ሀ. ትንቢት
አቶ መስፍን ስዩም “የትግሬ የበላይነት የሚለው ከጀመረ ቆይቷል” ካሉ በዃላ “የአለፉትን ሥርዓቶች አላነሳም፤ በዚያ ሥርዓት ውስጥ በዘውዱ፤ በደርጉ ሁሉም የተናቀ ነው። የአማራ አገዛዝ ተብሎ የሚወሰደው በስሙ ተነገደበት እንጂ ብዙሃኑ ጭቁን የአማራ ሕዝብ ከማንም ሕዝብ በታች ይኖር የነበረ ሕዝብ ነው።” አሉና የሚከተለውን ቀጠሉ፤
“የደርገ ሥርዓት ተገርስሶ ኢህአዴግ አዲስ አበባ የገባ ዕለት ……. ኢህአፓና መኢሶን እርስ በርሳቸው ሲናቆሩ የነበሩት፤ በጋራ ያሰባሰቡት ካናዳ ላይ ተሰብሰበው በሰጡት መግለጫ – ሰነዱን ልታገኙት ትችላላችሁ፤ የትግሬ የበላይነት፤ የቲፒኤልኤፍ ፋሺስታዊ አገዛዝ ከደርግ በላይ ግፈኛ ነው፤ ዘረኛ ነው፤ ይሄ መንግስት የሚመሰርተውን መንግስት አንቀበልም የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዳይቀበል፤ ተማጽነዋል። ተፋለሙት ብለው ተንቀሳቅሰዋል።” ምንጭ (ፌስ ቡክ)
ስለነጥቡ ቆየት ይበለኝና በቅድሚያ ስለ አቶ ስዩም መስፍን፤- ከወያኔ “ታላላቅ” ሰዎች መካከል በአካል ከማውቃቸው ሁለቱ አንዱ አቶ ስዩም መስፍን ናቸው። ከንግሥ በፊትም፤ ከንግሥ በዃላም አግኝቻቸዋለሁ። ወያኔ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በዃላና አቶ ስዩምም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው እንደተሾሙ፤ በውጭ የመጀመሪያ ሥራቸው የነበረው፤ የቀድሞውን መንግሥት ኢምባሲ ማጽዳት ስለነበር፤ በየኢምባሲው የነበሩ የቀድሞ ሹማምንት መካከል ብዙዎቹ፤ – እራሳቸውን በደንብ የሚያውቁት – ወያኔ ከሎንዶን “ኮንፈረንስ” በዃላ ወደ ኢትዮጵያ ለሚያደርገው ጉዞ ሻንጣውን መቀርቀብ ሲጀምር፤ ኢምባሲውን እየለቀቁ ጥግ ጥጋቸውን ይዘዋል፤ ሌላው ጉዱን አያለሁ ብሎ እዚያው ቢቆይም ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ የምትለዋ ደብዳቤ ስትደርሰው ሞኝሕን ፈልግ እያለ እንደሚሆን ሆኗል።
አቶ ስዩም በዚሁ ጊዜ በጀርመን አገር የሰሯቸው አንዳንድ የማስታውሳቸው በጎ የሚመስሉ ነገሮች፤- አንደኛ/ በደርጉ ጊዜ ሌላ ቀርቶ በኢትዮጵያ ፓስፖርት የሚኖር ኢትዮጵያዊ እንኳን ወደ ሃገሩ ለመሄድ ሲፈልግ፤ ተጨማሪ የኢምባሲው የድጋፍ መረጃ ከሌለው መጓዝ አይችልም ነበር። ይህ እንዲቋረጥ አድርገዋል። ይህ ብቻም አይደል፤ የስደተኛ ወረቀት ያለውንና በዚያ ወረቀት ደግሞ ወደትውልድ አገሩ መጓዝ የማይችለውን ሊሴ ፓሴ የሚባለውን መረጃ በገፍ በመበተን፤ – ወያኔ የሚገፍፋትን ገንዘብም ከግንዛቤ ሳያስገባ እንዳልሆነ ግልጽ ይሁንና – እናቱ፤ አባቱ፤ አክስቱ አጎቱ .. ወዘተ የናፈቁት ሁሉ በየአቅጣጫው እያቆራረጠ ወደ አገሩ በመግባት ናፍቆቱን እንዲወጣ አደረጉት።
ሌላ ለየት የሚል ደግሞ፤- አንድ የፖለቲካ ስሪቱ ኢሕአፓ የነበረ የትግራይ ተወላጅን የሚመለከት ነው። ሰውየው ለቲፒኤልኤፍ ያለው ጥላቻ እኔ እስተማውቀው ድረስ ድንበር የለሽ ነው። ለድርጅቱ (ለኢሕአፓ) ካለው የጠበቀ ፍቅር/ታማኝነት የተነሳ በዚያ ዘመን የተቃውሞ ሰልፍ እነደኮሜዲያኑ ክብበው ገዳ ሚስት ነፈሰጡር ሆና ሰላማዊ ሰልፍ አማረኝ አንዳለችው ሁሉ፤ ሴቶች ተመሳሳይ ጥያቄ ቢያቀርቡ ለነሱ ያህል እንኳን የሚሆን ሰላማዊ ሰልፍ በማይታይበት ጊዜ፤ ይሄ የትግራይ ሰው የውሻ ምላስ የምታክል ካርቶን ላይ ኢፒአርፒ ለዘለዓለም ይኑር የሚል መፈክር ጽፎ እሷን ተሸክሞ ብቻውን ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣ ሰው ነበር። በዚህ አድራጎቱ በጣም አድናቂዎቹም ነበርን።
አቶ ስዩም ኢምባሲውን በማከረባበት ላይ እንዳሉ፤ ይህ ሰው በጠና በሽታ ይታመምና ይሞታል። እሳቸውም የዚህ ሰው የቀብር ስነስርዓት በኢንባሲው ሃላፊነት እንዲከናወን ያዝዛሉ፤ በዚሁም መሰረት ይፈጸማል። ይህ አፈጻጸማቸው በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያሳደረው ሁለት ስሜት ነበር፤ የመጀመሪያው/ አቶ ስዩም/ወያኔ ሃይለኛ ተቃዋሚያቸው ቢሆንም እንኳን ቂም ሳይዙ የዚህን ዓይነት አክብሮት ለዜጋቸው በማድረጋቸው፤ ሁለተኛው/ ይህ አፈጻጸማቸው በሌሎች ስለሬሳቸው መውደቂያ ብዙ በሚጨነቁ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያሳደረው ከፍተኛ ጉጉት ነበር። አንዳንዶች ፈጣሪያቸው ሞታቸውን እዚሁ አገር እንዲያደርግላቸው የልመና ጸሎት ማድረግ የጀመሩም ነበሩ። ምክንያቱም በባዕድ አገር ሞቶ በኢንባሲ አማካይነት በሚመራ የቀብር ስነስርዓት መቀበር እንደቀላል የሚታይ ባለመሆኑ።
ታዲያ ምን ይሆናል! ይህ ሁለተኛው ቀብርን በተመለከተ የተፈጸም መልካም ተግባር የመጀመሪያውም የመጨረሻው ትርዕይት ከሟቹ ጋር አብሮ እነደተቀበረ ሁሉ፤ ከዚያ በዃላ ብዙ ሰው ሞቷል፤ አንድም ቀን ያ ስነሥርዓት አልተደገመም። ያ ሞቶ ቀብሩ ያገኝ ስለነበረው ክብር ትልቅ ተስፋ የነበረው ወገን ሰለጉዳዩ አለመደገምና ለምንስ ለዚያ ሰው ብቻ ተደረገ የሚለውን ጥያቄ እያነሳ በመጣል ሃሜት በሃሜት ሆኖ ከረመ። ስለሃሜቱ አይነት ተነስቼ አላድክማችሁ ወደ ዋናው ጉደይ ልመለስ፤
አቶ መስፍን ኢሕአፓና መኢሶን ካናዳ ተሰብስበው ተናገሩ ስላሉት ጉዳይ፤ ምናልባት የተምታታባቸው ነገር አለ ብዬ ስላሰብኩ፤ የሚከተለውን ልበል፤ ወያኔ በግንቦት 20 83 አ.ም. አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት በሃምሌ 82 ገደማ ይመስለኛል፤ ካናዳ ቶሮነቶ አንድ ጉባዔ ተጠርቶ ነበር፤ ይህ ጉባዔም የተጠራው በኢህአፓና በኢድዩ (በራስ መንገሻ ስዩም የሚመራው) ሲሆን፤ ለዚህ ጉባዔ ከተጋበዙት መካከል የትገሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር፤ የኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ግንባርና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ነበሩ። ከነሱ መካከል የኤርትራው ሕዝብ ነጻነት ግንባርና የኦሮሞው ነጻነት ግንባር ጉዳዩ እኛን የሚመለከት አይደለም፤ የኢትዮጵያውያን ነው በማለት አንካፈልም ሲሉ፤ የትገሬው ህዝብ ነጻነት ግንባር ለመካፈል ፈቀደኝነቱን ገልጾ፤ ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔውን ለማስታወቅ ጊዜ እንዲሰጠው ይጠይቃል፤ ከነገ ከዛሬ መልስ ይሰጣል እየተባለ በተደጋጋሚም ማሳሰቢያ እየደረሰው፤ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ሲያጓትት በመቆየቱ፤ ጉባዔው በተገኙት ተሳታፊዎች እንዲደረግ ተወሰነ፤ ከዚያም አንድ ቀን ጉባዔው ተጀምሮ በመካሄድ ላይ እንዳለ፤ የጉባዔው ጊዜ እንዲራዘምለት ጥያቄ ያቀርባል፤ የማይመስል ጥያቄ ሆነና ጉባዔው በተጀመረው መልክ ተካሂዶ የሚቀጥለው ጉባዔ አሜረካ አገር እንዲሆን ተወስኖ ነተሳ። ከዚህ ውጭ በካናዳ ኢሕአፓና መኢሶን በጋራ ያደረጉት ስብሰባ ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም በተጠራውም ስብሰባ ላይ ጋበዡ የኢዲዩው ራስ መንገሻ ስዩም የወያኔን የበላይነትና ዘረኛነትን ኮንነው ተናገሩ ማለት፤ እንኳን ለሰው ለአማልክትም ግራ የሚያጋባ ክስተት ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ግን አቶ ስዩም አለ ያሉትን ሰነድ ይፋ ያደርጉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
እስከዚያው ግን ሰነዱን እየጠበቅሁም ቢሆን፤ የሳቸውን ሃቀኝነት ላለመጠራጠርም በመፈለግ፤ ነገሩ ተብሏል በሚለው ላይ ልቆይና ከተባለ ብዬ ልሂድበት፤ አቶ ስዩም፤ በእርግጥም ዛሬ እትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ፤ የበላይነቱም፤ ዘረኝነቱም፤ ክፋቱም፤ ፋሺስትነቱም ፍጥጥ ብለው እያየናቸው ስለሆነ፤ ተናገሩ የተባሉት ድርጅቶች በጣም አርቆ አሳቢና መጭውን ጊዜ በሚገባ የገመገሙ ትንቢተኞች ነበሩ ቢባል ከዕውነቱ ያልራቀ መሆኑን መገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም።
ከወያኔው መወንጀያዎች ውስጥ “የትገሬ የበላይነት” የምትለዋ መቃናት የሚያስፈልጋት ሆና ስላገኘዃት እሷን ላቃና፤ ከሁሉ አስቀድመን ልንስማማበት የሚገባ ዋና ነገር አለ። ይኸውም የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር የባርነት አገዛዝ ስር የምትገኝ መሆኗ ነው። በዚህ ላይ ስምምነት እስካለ፤ ከ6 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የትግሬ ሕዝብ የበላይ ሆኖአል ለማለት የሚያስችል መረጃ ማግኘት የምንችልበት ምንም መንገድ ስለሌለን፤ ይህንን ሕዝብ እንደሕዝብ በወንጀል ሥራ መክሰስ ቀርቶ መጠርጠርም አንችልም። በዚሁ ትይዩ ግን የትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር አባላትና ደጋፊዎች ከገደል ስር እንደእጭ የፈሉ ሳይሆኑ፤ ትግርኛ ተናጋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች አብራክ የተከፈሉ ስለሆኑ ትግሬዎች ናቸው። ዘፋኙ ወዳጁን ሲያሞግስ ” እናትና አባትሽ ምንኛ ታደሉ፤ በጭለማ ዘርተው አንቺን ያበቀሉ” እንዳለው እኛስ እነዚህን የወያኔ ጉጅሌዎች ያፈራውን ማህጸን ብንርገም? ያስጨንቃል! ያም ሆነ ይህ የትግሬ የበላይነት ስንል የእነዚህን ትግሬዎች በአገዛዙ ውስጥ ያላቸውን ሚና በማገናዘብ የነሱን የበላይነት ማለታችን እንደሆነ ሰፊው የትግራይ ሕዝብ እንደሚረዳ ተስፋ አደርጋለሁ። እሱም እንደሌላው ኢትዮጵያዊ በእነሱ ጭቆና ስር እየዳሸቀ መኖሩ ግልጽ ነው። ፈጥኖም ሆኖ ዘግይቶ ሰልፉን ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ማድረጉ የማይቀር ነው።
የበላይነቱ የመጀመሪያው መገለጫ፤- የኢህአዴግን አፈጣጠር ልብ እንበልና የወያኔ ጥፍጥፎች፤- 1. ኦፒዲዎ የተቋቋመው ሻቢያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሚያካሂደው ጦርነት ማርኮ ድንጋይ ያስፈልጣቸው ከነበሩት ወታደሮች መካከል የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑትን ወያኔ ወስዶ ያቋቋመው እንደሆነ፤ አስር ዓመት ያህል ከገዙን በሁዋላ፤ አልጋ እገለብጣለሁ ብለው ጉድ ጉድ ሲሉ ተገኝተው ዛሬ የወያኔ ተፈናቃይ ሆነው የሚገኙት አቶ ገብሩ አስራት በመጽህፋቸው ተርከውልናል። አቶ ገብሩ አስራት የደበቁን አንድ ነገር ግን አለ። የኸውም ሻቢያ የጉልበት ሰራተኞቹን መቼም በነጻ ይሰጣል ብሎ ማሰብ ስለማይቻል ሰዎቹን ለመግዛት ምን ያህል እንደተከፈለ አልነገሩንም። ምናልባት በምርኮ መሻሻጥ ወንጀል ተጠያቂ ከመሆን ለመዳን ይሆን? የተገዙ ምርኮኞች መሆናቸው ግን አያጠራጥርም። 2. ኢፒዲኤም – እናት ኢሕአፓ ጣፊያ እያለች የምትጠራው – ደግሞ ወያኔ እራሱ ከኢሕአፓ ጋር ሲዋጋ የማረካቸው ድብልቅልቃቸው የወጣ የዛሬው “ባሕታዊ” ታምራት ላይኔን፤ እስከዛሬም በአገልጋይነታቸው ደልበው የሚገኙትን በረከት ስምኦንን፤ ተፈራ ዋልዋን ወዘተ… በመሳሰሉ ድኩማን የተቋቋመ ሲሆን፤ 3. ከደቡቡ አካባቢ ወያኔ የጠፈጠፈው ድርጀት ደግሞ፤ ወያኔ አንተ የዚህ አካባቢ ሰው ትመስላለህ እያለ ከመንገድ ላይ እየጎተተ ባሰባሰባቸው ሰዎች የተቋቋመ እንደሆነም እናአውቃለን።
ታዲያ አቶ ስዩም እንዲያው ከህሊናዎ ጋር ታረቅ ብለው፤ ረጋ ባለ መንፈስ አጢነው ሲያዩት፤ ምርኮኛ ማራኪው አድርግ፤ ፍጠር ከሚለው ውጭ የራሱ ስብዕና ኖሮት፤ ለሕሊናው ተገዢ ሆኖ ይሰራል ብለው ሊያሳምኑን እንደማይሞክሩ እርግጠኛ ነኝ። ከሞከሩ የምርኮኛን ተፈጥራዊ መብት እየተፈታተኑት ነው ማለት ነው። ክቡር አምባሳደር፤ የነሱ አገልግሎት አንደኛ/ ወያኔን በኢትዮጵያዊነት ካባ መጀቦን፤ ሁለተኛ/ የየመጡበትን ዘውግ ለወያኔ ተገዢ እንዲሆን እያዘጋጁ መስዋዕት ከማቅረብ በስተቀር ምንም እርባና ያላቸው እንዳልሆኑ እኛ ብቻ ሳንሆን፤ ዓለም የሚያውቀው ስለሆነ፤ በማራኪና በተማራኪ መካከል ያለው ግንኙነት የጌታና የሎሌ ግንኙነት መሆኑን ለማስተባበል ቢሞከር፤ ከዕውነት ጋር ከመላተም በስተቀር ትርፍ የለውም። ሌላም ሌላም በዝርዝር ሊቀርቡ የሚችሉ መገለጫዎችን ማቅረብ ባይገድም፤ ምንጩ በሚገባ ከተያዘ በቂ ስለሚሆን፤ በዚህ ረድፍ ያለውን ከዚህ በላይ አላራዝመውም።
ለምን እንደደነቀሩት ምክንያቱ ባይገባኝም፤ ስለ አማራው ያነሱት “በስሙ ተነግዶበታል” የሚለው ቀልቤን ስቦታል። እኔ እሰከማውቀው እንግዲህ በአማራ ሕዝብ ስም የነገደው ወያኔ ነው። ንግዱ የተጠናቀቀውም ትርፍ በትርፍ በሆነ ውጤት መሆኑ አይካድም። የተጠቀማችሁበት የንግድ ምልከትም፤ “አማራ የጎሳዎች ሁሉ ጨቋኝ ጠላት፤ በተለይም ደግሞ ለትግሬ ሕዝብ አንድ ቁጥር ጠላት” የሚለውን ገጸ ባህርይ ሰጥታችሁ የትግራይ ገበሬ ይህንን ጠላቱን ለመምታት 60000 የሚሆን ወጣት ልጆቹን እንዲገብርላችሁ ማድረጋችሁን ደጋግማችሁ ስለምትነግሩን በሚገባ አጢነነዋል። በእውነትም ደግሞ በዚህ ዓይነት ጣላት ላይ ዓይኑን እንዲያተኩር ባታደርጉ ኖሮ፤ አሁን አላችሁበት ደረጃ መድረስ ቀርቶ እከሌ የሚባል ህልውና አይኖራችሁም ነበር። አቶ ስዩም ያማራ ገዥ መደብ ለማለትም የቃጣዎት እንደነበሩ ተገንዝቤ ስለነበር፤ የሚከተለውን ላስታውስ፤ የወያኔ መስራቾች ከአዲስ አባባ ዩኑቨርስቲ ትምሕርታችሁን አቋርጣችሁ ወደጫካ በገባችሁ ጊዜ እኮ በኢትዮጵያ የመደብ ትግሉ ተቀጣጥሎ የነበረበት ጊዜ ሲሆን፤ እናንተ ግን ዛሬ የመደብ ትግል ሳይሆን የዘውግ ጭቆናን መታገል ነው ብላችሁ አማራ የተባለውን ጨቋኛችሁን ለመታገል እንደነበር ይዘነጉታል?
ያም ሆነ ይህ ግን እንግዲህ ግንቦት 20. 83 ዓ.ም. ወያኔ አዲስ አበባ የገባ ዕለት ማታ ኢሕአፓና መኢሶን ካናዳ ላይ ሆነው በትንቢታቸው ያደረጉትን ጥቆማ በድጋሚ እያደነቅሁ፤ አቶ ስዩም መረጃውን ይፋ እንዲያደርጉት አደራ እያልኩ ከዚህ ርዕስ ወጥቻለሁ።
ለ. የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሁኔታ
- የሃገር ቤት እንቅስቃሴ፤- በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰሜን፤ በደቡብ፤ በምስራቅ፤ በምዕራብ፤ የሚካሄደው እንቅስቃሴ የየራስን ችግር እያነሱ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ወደ ችግርህ ችግሬ ነው ወደማለት መሸጋገሩን እየተመለከትን ነው። መበረታታት ያለበት ነው። ወያኔም ከቀደመው ይልቅ የዃለኛው የበለጠ ጤና የነሳው ስለሆነ፤ ይህንን ትግል ለማዝረክረክ የነፍስ ውጭ የነፍስ ግቢ ትንቅንቅ ይዟል።
ስለሆነም ታዲያ ችግርህ ችግሬ ነው የሚለው ተዋሕዶ ችግራችን አንድና አንድ ነው! እሱም የችግራችን ሁሉ ምንጭ የሆነው የወያኔ ሥርዓት ነው ወደሚለው በፍጥነት ተሸጋግሮ፤ አላማችን በጋራ ይህንን ምንጭ ማድረቅ ነው ብሎ እንዲነሳ ለማድረግ ፈጠን ያለ ትጋት መደረግ አለበት። በአንድ ጊዜ ብዙ ጥያቄዎችን አግተልትሎ መምጣጥ መቋረጥ አለበት። ለዚህ የሚሆን አንድ ምሳሌ፤- ከአረቡ ስፕሪኒግ የግብጹን እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል። እንደምናስታውሰው ሙባራቅ ጭንቅ ሲይዘው፤ ሕገመንግስት አሻሽላለሁ፤ እኔ ከእንግዲህ አልወዳደርም፤ ምክትል ፐሬዚዴንት ሾሜላችዃለሁ፤ ወዘተ… በማለት ያልቀባጠረው አልነበረም። ያ ሌት ተቀን ካይሮንና ሌሎች ከተሞችን ሲያጨናንቅ የነበረ ተቃዋሚ ሰልፈኛ መስማት የሚፈልጋት አንድ ቃል ብቻ “ከስልጣኔ ወርጃለሁ” የምትለዋን ስለነበር፤ ሙበራቅ እሷን እስኪተነፍስ ድረስ ሌላ ምንም ነገር አንሰማም ብሎ ንቅንቅ ሳይል ወጥሮ ያዘ። በመጨረሻም ከሙባራቅ ሊሰማ የሚፈልጋት ቃል ወጣች። ሰልፈኛው በዕልልታና በሆታ ታጅቦ ደስታውን ገለጠ። ሰልፉም ፍጻሜ አገኘ። ወያኔም ከድብደባው፤ ከእስሩ፤ ከግድያው በተጓዳኝ፤ ዛሬ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለማዝረክረክ አንዳንድ ማባበያዎች፤ ማታለያዎች፤ ለማድረግ እየሞከረ ነው። ስለወልቃይት የተጠየቀውን ትቶ ራስ ዳሸንን መልሻለሁ ይለናል፤ ላሊበላንም እንደዚሁ ትግራይ ውስጥ ተሳስቶ ዘልሎ ገብቶብኝ ነበር እያለ ነው። ለኦፒዲዎም በኦሮሚያ ያመጹብኝ ስራፈቶች ናቸው በማለት እነሱን አባብልበት ብሎ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር መድቤልሃለሁ ብሎአል፤ ለዚህ ሁሉ የወያኔ ማደናገሪያ! ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት፤ የአባይ ጸሃዬንም ብታፈርሱን ትፈራርሳላችሁ የምትለዋን ቅርሻት – ቅርሻት የምትለዋን ቃል ተበድሬ ነው – ላንተው ለጥፋትህ ትሁን በማለት፤ “የወያኔ ስርዓት ይውደም በሱ መቃብር ላይ ኢትዮጵያ ትለምልም!” የሚለውን ተክተን፤ ግብጾች እንዳደረጉት “የወያኔ ስርዓት ሳይወድም መመለስ የለም ብሎ ከተወጣ ምንም ይከፈል ምንም፤ የወያኔ ሥርዓት ይወገዳል። ታዲያ መረሳት የሌለበት የወያኔ ሥርዓት መወገድ ብቻውን በራሱ በቂ አለመሆኑ ሲሆን፤ በተወገደው ሥርዐት ላይ ለምልማ ለማየት በምንመኛት አንዲት ኢትዮጵያ ጥላ ስር ተሰባስቦ፤ የሚገዛን ሳይሆን የሚያስተዳድረን፤ የሚፈራ ሳይሆን የሚከበር፤ የሚያዝ ሳይሆን የሚታዘዝ መንግሥት እስክንመሰርት ድረስ ብቻ ዕድሜ የሚኖረው የሸግግር መንግሥት እናቋቁማለን በሚል መተማመኛ ከወዲሁ ተደግፎ ከተያዘ ብቻ ነው፤ የስርዓቱ መወገድ ፍሬያማ አቅጣጫ የሚይዘው። ባጭሩ ከወያኔ ሥርዓት መወገድ በዃላ ስለምትቀጥለዋ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ የወያኔን ሥርዓት ማስወገድ የሚል ፈረስ ጭኖ መጋለብ “ግማሹን ተላጭቶ ግማሹን ትቶ” እንዲሉ ይሆንና ወደሌላ አሳፋሪና አሳዘኝ ሁኔታ ውስጥ መዘፈቅን ያስከትላል።
- ለድርድር፤– ስለድርድር ጉዳይ ሰሞኑን ከየአቅጣጫው ድምጾች ይስተጋባሉ። እንደሚመስለኝ ድምጽ ከሚያሰሙት አንዳንዶቹ ወያኔውን አዳምጠውት የማያውቁ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሰምተውት እንዳልሰሙ ሆነው ያለፉት ይመስለኛል። ምክንያቱም እስቲ የ97ቱን ምርጫ እንመልከት፤ መለስ ዜናዊ ከተቃዋሚ ፓረቲዎች ጋር ለድርድር ተቀምጦ፤ አቅመ-ቢስ መሆናቸውን ካረጋገጠ በዃላ፤ “… እኛ (ማለት ኢህአዴግ) በደርግ ጊዜ እንዳደረግነው በረሃ ሄዳችሁ ከሕገመንግሥቱ ጥላ ስር ወጥታችሁ ትታገላላችሁ (ድፍረቱ ካላችሁ)፤ …” (የነጻነት ጎህ ሲቀድ – ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ግንቦት 1998 ገጽ 436) በማለት ነበር “ባለራዕዩ” መሪ ተደራዳሪዎቹን የሸኛቸው። ያ ጊዜም አልፎ የሚቀጥለው የ2002 ምረጫ ጊዜ ስለሥልጣን ማካፈል/መካፈል የሚል ወሬ በተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ምሁራንና በሌሎችም ተቋማት አካባቢ ሲነፍስ ያዳመጠው መለስ፤ የራሱን ጋዜጠኞች ሰብስቦ ስልጣን ማካፈል ስለሚባል አጉል ወሬ እየሰማሁ ነውና ለማንኛውም በዚህ ጉዳይ ላይ አቋሜ ምን እንደሆነ ጠይቁኝና ለሚቃዡት ሀሉ ላሳውቃቸው ብሎ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ የሚከተለው ነበር፤ “ስልጣን ካካፈልኩ እኮ የኔ ፐሮግራም (አብዮታዊ ዴሞክራሲ) ስራ ላይ አይውልም ማለት ነው። እኔ እንደዚህ ያለው ሙከራ ውስጥ አልገባም። ስሸነፍ (ስርዝ የኔ ነው) ጥዬ መሄድ ብቻ ነው።” ነበር ያለው።
ልብ በሉ፤ እነዚህ አቋሞች እስከዛሬም ጸንተው የቆዩ ናቸው። ምክንያቱም ራዕየ-አልባዎቹ እነደሳለኝ እንደሚነግሩን “የታላቁን መረያችንን ራዕይ ሳይበረዝ ሳይሸራረፍ እስራ ላይ እናውላለን” አያሉ ስለሆነ፤ ይህንን መገንዘብ ብዙ ድካም የሚጠይቅ አይመስለኝም። አንዳርጌ መስፈን “በሙት መንፈስ አገር ሲታመስ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሃፋቸው የሚተርኩት የነዚሁኑ ራዕይ-አላባ መሪዎች የሙት ራዕይ ተሸክመው እያደረሱብን ያለውን መከራ በማጤን ነው፡፡
ወያኔ ሲያቅተው ጥሎ መሄድ እንጂ አይደራደርም የሚለውን አጥብቄ የማምንበት መሆኑ ተጠብቆልኝ፤ ይህንን አቋሜን ላንዳፍታ ለስለስ ላድረገውና ድረድር ከሚሉት ጋር ልቀላቀል፤ መቼም ልምድና አሰራር እንደሚመሰክሩት፤ ሁለት ወገኖች ወደድርድር የሚመጡት፤ በመካከላቸው ያለውን ችግር ለመፍታት ሲሉ፤ አንዱ ሌላውን እጅ እንዲሰጥ የሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ሲያረጋግጡ ካልሆነ በስተቀር፤ የድርድር አምሮት ለመወጣት የሚያደርጉት እንዳልሆነ ሰው ሁሉ የሚስማማበት ይመስለኛል።
ብሎም ይህንን ሃቅ ጠብቀን የወያኔን ውሎና አዳር ስንቃኘው ምንድነው የምናየው? ዛሬ ወያኔ ተቃዋሚዎቹን፤ በመግረፍ፤ በማሰር፤ በመግደል፤ ከሃገር በማባረር ጥግ እያሲያዘ አገር እየገዛ እንደሚገኝ አይደለም? ጎላ ጎላ ያሉትን ግድያዎች እናንሳቸው እሰቲ ጋምቤላ ለግድያ በዘራቸው የተመረጡ ሰዎች ስምን በዝርዝር ይዞ ጨፈጨፈ፤ ሲዳማ ጥያቄ ያነሱትን በገፍ ጨፈጨፈ፤ በኦጋዴን ለህሊና የሚቀፍፍ ዘግናይ ጭፍጨፋ ፈጸመ፤ ከ97 ምርጫ ጋር በተያያዘ ድምጻችን ይከበር ብለው ሰልፍ የወጡን በመቶዎች የሚቀጠሩ ሰዎችን ጨፈጨፈ፤ ከጉራ ፈረዳ አማራ ንብረቱን ተነጥቆ ለዘመናት ከኖረበት መሬት ነቅሎ በግፍ ያባረራቸው የት እንደደረሱ የሚያውቅ አለ? ከቤኒሻንጉል ባንድ ጀንበር ከ5ሺ የሚበለጥ አማራ በግፍ ከኖረበት ተባሮ ምን ያህሉ እንደተመለሰ ባይታወቅም ንብረት አልባ ሆኖ፤ ህይወት ጭምር የጠፋበት ወንጀል ፈጸመ፤ በቅርቡ ደግሞ በኦሮሞውና በአማራው አካባቢ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ዜጎችንጨፈጨፈ፤ እየጨፈጨፈም ነው። ስንቱን ዘርዝሮ መጨረስ ይቻላል? ለመሆኑ ግን ወያኔ ይህንን ሁሉ በደል ፈጽሞና እየፈጸመም እያለ፤ ተጠያቂ ሆኖ ያውቃል?
ከዚህ ተጨማሪ የወያኔ ቧልት ደግሞ “ያይጥ ምስክሯ ደንቢጥ” እንዲሉ በየቦታው የሚፈጽመውን የግድያ ወንጀል እየተመለከተ አበጀህ የሚለው “የሰብአዊ መብት ኮሚሺን” የሚባል አቋቁሞ ሲቀልድብንም እያየን ነው። ታዲያ እነኝሕን የዘረዘርኳቸውን ሁሉ እያደረገ ተቀማጥሎ አገር የሚገዛን ሃይል ምን ጠብ ይልለታል ብለን ነው ወደድርድር የምንጠራው? እሱስ ምን ጠብ ይልልኛል ብሎ ያዳምጠናል? እንደኔ በዚህ ሁኔታ ወያኔን ለድርድር መጠየቅ፤ አልኩ ከማለት ያለፈ ዋጋ ያለው ጥሪ አይደለም። ጉዳት ግን አለው። በተለይ ባሁኑ ጊዜ ከሁለት ዓመት በፊት ዶ/ር መራራ ጉዲና ከአንድ ሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ፤ “ለመሆኑ እናንተና (ተቃዋሚዎች) መንግሥት በምን ሁኔታ ላይ ነው የምትገኙት” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ ” እኛ የኢሕአዴግን ጠብመንጃ እንፈራለን፤ ኢህአዴግ ደግሞ የ97ቱን ጎርፍ ይፈራል፤ በዚህ ዓይነት ነው የምንገኘው” ያሉትን ሳስብ፤ ፍርሃቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን፤ የሕዝቡም ጭምር እንደሆነ ግልጽ የሆነውን ያህልና ባሁኑ ጊዜም ደግሞ፤ ሕዝብ ከዚህ የፍርሃት ቆፈን ተላቆ ማካሄድ የጀመረውን የእምቢ ባይነት እንቅስቃሴ እየተመለከትን፤ እዚህ ይደርሳል የማይባል የድርድር ወሬ ማናፈስ፤ በተጀመረው እንቅስቃሴ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ለማፍሰስ እንደመሞከር ተደርጎ የሚታይ ነው።
ወያኔ በምንም መንገድ ይሁን፤ እሱ ሥልጣን ለቆ ሌሎች የሚያስተዳድሯት ኢትዮጵያን ከማየት፤ መሬቷ ተከፍታ ብትውጠው እንደሚመርጥ አትጠራጠሩ። “ሲያቅተኝ ጥዬ መሄድ ነው” ያለውን በሚገባ አጢነን፤ ትኩረታችን መሆን ያለበት እንዴት እንዲያቅተው እንደምናደርግ መላ መምታቱ ላይ ነው። እዚህ ድረስ ከድርድር ጋር በተያያዘ የተረክሁት በወገኖች በኩል ያለውን በሚመለከት ሲሆን፤ የድርደሩን ወሬ የሚያናፈሱት የውጭ ሃይሎችም ጭምር እንደሆኑ ልብ እንደሚባል አልጠራጠርም። ወደዃላ መለስ ብሎ ቅኝት ማድረግ ጠቃሚ ነው። ከቅንጀት ጋር ከሰማይ በታች ባለ ነገር ሁሉ እወያያለሁ፤ ያቺን የቤት መዋል ተቃውሞን ብቻ አቋርጡልኝ ሲል፤ይህ የወያኔ ጥያቄ አወንታዊ መልስ እንዲያገኝ የውጭዎቹም ጫና እንደነበረበት እናስታውሳለን፤ ይቺን ከደረሰ በዃላ ምን ሆነ? መልሱን እላይ በዚህ ክፍል መጀመሪያው ፓራግራፍ ውስጥ አሳይቻለሁ አልመለስበትም። ከዚያ በዃላስ የውጭዎቹ ቃሉን እንዲጠብቅ በማለት ምን አደረጉ? የቅንጅት አመራሮች ያንን ተቃውሞ በመቀልበሳቸው ስህተት ቢፈጽሙም፤ ባሳዩት ቀጣይ እመቢተኝነትና በከፈሉት መስዋዕትነት ትገል እንዳይሞት አድርገዋል ባለውለታችን ናቸው።
አሁንም ወያኔ ምንአልባት ለጊዜ መግዣ ይሆኑኛል የሚላቸውን ምክንያቶች አፈላልጎ፤ ጌቶቹንም ከጎኑ አሰልፎ በሱ አጀንዳ ድርድር ለማድረግ መሰሎ ለመቅረብ አይሞክርም ማለት አይቻልም፤ በተቃዋሚዎች በኩልም፤ የተደራደርነው፤ እዚያ የገባነው፤ በዚያ የወጣነው ፈረንጆች እንዲህ ስላሉን ወይም እንዲህ ይሉናል ብለን ነው የሚለው የይሉኝታ ይሁን የፍርሃት ዘይቤዎች የቅርብ ትዝታዎቻችን ናቸው። ፈረንጆቹ ባንድ ወገን ድርድር ያስፈልጋል ሲሉ ከዚያው ጋር አያይዘውም ኢትዮጵያ በጸረ-ቴሬሪዝም ትግል የቅርብ ወዳጃቸው እንደሆነችም ያስታውሱናል፤ “ሳይጠሩት አቤት፤ ሳይለኩት” ወዴት የሚል አሽከራቸውን ስም ጠርተው ለመናገር የዲፕሎማሲ ጉዳይ ሆኖባቸው ነው እንጂ፤ በጸረ-ቴሬሪዝምነት ወያኔ የኛ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን አትርሱ ማለታቸው እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ያለበለዚያማ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካል እንደመሆኗ፤ ዓለም አቀፍ የሆኑ ሰላምን የሚያደፈርሱ ድረጊቶችን ለመከላከል የማንም የግል ወዳጅ መሆንን የሚጠይቃት አይመስለኝምና ፈረንጆች እንዲህ ስላሉን፤ ወይም እንዲህ ሊሉን ይችላሉ የሚለውን ወደጎን አስቀምጦ፤
ሕዝባችን ምን እያለ ነው!?
ወያኔን ወጊድ እንበለው!
የሚለውን አጠንክረን ሁላችንም ከፍርሃት ተላቅቀን “ያለመከራ ጸጋ አይገኝም” እንደሚባለው፤ እኔ አልፌ የሚቀጥለው ትውልድ እኔ ዛሬ የምኖረውን ኑሮ ወራሽ እንዳይሆን ማድረግ አለብኝ ብለን ሰላማዊውንም ሆነ፤ የትጥቁን አመጹ ማፋፋም ነው። ከዚያ በተረፈ በወያኔ አጀንዳ ተደራድሮ ምንም መፈየድ ካለመቻሉም በላይ፤ የሚተርፍ ነገር ቢኖር ሳይታሰብ ትግሉን በማዝረክረክ የወያኔ ተባባሪ ሆኖ መገኘት ነው። ይህ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ተገድዶ ለድርድር ይመጣል የሚል አባዜም አለ።
አለመደማመጥ ካልሆነ በስረቀር “ሲያቅተኝ” የሚለው እኮ ሌላ ነገር አይደለም። ስገደድ፤ ስደክም፤ አቅም ሲያንሰኝ ማለት ነው። ዊን-ዊን የሚሉትም ነገር ይሰማል፤ ይህም ሁሉም አትራፊ የሚሆንበት እንደማለት መሆኑ ነው። ታዲያ ወያኔ ከተሸከመው ዘረኝነት የተባለ ግም ነገር ላይ ምን ያህል በመቶ ሊቀርለት ይችላል? ዘረኝነት በማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር – ከዘረኞቹ በስተቀር – መቃብሩ የሚቆፈርለትና ከምድረገጽ እንዲጠፋ የሚዶለትበት ሲሆን፤ ወያኔ ደግሞ እሷ ከተነደለችበት ያለቀለት ፍጡር መሆኑን ሰለሚያውቅ፤ ሲያቅተኝ ጥዬ መሄድ ነው የሚለው ውሳኔው አግባብና አርቆ አስተዋይነት ያልተለየው ነው። ከዚህ ይለቅ በተበዳዮች በኩል መታሰብ ያለበት አቅቶት ሲሄድ፤ – ባባይ ጸሃዬ በኩል ያስተላለፈውን መልዕክት ልብ ይሏል – አህያዋ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አለች እንደተባለው ለሱ የማትሆን ኢትዮጵያን ምን አድርጓት ለመሄድ እንደሚፈልግ ተገንዝቦ፤ ይህ እንዳይሆን መከላከያውን ማበጀት ነው። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ በድንገት ድቅን ይልብኛል፤ ከገዥዎቻችን (ወንድሞቻችን/ወገኖቻችንም እንላቸዋለን መሰለኝ) አንደበት “ከፈረስን እናፈራርሳችዃለን” የሚሉንን እየሰማ የማይመረው ኢትዮጵያዊ ይኖር ይሆን? የሚለው ነው። መቼም ለጉድ የተፈጠረ ስለማይጠፋ ይኖራል። ወገኖቼ እንደአህያ ታስቦብን እንደሰርዶው እንዳንሆን ከፈለግን የሚከተለውን ብዬ ይህንን ክፍል ልዝጋ፤ ቀላል ነው ጉዳዩ። ብዙ ነገር አያስፈልግም። በጣምም ቀላል ነው!
መስፈንጠሪያ፤- ብንራብባት ብንጠማባትም፤ ብንታረዝ ብንበረድባትም፤ ብንጠቁር ብንነጣባትም፤ ብንደኸይ ብንከብርባትም፤ ላንደኛችን ጨለማ ለሌላችን ብርሃን ብትሆንም ወዘተ… ያለችን አንድ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ነች ብሎ፤ የትግላችን መነሻና መድረሻ እሷዋኑ ማድረግ። ይህንን ያስቀደምኩት ያለምክንያት አይደለም። ዕውነት መናገር ጥሩ ነውና “ያለችኝ አንዲት እትዮጵያ የምትባለ አገር ነች” የምትለዋ ጽንሰ-ሃሳብ እንደማር የምትጣፍጠንን ያህል ደግሞ እንደቃር ብጤ የምትሆንብንም እንዳለን ስለማውቅ ነው። የለንም? አለን።! ይሕቺ የቃር በሽታ ደግሞ ለወያኔ ምኑ እንደሆነችም እናውቃለን። ጮቤ መርገጫው!! አትስማሙም? ተናገሩ! ከምግብ ወይም ከመጠጥ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመንን የቃር በሽታ ባሁኑ ጊዜ እንደምሰማው መድሃኒቱ ስኳር መላስ ነው ሲባል ነው። ከአንዲት አገራችን ኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ የገጠመን የቃር በሽታስ መዳኛው ምንድነው?
እኔ መድሃኒት አለኝ። በጀርመን አገር የቁርጥማት ሊግ የሚባል ስብስብ አለ። የዚህ ሊግ ተግባር የቁርጥማትን በሽታ ለመታደግ የቁርጥማት በሽታ ተጠቂ የሆኑት፤ የማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኞችና እንዲሁም ሃኪሞች ሆነው በአንድ ላይ ያቋቋሙት ሲሆን፤ ስራው በጋራ ተቀምጦ ስለበሽታው የልምድ ልውውጥን በማድረግ፤ በመወያየትና ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎችን በጋራ በመፈጸም በሽታው የሚያደርሰውን ስቃይ ለታማሚው እንዲቀንስለት ማድረግ ነው። ይህንን ምሳሌ ተከትለን፤ የኛንም የአንዲት ኢትዮጵያ የምትባል የቃር በሽታ በተመለከተ በበሽታው የተጠቁት፤ ያልተጠቁትና ሌሎችም ጉዳዩን በተመለከተ ቢያንስ ድጋፍ አደርጋለሁ የሚሉ የሚሳተፉበት አንድ ሊግ አቋቁመን ብንመክር በሽታው እያደረሰብን ያለውን ጉዳት ወደዝቅተኛ ደረጃ እንዲወርድ ማድረግ እንችላለን የሚል እምነት አለኝ። ምን ማለቴ እንደሆን ትረዱኛላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህን ካላደረግን ግን ሁላችንም ከወያኔ ጮቤ መርገጫነት ለመላቀቅ የምናደርገው ተጋድሎ ጉዞው መርዘም ብቻ ሳይሆን፤ ጉዞው በምን መልክ እንደሚያከትምም ለመተንበይ ያስቸጋሪ ሆኖ ይቆያል። አንድ የቆየ መልዕክቴን ልድገም፤ ተቃዋሚ የአንደነትና የግንጠላ ሃይላት ሆይ! ሁልህም ዴሞክራት ነኝ እያልክ እራስህን የምትጠራ ሁሉ! ችግራችንን ዴሞክራት ነኝ በማለት ብቻ ስለማንወጣው፤ የግድ የዴሞክራሲ አርበኛ መሆንንም ይጠይቀናልና። አርበኛ እንሁን!! ነጻና ፍትሃዊ የሆነን የኢትዮጵያ ሕዝብን ውሳኔ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ብቻ ሳይሆን፤ ነጻና ፍትሃዊውን የኢትዮጵያን ህዝብ ውሳኔ ልናገኝበት የምንችልበትን የኢትዮጵያን ሜዳ በአንድነት እናመቻች! ይህም በዚህ ይብቀኝ፤
- መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ መልስ አይሰጥም! እየሰጠም አይደለም፤
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በየአካባቢው በመንግስትና በህዝበ መካከል የሚካሄዱትን ግጭቶች አስመልክቶ እታች ከሚገኘው ውሎ ገብ ሕብረተ ሰብ ጀምሮ እስከላኛው ሊቅና ከፖለቲካ ድርጅቶች ተጠሪዎች ሳይቀር፤ በጽሁፍና በተገኙ ዜና ማስራጫዎች በሚያስተላልፉት መልዕክት፤ በሚያሰሙት እሮሮ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ መልስ አይሰጥም፤ አልሰጠም ይሉና እዚያው በዚያው ደግሞ ተከታትሎ የሚነገረው መንግሥት ጥያቄ ያነሱትን ገደለ፤ ደበደበ፤ አሰረ … ወዘተ የሚል ነው። እነዚህን ሁለት ሃሳቦች ልብ ብላችሁ ያዟቸው።
እንደኔ የወያኔ መንግሥት ለተጠየቀው መልስ አልሰጠም በሚለው ለመስማማት ይቸግረኛል። እንደሚባለው ጥያቄ የጠየቁ በተጠያቂው ተገደሉ የሚባለው ሁኔታ ጥያቄና መልስ ካልተባለ ምን ሊባል ነው? ጠያቂው የሚጠብቀውን መልስ አላገኘም ብሎ መከራከር ያባት ስለሆነ፤ በዚያ መልክ ጥያቄን አንስቶ መከራከሩ አግባብነት ያለው ነው። ከዚያ ባለፈ ግን፤ መንግሥት የሰጠውን ህይወት እስከማጥፋት የደረሰን ቆራጥ መልስ እንደመልስ ሳይቆጥሩ እንዳላዩ ሆኖ ለማለፍ መሞከሩ፤ ቀረበ የተባለውን ጥያቄ አልባሌ ማድረግ ነው። ከዚያ ይልቅ የአርቆ አስተዋይ ግንዛቤ መሆን ያለበት፤ ያቀረብኩት ጥያቄ ለተጠያቂው ያስተላለፈው መልዕክት ምን ቢሆን ነው? እኔ የጠበቅሁትን መልስ ሳይሆን፤ በተቃራኒው የሆነው? ጥያቄው የቀረበው በእርግጥ ተጠያቂው ሊረዳው በሚቸል ቋንቋ ነው የቀረበው? ብሎ መጠየቅ ማንንም አይጎዳ፤ እንዲያውም “መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ” እንዲሉ፤ ዕውቀት ይገበይበታል። ጥያቄው ያልተመለሰለት ወገን ነገም መልሶ የሚያቀርብ ከሆነ፤ የመጀመሪያው ጥያቄ ያስከተለውን አይነት ሁኔታ እንዳያስከትል አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጎ ለማቅረብ ይረዳል። የኔ ድምዳሜ መንግስት የሰጠው መልስ የቀረበለት ጥያቄ ባስትላለፈለትና እሱ ሊረዳው በቻለው መጠን የሰጠው መልስ ነው ብዬ ነው የማምነው። መልስ አልሰጠም ብሎ በደፈናው ማለፉ ተመጣጣኝ የሆነ የመልስ መልስ ለመስጠት ሊኖር የሚገባውን ቆራጥ መንፈስ ማላሸቅ ይሆናል።
ቸር ይግጠመን
tassat@t-online.de
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply