
ለቢንላደን ቀብር ምስካሪ የባህር ኃይል የለም
በሚያዚያ ወር 2003ዓም ድንገተኛ ወረራ ተካሂዶበት ቀብሩም ወዲው ተጠናቅቆዋል የተባለው ኦሳማ ቢንላደን ባህር ውስጥ ሲቀበር የተመለከተ አንድም የአሜሪካ የባህር ኃይል አባል እንደሌለ ተገለጸ፡፡ አሶሺየትድ ፕሬስ “የመረጃ ነጻነት ሕግን” ጠቅሶ በጠየቀውና ባገኘው መረጃ መሠረት “ባልታወቀ ባህር” ተቀበረ የተባለው ቢንላደን ሲቀበር ምስካሪ እንደሌለ የዘገበ ሲሆን ከፓኪስታን ወደ ካርል ቪንስ የአሜሪካ የጦር መርከብ በተጫነበት ወቅት የተነሳ ፎቶግራፍም ሆነ ቪዲዮ የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) ማግኘት እንዳልቻለ ጨምሮ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የድህረሞት ምርመራ፣ የሞት ሠርቲፊኬት፣ የዲኤንኤ ምርመራ፣ … እንዳልተካሄደና ይህንኑ የሚያሳይ መረጃ የመከላከያ ሚ/ር ማቅረብ እንዳልተቻለ ተገልጾዋል፡፡
የቢንላደን ሬሣ ከታጠበና በነጭ ጨርቅ ከተጠቀለለ በኋላ በእምነቱ መሠረት በተከናወነ ሥነስርዓት ወደባህር ተጥሏል የሚለው ጾዳቤ (ኢሜይል) መልዕክት ለጥቂት ከፍተኛ የጦር ኃላፊዎች ተላልፎ ነበር፡፡ በወቅቱ በፓኪስታን የአቦታባድ ከተማ ወረራው ሲካሄድ ከተሠማሩት ሁለት ሄሊኮፕተሮች ወድቆ ስለነበረው ጥገናም ሆነ ሌላ መረጃ እንዲሁም ጉዞውን በተመለከተ የበረራ መረጃ ስለመኖሩ የመከላከያ ሚ/ር የክህደትም ይሁን የማረጋገጫ ቃሉን ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
“ቢንላደን ሲአይኤ ጠፍጥፎ የሠራው ነው” ብለው የሚያምኑ እየበረከቱ በሄዱበት ባሁኑ ወቅት ይህ የኤፒ ዘገባ ትልቅ ዓይን ከፋች ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢንላደን የዛሬ 10ዓመት አካባቢ ታሞ እንደነበርና ከአሜሪካ ባለሥልጣናት በጣም ጥቂቶች ሆስፒታል ድረስ እንደጎበኙት የሚናገሩ አሉ፡፡ ከዚያም ጥቂት ጊዜያት ቆይቶ በህመም ምክንያት ከዚህዓለም በሞት እንደተለየ በርካታ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ለሚናገሩ ይህ ዘገባ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጥ ነው፡፡
ወሲብ ከአጽም ጋር
በመኖሪያ ቤቷ የወንዶችን አጽም እየሰበሰበች ከእነርሱ ጋር ወሲብ ስትፈጽም ነበር በማለት የስዊድን ፖሊስ በ37 ዓመቷ ግለሰብ ላይ ክስ መስርቷል፡፡ ስሟ ያልተገለጸው ስዊድናዊት መኖሪያ ሲመረመር ወደ 100 የሚደርስ የሰው አጥንት የተገኘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ስድስት የራስ ቅልና አንድ የጀርባ አጥንት ይገኝበታል፡፡
አጽሙን በመኝታ አልብሳ በማስተኛት ወሲብ ፈጽማለች ያለው የዓቃቤህግ ማስረጃ ግለሰቧ የራስ ቅል ስትልስ፣ ስትስምና ስታቅፍ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ፖሊስ ማግኘቱን በክሱ ጠቁሟል፡፡ አጥንቶቹን ለታሪካዊ ፍላጎት እንደሰበሰበቻቸው የተናገረችው ተከሳሽ ክሱን ብትቃወምም የሚመጣባትን ቅጣት ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ከዚህ በፊት በድረገጽ መድረክ ላይ ተናግራ ነበር፡፡
ዓቃቤህግ “የሙታንን ሰላም በማደፍረስ” በማለት ክሱን የመሠረተ ሲሆን ተከሳሽዋ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እስከ ሁለት ዓመት ቅጣት ሊበየንባት ይችላል፡፡
“የቤተሰብ ዘራፊዎች”
በቤተሰብ ደረጃ የተዋቀረ የሌቦች ቡድን በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ የቡድኑ መሪ አባት ሲሆን የ20ዓመቱን ወንድ ልጁን የዝፊያ ረዳቱ፤ የ18ዓመቷን ሴት ልጁን ደግሞ ዘራፊዎቹ ተግባራቸውን ሲያጠናቅቁ በፈጣን የመኪና አሽከርካሪነት ተግባር የተሰማራች ነበር፡፡
እስካሁን ለተለያዩ ስድስት የባንክ ዝርፊያዎች ተጠያቂ እንደሆኑ የተጠቆሙትና “የቤተሰብ ዘራፊዎች” በመባል ስም የተሰጣቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉት በቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት ሂውስተን ከተማ ባንክ ከዘረፉ በኋላ እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ አባትየው ልጆቹን በልዩ ሁኔታ እንዳሰለጠናቸው የጠቀሰው ፖሊስ በዚሁ የባንክ ዘረፋ ወቅት አባትየው የቀን ሠራተኛ ልብስና የቀለም ቀቢ ጭምብል ያደረገ ሲሆን ወንድ ልጁ ደግሞ የሃሰት ጺም በማድረግ ራሱን በመቀየር እንደሆነ ተገልጾዋል፡፡ ዝርፊያው እንደተጠናቀቀ ሴት ልጁ ውጪ ሆና በፍጥነት መኪና በማሽከርከር የማምለጥ ተግባር ድርሻዋን ተወጥታለች፡፡
ከስድስቱ የባንክ ዘረፋዎች መካከል አምስቱ የተካሄዱት በኦሪጎን ጠቅላይ ግዛት እንደነበር አብሮ ተጠቁሟል፡፡
በማኅጸን ውስጥ ማዛጋት
በእንግሊዝ የዱርሃም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያልተወለዱ ህጻናት በእናታቸው ማኅጸን ውስጥ ሆነው እንደሚያዛጉ አረጋግጠናል ይላሉ፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ህጻናቱ ከማደግ ድካም የተነሳ በአማካይ በሰዓት ስድስት ጊዜ እንደሚያዛጉ ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ ማዛጋት አይደለም በማለት የሚከራከሩት ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ “ህጻናቱ ምንም የሚያደክማቸው ነገር የለም፤ ስለዚህ የሚያዛጉ ሳይሆን በተለምዶ አፋቸውን ሲከፍቱና ሲዘጉ ነው የታዩት” ይላሉ፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ማዛጋት ነው በማለት የሚከራከሩት ተመራማሪዎች “ህጻናቱ ደክሟቸው ነው የሚያዛጉት ለማለት ባይቻልም ህጻናቱ ልክ የማዛጋት ያህል የሚያሳዩት ረጅም የአፍ አከፋፈት የአገጭ እንቅስቃሴን የሚቆጣጠረውን የአእምሮ ክፍል እድገት በመርዳት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽዖ” እንዳለው መስክረዋል፡፡
ሲሆን “ኋይት-ሐውስ” ሳይሆን “ዲዝኒ-ዓለም”
ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተሸነፉት ሚት ሮምኒ በምርጫ ዘመቻ ውጥረት ያመለጣቸውን እያካካሱ እንደሆነ የተለያዩ የሚያስደምሙ ወሬዎች ሰሞኑን ሰምተናል፡፡ የግል አውሮፕላን እና ልዩ የደኅንነት ጥበቃ ሲደረግላቸው እንዳልቆየ አሁን ግን የራሳቸውን ጋዝ ቤንዚን ማደያ ቆመው ሲቀዱ የሚያሳየውን ፎቶ የተመለከቱ አንድ አስተያየት ሰጪ “በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አንዱ ዓለምን እየዞረ በየአገሩ እጅግ ከፍያለ አድናቆትን ሲያገኝ ሌላው ደግሞ ልክ እንደ እያንዳንዳችን የራሱን ጋዝ ሲቀዳ ይታያል” ብለዋል፡፡
ጸጉራቸው ሳይበጠር ሸሚዝ አድርገው የታዩት የ65ዓመቱ ሮምኒ ከልጆቻቸውና ቤተሰባቸው ጋርም በካሊፎርኒያ የዲዝኒ ዓለም በፈጣን ሸርተቴ ሲጫወቱና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ለረጅም ጊዜያት ያጡትን የመዝናኛ ጊዜ አካክሰዋል፡፡
“ወደህ ነው በቀበሌ ተገድደህ”
አደንዛዥ ዕጽ በመጠቀም የማሻሻያ ቅጣት ላይ የነበረችው ክሪስቲ ሳንቶስ የወንድ ጓደኛዋ ከእርስዋ ጋር ወሲብ ለመፈጸም ባለመፈለጉ በቡጢ አጠጣችው፡፡ በተደጋጋሚ የወሲብ ፍላጎትዋን ስትገልጽለት ችላ በማለት የቆየው ግለሰብ ቡጢውን ከጠጣ በኋላ ፖሊስ ጠርቶ ጉዳቱን አሳይቷል፡፡
የፍሎሪዳ ጠቅላይ ግዛት ነዋሪ የሆነችውና የ45ዓመቷ ግለሰብ ለፖሊስ በሰጠችው ቃል በዕለቱ በተደጋጋሚ ላቀረበችው የፍላጎት መግለጫ የወንድ ጓደኛዋ የሰጣት ምላሽ ካለመኖሩ ባሻገር የአሜሪካ ፉት ቦል በማየት ጥያቄዋን ችላ እንዳለው ገልጻለች፡፡ ከወሲብ ይልቅ ፉትቦል በማስቀደሙም በቁጣ ነድዳ በቦክስ እንዳጎነችው ተናግራለች፡፡
ሁለቱም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቢወሰዱም በግለሰቡ ላይ የተመሰረተ ምንም ክስ የለም፡፡
አልማዝ እንደ ኪኒን
አስገራሚው ዜና የተሰማው ከወደ ደቡብ አፍረካ ነው፡፡ በአሶሺየትድ ፕሬስ የተዘገበው ይኸው ዜና እንደሚስረዳው የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ከጆሃንስበር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የአየር ማረፊያ አንድ የ25ዓመት ወጣት 220 የአልማዝ እንክብሎችን ወደ ዱባይ በኮንትሮባንድ ሊያስተላልፍ ሲል ተይዟል፡፡
ግለሰቡ አልማዞቹን እንደ ኪኒን በመዋጥ ሊያስተላልፍ መሞከሩን የገለጸው የፖሊስ ኃላፊ የከበሩት ድንጋዮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሲናገር እንዴት ገቢ እንደተደረጉ ምንም የሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ የለም፡፡
በሰውነት መመርመሪያ ዕርዳታ ሊያዝ የቻለው አልማዝ ዋጋ 2.5 ሚሊዮን ዶላር ተገምቷል፡፡
አዲስ ፓትርያርክ
ብጹዕ ወቅዱስ ዳግማዊ አቡነ ቴዎድሮስ (ታውድሮስ) 118ኛው የግብጽ ፓትሪያርክ በመሆን በዓለ ሲመታቸው ተከናወነ፤ ጳጳሳዊ አክሊል በመድፋትም የእምነቱ ጀማሪ በሆነው የቅዱስ ማርቆስ መንበር (ዙፋን) ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ከ40 ዓመት አገልግሎት በኋላ ባለፈው መጋቢት ወር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቡነ ሸኖዳ ሣልሳዊን የተኩት አዲሱ ፓትሪያርክ የ60ዓመት አዛውንትና የፋርማሲ ምህንድስና ምሩቅ ናቸው፡፡ ለረጅም ሰዓታት በተካሄደው በዚህ በዓለ ሲመት ወቅት እጅግ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የተገኙ ሲሆን ዳግማዊ አቡነ ቴዎድሮስ በቴሌቪዥን የተሰራጨ ንግግር አላደረጉም፡፡ ሆኖም በወኪላቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ክርስቲኑም ሆነ ሙስሊሙ ለግብጽ ሰላም ተባብረው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
የአቡኑ ምርጫ በተከናወነበት ወቅት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ 5 ተወካዮች እንደተገኙ የዘገበው ማኅበረ ቅዱሳን በሥርዓተ ሲመቱ ላይም በብጹዕ አቡነ ናትናኤል የሚመራ የልዑካን ቡድን መገኘቱን ጨምሮ ገልጾዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ባለፈው ነሐሴ ወር ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ እስካሁን ፓትርያርክ አልመረጠችም፡፡ በመንግሥት በኩል የተጠቆሙ የትግራይ ተወላጅ ጳጳሳት እንዳሉ እየተነገረ ባለበት ባሁኑ ወቅት የሕጋዊው ሲኖድ መሪ ናቸው የሚባሉት አቡነ መርቆሪዮስ ወደ አገር ቤት ተመልሰው የፓትርያርኩን መንበር እንዲረከቡ ከየአቅጣጫው ግፊቶች አሉ፡፡
በግብጽ በተካሄደው ምርጫ የመጨረሻውን ዕጣ ያወጣው ዓይኑ በጨርቅ የተሸፈነው ብላቴና ቢሾይ ነበር፡፡
“ሸጥከኝ”
ጎረቤቱን አንቆ በመግደል በአንደኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል የተከሰሰው ጀሮም ፓወር ፍርድ ቤት ተሰይሞ እማኝ ዳኞች (ጁሪ) ውሳኔ ለመስጠት እየተወያዩ ባለበት ወቅት “ሸጥከኝ” በማለት በጠበቃው ላይ ኩባያ ሙሉ ውሃ ማፍሰሱ የተሰማው ከአሜሪካዋ ግዛት አየዋ ነበር፡፡
ገዳዩ እርሱ ሳይሆን በተመሳሳይ የመኖሪያ ቦታ የሚገኝ ነጭ እንደሆነ 100 ጊዜ በፖሊስ ምርመራ ወቅት የተናገረው ጀሮም ጉዳዩ የ“የሃሰት ክስ” (mistrial) ተብሎ ነጻ መለቀቅ እንደነበረበት ተናግሯል፡፡ ይህ እንደማይሆን እየተረዳ በመጣበት የመጨረሻ ሰዓት ላይ እማኝ ዳኞች በጉዳዩ ላይ ሊወስኑ ውይይት ተቀምጠው ሳለ በብሽቀት ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ ውሃውን በጠበቃው ላይ አፍስሷል፡፡ በፍርድቤቱ የነበሩ ፖሊሶች ወዲያው ያስቆሙት ቢሆንም ዳኛውና የፍርድቤቱ ታዳሚ ፍጹም ግራ ተጋብተው እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ዕድሜ ይፍታህ ያለ አመክሮ ይበየንበታል፡፡
የመስታወት መጸዳጃቤት
ሰልፈር ስፕሪንግስ በተባለ የቴክሳስ ከተማ በ54ሺህ ዶላር የተገነባው የአሜሪካ የመጀመሪያው የመስታወት መጸዳጃቤት የቱሪስት መስህብ እንደሚሆን ተነገረ፡፡ ይህ ሙሉ በሙሉ ከመስታወት የተሰራው መጸዳጃቤት ከውስጥ ወደ ውጪ ሁሉንም ነገር የሚያሳይ ሲሆን ከውጪ ወደ ውስጥ ግን አንዳችም ነገር ማየት የማይቻልበት ነው፡፡
መስታወቱ ላይ ተለጥፈው ወደ ውስጥ ለማየት የሞከሩ ምንም ማየት እንዳልቻሉ ተረጋግጦዋል፡፡ “መጀመሪያ እንደገባሁ ሰዎች ያዩኝ እንደሆነ ለማረጋገጥ ሞከርኩኝ” የምትለው ሜሪደት “አራት ወንዶች ሊያዩኝ ሙከራ ሲያደርጉ ከውስጥ ሆኜ ሳያቸው ትንሽ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን ምንም ነገር ማየት እንዳልቻሉ” ማረጋገጥ መቻሏን ተናግራለች፡፡
በስዊትዘርላድ ባለው ዓይነት የተሠራው ይህ የመጸዳጃቤት የፖሊስ መምሪያው ቀጥተኛ ቁጥጥር የሚያደርግበት ዘጠኝ የደኅንነት ካሜራዎች ተገጥመውለታል፡፡
“ወንጀለኛው ዳኛ” በትራንስፖርት መምሪያ
በአሜሪካ የማሳቹሴትስ ጠቅላይ ግዛት የመንገድ ትራንስፖርትና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ግለሰብ ዘጠኝ የትራፊክ ትኬት ቅጣቶችንና የሰባት መኪና አደጋ “ባለሃብት” መሆናቸው ተዘገበ፡፡ ቦስተን ግሎብ እንደዘገበው የ48ዓመቷ ሺላ በርገስ በቅርቡ ከፍተኛ የመኪና አደጋ ባደረሰቡበት ወቅት በውል ያልታወቀ የጭንቅላት ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ በአስተዳደራዊ ፈቃድ ከሥራ እንዲገለሉ ተደርጓል ብሏል፡፡
በሙያቸው ብቃት ወይም በትራንስፖርት ደኅንነት ምንም ዓይነት ቀዳሚ የሥራ ልምድ ኖሯቸው ሳይሆን ከታዋቂ ፖለቲከኞች ጋር ባላቸው ግንኙነት ይህንን 87ሺህ ዶላር ደመወዝ በዓመት የሚያስከፍል የመንግሥት ሥራ ለማግኘት እንደቻሉ በተጨማሪ ተዘግቧል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተገኘ መረጃ ባለፉት ሦስት ዓስርተ ዓመታት 34 የትራፊክ ህግን የጣሰ ድርጊቶች የተገኙባቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከተወሰነው ፍጥነት በላይ መንዳት፣ ለፖሊስ ትዕዛዝ አለመቆም፣ ያለመንጃ ፈቃድ መንዳት፣ … ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ግን የመቀመጫ ቀበቶ እንዲደረግ የሚያሳስበውን ዘመቻ ለጠቅላይ ግዛቱ ነዋሪዎች እያሳሰቡ ባሉበት ወቅት ራሳቸው የመቀመጫ ቀበቶ ሳያደርጉ የመምሪያውን ተሸከርካሪ እየነዱ አደጋ አድርሰው በጭንቅላታቸው ላይ ጉዳት ያደረሱበት ነው፡፡
ኃላፊዋ ወደሥራ የሚመለሱበት ጊዜ መቼ እንደሚሆን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡
“በመንፈስ መንዳት”
በሰዓት 30ማይል (48ኪሎሜትር) በሚነዳበት ክልል ውስጥ በሰዓት 100 ማይል መኪናዋን ታሽከረክር የነበረችው መሊሳ ሚለር ለድርጊቷ ፈጣሪን ተጠያቂ አደረገች፡፡ በአሜሪካ የፍሎሪዳ ጠቅላይ ግዛት ከመደበኛው ሶስት ዕጥፍ በላይ ከፍተኛ ፍጥነት በመንዳት ላይ የነበረችው የ41ዓመቷን ግለሰብ ለማስቆም ፖሊስ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ከቶዮታ መኪናዋ የማያቋርጥ ጥሩምባ ታሰማ ነበር፡፡
በፍጥነት ታሽከረክር እንደነበር ያልካደችው መሊሳ ፖሊስ ምክንያቷን በጠየቃት ወቅት “ጌታ በፍጥነት እንዳሽከረክርና ጥሩምባውንም እንድነፋ ተናግሮኛል” በማለት መመለሷ የፖሊስ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል፡፡ ግለሰቧ በግዴለሽ አሽከርካሪነት የተከሰሰች ሲሆን የ375 ዶላር ዋስ በመጥራት ከአውራጃው ማረሚያ ቤት ወጥታለች፡፡
የሰሞኑ ምርጥ ፎቶ
በእስያ ጉብኝት ወቅት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና የታይዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ዪንግለክ ሺናዋትራ
ዘገባውን ለማጠናቀር በየጽሁፉ ከጠቀስናቸው ምንጮች በተጨማሪ ሌሎችንም የሚዲያ ውጤቶች መጠቀማችንን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ከዜናዎቹ ማነስ አኳያ በየጸሁፉ ለመግለጽ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
betam arif newu bertu