እሙሩ ብሪታንያዊ የምርመራ ጋዜጠኛ ኒኮላስ (ኒክ) ዴቪስ የብዕሩ ሞገስ ይደርጅለትና ዕውነት እንዳንናገር፣ ሀቅ እንዳንዘረዝር የሚያደርጉን ሠለስቱ ቀታሊያን ሥህተቶች፣ ሦስቱ ገዳይ ድክመቶች:-
“1) የምንመርጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዕውነታውን በመሠረታዊ መንገድ የሚያፋልሱት እንዲሆኑ በማድረግ ዋናውን ጭብጥ ማሳት፣
“2) በተደጋጋሚ የምንጠቀምባቸውን ኢተአማኒ፣ አንዳንዴም ፈጽሞ ውሸት፣ የሆኑ ጭብጦች ደጋግመን በመጠቀም ዕውነተኛ ማስረጃዎች እንዲመስሉ ማድረግ፣
“3) ከአካባቢው ህብረተሰብ መካከል ኃይለኛ ጉልበት ያላቸውን ወገኖች የሚያደምቁ ዕሴቶችን የማያቋርጥ አሻራ እንዲኖራቸው ፖለቲካዊና ሞራላዊ ውትወታን ማብዛት፣ ናቸው” ሲል የጣፈው ቀልብ የሚማርክና ለአብነት የሚጠቀስ መንደርደሪያ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ማለፊያ አስተዉሎት ነው መቼም።
ታድያ ይህን የኒኮላስ ዴቪስን ሓቲት ባስታወስኩ ቁጥር በሃሳቤ ወዲያው ደርሶ የሚደቀነው ፀሐዩ መንግሥታችን (ኢህአዴግ) ነው። ዉሸት የኢህአዴግ መለዮ ማንነቱ ሆኗል። ተሳስቶ እዉነት መናገር አልፈጠረበትም፣ ሲያልፍም አይነካካው። እንዲያው ተገዶ ለመናገር ቢገፋፋም ሺህ ዉሸቶች አካቦ፣ ሁልቆ መሳፍርት የሌላቸው የፈጠራ እብለቶች ቀንብቦ ነው። ስለ ምጣኔ ሀብት እድገት፣ ስለህዝብ ኑሮ መሻሻል፣ ስለድንበር ጉዳይ፣ ስለ ሃይማኖት ተቋማት፣ ስለ መለስ ሞት፣ ስለአንዳርጋቸው አፈና፣ ስለ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ስለጋዜጠኞችና ፀሐፍት፣ ለሰላም ማስከበር ሥራ ወደተለያዩ ሀገሮች ስለሚሄዱ የሠራዊት አባላት፣ ስለምርጫ፣ ስለባድመና የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት፣ ስለመተካካት፣ የቱን አንስተን የቱን እንተው? ዉሸት ያልቀላቀለበትን፣ ሐሰት ያልዶለበትን ጉዳይ አስሶ ፈልጎ ማግኘት ዘበት ነው ያሉ ዋሹ አይሰኙም። ይዋሻል። ሎሌዎቹንም ዓይናቸዉን በጨው አጥበው ይዋሹለት ዘንድ ያሰልጥናል፣ ይገራል፣ ያዛል። ማጅራታቸዉን አንቆ ይዞ፣ በፍርፋሪ ሹመትና ጉርሻ አንብዞ፣በሙስና (በስኳር) አፍዝዞ ያስዋሻቸዋል። በሁሉም ትካር (ጉዳይ) ላይ ቅጥፈትን ዋልታ አድርጎ ነው ሃሳብና ድርጊትን የሚቀልሰው። አንዳንዴ ሳስበው፣ የዚህ ሥርዓት ግፈኝነት ምንጩ ከጥላቻ ቀጥሎ በዉሸትና ክህደት ላይ መመስረቱ ነው ብዬ ለማመን እገደዳለሁ። ተቆጠቡም ተናገሩት፣ ገለፁትም ደበቁት ኢትዮጵያዉያን ይህን አመሉን አንጥረው አብጠርጥረው ያውቁታል። “ማወቁንማ እናውቃለን፣ ብንናገር እናልቃለን” ሆነ እንጂ ችግሩ!
የሥነ ልቡና ጠበብት እንደሚያስተምሩን፣ ዉሸት የደካሞች ባህርይ ሲሆን መጨረሻዉም ዉድቀት መሆኑ አያጠራጥርም። ሌላው ሌላው ይቅርና ትላንት ከአለም 46ኛ ከአፍሪካ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፣ አቻ የሌለው የዘመኑን ቴክኒዎሎጂ ታጥቋል፣ ሰው አልባ አውሮፕላን ሰርቷል፣ አለምን ያርበደብዳል ተብሎ ወታደራዊ ትዕይንት ያሳየው የመከላከያን ቀን በድምቀት ያከበረው ሠራዊት፣ መሳሪያዎቹ ሁሉ ጊዜ ያለፈባቸዉና ያረጁ፣ ምንም ጥቃት ለመቋቋም አቅም የሌለው መሆኑን በምሥጢር በተካሄደው የአመራሩ ስብሰባ ላይ ጄኔራል ሳሞራ ያቀረበው ሪፖርት የመንግስታችንን እኩይ ገፅታ በአሳፋሪ ሁኔታ አጋልጦታል። መከላከያ ኦዲት የማይደረግ፣ የህዝብ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ እየተመዘበረ ጎጠኞች ያበጡ የናጠጡ ቱጃሮች የሆኑበት የገለማ የነቀዞች እልፍኝ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። እድሜ ለአርበኞችና ግንቦት ሰባት ገና አንድ ጥይት ከመተኮሳቸው የመንግሥታችን ጭንብል ተገለጠ።
መንግስታችን አሁንም የልማዱን ይዋሻል። የወጋችን ኤርትራ አይደለችም። የኢህአዴግ የአፈና ሥርዓት ሆድ ያስባሰው ወገን ኢህአዴግን አስወግዶ፣ ዴሞክራሲና ፍትህን ለማስፈን የሚያደረገው ሁለገብ ትግል አካል መሆኑን ነገሮናል። ኤርትራ የወጋችን በማስመሰል የህዝብን ሆድ ለመብላትና እነሱ ፎቅ በፎቅ ላይ ሲገነቡ መኖሪያ ቤት አሳጥተው ሜዳ የወረወሩትን፣ እነሱ የሰሊጥ እርሻ ለማስፋፋትና ሚሊየነር ለመሆን ከአያት ቅድመአያት ቀዬው ያፈናቀሉትን ምስኪን ዛሬም በደሙ ሥልጣናቸዉን እንዲያቆይላቸው አፈሳና አፈናቸዉን አጡፈዉታል። እንደ ባድመው ጊዜ ሆ ብሎ ተነስቶ ላያፀድቅ አንገቱን የሚሰየፍላቸው ሞኝ ማግኘታቸው ግን ሲበዛ ነው የሚያጠራጥረው። አሁንም ሳሞራ የኑስ ሃያ ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት ባስቸኳይ ፀድቆ የጦር መሳሪያ ካልተገዛ ባለን አቅም የትም አንደርስም ሲል በቃሪያ ጥፊ እንዳጮሉት ብላቴና ሲለፈልፍ ተሰምቷል። ስለመከላከያ ሠራዊቱ የተደሰኮረው፣ የተዘፈነው ሁሉ እብድ የያዘው በሶ ሆኖ በነፋስ በኖ ቀረ ማለት ነው?? ዉሸታም ሥርዓት!
“ሲበዛ ማርም ይመራል።” ኢህአህዴግ በዉሸቱ ሊቀጥል አይችልም። “ጥቂት ሰዎችን ሁልጊዜ ማታለል ይቻላል፤ ሁሉንም ሰው ለጥቂት ጊዜ ማታለል ያቻላል፤ ነገር ግን ሁሉንም ሰው ሁልጊዜ ማታለል አይቻልም፤” እንዳለው አብርሃም ሊንከን፣ ኢህአዴግ ሁልጊዜም አታልላችሁዋለሁ ብሎ ካሰበ ራሱ ተታሏል፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አያውቅም ማለት ነው። ወይም እንደትላንት ለኢሕአዴግ ድጋፍ ወጥቶ በፍቅር አስክሮአቸው፣ በነጋታው በእጥፉ አደባባዩን አጥለቅልቆት ከቅንጅት ጎን ተሰልፎ ያሳበደዉን ሕዝብ አመል ዘንግቶታል ማለት ነው። ከዚያም ተምሮ አለመለወጡ በራሱ በሽተኛነቱን አምኖ፣ እዉነቱን ተናግሮ መድሃኒት ለመፈለግ አለመወሰኑን ይመሰክርበታል። ለዉጥ የህይወት ሕግ ሲሆን በጊዜ፣ ሁኔታና ቦታ ያልተለወጠ ደግሞ ከገፀ ምድር መጥፋቱ አሌ አይባልም።
የኢህአዴግ ዉሸት ከዉድቀት እንጦርጦስ ሊፈጠፍጠው ዥው አድርጎ እየወሰደው ነው። ከ20ኛ ፎቅ ላይ እየወደቀ ሳለ 8ኛ ፎቅ ያሉ ሰዎች “እንዴት ነህ?” ቢሉት፤ “እስካሁን ደህና ነኝ” አለ እንደተባለው ሩሲያዊ እየመሰለኝ መጥቷል። ዉሎ አድሮ የሚሆነው አይታወቅም፣ ሁሌም እንዳማሩ መኖር አይቻልም ።
ቸር እንሰንብት።
ka139693@gmail.com
Leave a Reply