ፕሬዚዳንት ኦባማ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው በፊት የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ የሆኑት ሱዛን ራይስ ወደ ኬኒያ እና ኢትዮጵያ ስለሚደረገው ጉብኝት መግለጫና ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሸ ሰጥተው ነበር፡፡
የጉብኝት ዝርዝር መርሃ ግብር በማስረዳት ንግግር የጀመሩት ራይስ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢህአዴ ሹማምንትና ከአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎች እንዲሁም ከአህጉሪቱ መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩ አስረድተዋል፡፡
ከጠያቂ ጋዜጠኞች መካከል ተራው የደረሰው አይዛክ አምባሳደር ራይስን ስለ ጉዞው የጸጽታና ደኅንነት ጉዳይ ከጠየቀ በኋላ ከዚህ በፊት ሌላኛዋ ጋዜጠኛ (ክሪስቲ) ያነሳችውን ሃሳብ በማጠናከር “ፕሬዚዳንት (ኦባማ) የኢትዮጵያና የኬኒያ መሪዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ አድርገው ይቆጥሯቸዋል?” በማለት ጠየቀ፡፡
ሱዛን ራይስ ማስረዳት ጀመሩ የጸጥታውና የደኅንነቱ ጉዳይ እምብዛም የሚያሳስብ እንዳልሆነ ዝርዝሩን በተመለከተ የምሥጢራዊ አገልግሎት ኃላፊው ማብራሪያ እንደሚሰጡ ጠቆሙ፡፡ በአካባቢው ያለውን የአልሻባብን ሁኔታን አስረዱ፡፡ “ዴሞክራሲን በተመለከተ” አሉ ሱዛን ራይስ “የኬኒያው ፕሬዚዳንት በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደተመረጡ አስባለሁ፤ የምርጫውም ሂደት ፉክክር የበዛበት ነበር፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ በተደረገ ምርጫ በመቶ ድምጽ ያሸነፉ ይመስለኛል፤ ይህንን በተመለከተም እኛም ባወጣነው መግለጫ በምርጫው ውጤት ላይ ባይሆንም እንኳን ቢያንስ የምርጫውን አካሄድ በሚያግዙ አሠራሮች ላይ እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የምርጫ ዘመቻ የማድረግ ነጻነትን በተመለከተ በምርጫው ሒደት ተዓማኒነት ላይ አንዳንድ የሚያሳስቡን ጉዳዮች እንዳሉ አስታውቀን ነበር፡፡”
ጠያቂው ግን አላቆመም፤ ስለዚህ ፕሬዚዳንት (ኦባማ) ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ነው ብለው ያስባሉ? በማለት ተያዥ ጥያቄ አስከተለ፡፡
የአቶ መለስ ቅርብ ወዳጅ የነበሩትና ይህንንም ወዳጅነት በመለስ የቀብር ስነስርዓት ላይ እንደ አንድ የኢህአዴግ ካድሬ ስለመለስ ሲዘክሩ የተሰሙት ሱዛን ራይስ ለጥያቄው “ልማታዊ” መልስ ሰጡ፤ “ያለ ጥርጥር – መቶ በመቶ” በማለት!
ከዚህ በኋላ ለተወሰኑ ሰከንዶች የተሰማው የአምባሳደሯ የማያቋርጥ ሳቅ ነበር፡፡ መቶ በመቶ ማሸነፍ እንዴትና ለምን ያስቃል?
ቪዲዮውን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
(ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ)
Leave a Reply