አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ
ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?
ይህ ታሪክ አይደለም። ታሪክ ያለፈ ነው ነገር፣ ያለፈ ጉዳይ ነው። ታሪክ ከከርስቶስ ልደት በፊት፣ የምንሊክ ንግሥና ጊዜ፣ የጣሊያን ወረራ ጊዜ፣ የመንግሥቱ ንዋይ ግርግር ጊዜ፣ ወያኔ አዲሳባ የገባች ጊዜ ተብሎ ይጀመራል …. እና ያልቃል። አዎን ያልቃል። እንኳን ሌላው ቀርቶ ሰማይና ምድር ያልፋሉና!
ይህ የማላቀቸው ሰውዬ ታሪክ ነው ብዬ ብጀምር ይቀለኝ ነበር – ታሪክ ያለቀ ነገር ነውና! ያለቀ ነገር ህሊናን አይቦረቡርም። መጥፎ እንኳን ቢሆን የሚያጽናና ነገር ትቶ ያልፋልና። ምሳሌ፣ ጣልያን አቡነ ጴጥሮስን በግፍ ገደለ። የአቡኑ መሰዋት ግን ሺዎችን ለነጻነታቸው አነሳሳቸው። ይህ መጽናናትን ይሰጣል። የማላቀቸው ሰውዬ ታሪክ ግን አላለቀም። የማያልቅ ነገር ምን ይባላል? ምን ተብሎ ይጀመራል?
ህንጻው ንግሥተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘውድ የደፉበት ነው። ህንጻው የተገነባው በእምዬ ምንሊክ በተማረኩ “ጥልያኖች” ነው። ህንጻው በጣልያኖች የቁጭት ስሜት ተቃጥሎ የነበረና እንደገና የታነጸ ነው። ህንጻው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግስናን ዘውድ የደፉበት ነው። ህንጻው የራስ ተፈሪያን የ“ሽንብት“ – pilgrimage ሥፍራ ነው። ህንጻው ያፈወርቅ ተክሌን ጥበባዊ ሥራ የያዘ ነው። ህንጻው ታሪካዊ ነው። ህንጻው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን ነው።
አመሻሽ ላይ በግሬ መጓዝ አዘወትራለሁ። በመንገድ ላይ ያለውን ሁሉ እያየሁ፣ ከራሴ ጋር እየተወያየሁ፣ ከራሴ ጋር እየተወያየሁ፣ ከራሴ ጋር እየተወያየሁ …። ጭንቅላቴ እስኪፈነዳ! እሄድ እሄድና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን እገባለሁ። አጥር ጥግ እቆምና ከራሴ ጋር መወያየቴን ቀጥላለሁ … ጭንቅላቴ እንዳይፈነዳብኝ ጥርቅም አድርጌ ይዤ።
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ዛሬም እንደተለመደው ጭንቅላቴን ጥርቅም አርጌ ይዤ አንድ ጥግ ቆሜ እያለሁ መጡ። ሽማግሌ ናቸው። የያዙትን ሁላ መሬት ላይ አስቀመጡ። ጣሉት ማለት ይቻላል። ድንገት….
ካድማስ እየራቀ ምነው ይኸ መንገድ ያባክነኛል
በየት በኩል ብሄድ ወደ እረፍት ሃገሬ ቶሎ ያደርሰኛል?
ሲሉ ሰማሁ። ተጠራጠርኩ። እሳቸው ናቸው እነዚህን ሥንኖች የወረወሯቸው? ሥንኞቹን አውቃቸዋለሁ።
“የቴዲን ዘፈን ይወዱታል?” ጠየቅኳቸው?
“ማነው ቴዲ?” ቢሉኝ ግራ ገባኝ።
“ማለቴ … የዘፈኑ ባሌቤት ነዋ”
“ዘፈኑ አልከኝ?” ዝም አልኩ። ያበዱ የኔ ቢጤ ናቸው ብዬ ደመደምኩ። እና ከራሴ ጋር መወያየቴን ቀጠልኩበት። ‘እኛኮ’ አልኩኝ። ‘እኛኮ የምንገርም ፍጡሮች ነን። ቅልጥ ያልን ሃብታሞች ሆነን ለማኙን ለማኝ አንልም። የኔ ቢጤ እንላለን። እንደኔ አይነት ለማለት። ቅልጥ ያለው ሃብታም ድሃውን ለማኝ የኔ ቢጤ ብሎ ሲጠራ ምን ማለት ነው? ማሾፍ ነው? ማዘን ነው? ካዘነ ለምን ከሃብቱ አያካፍለውም? ለምን ከድህነት፣ ከልመና እንዲወጣ አይረዳውም? ሃብታሙ ሰው ለማኙን የኔ ቢጤ ማለቱ ግብዝነት አይደለምን? “አይደለምን” – ልክ በመጽሃፍ ቅዱስ እንደሚጻፈው አድርጌ፣ ብዬ ራሴን ጠየቅሁት። ከዚያም በልቤ
በል አትዛል ቀና ሁን ልቤ
የህልሜን ከንዓን እንዳይ ቀርቤ
ብዬ አዜምኩ በሆዴ፣ በልቤ።
“ዛሬ መኪና እንዲገጨኝ እየተንደረደርኩ አስፋልት መሃል ብገባ ሹፌሩ ሲጢጢጢጢጢ አድርጎ አቆመና የሥድብ መዓት አወረደብኝ። ‘አህያ መሰለህ እንዴ? እንደ ጫጩት ይደፈጥጠሃል! የት ነው የምትጣደፈው?’ ሲል ወረደብኝ። እሱ አያቀኝም፣ እኔ ግን አውቀዋለሁ።”
“ሹፌሩን ያውቁታል? የሚያውቁት ሰው እንዲገጭዎ ነው የሚፈልጉት?”
“አዎን! ምናለበት? እረፍት አማረኝ ልጄ? እስከመቼ እየተንከራተትኩ ልኑር? እስከመቼ እየለመንኩ እኖራለሁ?”
ቀስ በቀስ ተገለጸልኝ።
ካድማስ እየራቀ ምነው ይኸ መንገድ ያባክነኛል
በየት በኩል ብሄድ ወደ እረፍት ሃገሬ ቶሎ ያደርሰኛል?
ራሳቸውን ማጥፋት ፈልገው ነው ይህንን ያሉት። ገባኝ። ግን ለምን የሚያውቁት ሰው እንዲገጫቸው ይፈልጋሉ? ምን መመለሥ እንደሚገባኝ አላወቅኩም።
“ይህ እኮ አጥያት ነው” አልኩኝ።
“ምኑ?”
“እግዜር የፈጠረውን ነፍስ …” አልጨረስኩትም።
“እግዜር የፈጠረውን ነፍስ ማጥፋት? ይቺ የምትሰቃየውን ነፍስ እንዳትሰቃይ ማጥፋት ነው አጥያቱ? ያልተነካ ግልግል ያውቃል አሉ።” በትዝብት አይን ቃኙኝ።
“ማለቴ….” ማለቴ አልኩኝ። ምን ማለቴ እንደሆነ አላውቀውም። ምን ማለት እንዳለብኝም፣ እንደሚገባኝም አላቅም። ግራ ገባኝ። ጭንቅላቴ እንዳይፈነዳብኝ ጥርቅም አርጌ ያዝኩ።
“ያልተነካ ግልግል ያውቃል አሉ። አየህ፣ አየህ” አሉኝ ጣታቸውን ቀሥረው።
“አየህ እኔ ረሃብ የተፈራረቀብኝ ሰው ነኝ። ያለየሁት ረሃብ የለም። የኃይለ ሥላዜ ዘመን ረሃብ፣ የደርግ ዘመን ረሃብ፣ በኢሃድግ ዘመን ደግሞ በየአመቱ የሚመጣው ረሃብ፣ ሁሉም ተፈራረቁብኝ። ተፈራረቁብኝ! ሁሉን ችዬ ኖርኩኝ። ረሃብ ሲመጣ እየተሰደደኩ እየለመንኩ ኖርኩኝ። የሞተብኝን ቀብሬ፣ ችግሬን በሆዴ ቀብሬ ኖርኩ። የትም ተሰድጄ ለምኘ፣ ነፍሴን ከመሞት አድኜ ሥመለስ ታዲያ ያቺ ጎጆዬ ትጠብቀኛለች። ደስታም ሃዘንም ያየሁባት ጎጆዬ። ሁሉን ችዬ የኖርኩባት ጎጆዬ፣ ቀየዬ ትጠብቀኛለች። እስከዛሬ ተራብኩ፣ ተቸገርኩ ብዬ አላማረርኩም።”
አንተ አብርሃም የኦሪት ስባት
የእነ እስማኤል፣ የይስሃቅ አባት
እንደ አክሱም ራስ ቀርፀሃት ራሴን
በፍቅር ጧፍ ለኩሳት ነብሴን
ብዬ አዜምኩ። ጭንቅላቴ እንዳይፈነዳብኝ ጥርቅም አርጌ ይዤ። ሰውየው ቀጠሉ።
“አዎን ልጄ! ኖርኩ። ኑሮ ከተባለ ኖርኩ። እስከዛሬ ኖርኩ። ዘንድሮ ግን የባሰው መጣ።”
“ዘንድሮ ምን መጣ? ከተለመደው ረሃብ ውጪ ሌላ ነገር ደግሞ ምን መጣ?” ራሴን ጠየቅኩት።
“ዘንድሮ እንደተለመደው በረሃቡ ምክንያት ተሰድጄ ለማምኜ ነፍሴን አድኜ ወደ ጎጆዬ ብመለስ፣ ጎጆዬ የለችም”
“እንዴ? ምን ማለትዎ ነው? ሃይለኛ ንፋስና ዝናብ አፈረሳት?”
“ዝናብ አይደለም። ግን ልክ ነህ ሃይለኛ፣ ጉልበተኛ ነው ያፈረሳት”
“አልገባኝም አባቴ”
“ሃይለኛ ነዋ! ጊዜ የሰጠው ሃይለኛ ነዋ! ቦታው ለልማት ይፈለጋል ብሎ አፈረሳት። አባረረኝ። ጎጆ የለኝ። ቀየ የለኝ። አያት ቅድማያቶቼ ያወረሱኝን ተነጥቄያለሁ፣ በገዛ ሃገሬ ስደተኛ ሆኘ እያየኸኝ፣ ልጄ። እንግዲህ እኔ እኮ ሞቻለሁ። የሞተ ሰው ራሱን ቢያጠፋ አጥያት ነው?እንግዲህ እኔን የቀረኝ አንድ ነገር ቢኖር የገደለኝ ሰውዬ መግደሉን እንዲገነዘብ ማድረግ ነው። የገደለኝ ሰውዬ የት እንደሚኖር፣ ምን እንደሚሰራ ደርሸበታለሁ። የሚነዳትንም መኪና ጭምር አውቃለሁ። ዛሬ አልተሳካልኝም።”
ምን ማለታቸው እንደሆነ ቀስ በቀስ ተገለጸልኝ።
“መሬትዎን የወሰደብዎ ሰው በመኪናው እንዲገጭዎ ይፈልጋሉ?”
“እሱኮ አንዴ ገድሎኛል። መግደሉን ግን የተገነዘበ አይመስልም። እኔ ደግሞ እንዲገነዘብ ማድረግ ነው የምፈልገው። ገባህ?”
ጭንቅላቴ እንዳይፈነዳብኝ ጥርቅም አርጌ ያዝኩት። ኪሴ ውስጥ የነበረኝን ገንዘብ አወጣሁና እጄን ዘረጋሁ።
“እግዜር ይስጥልኝ ልጄ። ይሄ ለኔ አያስፈልገኝም። አንተው ያዘው።”
ወደ ቤቴ ሄድኩ።
በሁለተኛው ቀን እንደተለመደው ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን አቀናሁ። ቤተክርስትያኑ ልደርስ ትንሽ ሲቀረኝ መሃል አስፋልቱ ላይ ሰዎች የከበቡት መኪና ይታያል። ከከበቡት ሰዎች አንዱ ወደኔ አቅጣጫ መጣ። ጠየቅሁት ምን እንደሆነ።
“አንዱን ለማኝ መኪና ገጭቶት ነው”።
“ሞቷል?” በጩኸት ጠየቅሁት።
”እኔ ምናቃለሁ? ዶክተር አይደለሁም።“
ሰዎቹን ገፋፍቼ ወደፊት ሄድኩ። ትላንት ያዋሩኝ፣ የማላውቃቸው፣ የማውቃቸው ሰውዬ ነበሩ።
ገጪው የመኪናውን በር ከፍቶ ተደግፎ በcellphone ያወራል። ጣቶቹ በወፍራም የወርቅ ቀለበቶች ታጥረዋል። ወፍራም አንገቱን እንደ ውሻ ሰንሰለት የወፈረ የወርቅ ሃብል ተጠምጥሞበታል።
“ምን ባክህ…የሆነ ሽማግሌ ነው። የሆነ … የኔ ቢጤ ሽማግሌ ነው።” የመኪናውን በር ከፍቶ ተደግፎ በcellphone ያወራል።
ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ
ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ
እኔን አመመኝ፣ እኔን አመመኝ፣ እኔን አመመኝ፣ እኔን አመመኝ፣ እኔን አመመኝ . . .
ይህ የማላቀቸው ሰውዬ ታሪክ ነው ብዬ ብጀምር ይቀለኝ ነበር። የማላቀቸው፣ የማውቃቸው ሰውዬ ታሪክ ግን አላለቀም። የረሃብ ታሪክ አላለቀም። የስቃይ ታሪክ አላለቀም። የሰቆቃ ታሪክ አላለቀም። የግብዝነት ታሪክ አላለቀም። የማያልቅ ነገር ምን ይባላል? ምን ተብሎ ይጀመራል? መጽናናትስ እንዴት ይገኛል? … ህሊናዬ ተቦረቦረ። እስካብድ አመመኝ! እኔን አመመኝ፣ እኔን አመመኝ፣ እኔን አመመኝ … ጭንቅላቴ እንዳይፈነዳብኝ ጥርቅም አድርጌ ያዝኩት።
++++++++++++++
ግጥሞቹ በሙሉ ከቴዲ አፍሮ ዘፈን የተወሰዱ ናቸው። (ምስሉ ለማሳያነት የቀረበ)
Leave a Reply