• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ይድረስ ለሰብአ ትግራይ

January 24, 2019 08:16 pm by Editor Leave a Comment

1) በመጀመሪያ ራሴን ላስተዋውቅ፤ የተወለድሁት አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው፤ ዘመኑም 1922 ዓ. ም. ነው፤ የአገዛዝ የመንግሥት ለውጥ የተደረገበት ዘመን ነበር፤ አባቴ አቶ ወልደ ማርያም እንዳለ (ከአንኮበር፣ ሸዋ)፣ እናቴ ወይዘሮ ይመኙሻል ዘውዴ (ከየጁ፣ ወሎ) ናቸው፤ ሚስቴ የነበረችው በአባትዋ ሸዋ (መርሐቤቴ) በእናትዋ ትግራይ (አድዋ፣ እንትጮ) ነች።

በሥራዬ አብዛኛው ዕድሜዬ ያለፈው በአስተማሪነት ነው፤ መጀመሪያ በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት፣ በኋላ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ከዚያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሳስተምር ነበር፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ በፓርላማ ተመርጬ ለአንድ ዓመት ያህል በመርማሪ ኮሚስዮን ሠርቻለሁ፤ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤን አቋቁሜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ሰብአዊ መብቶች ለማስተማር ሞክሬአለሁ፤ የመጨረሻ ሥራ የምለው በቅንጅት የፖሊቲካ ፓርቲ አባልነት ነው፤ ከዚያ በኋላ በመጻፍና በማሳተም ቆይቻለሁ፤

2) ከትግራይ ጋር የተዋወቅሁት በ1951 ነው፤ ክፉ ዘመን ነበረ፤ ገና ዕድሜዬ ሠላሳ ሳይሞላ በትግራይ የተመለከትሁት ስቃይና መከራ ልቤን ሰንጥቆ የገባ ነበር፤ በአገሬ በኢትዮጵያ፣ በወገኖቼ በኢትዮጵያውያን ላይ የተጫነውን አገዛዝና ግፈኛነነቱን የተረዳሁበትና ከማናቸውም አገዛዛ ጋር በተቃውሞ ለመቆም የወሰንሁበት ዓመት ነበር፤ ያን ሁኔታ አይቼ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለቀስሁበት ዓመት ነበር፤ በችጋር ለተጠቃው ሰብአ ትግራይ መፍትሔ ልዑል ራስ ሥዩም ለትግራይ አውራጃዎች በሙሉ በየቀኑ ጸሎት እንዲደረግ አዝዘው ነበር፤ አገዛዙ ከጊዜው የዓለም ሁኔታ ጋር መራራቁን የተገነዘብሁበት ዓመት ነበር፤ ሁለት የትምህርት ቤት ጓደኞቼን (ነፍሱን ይማረውና) መንገሻ ገብረ ሕይወትንና ኃይለ ሥላሴ በላይን አግኝቻቸው ያየሁትን አይተዋል፤ በዚያን ጊዜ ትግራይ አገሬ ነበር፤ የሰብአ ትግራይ ስቃይ የኔም ስቃይ ነበር፤ በሰብአ ትግራይ ላይ የደረሰው ችጋር የኢትዮጵያ ነበር፤ ስለዚህ የኔም ችጋር ሆኖ ተሰማኝ፤ በሕይወቴ ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ በመሳፍንትና መኳንንት ቤት እየዞርሁ ደጅ ጠናሁ፤ በዚያን ጊዜ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ “እኔን ትግሬ ስለሆነ ነው ይሉኛልና ተወኝ” ብለውኛል።

3) ከሀያ አምስትና ከሠላሳ ዓመታት በኋላ በጉዳዩ ላይ ሁለት መጽሐፎችን (Rural Vulnerability to Famine in Ethiopia: 1958—1977. Suffering Under God s Environment: A Vertical Study of the Predicament of Peasants in North-Central Ethiopia) እስክጽፍ ድረስ ችግሩ ከአእምሮዬም ከልቤም አልወጣም ነበር፤ ትግራይን ከአክሱም ጽዮንና ከያሬድ ለይቼ አላይም፤ ኤርትራን ከደብረ ቢዘንና ከዘርአይ ደረስ ለይቼ አላይም፤ የኔ ኢትዮጵያዊነት የሚፈልቀው ከነዚህ ምንጮች ነው፤ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ወያኔና ሻዕቢያ እነዚህን ምንጮች ለማደፍረስ ሞክረዋል፤ በተለይ በአለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያ በገዛ ልጆችዋ በጣም ደምታለች፤ ጥቂት ልጆችዋ በባዕድ ፍልስፍና ተመርዘው ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ለመመረዝ ተደራጅተው ፍቅርን በጦር መሣሪያ፣ ኢትዮጵያዊነትን በዘር ለውጠው የታሪክ ቅርሳችንን ሊያሳጡን ሞክረው ነበር።

4) የምንጮቹን ጥራት ለመጠበቅ አዲስ ትግል ተጀምሯል፤ በፍቅርና ይቅር ለእግዚአብሄር በመባባል በሰላማዊ መንገድ ኢትዮጵያን ለማደስ አዲስ ትውልድ ተነሥቷል፤ ይህ ትውልድ ድምጽና የፖሊቲካ ኃይል ያገኘው ወያኔ ከሥልጣን ከመገለሉ በኋላ ነው፤ ከሥልጣን (ከአድራጊ-ፈጣሪነት) የወረዱት የወያኔ ባለሥልጣኖች የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው በአለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያውያን (ሰብአ ትግራይን ጨምሮ) ላይ የደረሰውን ግፍ ሰብአ ትግራይ ሰርዘውታል ማለት ነው ወይስ የተፈጸመው ግፍ በጎሣ ሚዛን ታይቶ ተናቀ የሚሰረዝም የሚናቅም አይደለም፤ በዚያው በትግራይ ውስጥ ብዙ ግፍ እንደተፈጸመ የሚመሰክሩ የትግራይ ተወላጆች ሞልተዋል።

5) ግፍንና ግፈኛን ለማውገዝ የግፍ ተቀባዩ ወገን መሆን አስፈላጊ አይደለም፤ አእምሮና ኅሊና ያለው ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፤ ዛሬ የሰው ልጅ እንኳን ለሰውና ለእንስሳም በጣም የሚቀረቆርበትና ዘብ የሚያቆምበት ጊዜ ደርሰናል፤ ሰብአ ትግራይ እንዴት ከዚህ ውጭ ይሆናሉ? በአለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ግፍ እንደሚካሄድ ሰብአ ትግራይ አላዩም አልሰሙም ለማለት ይቸግራል፤ በሌላ በኩል በወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ሰብአ ትግራይ በሙሉ ተጠቃሚዎች ነበሩ የሚል ሐሜት አለ፤ ስለዚህም የግፍ አሳላፊዎች እንጂ የግፍ ተቀባዮች አልነበሩም የሚባለው ልክ ነው ልንል ነው፤ በበኩሌ ይህንን የመጨረሻውን አስተያየት ለመቀበል በጣም ያዳግተኛል፤ ለማንኛውም ሰብአ ትግራይ በቅርቡ እውነተኛ መልሱን እንደሚሰጡን እተማመናለሁ።

6) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣኖች ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው ሳይጠበቅላቸው በአስከፊ ሁኔታ እየተጨፈጨፉ አልቀዋል፤ የደርግ አባሎች በፈጸሙት ግፍ ተከስሰውና ተከራክረው ተፈረደባቸው፤ በምሕረት ወጡ፤ አሁን ደግሞ የወያኔ ባለሥልጣኖች ተራ ሆነ፤ የወያኔ ተራ ሲደረስ ትግሬነታቸው ተነሣ፤ ሁሉም የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው ከተከሰሱበት ወንጀል አንዱ ይመስለኛል፤ ወያኔ የሥልጣን መሰላሉን ለመውጣት ትግሬነትን መሣሪያ አድርጎ እንደተጠቀመበት እውነት ነው፤ አሁን መውረድ ግዴታ ሲሆን የወጡበትን መሰላል መካድ አይቻልም፤ የወያኔ ባለሥልጣኖች ከአለፉት ሁለት አገዛዞች የሚለዩት በወያኔ ዘረኛነት ብቻ ይመስለኛል፤ ስለዚህም ዛሬ ለፍርድ የሚፈለጉት ትግሬዎች በመሆናቸው አይደለም፤ የሚፈለጉት ትግሬነትን የዘረኛነት ሥልጣን መሠረት አድርገው ፈጽመዋል በተባሉት ወንጀሎች ነው፤ ትግሬነት ከወያኔ ወንጀል ውጭ ነው፤ ፍርዱ በሥርዓት ከተካሄደ ከወያኔ ባለሥልጣኖች ጋር በወንጀል ተያይዘው የሚቆሙ የሌሎች ጎሣዎች አባሎች ይኖራሉ፤ የነሱ ድርሻ በፍርድ ካልታየ የዘር አድልዎ ተፈጸመ ለማለት እንችላለን፤ ይህ አድልዎ ሐቅ ቢሆንም የወያኔን ባለሥልጣኖች ወንጀል ወደትግሬነት አይለውጠውም፤ ስለማይለውጠውም አይሰርዘውም፤ ወንጀለኛነት ከትግሬነት ተለይቶ ብቻውን ይቆማል፤

7) ሰብአ ትግራይ አክሱም ጽዮንን አቅፎ የወንጀል ምሽግ መሆን አይችልም፤ ሰብአ ትግራይ አክሱም ጽዮን የዕርቅና ይቅር የመባባል መንፈሳዊ ኃይል እንጂ የወንጀለኞች ምሽግ እንደማትሆን ያውቃሉ፤ በኢትዮጵያውያን መሀከል አለመግባባት ሲከሰት በሰላማዊ መንገድ በንግግርና በክርክር፣ በውይይትና በምክክር መፍትሔ ማግኘት ከከፍተኛ ጥፋትና ደም መፋሰስ እንደሚያድን ይታመናል፤ ስለዚህም የሰብአ ትግራይ ምርጫ ከወንጀል ተነጥሎ ከአክሱም ጽዮን ጋር መቆም ነው።

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ታኅሣሥ 2011

(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የኦሮሞ ልሂቃንና ፖለቲከኞች በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን “የዘር ማጥፋት” ወንጀል እንዲያወግዙት አብን ጠየቀ July 6, 2022 01:38 pm
  • “አማራን ኦሮሚያ ውስጥ የመግደል እና የመጨፍጨፍ እቅድ የኦነግ ሳይሆን የኦሮሚያ ብልጽግና ነው” አቶ ሃንጋሳ July 6, 2022 01:53 am
  • “በኢትዮጵያዊያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሀገሪቱን ማተራመስ አለብን” አይማን አብድልአዚዝ ግብጻዊው ፖለቲከኛ July 5, 2022 12:57 pm
  • ባልደራስ የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣል ሊጠየቅ ይገባዋል ተባለ July 1, 2022 09:23 am
  • “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ቴዲ አፍሮ June 29, 2022 03:30 am
  • “የእኔን ልጆችና የልጅ ልጆች (22ቱንም) የቀበርኩት እኔ ነኝ” አቶ መሀመድ የሱፍ ከምዕራብ ወለጋ June 28, 2022 01:07 pm
  • የገዳ ሥርዓት እና የኦሮሞ ገዢ መደብ June 20, 2022 11:34 pm
  • “የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው” ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል June 12, 2022 07:09 pm
  • የሰሜን ምዕራብ ዕዝና የአማራ ልዩ ኃይል ተከዜ ክፍለ ጦር ዕውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው June 12, 2022 06:21 pm
  • ሀገር በቀል ባህላዊ የግጭት አፈታቶችን በተገቢው በመጠቀም ዘላቂ እርቅና ሰላምን ማምጣት ይቻላል June 12, 2022 05:40 pm
  • የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በገረጂና በቀበና ያስገነባቸውን የመኖሪያ አፓርትመንቶች አስመረቀ June 12, 2022 05:35 pm
  • በኦነግ ሸኔ ፈርሶ የነበረውና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀመረ June 10, 2022 09:13 am
  • ጃዋር በዳውድ ኢብሣ ቀይ መስመር ተሰመረለት June 8, 2022 12:59 pm
  • ወልቃይት: ቢመረንም ለመዋጥና ራሳችንን ለመመልከት እንሞክር June 8, 2022 11:53 am
  • እብድ ይሻለዋል እንጂ አይድንም፤ ሐጂ ጃዋር አሁን ለምን ብቅ አለ? June 8, 2022 05:59 am
  • ሕዝብ ድምፅ የነፈጋቸው “ፓርቲዎች” የሽግግር መንግሥት ይቋቋም አሉ June 7, 2022 01:11 am
  • “አድጌ እንደናንተ መሆን እፈልጋለሁ” June 5, 2022 06:58 pm
  • በሳምንት ለ100 ያህል ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ሥራ ጀመረ May 30, 2022 02:20 am
  • የጥቁር አንበሳ ዕጩ መኮንኖች (ካዴቶች) ተመረቁ May 29, 2022 04:01 pm
  • “ኢትዮጵያን መንካት አይቻልም!!” በሚል ቁጭት ነው እየሠራን ያለነው May 29, 2022 01:04 pm
  • “ከሞፈርና ቀንበር ወደ ትራክተር” በሚል መርህ ለአማራ ገበሬዎች የግብርና ሜካናይዜሽን ተሰጠ May 29, 2022 02:02 am
  • ኢትዮ 360 “የወያኔ፣ የጁንታ ሚዲያ ነው” – ባለከዘራው ጄኔራል May 27, 2022 02:51 am
  • “እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ የሚያጣሉን ፖለቲከኞች ናቸው” የአማራ ወዳጃቸውን አደራ ቤት የመለሱ የቅማንት ተወላጅ May 27, 2022 01:40 am
  • ትግራይን አገር እናደርጋለን፤ “በውይይት እና በጦርነት” ሁሉንም ጉዳይ እንቋጫለን – የወንበዴው መሪ ደብረጽዮን May 26, 2022 09:18 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2022 · Goolgule