ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳቹህ እጽፍላቹህ ዘንድ ግድ ሆነብኝ ይሁ. 1፤3
በዚህ ጽሑፍ ላይ ጥንታዊቷና ሀገር በቀሏ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ ከምእመናኗ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ማሽቆልቆል መንስኤውንና ተጓዳኝ ነገሮችን እናያለን፡፡ ይሄንን እንድናይ ግድ የሚልበትም ምክንያት ይህ አደጋ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ማንነትና እሴት ለማጥፋት በተለያየ መንገድ ሲጥሩ የኖሩ ባዕዳን ጥረታቸው ሠምሮላቸው አሁን ላይ ኢትዮጵያዊነት በዜጎች ዘንድ ዋጋ እያጣና እየጠፋ ከመሄዱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለውና የሚነቃ ካለ ለማንቃት በማሰብ ነው፡፡
ስለ እውነት ለመናገር ከማንነት አንጻር ካየነው ለመረዳት ያለን አናሳ የታሪክ እውቀታችን ካልገታን በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ላይ በየትኛውም የእምነት ድርጅት ውስጥ ያለ ዜጋ ሁሉ ትናንትና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባል ያልነበረ የዘር ሥር ያለው የለምና የዚህች ቤተክርስቲያን ህልውናና ደኅንነት ጉዳይ እንደ ዜጋና የሀገር እሴት ባለቤት ሁሉንም ዜጋ ይመለከታል ይገዳል፡፡ ይሄንን በቀላሉ ለመረዳት “እምነቶቹ” ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡበትን ዘመን ማሰቡ በቂ ነው፡፡ ከእነሱ አስቀድሞ ግን ይህች ቤተክርስቲያን ከአዳም ወደ ልጆቹ በትውፊት እየተላለፈ የመጣውን አምልኮተ እግዚአብሔር ሳይቋረጥ እንደየኪዳኑ ስሟ እየተቀያየረ በዚህች ሀገር የኢትዮጵያን ሕዝብ በአምልኮተ እግዚአብሔር እየዋጀች እንደኖረች ከቅዱስ መጽሐፍ መረዳት ይቻላል፡፡
ከታሪካችን እንደምንረዳው ከጥንት ጀምሮ ምዕራባዊያንም ሆኑ ዓረቦች የየራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅና ኢትዮጵያዊ የሆነውን ማንነት ለመሸርሸርና ለማፈራረስ ከዜጎች ልቦና ለማጥፋት የጣሩት ጥረት የየድርሻቸውን እንዲወስዱ አድርጎ ዛሬ ላይ ያለው የሚታየው ውጥንቅጥ ውጤት እንዲደርስ አስችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ እጅግ በሚያሳዝን በሚደንቅና በሚገርም ሁኔታ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያላቸው ሆነው እያለ ከገዛ ሀገራቸው ሕዝባቸውና ማንነታቸው ይልቅ ከየጭንቅላታቸው ማንነታቸውን ደምስሰው እምነታቹህ ነው ብለው እንዲይዙት ያደረጓቸውን ባዕዳን የቅኝ ግዛት ሰላዮች ሚሲዮናዊያንና የዓረብ ነጋዴዎችን ሀገራትና ሕዝብ ማንነትና ጥቅም የሚበልጥባቸው የሚያንገበግባቸው ዜጎች በድምሩ የሚበዛውን የሕዝባችንን ቁጥር የሚይዙ ሆነዋል፡፡ ከዚህ አስተሳሰባቸው አንጻር እነዚህ ዜጎች የእምነትንና የማንነትን ልዩነትና አንድነት፣ ድንበር፣ የዜግነትን ግዴታና ኃላፊነትን ጉዳይ በተመለከተ የተማረ ነው ከሚባለው አንሥቶ እስከ ጎጋው ድረስ ጨርሶ ምንም የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌለ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ መሆኑ በዜግነታቸው ወይም ዜጋ በመሆናቸው ብቻ ኢትዮጵያዊ ለሆነው ማንነታቸው ሊያደርጉት የሚገባውን ጥበቃ እንዳያውቁና እንዳያደርጉ የገዛ ራሳቸውን ማንነት በገዛ እራሳቸው እንዲያጠፉት አድርጓል፡፡
ፊት አውራሪ አመዴ ሲናገሩት የሰማሁትን አንድ ቁም ነገር ላጫውታቹህ፡፡ ሃይማኖታዊ ጉዞ ለማድረግ ወደ መካ መዲና ሄደው በነበሩበት ሰዓት እንደሳቸው ሁሉ ከሩቅ ምሥራቅ የመጣ ተጓዥ ጋር ሲጫወቱ ያጋጠማቸውን ሲያወሩ ነው፤ ይህ ሰው ፊት አውራሪ አመዴ እንደሚያስቡት የሙስሊም ስምና አለባበስ አልነበረውም ነገር ግን ደንበኛ ሙስሊም ነው፡፡ ታዲያ ገረማቸውና ጠየቁት እሱም “የሙስሊም ስምና የሙስሊም አለባበስ ማለት ምን ማለት ነው?” ብሎ መልሶ ጠየቃቸው እሳቸውም በነበራቸው ግንዛቤ “የሙስሊም ስሞችማ እነ መሐመድ ጀማል ከድር … የሙስሊም አለባበስ ደግሞ ጀለቢያ…” በማለት መለሱለት ያም ሰው በግርምት እየተመለከታቸው “ይሄውልህ ወንድሜ አሁን ያልከኝ ነገር ሁሉ የሙስሊም ሳይሆኑ የዓረብ ናቸው፡፡ ዓረቦች ነቢዩ መሐመድ መጥተው እስልምናን ወይም ቁርአንን ከመስበካቸውና ዓረቦችም እስላም ከመሆናቸው በፊትም የነበሩ ስሞችና አለባበሶች ናቸው፡፡ ዓረቦች ሙስሊም ከሆኑ በኋላ የያዙት ወይም እስልምና ያመጣቸው ነገሮች አይደሉም፡፡ ያልካቸው ነገሮች የዓረብኛ ቋንቋና የዓረብ ባሕል ጉዳይ እንጅ የእምነት ጉዳይ አይደሉም፡፡
“በመሆኑም እኔ እስልምናን የተቀበልኩት ከማንነቴ ጋር ነው፡፡ እኔ ኢንዶኔዢያዊ እንጅ ዓረብ አይደለሁምና ባልከው ስም የመጠራት ያልከውን ልብስ የመልበስ የራሴን ጥዬ የዓረብ ባሕል የመያዝ ግዴታ የለብኝም አይኖርብኝምም፡፡ እስልምና እኔ ሙስሊም ስሆን ቋንቋየንና ባሕሌን እንድቀይር ያዘዘበት ወይም የሚያስገድድበት አንድም ቦታ የለም፡፡ ይሄ በጣም ደካማ ያልበሰለና አደገኛ አስተሳሰብ ነውና ከጭንቅላትን አውጥተህ ጣል” አላቸው የሴቶቹ ሂጃብና ጂልባብ ግን ሃይማኖታዊ እንደሆነ ሙስሊሞቹ ይናገራሉ ኒቃብ ግን የታዘዘበት ቦታ የለም ያላሉ፡፡ ፊታውራሪም ይህ ሰው የሰጣቸው በሳል ትምህርት በሚገባ ገብቷቸው ስለነበር ከዚያ በኋላ ጀለቢያውን አውልቀው እስኪሞቱ ድረስ እንደ ፊት አውራሪነታቸው የሀገራቸውን ልብስ በእጀጠባባቸው ላይ ኩታቸውን ጣል አድርገው በኩታቸው ላይ ካባቸውን ደርበው ከታች ተነፋነፋቸውን (ተፈሪ ሱሪ አይባልም አዲስ አበባ ቤተ መዘክር ገብታቹህ ከ2500 ዓመታት በፊት የነበረ ባሕላዊ ሱሪ እንደሆነ በቁፋሮ በተገኘ የአለት ሰሌዳ ላይ የተቀረጸው ሥዕል ያሳያል) ብቻ እንዳደረጉ ሌላ ልብስ ሳያደርጉ ኖሩ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል አሁን አሁን እየተለወጠ መጣ እንጅ ይሄ እውነት ስለገባቸው እኔ ባገሬ ጎንደር የማውቃቸው ጎረቤቶቻችንና የሰፈር ሙስሊሞች ብዙዎቹ የአማርኛ ስም ያላቸውና ኢትዮጵያዊውን ባሕል የሚከተሉት፡፡ ከማውቃቸው በጣም ጥቂቶቹ ናቸው የዓረብኛ ስሞች የነበራቸው፡፡ በክርስቲያኑም ቢሆን ካለማወቅ ከሃይማኖታዊ ግዴታ ወይም ትእዛዝ ውጪ በገጠር ሳይሆን ሰለጠንኩ በሚለው በከተማ የክርስቲያንነቱን ግዴታ እየተወጣ እየመሰለው የራሱን ማንነቱን እየተወ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየፈለፈለ የአይሁድ ስም እያወጣ ለልጆቹ የሚሠይመው እየተበራከተ መጥቷል፡፡
በዚህ አጋጣሚ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች እየፈጸሙት ያለውን ስሕተት ጠቁሜ ልለፍ አንዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለእስልምና ተከታዮች በሚል ከወለድ ነጻ ነገር ግን ባንኩ በገንዘባቸው ሠርቶበት የሚያገኘውን ትርፍ ሊጋሩ የሚችሉበትንና አስቀድሞ እንደ ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ያሉ በአማርኛ ሲሰጣቸው የነበሩትን የባንክ አገልግሎቶች ወደ ዓረብኛ ለውጦ ዋዲያማና፣ ቀርድ፣ ኢጃራህ፣ ሙሸራካ፣ ኢስቲስናህ ወዘተ. እያለ እንግሊዝኛው በከለን ኧረ እየተረጎምን እንጠቀም እያልን በምንወቃቀስበት ወቅት አሁን ደግሞ ጭራሽ ሌላም ጨምረው ዐረፉት፡፡ ማለት የፈለጉትን አማርኛው ሳይገልጽላቸው ቀርቶ ነው እንዳይባል አስቀድሞ ሲሰጥ የቆየ አገልግሎትንም ነው ወደ ዓረብኛ የመለሱት፡፡ እኔ የሚገርመኝ እነዚህ ወገኖች እኮ ዓረቦች አይደሉም፡፡ የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ምናለ ቅርባቸው በሆነው በሚገባቸው በገዛ ቋንቋቸው ሁሉም በሚረዱት ብታስተናግዷቸው፡፡ ለምን ወደ ባዕድ ይገፋሉ? ለምን ባዕድነት እንዲሰማቸው ይደረጋል? ለምን አላግባብ ዓረባዊ ተጽእኖ እንዲጫናቸው ይደረዳል? ሃይማኖት ሌላ ማንነት ሌላ ጉዳይ ሆነው እያለ ሊቀላቀሉ በማይገባ ጉዳይ ላይ ለምን ትቀላቅሏቸዋላቹህ? እባካቹህ ለማንነት ተጠንቀቁ? ወለድ መቀበል እስልምና የሚከለክል ቢሆንም ይህንና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶች የሚገለጽበት ቋንቋ ጉዳይ ግን ከእስልምና ጋራ የሚያገናኘው ጉዳይ የለምና ኃላፊነት እንደሚሰማው እንደ ተማረ እንደ ባለ አእምሮ ዜጋ አስቡና ምን ለማን በምን ቋንቋ እንደሚባል ተረድታቹህ ሥሩ፡፡
ከላይ ኢንዶኔዢያዊው የተናገረውን ምሁራዊ ግንዛቤ ዛሬ ላይ ማንነትን ከሃይማኖት ለመለየት ለተቸገሩት የዜግነት ግዴታቸውንም ጨርሶ ለዘነጉና መረዳት ለተሳናቸው የአውሮፓና የዓረብ ሰለባዎች ሁሉ ያስፈልጋል፡፡ ይሄንን ስል ያለ እጀ ጠባብና ያለ ሐበሻ ቀሚስ ሌላ ልብስ ፈጽሞ አይለበስ እያልኩ አይደለም የራስ ማንነት አጥርና ድንበር አርቆ ሲታጠር የት እንደሚደርስ ለማሳየትና ከዚህ በመለስ ልንደራደርባቸው የማይገቡ ብዙ እሴቶች አሉንና በእነሱ ላይ እንድንጠነቀቅ ለማስገንዘብ እንጅ፡፡ እነኝህ ወገኖች ኢትዮጵያዊነታቸውን ማንነታቸውን መጠበቅ መንከባከብ ካለባቸው የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ማኅደር የሆነችውን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን መጠበቅና መንከባከብ ይኖርባቸዋል እንጅ ማንነታቸውን ክደው እራሳቸውን የነጭና የዓረብ ቅጥረኛ አድርገው በጠላትነት ሊዘምቱባት አይገባም ይሄ ሌላ ምንም ሳይሆን እብደት ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በአንድ ጽሑፌ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን እማኝ አድርጌ እንደገለጽኩት “እኛ ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖትን ያገኘነው እግዚአብሔርን ያመነው ከየትም መጥቶልን አይደለም፡፡ ይልቁንም እስራኤሎቹ በእግዚአብሔር እንዲያምኑ አስተዋጽኦ አበረከትን እንጅ በእግዚአብሔር እንድናምን እነሱ ለእኛ ያበረከቱት አንድም ነገር የለም፡፡ እርግጥ ነው ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ከነሱ ወደኛ መጥተዋል እነዚህ ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ በዚያች በአንዲቷ ሃይማኖት ውስጥ ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲፈጸሙ ቀጠሮ ይዞላቸው የነበሩና የተፈጸሙ ኪዳናት ናቸው እንጅ ሃይማኖቶች አይደሉም አልነበሩምም” ማለቴ ይታወሳል፡፡ ይህ ወርቃማ ማንነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ሊቆምለት ሊጠብቀው የሚገባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት ማንነትና ቅርስ ነው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ እንደመሆኑ ሁሉ ይሄንን የበሰለና የዜግነት ግዴታ የሆነ አማራጭ የሌለውን አስተሳሰብ ያለ ልዩነት ስላልያዝን ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢትዮጵያዊ የሆነው እሴትና ሀብት እየጠፋና እየደከመ አሁን ካለንበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ዛሬ ላይ ጭራሽ ባዕዳኑ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያዊ የሆኑ እሴቶችን ከማጥፋትና ከማዳከም አልፈው ቅጥረኛውን መንግሥት ብሎ እራሱን የሚጠራውን የጎጥ ቡድን እና ማርከው የወሰዷቸውን ዜጎች በመጠቀም የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ግምጃ ቤት የሆነችውን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን አጥፍተው የኢትዮጵያዊነትን ግብአተ መሬት ለሚፈጽሙበት ዋዜማ ደርሰዋል፡፡ ይህች ቤተክርስቲያን ላይ ላዩን ሲያዩዋት ያለች ትመስላለች እንጅ የለችም፡፡
ይህ የአገዛዝ ሥርዓቱ አጋንታዊ በሆነ በሚደንቅ ብቃትና አፈጻጸም በመላ ሀገሪቱ ካድሬዎቹ የቤተክርስቲያኗን ከፍተኛ መዋቅርና አጥቢያ አብያተክርስቲያናትን ከታች እስከ ላይ እንዲቆጣጠሯት በማድረግ እንኳን የእግዚአብሔር ቤት ከሆነችው ይቅርና በየትም ቦታ አለ ከሚባል በሙስናና በዝርፊያ በብልሹ አሥተዳደር ስሙ ከጠፋ ከረከሰ ከጎደፈ ተቋም እንኳን ጨርሶ በማይጠበቅ ብልሹ አሥተዳደር ዝርፊያና ሙስና አዝቅጧታል አንቅዟታል፡፡ በዚህ ምክንያት ሐዋርያዊ ተልእኮዋን መወጣትና መንጋዋን መጠበቅ ጨርሶ አልቻለችም ተሽመድምዳለች፡፡ ዛሬ ቤተክርስቲያን ያለች ትመስላለች እንጅ የለችም ምስጥ እንደበላው እንጨት ናት፡፡ ምስጥ የበላው እንጨት አለ ሲሉት ድንገት ፍርክስ ብሎ በፊቱንም እንዳልነበረ እንደሚታወቀው ሁሉ ይህ ዓይነት አደጋ በዚህች ቤተክርስቲያን ላይ ፈጦ ተጋርጧል፡፡
እንዳልኳቹህ ሥራውን እየሠሩ ያሉት መንግሥት ተብየውና መናፍቃኑ በጥምረት በመሆኑ አደጋውን እያፋጠነው ይገኛል፡፡ ዛሬ ላይ ቤተክርስቲያን ትናንት ከነበራት የምእመናን ብዛት ሲሶ ያህሉ እንኳን በእጇ የለም ባለፈው ጊዜ ከሰጠኋቹህ የተለየ ዳታ (አኃዛዊ መረጃ) ልስጣቹህ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና ቤት ቆጠራ በደርግ ጊዜ በተደረገው ቆጠራ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባላት ቁጥር ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ 54.02 % ያህሉ ነበር መናፍቃኑ ደግሞ ባጠቃላይ 6.46% ነበሩ፡፡ በዘመነ ወያኔ እስከ 1997ዓ.ም. ቆጠራ ድረስ በሠሩት የተቀናጀ ሥራ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከአጠቃላዩ ሕዝብ 43.5% በመሆን ከነበራት 11% ስታጣ መናፍቃኑ ደግሞ ከ6.46% ወደ 19.2% ማሻቀብ ችለዋል፡፡ ይህ ቁጥር ከየትም የመጣ ሳይሆን በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የተበሉ ናቸው፡፡ መናፍቃኑ በየ ዐሥር ዓመቱ በተደረገው ቆጠራ ከአምስት በመቶ ወደ ዐሥር በመቶ ከዐሥር በመቶ ወደ19 በመቶ እጅግ በሚያስደነግጥ ሁኔታ በየቆጠራው የነበሩበትን እጥፍ እያደረጉ መጥተዋል፡፡ ይህ ውጤት በሚሰጠን ሬሾ (አማካኝ ስሌት) ሄደን በሚቀጥለው ዓመት 2008ዓ.ም. በሚደረገው ብሔራዊ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ስንገምት መናፍቃኑ 38%ቱን የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደሚይዙ ሲገመት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምእመናን ደግሞ ከ22-20% እንደሚያሽቆለቁል ይገመታል፡፡
ጠቋሚ ሁኔታዎች የሚያመላክቱት ግን ውጤቱ ከዚህም ሊከፋ እንሚችል ነው የሚያረጋግጡት፡፡ በየሰፈራቹህ አማትራቹህ በየጎረቤታቹህ ጠጋ ብላቹህን እየሆነ ያለውንና የሆነውን አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ትውልዱ እንዳለ በተኩላት መወሰዱን በማየት ማረጋገጥ ትችላላቹህ፡፡ በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ከወላጅ በስተቀር ያሉ ልጆች በሙሉ ሃይማኖትን ክደው ወደ ተኩላት ድርጅት ገብተዋል፡፡ ብዙ ወላጆች እግዚአብሔር በልጆቻቸው ነፍስ መጥፋት እንደሚጠይቃቸው ጨርሶ ባለመገንዘብ ሁኔታውን ከወላጅ በማይጠበቅ ቸልታ በዝምታ ከመመልከታቸውም ባሻገር ጭራሽም ለልጆቻቸው መመንፈቅ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ወላጆችም ልጆቻቸውን ተከትለው የሄዱ አሉ፡፡ ብቻ ምን አለፋቹህ በየሰፈሩ ስታማትሩ በሚያስደነግጥ ደረጃ ሰዉ ተወስዶ እያለቀ ነው፡፡ ሁኔታው እንዴ! ምንድን ነው የተፈጠረው? ምን ጉድ መጣ? ያሰኛል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ እኔ እንዴት እነደሆን ባይገባኝም ስታዩዋቸው ማተብ ያደረጉ ናቸው ገባ ብላቹህ ስታዩዋቸው ግን መናፍቃን ሆነው የምታገኗቸው በርካታ ሰዎች በተደጋጋሚ በተለያዩ ሥፍራዎች አጋጥሞኛል፡፡ አንድ ቦታ ላይ ምን አጋጠመኝ? ሁለት ሴቶች ናቸው ከእነሱ ጋር አንድ ወንድ አለ እየተከራከሩ ነበር ያገኘኋቸው:: ጉዳየን እስክፈጽም ድረስ እየገረመኝ ክርክራቸውን ሳዳምጥ ቆየሁ፡፡ ልጁ የተቻለውን ያህል ይከራከራል፤ በተመቸው ጊዜ ወደ አዳራሻቸው ሊወስዱት እሽ እንዲላቸው ይወተውቱታል አሁን ጣልቃ መግባት ስለነበረብኝ የሚገባቸውንና አፋቸውን የሚይዙበትን የእግዚአብሔር ቃል ሰጥቻቸው ወጣሁ ልጁ ደስ አለው፡፡ ለምን ማተብ ሊያስሩ እንደቻሉ ግን ሊገባኝ አልቻለም ሳልጠይቃቸውም ቀረሁ፡፡ ማተባቸውን ለመፍታት በወላጆቻቸው የማይፈቀድላቸው ሆኖ ይሆናል እንዳልል እነዚህ ሴቶች ጠና ጠና ያሉ ናቸው፡፡
እንግዲህ ይሄንን የኢትዮጵያ ሕዝብና ቤት ቆጠራን ዳታ (አኃዛዊ ስሌት) ተከትለን ስናሰላ በየግላቹህም ልታሰሉት ትችላላቹህ የሰይጣን ጆሮው ይደፈንና ከአምስት ዓመታት በኋላ እየሰማቹህኝ ነው? ከአምስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አንድም ምእመን አይኖራትም፡፡ ይሄንን ልታምኑ ትችላላቹህ? መንጋዋ በአውሬው ተበልቶ ያልቃል፡፡ አኃዙ የሚያሳየን ይሄንን መራራ እውነት ነው፡፡ ይሄንን ለሚሰማው ሁሉ ሁለት ጆሮዎቹን አስይዞ በጨለማ እንደሚሄድ ሰው የእንብርክክ የሚያስኬድ መርዶ ሰምቶ የሚተኛ “እግዚአብሔርን ነው የማገለግለው” ባይ ካህን ካለህ እርግጠኛ ሆኘ የምነግርህ እግዚአብሔርን ጨርሶ አታውቀውም እያገለገልክ ያለኸው ሆድህን ነው ከአምስት ዓመታት በኋላ የምትበላውን ስታጣ አንተም ሄደህ ትገባለህ፡፡
ይሄንን ከመርዶዎች ሁሉ የከበደ መርዶ ሰምቶ አርፎ የሚቀመጥ “መድኃኔዓለም አምላኬ ድንግል ማርያም እናቴ” እያልክ ክርስቲያን ነኝ የምትል ምእመን ካለህ እርግጠኛ ሆኘ እነግርሀለሁ ክርስቶስ ኢየሱስንም ወላዲተ አምላክንም ፈጽሞ አታውቃቸውም፡፡ አስመሳይ ውሸታም ነህ ሃይማኖት የሚባል የለህም፡፡ “ሃይማኖት የግል ነው” የሚል የደነቆረ አባባል ይዘህ ቤተክርስቲያንን አስበልተሀልና ባለእዳ ነህ ትጠየቃለህ፡፡ ኧረ ለመሆኑ ሃይማኖት የግል ሆና የምታውቃት መቸ የትና እንዴት ነው? ከጥምቀት እስከ ቁርባን የትኛው አገልግሎት ነው አንድ ሰው ብቻውን ለራሱ ሊያደርገው የሚችለው መንፈሳዊ አገልግሎት? ምእመናን ሳይኖሩ ምእመን፣ ካህናት ሳይኖሩ ምእመናን፣ ምእመናን ሳይኖሩ ቤተክርስቲያን ሊኖሩ ይችላሉ ወይ?
መናፍቃኑ ይህን ውጤት ሊያገኙ የቻሉት መንግሥት ነኝ ባዩ የባዕዳን ቅጥር የወንበዴ ቡድን ሕገ መንግሥቴ ነው የሚለውን ሕጉን ጥሰው እንዲሠሩ ስላስቻላቸው ነው፡፡ ይህ የወያኔ ሕገመንግሥት ለአምልኮ ከተፈቀደ ቦታ ውጭ በመንገድ፣ በአውቶቡስ ፌርማታዎች፣ በትምህርት ተቋማት፣ ሕዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች ሁሉ ሃይማኖታዊ ስብከት መስጠት የተከለከለ እንደሆነ ከዚህም በተጨማሪ እርዳታንና የሚያቋቁሟቸውን አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የሚሰጡትን አገልግሎት የሃይማኖት ልዩነት በማድረግ መስጠት ማስተናገድ ወይም በመደለያነት መጠቀም የተከለከለ እንደሆነ በግልጽ ደንግጎ እያለ መናፍቃኑ ግን ያለ ገደብ መንገድ የትምህርት ተቋማት ፌርማታዎች ብቻ አይደለም የዜጎችን የግል መብት በመጣስ ቤት ለቤት እያንኳኩ ሁሉ አሳሳች ስብከታቸውን እንዲሰብኩ ዕድል ስለሰጠና ሁኔታውን ስላመቻቸላቸው በሕጉ እንዲገዙ ሕጉን እንዲያከብሩ ባለማድረጉ እዚህ ሊደርሱ ችለዋል፡፡
የመናፍቃኑን አሳሳች ስብከት ነገር ካነሣን ዘንዳ ምን እንደሚመስል ብናይ ግንዛቤያቹህን ለማዳበር እነሱንም ለመታዘብ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ዋነኛ ስልታቸው “በደካማ ጎን መግባት” የሚለው ነው፡፡ በዚህ ስልት ይሄንን ለሃይማኖት አይደለም ለሞራል (ለግብረ-ገብ) ሕግጋት ዴንታ የሌለውን የትውልዱ አካል በደካማ ጎኑ በመግባት የሃይማኖት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ የሰው ልጆችን ለኃጢአትና ለእርኩሰት ማብቃት፣ ማስገዛት፣ ማርከስ፣ ልቅ ማድረግና ማጉደፍ ይመስል ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮና ዓላማ በተጻራሪ ቃሉ “ማመን እማ አጋንንትም ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል” ያዕ.2፤17-26 በማለት አጋንንት እንኳን ከማመንም አልፈው እምነታቸው ከመፍራት ከመንቀጥቀጥ ጋራ መሆኑን በመግለጽ ማመን ብቻ እንደማይጠቅም ከአጋንንት የምንለየው በጽድቅ ሥራ መሆኑን ግልጽ አድርጎ አስረድቶ እያለ እነሱ ግን “እመን ብቻ እንጅ ድነሀል ምንም ኃጢአት ብትሠራ አይፈረድብህም አትኮነንም መጾም፣ ሌት ተቀን መጸለይ፣ በሥግደት ራስህን ማድከም፣ የተለያየ ዓይነት መከራ በራስ ላይ ማድረስ ወዘተ. አያስፈልግህም አንዴ በጸጋው ድነሀል! በክርስቶስ ነጻ ሆነሀል! አርነት ወጥተሀል” እያሉ ሁሉም ሊሰማው የሚወደውንና የሚፈልገውን ሳቢና አማላይ ነገር ግን የሌለና ፈጽሞ ያልተባለ ሰውን ከንቱ የሚያስቀር ቃል እየተናገሩ፤ ቃሉን ያለ ትርጉሙ ትርጉም በመስጠት ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና አጋንንታዊ የሐሰት ትምህርት በመስበክ ከሴተኛ አዳሪ እስከ ግብረ ሰዶማዊ፣ ከአወናባጁ እስከ ምግብ ተለይቶ ሰዓት ተለክቶ ቀናት ተሰልቶ ስለ ክርስቶክ ፍቅርና ቤዛነት ጹም ተብሎ መጾምን እስከሚጠላውና እንደ መጋዣ በፈለገው ሰዓት ማመንዠክ እስከሚፈልገው ሆድ አምላኩ ድረስ እንዲሁም ኢክርስቲያናዊ አለባበስ ለመልበስ መከልከል የማትፈልገዋን ጭምር ሁሉንም በየ ደካማ ጎኑ በመግባት ከእግዚአብሔር ፈቃድና ቃል (ሕግና ሥርዓት) ጋራ ችግር ያለበትን በሙሉ በማታለል ከነአለባቸው ስብራት ድካም ወይም የመንፈስ ድቀት ቢኖሩ ምንም ችግር እንዴለለው ጌታም እንደሚቀበላቸውና እንደሚድኑ ምንም የማድረግ ነጻነት እንዳላቸው አድርገው በመስበካቸው ባየነውና እያየነው ባለው መልኩ ነጉዶ እንዲገባላቸው ማድረግ ችለዋል፡፡ ከሃይማኖት ከድቶ የመጥፋቱ ጉዳይ እየተመራ ያለው በተወናበደና በተደለለ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንጅ በእውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ያ ፍላጎት ደግሞ ሥጋዊ መሆኑ ነው ችግሩ፡፡ የሚሄዱና የሄዱ ሰዎች መሳሳታቸውን ኅሊናቸው ከሚነግራቸው እውነት ውጭ ጠለቅ ብለው ስለ ሃይማኖት የሚያውቁት ምንም ነገር የለም፡፡
ስለ እውነት ከሆነ እነዚህ የእምነት መሰል ድርጅቶች ዓላማቸው ሌላ ስለሆነ እንጅ ይህ ድርጊታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋራ ፍጹም ተቃራኒና የማይጣጣም መሆኑን አጥተውት ነው ብየ አላምንም፡፡ አይደለም መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤያለሁ የሚል ይቅርና ምንም ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የሌለው ሰው እንኳን ቢሆን የዚህን ስብከት አጋንንታዊነት ወይም ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊነት ለነገሮች ካለው አጠቃላይ ግንዛቤ ወይም ከንጹሕ የኅሊናው ዳኝነት በመነሣት ሊያረጋግጠውና ሊረዳው የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩን የሚፈጥረው ለሥጋዊ ምቾት ጥቅምና ፍላጎት መታወርና በአጋንንት ፈተና መውደቅን ተከትሎ በሚመጣው የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን የሚፈጥረው የጥፋት ዓላማ ነው እንጅ እውነቱን የማይረዳ፤ እንኖርባትና መንግሥቱንም መውረስ እንችልባት ዘንድ እግዚአብሔር የመሠረታት ሃይማኖት የትኛዋ እንደሆነች ልቡናው የማያውቅ አንድም ሰው ይኖራል ብየ አላስብም፡፡
ምክንያቱም ይሄ ጥልቅ የሆነ የሃይማኖት ዕውቀት የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለምና፡፡ ሁሉም እግዚአብሔር የራሱ እንደራሴ ዳኛ እንዲሆነው በውስጡ ያስቀመጠለትን ኅሊናውን ቢያዳምጥ ሊያገኘው የሚችለው ምላሽ ነውና፡፡ እግዚአብሔር የመሠረታት ሃይማኖት የትኛዋ እንደሆነች፣ ሃይማኖት መሰል የእምነት ድርጅቶች ደግሞ የትኞቹ እንደሆኑ፣ ሃላፊውን ጠፊውን ጊዜያዊውንና ሥጋዊውን ጥቅም የሚሰብኩት የሚያስጠብቁትና ለዚህም ሲባል በሐሰተኞች ነቢያትና መምህራን የተመሠረቱት የትኞቹ እንደሆኑ፣ የትኛዋ ደግሞ የማያልፈውን የማይጠፋውን ዘለዓለማዊውንና መንፈሳዊውን ጥቅም እንደምታስጠብቅና እንደምትሰብክ ሁሉም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ሁሉም እንደማይሆን ልቡናውና ኅሊናው እያወቀው የሥጋዊ ጥቅሙ በልጦበት ሥጋዊ ጥቅሙንና ፍላጎቱን በሚያስጠብቅለት ሃይማኖት መሰል ድርጅት እየታጎረ እራሱን እያጃጃለ ነው እንጅ እውነቴን ነው የምላቹህ ይሄን የሚያጣው አለ ብላቹህ አታስቡ፡፡
ከዚህም የተነሣ ፈጣሪ ራሱ በዚህ ሰማይ ላይ ተገልጦ “እኔ የሰጠኋችሁ ትክክለኛዋ ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት” ብሎ እያስተጋባ ቢናገር በተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ውስጥ ያሉ የሰው ልጆች ሁሉ ደንገጥ ብለው “ነው እንዴ? እሰይ! እንኳን ነገርከን ፈጣሪ በቃ አሁኑኑ አምነን በእርሷ ውስጥ አንተን እናመልካለን እንድናለንም ተመስገን!” የሚል እንደማይኖር እኔ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እያንዳንዱ ኅሊናው ምን እያለው ምን ፈልጎ እንደሄደና እዚያ እንደሚኖር ጠንቅቆ ያውቀዋልና፡፡ አሁን አሁንማ ጭራሽ መጽሐፍ ቅዱስን ለራሳቸው እንዲመች እያደረጉ አጣመው ከመስበክ አልፈው “አዲስ ትርጉም፣ መጽሐፍ ቅዱስ በቀላል አማርኛ” ምንትስ በሚል ሽፋን የማይመቻቸውን እያወጡ የሚፈልጉትን ያልነበረውን እየጨመሩ መጽሐፍ ቅዱስን ከመጽሐፍ ቅዱስነት አውጥተው የየግል ድርሰታቸው አድርገውታል፡፡ ባጠቃላይ ሃይማኖት መሰል ድርጅት እያቋቋሙ በዘርፉ መሰማራት ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝ መብያ ዘዴ (ቢዝነስ) ሆኖ በመገኘቱ ሥራ ያጣው ሁሉ በሰፊው ተሠማርቶበታል፡፡
ነገር ግን የሚኖረውን እምነት ከወላጆቹ ወርሶ ሳያገናዝብ ሳያመዛዝን እውነት መስሎት የሚኖር ካለ ለእሱ የምነግረው ነገር ቢኖር ከአዳም ጀምሮ የነበረችው እነ ነቢዩ ኤርሚያስ 6፤16 ላይ ለነፍስ እረፍትን የምታሰጠው የቀደመችው መንገድ ሲል የገለጻት፣ እነ ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብ. 3፤14 የመጀመሪያዋና የክርስቶስ ተካፋይ ለመሆን የምታበቃው እንዲሁም በኤፌ. 4፤5 አንድ ሃይማኖት ሲል የገለጻት፣ የያእቆብ ወንድም ሐዋርያው ይሁዳ 1፤3 ላይ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠ ሃይማኖት ናት ተጋደሉላት ያላት፤ እግዚአብሔር በኢትዮጵያና በእስራኤል ብቻ ይመለክ የነበረበት ዘመን አብቅቶ ዓለሙ ሁሉ በልጁ ደም ይዋጅና ይቀደስ ዘንድ በወደደ ጊዜ አንድያ ልጁን ልኮ ዓለም በሐዲሱ ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ተዋውቆ ክርስትና በዓለም እየተስፋፋ እሱንም ማምለክ ቀጥሎ እስከ 450 ዓ.ም. ከቆየ በኋላ ከአጋንንት ፈተና ብርታት የተነሣ በ450 እና 451ዓ.ም. ላይ በሮማው ፓፓ በልዮንና በቁስጥንጥንያዋ ንግሥት ብርክልያ (ፑልኼሪያ) አማካኝነት በተዘራው የክህደት ትምህርት መንጋውን ይዘው በመጥፋት ይህች ሃይማኖት እንደገና ከብዙ ሀገራት ጠፍታና በመናፍቃኑ ተተክታ ዛሬ በግብጽ፣ በሶሪያ፣ በአርመን፣ በህንድና በሀገራችን በኢትዮጵያ (Oriental Churches) ብቻ ተወስና ያለችው ናትና ወደሷ ተመለስ፡፡
ከ450 ወዲህ የምዕራቡ ዓለም ክርስትና የሐሰት አባት ዲያብሎስ ሠልጥኖበታልና ዛሬ ላይ እንደምታዩዋቸው በግልጽ እርኩሰትን ለመስበክ ተገደዋል፡፡ በብዙኃን መገናኛ እንደምትከታተሉት የፕሮቴስታንቱ ዓለም ግብረ ሰዶምን በይፋ ከተቀበለ ቆይቷል፡፡ ካቶሊካዊያኑም ይሄንን ለማወጅ ዋዜማ ላይ ናቸው፡፡ ፓፓ ቤኔዲክት ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁት ግብረ ሰዶምን ሕጋዊ እንዲያደርጉ በሌሎች ፓፓዎች በተደረገባቸው ጫና ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቀጥለው ሥልጣኑን የተረከቡት ፓፓ ፍራንሲስም “የግብረ ሰዶም ጉዳይ ሊታይ ይገባል” በማለት ተስፋ እንደሰጧቸው በብዙኃን መገናኛ ተዘግቧል፡፡ ይሄንን ያህል ናቸው እንግዲህ ቃሉም እንደሚል “እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው” ሮሜ 1፤28 “ስለዚህም ምክንያት በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል” 2ተሰ. 2፤11-12
እናም አንተ ወገኔ በሚስዮናዊያን ብስኩትና በዓረብ ነጋዴያን ተምር ተታለው በኋላም በግራኝ መሐመድ ሰይፍ ተገደው በሐሳውያን ተጠልፈው ዛሬ ላይ አንተ በሌላ በረት ውስጥ እንድትገኝ ያደረጉህ አያቶችህ ተሳስተው ተደልለውና ተገደው ነውና አንተ ግን ተመለስ በኔ ይሁንብህ መዳን ከፈለክ ድኅነትን የሚሰጥህን ኢየሱስ ክርስቶስን የምታገኘው በዚህች በረት ውስጥ ብቻ ነውና ሳታወላዳ አሁኑኑ ና ልለው እወዳለሁ፡፡ የተኩላት በረት ውስጥ ሆኖ ሁላችንም ፈጣሪን አምላኪ ነን ወይም እኛም ክርስቲያኖች ነን የእኛ ከእነሱ የሚለየው …. የሚባል ነገር የለም፡፡ እንደ እግዚአብሔር ቃል ያለው አንድ ሃይማኖት ብቻ ነው ኤፌ.4፤5፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ባለፈው ብዙ ተማምረናልና አሁን አልደግመውም መጨረሻ ላይ ያለውን ይዝ (ሊንክ) ይመልከቱ፡፡
ይሄንን ስል ግን ሰዎች እንዳይድኑ እንዲሰናከሉ እንዲጠፉ የሚያደርጉ የተለያዩ ዓይነት እንቅፋቶች መሰናክሎች ደንቀራዎች ፈተናዎች በዚህች በረት ውስጥ የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ ሰይጣን ሥራው ምን ሆነና? ዓላማው ምን ሆነና? የሚደክመው ምን ለማግኘት ለምን ሆነና? ስለሆነም አዎ በዚህች በረት ውስጥ አሰናካይ አደናቃፊ የሰይጣን ባሮች የይሁዳና የሲሞን መሰሪ ልጆች አሉ እናም ይሄም እንዳለ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አጋንንት እንዳታገኘው የተለያየ መሰናክል እንቅፋት በማስቀመጥ የሚከላከሉህን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈተናቸውን በትእግስት በጽናት በማሳለፍ የክርስቶስ የክብሩና የመንግሥቱ ወራሽ እንድትሆን እመክራለሁ፡፡ ቤተክርስቲያን በአጋንንት መፈተን ጸጋዋ ነው ተጠርተው ከመጡት ውስጥ ሰይጣንም የድርሻውን ይወስዳል፡፡ ይሁዳ በጌታ “ተከተለኝ” ተብሎ የተጠራ የአምላክነት ተአምራቱን ያየ የቃሉን ስብከት የተማረ የእጁን በረከት የበላና የጠጣ ለማታልፍ ጸጋ የተመረጠ ሆኖ ሳለ ወድቋል በሰይጣን ተወስዷል፡፡ ዛሬም ተጠርተን ሳለ የምንወድቅ የምንወሰድ የምንስት ብዙ ይሁዳዎች ብዙ ሲሞን መሰሪዎች ብዙ ዴማሶች አለን እንኖራለንም፡፡ “በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ” ማቴ. 24፤10 “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እሱ ይድናል” ማቴ. 24፤13
እንግዲህ ከዚህ አንጻር ነው በሥጋ ፈቃድና ጥቅም የተሸነፉት ሥጋዊያኑ ሐሰተኞች ነቢያትና መምህራን “በጸጋው ድነናል” የምትለዋን ቃል ቅንጣትም ሐፍረት ሳይሰማቸው “ምን ይሉን” ሳይሉ አእምሮ ባለው ሁሉ ለትዝብት ሊዳርጋቸው በሚያስችል መልኩ ቃሉን ቆንጽለውና አጣመው ለሥጋዊ ጥቅማቸው መጠቀሚያ አድርገውት ይገኛሉ፡፡ እስኪ ሙሉ ቃሉ ምን ይላል? እንይ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎሏቸዋልና በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ እሱንም የሆነ ማስተሥረያ አድርጎ አቆመው ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው” ሮሜ. 3፤23-26 “ከእንግዲህ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና” ሮሜ. 6፤6 በማለት እንዲሁ በጸጋው መዳን ማለትና ለማን እንደተፈጸመላቸው “የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና” በማለት ከክርስቶስ ቤዛነት ስለ እኛ መሞት በፊት ሞተው 5500 ዘመን በሲኦል ሲጋዙ ለነበሩት እንደሆነ ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ በሮሜ. 3 ላይ ቀጠል አድርጎም “ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው” በማለትም ከክርስቶስ ሞት በኋላ ላለነው ደግሞ “እንዲሁ በጸጋው (በቸርነቱ) ዳንን” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገልጧል፡፡
ይህም ማለት የአዳም ልጆች በመሆናችን ብቻ ልንወርሰውና ኃጢአተኛ ልንሆን እንችል የነበረበትን “የውርስ ኃጢአት ወይም ጥንተ አብሶ” ተሸክሞልን ለመስቀል ሞት በመዳረግ ደምስሶ ከውርስ ኃጢአት ተጻ አውጥቶናልና በጸጋው መዳናችን ከዚህ አንጻር ነው እንጅ “ከክርስቶስ ሞት በኋላ ገና የምንፈጠር ሰዎች ተፈጥረን የምንሠራውን ኃጢአት ደመሰሰ ስለዚህም በምንሠራው ኃጢአት ሁሉ አንጠየቅም” ማለት አይደለም በፍጹም፡፡ እንዲህ ማለት ቢሆን ኖሮማ በብዙ ቦታዎች ላይ እሱ ራሱ ጌታ ትእዛዛቱ ወይም ሕግጋቱ እንዲጠበቁ ባላስጠነቀቀ ባላሳሰበ ነበር “ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ” ዮሐ. 14፤15 “ትዕዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም፡፡ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሟል” 1ኛ ዮሐ. 3፤5
እንግዲህ በኢየሱስ የሚያምን ማለት ብዙዎች እንደሚያስቡት በቃ አምኛለሁ ማለት ሳይሆን ሮሜ. 8፤1-8 እንደተገለጸው የሥጋን ነገር ጣል እርግፍ አድርጎ የመንፈስን ነገር መያዝ ማለት እንደሆነ በማያሻማ መልኩ ግልጽ አድርጎታል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ካልታከለበት በስተቀር በሥራው ብቻ የሚጸድቅ የለም ምክንያቱም ምንም ያህል የጽድቅ ሥራ ቢኖረን ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው “ጽድቃችን እንደመርገም ጨርጭ ነውና” ሐዋርያትም “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” 1ኛ ዮሐ. 1፤9 ይላሉና ከሠራነው የጽድቅ ሥራ ጋር ቸርነቱ ታክሎበት የምንጸድቅ በመሆኑ “እንዲሁ በጸጋው (በቸርነቱ)” ጸደቅን ማለት ይቻላል እንጅ እርኩሰት እየተፈጸመ ንስሐን ሳያውቁ “በጸጋው ጸድቀናል” የሚባል ነገር የአጋንንት ወንጌል ካልሆነ በስተቀር የክርስቶስ ወንጌል ይሄንን ፈጽሞ አላለም፡፡ እናም ቃሉ የማያሻማ በመሆኑ ማምታታት ማወናበድ አይቻልም፡፡
“እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፡፡ ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፡፡” ማቴ. 16፤24-28 ጌታ ያለውን ልብ አላቹህ? “ለሁሉ እንደሥራው” ነው ያለው ይህ ሁሉ ግልጽ የጌታ ቃል በብዛት ተጽፎ እያለ መናፍቃኑ ግን ያለማወቃቸው አለማወቅ አይሁድ በክርስቶስ ሳያምኑ ሕግን በመፈጸም ብቻ እንደሚጸድቁ ያስቡ ነበርና ሐዋርያት ለአይሁድ በክርስቶስ ሳያምኑ ሕግን በመፈጸም ብቻ መዳን እንደማይችሉ የተናገሩትን ቃል ሮሜ. 3፤11-20 እንዲሁም ገላ. 2፤16 በመጥቀስ በክርስቶስ አምነን “ትዕዛዜን ጠብቁ” ያለንን የአምላካችንን ቃል አክብረን ሕጉን ትዕዛዙን ለመጠበቅ ለምንጥረው ለእኛ እየጠቀሱ “ሕግን መጠበቅ አያድንም ማመን ብቻ ነው የሚያድነው” እያሉ ሲጠቅሱ ይደመጣሉ፡፡ “በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጅ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና” ሮሜ. 2፤13
ሐዋርያትም ከጌታ እንደመረዳታቸው ሁሉ ሲሰብኩ ምን አሉ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” አሉ የሐዋ. ሥራ 14፤22 “በኋላየ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ” ሉቃ. 9፤23 ቃሉ መስቀሌን ሳይሆን መስቀሉን በማለት የየራሳችንን መስቀል ነውና የሚለው መስቀል መሸከም ማለት ክርስቶስ ስለ እኛ የተቀበለውን መከራ በማሰብ እንደተራበ እንደተጠማ እንደወደቀ እንደተነሣ ሁሉ አብዝቶ በመጾም መራብ፣ አብዝቶ በመጸለይ በመስገድና እራስን በማድከም እንደየ አቅማችን ክርስቶስን በመከራው መምሰል ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን ግን ከዚህም አልፈው ማለትም አብዝቶ ከመጾም ከመጸለይ ከመስገድ ባሻገር በየገድላቸው ተጽፎ እንደምናገኘው ሁሉ ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ ያህልም እንኳን ባይሆን ምክንያቱም የእሱን መከራ ማንም የሚችል የለምና ነገር ግን እንዳስቻላቸው መጠን ብዙ ዓይነት ለእኛ ለሥጋውያኑ ፈጽሞ ሊታሰብ የሚከብዱ የመከራ ዓይነቶችን በየገዳሙ፣ በየበረሀው፣ በየዋሻው፣ በየፍርኩታው ስለ ፍቅሩ ስለስሙ ክብር ስለአምላክነቱ ይቀበላሉ በመከራውም ይመስሉታል፡፡ አስቀድሞም ቃሉ ስለ እነሱ “የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉት” ገላ. 5፤24 እንዳለው ሁሉ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሥጋቸውን ብዙ መከራ እንዲቀበል በማድረጋቸው እንደዛ የሆኑለት አምላካቸው መድኃኔዓለም ክርስቶስም ለብዙ ክብርና ጸጋ አብቅቷቸዋል፡፡
“የተጠራቹህት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉት ምሳሌ ትቶላቹህ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና” 1ጴጥ. 2፤21 “ቀንበሬን በላያቹህ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳቹህም ዕረፍት ታገኛላቹህ” ማቴ. 11፤29 ከዚህ በላይ እንደምን አድርጎ በግልጽ ይናገር? ክርስትና ማለት መከራ መቀበል እንጅ “አንድ ጊዜ ቤጸጋው ድነናል” በማለት የሥጋ ድሎትን ዓለምን ማሳደድ አይደለም፡፡ ሌላም እንጨምር? “ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላቹህ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጅ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ እናንተ ደግሞ ያን ሐሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋቹህ ያዙት በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቷልና” 1ጴጥ 4፤1 “ሞትን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ በእርሱ ጋር እንተባበራለን” ሮሜ 6፤5
ይሄ ሲባል ግን ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን መናኝ የበረሀ ባሕታዊ መሆን አለበት ሀገርም ወና ትሁን ትውልድም ይቋረጥ ማለት አይደለም፡፡ ክርስቶስም ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል “ለተሰጣቸው ነው እንጅ ለሁሉ አይደለም” ማቴ. 19፤11 ብሎ “ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው” ማቴ. 19፤12 የተቀረነው ደግሞ በዓለም ሆነን ሃይማኖታችንን ጠብቀን ሥራችንን እየሠራን ሀገር እያለማን ቤተክርስቲያን በዓለም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንደየአቅማቸው የደነገገችውን የጾም የጸሎት የሥግደት የሌሎችንም ትሩፋቶች ሥርዓት እየፈጸምን ክርስትናን እንኖራለን ማለት ነው፡፡ እንጂ የሌለ ነገር እየተጠቀሰ ክርስቶስ እንዲህ ሆኖልኛል ምንትስ እየተባለ መረን ተለቆ የሚኖር ክርስትና ጨርሶ የለም፡፡
ለዚህም ነው ቃሉ “ወንድሞች ሆይ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?….ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንደዚሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” ያዕ. 2፤14-26 “በጠበበው ደጅ ግቡ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጁ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው ወደ ሕይዎት የሚወስደው ደጁ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው፡፡ የበግ ለምድ ለብሰው (ክፉ ሆነው ሳለ ለማታለል በማስመሰል በበግ የሚመሰሉትን የጻድቃንን ጠባይና ሥራ እየሠሩ) ከሚመጡባቹህ በውስጠቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ሐሰተኞች ነቢያትና ሐሰተኞች መምህራን ተጠንቀቁ…. በሰማያት ያለው የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጅ ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙዎች ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃቹህም እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብየ እመሰክርባቸዋለሁ” ማቴ. 7፤13-23 በስምህ ይሉኛል አለ እንጅ በስሜ አለማለቱን ልብ ይሏል፡፡ ሐሰተኞች ክርስቶሶች እንደሚመጡና በእነሱም ስም የተጠቀሰው ሁሉ ተአምራትና ከዚያም በላይ እንደሚያደርጉ አስቀድሞ ተናግሯልና፡፡ ማቴ.24፤25
“አመንዝሮች ሆይ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ ለዓለም ወዳድ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኗል፡፡…..እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል፡፡ እናንተ ኃጢአተኞች እጆቻቹህን አንጹ ሁለት ሐሳብም ያላቹህ እናንተ ልባቹህን አጥሩ፡፡ ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም ሳቃቹህ ወደ ኃዘን ደስታቹህም ወደ ትካዜ ይለወጥ፡፡ በጌታ ፊት ራሳቹህን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋቹሀል፡፡” ያዕ. 4፤4-10 እንግዲህ ቃሉ እንዳረጋገጠልን የሃይማኖተኝነት ወይም የመንፈሳዊነት መንገድ ይሄው ነው ሌላ የለም፡፡ የጌታ ቃል የሚለው ይሄንን ከሆነ እነሱ ከየት አምጥተው እንደሚዘባርቁ ልብ ያለው ልብ ይላል፡፡
እነዚህ ሰዎች ጥቅመኛ የሆነውን የከተማ ሰው ብቻ አይደለም እያሰናከሉት ያሉት በገጠሩ የሀገራችን ክፍልም ያለው ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያስደነግጥም ሆኗል፡፡ አንዳንድ የገጠር አብያተክርስቲያናት አንድ ምእመን እንኳን ጠፍቶ ወናቸውን ቀርተዋል፡፡ መናፍቃኑ ወፍጮ ቤት፣ ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤት ወዘተረፈ. በማባበያነት በመክፈትና ለተቸገሩትም በየወሩ የሚያገኙትን እርዳታ በመስጠት አሟጠው ወስደውታል፡፡ የዚህን ሁሉ ጉድ ውጤት በሚቀጥለው የሕዝብ ቆጠራ ላይ የምታዩት ይሆናል ካልተጭበረበረ፡፡
ይህ የምእመናን ቁጥር የማሽቆልቆል አደጋ ባለፉት ዓመታት ጀምሮ ሊጠናቀቅ ይችል ነበር እግዚአብሔር ከዚህ ሲታደገን ብልሁን አርቆ አሳቢውን ቅዱሱን አባት አቡነ ጎርጎርዮስ ካልእን አሳስቦ በጣት በሚቆጠሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች የተጀመረው ማኅበር ለእናት ቤተክርስቲያን ቶሎ ጎልምሶላት በርካታ አስመስጋኝ ሥራዎችን ሠርቶ ታደጋት እንጅ፡፡ እንደምታስታውሱት ቀደም ባለው ጊዜ መናፍቃኑ የተማረውን ክፍል ከያዙ ሌላው እንደማይቸግራቸው በመረዳት የተማረውን ክፍል ለመያዝ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እግራቸውን ተክለው እየተመረቁ የሚወጡ ተማሪዎችን መናፍቅ አድርገው እያወጡ መናፍቅነት የምሁራን ሃይማኖት መስሎ እንዲታይ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሕዝብ ለመብላት ያስቻላቸውንና ባይገቱ ኖሮ ባጠቃላይ ቤተክርስቲያንን መውረስ ያስችላቸው የነበረውን ሰይጣናዊ ሴራ ያከናውኑ ነበር፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በእግዚአብሔር ረድኤት በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ትጋት በመላ ሀገሪቱ ባሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት “የግቢ ጉባኤያትን” በማደራጀት ይሄንን ሰይጣናዊ ሴራ ያመከኑ ጀግኖች የእምነት አርበኞች ናቸው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የማኅበሩ አባላት ምሁራን ናቸው፡፡ በርካቶቹ ዲያቆናትና ቀሳውስት ሆነው ሳለ በዓለማዊው ዕውቀት ደግሞ ዶክተሮች ኢንጂኒየሮችና የመሳሰሉት ናቸው ሩቅ በማይባል ጊዜም ብዙ ፕሮፌሰሮችን ከዚህ ማኅበር እንደምናገኝ ይጠበቃል፡፡ የእግዚአብሔር እጅ ስላለበት ሆነ እንጅ እንዲህ ዓይነት ማኅበር ያስፈልጋልና እናቋቁም ቢባል እንዲህ ዓይነት ማኅበር በዚህ መልኩ መመሥረት ጨርሶ የማይታሰብ ነው፡፡ ይህ ማኅበር የቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የሀገርም ሀብት ነው፡፡
ዛሬ ላይ ይህ ማኅበር በቅጥረኛው አገዛዝ በከሀድያንና መናፍቃን ጥምረት በሚሰነዘርበት ጥቃትና ሴራ እጅግ ከባድ ፈተና ላይ ይገኛል፡፡ እነኝህ የጥፋት ኃይሎች ይሄንን ስንት የተደከመበትና ስንት ተስፋ የተጣለበት መንፈሳዊ ማኅበር ለማፍረስና ያሰቡትን ሰይጣናዊ ጥፋት ለመፈጸም ሴራ እየጎነጎኑ ይገኛሉ፡፡ አገዛዙ ማኅበሩን ለመበረዝና በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ አባሎቹን ጠቅጥቆ በማስገባት የፈለጉትን ለማድረግ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከሚያጋጥማቸው ፈተናዎች ክብደትና ጫናዎች የተነሣ እኔም በግል አጋጥሞኝ እንዳየሁት ከመሥራች አባላት ሳይቀር ሊያንጸባርቁት የማይገባ ነገር ሲያደረጉ የተመለከትኩበትና የተወዛገብኩበት አጋጣሚ እሰከ መፈጠር ተደሶ እያዳከሟቸው ይገኛሉ፡፡
በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የቤተክርስቲያን አባት ነኝ እረኛ ነኝ የሚል ለቤተክርስቲያን ጥቅም የሚታትር አባት ቢኖር ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ሊይዝ የሚችለው አቋም አዎንታዊ አበረታች ደጋፊ እንደሚሆን ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ቤተክርስቲያኗን ለመምራት ከፍተኛውን ሥልጣን የያዘው የፓትርያርክ ጽ/ቤት ይሄንን የቤተክርስቲያን ከፍተኛ አቅም አፍርሰው ቤተክርስቲያንን የመናፍቃን መረካረኪያ ለማድረግ ወይም ለማጥፋት በግላጭ እየዶለቱና እየዛቱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ሰይጣናዊ ሥራቸው የተነሣ የእነሱን ማንነትና ዓለማ መረዳት ይቻላል፡፡ ከቀን ወደቀን የምእመናን ቁጥር እያሽቆለቆለ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ አደጋ ላይ እያለች “ልጆቻችን እስኪ በርቱ እንጠንክር ምን ብናደርግ ይሻላል?” ማለት ሲገባ ማሽቆልቆሉን ግት (ታኮ) ሆኖ የያዘውን ማኅበር እንመታለን እናስወግዳለን ሲባል ለምንና ምን ለመፍጠር እንደሆነ በጣም ግልጽ ነው፡፡ በመሠረቱስ የዚህን ያህል ተዳፍረው ቤተክርስቲያንን እንደግል ንብረታቸው ያሻቸውን ያደርጓት ዘንድ ሥልጣኑን የሰጣቸው ማን ነው? የሚያስፈልገውን ቁጥር ያህል አይሆን ይሆናል እንጅ ይሄንን የእብደት የክህደት የባንዳነት ወንጀል ሲፈጽሙ ምእመናን በዝምታ ያዩናል ብለው ያስባሉ? የሚፈጠረውን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
እንግዲህ “እኔ እንኳን የክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ” የምትል እረኛ ካለህ “እኔም የመድኃኔዓለም ልጅ ነኝ” የምትል ምእመንም ካለህ ሰይጣን ባሠማራቸው ከሀዲያን አላዊያንና መናፍቃን የተቀናጀ ዘመቻ በዐይንህ ላይ እየጠፋች ያለችውን ክርስቶስ በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን ትታደግ ዘንድ ለክርስቶስ እስከሞት ድረስ የታመንክ ሆነህ የተጣለብህን አምላካዊ አደራና ግዴታ ትወጣ ዘንድ ቁረጥ፡፡ አቅም ድፍረቱና የዚህን ያህል ታማኝነቱ የለኝም ስመ ክርስቲያን ብቻ ነኝ የምትል ካለህ ደግሞ ቢያንስ ከተጠያቂነት ትድን ዘንድ “የቤተክርስቲያንን ጥፋት አታሳየን” ሳይሆን ምክንያቱም “የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየኝ” የሚለው የአቤሜሌክ ጸሎት እሱን የኢየሩሳሌምን ጥፋት እንዳያይ እስቻለው እንጅ ኢየሩሳሌምን ከጥፋት አልታደጋትምና “የቤተክርስቲያንን ጥፋት አታሳየን” ሳይሆን “ቤተክርስቲያንን ከጥፋት ታደጋት” በማለት በጾም በጸሎትና በስግደት ፈጣሪን መማጸን ክርስቲያናዊ ግዴታው መሆኑን ዐውቆ ይሄንን በማድረግ ይትጋ፡፡
ከሁለቱ አንዱንም ሳናደርግ ግን ጨርሶ ምንም እንደማያገባን አድርገን “ልጆችን የሚያሳድግ እግዚአብሔር አይደለም በእኔ ጥረትና ጥበቃ ነው የሚያድጉት” በሚል እሳቤ “ምን ላድርግ? ልጆቸን ላሳድግበት” በማለት እየተፈጸመ ያለውን አጋንንታዊ የጥፋት ሥራ በዝምታ ተባባሪ በመሆን ከተመለከትን እመኑኝ ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ይህች ቤተክርስቲያን አጋንንት በቆረጡላት የጊዜ ርቀት ከዚህች ሀገር ከመጥፋቷ በፊት ይህ ትውልድ ከእግዚአብሔር በሚመጣ አንዳች ቁጣ መዓት ወይም መቅሰፍት ይጠፋል፡፡ ያኔ ለልጆቻችን የፈጠራቸው አምላክ እያለ ልክ አራጊ ፈጣሪያቸው እኛ እንደሆንን ሁሉ ሳስተንላቸው እንድንኖርላቸው ከአምላክ ፈቃድና ሃይማኖታዊ ግዴታ ራሳችንን ያራቅንላቸው ልጆች በዚህ በሠራነው በደልና ክህደት የእግዚአብሔር ቁጣ መጥቶ የሥራችንን ባገኘን ጊዜ እነሱንም እራሳችንንም ከምንም ልናድን አለመቻላችንን ስናውቅ ያኔ መግቢያ እስክናጣ ድረስ በታላቅ ሐፍረትና መሸማቀቅ በፊቱ እናቀረቅራለን፡፡ እግዚአብሔርን መቅደም አይቻልም፡፡ እግዚአብሔርን ሳናስቀድም የምንሠራው ሥራ የምንሮጥበት ጉዳይ ሁሉ ፍሬ አይኖረውም፡፡ የምናዝንበት የምንጎዳበት እንጅ ደስ የምንሰኝበት የምንጠቀምበት አይሆንም፡፡ ይሄንን ማወቅ ከጥፋት ይታደገናልና እናስተውል፡፡
መግቢያዬ ላይ እንዳነሣሁት ይህ ቤተክርስቲያኗን ከጥፋት የመታደግ ግዴታ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ የሁሉም ዜጎች ግዴታ ነው፡፡ ይሄንን የምለው ያለማወቅ በቤተክርስቲያኗ ላይ የጥፋት ሠይፋቸውን ያነሡት እነማን እነማን እነደሆኑ ሳላውቅ ቀርቸ አይደለም፡፡ ነገር ግን እየሠሩት ያሉት ሥራ እራስን ማጥፋት እንደሆነ ሳይረዱ አብረው የተሰለፉ ሆይ ሆይ የሚሉ እንዳሉ ስለማውቅ እንጅ፡፡ እናም ለእነኝህ ወገኖች በነፍሳቸውም በሥጋቸውም እራሳቸውን ለፈጣሪ የቅጣት ፍርድ ከሚዳርግ ጥፋት ያርቁ ይጠብቁና ቤተክርስቲያንን ይጠብቁ ዘንድ ማስገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህች ቤተክርስቲያን ለዚህች ሀገር ገናና ሥልጣኔ ብቸኛውን ሚና ከመጫወቷ በተጨማሪ ይህች ሀገር በነጻነቷ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ታቦት መስቀል እየተሸከመች በየግንባሩ ተሰልፋ መሪር ዋጋና የማይተካ መሥዋዕትነት ስትከፍል የኖረች ነች፡፡ በምን ሒሳብ ነው ለዚህ ውለታዋ የሚከፈላት ዋጋ ይህ የሚሆነው?
ለባዕዳኑም ቢሆን ይህች ቤተክርስቲያን ከህክምናና መድኃኒት ቅመማ (Medicine and Pharmacology) እስከ ምህንድስና (ስለ አክሱም ሀውልትና የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የአልባሬስና ቀደም ሲልም የሌሎቹ አሳሾች ምስክርነት ለምእራባዊያን የምህንድስና ጥበብ እድገት ጉልበትና የእልህ መነሣሣት (inspiration) እንደሰጠ ልብ ይሏል) ፣ ከዘመን አቆጣጠር ቀመር እስከ ዜማና ዜማን መጽሐፍ ላይ ማስቀመጥ የሚቻልበት ዘዴ (note) ፣ ከጥልቁ ህዋ ምርምር እስከ ከርሰ ምድር ሀብት ወዘተረፈ በየጊዜው ከሽህ ዓመታት በፊት ጀምሮ እየዘረፉ ከወሰዷቸው በየ ዩኒቨርስቲው ከሚያጠኗቸው ጥንታዊ የብራና መጻሕፍቶቻችን ምን ያህል እንደተጠቀሙ እራሳቸው እየተናገሩ እየመሰከሩ እያለ ለሥልጣኔያቸው ስንት ያበረከተችን ቤተክርስቲያን ለማጥፋት ቅጥረኛ አገዛዙንና ያደራጇቸውን የመናፍቃን ድርጅቶች በመጠቀም ይሄንን ያህል መኳተናቸው ምን ያህል የወረደ የሞራል (የቅስም) ደረጃ ቢኖራቸው ነው? የሚለው የትዝብት ጥያቄ ዘወትር ያቃጭልብኛል፡፡
ይህች ቤተክርስቲያን በክብር በነበረችበት ዘመናት ይህች ሀገር በዓለም ውስጥ ከነበሩት አራት ኃያላን መንግሥታት አንደኛዋ ነበረች፡፡ ይህች ሀገር ከውድቀቷ መነሣቷን የምንሻ ከሆነ ወደድንም ጠላንም ቁልፉ ያለው በዚህችው ቤተክርስቲያን እጅ ነው፡፡ መረጃውን ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ እንደ በደላችን ሳይሆን እንደቸርነቱ ተመልክቶ ቅድስት ቤተክርስቲያንንም እኛንም በራሱ መንገድ ካንዣበበብን የመጥፋት አደጋ ይታደገን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን!!!
ኢትዮጵያ ከሃይማኖቷና ከእሴቷ ሁሉ ጋር ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
አስናቀ ደመና says
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው በየጊዜው ስለቤተክርስቲያናችንና ስለሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ለሚያካፍሉን እጅግ በጣም ጠቃሚ መረጃዎች ለማመስገን አልሞክርም። ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ ረጂም ዕድሜና ጤና ሰጥቶ ሀገራችንን የነፃነትና የዕኩልነት ተምሳሌት ሆና ማየት ከልብ እንዲችሉ እመኛለሁ።
Helen says
selam lante yehun ,kelaye betetsafew meseret manager yemefelegew neger benore andegna negeren jemero eskemecheres derese telacha yetemolabet meselo setaye hasabu hulu yetebetatene hono andu andun aferashe hono yetayal,bezalay wededekem telakem ye Egezeyabeher hasabe alemen beKerstos metekelel sehone ante beze etofanta letasekomew atechelem hayemanot mengeste semay ayasegebam,enqwa ante sawolem aletesakaletem bayehone ye Ethiopian Orthodox Muslim hono new nege yanesebek pente hono ayelem lemanegnawem yetsafekewen melese anebebew hayemanotena bahel betam yeleyal bless u
Helen says
yeresahut neger benore degemo meche pente Geberesedom endefekedu bemereja betakereblen ,degemo Ethiopia zafe kebe eyekebu yemeyamenu hebereteseb new nege yeneberat sefetera tekekelegna amelaken yete yawekalu bekereb aydel ende hezebu metsafena manebe yejemerew ahun ayenun geleto hezebu manebebe sechel wengelen tereda ya degemo anten abesache tawekalek gena hulum anbebo yeredal keze eserate yameletal yetelat hasabema zelalem geregeda eyasame leyanor neber aletesakaletem gezew yemenkat new
Helen says
I think alanebebekem meselegne the bible said 1 Corinthians 3:16 ►
Don’t you know that you yourselves are God’s temple and that God’s Spirit dwells in your midst? yelal yehe malet degemo mekedesu betechristan weste sayehon anteweste new degemo 2teselonke2:4 antichristtu kebetechristian weste endemeweta yenageral so my bro eraseken adene
ፍሬህይወት አሰፋ says
ቃለ ህይወት ያሰማልን ፀጋውን ብዝዝዝዝት ያድርግልዎት ስለ እውነት አንገብጋቢ
የሆነውን ለጥያቄ ሙሉ መልስ አግንቼ ጠላቴ ድያቢሎስ ያጠረውን ወጥመድ እንድበጣጥስ
ስለረዱኝ የክርስቶስ ሰላም ፀጋው እድሜ ጤና ይስጥዎት እያልኩ በዚሁ ይቀጥሉበት
አንብቦ ለመረዳት እንዲህ የተፃፈ ካለ ከምንም በላይ መልስ ስለሆነ ብዙ እንደኔ
ያሉት እህት ወንድሞቼ ከመናፍቃን ሴራ የሚያመልጡበት ስለሆነ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው