
ላለፉት 10 ቀናት ደብዛው ጠፍቶ የሰነበተው እና በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዝዋይ ማረሚያ ቤት እንዳገኙት ቤተሰቦቹ አስታወቁ፡፡ ቤተሰቦቹ “ተመስገን ዝዋይ የለንም ተብለናል” ሲሉ አቤቱቻቸውን ለተለያዩ አካላት ሲያቀርቡ ሰንብተዋል፡፡ ዛሬ ለጥቂት ደቂቃዎች ተመስገንን መመልከት እንደቻሉና ጤንነቱ መቃወሱን ተናግረዋል፡፡
በጻፋቸው እና ባሳተማቸው ጽሁፎች ክስ ቀርቦበት እና ተፈርዶበት ዝዋይ ማረሚያ ቤት እስሩን እየገፋ ይገኝ የነበረው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ደብዛ መጥፋት የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ፡፡ ከሰብዓዊ መብት ተቋማት እስከ ጋዜጠኛ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተው መግለጫ እስከ ማውጣት እና በማኅበራዊ መገናኛዎች ዘመቻ እስከመክፈት ደርሰዋል፡
የተመስገን ደሳለኝ ቤተሰቦች በዝዋይ ማረሚያ ቤት “ተመስገን እዚህ የለም” ተብለናል ካሉበት ቀን አንስቶ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር ባሉ የተለያዩ እስር ቤቶች ጋዜጠኛውን ሲያፈላልጉ ቆይተዋል፡፡ ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤትም በየቀኑ በመሄድ ጥያቄቸውን በተደጋጋሚ አቅርበዋል፡፡ እስከዛሬ ረፋድ ድረስ ግን ያገኙት የነበረው ተመሳሳይ ምላሽ “የለም” እንደነበር ሲገልጹ ነበር፡፡
ዛሬ ዓርብ ታሕሳስ 7 ከአዲስ አበባ ወደ ዝዋይ ተጉዞ የነበረው ወንድሙ አላምረው ደሳለኝ ግን አምስት ደቂቃ ላልሞላ ጊዜ ተመስገንን አግኝቶት እንደነበር ለዶይቸ ቨለ ገልጿል፡፡ ወንድሙን እንዴት ለማየት እንደተፈቀደለት በዝርዝር ያስረዳል፡፡
“ከበር ላይ ጠብቅ ቆይ ተባልኩኝ፡፡ ከዚያ ተደዋወሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ይዘውኝ ሄድን፡፡ በፊት በምንጠይቅበት አይደለም፡፡ በሌላ ቦታ ነው፡፡ ገባን፣ አስጠሩት፣ ጠየቅን፡፡ ከሶስት ደቂቃ እንኳ ያልበለጠ ነው፡፡ ምንም ነገር ያወራነው የለም፡፡ ሰባት ስምንት ፖሊሶች አጠገባችን አሉ፡፡ ስንቅ አልያዝንም፡፡ ሰላምታ [ተለዋወጥን]፡፡ ‘ጤንነትህን ስለው?’ ‘ጨጓራዬን በጣም እያመመኝ ነው’ ያለው፡፡ ሌላው በሽታም እንዳለ ነው- ወገቡም፣ ጆሮውም፡፡ ‘ሌላውን ምን ትጠይቀኛለህ?’ ነው ያለኝ፡፡ ‘ጆሮዬንም ያመኛል፤ ህክምና የለም፤ ግን ጨጓራዬን አሁን በጣም እያመመኝ ነው’ አለ፡፡ አሁን ካልኩህ ውጭ ምንም ነገር ማውራት አትችልም፡፡ ተከብቦ ነበር፡፡ ” ሲል የነበረውን ሁኔታ ገልጿል፡፡
የተመስገን ቤተሰቦች ከዚህ ቀደም “መጎብኘት አትችሉም” በሚል ተከልክለው እንደሚያውቁ እንጂ እንዲህ እንዳሁኑ “ጭራሹኑ በዝዋይ ማረሚያ ቤት የለም” የሚል ምላሽ አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ የ70 አመት አዛውንት የሆኑትን የተመስገንን እናት ለከፍተኛ ጭንቀት እና ህመም ዳርጓቸው እንደነበር አላምረው ይናገራል፡፡ ተመስገንን በኋላም በቀጥታ የደወለው ወደ እርሳቸው ነበር፡፡
“መጀመሪያ ከማረሚያ ቤት እንደወጣሁ ሰልኬን ስቀበል ወደ እናቴ ጋር ነው የደውልኩት፡፡ ‘አገኘሁት’ ብቻ ስላት ለረጅም ጊዜ ነው እልል ያለችው፡፡ ጠዋት ስወጣ እንደውም ‘ልጁ ቅዱስ ሚካኤል አባቱ ነው፤ ለእርሱ ሰጥቼያለሁ ከዚህ በኋላ እኔ አቅም የለኝም’ ብላ ነበር፡፡ እናቴ ስለሆነች አይደለም፡፡ ማውራት ሁሉ የለ፡፡ በጣም ተጎሳቁላለች፡፡ በጣም ትጨነቃለች፡፡ እንቅልፍ የለም፣ ጭንቀት ነው፡፡ አሟት ሁሉ ነበር፡፡ ከሦስት ቀን በፊት ሀኪም ቤት ሁሉ ወስደናታል፡፡ ዶክተሩ ‘ምንም ነገር የለም፤ አትጨነቁ’ ነው ያለው ግን የእርሷ ሁኔታ በጣም ይከብድ ነበር” ሲል እናቱ ያሳለፉትን አስጨናቂ ቀናት መለስ ብሎ ያስታውሳል፡፡
ተመስገን ደሳለኝ መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ፈጽሟል በሚል ሦስት ዓመት እስራት የተበየነበት በጥቅምት 2007 ነበር፡፡ ሁለት ዓመት ከአንድ ወር በእስር ያሳለፈው ተመስገን አመክሮ ቢጠበቅለት ኖሮ ከእስር ተፈቺ እንደነበር ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡ ዓለም አቀፉን የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት (ሲፒጄን) ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋዜጠኛው ሀሳቡን በነጻነት በመግለጹ ምክንያት መታሰር እንደሌለበት ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡ (ምንጭ: ዶይቸ ቨለ ተስፋለም ወልደየስና ሸዋዬ ለገሠ)
Leave a Reply