ዛሬ (ሰኞ) በሸራተን አዲስ እየተከበረ በሚገኘው የኢትዮጵያዊነት ቀን የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር ዲማ ነገዎ የማንነታችን መገለጫዎች ማሰሪያው ኢትዮጵያዊነት ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የህዝቦች የተለያዩ የማንነት መገለጫዎች መኖራቸውን የገለጹት ዶ/ር ዲማ እነዚህን ሁሉ አጠቃሎ አንድ ዓይነት አገራዊ ማንነት የሚሰጠን ኢትዮጵያዊነታችን ማንነት ነው ብለዋል፡፡
አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነት አንድነትን በብዝሀነት አጣምሮ ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት የሚያስተናግድ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አገሪቷ አሁን ያለችበትን ውስብስብ ፈተና እንድትሻር ለማስቻል በህግ ማስከበር እና በሌሎች በሚወሰዱ እርምጃዎች የአገርን አንድነት እና ኢትዮጵያዊነትን እንዳይሸረሽር ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ (ኢብኮ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ማስታወሻ፤ የኦሮሞ መብት አቀንቃኝ ነን ለሚሉትና በነፍስ ግድያ ተጠርጥረው በእስር ለሚገኙት ጃዋር መሐመድና በቀለ ገርባ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም ካለም ተጭኖብኝ ነው በማለት የግል ብስጭቱን በፖለቲካ ሽፋን የሚያወራው ጸጋዬ አራርሳ የዶ/ር ዲማ ንግግር ኦነጋዊ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ምንም ቦታ የሌለው መሆኑን የሚያመላክት ሆኗል፡፡
Tesfa says
እንደዛሬው ሳይሆን ድሮ ድሮ ሰው በበሬ ሳይሆን በድሮ አረሰ ሲባል ህዝባችን በፍቅር በአንድነት አንድ የአንድን ባህል አክብሮ እንደኖረ ይታወቃል። አሁን ሰለጠን ብለን ሰይጣን ከሆን ወዲህ የሚደረጉ ነገሮች ሁሉ ለጀሮ የሚቀፉ፤ ለዓይን የሚዘገንኑ መሆናቸውን በሃገርና በዓለም ዙሪያ የሚናፈሱ ወሬዎች ይናገራሉ። የሰው ልጅ ሰልጥኖ ጨረቃን መርገጡ የክፋት ቋት ከመሆን አላዳነውም። እንዲያውም ሰለጠንኩ ባለ ቁጥር ሰንጣቂ ሃሳቦችን እያመነጨ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መላቱምን አበዛ እንጂ። በቅርቡ በስራ ቦታ ፎርም እየተሞላ ጾታ በሚለው ሥፍራ ላይ (Genderless) ከሴትም ከወንድም ያልሆነ ማለት ይመስለኛል የሚል ስመለከት ግራ ገባኝና ቀና ብዬ የማመልከቻውን ባለቤት ስመለከት ሴት መሆኗ ከራስ እስከ እግሮቿ ይናገሯሉ። እግዚኦ እንዲህም አለ እንዴ? አታድርስ በማለት ነገሩ አልፌ የቀን ሥራዬን ቀጠልኩ።
ታዲያ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ከተናገሩት ጋር ይህ ጉዳይ ምን አገናኘው ለምትሉ ረጋ ብላችሁ ሃሳቤን ተከተሉ። የኦሮሞ ህዝብ አቃፊ፤ ሰላምን የሚወድ፤ ያለውን የሚያካፍል፤ ለሌላው የሚያዝን እንደሆነ በመካከሉ በመኖር የማውቀው ስለሆነ አሁን ከደርዘን በላይ ለኦሮሞ ህዝብ ይገደናል እያሉ በውጭም በሃገር ቤትም የሞት ጥሩንባ ከሚነፉት ወገን የሚባለውን አልሰማም። በዚህ አንጻር ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በተለይም በ60 ዎቹ አካባቢ ጀምሮ እልፍ የኦሮሞ ልጆች ለዚህም ለዚያም በአመኑበት ተፋልመዋል። ታስረዋል፤ ተሰደዋል፤ ተገድለዋል፤ ተፈናቅለዋል። አሁን እንሆ ቀደምት የኦሮሞ ህዝብ ነጻነት ታጋዮች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ህዝብን የሚያረጋጋ፤ ወደ አንድነትና መከባበር የሚያመጣ፤ አንድ ለሌላው ተደራሽና ተደጋጋፊ ሃሳቦችን ሲያጋሩ ማየት ልብን ያሞቃል። በአንጻሩ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ተቀምጠው የሞትና የእልቂት ከበሮ እየመቱ ህዝባችን የሚያተራምስ ነገር ሲሰሩ ማየት ደግሞ በእጅጉ ያሳዝናል። እነዚህ አጥፊ ሃይሎች የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ በዘርና በቋንቋ ተሰላፊዎችን ሁሉ ያጠቃልላል። ዘረኝነት የበታችነት ስሜት መግለጫ ነው። ዘረኛ ሰው ሁልጊዜም የደቦ ፓለቲካ ፈላጊ ነው። ያ በመሆኑ ነው 27 ዓመት በደምና በዝርፊያ አጨማልቆ የገዛትን ሃገር እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በማለት ወያኔ ዛሬ የትግራይን ህጻናት በጦርነት እየማገደና በአማራና በአፋር ከአውሬ ባህሪ በማይለይ ሁኔታ አርሶ አደሩን፤ የጋማና የቀንድ ከብቱን በጥይት የሚረፈርፈው። የፓለቲካ እብደት ይሏቹሃል ይህ ነው። ወያኔ እሳት መቆስቆስ ብቻ ሳይሆን እሳት ማቀበልና ማቀጣጠልም ተክኖበታል። ትላንት ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ እያለ ይለፍ የነበረው ወያኔ ዛሬ ከተራራ አናት ላይ መሽጎ ከተሞችን ይዘርፋል፤ ያቃጥላል፤ ሊጥና በርበሬ ሳይቀር ወደ መቀሌ ያጋግዛል። ትላንትም ሌቦች ዛሬም የባንክ ዘራፊዎች። የማይድኑ የመከራ ጆኒያዎች።
በሃሳብና በገንዘብ ድለላ የዛገ ሃሳብ የሚከተሉ የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች ከወያኔ ጎን ተሰልፈው ሌላውን ወገናቸውን ሲወጉ በ 27 ዓመቱ የወያኔ አገዛዝ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የደረሰውን በደል ዘንግተውት አይደለም። እያወቁ አብደው እንጂ። በፈጠራ ታሪክ የሰከሩት እነዚህ የዘር ድውያን ዓለምና አህጉራዊ እይታቸው ከመንደራቸው አይርቅም። ተማሩ አልተማሩ ታጥበው አይጠሩም። ልብ ላለው ሰው ግን ዛሬም ሳንጃ በአፈሙዝ ትላትንም አባረህ በለው፤ ያዘው ጥለፈው የምንለው ለምን ይሆን በማለት ይጠይቅ ነበር። ከነጭና ከዓረብ ጋር ተጎዳኝቶ ህዝብን መጉዳት አረመኔነት ነው። ዛሬ በወለጋ የምንሰማውና የምናየው የዘር ጭፍጨፋ የኦሮሞ ህዝብን የሚወክል ሳይሆን የጥቂት እብዶች የተላላኪነት ተግባር ነው። ይህ ተግባራቸው በጎንደር ዙሪያ በተለይም በጭልጋ የቅማንት አጥፊ ሃይሎች በህበረተሰቡ ላይ ከሚያደርሱት ገመና ጋር ይገናኛል። በተል እኮም በሃሳብም አንድ ነው። ዝርፊያና ግድያ። ሰውን ማሸበር። የሃገሪቱን ሰላም መናጥ። አይ ነጻ አውጪ መሆን ድንቄም ነጻ ታውጣኝ።
ባጭሩ እውነተኛ የኦሮሞ ልጆች ያኔም ነበሩ ዛሬም አሉ። በነጮቹ ቋንቋ (the silent majority) አንድ ቀን ሆ ብሎ ስለሚነሳ ዛሬ በዘር ፓለቲካ የሚነግድ እብድ የጌሾ ነጋዴዎች ቆም ብለው ቢያስቡ መልካም ነው። ነገርን መዝነው ልክ እንደ ዶ/ር ነገዎ ሃሳብን በሃሳብ ፈትገው ስንዴና ገለባውን በመለየት ለህዝባችን ሰላምና መረጋጋት መትጋቱ ለአሁኑም ሆነ ለወዲያኛው ዓለም ይጠቅማል። ለጥቁር ህዝቦች አንድነት መስራት ከመንደር እይታና የከዘር ፓለቲካ ነጻ ያወጣል። የሰፋ እይታ ተሻጋሪ ሃሳብ ያፈልቃል። ከተንኮልና ከሸር ርቀን ዛሬም የሚያነባውንና ተርቦ የሚያድረውን ወገናችን እንታደግ። በቃኝ!