
ዳሪ
ወዳጄ እንደምነህ – ውዱ ጎረቤቴ
ባለህበት ቦታ – ይድረስህ መልክቴ
የልጄ ሰርግና – የሟች ልጅህ ቀብር
አንድ ላይ መሆኑ – ፈጥሮብኛል ችግር
መቼም ይገባሃል – ግልጽ ነው ነገሩ
ብዙ ነው ማዕረጉ – የሠርገኛ ክብሩ
ስለዚህ አደራ – የልጄን ታላቅ ሠርግ
በደስታ በሆታ – እንዳሳልፍ በወግ
በዛ ቀን ተነስተህ – ልጅህን ስትቀብር
ስዎችን ሰብስበህ – አታብዛ ግርግር
በሳቅ በደስታ – በ`ልልታ ቅበራት
ለለቅሶኛው ሁሉ – ይኼን ንገርልኝ
ነገ ማታ ድረስ – መልስህን ላክልኝ
ቀባሪ
ክቡር አስተዳደር- የላኩልኝ መልዕክት
እጅግ አስገራሚ – ድንቅ ነው በእውነት
ታስራ ተገንዛ – ልጅ ልትቀበር
ተሞሸረች አሉኝ – የርስዎ ልትዳር
ለክብርዎ ሲባል – ለርስዎ ወግ ማዕረግ
እንድስቅ አዘዋል – ለቅሶዬን በመንፈግ
እንደዚህ አድርጎ – ቀኑ ከከበደ
በርስዎ አስተዳደር – ታምር ከወረደ
ሀዘንና ደስታ – መውጣቱ መውረዱ
አንድ ስለሆነ – ሁለቱም መንገዱ
መቼም ምን ይደረግ – በእልልታ ልቅበራት
እርስዎም ልጅዎን – በለቅሶ ይዳሯት
ወይም ደስታ ሀዘን – እንዳይቀያየጥ
ስምምነት አ’ርገን – ቤት እንለዋወጥ
እግረ -መንገዱንም – በዚህ – አዲስ መንገድ
መከራን ይቅመሱ – እኔም ደስታ ልልመድ
Leave a Reply