ዶ/ር ፍቅሬ በ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” መጽሐፉ አዲስ እሳት ለኵሶልናል። እሳቱ ባጭሩ፣ ሁሉም የሚስማማውን ታሪክ ይጻፍ የሚል ነው። ቍጥራቸውና ማንነታቸው ያልታወቀ አወዳሾቹ፣ “ሐቀኛ የኦሮሞ ልጅ የኢትዮጵያ ልጅ” “የመከራ ቀን ደራሽ” “የመከራ ቀን ልጅ” “የታሪክና የፍቅር አባት” “የኢትዮጵያ መድን” “የህዝብ እርቅ አባት” “አስታራቂ” “የኢትዮጵያ ቤዛ” “ነብይ” ብለውታል። ሙገሳው የለመደበት “ካብ ካብ፣ ጣል ጣል” ባህላችን ነው ብለን እንለፈው።
አንዳንድ “ምሑራን” ጭሱ አፍኗቸው መስኮት ለመክፈት ይሯሯጣሉ። አንዳንዶች የጎሳ ክልል መደብዘዝ የሥልጣን ወንበር እንዳያሳጣቸው ሠግተው። ሌሎች በአገር ወዳድነት። አንዳንዶችም ያልተፈጠረ ንጹሕ ጎሳ በስውር የሚያውጁ ናቸው። ከኢትዮጵያ መንደር ውጭ ማሰብ የተሳናቸው፤ በምድር ዙሪያ የሕዝቦች አሠፋፈር፣ መፍለስና መተካካት፤ መገፋፋትና ባህል መወራረስ የከረመ እውነት መሆኑ አልዋጥ ያላቸው ናቸው። ሕዝብ ካነሳሳልን እሳቱ ይሻለናል ያሉ አሉ፤ እሳቱን በፈለጉት ሰዓት ማዳፈን የሚችሉ መስሎአቸዋል። በእሳት መጫወት የታሪክ ዐመድ እንደሚያስታቅፍ ያልገባቸው ናቸው።
ጎሠኛ ክልል ያቆረፈደው እንደ እሳት እራት ወላፈኑን ከብቦ “ከከፋፋይ ታሪክ የሚያቀራርበን ልብ ወለድ” ይሻለናል እያለ ነው። ከሚመርር እውነት “ልብ ወለድ” ይመረጥ? ሁሉም ራሱን እያወደሰ ሌላውን እያንኳሰሰ እውነቱን ላለመጋፈጥ ሽሽት ይዟል። “ከፋፋይ ታሪክ” = ኦሮምያ በአማራ፣ ደቡብ በትግራይ ጉዳይ አያገባውም መባሉ ነው። “ከፋፋይ”፣ እኔ ካልኩት ውጭ ሌላው ሁሉ ስሕተት ነው ነው። “ከፋፋይ፣” እኔ ብቻ ተበዳይ ነኝ ነው። እያንዳንዱ ራሱንና ሌላውን አጕድሎ ስለ መዘነ መፍትሔውም የሳተ ሆነ። እነሆ፣ “ከከፋፋይ ታሪክ የሚያቀራርብ ልብ ወለድ” ተመረጠ። የሠርቶ አደሩ የበላይነት ተመረጠ፤ የጎሳ ፌደራሊዝም ተመረጠ፤ ቅድስት ኢትዮጵያ ተመረጠ። በተነቃነቀ ጥርስ ቆሎ እንደ መቆርጠም ሆነ። በሌላ አነጋገር፣ ከሁለት ጎባጣ አናሳውን አምጣ። ቀና ጠፍቶ ጎባጣ መምረጥ ግን የታሪክ ኃፍረት መሆን ነው። በሃምሳ ዓመት ጉዞአችን ሩቅ አሳቢ የአስተሳሰብ ለውጥ ወይም እድገት አለማሳየታችን ለምን ይመስለናል? ዙፋን ለመገልበጥ የጎሳ ፖለቲካ የለኮሱ ያልበሰሉ ያልተሞከሩ ወጣት ምሑራን፣ የአገር መሪነትን ሲይዙ የተዳፈነውን እሳት እንደ ቆሰቆሱ አንርሳ።
ዶ/ር ፍቅሬ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” ጎጃም ነው ይለናል። ከአባይ ማዶ ገዳም ተገኘ በሚለን ሠነድ መሠረት ሁለቱ ጎሳዎች በአባትና በአያት አንድ ናቸው። አዳምና ሄዋን የተፈጠሩት ጎጃም፣ ዳሞትና ጣና አካባቢ ነው። ሲነሽጠው ሁላችንንም አሳፍሮ ወስዶ ቅድስቲቱ ከተማ ያራግፈናል። “ኤደንን ከሚያጠጡ አራት ወንዞች ውስጥ አባይ የምንለው ነው ኤፌሶን የሚባለው። በኦፌር ወርቅ ዙሪያ የሚዞር መሆኑ ተፅፏል። በኔ ድምዳሜ፣ የኤፌሶን ወንዝ የአሁኑ ዋቢ ሸበሌ ነው። ጤግሮስና ኤፈራጥስ ደግሞ ጊዮን ራሱ ጥንት ሜዲትራኒያን ባህር ይገባ ነበር። ድሮ ሜድትራኒያን ‘ኪቲ’ ይባል ነበር። ጥንት ጊዮን ወንዝ ሜድትራኒያን ሲደርስ ተራራ ስለነበር ተጋጭቶ ይመለስ ነበር። ከዚያ ነው መሬት ተነቃንቆ፣ ቦታው ተቆራርጦ አሁን ወዳለበት ኢራቅ የሄደው እንጂ አካባቢው እዚሁ ነበር።” ካበዱ አይቀር እንዲያ ጨርቅ መጣል ነው! በሌላ አነጋገር፣ መጽሐፈ ዘፍጥረት [ብሉይ] አፈታሪክ ስለሆነ ምሑራዊና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን አፍርሶ ሁሉም የሻውን አፈታሪክ መቀፍቀፍ ይችላል ነው። አሁን እዚህ መዘርዘር የማያሻንን ድምፀቶችን በማመሳሰልና በማያያዝ “ማራ” አማራ ነው ይለናል። ልኩ ለጠፋበት፣ ሁሉ ልክ ሲሆን። ራስን መካብና ሌላውን ማንኳሰስ፣ ዘረኛነትና የአብሮነት ጠንቅ ነው። ዶ/ር ፍቅሬና አወዳሾቹ የሚቃወሙትን “ከፋፋይ” ታሪክ በሌላ መልኩ እየደገሙት እንደ ሆነ አላስተዋሉም። ይልቅ ከጥንት በተቀበልነው “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” [ዘፍጥረት 1:27] በሚለው የፈጣሪ ቃል ብንጸና ይኸ ሁሉ አሣር ባልገጠመን!
ዶ/ር ፍቅሬ የሚያደርገውን የማያውቅ እንዳይመስለን። ገጣሚና ጸሐፌ-ተውኔት እንደ መሆኑ፤ ይበልጡኑ አብዮተኛ ትውልድና አገር ወዳድ። ፈጠራ ሙያው ሆኖ የሥነ-ሐተታ አማልክትን ልብና ቀልብ የመስረቅ ምሥጢር የተገነዘበ የሊተራቱር ሊቅ ነው። ጆሴፍ ካምበልን ያስታውሰናል። ካምበል፣ አፈ-ታሪክ፣ ልብ ለማሸፈት፣ ሰው ምኞቱን ተንተርሶ እንዲያልም ፍቱን መሳሪያ እንደ ሆነ፤ የታሪክ ጭብጥ ባይኖረውም የማሳመን ኃይሉ እሙን ነው ብሎናል። ጥቁር አሜሪካዊውን ሞሌፊ አሳንቴን ያስታውሰናል። ሞሌፊ [ነጭ] ግሪኮች [ከጥቁር] ግብጽ አፍሪካ ሠርቀው እንጂ በሥልጣኔ አይቀድሙንም ይላል። የነጮችን የታሪክ አጻጻፍ ግድፈት ሲያጎላ ሳያስበው ራሱ በተበተበው ገመድ ተጠልፎ ወድቋል። ዶ/ር ፍቅሬም ሲሰብከን “ኢትዮጵያ የሚለው ከግሪክ ቃል የመጣ ነው የሚለው ውሸት ነው። ይሄን አጣርቻለሁ። [ሄሮዶቱስ ለመኖሩ አጣርቶ ይሆን?] በነሱ መዝገበ ቃላት ውስጥ ይሄ ቃል የለም። ‘ፊቱ የተቃጠለ’ የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ኢትዮጵያ የሚለውን ሳይሆን ሌላ ትርጉም ነው የሚኖረው። ግሪኮቹ ከኛው ሰምተው ነው መልሠው ኢትዮጵያ ያሉን። እኛ ከነሱ በፊት ነበርን እንጂ እነሱ ከኛ በፊት አልነበሩም፤ ስማችንን ሊያወጡልን አይችሉም” ይለናል። ለመሳቅ እንኳ የሚቸግር አካሄድና ድምዳሜ ነው።
ፒተር መንዝ በ “ሂስትሪ ኤንድ ምት[ስ]”፣ ማህበረሰብ “ታሪክ ከተጻፈ በኋላም” እንኳ አዲስ የምኞት ታሪክና ያልተኖረበት ዓለም ይፈጥራል ይለናል። ወደ ፈጠራ ዓለም በመንጋጋት ሃብታምና ደኃ አንድ መሆናቸው፣ ሰውን ማጥመድ በምኞቱ በኩል መሆኑን ያስረዳል። የስድሳ ስድስቱ አብዮትና የሰማንያ ሦስቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በመሠረታቸው የምኞት ጉዞዎች ናቸው።
ዶ/ር ፍቅሬ የምርምር ውጤቶችን ወደ ጎን አድርጎ ሁሉን “ሀ” ብሎ መመርመር ይሻል። ታሪካዊ መረጃዎች አለመሟላታቸው ግድ አይሰጠውም። መጽሐፉን “እውነተኛው ታሪክ” ብሎ የሰየመው የሳሳውን መረጃ ለማለባበስና ሌላው ሁሉ ውሸት ነው ለማሰኘት ነው። በኤስያን አፌርስ መጽሔት [ጥር 2002 ዓ.ም] ተጠይቆ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የቊራን አምላክ አንድ፤ ነቢያቱ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ኢየሱስ፣ መሐመድ የጸለዩት ለአንድ አምላክ ነው ብሎናል። ሁሉ ኃይማኖት አንድ ይሁን ለሚሉ የዶ/ር ፍቅሬ ምላሽ ጥያቄ አይፈጥር ይሆናል። በኢየሱስና በመሐመድ ማንነትና ትምህርት ላይ ግን ይህን መሳይ ስህተት መፈጸም ከሞራላዊና ምሑራዊ ስነ ምግባር መጕደል ነው። በዚህ ሳያበቃ፣ ኢየሱስ ከ22 እስከ 25 ዓመቱ ድረስ በኢትዮጵያ ኖሯል ይለናል። የግፍና የዓመጽ መቀፍቀፊያም እንደ ሆነች ተዘንግቶ፣ ምድራችን ቅድስት፣ ህዝቦቿም የእግዚአብሔር ምርጦች ናቸው ለሚሉ ምኞተ ብዙኃን፣ ምኞታቸው እንደ ያዘላቸው እንጂ መሠረተ ቢስ ስብከት መሆኑ ግድ አይሰጣቸውም።
ዶ/ር ፍቅሬ እንዴት እንዲህ ሊሳካለት ቻለ? ዋናው ምክንያት ማኅበራዊና ስነ ልቦናዊ ክፍተት መኖሩ ነው። አገር በቋንቋ መካለሉ፣ የትምህርት ጥራት መውደቁ፤ የዜጎች ተሳትፎ መመንመኑ። ትውልድ የቅርብ ዓመታት ታሪኩን እንኳ አጥርቶ አለማወቁና ከዘመኑ ጋር ለማነጻጸር አለመብቃቱ። ክፍተቱ በከፊል ሆን ተብሎ፣ በከፊል ተቆርቋሪ በመጥፋቱ የተከሰተ ነው። አርስጣጣሊስ በአንደኛው ትዝብቱ፣ ክፍተት በተገኘበት በተገኘው ይሞ-ላ-ል ብሏል። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ነው ነገሩ። ሌላው ምክንያት፣ ብዙኃኑ በገዛ አገሩ ሙሉ ተሳትፎ እንዳይኖረው መደረጉ፤ የኦሮሞና አማራ ሕዝብ ቊጥር 70 ሚሊዮን ያክል መድረሱ [በ100 ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት ሲሰላ]። ሕዝብ ብሶቱን ማንሸራሸርያ ማግኘቱ። መንግሥት መጽሐፉን ማገዱ። የምሑራን ስንፍናና አድር ባይነት፤ ስንፍናቸው ለስምብቻ ምሑራን መድረክ ማቀዳጀቱ። ስለ አገራችንና ስለ ሕዝቦቿ በትምህርት ቤት፣ በመንግሥት አፈቀላጤዎች፣ በክልል ፖለቲከኞችና ውጭ አገር በተበተነው ተቀናቃኝ የተዘራው እንክርዳድ የእውነትን ረኃብ ለማስታገስ አለመቻሉ። የሥጋና የመንፈስ ራብ መመሳሰሉ ለዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ መግነን ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።
ማህበራዊ ድንቍርናና ውዥንብር መበርከቱ። ቤተ ክርስቲያን መስቀል ከሰማይ ወረደ ብላ ቀኝና ግራውን የማያውቅ ምእመን ስትበዘብዝ። የናይጄሪያ ጠበል ሕዝብ ላይ ረጭቶ ፍራንክ ሲለቅም። ሥርዓተ አልበኛ ነብያት ምኞቱን እንዲነግሩት ለሚሻ ሁሉ ቀምመው ትንቢት ሲነሰንሱ። ለማበጣበጥ የተፈጠሩ ጥያቄዎች እንደ ጎን ውጋት በየሁኔታው መቆስቆሳቸው፦ አማራ ማለት አማርኛ ተናጋሪው ነው? አማራ የሚባል ጎሳ አለ? ሁሉ ጎሳ እኵል ነው? “እኵል” ማለት ምን ማለት ነው? ትግሬ ከጤግሮስ ኢራቅ ተገኘ? እውን [ገዳ] ዲሞክራሲ ነው? ከግሪኮች ዲሞክራሲ ይቀድማል? ኦሮሞ መጤ ነው? ሌላው ከየት መጣ? ወዘተ።
ፖል ካርትሌጅና ዳያን ክላይን፣ የጥንት ግሪካውያን ዲሞክራሲ፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በምዕራቡ ዓለም ከተከሰተው በብዙ መልኩ የተጻረረ ነው ብለውናል። ሁሉም የየራሱን እውነት ይዞ የሌላውን ያንቋሽሻል። ሌላውን ሳያከበር ልከበር ይላል። የቋንቋ ፖሊሲ ለምን በእንጥልጥል ተተወ? ሁለት “ሕጋዊ” ፓትርያርክ ለምን አስፈለገ? ዛቻ፦ የትግራይ ሪፐብሊክ ዛቻ። የኦሮሞ ሪፐብሊክ ዛቻ። እነዚህ ክፍተቶች ለዶ/ር ፍቅሬ እሳት መለኮሻ ጉልቻ ፈጥረውለታል። ትውልዱ የተነገረው ታሪክ ውሸት መሆኑን ሲያውቅ በደርግ፣ በኃይለሥላሴና በዚህ ዘመን ካሳየው ዐመጽ ውጭ ምን እንዲያደርግ ይጠበቃል? ወይስ ጊዜው ሲደርስ በአፈ-ሙዝ ማዳፈን ይቻላል? ስንቱን እናንሳ። ባጭሩ፣ ግርግር ለሌባ ያመቻል። ሌባው ግን ሁሌ ሌላኛው ነው።
መፍትሔውስ ምንድነው? መፍትሔው፦ ብርሃን የበራላቸው ማታለል ያቁሙ። ለግራና ለቀኝ የማይል እውነት ያስተምሩ። ብርሃንን ከእንቅብ በታች ማኖር ብርሃንን መቀማት፣ ለጨለማ መንበርከክ እንደ ሆነ ይወቁ። ያልተማሩ ይማሩ። አርነት የሚሹ ከእውነት አይሽሹ።
ምትኩ አዲሱ (info@ethiopianchurch.org)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Wogene says
መረሳት የሌለበት መሠረታዊው ጉዳይ፤ ዶር. ፍቅሬ የጻፈው ሁሉ ዋናው ምንጩ መሪራስ አማን አገኘሁት በሚሉት ሰነድ ላይ ነው። ይህን ሰነድ ደግሞ እስካሁን ድረስ ከርሳቸው ሌላ ያየው የለም። እንደዚህ ላለ ጥንታዊ ሊሆን ስለሚችል ሰነድ የማረጋገጫ፤ የታወቀ ሥልት አለ። በዚያ ሳይንሳዊ መስፈርትና አሳማኝ መንገድ ካልተረጋገጠ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ለምሳሌ፤ Dead Sea Scrolls እንዲሁም The Shroud of Turin የተሰኙት ግኝቶች የተመረመሩት በዚያ ሥልት ነው።
በተጨማሪ ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ፤ መሪራስ አማን እንደሚሉት፤ ሰነዱ በታሪካዊ ቅርስ ደረጃ ከተረጋገጠ ዋጋው በሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት እንደሚሆን የታወቀ ነው። እንዲሁም፤ ለምርመራው የሚያስፈልገው፤ መሪራስ አማን እንደሚያስቡት የርሳቸውን ባለቤትነት በሚያሰጋ መንገድ ሳይሆን ከብራናው ጥቂት ብጣሽ ለሚመለከታቸው በሙያው ብቃት ላላቸው በማቅረብ ብቻ ነው።
መሪራስ አማንና ዶር. ፍቅሬ እንዳሉት ተገኘ በተባለው ሰነድ ውስጥ የተጠቀሰው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እድሜው 22-25 በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያ እንደነበረ የሚያትተው ከተረጋገጠ የዓለምን ታሪክና የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክትም እንደ ገና የሚያስመለክት ሊሆን ስለሚችል፤ መሪራስ አማን ሰነዱን ለራሳቸው፤ ለኢትዮጵያም ለዓለምም ጥቅም ሲሉ በባለሙያዎች ቢያረጋግጡ ያስከብራቸዋል። አለበለዚያ ጥርጥር ላይ ይጥላቸዋል!
በለው! says
ታሪክ…አፈታሪክ…ሁሉን ውድ የሚያደርግ ልብ ወልድ!?ወይንስ ለብውልቅ?
»> ወደድንም ጠላን የአዳምና ሄዋን ዘር እግዝሐብሔር በአምሳሉ እስትንፋስ የፈጠረን ነን።ይህ ኦሮሞና አማራ ዘር ብቻ ሳይሆን የሰውን ሁሉ ልጅ እንግዲህ በህወአት/ኢህአዴግ በመፈቃቀርና በመፈቃቀድ የተፈጠሩትን ጨምሮ የቀድሞውን ‘ሰፊ’ የአሁኑን ቦርቃቃ(ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችንም)ጨምሮ መሆን አለበት። በእኛ የተፈጠራችሁ! ለእኛ የምትኖሩ! ያለእኛ የምትበታተኑና የምትጠፉ የተባሉት መጽሐፍ ሳይጻፍላቸው የዘር ምንጫቸው ሳይጠና ከሁሉም መገፋት የለባቸውም። አንተ ጎጃም የተከሰትክና ለመራሪስ አማን በላይ በሳጥን ታሪክ ያስቀመጥክ ሳትታይ ያሳመንክ ሆይ፤ ወይ ውረድ ወይ ፍረድ!!
************************!
ሊ/ጠበብት ጌታቸው ኅይሌ በመራራስ አማን በላይ የመጽሐፍ ግኝት ትችት….
….ታሪኩ የተመሠረተውም በመጽሐፍ መደብሮች በሚገኙ የአማርኛ እና የእንግሊዝኛ ሥነ-ጽሑፎች ላይ ነው። ከእነዚህ ጽሑፎች ሱዳን ኑብያ፣ ጀበል ኑባ በተባለ ስፍራ በአንድ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ አጠገብ ተቀብረው መሪራስ አማን በላይ በተባለ ወጣት መናኝ ከ50 ዓመት በፊት የተገኙና አጥረውና ወደ አማርኛ ተተርጉመው “መጽሐፈ፡ ሱባኤ” እና “የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ” በሚሉ ርዕሶች የታተሙ ጥንታውያን የግዕዝ ብራና ጥቅሎች ይገኙባቸዋል። እነዚህ የኢትዮጵያ ብራና ጥቅሎች እስራኤል አገር ኩምራን በተባለ ቦታ በአንድ ዋሻ ውስጥ በእረኞች ከተገኙት የሙት ባሕር ብራና ጥቅሎች ጋራ ተመሳሳይነት አላቸው። እነሱ፣ እነዚህና ሌሎችም መጻሕፍት ከስድስት ዓመት በፊት ድንገት እጄ ገቡ።
“መቼም ቢሆን አንድን ምሁር ችሎታው በአንድ መስክ ሥሉጥ ካደረገው በሌሎች መስኮች ላይም (ከመ፡ ዘሥልጣን፡ ቦ፡) ሥሉጥ እንደማያደርገው ለፕሮፌሰር ፍቅሬ የተደበቀ ነገር አይመስለኝም። ሁኔታው ይኼ ሁኖ ሳለ፥ እስካሁን ያለውን የታሪክ ምንጭ በታሪክ ጸሐፊዎች ደረጃ ምሁር ሆኖ ሳያጠናቸው፥ መቅድሙ ውስጥ፥ “ይህ ፅሑፍ ሀተታ እስካሁን የነበሩና የተለመዱ አንዳንድ መሰረታዊ ግንዛቤዎችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ አዲስ ታሪክ ነው” ይለናል።
******************!
የምትኩ አዲሱ ዝርዝር ማብራሪያ ስለሌለው ጠቅላላ ሀሳቡን ለመረዳት አስቸጋሪ ነው።
” ዶ/ር ፍቅሬም ሲሰብከን “ኢትዮጵያ የሚለው ከግሪክ ቃል የመጣ ነው የሚለው ውሸት ነው። ይሄን አጣርቻለሁ። [ሄሮዶቱስ ለመኖሩ አጣርቶ ይሆን?] በነሱ መዝገበ ቃላት ውስጥ ይሄ ቃል የለም። ‘ፊቱ የተቃጠለ’ የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ኢትዮጵያ የሚለውን ሳይሆን ሌላ ትርጉም ነው የሚኖረው። ግሪኮቹ ከኛው ሰምተው ነው መልሠው ኢትዮጵያ ያሉን። እኛ ከነሱ በፊት ነበርን እንጂ እነሱ ከኛ በፊት አልነበሩም፤ ስማችንን ሊያወጡልን አይችሉም” ይለናል። ለመሳቅ እንኳ የሚቸግር አካሄድና ድምዳሜ ነው።”
*** ግለሰቡ እንደቋንቋው ተናጋሪ ያስረዳ»> ግሪኮች እንዲህ ተብለው ተምረዋል” በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት ሰው አለ እነሱም እኛ ግሪኮችና እኛን ግሪኮችን ለመሆን የሚፈልጉ ናቸው”ይላሉ ለመጽሐፍና ለአውሮፓ ቅርብ ናቸውና ብዙ አድማጭና ተከታይ አግኝተዋል፡ እኛም ፩ሺህ ዓመት ከዓለም መገለላችን ለእነሱ ተፎካካሪም ተወዳዳሪም መሆን አልቻልንም…’ኢትዮፒከስ’ በጥንቱ የዐለም ካርታ ላይ የአፍሪካ መጠሪያ እንደነበር ማስረጃ አለን። የመንግስት የንጉስ መዋቅር እኛ እንዳለን ስለፍትሕ ሌላውን ማስርጃ ትተን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ግሪክ አምባሳደር አናታሲዩ ማኩ “እነኝህ ሰዎች ሃይማኖትና ፍትሕን ተክነውበታል ሲል በሐረር ከተማ ሰው ስለገደለው ግሪካዊ (ኪሪቲኮስ) ፍርድና የቀ/ኅይልስላሴ ቢሮ ይግባኝ አቤቱታ እንዴት እንደነበር በደንብ ጽፎታል የቀድሞ መጠሪያዋ አብሲኒያ የአሁኗ ስሟ ኢትዮጵያ ይበል እንጂ እኛ ስሟን የሰጠናት ሀገር አላለም።
** ግሪክ…ግሪካዊ..ግሪክኛ…. ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያዊ…ኢትዮጵያዊኛ የሚል ስለሌለ ‘ኢትዮፒክ’ ይሉታል። ለመሆኑ ኢትዮጲክ የሚሉት አማርኛን ነው ግዕዝን? ግዕዝን አታንሱባቸው ‘ባልዮ ኢሊኒካ’ (የጥንቱ ግሪኪኛ) ሲነሳ ጉድ ይፈላል። ቀጥሎ ‘ፓሊዮ ኢሜሮሊጊቲስ’ የቀድሞው ቀን አቆጣጠር ሲመጣ ደግሞ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያን አቆጣጠር የሚከተሉ ግሪኮች መኖራቸውን ይታዘቧል። አቶ አማረ አፈለ ቢሻው “ኢትዮጵያ የሰው ዘርና የምርጥ ዘር መገኛ” በሚለው መጽሐፋቸው በስተመጨረሻ ገጽ ላይ ፊደላቶቻችን ሳይቀር መዘረፋቸውን በዓመተ ምሕረት እያወዳደሩ አስቀምጠውታልና ማየት ይቻላል።….ልቦለድ (ሚት) ሲነሳ አንድ አባባል ነበር። ግሪኮች ባሕር ባለበት እንደመንጎዳቸው(ዲያስፖራ) ናቸው የሕዝብ ቁጥራቸው ግማሽ በላይ ተሰዷልና…ሜጋ አሌክሳንድረስ ወደ ሕንድ እንደሄደው ሁሉ አፍሪካንም ገዝቷል የሚሉም ህልመኞች አይጠፉም ግብጽን ግን ቤታቸው አድርገው ኖረዋል እግረመንገዳቸውን ሱዳን ሲደረሱ ግን የመጀመሪያ ጥቁር ሕዝብ ያልሰለጠነ፡ልብስ አልባ፡ ዘላን፡የተበታተኑ እረኞች መንግስት አልባ (ዓረቢ) ባሪያ ሲሉም ተሳልቀዋል… ምድረገነት ኢትዮጵያ ሲደርሱ ለምለም፡የራሱ ቋንቋ ያለው፡ የሰለጠነ ባለወታደር መንግስት፡በሕግ የሚተዳደር ንጉስም እንዳለው ሲረዱ “እነዚህ በፀሐይ ብዛት ፊታቸው ተቃጠለ(ጠቆረ) እንጂ እንደኛው ሰው ናቸው”አሉ ይቺው እንግዲህ ግሪኮች ያወጡልን ሥም ሆነ ማለት ነው!? ለመሆኑ’ ካሜኖ’ የተቃጠለ(ካይከ..ተቃጠለ)… ‘ፕሮሶፖ’ ፊት(ሙትራ)… ሆኖ ሳለ (ካሜኖ ፕሮሶፖ-የተቃጠለ ፊት) እንዳይሆን …አቲዮ…(የተቃጠለ) ኦፕስ…(ፊት) ከሆነ ዶ/ር ፍቅሬ እንደገጣጠሙት ሊ/ጠ ጳወሎስ ሚልኪያስ ብዙ ማስረጃ እንደሚጠይቁት ከሆነና ሊ/ጠበብት ጌታቸው ኅይሌ እንድሚተነትኑት ይህ የግሪኮች ስልት እዚህም ሰርቷል… “ጎሣ “ጐሥዐ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ነው” ይላል። ልክ አይደለም፤ በሁለት ቋንቋዎች ውስጥ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ቃላት ሁሉ ተመሳሳይ ሥርና ትርጉም እንዳላቸው የሚያውቅ የፊሎሎጂ ዕውቀት ያለው ሰው ብቻ ነው። አለበለዚያ የእንግሊዝኛውን grocery ከአማርኛው “ጥሮ ግሮ ሠሪ” ጋር ያዛምዳቸዋል። ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ቃላት ሲያጋጥሙት ሳያዛምድ አይለቃቸውም። ይኼ folk’s etymology “ሕዝባዊ የቃላት ሥር ትንተና” ይባላል። “Magician” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ማጂ ከሚለው ከኦሮምኛ ስም የተወሰደ ነው ይላል። ሁለቱ እንዴት ተገናኝተው ይህ ሊሆን እንደተቻለ የሚያሳይ ተጨማሪ ተረት ያስፈልጋል።“ስለ ደሸት ስንናገር ምንም እንኳን ተረት ቢመስልም ሐቅ ስለሆነውና ለየት ስለሚለው ውልደቱ [= ልደቱ] መናገር ጠቃሚ ነው። የቤላም (በልዓም) የልጅ ልጅ የሆነችው እናቱ ነቢይትዋ ሼምሼል መነኩሲት ነበረች። ከወንድ እርቃ በግዮን አካባቢ በገዳምም ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት ትመራ ነበር። አንድ ቀን በግዮን ወንዝ ሳይሆን አይቀርም ገላዋን ስትታጠብ የወንድ ዘር በማሕፀንዋ ዘልቆ ገባና ደሼት (ደሴት) ተፀነሰ። … ይህ የሆነው ከሦስት ሺ አምስት መቶ ዓመት በፊት ስለሆነ ማስረጃው ሁሉ ቢጠፋ አያስገርምም” ይላል። ኦሮሞዎች ከባሕር ወጣን የሚሉት፥ የኦሮሞና የአማራ አባት ደሼት (ደሴት) እውሀ ውስጥ ስለተፀነሰ ነው ማለት ነው። ግሩም የሚቶሎጂ ትረካ ነው። ግን ከታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። ነቢዩ በልዓም ይኖር የነበረው ሜሶፖታሚያ (ዒራቅ) ነበር። ሚቶሎጂውን ለማሟላት ሼምሼልን ከዚያ አንሥቶ ጎጃም ላይ የጣላትን የነፋስ ሰረገላ ፈጥሮ ታሪኩ ቢጨመርለት ጥሩ ነበር።
“ዓላማ ዘዴን ያጸድቀዋል” እንዲሉ፥ “ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ዓላማው አማሮችና ኦሮሞች በአንድ አገር ውስጥ በወንድማማችነትና በሰላም እንዲኖሩ ምክንያት ለመስጠት ስለሆነ በምንም ዘዴ ቢጠቀም ክፋት አናይበትም” የሚሉ አሉ። እንዳፋቸው ያድርግላቸው።” ሲሉ ይሞግታሉ እንደ እኔ…..’ፈያ’ ከሚለው ጉራጊኛ ‘ፋይን’ ተወስዷል ብዬ እንግሊዞችን ጉዳቸውን ላውጣው ይሆን! ማን ከማን ያንሳል? ሁ ማይነስ ሁ? መሆኑ ነው።
*** ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ እናፈርሳታለን ለሚሏት ኢትዮጵያ ተጨንቀዋል ተጠበዋል…አንድ አደለንም የራሳችን ባሕሌ፡ ቋንቋዬ፡ መሬቴ፡ ሕዝቤ ለሚሉ አዝነዋል ግን ይህ ማርገቢያ ቢሆን ፈውስ ነውን!? ሙከራቸው ግን እጅግ የሚገርምና የሚደነቅ ነው፡የመራሪስ አማን በላይ ሽምደዳና ሽምጠጣ በፍጹም አልተመቸኝም አሁንም የአንድ ታላቅ ጥንታዊ ሀገር ታሪክ ነውና የጨዋ ደንብ ውይይቱ ይቀጥላል በለው! ከምሥጋና ጋር በቸር ይግጠመን።
ምትኩ says
ውድ በለው፣
የምትኩ አዲሱ ዝርዝር ማብራሪያ ስለሌለው ጠቅላላ ሀሳቡን ለመረዳት አስቸጋሪ ነው ስላልከው፣ ችግሩ የመጣው ትምህርተ ጥቅሱን አለቦታው ስለ ጨመርከው ነው። ያንተ፦ [”]ዶ/ር ፍቅሬም ሲሰብከን “ኢትዮጵያ የሚለው ከግሪክ ቃል የመጣ ነው የሚለው ውሸት ነው። ይሄን አጣርቻለሁ። [ሄሮዶቱስ ለመኖሩ አጣርቶ ይሆን?] በነሱ መዝገበ ቃላት ውስጥ ይሄ ቃል የለም። ‘ፊቱ የተቃጠለ’ የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ኢትዮጵያ የሚለውን ሳይሆን ሌላ ትርጉም ነው የሚኖረው። ግሪኮቹ ከኛው ሰምተው ነው መልሠው ኢትዮጵያ ያሉን። እኛ ከነሱ በፊት ነበርን እንጂ እነሱ ከኛ በፊት አልነበሩም፤ ስማችንን ሊያወጡልን አይችሉም” ይለናል። ለመሳቅ እንኳ የሚቸግር አካሄድና ድምዳሜ ነው።[”] = ከላይ ዋናውን ቅጂ ተመልከት።
በሁለቱ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። የኔ አነሳስ፣ ማህበራዊ ክፍተቶች መረጃ ለሌላቸው ጭፍን ድምዳሜዎች ዳርገውናል ለማለት ነው። “ከከፋፋይ ታሪክ የሚያቀራርበን ልብወለድ እንመርጣለን” መባሉን ነው። ሕዝቡን የማስተማር ኃላፊነታችንን ስለ ዘነጋን ይህ ሆነ ማለቴ ነው። የጻፍኩትን ቀስ ብለህ ብታነብ ጉዳዬ የዶ/ር ፍቅሬን በማስታከክ የገባንበትን ሰፋ ያለ የአስተሳሰብ ቀውስ ለመጠቆም ነው።
ዶ/ር ፍቅሬ ከሚጽፋቸው ብዙ ቁምነገሮች ጋር ችግር የለኝም። እንዲያውም ስለ ትጋቱና ጥረቱ የሚገባውን ምሥጋና ያገኘ አይመስለኝም። ችግሩ አሁን ባቀረበልን መጽሐፍ የመረጃው መሳሳትና የሚያስከትለውን ውጤት አለማጤኑ ነው። ሁለተኛው፣ የአገራችንን ሕዝብ የከፋፈለው ገዥው እንጂ ሕዝቡ አይደለም [ኃ/ሥላሴ ባላባትና ጭሰኛ/መሳፍንትና ደኃ። ደርግ በመደብ። ዛሬ በጎሳ]። በዓለም ዙሪያ የሕዝቦች ከአንድ ምንጭ መገኘት በሚታወቅበት ሰዓት እኛማ አብረን የኖርን የተጋባንና አብረን የሞትን ልዩነታችን መጕላቱ ለፓለቲከኞች እቅድ ካልሆነ እውነትነት የለውም። መሪራስን ሳይጠቅስ ይህን ታሪካዊ እውነት መተረክ ይቻላል ማለቴ ነው። ለማንኛውም ስለ አስተያየትህ አመሰግናለሁ። ብትፈቅድ ጥናትህን አስፋፍተህ ለአንደኛው ድረ ገጽ ብትልክ ብዙ ሰው ትጠቅማለህ።
በለው! says
>> ወንድም ምትኩ አዲስ…በአንድ ወቅት ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ መንገድ ላይ አንድ ጸጉሩን ያጎፈረ ባለሎቲ ወጣት በእንግሊዘኛ (BURNED FACE) በኢትዮጵያ ካርታ ላይ የተጻፈ ለብሶ ነበር። አልገባኝም! በሚቅጥለው የሠርግ ቀን ጭራሽ በአማርኛ ‘ፊቱ የተቃጠለ’ የሚል አየሁ ወዳጄን ምንድነው?ብዬ ጠየኩት በቀኝ የቆመው ጅግና ትንታኔውን አወረደው! የሰው ሠርግ መርዶ እንዳይሆን በደረቁ ውጬ ዝም!…ግርግር ተፈጥሮ አዳራሽ መግቢያ ላይ ስንገላገል ወዳጄ ትምህርቱ እንዴት ነበር? ብሎ ሳቁን ለቀቀው!…አልመለስኩም ጭራሽ ሳኩ!… ወዳጄም ወይ ሰው አለማወቅ እዚህ እኛን የመሳሰሉ ላይ ያፏጫል ለምዶ ነው አለኝ…አሁንም ዝም! ቦታ ከተያዘ በኋላ ሰሀኑን እንደተሸከመ መጣና ቅድም እንደጀመርኩልህ…ብሎ ወረደበት! እንኳንም ወሬ ማር ይመራል አሉ። አሁን በተራዬ ከምግብ ጋር ተስማሚ ነገሮችን አቀረብኩለት ከምግብ በኋላ በንግስቲቷ እንባ አጣጣማት የመጨረሻው ጥያቄ ግን ፎቶ ኮፒ ማድረግ ቢቻል አንተን እዚህ ማስቀረት ነበር አለኝ…ተልዕኮዬን ጨርሼ ፍቶ ኮፒ ሳልደረግ ተፈተለኩ….!በዚያው ዓመት ሊ/ጠ ማሞ ሙጬ በአቡጊዳ ድረ ገጽ ላይ ይህንኑ ጠቅሰውት ተግቢውን ተመሳሳይ መልስ የሰጠሁ ይመስለኛል።
ከምስጋና ጋር..ወደውይይታችን ለመግባት ያህል…
** የኔ አነሳስ፣ ማህበራዊ ክፍተቶች መረጃ ለሌላቸው ጭፍን ድምዳሜዎች ዳርገውናል ለማለት ነው።
___ ይቺ ጭፍን (ዕውር) ድጋፍና ድምዳሜ’ ትልቅ ነበር ትልቅ እንሆናለን!’ የሚለውን አጥፍቷል።ዛሬ መረጃና ማስረጃ አላስፈለገም አርዕስት ፈጥሮ ማስጮህ ማጯጯህ ማስጨብጭብን የተካኑ ሁሉ ክልላዊ ሚዲያን በቡድን ለጥቂቶች ጥቅም እንዲውል ከሰፊው ህዝብ ሰውረው ተቆጣጥረውታል።
**“ከከፋፋይ ታሪክ የሚያቀራርበን ልብወለድ እንመርጣለን” መባሉን ነው።
___ “አንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመገንባት” ሲባል በመፈቃቀድና በመፈቃቀር ለፈጣሪዎችህ ገባር ትሆናለህ ማለታቸው መሰለኝ…”ሁላችንም ወያናይት ነን!” ያሉት ማን ነበሩ? የትግራይ የሥራ ቋንቋ እንግሊዘኛ ይሁን ከሚሉ….እኔ የሚመስለኝን ለሕዝቤ ታሪክ ጻፍኩ ከሚሉ መምህር ገብረኪዳን ደስታን ያየ አዎን! ዶ/ር ፍቅሬ ከሚጽፋቸው ብዙ ቁምነገሮች ጋር ችግር የለኝም። እንዲያውም ስለ ትጋቱና ጥረቱ የሚገባውን ምሥጋና ያገኘ አይመስለኝም። ችግሩ አሁን ባቀረበልን መጽሐፍ የመረጃው መሳሳትና የሚያስከትለውን ውጤት አለማጤኑ ነው።(ያሰኛል) ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም!። ቢኖርም የአማራና የትግሬ ነው ዳቦና ጠላ…ዘፈንና የባሕል ልብሱ ነጠላና ጋቢ በግድ ተጭኖብናል የሚሉት ሲደመጥ እሰይ! ፐሮፌሶሬ፡ ዶክተሬ፡ኢንጂነሬ አለ የቸገረው።
**”… ሕዝቡን የማስተማር ኃላፊነታችንን ስለ ዘነጋን ይህ ሆነ ማለቴ ነው። የጻፍኩትን ቀስ ብለህ ብታነብ ጉዳዬ የዶ/ር ፍቅሬን በማስታከክ የገባንበትን ሰፋ ያለ የአስተሳሰብ ቀውስ ለመጠቆም ነው።
__” ወይ ባይ እንደጠሪው ነው” ለመማርና ማስተማር ፈቃደኛ መሪ አለን? ሥራዓቱ አስርፅበት ይላል እንጂ(ጥርነፋን ያስቧል) አንብቦ፡ ጠይቆ፡ ተሟግቶ፡ የራሱን ግላዊ ግንዛቤ ላይ እንዳይደርስ የባከነና የመከነ ትውልድ!? ተከልሏላ ምን ያያል? ልዩነታን ውበታችን! ይፎክራል። በማንነት ጥያቄ ተወናብዷል…እያንዳንዱ ሥርዓት የራሱ ጥልፋጥልፎች ቢኖሩትም እንዴት አንድ ኩታ አድርተን መሸመን አቃተን !?
___ ግሪኮች ከ፬፻ ዓመት የቱርክ ባርነት በኋላ ከጀርመን ጦርነት አገግመው ዛሬ የአውሮፓ አካል መሆን እስከቻሉበትና ደግመው የኢኮኖሚ ባርያ እስከደረሱበት ድረስም ከእኛ ባልተናነሰ የችግር ማጥ ገብተዋል። እኛ በአንድ የባሕር በር ሁለት ትውልድ ስናስበላ የውሃ ላይ መርከቦቻቸውን ቁጥር ሳያውቁ የሞቱም ዮናስስ አየር መንገድን ለሀገራቸው መቸር ላይ ደርሰዋል።
___ የሆነው ሁሉ ሆኖ ኢትዮጵያውያንን የምማፀነው ቢያንስ ግሪኮች የሚያከብሯትን ሀገርና የሚፈሩትን የኢትዮጵያ ሕዝብ እራሳችን ለራሳችን ኩራትና ክብር ልንሰጠው ይገባል!።አራት ነጥብ። የሥም አወጣጡን ትተን የመንግስት አወቃቀር፡ ፍትሕና ደግነታችን ባሻገር..የግብር አሰባሰብ ጅማሮ …የገንዘባችን ጥንካሬ በዶላር ዘመን ግሪክ (አቴንስ) በቀጥታ ግብይት ይፈጸምበት እንደነበር…ዲሞክራሲያችን የመንዝና ግሽን ምንጃር ቡልጋ…ተራሮች ቆመው ሰው መኖር ከጀመረ ዘመን አንስቶ ሴቶቻችን ለጉልጓሎ፡ አረም፡ አውድማ ሥራ ላይ፡ ጭፋሮ ላይ ‘ እግረጠባብ ሱሪ’ አድርገው በውጊያውም ተሰልፈው፡ ሰንቀው ባሎቻቸውን አበረታተዋል። በግሪክ ዴሞክራሲ ዛሬ በ፳፩ኛው ክ/ዘመን ሴት ሱሪ ማድረጓ ሀጢያት፡ የወንድ ሥራ መኪና መንዳት፡ በቢሮ ተቀጥሮ መሥራትን ይጸየፋሉ ሴትና ልጅ ወደ ጓዳ…?ይቺ ናት ጨዋታ! እኛን የሚቀድሙን ካርታቸው አውሮፓ መሸጎጡ እንጂ እንግሊዞች እንደሚሏቸው (ኋይት ትራሽ) ለማለት ኢትዮጵያዊነቴ ይይዘኛል ልበል? “ሰዶ ማሳደድ ሲያምርህ ሀገርህን በክልል ለውጥ” ሆነ እንጂ የቆጡን አወርድ ብለን መውደቃችን እንጂ… ጎበዝ ያልተነገረላቸው የተረሱ ፈላስፎች አሉን… ጥንታዊት ሀገር ሥንል ያረጀን ማለታችን የ፻ ዓመት ታሪክ መናፈቃችን አደለም በማግስቱ ሚሊኒየም ማክበር!? ግን እግዚኦ ወዲያና ወዲህ ሆነ በለው!(ወይ መኮርኮር…ምትኩ አዲሱ ባሉበት ሰላምታዬ ከምሥጋና ጋር ነው። በቸር ይግጠመን