ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከሁለት ሳምንት እንግልት በኋላ ዛሬ ምሽት ከቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ ተነስቶ ወደ ኦስሎ ኖርዌይ ጉዞውን ጀምሯል።
ኢትዮጵያዊው የፖፕ እና ሬጌ ሚዚቃ አቀንቃኝ በአውሮፓ ከተሞች የሙዚቃ ዝግጅቱን ለማድረግ ከአዲስ አበባ ተነስቶ የነበረው በወሩ መጀመርያ ላይ ነበር። ባለፈው ሃሙስ ዲሴምበር 4፣ 2014 ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣብያ እንደደረሰ የደህንነት አካላት እንዳገቱት እና ፓስፖርቱንም እንደቀሙበት በልዩ ልዩ የዜና ምንጮች መዘገቡ ይታወሳል።
አርቲስቱ ለምን ወደ ውጭ እንዳይወጣ እንደታገደና ፓስፖርቱም ለምን እንደተቀማ እስካሁን በይፋ የተነገረ ነገር የለም። አንዳንድ የዜና ምንጮች ጉዳዩን ቀረጥ ካለመክፈል ክስ ጋር አያይዘው አቅርበውታል። ይህ መላ ምት ፍጹም ስህተት ነው። ምክንያቱም ድምጻዊው በጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መርማሪ ቡድን ሙሉ ቀን ታስሮ ቢውልም ያለምንም ክስ ነበር የተለቀቀው። ቴዲ አፍሮ በዚህ ጉዳይ ቢከሰስ እንኳን አገር ውስጥ ሲገባ ታክስ ያልተከፈለበት መኪና መንዳት ፓስፖርት የሚያስነጥቅ ወንጀል አይደለም። ቴዲ አፍሮ፣ የተጠቀሰውን ተሽከርካሪ የገዛው በሕጋዊ ደረሰኝ ቀረጥ ከፍሎ መሆኑን በወቅቱ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ ነበር የተለቀቀው።
በጉዞ እገዳው ሳብያ ሁለት የአውሮፓ ኮንሰርቶቹ ተሰርዘዋል። ቀድሞ አውሮፓ የገባው የቴዲ አፍሮ ማናጀር ዘካርያዝ ጌታቸው እና አቡጊዳ ባንድ ስራቸው እንዲተጓጎል ተደርጓል። በአውሮፓ የቴዲ ኮንሰርት ፕሮሞተሮች ለአላስፈላጊ ወጪ ተዳርገዋል። የድምጻዊው አፍቃሪዎቹ ስሜት በእጅጉ ተጎድቷል።
ቴዲ አፍሮ ከጠበቆቹ እና ከስራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ላለፉት አስራ አንድ ቀናት፤ ጉዳዩን ለማጣራት እና እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ሲጥር እንደነበርም ታውቋል።
ከሁለት ሳምንታት እንግልት በኋላ በትላንት ምሽት የገዛ ፖስፖርቱን አግኝቷል።
አርቲስቱ ከሃገር እንዳይወጣ መከልከል፣ ፓስፖርቱ መቀማትና እንዲጉላላ ማድረጉ በአብዛኛው ኢትዮያዊ ዘንድ ቁጣ ማስነሳቱን እና በገዥው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህ ከአንድ መንግስት በማይጠበቅ ድርጊት የተነሳ የገዢው ፓርቲ አባላት ሳይቀሩ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተስተውለዋል።
ቴዲ አፍሮ በነገው እለት ማለትም ቅዳሜ – 20 ዲሴምበር 2014 ኦስሎ ላይ ዝግጅት አለው። ሌሊቱን ተጉዞ አድሮ ምሽቱን ይጫወታል። ባንዱም ኦስሎ ላይ በልዩ ዝግጅት ይጠብቃዋል። ከዚያም በሳምንቱ ማለትም በ 27 ዲሴምበር 2014 በስዊድን ከተማ፤ በ 31 ዲሴምበር 2014 ፍራንክፈርት፤ በ 3 ጃንዋሪ 2015 በሎዛን-ስዊዘርላንድ የሙዚቃ ስራውን ያቀርባል።
ከዚያም በ ጃንዋሪ 10፤ 2015(ለኢትዮጵያ ገና) አምስተርዳም ላይ ልዩ ዝግጅቱን ይዞ ከአቡጊዳ ባንድ ጋር ይመለሳል። ከአምስተርዳም በኋላ ቀጣይ ስራዎቹ ፊንላንድ እና ዱባይ ናቸው።
በዘንድሮው የቴዲ አፍሮ አውሮፓ ኮንሰርቶች ከምንግዜውም የበለጠ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያውያን የሙዚቃ አፍቃሪዎች እንደሚገኙ ይገመታል።
Leave a Reply