ታላቁ መጽሐፍ መጽሐፈ መክብብ
ምዕራፍ አስራ አራት በአንክሮ ሲነበብ
እንዳትነቃነቅ ካለህበት አገር …»
በሚለው የጸናህ የቆየህ በቃሉ
ለካ! አንተ ኖረሃል ተሜ ባለውሉ
በአንድ ብዕር ብቻ
አላንዳች ፍራቻ
ገዢን ያንበረከክ
ዝምታን የሰበርክ
ዕውነትን ያበሰርክ
ተሜ ባለ ውሉ
ተሜ ባለ ቃሉ
ነጻነት ቃጭሉ
የፍትህ አክሊሉ
የታለ መሣሪያህ?
የታለ ጦር ጋሻህ?
እኮ! በምንህ ነው? እንደዚህ የፈሩህ!
የጀግንነት ምስጢር
ውስጡ ሲመረመር
መግደል ብቻ ሳይሆን በጫካ መሽጎ
ጽፎ የሚያጎርስም ቁጣውን ሰንጎ
እንደሆነ ጎበዝ እንደሆነ ጀግና
ትምህርት አስተማርከን አንተ ብቅ አልክና
ተሜ ባለ ውሉ
ተሜ ባለ ቃሉ
የፍትህ አክሊሉ
ብዕርህን ነጥቀው ወረወሩት አሉኝ
ማጎርያ ከተቱህ አሰሩህ ሰማሁኝ
ባያውቁት ነው እንጂ! አንተ መቼ ታሰርክ
በመዝገብ አስፍሮ ሾመህ እንጂ ታሪክ
ማንም ያልሰማብኝ እኔ ነኝ እስረኛ
ጠፍሮ የያዘኝ የስደት ምርኮኛ
ካነሳሁት አይቀር አንዴ ከተናገርኩ
የናት ሀገር ፍቅር በምላሴ የያዝኩ
እራሴን ከስሼ በራሴ የፈረድኩ
ምን ያስደብቀኛል እኔ ነኝ የታሰርኩ
መሬት የቀበርኩኝ ዲናር ተበድሬ
ዕዳዬን ያልከፈልኩ ያላፈራሁ ፍሬ
ስደትን ያገባሁ ፍርሃት ሚዜ ሆኖኝ
እውነት ለመናገር የታሰርኩ እኔ ነኝ
እናንተም ተመስገን ታሰረ እንዳትሉ
እንዳትቀልዱበት በጀግንነት ውሉ
በአቋሙ የጸና ያላወላወለ
የሀገር ባለዕዳነት እዛው የከፈለ
የነጻነት ሎሌ ግፍ ፍራቻ ደምሳሽ
ተሜ ባለ ውሉ
ተሜ ባለ ቃሉ
ነጻነት ቃጭሉ
የፍትህ አክሊሉ
ድፍረትህ አረካኝ
ጀግነትህ ጠራኝ
ወኔህ ልቤን ሞላኝ
ተመስገን ደሳለኝ
Leave a Reply