* የጅዳ ቆንስል ለባላቴናው መሀመድ ፍትህ ይትጋ
* የጅዳ ቆንስል የስደት ያሰናከለውን ወንድም ይሸኝ
* “ጅቦቹ!” የአንባሳደሩን ተሀድሶ ያኮላሹት ይሆን?
የማለዳ ወጌ መነሻ መድረሻ ከወራት በፊት ለኦማኗ ተገፊ ለአልማዝ እና ሰሞኑን እርዳታ ስናሰባሰብለት ለሰነበትነው ወንድም ወጣት አባወራ ለመሀመድ ስላደረጋችሁለት ድጋፍ ምስጋና ለማቅረብ ነው። በላዩ ላይ የአልማዝ እርዳታ ሀገር ቤት በእንክብካቤ ለያዛት ለሜቅዶንያ የማስረከባችን መረጃ አካፍየ በሳምንት እድሜ ለመሀመድ ሁሴን ከ10 ሽህ የሳውዲ ሪያል ወይም ወደ 60 ሽህ የኢትዮጵያ ብር የሚጠጋ ገንዘብ በላይ ማሰባሰቤን መረጃ ከማቅረቡ ጋር ምስጋናየን ለማስተላለፍ ነበር።
ለዚህ መረጃ አቅርቦት ስሰነዳዳ በተዛማጅ ስለ ዜጎች መብት ጥሰትና ስለመብት ማስከበሩ ጭብጥ አስተምሮት እናገኝ ዘንድ አንድ መረጃ አገኘሁ። ምስጋናየን ወደ መጨረሻ በማድረግ በመብት ማስከበሩ ተግዳሮት አቢይ ትኩስ መረጃ ምሳሌ አግኝቻለሁና ወደዚያው ላምራ . . .
የፊሊፒን ኢንባሲ ለዜጋው መብት ፍርድ ቤት መቆሙን በሚመለከት የሳውዲ ታዋቂ እንግሊዝኛ ጋዜጣ ሳውዲ ጋዜጥ ሀሙስ እትሙ አስነብቦናል። የፊሊፒንን ጨምሮ የኢንዶኖዠያና የተለያዩ ሩቅ ምስራቅ ሀገራት ተወካይ ኢንባሲና ቆንሰላ መ/ቤት ተወካዮች ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መንገድ የዜጎቹን የመብት ጥሰት ከመከላከል ጀምሮ አልሆን ሲላቸው ዜጎቹ ሳውዲ እንዳይመጡ ጫና እስከ ማድረግ ያረሰበ መንገድ እንዲሚደርሱ አውቃለሁ። ይህ ትጋታቸው የተለመደ ሆኖ ባይደንቀኝም “የፊሊፒን ኢንባሲ 2000 የሳውዲ ሪያል አልከፍል ያለውን ድርጅት ከሰሰ!” የሚለው አዲስ መረጃ የእኛን ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤት በጨረፍታ እንዳይ አስገድዶኛል . . .
ዛሬ የወጣው ይህው የሳውዲ ጋዜጥ ዘገባ የፊሊፒን መንገስት 700 ሽህ በላይ ዜጎቹ ሳውዲ በስራ ላይ እንደሚገኙት በማተት ኢንባሲ የዜጎቹን መብት ለማስከበር ሳውዲ ጠበቃ ቀጥሮ የፍርድ ሂደቱን እየተጠባበቀ እንደሆነ ያስረዳል። ሸጋ ነው . . .! እርግጥ ነው የሰለጠኑ የተደራጁትን የኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤት ተወካዮች አሰራር ከእኛው ጋር ላወዳድር አይቃጣኝም። ለዜጎቻቸው ክብር የሰሩትና የሚሰሩት የተለመደ ነውና አይደንቀኝም፣ እነሱ እንዲህ ናቸው! ሁሌም የሚገርመኝ የሚደንቀኝ ነገር በመብት ማስከበሩ የእኛ ተወካዮች የኤሊ ጉዞም አይደለም። ለበደላችን ፍንትው ያለ መረጃ ተይዞ ወደ ፍትህ አካላት ማቅረብ የገደዳቸውን እንቆቅልሽ ግን አውጥቸ ባወረድኩት ቁጥር አልዋጥ አልሰለቀጥልህ እያለ እቸገራለሁ! ወደ ባጀን ወደ ከረምንበት የስደት ህይዎትና አልሰምር ያለ መብት ጥበቃና የእኛ አበሳ አላመራም። ለኤሊ ጉዟችን ማሳያ የማጣቅሳቸውን ሁለት ሰሞነኛ መነጋገሪያ ጉዳዮችን አነሳስቸ አልፈታ ወዳለኝ የመብት ማስጠበቅ እንቆቅልሽ አቀናለሁ!
በውል የማውቀውን ከአንባሳደር ተክለአብ እስከ ቆንስል ዘነበ ለተጫነንን የመብት ማስጠበቅ ህጸጽ በቂ መረጃ አይጠፋኝም። ያም ሆኖ ነገር ላለማንዛዛት የብላቴና መሀመድ አብድልዚዝን እና ስደት ያሰናከለውን ወጣት አባወራ መሀመድ ሁሴንን ጉዳይ በጨረፍታም ቢሆን ለጎደለው መብት ጥበቃ በቂ ምሳሌ ነውና አነሳዋለሁ! ወደ ማጠቃለያውም የቀድሞው ብርቱው የጅዳ ቆንስል “ገዠ” አንባሳደር ተክለአብ ከተሸኙ ወዲህ አልረጋ ስላለው የጅዳ ቆንስል ወንበርና በከባቢው አሉ ስለሚባሉት ተጽዕኖ ፈጣሪ “ጅቦች” በገደምዳሜ የምለውን እላለሁ!
የተጓተተው የብላቴናው ፍትህ እጦት . . .
መብት ማስጠበቁ ሲነሳ በ4 ዓመቱ ድክ ድክ እያለ በእግሩ ሮጦ ገብቶ በህልምና ስህተት 9 ዓመት የየተሰናከለውን ብላቴናው መሀመድ አብድልአዚዝን እናገኛለን። መሀመድ 9 ዓመት የአልጋ ቁራኛ ሆኗል። ወላጆቹ ከመካ ጅዳ እየተንከራተቱ ለ9 ዓመታት ፍትህን ቢጠይቁም ሰሚ አላገኙም! ይህ ሁሉ ሲሆን ከጅዳ ቆንስል እስከ ሪያድ ኢንባሲ ወላጆቹ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ጅሮ የሰጣቸው አልነበረም ። ተወካዮቻችን አቤቱታ ቀርቦላቸው እንኳ በሀኪሞች ስህተት የተሰናከለውን ዜጋቸውን ጉዳይ ወደ ፍትህ ማቀረብ ገዷቸው ከርሟል!
እርግጥ ነው ባሳለፍናቸው ወራት አምባሳደር ውብሸት መጡና የብላቴናው መሀመድ እናት አቤቱታ ተቀባይነትን አግኝቷል። አቤቱታውን ቢቀርብም መብት ማስከበሩ አሁንም ጎድሏል። ከአንድ ወር በፊት በህክምና ስህተት ልጇን ለአልጋ ቁራኛ ያበቃው ሆስፒታል የመሀመድን እናት ከሰጣት የማስታመሚያ መጠለያ ሲያባርራት ጉዳዩን መከታተል የጀመረው የጅዳ ቆንስል የመሀመድንና የቤተሰቦቹን መብት ለመከላከል አልቻለም። የጅዳ ቆንሰል አንድ ሃላፊ በተገኙበት በቅርቡ የጤና ጥበቃው ኮሚቴ የመሀመድ መሰናከል ምክንያቱ በህክምና ስህተት መሆኑን በተሰጠው ውሳኔ አረጋግጦ የውሳኔ ሰነዱን በአሳር በመከራ ቢቀበልም ቆንስል መስሪያ ቤት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አላደረሰውም . . .! ግን ለምን? ብለን እንጠይቃለን! ጉዳዩን የያዘው የጅዳ ቆንስል መረጃ ይስጠን!
የብላቴናው መሀመድና ቤተሰቦቹን በደልና እንግልት የሳውዲው የሸሪአው ህግና ስርአት የማያውቀው የህግ ጥሰት አለበት ባይ ነን። ይህ በመሆኑም ለሳውዲ ከፍተኛ ኃላፊዎች መሀመድ ሰብአዊ ጥሰትን አጥብቆ የሚቃወመ ው ህግና ስርአት ተጥሶ ስለመበደሉ ድምጻችን ለማሰማት የማንደርስበት ቦታ አይኖርም!
ስደት ያሰናከለው አባወራ . . .
ወጣቱ አባወራ መሀመድ ሁሴን ስደት አካሉን አሰናክሎት አልጋ ላይ ከዋለ 9 ወራት ተቆጥረዋል። ከየመን ሳውዲ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ሲገባ አደጋ ደረሰበትና ከወገቡ በታች እንዳይላወስ ሆኖ ተሰናከለ። ከወራት በፊት ስለመሀመድ ጉዳይ አንስቸ የጅዳን ቆንስል አንድ ኃላፊ ጥይቄያቸው መኪናውን የገለበጠው ወዲያውኑ በመሞቱ ለጉዳቱ ኢንሹራን እንደማያገኝ አጫውተውኛል፣ ለእሱም ይህው ተነግሮት በሳምንት የጊዜ ልዩነት ወደ ሀገር ይሸኛል ከተባለ ከአራት ወር በላይ ሆኖታል። አባወራው መሀመድ ሁሴን ግን “እባካችሁ ወደ ሀገሬ የምገባበትን መንገድ ፈላልጉልኝ!” የሚል የድረሱልኝ ጥሪውን አቅርቧል . . .
እድሜ ለወዳጆቻችን ወጣቱ አባወራ መሀመድ ሁሴን በወገኑ በተደረገ ርብርብ መቋቋሚያ የምትሆን ገንዘብ እየተሰበሰበለት ነው። መሀመድ ወደ ሀገር ለመሸኘት የሚችለው ብቸኛ አካል ደግሞ የጅዳ ቆንሰል ነው። መች ለመሸኘት እንደታቀደ መረጃ የለም። ጉዳዩን የያዙትን ዲፕሎማት አነጋግሬያቸው ጉዳዩ እየተንቀሳቃ መሆኑን ነግረውኛል። እኛ ስንጯጯህ ጉዳዩ መንቀሳቀስ መጀመሩት መልካም ነው እንበል . . . ወጣም ወረደ የምንሻው መፍተሔ ነው! በመሀመድን ሁሴን ጉዞ ዙሪያ ግልጽ መረጃ ሊሰጠን ይገባል!
ተባብረናልና ተሳክቶልናል ምስጋናየ ይድረስ!
ወጣቱን አባወራ የመሀመድ ሁሴን እርዳታ
ወጣቱን አባወራ ለመርዳት በያዝኩት እቅድ እናንተኑ አስተባብሬ በሳምንት እድሜ 10.000 በላይ የሳውዲ ሪያል 60 ሽህ የኢትዮጵያ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተሰብስቧል። እርዳታው እስከ መጭው መሀመድ እስኪሸኝ አለያም እስከ ሮመዳን መጨረሻ ቀጣይ እንዲሆን ወዳጆቸ ጠይቀውኛል። . . . ተቃዋሚ ሃሳብ ከሌለ እርዳታ ማሰባሰቡን እንገፋበታለን! አዎ ፈጣሪ ረድቶናል፣ ጥቂቶች ጥቂት አድርገው ለውጥ አይተናል. . .
የኦማኗ ለአልማዝ እርዳታ . . .
በተመሳሳይ ሁኔታ በመኪና ግጭት ተሰናክላ ሀገር የገባ ችው የኦማኗ ለአልማዝ ዛሬ በሜቅዶንያ አረጋውያን መርጃ ድርጅት እየተደገፈች በጥሩ ይዞታ ላይ ትገኛለች ። ለአልማዝ የሰነሰብነውን 170 ሽህ 895 ብር ከ79 ሳምቲም ለሜቄዶንያ አረጋውያን መረጃ ድርጅት አስረክበናል ! ብዙ ብንሆን የስንቱን እንባ እንጠርገው ይሆን ? ስል ራሴን ጠይቄ እናንተና እኛ ለሰብዕና ከተጋን በከፋ አደጋ የተሰናከሉ ወገኖቻችን አንገታቸውን እንዳይደፉ እንደምናደርግ ተስፋ ውስጤን ሞልቶታል ።
የጅማው ገበሬ የራያው ጀማል እርዳታ . . .
ከዚህ ቀደም ከወራት በፊት ለሀጅ ጸሎት መጥቶ ሰውነቱ ደቆ ለሁለት አመት በሳውዲ መንግስት ታክሞ ዳነ። ከጉዳቱ አገግሞ ከሆስፒታል ሲወጣ ለጉዳቱ መብት አስከባሪ አጥቶ በጅዳ ቆንሰል አንድ ታዛ ሁለት ሳምንት ኩርምት ብሎ ሲሰቃይ አየሁት። አሳወቅኳችሁ፣ እርዳታም ጠይቀኳችሁ ሳታሳፍሩኝ ደገፋችሁት ወደ ሀገር ሸኛችሁት! ራያ ጀማል የደረሰበት እንግልትና ጉዳት ማግኘት የሚገባውን ካሳ ሳያገኝ ቢሸኝም በእናንተ ድጋፍ ከ50 ሽህ የኢትዮጵያ ብር በላይ አብጦና ተደስቶ እየተፍለቀለቀ ነበር ከምስጋና ጋር ገስግሶ ወለጋ የደረሰው. . .
ለመልካም ነገር የምትሽቀዳደሙ ወገኖቸ ደስ ሊላችሁ ይገባል “ተረዳዱ!” የሚለውን ቅዱስ ቃል አክብራችኋልና የፈጣሪ ድጋፍ ሳይለያችሁ እናንተ ስላደረጋችሁት በስኬቱ ሰው ተደግፏል! በሰብአዊው እርዳታ ማሰባሰብ ሁሌም ከጎኔ ለሆናችሁና ለምትሆኑ ሁሉ ምስጋናየ ይድረሳችሁ!
የአንባሳደር የውብሸት ተስፋ . . .
አንባሳደር የውብሸት ከወራት በፊት ስራ በጀመሩ በሳምንታት ልዩነት ተሀድሶ ጀመሩ፣ ደስ አለን! ከአምባሳደር ተክለአብ እስከተኳቸው ቆንስል ጀኔራል ዘነበ አምባሳደር ውብሸት ጅዳን እና እኛን አሳምረው ያውቁናል። ልዑክ ሆነው በመምጣት ችግራችን አሳምረው የተረዱ ጥንቁቅ ዲፕሎማትም ናቸው። አምባሳደር ውብሸት ከትልቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስልጣናቸው ተነስተው ወደ ጅዳ ሲላኩ ያልተደሰተ አልነበረም! ብዙም ሳይቆዩ በአዲስ ጉልበት በጀመሩት አሰራር እኔ “ተሃድሶ ” በምለው መንገድ ተጉዘው የቆንስሉን በማደራጀት፣ ተገልጋዩ እንዳይንገላታ ያደረገ የተቀለጠፈ ስራ ጀምረው አይተናል። በግል ለምንሰጣቸው መረጃዎች አፋጣኝ ምላሽና ለዜጎች ድጋፍ ሲያደርጉ ታዝበናል። ምርጫው ሲጠናቀቅ አብሮ በተጠናቀቀው በሳውዲ ጠረፍ በጅዛን በኩል ከየመን ዜጎችን በመመለሱ ስራ አምባሳደር ውብሸት የመሩት ቡድን ድንቅ ስራን ከውኗል። በዚህና በዚያ እርግጥ ነው ተስፋ አይተንም ነበር . . .
የጅዳ ቆንስል ዋና ኃላፊ አምሳደር ውብሸት በዲፕሊማሲ ው ስራ አቅም ያላቸው ለመሆናቸው ጥርጥር የለኝም። ውብሸት ከመጡ ወዲህ ባሉት ወራት ተጨባጭ አበረታች ለውጦችን አይተናል። ነዋሪውን በአደረጃጀትም ይሁን በግል፣ ፈርጀ ብዙ በሆነ የተለያየ መንገድ እያገኙ በረጋ መንፈስ አድምጠውታል! ውብሸትን ነዋሪው ተስፋ ጥሎ አምኗቸው ከቆንሰሉ የከረመ የባጀ የበከተ የውስጥ ቢሮክራሲ የተበተበው የቆንስላ ጽ/ቤት አሰራር የማስተካከል ስራ ጀምረው ነበር። ውብሸት መላ ጠፍቶ ሲንከላወስ የከረመውን ኮሚኒቲ ለማደራጀት ያለውን የአደረጃጀት ብቸኛ አማራጭ ተጠቅመው ለማዋቀር አልሰነፉም። ውብሸት በየአጋጣሚው ከነዋሪው ተገናኝተው ነዋሪው ጨንቆት ከርሟልና የሆድ የሆዱን ሁሉንም ዘክዝኮ የነገራቸው ብቸኛ ሹም ናቸው። እርግጥ ነው፣ ብልሁ አምባሳደር ውብሸት “ለችግሩ ሁሉ መፍትሔ የሚገኘው የተባብረን ስንሰራ ነው!” በማለት አነቃቅተውነወ ፣ ብሩህ ተስፋም አሰንቀውን ከርመዋል . . .!
ዳሩ ግና ዛሬ ያለው ነባራዊ እውነት አያስደስትም፣ ተሀድሶውን በስኬት የጀመሩት አምባሳደር ውብሸት የውስጥ እክል የጠለፋቸው ይመስላል። ውሎ ሲያድር ተስፋው እየጨለመ መጥቷል! ይህንን ሂደት ውስጥ አዋቂዎች ሲያሸሙሩት “ምስጉኑ አምባሳደር ውብሸት የፖስፖርቱን ወረፋ ስርአት ከማስያዝና አንዳንድ ችግሮች ለመቅረፍ ከመሞከር ባለፈ እንዳይሰሩ እየተሰናከሉ መጥተዋል!” ይሏቸው ይዘዋል…
በኮሚኒቲው እንዳሉት አይጦች ገንዘብ ሸቶት የሚያነፈንፍ ባይሆንም የማህበረሰቡን ጥቅም የተጉትን የሚሸበርክ፣ ርዕዮት አለም አምላኪ፣ ለሰብዕና ቅድሚያ የማይሰጥ፣ የማይታይ ግን የተቧደነ “ጅብ አለ!” አሉ እዚህ ቤት … ብርቱዎችን የሚያሸበርክ፣ የማይበገር ተጽዕኖ ፈጣሪ “ጅብ” የተባለ መንፈስ …
አንድ በእንስሳትን ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ከዱባይ የሚተላለፍ ጆግራፊክ ጣቢያ የምታይ ወዳጀ ስለ ጅብ ክፉነት ያጫወተችኝ አይዘነጋኝም። እንስሳውን ጅብ አትወደውም፣ ከመጥላቷ የተነሳ ደግሞ “እርጉም ነው!” ትለዋለች፣ ምነዋ? አልኳት ባንዱ ቀን “ጅብ እንደ አንበሳ ገድሎ አይበላም፣ ነፍስ ሳትወጣ በጫጭቆ የሚበላ አውሬ ነው!” ስትል ጭካኔውን አጫወተችኝ የክፉውን ጅብ … የእኔ ምዕናብ ፈጠር ” ጅቦች ” ህዝብን ለማገልገል የመጡ ተወካዮች ተግተው እንዳይሰሩ፣ ኃላፊዎች ተሾሙባቸው ሲመጡ ሀይላቸው ያሳዩዋቸዋል። ኑሯቸውን እንዲገነቡ እንጅ በማህበረሰቡ ጥቅምና መብት ማስጠበቅ ከተጉ እንደሚገፉ በእጅ አዙር ያስፈራሯቸዋል። ማስፈራራት ብቻ አይደለም፣ የጅዳ ቆንስል ወንበር እንዳይረጋ አድርገው፣ ትላልቆችን አዋርደው ሸኝተዋል! አምባሳደር መርዋና ቆንስል ጀኔራል ዘነበ አራት አመት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ በአስቸኳይ እየተጠሩ ላይመለሱ ተሸኝተዋል … ” ምክንያቶቹ “ጅቦች” ናቸው! ትላልቆቹን ዝቅ ያደረጉት የዚያ ቤት ተጽዕኖ ፈጣሪ “ጅቦች” እንደ አምባሳደር መርዋና ቆንስል ጀኔራል ዘነበ ሁሉ አምባሳደር ውብሸትን የሚተዋቸው ባይመስልም፣ ውብሸት የኃይል ሚዛኑን አዟዙረው ቢያጤኑት በብዙሃኑን ነዋሪ ተቀባይነት አላቸውና ላለመገፋት ጉልበቱና ድጋፉ ያላቸው አይነት ወንድም ናቸው! ይህን አጢነውት እንደሁ እንጃ . . .
ዛሬ ዛሬ አምባሳደር ውብሸት ተቀያይረዋል እንላለን፣ ምን እንደነካቸው ባናውቅም ተሀድሶ ጀማሪው አምባሳደር ውብሸትን ቀዝቀዝ ብለዋል …! ጉዳዩን የሚሰሩ ያሉት ፣ ላይ ታቹን የሚያዙ የሚያተረማምሱት የቀደሙት ” ጅቦች” መሆናቸው በሰፊው እየተነገረን እያየንም ነው። ይህ ያስፈራል፣ ይህ እንዲህ ከቀጠለ ችግር ይኖራል! ይህ ደግሞ ወደ ቀድሞው መደናቆር እንዳንመለሰን ያሰጋኛል!
“ጅቦቹ!” የአንባሳደሩን ተሀድሶ ያኮላሹት ይሆን ?
“ጅቦቹ!” የአንባሳደሩን ተሀድሶ ያኮላሹት ይሆን? አዎ! ለዚህ መልሱን የምናገኘው ሰነባብተን ሊሆን ይችላል፣ ዛሬ ግን አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻውን የዜጎች ጥያቄ መልስ ያገኝ ዘንድ የሚመለከታችሁ የመንግስት ተወካዮች ድምጻችን ልትሰሙት ይገባል! ብላቴናውን መሀመድ ጉዳይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅድሚያ ህክምናና የሚያገኝበት ይፈለግለት! ሲቀጥልም “9 ዓመት ለተንገላቱት፣ ለተንከራተቱ ቤተሰቦች ካሳ ለማስገኘት ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ተመርቷል!” የሚል ጭብጥ መረጃ ይሰጠን!
ከአራት ወር በፊት ወደ ሀገር ሊላክ ሳምንት ቀረው የተባልነው ስደት ያሰናከለው ወጣት አባወራ መሀመድ ሁሴን ከናፈቃቸው ልጆቹና ከቤተሰቦቹ እንዲገናኝ ወደ ሀገር ይሸኝ ዘንድ ደግመን ደጋግመን እንማጸናችኋለን! ጀሮ ያለው ይስማ!
እስኪ ቸር ያሰማን!
ነቢዩ ሲራክ
ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓም
Leave a Reply