በአሁኑ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉ ነገር እያለው ሁሉንም ያጣ ዜጋ ዐማራው ነው ቢባል የተጋነነ ነው ሊባል አይችልም። በግልጽ እንደሚታወቀው፣ ዐማራው ቋንቋው አማርኛ ነው። ይህንን ቋንቋውን ከሌሎች የኢትዮጵያ ጎሣዎች ቋንቋዎች ጋር አጣጥሞ በማሳደግ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ መግባቢያ እንዲሆን አበርክቷል። ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ጊዜ የአማርኛ ቋንቋ ለዐማራው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተለይቶ መከበሪያው መሆኑ ቀርቶ መጠቂያው ሆኗል። በአማርኛ ቋንቋ የሚጻፉት፣ በሬድዮ እና በቴሌቪዥን የሚቀርቡት ዝግጅቶች በአብዛኛው ማለት ይቻላል፣ ዐማራው የሚወገዝባቸው፣ የሚዋረድባቸው እና የሚኮነንባቸው እየሆኑ ከመጡ ዓመታትን ተሻግረው ዘመናት ተቆጥረዋል። ስለሆነም ዐማራን እና አማርኛን በጠላትነት ፈርጀው የጥፋት ተግባራቸውን ለፈጸሙና ለሚፈጽሙ ኃይሎች አጸፋውን በመስጠት፣ የአማርኛ ቋንቋም ሆነ የዐማራ ነገድ ተገቢ ቦታቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ለማስቻል፣ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ተመሥርቶ ሠፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። ከሞረሽ ወገኔ የተግባር እንቅስቃሴዎች ውስጥ የዐማራው ድምፅ የሆነ፣ የዐማራ ድምፅ ሬድዮን ማቋቋሙ አንዱ ነው።
የዐማራ ድምፅ ሬድዮ ሥራውን በመስከረም 21 ቀን 2009 ዓም (October 1, 2016) በይፋ ሲጀምር ዓላማዬ ብሎ የተነሣው ድምፁ ለታፈነበት ዐማራው ኢትዮጵያዊ ድምፅ ለመሆን ነው። ይህ ሬድዮ በእኒህ ሁለት ወራት ባልሞሉ ጊዜያት ውስጥ ለዓላማው ስኬት ተስፋ ሰጪ የሆነ እንቅስቃሴ አድርጓል። ይህ እንቅስቃሴ ያሰጋቸውና ዐማራው ራሱን የቻለ ኃይል ሆኖ መውጣት እነርሱ ላቀዱት ዐማራን ተዋራጅ እና ተሰዳች፣ ሟች እና አናሳ አድርጎ የመግዛት አባዜ የተጫናቸው ቡድኖች፣ የዕድሜ-ጠገቦቹ የሚዲያ ተቋሞች እንኳን ሊያሟሉት ያልቻሉትን በሁሉም ዘርፍ እንከን የለሽ ዝግጅት እንድናቀርብ ከተለያዩ አቅጣጫዎች አስተያየቶችና ትችቶች ይደርሱናል። አስተያየቶቹም ሆነ፣ ትችቶቹ ለራዲዮው ዕድገት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ እናምናለን። ሆኖም ትችቶቹ እና አስተያየቶቹ ለዐማራ ድምፅ ሬዲዮ ዕድገት አስተዋጽዖ የሚኖራቸው ገንቢ እና በሐቅ ላይ የተመሠረቱ ሲሆኑ እንደሆነ ግልፅ ነው።
ይህ ይሻሻል፣ ይህ ይጨመር፣ ይህ ይደረግ፣ እንዲህ አይባል፣ ወዘተርፈ የሚባሉት አስተያየቶች ዋጋ የሚኖራቸው ዝግጅቱን ለማቅረብ ምን ያህል ገንዘብ አለ? ስንት ሙያተኛ ሙሉ ጊዜውን ይሰጣል? ስንቱስ ተገቢ መረጃ ያቀርባል? ለእንከን የለሽ ዝግጅት ምን ምን ነገሮች መሟላት ይኖርበታል? የሚሉትን ጥያቄዎች አንስተን ተገቢ መልስ ስናገኝ ነው። በሌላም በኩል የሚጎድለውን ስንሞላ፣ የራቀውን ስናቀርብ እና ከእኛ የሚጠበቀውን ኃላፊነት ስንወጣ ነው። መሥራት አንድ አስቸጋሪ ነገር ነው። በተሠራ ሥራ ላይ መተቸት ደግሞ በጣም ቀላል ተግባር ነው። ይህም በመሆኑ በቀረቡት ዝግጅቶች ላይ ስሕተቶች እንደሚኖሩ እናምናለን። የማይሳሳት ሬሳ ወይም የማይሠራ እንደሆነ እናምናለንና! ትችቶቹን እና አስተያየቶቹንም በአግባቡ እንቀበላለን፤ እናርማለንም። ከዚያ አልፎ ግን የሚቀርቡትን ዝግጅቶች በጥቅሉ ማጠልሸት እና ውግዝ ከመ-አርዮስ ማለት ለዐማራው ድምፅ ከማሰብ ሳይሆን፣ የዐማራውን ድምፅ ለማፈን ከሚደረግ ሙከራ ተለይቶ አይታይም።
በመሠረቱ ዐማራው፣ ከውስጥ እና ከውጭ ከምድረ-ገፅ ሊያጠፉ የተነሱ ጠላቶቹን በተቀነባበረ ሁኔታ ለመታገል እና ኅልውናውን ለማስጠበቅ በማንነቱ ዙሪያ መደራጀቱ እና ድምፁን ለማሰማት መትጋቱ፣ ዐማራው፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በተቃራኒ በጠላትነት ቆሟል ማለት እንዳልሆነ ወዳጅም ጠላትም ሊረዳው ይገባል። ዐማራው ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲል፣ ሌሎች ነገዶችን እና ጎሣዎችን በጠላትነት ፈርጆ ሳይሆን፣ ከእርሱ በምንም መልኩ ሊነጠሉ የማይችሉ አካሎቹ መሆናቸውን አምኖ ነው። ይህም በመሆኑ፣ ዐማራው ለማንነቱ በሚያደርገው ትግል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ያስፈልገዋል፣ የእርሱም ድጋፍ ለሌሎቹ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታ ጭምር እንደሆነ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ያምናል።
በአሁኑ ጊዜ ዐማራው በማንነቱ ዙሪያ ለመደራጀት የተገደደው ኅልውናውን ለማጥፋት የተነሱበት ታሪካዊ ጠላቶቹ በፈጠሩበት አደጋ ምክንያት ተገዶ እንጂ፣ ወዶ ወይም ፈቅዶ አለመሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል ከመሆን አልፎ፣ በቁጥሩ ብዛት፣ በአገሪቱ አንድነት እና ነፃነት አጠባበቅ ሂደት ከተጫወተው ሚና በላይ ለኢትዮጵያዊነት ዳብሮ መቀጠል ብሎ በጽኑ እምነት የተነሳው ኢትዮጵያዊው ዐማራ ከምድረ-ገጽ እንዲጠፋ ሲፈረድበት፣ የሌሎች ነገዶች እና ጎሣዎች ተወላጆች በዝምታ የመመልከታቸው ሁኔታ፣ በራሱ ማንነት ዙሪያ እንዲደራጅ እንዳስገደደው መረዳት አይከብድም። በዓለም ታሪክ እንደሚታወቀው ኦቶማን ቱርኮች አርመኖችን እና ግሪኮችን፣ ናዚ ጀርመኖች አይሁዶችን፣ ሁቱዎች ቱትሲዎችን በጅምላ ለመጨረስ ተነስተው የብዙ ሕዝብ ሕይዎት ቢቀጥፉም በመጨረሻ ግን በታሪክ የሚያስጠይቃቸውን እጅግ አሣፋሪ ተግባር ፈፀሙ እንጂ፣ አሸናፊዎች አልሆኑም። የማታ ማታ ድሉ የተገፉት ሆነ። በዚህ በያዝነው እና በምንገኝበት ዘመንም ዐማራውን ለማጥፋት የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ብዙ ርቀት የተጓዘ ጥፋት ፈጽመውበታል። የማታ ማታ ግን ድሉም ሆነ አኩሪ ታሪኩ የዐማራው እንደሚሆን ጥርጥር የለንም። ስለዚህም ዐማራው ለኅልውናው በሚያደርገው ትግል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጎኑ ሊቆም ይገባል እንላለን፤ የዐማራው ኅልውና መጠበቅ ለመላ ኢትዮጵያውያን ህልውና መጠበቅ ዋስትና ነውና።
ይህ ሲባል ግን በተለይ የኢትዮጵያን እና የዐማራውን ጠላቶች ሤራ ለማክሸፍ፣ የዐማራ ተወላጆች እጃቸውን አጣጥፈው ይቀመጡ ማለት አይደለም። እንዲያውም ኅልውናችንን ለማስጠበቅ ከፍተኛው ኃላፊነት ያረፈው በእኛው በዐማሮች እጅ ነው። ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ለዐማራው ድምፅ እንዲሆን ያቋቋመው የሬድዮ ጣቢያ ዐማራው በማንነቱ ዙሪያ ተደራጅቶ ኅልውናውን በማስጠበቅ የኢትዮጵያ አንድነት ትንሣኤ አብሳሪ የሆነ ተግባር እንዲሠራ ከእያንዳንዱ የዐማራ ነገድ ተወላጅ እና ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል ዜጋ ገንቢ ትችት እና አስተያየት የዝግጅት ክፍሉ ይጠብቃል። ዛሬ የዐማራ ድምፅ ራዲዮ በሚያቀርበው ዝግጅት ያልተደሰቱ ግለሰቦች ፣ ዐማራው በሐረርጌ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሲዳሞ፣ በጋሞጎፋ፣ በከፋ፣ በኢሉባቦር፣ በወለጋ፣ በሸዋ፣ በወሎ፣ በጎንደር፣ በጎጃም እና በትግራይ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተለይቶ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ሲፈጸምበት ምን ዓይነት ድምፅ አሰምተው እንደነበረ የሚያውቁት ራሳቸው ብቻ ናቸው። ከአራት ዓመታት በፊት ዐማራው ከጉራፈርዳ በገፍ እና በግፍ ሲባረር ምንም አላሉም። በጋምቤላ፣ በአሶሳ እና በመተከል ዐማራው በዘሩ ተለይቶ ሲጨፈጨፍ ድምፃቸው የአሁኑን ያህል አስተጋብቶ ቢሆን ኖሮ፣ የዐማራው ጥፋት በእጅጉ ይቀንስ እንደነበር እናምናለን። ከዓመት በፊት በመተከል ዐማራው እንደከብት ታርዶ ሥጋው ሲበላ፣ ያንን ሃቅ ያልተቀበሉ እንደነበሩ ስናስታውስ የዐማራው ጠላቶች የቱን ያህል ሥር የሰደዱ እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል። ዛሬ እኒህ ዐይናቸውን በጨው የታጠቡ የዐማራው ጠላቶች የዐማራው ድምፅ እንዳይሰማ ዝግጅቱን በተለያዩ መንገዶች ለማጥላላት ሲጥሩ እያስተዋልን ነው። ይህን ድርጊት የዐማራው ልጅ በዝምታ ሊያልፈው የሚገባ አይሆንም። ማለፍም የለበትም። ይህ ሬድዮ ጣቢያ ሥራውን እንዲቀጥል ከተፈለገ በውጪ ያለነው የዐማራ ልጆች ተቀዳሚው ኃላፊነት አለብን። ይህንን ጉዳይ አገር ቤት ያላችሁ ወገኖቻችን በውጭ ላሉት ወገኖቻችን አስገንዝቡልን። ይህ ሬድዮ ጣቢያ ገና በእንጭጩ በዐማራው ጠላቶች የተቀነባበረ ሤራ ቢዘጋ፣ በታሪክ ይቅር ሊባል የማይችል ስህተት የሠራነው በስደት ያለነው የዐማራው ልጆች እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
[ዕርዳታ ለማድረግ እዚህ ላይ ይጫኑ]
[በየጊዜው የሚተላለፉትን የሬዲዮ ፕሮግራሞች ለመከታተል እዚህ ላይ ይጫኑ]
ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ፈለገ-አሥራት የትውልዳችን ቃል-ኪዳን ነው!
ዐማራው ኅልውናውንና መብቱን በትግሉ ያስከብራል!
አርብ ኅዳር ፱ ቀን ፪ሺህ፱ ዓ.ም. ቅፅ ፭ ፣ ቁጥር ፬
Leave a Reply