጃዚራ “መንግሥትዎ ዲሞክራቲክ ነው?”
¼ኛ ጠ/ሚ ደሳለኝ “ያለጥርጥር።”
ደሳለኝ አሳቀኝ። ጥርሴ እስኪነቃነቅ።
ማርቲን ዴኒስ ከአልጃዚራ “የእርስዎ መንግሥት የሚኮራበትና ሁሌም የሚለው ሃገርዎ እንዴት እያደገች እንዳለች ነው። አነጋጋሪው ጉዳይ ግን የእድገቱ ተጠቃሚዎች በአንድ እጅ ላይ ባሉ ጣቶች ብቻ የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው መባሉ ነው። ምን ይመልሳሉ ለዚህ?”
¼ኛ ጠ/ሚ ደሳለኝ “ጥያቄሽ ጠለቅ ያለ ምርመራና ጥናት የጎደለው ነው። በሃገራችን ከ70 ሚሊዮን ገበሬዎች መሃከል ከድህነት መሥመር በታች ያሉት 15 በመቶ ብቻ ናቸው። ሌላው ሃብታም ነው።”
ማርቲን ዴኒስ ከአልጃዚራ “ሃብት በሃብት ከሆናችሁ ታዲያ እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን ለምን ይሰደዳሉ?”
¼ኛ ጠ/ሚ ደሳለኝ “እንዴ? አልጃዚራ ስለ ስደተኞች ዶክሜንተሪ ሲሰራ አንድም ኢትዮጵያዊ አላሳየም እኮ! ይህ በመሆኑ በጣም ነው ደሳለኝ።” [2] ከ10:47 ደቂቃ ጀምሮ ያዳምጡ።
ደሳለኝ ደሳለኝ አለ። እኔን ግን ደሳለኝ ደበረኝ።
ማብራሪያ ¼ኛ ጠ/ሚ ደሳለኝ ላልኩበት ምክንያት።
ባለፈው ሰሞን አንድ ደሳለኝን የሚያሞግስ ጽሁፍ አነበብኩ። እኚህ ሰውዬ ደሳለኝ ሥልጣን የሚጋሩት ኒዎ ሊበራሎች እንደሚናገሩት አሻንጉሊት ሆነው ሳይሆን በሃገራችን ሥልጣን የመጋራት ልምድ ኢህአዲግ በማስለመዱና በማስፈሩ ነው ብለው ይደመደማሉ። ከሌሎች ሶስት ሰዎች ጋር ሥልጣን ከተጋሩ ደሳለኝ እንግዲህ ¼ኛ ጠ/ሚ ናቸው። በጫወታችን ላይ የሚያስቀኝ ነገር በጠፋበት ዘመን እኝህ ሰውዬ ይህንን ጽፈው ስላሳቁኝ ባለውለታዬ ናቸው።።
[1] https://www.youtube.com/watch?v=pOSDvm4weOM
[2] https://www.youtube.com/watch?v=VwimUr2C7mY
***********
ጌቱ ኃይሉ አማዞን (amazon.com) ላይ በመሸጥ ያለው ጸሃዮቹ (tsehayochu) የተባለው መጽሃፍ ደራሲ ነው።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply