
በተለያዩ ቦታዎች በሕገ-ወጦች አማካኝነት ተከማችቶ የተገኘ ብረት በሕጋዊ መንገድ ወደ ገበያ ገብቶ እንዲሸጥ እና ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን መወሰኑን ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በ13 የተለያዩ ቦታዎች በህገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘውና በዋጋ አረጋጊ ግብረ-ሀይል በቁጥጥር ስር የዋለው ከ1ሺ በላይ መኪና ብረት በህጋዊ የግብይት ስርዓቱ ውስጥ ገብቶ እንዲሸጥና ገቢው ለመንግስት እንዲገባ መወሰኑን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሌላ በኩል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ሲሚንቶ እና የቴሌ ጥቅል ኬብል በመኪና ሲያጓጉዙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክፍለ ከተማው የህዝብ ግንኙነት ቢሮ አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ ትናንት ምሽት በወረዳው አደይ አበባ ስታዲየም አካባቢ ጨለማን ተገን በማድረግ 400 ኩንታል ሲሚንቶ እና ጥቅል የቴሌ ኬብሎችን በሁለት ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች ጭነው ሲያጓጉዙ በአካባቢው ኅብረተሰብ ጥቆማ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፊሊሞን በጋሻው አስታውቀዋል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የገለጹት ፊሊሞን፤ አስተዳደሩና የወረዳው ኮማንድ ፖስት በማንኛውም መንገድ ወቅታዊ ፈተናን ጨለማን ተገን በማድረግ የሚደረጉ ሕገወጥ ተግባራት ላይ ቁጥጥሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ በመግለጽ የተጀመረው የሕዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply