በ16 ዓመቷ ታዳጊ ሃና ላላንጎ ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በመፈፀም ለሞት አብቅተዋታል በተባሉ አምስት ተጠርጣሪዎች ላይ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ክስ መሰረተባቸው። ዐቃቤ ሕግ ትናንት ማክሰኞ ታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ሁለት ሲሆን፤ ለአካለመጠን ያልደረሰችን ሴት በአሰቃቂ ሁኔታ መድፈር እና ከባድ የሰው መግደል ወንጀል የሚሉት ክሶች ተጠቅሶባቸዋል። ከትናንት በስቲያ ሜክሲኮ በሚገኘው በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የነበረውን የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ያጠናቀቀው ይህ ጉዳይ ከዚህ በኋላም በልደታ ፍርድ ቤት መታየቱን ይቀጥላል።
በመሆኑም በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው የተጠቀሰው አምስቱ ተጠርጣሪዎች 1ኛ ተከሳሽ ሳምሶን ስለሺ ሙያ ሹፌር፣ 2ኛ ተከሳሽ በዛብህ ገ/ማርያም ሾፌር፣ 3ኛ ተከሳሽ በቃሉ ገ/መድህን የታክሲ ረዳት፣ 4ኛ ተከሳሽ ኤፍሬም አየለ የታክሲ ረዳት እና 5ኛ ተከሳሽ ተመስገን ፀጋዬ ሾፌር ናቸው። ትናንት በችሎት ቀርበው ማንነታቸውን ለፍርድ ቤቱ ያረጋገጡ ሲሆን፤ የተከሰሱበት ወንጀል የዋስትና መብት የማያሰጥ በመሆኑም ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ሲል ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ለመፈፀም አስበው መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 11 ሰዓት ሲሆን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ክልል ልዩ ስሙ ጦር ኃይሎች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የ16 ዓመት ዕድሜ ያላትን ታዳጊ ሟች ሃና ላላንጎን ታክሲ ቆማ በምትጠብቅበት ወቅት 1ኛ ተከሳሽ ከሚያሽከረክረው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1-21253 አ.አ. ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ጠርቶ በማስገባት ቀራኒዮ አደባባይ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ አብረው እስከምሽቱ 2፡30 ከቆዩ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ 2ኛ ተከሳሽን በስልክ ደውሎ በመጥራት፤ 2ኛ ተከሳሽም በሚያሽከረክረው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1-17035 አ.አ. ሚኒባስ ታክሲ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችን ይዞ በመምጣት ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመገናኘት ሟችን ወደቤቱ ይዞ እንደወሰዳትና እርሱም የሚያሽከረክረውን ታክሲ አቁሞ ተመልሶ እንደሚያገኛቸው በመናገር 4ኛ ተከሳሽ ደግሞ ሟችን 2ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ታክሲ እንድትገባ በማድረግ 2ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ሟችን ይዘዋት ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ክልል ልዩ ቦታው አንቺን አሉ ህንፃ አካባቢ ከሚገኘው የ2ኛ እና የ3ኛ ተከሳሾች መኖሪያ ቤት በመውሰድ በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ሌሊቱን በሙሉ ሁሉም ተከሳሾች እየተፈራረቁ በአሰቃቂ ሁኔታ የግብረስጋ ግንኙነት ሲፈፅሙባት ያደሩ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ 18 ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ የሚፈፀም የግብረስጋ ድፍረት በደል ወንጀል ከስሻቸዋለሁ ይላል።
በሁለተኛው ክስ ስርም ተከሳሾቹ ድርጊታቸው ህገወጥና የሚያስቀጣ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል እያወቁ በግዴለሽነት እየተፈራረቁ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደፈፀሙባት፤ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰማች ማህፀኗ እየደማ በተለይ ጨካኝነታቸውን፣ ነውረኝነታቸውን እና አደገኝነታቸውን በሚያሳይ ሁኔታ ለአምስት ቀናት አቆይተዋታል ይላል ዐቃቤ ሕግ በክሱ፤ ከዚያም ከአምስት ቀናት በኋላ 2ኛ ተከሳሽ በ3ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ሟችን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ክልል ልዩ ቦታው ጦር ኃይሎች ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ወስደው ጥለዋታል፡፡ ለመጣል ሟች በደረሰባት ጉዳት የሰውነት ክፍሎቿ ስራ በማቆማቸውና ብዛት ያለው ደም የፈሰሳት በመሆኑ ከቀናት በኋላ ህይወቷ ያለፈ በመሆኑ በፈፀሙት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ተከሰዋል ይላል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎትም በትናንትናው ዕለት የተከሳሾችን ማንነት በማጣራትና ክሱ እንዲደርሳቸው በማድረግ፤ በችሎቱ ፊት ክሱ ከመነበቡ በፊት በማረሚያ ቤት ቆይተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ እና ተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ የማቆም አቅም የለንም በማለታቸውም መንግሥት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ክሱን ለማንበብም ለታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ምንጭ: ሰንደቅ)
ስለሺ says
አስተማሪ የሆነ ቅጣት በአፋጣኝ ልሠጣቸው ይገባል ፡፡ ግቢ ውስጥ ያሉትም ተከራዮችም ሆኑ ነዋሪዎች ልቀጡ ይገባል ፡፡
dij mj says
ለካ! ሞኞች ናቸዉ የደፈሩ፤ከሞት የምበልጥ ዉሳኔ ካለ ይሰጥ !!!
Adferes solomon says
ቅጣቱ የማያዳግምና ለሌሎች ወጣቶች ከፍተኛ ግንዛቤ የሚሰጥ መሆን አለበት ሌላው በዚህ ወንጀል ላይ ሊጠየቁ የሚችሉ የፖሊሰ አካላቶች ካሉ ሊካተቱ ይገባል
Sara says
Death penalty is a good lesson in future. Right noq.