• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የገዢዎቻችን መጨረሻና የተከተላቸው ሀቅ

March 5, 2014 05:30 am by Editor Leave a Comment

የመጨረሻውን በማያውቁት ያዘቀዘቀ ጨለማ መንገድ እየተውዘረዘጉ፤ መሪዉን በማስተካከል ከማያውቁት መጨረሻ ለመድረስ የሚጣድፉ መሪዎች፤ የድንቁርና ኒሻን ይገባቸዋል። በፈጠሩት የራሳቸው የመኖሪያ የገዢነት መኮፈሻ “ሀቅ” ተጀንነው በመቀመጥ፤ ፈንጠር ብሎ ርቆ ሌላውን ማየት ባለመቻላቸው፤ የተከተላቸውን ሳይውቁት እጃቸውን ሠጥተዋል። የተለዬ የመሰለ የራስ “ሀቅ” የብዥታ ጭጋግ፤ ሩቅ ማየትን ነፈጋቸው። ማስተዋልን ከአእምሮ መዝገባቸው ሰወረው። መደናበርን አነገሠባቸው። ካይናቸው ፊት በተገተረው የእብሪታቸው መነፅር፤ ዓለምን ግቢ ውጪ እያሉ በማስገደድ፤ ያለው የሌለ ሆኖ፣ ከተጨባጩ ይልቅ በምኞታቸው ዓለም ሲዳክሩ፤ የቆሙበት መሬት ከዳቸው። ከሕዝቡ መሆናቸው ቀርቶ ሕዝቡ የነሱ አገልጋይ ሎሌ ሆነና፤ የነሱ መኖሪያና የሕዝቡ መኖሪያ በአጥር ተለያዬ። መኖሪያቸው ዓለማቸው ሆነና ከሕዝቡ ዓለም ወጡ። ረጋ ብለው ያሉበትን ለመመርመር ጊዜ አጠራቸው። ያጠራቸው ጊዜ ጥሏቸው ሄደ። እናም ባሉበት ቆመው ቀሩ።

መንግሥትን ለመምራት፤ ከፍተኛ ብስለትና ጥንቃቄ ታላቅ መሣሪያ ናቸው። መንግሥትን ማስተዳደር ማለት፤ ሕዝቡን “ጠላት” እና “ወዳጅ” ብሎ በመፈረጅ፤ ወዳጅን መጥቀምና ጠላትን መጉዳት በሚል ጋቢ ከተሸፈነና በዛሬ ወንበር ተኮፍሰው ከተጀነኑ፤ ነገ የራሷን ወዳጅና ጠላት ከሕዝቡ መካከል አበጅታ ከጎን ብቅ ስትል፤ የሚይዙትን ታሳጣለች። ለሁሉ ጥሩ ነገሮች ባለቤት “ወዳጅ” ብሎ የፈረጀውን ወገን ያቀሰሰና ለሁሉ ነገር መጥፎ ባለንብረት፤ “ጠላት” ብሎ የፈረጀውን ሠፈር የወነጀለ ገዢ፤ መጨረሻው አያምርም። የኛ ገዢዎች እንዲያ ነበሩ፤ አሁንም እንዲያ ባይ በጀርባችን ተሸክመናል። ፍርሃትን በሕዝብ በመዝራት ለመግዛት የተነሱት ገዥዎቻችን፤ ራሳቸው በፍርሃት ተውጠው ከሕዝቡ ራቁ። ሕዝቡን ጠላት አድርገው ፈረጁት። የሚችሉትን ያህል ፈጁ። መውደቃቸው የጊዜ ጉዳይ ሆነ።

ገዢዎች ከአመጣጣቸው ማንነታቸውን መገንዘብ ይቻላል። አንድ የተለዬ ወገን ቦድነው የመጡ ክፍሎች፤ ያንኑ ምርኩዝ ይዘው እስከመጨረሻው ሲሄዱ አየናቸው። ያ አመጣጣቸው ለተከተሉት ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያቸው፤ መነፅራችን ነው። እናም እምነታቸውና ተግባራቸው ይኼንኑ አንፀባረቀልን። እብሪት የጉልበተኞች መመኪያ ነች። እብሪተኞች ዘለዓለማዊ ነን ይላሉ። በሥልጣን ላይ ሲሆኑ የረጋ አእምሮን መንገድ መጥረግ ያቆማሉ። በስሜትና በፍላጎት መብራት ጨለማውን ለማለፍ ይደናበራሉ። የኛዎቹ የሀገራችንን የተፈጥሮ ሕግ ጠምዝዘው ሊዘውሩ ሞከሩ፤ በሂደቱም ራቁታቸውን ተጋልጠው ቆማ። ንጉሡ ባሉበት ደነዘዙ፣ ደርጋማው መንግሥቱ ጭራውን ቆልፎ ወደ ሐራሬ በመፈርጠጥ ምሽግ ውስጥ ተደበቀ። ያሁኖቹ ደግሞ በተራቸው የት ይገቡ ይሆን?

እኔ ራሴ ባየኋቸው ሶስት የተከታተሉ ገዢዎቻችን፤ ይህ ሀቅ በጣም ጎልቶ ታይቷል።

በመጀመሪያ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ራሳቸው በፈጠሩትና ባመኑበት “ከአምላክ የተቀባሁ ነኝ!” ባይ እብሪት፤ ሕዝቡን ለሳቸው የተሠጠ አገልጋይ በማድረግ፤ ጊዜ ሲለውጥና የዓለም ፖለቲካ መልኩን ሲቀያይር፣ ከኋላችን የነበሩትና አዲስ ነፃ የወጡ የአፍሪቃ ሀገሮች ቀድመውን ሲሄዱ፣ በሀገራችን በሚሠጠው ትምህርት የዓለምን ግስጋሴ የተገነዘበው የተማረው ክፍል የስልጣኔ ናፍቆቱ ሲያድግ፣ የዓለም ህዝብ የኑሮ ደረጃ ከፍ እያለ ሲወጣና የኛ ኑሮ ባለበት ከመዘፍዘፉ የተነሳ የኋሊት ጉዞ ሲጀምር፤ ያመኑበት መለኮታዊ ገዢነታቸው ዓይናቸውን አውሮ ማየት ተሳናቸው። እናም የግል ጠባቂ ብለው ያደራጁት የጦር ኃይል ያለበት የኑሮ ሁኔታ አላስጨነቃቸውም። ሁሉም በተዓምርና በሳቸው ምኞት ብቻ የሚመራ አድርገው ሲያዩት፤ ታሪክ ያልተገናኙ አድርጎ ከሥራቸው መሬት ካዳቸው። እናም ሲነቁ በጨለማ ተውጠው የሚጨብጡትን አጡ። ተነድተው የታሪካቸው የመጨረሻ ምሽት፤ ባልታወቀበት ቦታ ሆነ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በየካቲት ፲፱፻፷፮ ዓመተ ምህረት ባንድነት ተነስቶ የራሱን መንግሥት ለመመሥረት ሲዘጋጅ፤ ባቋራጭ የገባው የወታደሮች ቡድን አብዮቱን አኮላሸው። በሂደቱም አንድ አምባገነን ወጥቶ፤ የፈራቸውን፣ የጠላቸውን፣ በሕልሙ የሚያስበረግጉትን፣ ለሱ ሠጥ ለጥ ብለው፣ አሜን ጌታዬ ብለው ያልተገዙለትን በማሰር፣ በመግደልና በተለያዬ መንገድ በማጥፋት ሊገዛ ተነሣ። ሰዎችን እንደ ጠጠር በፈለገበት ማስቀመጥና ማዞር፣ ማሽከርከርና መጣል የዕለት ተዕለት ተግባሩ ሆነ። ራሱን ኢትዮጵያ፣ የሱን ተቃዋሚ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ፣ እሱን ያልተቀበለ ኢትዮጵያን ያልተቀበለ በማድረግ ሊገዛን ፈለገ። በመሐል ቤት ራሱ በሚያልመው መነፅር ሀገሪቱንና የሀገሪቱን የፖለቲካ ሀቅ እየተመለከተ ከህዝቡ ተለዬ። ሕዝቡ ለማያባራ ጦርነት ልጆቹን መገበር እምቢ አለ። ሕዝቡም መጥፎ ነገር እንደነካ እንጨት ራቀው። እናም ብቻውን ቀረ። ዙሪያውን ሲከበበ፤ ጅራቱን ቆልፎ እንደሚሮጥ ፈሪ ውሻ፤ እግሬ አውጪኝ ብሎ ወደ ሐራሬ ፈረጠጠ።

በቦታው የተተካው ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ደግሞ፤ ራሱን ልዩና ብቸኛ ሆኖ የተፈጠረ አዳኝ በማድረግ፤ ለሁሉም ነገር እሱ ብቻ መፍትሔ አዋቂና ራሱ ብቻ ትክክለኛ ሆኖ በመቅረብ፤ እሱም እንደቀደሙት ሁሉ፤ ሕዝቡ ገዢው የሚለውን የሚሰማ፤ ገዢው የሚያዘውን የሚፈፅም አድርጎ እየገዛ ነው። በዚህ ተግባሩ ከሕዝቡ ተነጥሎ ተንሣፏል። ቀደም ያሉ ገዢዎቻችንን ያስቆጧቸው ወገኖች በሥራቸው እንዳቆጠቆጡት ሁሉ፤ በአዲሱ ገዥዎቻችን ላይም የሕዝብ ወገን የሆኑ ተቃዋሚዎች በየቦታው ተኮልኩለዋል። አሁንም ያለበትን ሀቅ ሳይሆን፤ የሚያልመውን እየተቀበለ እውነቱን ማየት አቃተው። ጊዜያዊ የመሰለያ አምስት ለአንድ ጥፋሮውንና ወታደራዊ ጥንካሬውን የማይበገር ምሽግ አድርጎ ወስዶታል። የሚታየውን በሀገሪቱ የሠፈነ የኅብረተሰብ ችግርና የኑሮ ሁኔታ እንዳያይ የራሱ ቅንጦትና ምቾት አውሮታል። እንደቀድሞዎቹ ራሱን ዘለዓለማዊ አድርጎ ወስዷል። እንደቀደሙትም ተራውን እየጠበቀ ነው።

ለኔ፤ የወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ቡድን ነገ፤ ጉዳዬ አይደለም። ጉዳዬ፤ የኛ የኢትዮጵያዊያንና የሀገራችን የኢትዮጵያ ነገ ነው። እንደትናንቶቹና ዛሬ በዙፋኑ ላይ ቁጢጥ እንዳለው፤ ሌላ አምባገነን ገዢ እንዲተካ አልፈልግም። የእስከዛሬው አንገፍግፎኛል። ይህ ምን ጊዜም መረሳት የለበትም። ግፉ እንዲቀጥል በምንም ሁኔታ መንገድ አሠልጢዎች መሆን የለብንም። ታዲያ እኛ ምን ማድረግ አለብን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። መልሱን ደግሞ ነገ ሳይሆን ዛሬ መሥጠት አለብን። እጆቻችን አጣጥፈን መጪውን መጠበቁ፤ በተዓምር ኢትዮጵያዊያን የምንፈልገውን ሀቅ እንዲከተል አያደርግልንም። እናም እኔ ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ። ብቻዬን የምጥረው የትም እንደማያደርስኝ አውቃለሁ። ችግሩ የሁላችን የኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነው። መፍትሔውም በሁላችን በኢትዮጵያዊያን ጥረት የሚገኝ ነው። እናም ለርስዎና ለመሰሎችዎ ጥያቄ አለኝ።

ያሁኑ ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ሲወገድ ምን እንዲተካ ነው የሚፈልጉት?

ይህ እንዴት ሊመጣ ይችላል?

የኔና የርስዎ፤ የያንዳንዳችን አስተዋፅዖ ምንድን ነው ይላሉ?

የኔን ላጋራዎ፤

አሁን በሀገራችን ያለው ወራሪ ዓይነት ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ነው። ሀገራችንን ወደ ከፍተኛ አደጋ እየመራት ነው። የነገው የሀገራችን ዕጣ አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቋል። እኛ የዚህን ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መከታተላችን፤ ኢትዮጵያዊያን የምንፈልገውን ሕዝባዊ አስተዳደር አያመጣልንም። የራሳችንን ተግባር ነው መወሰን ያለብን። ሀገር አቀፍ የሆነ ሁሉን ኢትዮጵያዊያንን ያጠቃለለ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ፤ የዴሞክራሲያዊ አሠራር መሠረቱ ሲጣል ብቻ ነው አስተማማኝ የሆነ የወደፊት የሚኖረን። ለዚህ ደግሞ ሁላችንን የሚካትት ራዕይና ተልዕኮ ሊኖረን ይገባል። ይህ መንግሥት በሕዝቡ ግፊም ሆነ ራሱ በውስጡ በመንቀዙ መውደቁ አሌ አይባልም። ጥያቄው መቼ? ብቻ ነው።

በኔ እምነት፤ ኢትዮያዊነታችንን የተቀበልንና የሕዝቡን ትግል የምንደግፍ ሁሉ፤ በመጀመሪያ ማመን ያለብን፤ የምንፈልገው ተከታይ ሥርዓት፤ ለምናደርገው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ነው። ምን እንፈልጋለን? በአንድነት ሆነን ተሰባስበን በምናደርገው የአደረጃጀት ተሳትፎ፤ በግል ወንም በቡድን ሥልጣን መያዝ ወይንም አንድን ርዕዩተ ዓለም የማራመድ ጉዳይ ቦታ የለውም። ቦታ ያለው፤ በአንድነት ሁላችን፤ ሀገራችን ከዚህ ወራሪ ከመሰለ አስተዳደር ነፃ ወጥታ፤ ሕዝቡ የወደደውን መንግሥት ለማቋቋም መሸጋገሪያ መንገድ ማዘጋጀቱ ነው። ሕዝቡ የወደደውን ከመምረጡ በፊት የመሸጋገሪያ ወቅት አለ። እናም የኛ የትግሉ ተሳታፊነት በትግል ዕሴቶቻችን ይመራል። እናም የትግል ዕሴቶቻችን የሚከተሉት ናቸው፤

ሀ) ሕዝቡ ሉዓላዊነቱ ተከብሮለት፣

ለ) የሀገራችን አንድነት ተጠብቆ፣

ሐ) የሕግ የበላይነት ሠፍኖና፤

መ) የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው፤

የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን የሚያመቻች የሽግግር መንግሥት መቋቋሙ ነው። እኒህ አራት የትግል ዕሴቶች ሁላችን በታጋይ ክፍል የተሠማራነው የምንጋራቸው ስለሆነ፤ በነዚህ ዙርያ መሰባሰቡ ወደ አንድ ወገን ያመጣናል። እናም እነኚህን አራት የትግል ዕሴቶች የተቀበልን ኢትዮጵያዊያን፤ በኢትዮጵያዊነታችን መሰባሰባችን ግዴታ ነው።

ታሪክ ጥሏቸው ሲጓዝ ባሉበት ቆመው የተያዙትን ገዢዎቻችንን እናጢን። ኃላፊነቱ የኛ ነው ብለን እስካልጨበጥንና ግዴታችንን እስካልተወጣን ድረስ፤ ሌሎች በሚያመጡት ለውጥ የኛን ፍላጎት እንዲሟላ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጡ፤ በቀላሉ ጅልነት ነው። ከአፄው የከፋና የከረፋ ደርግ ተከተለ። ከደርግ የገማና የተግማማ ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ ተከተለ። የከፋ አይመጣም እያልን የተሻለ ባጠገባችን አላልፍም አለ። የሚቀጥለው የመዓት ነው! እኛ ካላወቅንበት! ምን ይላሉ?

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • በወልቃይት 1.1ሚሊዮን ኩንታል ሰሊጥ ለመሰብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሠራተኛ ይፈለጋል September 27, 2023 10:42 am
  • በአማራ ክልል ሰላም ዕጦት ከ90.5 ቢሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክቶች ቆመዋል September 27, 2023 08:41 am
  • ወርቁ አይተነው የሸሹት ከዝርፊያ፣ ውንብድናና ዕዳ ጋር በተያያዘ ነው September 21, 2023 02:38 pm
  • ወደ አማራ ክልል ሊተላለፍ የነበረ መሣሪያና ሰነድ ተያዘ September 19, 2023 04:35 pm
  • በትግራይ መርዶ በይፋ ሊታወጅ ነው September 19, 2023 04:22 pm
  • ጃርቶች ለምን ይጮኻሉ? September 19, 2023 04:37 am
  • “ዐቢይ ግድቡን ሸጦታል” ጌታቸው ረዳ September 11, 2023 10:18 am
  • አቶ አገኘሁ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ዋጋ እንደሚከፍሉ ተሰማ September 10, 2023 06:52 pm
  • ለዋዜማ ሬዲዮ “ኢትዮጵያን ቋሚ የውሀ ባለ እዳ” ያደርጋል ያላችሁት ረቂቅ ሰነድ የታለ? September 10, 2023 01:58 am
  • ወደር የሌለው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና! ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም September 8, 2023 02:31 pm
  • የትግራይ መፍረስ በርዕሰ መስተዳደሩ አንደበት September 8, 2023 02:49 am
  • ከያቤሎ አዲስ አበባ የተላከ ኮንትሮባንድ ጉለሌ ተያዘ September 7, 2023 01:40 pm
  • “እንኳን ተለያይተንና እርስ በርስ ተባልተን በአንድነት ቆመንም ወጀቡን መሻገር አቅቶናል” September 7, 2023 01:31 am
  • ራሱን መሪ አልባ የሚያደርገው አማራ ክልል August 24, 2023 11:50 pm
  • ጀብደኛው August 24, 2023 10:06 am
  • ጎንደርና ባሕር ዳር ከተሞች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው ተመልሰዋል August 13, 2023 10:55 pm
  • ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል አስመረቀች August 13, 2023 10:26 pm
  • ሪፖርተር የፓርላማ ወንበር አስልቶ የአስቸኳይ አዋጁ በፓርላማ እንዳይደገፍ አቅጣጫ አመላከተ August 13, 2023 09:11 pm
  • ወደ ኤርትራ በኮንትሮባንድ የሚሻገሩ ቆሳቁሶች እየተያዙ ነው August 11, 2023 12:52 pm
  • የአማራ ክልል ትልልቅ ከተሞች ተኩስ ዓልባ ሆነው ውለዋል August 10, 2023 04:31 pm
  • “አንድ ሰው ለመግደል ኅንፃውን ማቃጠል” የኢ-ዲሞክራሲና ጽንፈኛ ኃይሎች ቅዠት፤ (ክፍል ሁለት) August 10, 2023 09:44 am
  • “አርበኛ” መሳይ – “የድል ዜና” ሳይበርድ 50ሺህ ዶላር በጎፈንድሚ August 10, 2023 09:08 am
  • በሕዝቡ ድጋፍ ከተሞች ከዘራፊው መንጋ ሥጋት ነጻ መሆናቸው ይፋ ሆነ August 9, 2023 11:47 am
  • ትህነግ አራተኛውን ሞት ሞተ  August 8, 2023 05:47 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule