ፌብርዋሪ 14, 2015 በኖርዌይ የሚኖሩ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ መተዳደሪያ ደንቡ በሚያዘው መሰረት የአባላት ጠቅላላ 3ኛ እና 4ኛ ሩብ ዓመት መደበኛ ስብሰባ የሥራ ክንውን ሪፖርት የቀረበበት የተሳካ አጠቃላይ ስብሰባ አድርገዋል። በስብሰባው ላይ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎና በተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች የሚኖሩ የድርጅቱ አባላቶች የተገኙ ሲሆን የአባላት ስብሰባው አስቀድሞ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት በኖርዌጂያን የሠዓት አቆጣጠር ከቀኑ 13፡30 ተጀምሮዋል።
ስብሰባውን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አቢ አማረ በ 24 ዓመት የወያኔ አረመኒያዊ አገዛዝ በግፍ ለተገደሉት እና በየእስር ቤቱ በግፍ ለሚስቃዮ ንጹሀን ዜጐች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጹሎት በማድረግ ስብሰባውን ያስጀመሩ ሲሆን በመቀጠልም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ሊቀመበር አቶ ዮሐንስ አለሙ አባላቱን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ንግግር አቅርበው የዛሬው የአባላት ስብሰባ ከሌሎቹ ጊዜያት በሁለት ምክንያቶች የተለየ መሆኑን ለተሰብሳቢው ገልፀዋል ይሄውም፦
1. የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ 60 ኛ ዓመት የልደት በአል የሚከበር መሆኑና
2. የዲሞክራሲ ለውጥ በኢትዩጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የተመሰረተበትን 10ኛ አመቱ ላይ መገኘቱ እንደሆነ በማስረዳት ድርጅቱ በእነኚህ አስር ዓመታት ውስጥ ብዙ አመርቂ ስራዎችን እንደሰራና ቅንጅት ይዞለት የተነሳው አላማ እስከ አሁን ድረስ ይዞ በመጓዝ ላይ ያለ ድርጅት በመሆኑ ኩራት የሚሰማቸው መሆኑን በመግለፅ ይህንንም አላማ ከግብ ለማድረስ በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ወጣቶች እየሰሩ ያለውን በማድነቅ ወጣቶች ወያኔን ከስልጣን ለማስወገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸው በመሆኑ ትግላቸውን አጠንክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል። ሊቀመንበሩ በንግግራቸው መጨረሻ አቶ አንድአርጋቸው ፅጌንና ሌሎችም በግፍ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን በትግላችን እናስፈታለን ብለዋል።
በመቀጠል የተለያዩ የስራ ክፍል ኃላፊዎች የስድስት ወር የስራ ክንውን ረፖርት ለአባላቱ ያቀረቡ ሲሆን ከበርገን፣ ከስታቫንገር፣ እና ከትሮንዳይም የመጡ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የስራ ኃላፊዎች በስድስት ወር ውስጥ ስለሰሩት ስራዎች እና ወደፊትም ሊሰሩ ያቀዱትን ስራዎች ለአባላቱ በዝርዝር አስረድተዋል።
ከአባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በድርጀቱ ሊቀንበሩ አማካኝነት ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን፣ በመቀጠል የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የሚረዳቸው ድርጅቶችን በማስመልከት በድርጅቱ በተወከሉት ሠዎች አማካኝነት ስለድርጅቶቹ አላማ እና ድርጅቶች እየሰሩ ስላሉት ስራዎች ሰፋ ያለ ግምገማ አቅርበዋል።
ግንቦት ሰባትን በመወከል ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም ንግግር ያደረጉ ሲሆን በቅርቡ ግንቦት 7 ከአርበኞች ጋር ውህደት እንደፈጠሩ በመግለፅ ውህደት ያስፈለገበትንና የውህደቱን ጠቀሜታ በመግለፅ ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የሚለው ስምም አርበኞች ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት የዲሞክራሲ ንቅናቄ በሚል መተካቱን በመናገር ድርጅቱን እየመሩ ያሉትን አመራሮች እነማን እንደሆኑ ለአባላቱ አስተዋውቀዋል።
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ እየደገፈ ያለውን የሰማያዊ ፓርቲ አላማ እና እየሰራ ያለውን ስራ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ያቀረቡት ደግሞ አቶ ተዘራ ሲሆኑ የሰማያዊ ፓርቲ ከአረመኔያዊው የወያኔ መንግስት የተለየ ወከባ እንደሚደርስበትና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችም ሆነ አባላቶች በወያኔ እየደረሰባቸው ያለውን ጫና በመቋቋም ትግላቸውን አጠናክረው በመቀጠል ላይ እንደሆኑ በማስረዳት ወደፊትም ዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ አባላቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ስለ አንድነት ፓርቲ አጠር ያለ ንግግር ያደረጉ አቶ ዮሐንስ ሲሆኑ እሳቸው በወያኔ መሰሪ ሴራ አንድነት ፓርቲ በመፍረሱ እንዳዘነኑና ነገር ግን ዘጠና ከመቶ የሚሆኑት የአንድነት አባላትም ሆነ አመራሮች ሠማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን ጠቅሰው ይሄም እንዳስደሰታቸውና ለጊዜው አንድነትን መደገፋቸውን በማቆም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አላማ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ድርጅቶች ሠማያዊ ፓርቲ እና አርበኞች ግንቦት 7 ድርጅቶችን በመደገፍ እንደሚቀጥሉ አባላቱ በአንድነት ድምፅ ወስነዋል። ከዚህ በፊት የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አንድነት ፓርቲን፣ ሰማያዊ ፓርቲ እና ግንቦት ሰባትን ሲደግፉ መቆየታቸው ይታወቃል።
በመጨረሻ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል አበበ የመዝጊያ ንግግር አድርገው የአባላት ስብሰባው 16፡30 ተጠናቋል።
በመቀጠልም የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን 60ኛ አመት የልደት በአል አከባበር የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ዮሀንስ የመክፈቻ ንግግር አድርገው ስለአቶ አንዳርጋቸው አጭር ንግግር በማድረግ ዝግጅቱን አስጀምረዋል። የአንዳርጋቸውን ታሪክ የሚዳስስ አጭር ፊልም በወጣቶች ክፍል የቀረበ ሲሆን በመቀጠልም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ማን ነው? በሚልህይወትታሪኩ ዙሪያ እና ለሀገሩ ያደረጋቸውን የትግል ተሞክሮዎች በቅርበት ከሚያውቋቸው ሰው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቀርቧል። እንዲሁም አቶ አንዳርጋቸውን የሚያወድሱና ስለጀግንነቱ የሚያወሩ የተለያዩ ግጥሞችም ቀርበዋል።
በመጨረሻም የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ምስል የያዙ ኬኮች ከድርጅቱ ዋና ፅፈትቤት እና ትሮንድላንድ ቅርንጫፍ ፅፈትቤት አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን በድርጅቱ ሊቀመንበር እንዲሁም በወጣቶችና ሴቶች ክፍል ተወካዮች የመልካም ልደት ኬኩ ተቆርሶ ስነስርአቱ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በተደረሰው ላንቺ ነው ሀገሬ ላንቺ ነው ላንቺ ነው ኢትዮጵያ ላንቺ ነው በሚለው ዝማሬ ዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ በኖርዌጅያን የሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 22፡00 ተጠናቋል።
በመጨረሻ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ወጣቶች ፕሮግራሙን በመዘጋጀትና
በመምራት ላደረጉት አስተዋጾ በድጅቱ ና በስራ አስፈጻሚኮሚቴ ስም ምስጋና እናቀባለን!1
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ
Leave a Reply