
መግቢያ
የዛሬ ስምንት ዐመት ባራካ ኦባማ ለፕሬዚደንትነት ምርጫ ለውድድር ሲቀርቡ፣ ከፕሪመሪው ጀምሮ የነበረውን የምርጫው ሂደት እዚህ አውሮፓ ሆነን በየሰዓቱ ሁኔታውን በጥብቅ እንከታተል ነበር። በማያጠራጥር መልኩ የብዝዎቻችን ፍላጎትና አድልዎ ለባራክ ኦባማ ቢሆንም፣ ባራክ ኦባማ ያንን አስቸጋሪ የፕሪመሪ ውድድር አልፈውና ተፎካካሪዎቻቸውን አሸንፈው የዲሞክራቲክ ፓርቲውን በመወከል ለፕሬዚደትነት ምርጫ ይቀርባሉ ብሎ የገመተ አልነበረም። የመጨረሻ መጨረሻ ወይዘሮ ሂለሪ ክሊንተን በአሸናፊነት በመውጣት ፓርቲያቸውን በመወከል የሪፓብሊካን ፓርቲን ከሚወክለው ጋር ለውድድር ይቀርባሉ የሚል ግምት ነበረን። አሁንም ቢሆን የኢንስቲቱሽናል ሬሲዝምነትና አጠቃላይ ሬሲዝምነት በነገሰበት በአሜሪካን ህብረተሰብ ውስጥ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ለፕሬዜደንትነት ምርጫ በመወዳደር በአሸናፊነት ይወጣል ብሎ መገመት በጊዜው የሚታሰብ ጉዳይ አልነበረም።
ቀደም ብሎ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ባራክ ኦባማ በአንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተጋብዘው በመቅረብ አሜሪካን በተለይም ቀደም ብሎ የነበራትን የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ የበላይነት ስለማጣቷና፣ ገበያውም ከቻይና በሚመጡ ምርቶች ስለመጥለቅለቁ ይሰጡት የነበረው አስተያየት በጣም የሚያረካ ነበር። በእሳቸውም አባባል፣ ርካሽ የሰው ጉልበትን ለመጠቀም ሲባል ብዙ ኢንዱስትሪዎች እየተነቀሉ ወደ ቻይናና እንደ ሜክሲኮ የመሳሰሉ አገሮች በመወሰዳቸው ከውስጥ የኢንዱስትሪ መስኩ መዳከሙ ብቻ ሳይሆን፣ የውጭ ንግዱም እንደተጎዳና፣ አሜሪካም ከአበዳሪነት ወደ ተበዳሪነት በመሸጋገር አስቻጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደወደቀች የሚሰጡትን ትንተና ላዳመጠ በእርግጥም እኚህ ሰው ለፕሬዚደንትነት ተወዳድረው ካሸነፉ የኢንዱስትሪ መስኩን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን በጊዜው በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሎ የነበረውን የስራ አጥ ቁጥር ሊቀንሱ ይችላሉ የሚል እምነት ነበረን። በዚህም ምክንያት የሰራተኛው ገቢ በማደግ በጊዜው የነበረውን ማህበራዊና ባህላዊ ቀውስ እስከተወሰነ ደረጃም ሊቆጣጠረው ይችላል የሚል የተሰፋ ብልጭታ ይታያል የሚል ግምት ነበረን። በተለይም አንድ ጥቁር ሰው የነጭ የበላይነት በሰፈነበት አገር ፕሬዚደንት ሆኖ ሲመረጥ የጥቁሩ ህዝብም ኑሮ የተሻለ እምርታን በማግኘት ጥቁሩ በራሱ ላይ የበለጠ እምነት ሊያገኝ ይችላል ብለን ያሰብን ጥቂት አልነበረም።
ባራክ ኦባማ የመጨረሻ መጨረሻ ውድድሩን አሸንፈው ለፕሬዜደትነት ሲቀርቡና ከሪፓብሊካኑ ከሜኬን ጋር ተወዳደረው በከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና በኤሌክቶራል ድምጽ ሲያሸንፉ፣ ውጤቱ በአሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ የሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖም እንደሚኖረው መገመቱ ቀላል አልነበረም። እንደሚታወቀው ባራክ ኦባማ ቀደም ብለው በፕሬዚደንት ቡሽ የሚመራው አስተዳደር በኢራክ ላይ ያወጀውን ጦርነትና ወታደርም የመላኩን ጉዳይ አጥብቀው የተቃወሙ ነበሩ። ስለሆነም የሳቸው መመረጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን የሚያስቀደም ፖለቲካና፣ በተለይም ደግሞ የሶስተኛው ዓለም ተብለው ለሚጠሩ አገሮች ወደ ውስጥ ለዕድገት የሚያግዛቸው የሚያፈናፍን ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል የሚል አስተሳሰብ በጭንቅላታችን ውስጥ ይብሰለሰል ነበር። እነዚህና ሌሎችንም የሰውየውን አቀራረብ ለተመለከተ የአሜሪካን ፖለቲካ ከአግሬሲብ ባህርይው በመላቀቅ በአገሮች መሀከል “በእኩልነትና በመከባበር” ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት እንደሚፈጠር ለማመን ተቃርበን ነበር።
የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የስምንት ዓመቱ የፖሊሲ ውጤት !
ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ከተመረጡና በጥር ወር 2009 ዓ.ም ስልጣናቸውን በመሃላ ከተረከቡ በኋላ የጠበቃቸው የቤት ስራ እጅግ ከባድ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ የግል ባንኮችና የእንሹራንስ ኩባንያዎች ለቤት መስሪያ ወይም መግዢያ ለተወሰነው ህዝብ በማበደር የአሜሪካንን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የከተቱበት ሁኔታ ነበር። በዚህም ላይ አብዛኛው የአሜሪካን ኢኮኖሚ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ከኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ይልቅ በአገልግሎት ላይ እየተመካ በመምጣቱ ይህ መስክ የስራ እድል ለመክፈት የነበረው ኃይል በጣም ውስን ነበር። በዚህም የተነሳ አሜሪካ ወደ ውጭ ከምትልከው ይልቅ ወደ ውስጥ የምታስገባው ከፍ እያለ በመምጣቱ የንግድ ሚዛኗ የተናጋበት ወቅት ነበር። ስለሆነም የአሜሪካን መንግስት፣ የመንግስት ቦንድን በማደል ከውጭው ዓለም ብድር በመቃረም በዕዳ የተተበተበበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በዚህ ላይ ደግሞ የቡሽ መንግስት ወደ ኢራክና አፍጋኒስታን ወታደሮችን በመላክ ለጦርነት ወደ አንድ ትሪሊዮን የሚቆጠር ያህል ገንዘብ በማውጣቱ ወደ ውስጥ የስራ መስክ ለመክፈት በሚያስችሉ ፕሮጀክቶችና ኢኮኖሚውን ሊያንቀሳቅሱ በሚችሉ የኢንዱስትሪ መስኮች ላይ የመዋዕለ-ነዋይ እጠረት በመከሰቱ ጠቅላላው ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ተናግቶ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ አገሪቱ በከፍተኛ የማህበራዊ፣ የህብረተሰብና የባህል ቀውስ ውስጥ በመውደቅ ከዚህ ሁኔታ ለማንሰራራት አዲሱ የባራከ ኦባማ አስተዳደር በቀላሉ ሊፈናፈን የሚችልበት ሁኔታ አልነበረውም።
የውጭ ፖለቲካውን ስንመለከት፣ ከ1989 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረው አዲስ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሁኔታ አሜሪካን እንደፈለገው የሚፈነጭ ስለመሰለው በተለይም አልታዘዙኝም ያላቸውን አገሮች ሁሉ በመተናኮል ወደ ጦርነት ውስጥ የገባበት ጊዜ ነበር። አክራሪ “ወግ አጥባቂዎች” (Conservative-Noe-Cons) በፕሬዜደንት ቡሽ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ የተካተቱና በፖሊሲ ደረጃም ተደማጭነት ስለነበራቸው፣ ከእንግዲህ ወዲያ ዘመኑ የአሜሪካን ዘመን ነው በማለት ያለ የሌለ ኃይላቸውን በሙሉ በጦርነትና አገሮችን በማተረማመስ ላይ በማዋል የዓለምን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል ወሳኝ የሆኑበት ጊዜ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ ዩኒላተራል ፖለቲካን በመከተል ዓለም አቀፋዊ ውዝግቡ እንዲጦፍና፣ የአሜሪካን ትላልቅ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎችና የዘይት አውጭ ድርጅቶች አገሮችን በማመስና በመዝረፍ የትርፍ ትርፍ ለማካበት የሚያስችላቸው አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ነበር። ከዚህም ባሻገር የኒዎኮንስ ስትራቴጂ ከመበታተን የተረፈችውን ራሺያን በመክበብና እንደገና የተቀረውን በመበታተን ኦይራሺያን የሚባለውን በጥሬ-ሀብት ክምችት የሚታወቀውን የራሺያን ግዛቶች በቁጥጥር ስር ማዋል አንደኛውና ዋናው ስትራቴጂያቸው ስለነበር አትክሮአቸው በሙሉ አሜሪካን በሁሉም አገር በሚለው መርሆቻቸው የዓለምን ማህበረሰብ በማወካብ ላይ ነበሩ።በብዙ አገሮችም ይህን የበላይነትን ፖሊሲያቸውን ተግባራዊ የሚያደርግና ከውስጥ ሆኖ ደግሞ አገሩን የሚያምስ አዳዲስ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና እንዲሁም የሚሊተሪ ኤሊት በመኮትኮትና በመንግስት መኪና ላይ በማስቀመጥ የበላይነታቸውን ለረዥም ጊዜ ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ በቅተው ነበር። ከዚህም በመነሳት ብቸኛውና አማራጭ የሌለው ዓለምን እንደፈለገው የሚያሽከረክር ኃያል መንግስት ሆኖ ለመውጣት የስለላና የሚሊታሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብነቱን ያጠናከረበት ጊዜ ነበር፤ ነውም። ይህ ዐይነቱ የውጭ ፖለቲካ ግን ወደ ውስጥ የአሜሪካንን ህብረተሰብ በሁሉም አቅጣጫ እያዳከመው እንደመጣና፣ የወንጀለኛውም ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ እንዳደረገው መገንዘብ ይችላል።
ባራክ ኦባማ ስልጣንን ሲረከቡ እነዚህን ሁሉ ማስተካከልና መጠገን ነበረባቸው። በመጀመሪያ ደረጃ እጅግ የተዳከመውን የባንክ መስክና የመኪና አምራች ኢንዱስትሪ እንደገና እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ወደ$ 800ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ አፍሰዋል። በዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲም ቢያንስ የመኪና ኢንዱስትሪው እንዲያንሰራራ አመቺ ሁኔታ ፈጥረዋል። ይሁንና ግን የካቢኔት ስዎቻቸውን ስንመለከት አብዛኛዎቹ ከዎል ስትሪት ጋር በጥብቅ የተሳሰሩና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲን በማራመድ የሚታወቁ ኢኮኖሚስቶች ስለነበሩ፣ በከፍተኛ ደረጃ የስራ መስክ ሊከፍቱ የሚችሉ ማዕከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን የሚደጉም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሊያደርጉ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛው ገንዘብ የፈሰሰው ወደ አክስዮን ገበያ(Stock market) ላይ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎችም ቀደም ብለው አየር በአየር ንግድ የካበቱ ሀብታሞችናቸው። ባራክ ኦባማ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ የስራ መስክ እድል ቢከፈትም፣ ፖሊሲው ግን በሀብታምና በዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል መሀከል የነበረውን የገቢና የሀብት ልዩነት ዝቅ ከማድረግ ይልቅ በከፍተኛ ደረጃ ልዩነቱ እንዲሰፋ ነው ያደረገው። ከዚህምበላይ የማዕከላዊ ባንኩ የሚከተለው የዜሮወለድ(Zero Interest)የገንዘብ ፖሊሲ የበለጠ የጠቀመው የአየር በአየር ንግድ ላይ የተሰማሩትን ኩባንያዎችና ግለሰቦችን ስለሆነ በዝቅተኛ ደሞዝ የሚተዳደረውን የህብረተሰብ ክፍል ከከተማ ውስጥ ተገፍትሮ እንዲወጣ ለማድረግ በቅቷል። በዚህ ዓይነቱ የኢኮኖሚና የሞነቴሪ ፖሊሲ እንደ ኒዎርክ በመሳሰሉት ትላልቅ ከተማዎች ውስጥ 19 ካሬ ሜትር አፓርትሜንት ኪራዩ ከ900 $ ዶላር በላይ ነው። ከዚህም ባሻገር ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲበአጠቃላይ ሲታይ የኑሮ ውድነት እንዲናር ያደረገና፣ አብዛኛው የአሜሪካን ህዝብም በክሬዲት ካርድ ላይ የባሰውኑ ጥገኛ እንዲሆን ነው ያደረገው። ባራክ አቦማ ከብዙ ጊዜ ትግል በኋላ ተሳካላቸው የሚባለው ኦባማ-ኬር(Obama care) የሚባለውን ለ12 ሚሊዮን ህዝብ የጤንነት ኢንሹራንስ ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው። ይሁንና ይህ ጥሩ የሆነውን ያህል በቀረጥ የተደጎመ ባለመሆኑና፣ በጣምም ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ የበዛበት በመሆኑ እስከዚህም ድረስ አብዮታዊ እንዳልሆነ ብዙ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የባራክ ኦባማን የውጭ ፖለቲካ ስንመለከት፣ ከቡሽ የአግሬሲብ ፖለቲካ የተላቀቁ ቢያመስላቸውና የተወሰነ የወታደር ኃይል ከኢራክ ቢያስወጡምና የመጨረሻ መጨረሻም ከኢራን መንግስት ጋር የአቶም ስምምነት ቢያደርጉም፣ እጅግ በረቀቀ መንገድ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያና ሶሪያ ውስጥ የተቀጣጠለውን ጦርነት እንዲፋፋም በማድረግ የመንግስት ለውጥ(Regime Change) እንዲመጣ ከሚያደርገው የአሜሪካን ስትራቴጂ በፍጹም ለመላቀቅ እንዳልቻሉ እንገነዘባለን። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢስላሚክ መንግስት(IS) የሚባለውን የገዳይ ድርጅት በመሳሪያ፣ በምክርና በገንዘብ በመደገፍ ለብዙ መቶ ሺህ ህዝብ ማለቅ ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል። ይህም ፖሊሲያቸው ከሌሎች የአውሮፓ መንግስታት፣ በተለይም ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በማበር በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሶሪያውያን አገራቸውን ለቀው ወደ አውሮፓ እንዲጓዙ ለማድረግ በቅቷል። ራሺያን ለማዳከምና ብሎም ለመበታተን ሲባል በዩክራይን ላይ የተከተሉት የመንግስት ግልበጣ ፖሊሲና የባልቲክ መንግስታትን (Baltic States) አስታጥቆና ወታደር ልኮ ራሺያን መክበብና፣ የሶስተኛው ዓለም ጦርነት እንዲነሳ መቀስቀስ ባራክ ኦባማ የዴሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው ስልጣን ላይ ቢወጡም ፖሊሲያቸው በሙሉ በምንም ዐይነት ዲሞክራሲያዊ ነው የሚያስብለው አንዳችም ነገር የለም። ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው የአሜሪካን የፖለቲካ ኤሊት አካል በመሆናቸው የአሜሪካንን የበላይነት ከማስቀደምና አገሮችን አዳክመው ከመበታተን እንደማይመለሱ ከሊቢያና ከሶሪያ መማርና ማየት ይቻላል። ስለሆነም የስምንት ዓመቱ አገዛዛቸው በዓለም ታሪክ ውስጥ ስላምን፣ መረጋጋትን፣ በአገሮች መሀከል መከባበርንና ለዕድገት አመቺ ሁኔታን ፈጥሮ ያለፈ ሳይሆን፣ የበለጠ አለመረጋጋትንና፣ መንግስታት የበለጠ አሸባሪዎችን መዋጋት አለባቸው በሚለው ፈሊጥ ላይ አትኩራቸውን እንዲቀይሩ ያደረገና፣ወደ ወስጥ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እንዳይሰማሩ ያደረገ እጅግ አደገኛ ፖሊሲ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በባራክ አቦማ የአገዛዘ ዘመን የዓለም ህዝብ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትያመራ ሳይሆን የበለጠ ወደ ጨቋኝና ወደ መዝባሪ ስርዓት ያመራ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።
ክሊንተን ወይም ትረምፕ- ተስቦ ወይስ ኮሌራ !
በምርጫው የውድድር ሂደት ውስጥ እዚህ ጀርመን አገር የሚወራው ወሬ በወይዘሮ ሂለሪ ክሊንተንና በዶናልድ ትረምፕ መሀከል ያለውን ልዩነት የነቃው ምሁር ይገልጽ የነበረው በተስቦና በኮሌራ በሽታ መከሀከል እንደመምረጥ ያህል ነው እያለ ነበር። ሁለቱም የወረርሽኝ በሽታዎች የመጨረሻ መጨረሻ ሰውን አሰቃይተው የሚገድሉ ስለሆነ ሁለቱም ለምርጫ የሚቀርቡ አይደሉም እንደማለት ነው። ይሁንና በሚዲያ ዘንድና በፖለቲኮኞች መሀከል የነበረው አድልዎ ለወይዘሮ ክሊንተን ነበር። ዶንላድ ትረምፕ በሚሰነዝሩት ያልተገራ አውራርና፣ በተለይም ደግሞ ዝቅተኛውን የህበረተሰብ ክፍልና አካለ ስንኩሉ ላይ ወይም ሌላ የሴክሹዋል ኦሬየንቴሽን ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ይሰነዝሩ የነበረው አላስፈላጊ ቃላቶች የመመረጥ እድላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እንደሚያደርገው መገመቱ ይህንን ያህልም ከባድ አልነበረም። በተጨማሪም ደግሞ በነፃ ንግድና (TTIP) በሰሜን አትላንቲክ የጦር ስምምነት ላይ ያላቸው አመለካከትና፣ አሜሪካ መጀመሪያ (America First) የሚለው አባባለቸው የጦርነቱ ስምምነት አባል አገሮችን ከፍተኛ የመንፈስ አለመረጋጋት ውስጥ እንደከተታቸው ለመከታተል ችለናል። በዚህም ላይ ፕሬዚደንት ፑቲንን ማድነቃቸውና፣ አማካሪያቸውም ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ነበረው ብሎ ስለሚታማ የውጭ ፖሊሲያቸው የበለጠ የአውሮፓ መንግስታትን ሚና የሚያዳክም የሚያስመስለው ነበር። በዚህ ዐይነቱ አባባላቸው ወደ ፊት ይቀጥሉ አይቀጥሉ ከአሁኑ መገመቱ አስቸጋሪ ነው።
ወደ ወይዘሮ ክሊንተን ስንመጣ ከፈተኛ የፖለቲካ ልምድ እንዳለቸው የሚነገርና፣ የአሜሪካን የፖለቲካ ኤሊት አካል (Establishment) እንደመሆናቸው መጠን በተለይም ወደ ውጭ የበለጠ አግሬሲቭ ፖሊሲ ለመከተል እንደሚችሉ ግልጽ ነበር። ባላቸው ፕሬዚደንትቢል ክሊንተን ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ቢል ክሊንትን ይጎዝላቢያ እንድትበታተን በቦንብ ሊደበድቡ ሲቃጡ አንደኛውና በግልጽ የማይታየው አማካሪያቸው ሚስታቸው ወይዘሮ ክሊንተን እንደነበሩ መገመቱ ይህንን ያህልም ከባድ አልነበረም። የውጭ ጉዳይ ምኒስተርም ከሆኑ በኋላ ከፕሬዚደንት ኦባማ ጋር የነበራቸው ልዩነት ይህ ዐይነቱ አግሬሲብና የጦርነት ፖሊሲያቸው እንደሆነ አንዳንድ ተንታኞች ይናገራሉ። በተለይም ፕሬዜደንት ጋዳፊ እንዲገደሉና ሊቢያም እንድትበታተን ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት እኚህ ሴት እንደነበሩ በግልጽ ይታወቃል። ሶሪያንንም በቀጥታ ለመደብደብ ፕሬዚደንት ኦባማን ቢገፋፉም፣ ፕሬዚደንት ኦባማ የተከተሉት ፖሊሲ ግን የበለጠ „ሲስተማቲክ“ በሆነ መልክ አሸባሪዎችን በመደገፍ የፕሬዜደንት አሳድን መንግስት አዳክሞ እሳቸውና የአውሮፓ መንግስታት „ለዘብተኛ“ የሚሏቸውን „ተቃዋሚ ኃይሎችን“ ስልጣን ላይ ማውጣት ነበር። በመሰረቱ በሁለቱ መሀከል የነበረው ልዩነት የአመለካከት ሳይሆን የአካሄድ ወይም የስትራቴጂ ብቻ ነው።
ያም ሆን ይህ ወይዘሮ ክሊንተንን ይህን ያህልም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ የሚያሰኛቸው አንዳችም ነገር የለም። በብዙ ሺህ ድሮች ከዎል-ስትሪት (Wall Street) ጋር የተሳሰሩና ለአንድ የማይረባና የአንድ ሰዓት የውሸት ንግግር እስከ 600 ሺህ ዶላር የሚከፈላቸው ነበሩ። ወደ ውጭ ደግሞ ከሳውዲ አረቢያዊ የሞናኪ አገዛዝና የዋሀቢትን የእስልምና ሃይማኖት ከሚያስፋፋው ጋር የጠበቀ ግኑኝነት የነበራቸውና፣ አማካሪያቸውም አንድ የሳውዲ አረቢያ ሴት እንደነበረች በግልጽ ይታወቃል። ወይዘሮ ክሊንተንም ከሳውዲ አረቢያ የሞናርኪ መንግስት ለፕሬዚደንት ምርጫ ካምፔይናቸው 900 ሚሊዮን ዶላር እንደተቀበሉ ይነገራል። ጎልድ ማን ሳክስ የሚባለው፣ ገንዘብ ከሀብታሞች እየሰበሰበ ቁማር የሚጫወትና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በጥሬ-ሀብት ዘረፋ ውስጥ ከሚቀራመተው ጋር ያላቸው ግኑኝነት በጣም የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ፣ ተጋብዘው ባደረጉት ንግግር ላይ በአሜሪካን አገር በ2007/2008 ዓ.ም ለደረሰው የዕዳና የቤት ስራ ቀውስ(Subprime crisis) ዋናው ተጠያቂ የሰራተኛው መደብ ነው በማለት የውሸት ንግግር አድርገው ወደ 600 ሺህ ዶላር ተቀብለዋል። ይህንና ሌሎች ፀረ-ዲሞክራቲክ ባህሪያቸውን ለተመለከተና፣ ክሊነተን ፋውንዴሽን በመባል በሚታወቀው በተለይም በሃይቲ የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 1,76 % ብቻ መሄዱን ስንሰማ እሳቸው ቢመረጡ የአሜሪካን ህዝብ አዲስ የበራ ዕድል ሊገጥመው እንደማይችል መገመት ይቻላል። ያም ሆነ ይህ እንደቋመጡትና፣ ሚዲያውና ሊበራል የሚባለው ሁሉ ለሳቸው ያላደላውን ያህል 09.11.2016 ዓ.ም የምርጫው ውጤት ሲነገር እሳቸውም ሆነ እኛ ራሳችን ማመን ነው የተሳነን። ዶናልድ ትረምፕ በመራጩ የድምጽ ቁጥር ሳይሆን በኤሌክቶራል ድምጽ(Electoral Vote) ማሸነፍ እንደቻሉ ሊነገርና ሊበስር ችሏል። ዶናልድ ትረምፕን የምደግፍ ባልሆንም በወይዘሮ ክሊንተን 45ኛው ፕሬዚደንት ሆኖ አለመመረጥ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ። በተለይም የዲሞክራቲክ ፓርቲን ስም አንግቦ ውሸት የሚያወራና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን የሚያስፋፋ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከማራምደው የሰብአዊነትና የዴሞክራቲክ፣ እንዲሁም የእኩልነት መርሆች ፕሪንሲፕልስ ጋር የሚጣጣሙ ስላይደለ ባለመመረጣቸው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል። በሳቸውም አለመመረጥ የክሊንተን ዲናስቲ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ወደ መቃበር ዓለም እንዲጣል ተደርጓል።
የዶላንድ ትረምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ ያስፈራቸውም ያስደሰታቸውም አሉ። በአውሮፓ የፖለቲካ መስክ ውስጥ ፖፑሊስቶችና የቀኝ ፖለቲካ አራማጆች ደስ ሲላቸው፣ ወይዘሮ ክሊንተን እንዳይመረጡ የማይናቅ ሚና የተጫወቱት የራሺያ መንግስት ተወካዮች በጣም ነው ደስ ያላቸው። ከግብጹ ፕሬዚደንት አሲስ ቀጥሎ የደስታ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚደንት ፑቲን ናቸው። ምናልባትም ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋር የቅርብ ግኑኝነት አላቸው የሚባሉና በራሺያ የውጭ ቴሊቪዢን ላይ ቀርበው የሚጠየቁት ቀደም ብለው የመከላከያ ጦር አባል የነበሩት ግለሰብ የዶናልድ ትረምፕ የካቢኔት አባል ከሆኑ ከራሺያ ጋር የሚኖራቸው ግኑኝነት ጦርነትን በማራገብ ሳይሆን፣ በዲፕሎማሲ ችግርችን መፍታት ይሆን ይሆናል የሚል ግምት አለ። ያም ሆነ ይህ የአውሮፓ መንግስታት፣ በተለይም የኔቶ (NATO) ዋና ጸሀፊና የጀርመን መከላከያ ምኒስተር ከፍተኛ መደናገጥ እንደሚታይባቸው እንመለከታለን። በተለይም ራሺያ የጦር መሳሪያዎችዋን በጣም ውስብስብ ካደረገች ወዲህና፣ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ታንክ ካመረተችና እንደS-400 የሚባለውን ተንቀሳቃሽ የሆነ ከሁሉም አየር ጋር የሚስማማ የረጅም ርቀት የሚጓዝ በመሬትና በአየር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተዋጊ ጀቶችን የሚያሳድደውና፣ በተለይም ደግሞ የሚተኮሱ ፈንጂዎችን የሚያከሽፍ መሳሪያ ሰርታ ከተከለች ወዲህ የአውሮፓ መንግስታትም ሆነ አሜሪካ በፍርሃት ውስጥ ይገኛሉ። ራሺያን በቀላሉ ሊቋቋሙ እንደማይችሉ ለመገንዘብ ችለዋል። አሁን ደግም መጪው ፕሬዚደንት የተናገሩትን የውጪ ፖሊሲያቸውን ተግባራዊ ካደረጉ የኔቶ አላስፈላጊነት የበለጠ ግልጽ እየሆነ ሊመጣ ይችላል። ይህ ጉዳይ ግን ወደፊት የሚታይ ነው። የአሜሪካን የውስጥ ኢንስቲቱሽኖች፣ ፔንታጎን፣ ሲአይኤና ሌሎችም ወደ አስራስምንት የሚጠጉ የስለላ ድርጅቶና፣ እንዲሁም ኮንግረሱን በተመራጩ ብዛት የሚመሩት የሪፓብሊካን ፓርቲ አባላትና የአሜሪካን ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በቀላሉ መፈናፈኛ ላይሰጧቸው ይችላሉ።
ወደ ውስጥ ፖለቲካቸው ስንመጣ በተለይም ካለፈቃድ የሚኖረው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ፍርሃት እንደለቀቁ ይታወቃል። ሰሞኑን እንደሰማነው ወንጀለኛ ተብለው የሚታወቁ እስከ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ አገር ስዎችን፣ በተለይም ከሜክሲኮና ከተቀሩት የማዕከለኛውና የላቲን አሜሪካን አገሮች የመጡ ሰዎችን እንደሚያባርሩ ተናግረዋል። በተረፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን ለተመለከተ የዕገዳ ፖሊሲ (Protectionist Policy) እንደሚከተሉና የኢንፍራስትራክቸር ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ይህንን ፕሮጀክታቸውን እንዴት አድርገው ፋይናንስ እንደሚያደርጉ ግን ግልጽ አይደለም። የቀረጡን መጠን ክ35% በመቶ ወደ 15% ዝቅ የሚያደርጉ ከሆነ መንግስት በቀረጥ አማካይነት የሚያገኘው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ይላል ማለት ነው። በሌላ ወግን ግን አጠቃላዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው የኔዎ-ሊበራል ወይም ሌላ ይሁን የሚታወቅ ነገር የለም።
ያም ሆነ የፕሬዚደንቱን የወደፊት ፖሊሲ ከአሁኑ አፍን ሞልቶ እንደዚህ ይሆናል ብሎ መናገር በፍጹም አይቻልም። አንድ ማለት የሚቻለው ነገር በአሜሪካን ምድር የበለጠ ዲሞክራሲና ሰላም አይሰፍንም። ያለው ስርዓትም የበለጠ ይጠናከራል እንጂ በመላላት በመንግስት መኪናና በተለያዩ ኢንስቲቱሽኖች ዘንድ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሊንሸራሸር በፍጹም አይችልም። የአሜሪካኑ የኮርፖሬት ዴሞክራሲ የበለጠ ግፊት በማድረግ ሁኔታው ለሱ እንዲያመች ያደርጋል። ስርዓቱ ስር የሰደደና ዲሞክራሲንና ስላምን በማይፈልጉ ኃይሎች የተከበበና የተወጠረ በመሆኑ የአሜሪካን ህዝብ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚወድቅ መገመቱ ከባድ አይሆንም። በሌላ አነጋገር ምርጫ ተካሄደ አልተካሄደ በሰፊው ህዝብ ህይወት ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይህን ያህልም አይደለም። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ኢምፔሪያሊዝም ሆኖ ይቆያል ማለት ነው። ጦርነትን ከማካሄድና አገሮችን ከማዳከም ባህርይው ሊላቀቅ በፍጹም አይችልም።
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ታህሳስ 14፣ 2016
fekadubekele@gmx.de
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply