መግቢያ
እንደምናየውና እንደምንከታተለው የዓለም ሁኔታ እጅግ እየተወሳሰበ መጥቷል። በተለይም የጥቢው አብዮት በመባል ከሶስትና ከአራት ዐመታት በፊት በሰሜን አፍሪካ በአንዳንድ አገሮች የተካሂዱት እንቅስቃሴዎችና የለውጥ ፍላጎቶች የመጨረሻ መጨረሻ የተጠበቀውን ውጤት አላመጡም። ከዛሬ ሶስት ዐመት ጀምሮ የፕሬዚደንት አሳድን መንግስት ለመጣል የተካሄደውና የሚካሄደው እልክ አስጨራሽ ትግል ለብዙ መቶ ሺህ ሰዎች መገደል፣ መሰደድና መንገላታት፣ እንዲሁም ለጥንታዊ የታሪክ ቦታዎች መውደም ምክንያት ሆኗል። የፕሬዚደንት ሳዳም መንግስት ከተደመሰሰና ፕሬዚደንቱም ከተገደሉ በኋላ ኢራክ የሱኒቶችና የሺኢቶች መፋለሚያ በመሆን እስካሁን ድረስ ወደ ስድስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ሞቷል። ያን የመሰለ ጥንታዊ የታሪክ አገርና በዘይት ሀብት የተገነባ አገር አሁን ህዝቡ በድህነት የሚማቅቅበት፣ በበሽታ የሚሰቃይበትና ህይወቱ ብዠ ያለበት አገር ሆኗል። እነ ሊቢያ የመሳሰሉት ያልተሳኩ አገዛዞች (failed State) በመባል ወደ ርስ በርስ ጦርነት አምርተው ሀብት የሚወድምበትና የሰው ህይወት የሚጠፋበት አገር ሆነዋል። አምባገነኖችን ለማስወገድና የሊበራል ዲሞክራሲን ስርዓት ለማስፈን ተብሎ በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ለውስጥ የተቀሰቀሰው ሴራና ቀጥተኛ ድጋፍ እነዚህን አገሮች እንዲበታተኑ በማድረግና ህዝቦቻቸውም ጠንካራና አለኝታ የሚሆናቸውን መንግስት ለመመስረት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አሁን ደግሞ እንዲሁ በምዕራቡ የስለላ ድርጅትና በሳውዲ አረብያና በካታር ይደገፍ የነበረው አይሲ (ISI) የሚባለው የእስላም አክራሪ ድርጅት በመስፋፋትና የካሊፋትን መንግስት ለመመስረት ባለው ፍላጎት የሱን ዕምነት የማይከተሉትን ሁሉ እያረዳቸው ነው። ወደ ዩክሬይንም ስንሄድ ራሺያን አዳክሞና በታትኖ የአሜሪካንንና የምዕራቡን ዓለም የተቀጥያ መንግስታት ለማቋቋም የተደረገው ሴራ ዩክሬንን ለሁለት እየከፈላትና ህዝብ እየተላለቀባት ነው። በአወቅኹኝ ባይነትና በማን አለኝበት በሊበራል ዲሞክራሲ፣ በነፃ ገበያና በምርጫ ስም አሳቦ በምዕራቡ ዓለም የሚካሄደው ዐይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት የእስላቭን ወንድማማች ህዝቦች ርስ በርስ እያጨራረሰው ነው።
ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ ከአርባ ዐመታት በላይ ጀምሮ ለነፃነትና ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የተደረገውና የሚደረገው ትግል ወደ መረጋጋትና ወደ ስልጣኔ ያመራን ሳይሆን፣ የባሰውን ወደ መከፋፈልና በከፍተኛ ደረጃ ብሄራዊ ነፃነታችን የተደፈረበትና የተዋረድንበትን እጅግ አሳፍሪ ሁኔታ እንመለከታለን። የየካቲት አብዮት ሲፈነዳ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ባላባትዊና ንጉሳዊ አገዛዝ ሲወገድ ሁላችንንም የመሰለን ኢትዮጵያችን የስልጣኔ ብርሃን የሚፈናጠቅባትና የጠነከረችና ህዝቦቿም በኩራት የሚኖሩባት አገር መስሎን ነበር። በዕርግጥም ነበር። በማያዋለዳ አቋምና ዕምነት በግንባር ቀደምትነት በአብዮቱ ውስጥ የተሳተፉት መሪዎችና ካድሬዎቻቸው በዕምነት ያካሄዱት ትግል ህዝቦቿ ከድህነት ተላቀው ዲሞክራሲያዊ ህይወት እየኖሩ የበለጸገችና የጠነከረች አገር ለመገንባት ነበር። ስለሆነም በጊዜው ትግል ሲባል የሰፊውን ህዝብ መብት ሙሉ በሙሉ በማስከበርና በራሱ እንዲተማመን በማድረግ ዘላቂነት ያላት አገርና የማንም ባዕዳን ተገዢ ያልሆነች አገር ለመገንባት ነበር። ይሁንና ግን ሰፊው ህዝብና ታጋይ ልጆቹ ይህንን መብታቸውን የሚያረጋግጥላቸውን ድል ለጊዜውም ቢሆን ቢቀዳጁና የመንፈስም ኩራት ቢሰማቸው ከጥቂት ዐመታት በኋላ ያልጠበቁት ነገር በመከሰት ውድ አገራችን ወደ ጦር አውድማነት ተለወጠች። በአንድነት ተነስተን አገር መገንባትና የተከበረች አገር ጥሎ ከማለፍ ይልቅ ርስ በርስ በመናቆር ዛሬ ለምናያት ኢትዮጵያ የየበኩላችንን አስተዋፅዖ አደረግን። ድህነት ውስጥ ዘፍቀን የዓለም ህዝብ መሳቂያና መሳለቂያ ለመሆን በቃን። መሰደድና መንገላታት ሆነ እጣችን። አርቆ ባለማሰብ የተወሰዱ አላስፈላጊ እርምጃዎች ዕድሜያችንን በትግል ዓለም ውስጥ እንድንኖርና የትግልንም ትርጉም እንድናጣ አደረጉን። ትግል ሲባል ወደ አንድ ግብና ወደ መረጋጋትና ወደ ደስተኛነት የሚያመራ መሆኑ ቀርቶ ወደ ዘለዓለማዊ ሀዘንነት ተለወጠ።
ከ23 ዓመት ጀምሮ ደግሞ እጅግ በመረረ ስሜት አገራችንን የሚፋለማት ከትግሬ ብሄረሰብ የወጣ ጎጠኛ አገዛዝ ከእንግሊዝ፣ ከእሜሪካንና ከተቀረው የምዕራቡ ዓለም ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ለማውደም ከፈተኛ ፍልሚያ ውስጥ የገባ ይመስላል። በታሪክ ውስጥ በማይታወቅ ሁኔታ አንድ የመንግስትን ስልጣን የጨበጠ የአገር እሴትና የባህል ቅርስ እንዲበጣጠስ በማድረግ በዓለም ህዝብ ዘንድ እንድንዋረድ ሲያደርግን ምናልባት የኛው አገዛዝ ተብዬ በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል አበሽቃለሁ፣ ጊዜዬ መጥቷል በማለት ከራሱ ጋርም የተጣላና ለራሱ ልጆችና የልጅ ልጆች የማትሆን አገር ጥሎ ለመሄድ የተዘጋጀ ይመስላል። ታሪክንና ባህልን በማንቋሸሽና በመሳለቅ አገር የሚገነባ ስለመሰለው የአገራችን ህዝብ ርስ በራሱ አንዳይተማመንና ዘለዓለሙን እየተፈራራ እንዲኖር የተቻለውን ነገር አድርጓል፤እያደረገም ነው። ይህንን አደገኛና አገር አፍራሽ ተግባሩን የሚቃወሙትንና ለዲሞክራሲና ለነፃነት ብለው የሚታገሉትን በፀረ-ዕድገትና በአሸባሪነት በመፈረጅ እያሳደደ፣ እየገደለና እስር ቤት ውስጥ እየከተተ ነው። የዛሬው አገዛዝ ከአርባ ዓመት በፊት ወደ ጫካ ሲገባ ዲሞክራሲን እፈልጋለህ፣ ከጭቆና እወጣለሁ በማለት ነበር ትግሉን የጀመረው። እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች የትግልን አርማ በማንሳት፣ እንታገላለን እያሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችንና ምስኪን ህዝቦችን ግራ አጋብተው ዛሬ የምናያትና የምናዝንባት ኢትዮጵያ ውስጥ የከተቱት ትግል የሚባለውን አርማ በማንገብ ነበር። ይሁንና ግን በነፃነትና በዲሞክራሲ ስም ተሳቦ የተካሄዱት ትግሎች ሁሉ ወደ መረጋጋትና ወደ ብልጽግና አላመሩንም። የዚህ ሁሉ የትግል ውጤት መሰደድ፣ መታሰር፣ መገደልና ወደ ድህነት መገፍተር ሆኗል ። ከምርጫ 1997 እ.ኢ.አ መክሸፍ በኋላ ደግሞ ለዲሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገው ውስጥና ውጭ የሚካሄደው ትግል ከመጮህና አቅጣጫን ከመሳት ይልቅ ወደፊት ሲያራምድን አይታይም። አብዛኛው ግራ የገባው ህዝብ ይህንን ዐይነቱን መልክ የሌለ ትግል ካለመስማማት ጋር ነው ሲያያዘው የሚታየው። በሌላ አነጋገር በድርጅቶች መሀከል አለመስማማትና አለመተባበር ስላለ የወያኔ ዕድሜ ሊራዘምና የህዝባችንም ስቆቃ ሊባባስ ችሏል የሚል ተራ መደምደሚያ ተደርሷል።
ከዚህ ስነሳ ከረዝም ጊዜ ጀምሮ በጭንቅላቴ ውስጥ የሚብላላው ነገር ለመሆኑ ትግል ማለት ምን ማለት ነው? ትግልስ ሲባል ሳይንሳዊ መሰረት አለው ወይ? በፍልስፍናና በቲዎሪ ላይ የሚደገፍ ወይንስ ዝም ብሎ በፕሮግራም ዙሪያ እየተሰበሰቡና ሰላማዊ ሰልፍ እየጠሩ መጮህ ነው ወይ ትግል ማለት? የሚለውን እንዳውጠነጥን አስገድዶኛል። በተጨማሪም ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ሲባል የግዴታ ጫካ ውስጥ ገብቶ የጦር ትግል ማካሄድ፣ ወይም ደግሞ በከተማ ውስጥ ሽብር መፍጠር ያስፈልጋል ወይ? የሚለውን ጥያቄ እንዳነሳ ተገድጃለህ። ከዚህ ስነሳ ትግል የሚባለው ወደ አንዳች ነገር የሚያመራን እንቅስቃሴ ከሆነ ሳይንሳዊ፣ ፍልስፍናዊና የቲዎሪ መሰረት አለው ወይ? ወይስ ዝም ብሎ በስሜትና በጥላቻ ላይ ተመርኩዞ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ አንስቶ መወያያት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተለይም ስለ አገር፣ ስለሰው ልጅ ህይወትና ስለህብረተሰብ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ከፍልስፍናና ከሳይንስ ውጭ ልናመልጥና እንዲያው ትግል ትግል እያልን ግራ ተጋብተን ሌላውን ግራ ማጋባት አንችልም። ስለሰው ልጅና ስለህብረተሰብ በምናወራበት ጊዜ መለኪያችንና መመርመሪያችን ስሜታዊነት ሳይሆን ሳይንስና ፍልስፍና መሆን አለባቸው። ወደ አንዳች እርምጃና ውሳኔ ውስጥ ከመድረሳችንና ከመግባታችን በፊትም አንድን ሁኔታ በሰፊው በቲዎሪ መተንተን መቻል አለብን። እንደሚባለው ከቲዎሪ በፊት ተግባር ሊኖር ስለማይችልና ሰለማይሳካ ነው። ስለሆነም ትግል በሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ላይ ግልጽ አመለካከት እስከሌለን ድረስ ዘላለማችንን እየተደነባበርን መቅረታችን የማይቀር ነው። ስልጣኔን ከመቀዳጅትና ህዝባችን ደስተኝነትን እንዲጎናፀፍ ከማድረግ ይልቅ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ማድረጋችን የማይቀር ታሪካዊ ግዴታ ይሆናል።
ትግል ሲባል ስሜታዊነትን ወይስ አርቆ-አሳቢነትን ያሰቀደመ !
የሰው ልጅ ዕውቀትን ከመቀዳጀቱ ወይም በዕውቀት ከመመራቱ በፊት ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያደርጋቸው ትግሎች በአርቆ-አሳቤነት ወይም በሳይንስ ላይ በመመርኮዝና በመመራት ሳይሆን በደመ-ነፍስና በግብታዊነት እንዲሁም በስሜታዊነት ብቻ በመመራት ነበር። ይህ ዐይነቱ አርቆ-አሳቢነት የጎደለው የትግል ኑሮ ከዚህ ጋር ቀስ በቀስ እያደገ የመጣው የአገዛዝ አወቃቀርና ሀብትን በጥቂት ስዎች ቁጥጥር ስር ማድረግ ላለመረጋጋት፣ ለርስ በርስ ጦርነትና ለሀብት መውደም ምክንያት በመሆን በብዙ አገሮች የስልጣኔ ፍንጭ እንዳይንፀባረቅ ሆኗል። የጀርመኑ የሊትሬቸር ምሁር ፍሪድርሽ ሺለር እንደሚያሰተምረን የሰው ልጅ ህብረተሰብአዊነትና ማህበራዊ ባህርይን ለመቀዳጀትና ወደ ስልጣኔ ለማምራት ብዙ ውጣ ወረዶች መጓዝ እንዳለበት ነው። እራሱን አግኝቶና ማንነቱን አውቆ ታሪክ ለመስራት የብዙ ዐመታት የጭንቅላት ትግል ማድረግ አለበት ይለናል። ይህንን የተረዱት የተፈጥሮ ፈላስፋዎችና በኋላ ብቅ ያሉት የግሪክ ተመራማሪዎች ምርምራቸውን የጀመሩት የሰውን ልጅ ባህርይና የውጣ ወረድ ትግልና የርስ በርስ ጦርነት፣ እንዲሁም የጥቂቶችን በሀብት መባለግ በሰፊው ካጠኑና ከተመራመሩ በኋላ የደረሱበት ድምደማ የሰው ልጅ ድርጊት በቀጥታ ከጭንቅላት ወይም ከአአምሮ ጋር የተያያዘ ስለሆነ አስተሳሰቡ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በሚኖረው ልማዳዊ ኑሮና ውስን ዕውቀት ተፅዕኖ ስለሚደረግበት እሱን ጠጋ ብሎ መመርመሩ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘቡ። በመሆኑም የአንድ ሰው ወይም የፖለቲካ ኤሊት አርቆ-አሳቢነትና አላስቢነት ሊወሰን የሚችለው በትክክለኛ ዕውቀት የተቀረጸ ወይም ደግሞ በአሳሳች ዕውቀት በሚመስል ነገር የተመረዘ እንደሆን ነው። በእነሱ ዕምነት የሰው ልጅ ችግር ትክክለኛውን ዕውቀት ለማግኝት አለመቻል፣ የማሰብ ኃይልን ያለመጠቀምና እንዲሁም ራሱን በየጊዜው ለመመርመርና ለመጠየቅ ያለመቻል ችግር ነው የሚል ከረዢም ጊዜ ምርምር በኋላ የተደረሰበት ድምዳሜ ነው። ስለዚህም ዋና ምርምራቸው የሰውን ልጅ ጭንቅላትና ከዚያ በመነሳት የሚወስደውን ርምጃ ወይም የሚፈጽመውን ድርጊት መመርመር ነበር ዋና ዓላማቸው።
ስለሆነም የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ካለው፣ ዕውቀትን የሚያፈልቅ ከሆነ፣ የተወሳሰቡ ነገሮችን ለማጤን የሚያስችለው ጭንቅላት ካለው፣ ኮመን-ሴንስና አርቆ-አሳቤነት ባህርይ እንዲሁም ደመ-ነፍስ በጭንቅላት ውስጥ እዚያው በዚያው ያሉና የስራ ክፍፍልም ኑሮአቸው የሰውን ልጅ አሰተሳሰቡንና ድርጊቱን ለመቆጣጠር የሚችሉ ከሆነ ለምንድነው ይህንን በመጠቀም የስልጣኔ ባለቤት በመሆን የተረጋጋና ደስተኛ ኑሮ ለመኖር የማይችለው? ብለው በመጠየቅ ነበር ራሳቸውን ያስጨንቁ የነበረው። ይህንን ጉዳይ በሰፊው ከመረመሩ በኋላ የደረሱበት ዕውቀትና ዕምነት የሰው ልጅ አርቆ እንዳያይና በጭንቅላቱ ውስጥ ያሉ የማሰብ መሳሪያዎችን ሁሉ እንዳይጠቀምና በቁም ነገር ላይ ብቻ እንዳያተኩር የሚጋርዱት ነገሮች መኖር አለባቸው በማለት ነው። ስለሆነም ጭንቅላት በሚገባ ማየትና ለማገናዘብ የማይችል ከሆነ ይህ ጉዳይ የግዴታ ህብረተሰብ ውስጥ እንደልማድ ከሚወሰዱ የአሰራርና የተበላሹ የአኗኗር ስልቶች ጋር ሊያያዝ ሲችል፣ በተጨማሪም አሳሳች ትምህርት የአንድን ሰው ጭንቅላት የማሰብ ኃይሉን ሊያበላሽበትና ድርጊቱንም በየጊዜው እንዳይመረምር ያግደዋል የሚል ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ አንድ ሰው አንድን ነገር ሁለንታዊ በሆነ መንገድ ከመረዳትና ትንታኔ ከመስጠት ይልቅ በተወሰኑ ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር የራሱን ግምት ሊሰጥ ይችላል። ለአንድ ነገር መነሾ በሚሆነው ዋናው ምክንያትና በውጤቱ መሀከል ሊኖር የሚችለውን ትስስርና የቅደም ተከተል በደንብ እንዳይገነዘብ ይገደዳል። ከዚህም በመነሳት ጭንቅላት በደንበ መገንዘብ የማይችል ከሆነ በአንድ አገር ውስጥ የሚሰሩ ወንጀሎችና የሚፈጠረው ድህነትና ከገዢዎችም ጥጋብ የተነሳ የተወሳሰበ መሳሪያ እየሰሩና ህዝብን ለጦርነት ሲማግዱ ይህ ሁኔታ እንደ ተራና ግዴታ ሆኖ ሊወስድ እንደሚችልና፣ የተወሰነ ህብረተሰብ ክፍልም እንዳላየ ዐይቶ የሚያልፍበት ሁኔታ ወይም አንድን ዘግናኝ ድርጊት ትክክለኛ መሆኑን ለማሳመን የሚጥርበት ሁነታ እንዳለ በዲያሊከቲክ መነፅርና በአርቆ-አሳቢነት የሳይንስ ምርምር ዘዴ መረዳት እንደሚቻልና ትክክለኛ የግንዛቤና የምርምር ዘዴ ለመጣል ቻሉ። በመሆኑም የተፈጥሮን ምንነት ከመረዳትና በውስጥ የሚገኙትን ንጥረ-ነገሮች ከመመርመርና የሰውን ልጅ ባህርይ ለመረዳት በጭንቅላት ላይ ከማትኮር ውጭ የዕውቀት ምንጭ ሌላ ነገር ሊሆን እንደማይችል ማሳየትና በተግባርም ማስመስከር የተቻለበት ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ በግሪክ ፈላስፎች ተረጋገጠ።
ከዚህ በመነሳት የተፈጥሮንና የህዋን ህግ ማጥናት ጀመሩ። በተለይም አትኩሮአቸው የኮስሞስን ህግ ማጥናት ሲሆን፣ በኮስሞስ ውስጥ የሚገኙ ፕላኔቶና ኮከቦች እንዲያው በዘፈቀደ የሚንቀሳቀሱ ሳይሆን በተወሰነ ርቀት ስርዓትን ተከትለው እንደሚጓዙ ለማወቅ ቻሉ። በዚህ መሰረት የሰውም ልጅ የኑሮ ሁኔታ፣ ድርጊቱና ከተፈጥሮ ጋር የሚኖረው ግኑኝነት ዝም ብሎ በደፈናው የሚካሄድ ሳይሆን የግዴታ የኮስሞስን ህግ ወይም ሳይንስን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት። በዚህም መሰረት የፍልስፍና ዋና ጥያቄ ጥበብን መቅሰም ሲሆን፣ በዚህ አማካይነት የሰው ልጅ የራሱን ምንነትና፣ ድርጊቱንና ጉዞውን እንዲመረምር ከራሱ ጋር መታገል እንዳለበት፣ እንዲያው በዘፈቀደ ዝም ብሎ የሚጓዝ ሳይሆን ነገሮችን በመመለክት፣ በማጥናት፣ አመጣጣቸውን በመረዳት፣ ጥቅማቸውን መገንዘብና ከዚህ በመነሳት ትንትና በመሰጠት ለራስ መጠቀሚያ የሆኑ ነገሮች መስራት ዋናው የትግል ዕምብርት መሆን ጀመረ። ስለሆነም አንድ ሰው ወይም አንድ ህብረተሰብ ትግል ሲያደርግ፣ ትግል የሚባለው አካላዊ እንቅስቃሴ ከጭንቅላት ማሰብ፣ ማውጠንጠንና ከዚያም በመነሳት የቲዎሪ መሰረት በመስጠት አንድን ነገር ለመስራት መመሪያ ማውጣት ዋናው የፍልስፍና፣ የቲዎሪና የሳይንስ መሰረቶች ሆኑ። ይህም ማለት ትግል ሲባል ዝም ብሎ በአቦ ሰጡኝ፣ ወይም ደግሞ ይኸኛው መንገድ ብቻ ነው የሚያዋጣው፣ እኔ በዚህ ብቻ ነው የማምነው፣ አቋሜ ይህ ነው ብሎ በጭፍን ወይም በስሜትና በደፈናው በደመ-ነፍስ የሚካሄድ እንቅስቃሴ ሳይሆን፣ የሚደረገው ትግልና ሊደረስበት የሚታለመው ዓላማ በሰፊው በቲዎሪ፣ በሳይንስና በፍልስፍና መነጽር መገምገም አለበት ማለት ነው።
የግሪክ ፈላስፎች ፍልስፍናንና ከዚህ የሚፈልቀውን አርቆ-አሳቢነትን የትግል መመሪያቸው ሲያደርጉ የመጨረሻ መጨረሻ ሰብአዊነትን (Humanism) ለመጎናጸፍና በምድር ላይ ገነትን ለመመስረት ነበር ዋናው ዓለማቸው። በእነሱ ዕምነት በታሪክ ውስጥ አልፎ አልፎ ስልጣኔዎች ቢታዩም በአማዛኙ ግን የሰው ልጅ ኑሮ ከእንስሳ እንዳማይሻልና ዘለዓለሙን ርስ በርስ በመተራረድ መኖር የኑሮው ፍልስፍናው እንደሆነ በመገንዘብ ነበር። ለእንደዚህ ዐይነቱ እንስሳዊና የተዝረከረክ፣ እንዲሁም በጦርነት ዓለም ውስጥ መኖር በየታሪክ ወቅት የነበሩ ኦሊጋርኪዎች ተጠያቂ ሲሆኑ፣ አገዛዛቸውም የራሳቸውን ኑሮ በማደላደል አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ ገባር በማድረግና በጦርነት ውስጥ እንዲዘፍቅ በማድረግ በምድር ላይ ደስተኛ ኑሮን እንዳይመሰርት ማድረግ ነበር። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱን ኦሊጋርኪያዊ አገዛዝና በዘለዓለማዊ ጦርነት ውስጥ መዝፈቅ ከትክክለኛ ዕውቀት ማነስና ጭንቅላትም ሙሉ በሙሉ ኋላ-ቀር ከሆነ አስተሳሰብ ጋር አለመላቀቁ እንደሆነ መገንዝቡ ከባድ አልነበረም። ስለሆነም ዲያሌክቲክን ዋናው የጭንቅላት መመርመሪያና የትግል መሳሪያ በማድረግ እኩልነትን፣ ጥበባዊነትንና ስምምነትን ማስተማር ዋናው ዓላማቸው አደርጉ። ከዚህ ቀደም የግብጽ ቀሳውስት ዕውቀትን ለራሳቸው ብቻ በማድረግ ውጭ እንዳይወጣ አፍነው የያዙትን ፍልስፍና የግሪክ ፈላስፎች ወደ ውጭ በማውጣትና በማስተማር የክርክርና ሰፋ ያለ የዕውቀት መድረክ በመክፈት በጊዜው የነበረውን ኢሊጋርኪያዊ አስተዳደር በመጋፈጥ ብዙ ተከታዮችን በማፍራት ለግሪክ ስልጣኔ ልዩ ዕምርታ ሰጡት። ብዙ ደቀ-መዝሙሮችን በማፍራት በአጭር ጊዜ ውስጥ የስልጣኔን ጮራ በማንፀባርቅ ከአካባቢያቸው በማለፍ በቲዎሪ ብቻ ሳይሆን ወደ ተግባርም በመመንዘር አዲስ አስተሳሰብና የፈጠራ ስራ እንዲዳብርና እንዲስፋፋ አደረጉ። ውብ ውብ ህንጻዎችና ከተማዎች በመገንባት ቀደም ብሎ ተዝረክርኮ ይኖር የነበረውን ህዝብ ኑሮውን እንዲያሻሽልና በአስተሳሰቡም እንዲሾልና የራሱ ዕድል ባለቤት እንዲሆን ከፍተኛ አሰተዋፅኦ ለማድረግ በቁ። ይሁንና ግን ይህንን የሚቃወሙና በጊዜው የነበራቸውን ቦታ የሚያጡ የመሰላቸው ሶፊስቶች የሚባሉ ምሁራን የተለየ አቋም በመያዝ ወጣቱን ማሳሳት ቻሉ። በሶፊስቶችም ዕምነት ዕውቀት ከጭንቅላት ውስጥ የሚፈልቅ ሳይሆን ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገባና፣ ህግም ስልጣንን በጨበጡ ጥቂት ሰዎች የሚስጥ ስለሆነ በጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይችልም፤ ስለሆነም ከላይ የሚመጣ ህግንና ትዕዛዝን ዝም ብሎ መቀበል ያስፈልጋል በማለት ህዝቡ የኦሊጋርኪዎችን አገዛዝ ዝም ብሎ እንዲቀበል መስበክ ጀመሩ። በመሆኑም በሶክራተስና በፕላቶ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሶፊስቶች መሀከል ዕውቀትንና አስተዳደርን በሚመለከት የጦፈ ክርክር ይካሄድ ነበር።
የእነ ፕላቶንን ፍልስፍና አጥብቀው የሚጠሉት ሶፊስቶች በሶክራተስ ላይ የማይሆን ወሬ በማሰወራትና እንዲሁም በሀስት በመክሰሰ የመጨረሻ መጨርሻ በሞት ፍርድ እንዲገደል አደረጉ። ሶክራተስ የእግዚአብሄርን መኖርንና ምንነት የሚክድ በመሆኑ ወጣቱን ያሳስታል በማለት ይወነጅሉት ነበር። በአንፃሩ ደግሞ ሶክራተስና ፕላቶ ሶፊስቶችን ይከሷቸው የነበረው ወጣቶችን አሳሳች ትምህርት በመስጠት አንድ አገዛዝና ወጣት ትውልድ ወደ ብልግና እንዲያመራ በማድረግ በጦርነት ዓለም ውስጥ ዘፍቆ እንዲኖር ማድረግ ነው ብለው ይታገሏቸው የነበረው ። በመሆኑም በሶክረተስና ሶክራተስን ተመስሎ አያሌ የዲያሊከቲክንና የፍልስፍናን መጽሀፎች የጻፈው በፕላቶ መሀከል ይደረግ የነበረው ትግል ከዚህ አሳሳች አስተሳሰብ ለመውጣትና የተፈጥሮን ምንነት በመገንዘብ በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ለሰው ልጅ መጠቀሚያ መሳሪያ ለማድረግ የሚያስችሉ ዕውቀቶችን እንደ ማቲማቲክስና ሌሎች የተፈጥሮ ሳይንስን መመርመሪያ መሳሪያ መጣል ነበር። ከዚህም በመነሳት የሰው ልጅ ነፃነት ዝም ብሎ በአዋጅ ከላይ ወደ ታች የሚሰጥ ሳይሆን እያንዳንዱ ግለሰብ በማሰብ ኃይሉ ተመራምሮ ወደ ተግባር የሚመነዝረውና በህበረተሰብ ውስጥም ሚዛናዊነት ያለው አስተዳደር ሲዘረጋና ዕኩልነት ሲሰፍን ብቻ እንደሆነ በግልጽ ይቀርብ ነበር። ሆኖም ግን የሰው ልጅ ለስልጣኔና ለዕድገት የሚሆነውን ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መመሪያ የተጀመረው በአራተኛው ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ሲሆን፣ በተለይም በትልቁ አሌክሳንደር አማካይነት ዕውቀት ከፈተኛ ቦታ ተሰጥቶት መጻህፍት ቤት በአሊክሳንደርያ በማቋቋም ምርምርና መሳሪዎችንም መስራት የተጀመረውና ለወደፊቱ የሰው ልጅ ስልጣኔ የሚደረገው ትግል የተጣለው በዚህች ከተማ እንደሆነ ታሪክ ያረጋግጣል። የምዕራብ አውሮፓውም የስልጣኔ መሰረት በግሪክና በዚህች በአሊካስንድርያ በተዘጋጁት ሳይንሳዊ ግኝቶች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይታወቃል።
በመሆኑም በጭንቅላት ላይ ያተኮረው የግሪኩ ስልጣኔ ሁለንታዊ ባህርይ ሲኖረው፣ የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የሚያገናኘው ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮንና የህዋን ህግ በማጥናት የስልጣኔ ባለቤት በማድረግ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዲቀዳጅ የሚያደረግ ነው። ጦርነትና የጦርነት አፍላቂ የሆነውን ኦሊጋርኪያዊ ስርዓት አጥብቆ የሚጠላና የሰው ልጅም ተግባር ወደ ጦርነት መቀነስ እንደሌለበት የሚያሰተምርና መመሪያም ነበር። እንደዛሬው ዐይነቱ በነፃ ገበያና በሊበራል ዲሞክራሲ ላይ ብቻ ያተኮረ ተራ ግለሰበአዊነትን የሚያጎናጽፍ ሳይሆን፣ ማንኛውም ግለሰብ በአርቆ-አስተዋይነት፣ በሞራልና እንዲሁም በስነ-ምግባር በመመራት በስምምነትም እንዲኖር የሚያደርግ ነው። በተራ ግለሰብአዊ ነፃነት ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ሁለንታዊና እያንዳንዱ ግለሰብ ማንነቱን ተረድቶና ራሱን በማወቅና ከአውሬነት ባህርይው በመላቀቅ የሰለጠነ ስርዓት እንዲገነባ የሚያደርግ መመሪያ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሄር አምሳያ የተፈጠረ ሲሆን ድርጊቱ ሁሉ ወደ እግዚአብሄር የሚጠጋና በምድርም ላይ ውብ ውብ ስራዎችን መስራት እንዳለበት የሚያስተምር ነው። እንደዚያ ዐይነቱ የትግል መመሪያ ከዕውነተኛው ግለሰብአዊ ነፃነትና ከህብረተሰብአዊ ድርጊት ጋር የሚጣጣምና ይህንን የሚያግዝ ጥበባዊና ጦረኛ ያልሆነ መንግስት መመስርቱ ዋናው የፍልፍናው መሰረት ነበር። ስለሆነም በግሪክ ስልጣኔ ጊዜ ይደረግ የነበረው ዋና ትግል ጭንቅላትን ማረቅ፣ አርቆ-አስተዋይ እንዲሆን፣ የሰብአዊነት ባህርይ በመላበስ የጥበብና የስልጣኔ ባለቤት ማድረግ ብቻ ሳይሆን መንግስት የሚባለውም ነገር በፍልስፍናና በዕውቀት ላይ የተመሰረተና ለአንድ ወገን የሚያደላ ሳይሆን ህብረተሰብአዊ ሚዛን የሚያመጣ መሆን እንዳለበት ነው። በዚህም ምክንያት የሰው ልጅ ሰብአዊነትንና አርቆ-አስተዋይነትን ሙሉ በሙሉ ከጭንቅላቱ ጋር ለማዋሃድ ከፈለገ በየቀኑ ለሰውነቱ ለመንቀሳቀስና ለመስራት ጅምናስቲክ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ጭንቅላቱም እንደዚህ በየቀኑ መታደስ አለበት። የበለጠ መንፈሳዊነትን ለመጎናጸፍ ራሱንና ተግባሩን መመርመር አለበት። ይህንን ሲያደርግ ብቻ ስራው ሁሉ ሚዛናዊነት ያለውና ሌላውን የማይጎዳ ይሆናል። ሞራልንና ስነምግባርን መመሪያው በማድረግ የበለጠ ወደ ስምምነት በማምራት በህብረተሰብ ውስጥ መረጋጋት እንዲፈጠርና የአንድ ህዝብ ስራም ታሪካዊ እንዲሆን ያደርጋል።
ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የረቀቀና የስልጣኔ መሰረት የሆነው የግሪኩ ፍልስፍንናና ተግባራዊም የሆነው በሮማውያን ጦርና መስፋፋት ሲደመሰስ፣ የሮማውያን አገዛዝ ከወደቀ በኋላ የአውሮፓ ህዝብ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖርና የፊዩዳሉ ስርዓት እንዲነግስ መንገዱን ከፈተ። በአውሮፓ ውስጥ የፊዩዳሉ ስርዓት እንደ ስርዓት መፈጠር ማርክስ እንደሚለው የተፈጥሮ ወይም የህብረተሰብ ህግ ሳይሆን፣ በግሪክና በአሊክሳንደርያ የተጣለው ስልጣኔና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲስፋፋ የታቀደው በሮማውያን ጦር ከተቃጠለና የስልጣኔ መሰረቱ ከተደመሰሰ በኋላ እንደሆነ አሁን በቅርብ በምርምር የወጡ ጥናቶችና ዶኩሜንታር ፊልሞች ያረጋግጣሉ። ስለሆነም የአውሮፓው ህዝብ ከ 600 ምዕተኛው ዐመት ከክርስቶ ልደት በኋላ እስከ አስራ አራተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ከሳይንስና ከጥበብ ዓለም በመገለል ለሰምንት መቶ ዐመታት ያህል በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ለመገደድ በቅቷል። እጣውም ረሃብ፣ በተስቦ በሽታ ማለቅና መኳተን ነበር። ትግሉም በዚህ ዐይነቱ የጨለማ ኑሮ የተከለለ ስለነበር ታሪክን ሊሰራ የሚችል አልነበረም። የግሪክ ስልጣኔ ከመጀመሩ በፊት የነበረው ሁኔታ በመንገስ የአንድ አገር ህዝብ በጥቂት ኦሊጋሪኮዎችና ቄሶች በመሰቃየት አንድ ዐይነት ቋንቋ መናገር የማይችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ሆነ።
በአጠቃላይ በግሪክ ምድር ውስጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከአምስተኛው መቶ ዓመት ጀምሮ ትግል ሲደረግ ቀደም ብሎ በተለያየ ደሴቶች ውስጥ በሚኖሩ ጎሳዎች ዘንድ ይነሳ የነበረውን ጦርነትና መተራረድ በመመርመር፣ ይህ ዐይነቱ የአኗኗር ስልት ከአርቆ-አስተዋይነት ማነስና የሰው ልጅ ጭንቅላትም በዕውነትኛ ዕውቀት መታነፅ ባለመቻሉ እንደነበር በመረዳት ሰብአዊነትና እኩልነት፣ እንዲሁም ህዝቡን የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እስካልሰፈነ ድረስ ሁኔታው በዚያው እንደሚቀጥል ከፍተኛ ግንዛቤ ነበር። ስለሆነም እስከ አምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የነበሩ ጨቋኛና ህዝቡን በዕዳ ተብተብው ወደ ባርነት ስርዓት ውስጥ የጣሉት ሁኔታዎች በአቴኑ መሪ ሶሎን በሚባለው ተደምስሰው ተራው ህዝብ ነፃነቱን ሊቀዳጅ ቻለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፍልስፍናና ጥበባዊ ስራዓቶች እንዱህም ማቲማቲክስ ማበብ ቻሉ። የሰብአዊነት በሩ በመከፈት የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለይበት ሁኔታ ተረጋገጠ። ህዝቡም ወደ ውጭ ወጦ በተዘጋጀለት መድረክ ላይ ፖለቲካዊ ክርክር የሚያደርግበትና፣ የገዢዎችንም ብልግና በትራጄዲ መልክ የሚያይብት ሁኔታ በመፈጠሩ ሰው መሆኑን በመገንዝብ አንደኛው ግለሰብ ከሌላው ሊበልጥ እንደማይችልና፣ እያንዳንዱ ግለሰብም በህብረተሰብ ውስጥ እንደችሎታው ቦታ እንዳለው መረዳት ተቻለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ድራማ ልዩ ቦታ ተሰጥቶት ህዝብንና የገዢ መደቦችን የሚያስተምር ሆነ። ጭንቅላትን የሚከፍትና የሰው ልጅም መሳቅ፣ መቀለድ፣ ማዘን፣ ማውጣትና ማውረድ፣ እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ባህርዮች እንዳሉት በድራማ መልክ ይገለጽ ነበር። የድራማውም ዋና መልዕክት የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል ለማጎልመስና ጥበባዊ ስራ መስራት እንዲያስቸለው ነው። ከተንኮል፣ ከጦርነትና ከስግብግብነት ተላቆ ታሪካዊ ስራዎችን በመስራት በመፈቃቀር እንዲኖር ነው። የሰው ልጅ ክፉና ደግ ባህርዮች ቢኖሩትም ማንኛውም ሰው መጣር ያለበት ጥሩ ጎኑን በማጎልበስ ለጥበባዊ ስራ እንዲዘጋጅ ለማድረግ ነው። ትችታዊ አመለካከትን በማዳበርና የትችትን ምንነት በመረዳት ከቂም-በቀል ነፃ እንዲሆን የሚያደርግና በአንድ ህበረተሰብ ውስጥ ቦታውን እንዲረዳና ራሱንም መግለጽ እንዲችል የሚያደርግ ነው። ይህም ማለት በግሪክ ፈላስፋዎችና በኋላም በተነሱት ተመራማሪዎች ዕምነት መሰረት ትግል ሲባል በስሜት በመወጠር ወደ ቂም-በቀልና በእልከኝነት ስሜት ወደ ጦርነት በማምራት አንድን ህበረተሰብ ትርምስ ውስጥ መክተትና ኑሮውን አበላሽቶ ህይወቱ እንዲጨልምበትና ሀዘንተኛ እንዲሆን ማድረግ ሳይሆን፣ በምርምር ዓለም ውስጥ በመዋኘት ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር በማድረግና በምድር ላይ ገነትን መመስረት ነው። ባጭሩ ትግል ሲባል በሃሳብና በዕውቀት ዙሪያ የሚካሄድ ሲሆን፣ ሀቁን ለመፈልግና የስልጣኔ ባለቤት ለመሆን ነው። ዕውነትን ከውሸት ለይቶ በማወቅና ለታዳጊውም ትውልድ በማስተማር በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ኦሊጋሪኪያዊና የፀረ-ስልጣኔና ፀረ-ሳይንስ አገዛዝ እንዳይሰፍን ለማደርግ ነው።
የተሃድሶ እንቅስቃሴና የተፈጥሮ ሳይንስ ግኝት የትግል መመሪያዎች መሆን!
የሮማውያን አገዛዝ የግሪኩንና የግብጹን ስልጣኔ ከደመሰሰ በኋላ ወደ ኢምፓየርትነት በመለወጥ በብዙ የምዕራብና የደቡብ አውሮፓ አገሮች የጨለማ ስርዓትና በኋላም የፊዩዳሉ ስርዓት እንዲያቆጠቁጥና እንዲስፋፋ በሩን ይከፍታል። ይህ ዐይነቱ አስከፊ ስርዓት ለስምንት መቶ ዐመት ያህል የአውሮፓን ህዝብ አስተሳሰብ ቆልፍ በመያዝ የተፈጥሮ ተገዚ በማድረግ ኑሮው በጦርነትና በበሽታ እንዲሁም በረሀብ እንዲወሰን ለማድረግ ይበቃል። ይህ ዐይነቱ የጨለማና የጦርነት ምንጭ ስርዓት ቀስ በቀስ በከተማዎች መገንባት፣ በዕደ-ጥበብ ማበብ፣ በንግድ መስፋፋትና ከዚያም በኋላ በዚህ አማካይነት ብቅ ብቅ ባሉ ከግሪኩ የጥንት ስልጣኔ ጋር በተዋወቁ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ጥያቄ ውስጥ ይገባል። የቀሳውስቶችንና የመሳፍንታትን አጉልና ኋላ-ቀር ዕምነት በሳይንስና በፍልስፍና መነፅር በመመርመር መጋፈጥ ዋናው የትግል ዘዴ ሆነ። በመጀመሪያ ደረጃ እስከ 14ኛው ክፍል-ዘመን ድረስ መሬት የፕላኔቶችና ፀሀይንም ጨምሮ ማዕከላዊና የማትንቀሳቀስ ነች የሚለውን ኢ-ሳይንሳዊ ዕምነትና አመለካከት መዋጋት ተቀዳሚው ተግባር ነበር። ኮፐርኒኩስና ጋሊሌዮ መሬት ሳትሆን ፀሀይ ነች የፕላኔቶች ሁሉ ማዕከል የሚለውን በማረጋገጥ የካቶሊክን ዕምነትና ሰበካ ፉርሽ በማድረግ ለሳይንስ ግኝት በር መክፈት ቻሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለይም ጋሊሌዮ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ሰፍኖ የነበረውን በአርስቲቶለስ ላይ የሚመሰረተውን ዕውቀት በመጣል ለመካኒክስና በኋላ ለኢንዱስትሪ አብዮት የሚሆን ዕውቀትና መሰረት አፈለቀ። በህዋ ላይ ያሉትን የፕላኔቶችን ምንነትና ባህርያቸውን ለመረዳት በሰራው የሩቅና የአጉልቶ ማሳያ መነፅር በመመልከት ፕላኔቶች የሚንቀሳቀሱና የሚታዩ፣ እንዲሁም ለመጨበጥ የሚችሉ ወይም ማተርስ እንደሆኑ ለማረጋገጥ ቻለ። በመሆኑም በህዋ ውስጥ የሚገኙ ፕላኔቶች ሁሉ ከላይ የተገለጸው ባህርይ ብቻ ሳይሆን ያላቸው ግፊትና ኃይልም እንደሚደረግባቸውና፣ በዚህ አማካይነት ለመንቀሳቀ እንደሚችሉ አረጋገጠ። ይህም ማለት እንቅስቃሴና (Motion) ኃይል (Force) መሰረታዊ የመካኒክስ ህጎች እንደሆኑና በዚህም መሰረት የሰውን ልጅ ስራ የሚያቃልሉ መሳሪያዎች በመፍጠር ቀላልና የተወሳሰቡ መሳሪያዎችን ሊያሰራ የሚችለውን የፊዚክስን ዕውቀት ማዳበር ተቻለ። ጋሊሌዮ በዚህ ብቻ ሳይወሰን የአርስቲቶለሰን የተለያየ ክብደት ያላቸውን ክብ ነገሮች ከላይ ሆነው በአንድ ጊዜ በሚወረወሩበት ጊዜ በተለያየ ፍጥነት መሬት ላይ ይወድቃሉ የሚለውን በኮመን ሴንስ ላይ የተመረኮዘውን አስተሳሰብ በሙከራ ፒያዛ ላይ ሆኖ በመወርወር ትክክል አለመሆኑን አረጋጋጠ።
በሌላ አነጋገር የተለያየ ክብደት ያላቸው ሁለት ነገሮች ከላይ ሆነው ቢወረወሩ አርስቲቶለስ እንደገመተው ሳይሆን በተለያየ ፍጥነት ሊወርዱ የሚችሉት፣ ሁለቱም ከአንድ ከፍተኛ ቦታ ላይ ሲወረወሩ በተመሳሳይ ፍጥነት ይወርዳሉ በማለት ቀላሉ ነገር ከታች በአየር ግፊት ምክንያት በዝግታ እንደማይወርድ አረጋገጠ። ስለሆነም እስከዚያ ድረስ ይታመንበት የነበረውንና በካቶሊክ የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን የየቀሳቅውቶችን አመለካከት በመጋፈጥ ለሳይንና ለቴክኖሎጅ ግኝት የሆነውን መሰረት በማፍለቅ የሰው ልጅ ከትራዲሽናል አስተሳሰብ በመላቀቅ በማያቋርጥ ጥረት የህዋንና የተፈጥሮን ምንነት መረዳት እንዳለበት አመለከተ። ይህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ ምርምርና ግኝት በተመረጡ ኤሊቶችና ቀሳውስት ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን ማንኛውም ተራ ሰው ሊረዳው ይችላል በማለት ፖለቲካዊ ትርጉም መስጠት ቻለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጭፍን ዕምነት ሳይሆን ሳይንስና ፍልስፍና ተፈጥሮንና ህዋን መመርመሪያ መሳሪያዎች እንዲሆኑ በማድረግ የሰው ልጅ ከጭፍን ዕምነት እንዲላቀቅና የራሱን ኑሮ ስርዓት ባለው መልክ እንዲያዘጋጅ በሩ ተከፈተለት። በዚህ ዐይነቱ አዲስ የምርምር ዘዴና ሳይንስ የተደናገጡ የካቶሊክ ቀሳውስት፣ ፈላስፋዎችንና ሳይንቲስቶችን በማስፈራራት፣ በማሰርና በይፋ በመግደል የሳይንስን ፈለግና ግኝት ለማቆም ትንንቅ ያዙ። ይሁንና የተሃድሶ እንቅስቃሴ እየተስፋፋ በመምጣቱና ብዙ ምሁራንንም ማቀፍ በመቻሉ የካቶሊክ ሃይማኖት ይህንን እያደገና እየተስፋፋ የመጣ ሳይንሳዊ ምርምርና የተሃድሶ እንቅስቃሴ ሊገታው አልቻለም።
የጋሊሌዮ ምርምር ጥናት ይበልጥ በፕላቶን ፍልስፍናዊ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ሲሆን የቁጥርን ወይም የሂሳብን ስሌት ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ሳይንሳዊ ምርምርን በሙከራ አማካይነት ወደ ተግባር መመንዘር ነበር ዋናው ዓላማው። ስለሆነም ጋሊሌዮ የመጀመሪያው የሙከራ ሳይንስን ምሁርና ለአውሮፓው የስልጣኔ መሰረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል። ሌሎች በዚህ በመቀጠልና አድማሳቸውን በማስፋፋት የበለጠ ምርምር በማድረግ ለስልጣኔ መሰረት መጣል ቻሉ። በአዲሶቹ ተመራማሪዎች እንደነ ሬኔ ዴካ ዕምነት መሰረት ሳይንሳዊ ግኝት የሚቻለው አስፈላጊውን ነገሮች ከአላስፈላጊዎች በመነጠል ሲሆን፣ በትንታኔው መሰረት ከአጠቃላይ ሁኔታ በመነሳት ቀስ በቀስ በተናጠል ነገሮች ላይ በማትኮር ወደ ሳይንሳዊ ግኝት ላይ ለመድረስ ነው። የሰው ልጅ በራሱ ላይ ዕምነት እንዲኖረው ሲያሳስብና ይህም ዓለም አቀፋዊነት እንዳለው ሲገነዘብ- ማሰብ እችላለሁ፣ ስለዚህም እኔ ነኝ/(I think, therefore I am) አንድ ሰው ወይም ህብረተሰብ በማሰብ ኃይሉ እንጁ በልምምጥና ይግባኝ በማለት ራሱን ማግኘትና መሰልጠን እንዳማይችል ያስገነዝባል። በመሆኑም በሬኔ በዲካ ዕምነት የዕውቀት ዋናው መሰረትና ወደ ሀቀኛውም መንገድ መድረሻ ዘዴ በማቲማቲክስ አማካይነት አርቆ አሳቢነትን (Mathematical Reasoning) መቀዳጀትና ዕውነትን ለማግኘት መጣር ነው። ይህንን መሰረት በማድረግ የሰው ልጅ አንድን ነገር (matter) በሁለንታዊ መልኩና ውስጣዊ ባህርዩን መረዳት ሲኖርበት ከዚያም በመነሳት ጂኦሚትሪያዊ ቅርጻቸውን መረዳት ይቻላል ይላል።
በተለይም ፍራንሲስ ባኮን በተፈጥሮ ላይ ምርምሩን ይበልጥ በማትኮርና የተፍጥሮን ህግ መረዳት በማስመር የሰው ልጅ ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ማዋል እንዳለበት ያስተምራል። በእሱም ዕምነት አዲሱ ሳይንስ ፈጣሪና በተፈጥሮ ላይ ጣልቃ-ገብነተን (Creation & intervention) የሚያስችል መሆን አለበት። ይህ ማለት ግን ተፈጥሮን ወደ ተራ ተብዝባዥነት መለወጥ ነው ለማለት ሳይሆን የተፈጥሮን ህግ በመረዳት በዚያ አማካይነት ሳይንሳዊ ምርምርና ግኝት ይቻላል ለማለት ነው። በባኮን ዕምነት የተፈጥሮ ምንነትና የሰው ልጅ ትርጉም በአዲስ መልክ መጻፍ እንዳለበት ሲያሰተምር በዚህ አማካይነት ብቻ የሰውን ልጅ የበላይነት አቅጣጫና ይህ ከዕውቀት ጋር ሊኖር የሚችለውን ግኑኝነት ማሳየት እንደሚቻል ያምናል። ይህ ዐይነቱ የምርምር ዘዴና በኋላ ላይ ደግሞ የኒውተን አስተሳሰብና ምርምር ተቀባይነት በማግኝት ከሁለንታዊ ነገር ላይ ይልቅ በተናጠል ነገር ላይ ማትኮር ለአውሮፓው የሳይንስ መሰረት መሆን በቃ። ይሁንና ግን እነ ላይብኒዝ የመሳሰሉት የተፈጥሮ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች እንደዚህ ዐይነቱን በተናጠል ላይ ያተኮረ ምርምርና የአተናተን ዘዴ በመቃዎም በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለና፣ ይህም ትክክለኛው የሳይንስና የምርምር ዘዴ ሲሆን የሰውም ልጅ ጭንቅላት የተሳሰሩ ነገሮችን ማየትና መረዳት እንዳለበት፣ በዚህም ብቻ የስልጣኔ ባለቤት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከክስተታዊ ዕውቀት በመላቀቅ የበለጠ አርቆ አስተዋይነትን ከራሱ ጋር በማዋሃድ ካለብዙ ውዝግብ የስልጣኔ ባለቤት መሆን እንደሚችል ማስተማር ጀመሩ። ይሁንና ግን የሰው ልጅ የራሱን ምንነት በዚህች ዓለም ላይ ለመረዳት ከፈለገ ሳያቋርጥ ከራሱ ጭንቅላት ጋር መታገል እንዳለበት መሰረታዊ ጥያቄ ነበር። ያም ሆኖ ኔውተንና ላይብኒዝ አንደኛው የሌላውን ግኝት ሳያይ ሁለቱም በየራሳቻው ካልኩለስ የሚባለውን ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ምርምርና ዕድገት የሚረዳውን ሂሳብ ማግኘትና ለሰው ልጅም ማበርከት ችለዋል፡፡
በ14ኛውና በ15ኛው ክፍለ-ዘመን የተሃድሶ አብዮት ሲጀመርና ሲስፋፋ መሰረት የተደረገው በፕላቶናዊና በአርስቲቶለስ ፍልስፍናና አመለካከት ላይ በመመስረት ነበር። በአንድ በኩል ፕላቶ የሰው ልጅ ከዕውቀት ጋር የተፈጠረና ይህንንም ወደ ውጭ አውጥቶ መጠቀም ይችላል ሲል፣ አርስቲቶተለስ ደግሞ የዕውቀት ምንጭ ጭንቅላት ሳይሆን የሚታዩ ነገሮች ወደ ጭንቅላት ውስጥ በመግባት ከዚያ በመነሳት የሚደረስበት የምርምር ውጤት ነው ብሎ ያስተምር ነበር። ፕላቶ በማይታየው ውስጥ በማለፍ የሚታየውን ለማግኘት ሲጥር፣ አርስቲቶለስ ግን ከሚታየው በመነሳት የዕውቀትን ምንጭ ለመፈለግ ይሞከር ነበር፤ ይህም ትክክለኛው መንገድ ነው በማለትና አስተማሪውን ፕላቶንን በመቃወም ያስተምር ነበር። ይህ ዐይነቱ የዕውቀትን መሰረትና ምንጭ በዚህ መልክ ለያይቶ ማየቱ በሬናሳንስ ዘመንና ከዚያም በኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ክፍፍልና ክርክርን ያስከተለ ሲሆን፣ በኋላ ላይም በሳይንሳዊ ምርምር ላይ የራሱ ተፅዕኖ ሊኖረው ችሏል ብሎ መናገር ይቻላል። ስለሆነም የተፈጥሮንና የህዋን ህግና እንዲሁም የዕውቀትን ምንጭ በሚመለከት የተለያየ አስተሳሰብና ፍልስፍናዊ አመለካከት ነበር። ይሁንና ግን ሁለቱንም የዕውቀት መንገዶችና የህዋን ህግ መረዳት ትግል ዕውነትን ወይም ሀቀኛውን መንገድ ከመፈለግ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የፕላቶኑ የምርምር መንገድ ሁለንታዊና ጥልቀት እንዳለው የሚያከራክር አይደለም። ያም ሆነ ይህ የሁለቱም አካሄድ የሰውን ልጅ የማሰብና የመፍጠር ኃይል በመገንዘብ ሁለ-ገብ የሆነ ህብረተ-ሰብአዊ ፕሮጀክት መንደፍና መጣል ይቻላል የሚል ሳይንሳዊ መንገድ ነበር። በዚህም መሰረት የተፈጥሮን ህግ በመረዳት ጥበባዊና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብ መመስረት ነበር ዋና ዓላማው። ሆኖም ግን በፕላቶንም ሆነ በአርስቲቶለስ አመለካከት መሰረት ስነ-ምግባርና ሞራል እንዲሁም ቁጥብነት እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውና፣ ለአንድም ህብረተሰብ ተቻችሎ መኖርና ሚዛናዊ ዕድገት አስፈላጊ እንደሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም በሁለቱ ፈላስፎችና ተመራማሪዎች ዕምነት እኩልነት ኖርማቲቭ ባህርይ ያለው እንጂ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አንድ ወጥ በሆነ አመለካከት ለመቅረጽና ፍጹማዊ እኩልነትን ለማንገስ አለነበረም፤አይደለምም።
ከአስራ አራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣው ምሁራዊ እንቅስቃሴ በተግባር በመመንዘር ከኢጣሊያን ተሻግሮ ሌሎች የአውሮፓ አገሮችንም ማዳረስ ተቻለ። ጥበብ፣ ውብ ውብ የአርክቴክቸር ስራዎች፣ ቤተ-መንግስታትና ካቴድራሎች የተወሰነ የጂኦሜትሪን ቅርፅ ይዘው እንዲሰሩ በማድረግ ቢያንስ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል አስተሳሰቡ ከኋላ-ቀርነት እንዲላቀቅና ስራው ሁሉ የሰለጠነ እንዲሆን አመቺ ሁኔታ ተፈጠረ። በተለይም የዳንቴ የአምላኮች ኮሚዴ የሚለው የሰውን ልጅ ከጨለማው ዓለም ተላቆ ወደ ብርሃኑ ዓለም እንዲወጣ የሚያደርገው በመስፋፋቱ በአውሮፓ ምድር ውስጥ አዲስ ዓይነት የሊትሬቸር አጻጻፍ እንዲስፋፋና እንዲዳብር መንገዱን አመቻቸ። ይህ የሊትሬችር አጻጻፍ በተለይም በጣሊያን ምድር ተቀባይነትን በማግኘትና በመስፋፋት ለሬናሳንስ በር የከፈተና የጣሊያንም ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቋንቋ እንዲናገር በማድረግ ርስ በርሱ እንዲግባባና የስልጣኔ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ተቻለ።
የኢጣሊያኑ ሬናሳንስ ቀስ በቀስ ብርሃኑን በአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ሲፈነጥቅ፣ በዚያው መጠንም አዳዲስና የተገለጸላቸው ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች ብቅ ብቅ በማለት በየቦታው ሰፍኖ የነበረውን ኦሊጋርኪያዊ አስተዳደርና የጨለማ ኑር በመጋፈጥ ለሰው ልጅ ኑር አዲስ መልክና ትርጉም በመስጠት፣ ከተማዎች፣ የገበያ አዳራሾች፣ ጋርደኖችና ልዩ ልዩ መናፈሻዎች ጥበባዊ በሆነ መልክ በመሰራት የሰውን ልጅ አትኩሮና አስተሳሰቡን መለወጥ ተቻለ። የሰው ልጅ ማዕከላዊ ቦታ በማግኘት የበለጠ ለስልጣኔ እንዲነሳሳ በሩን ተከፈተ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል በአውሮፓ ምድር ውስጥ ንግድ መስፋፋት፣ የዕደ-ጥበብ ስራ መዳበር፣ በዚህ አማካይነት ደግሞ ህዝባዊ መተሳሰርና አጠቃላይ ህዝባዊ ሀብት መዳበር እንደሚቻል ግንዛቤ ውስጥ የተደረሰበት። ይህ ዐይነቱ ሂደት በዚያው መጠንም ሰፋ ላለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሩን ሲከፍት፣ በመንግስታት መሀከልም ፉክክር ይደረግ ነበር። በሌላ ወገን ግን የካቶሊክ ሃይማኖት አሁንም አይሎ በሚገኝባቸው እንደ ፖርቱጋልና ስፔይን የመሳሰሉት አገሮች ውስጥ የሳይንስን መሰረተ-ሃሳብ መሉ ለሙሉ ለማስፈንና የበላይነትን እንዲቀዳጅ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ ብዙ ተመራማሪዎችና ነጋዴዎች ሁለቱን አገሮች ሸሽተው በመሄድ በተለይም ሆላንድ ውስጥ ኑሮአቸውን በመመስረት የሳይንስ ምርምራቸውንና የንግድ እንቅስቃሴያቸውን እዚያው ቀጠሉ። በሁለቱም አገሮች የካቶሊክ ሃይማኖት የበላይነት መስፈን ቢያንስ ወደ ካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ስርዓት የሚደረገውን ሽግግር እንዳገደው የማይታበል ሀቅ ነው።
ዛሬ ላለውም በሁለቱ አገሮች ለሚታየው ቀውስ ዋናው ምክንያት ሁለቱም አገሮች ከካቶሊክ ጭፍን አስተሳሰብ ለመላቀቅ ባለመቻላቸውና ከበርቴያዊ ሰበአዊነትን በመጎናጸፍ ኋላ-ቀር የኢኮኖሚ ስርዓትን ለመደምሰስና በወርቅና በብር የሀብት ክምችት ከመመካት ይልቅ ወደ ፈጠራና ወደ ምርታማ ስራ ለመሸጋገር ያለመቻላቸው ነው። የካቶሊክ ሀይማኖት ማየልና በህዝቡም ዘንድ ሰርጎ መግባት በንግድ እንቅስቃሴና መዳበር ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረው የተረጋገጠ ነው። በጊዜው በሁለቱም አገሮችም ሆነ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ወርቅንና ብርን ማከማች የአንድ አገር ሀብት መለኪያው ሲሆን፣ ስፔንና ፖርቱጋል ከውጭ የዘረፉትን ሀብት እንዳለ የፍጆታን ዕቃ ከውጭ በማስመጣት ያባክኑ ስለነበር ወደ ሳይንስና ወደ ቴክኖሎጂ ዕድገት ሊያመሩ በፈጹም አልቻሉም። በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ግን ዕውቀትና የአሰራር ስልት በመስፋፋት አንዱ ከሌላው በመቅዳትና አገሩን ለማሳደግ ሲሽቀዳደም፣ ይህ ዐይነቱ ውድድርና ጥረት ለህብረ-ብሄር ምሰረታ በሩን መክፈት ቻለ። አገዛዞች አስተሳሰባቸውን ወደ ውስጥ በማትኮርና አሰፈላጊውን ሁኔታዎች በማመቻቸት አንድ ህዝብ እንዲተሳሰርና አገራዊ ስሜትን አዳብሮ ለዕድገት እንዲነሳ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል ጀመሩ። ይህ ሁኔታ ለፖለቲካ-ኢኮኖሚ በሩን በመክፈትና የአንድ አገር ዕድገት በዘፈቀደ ሳይሆን በዕቅድ የሚሰራና በዚህም አማካይነት ሰፋ ያለ ገበያ መመስረትና የስራ-ክፍፍልን ማዳበር እንደሚቻል ተደረሰበት። ይሁንና ግን በዕውቀት ዘርፍ ውስጥ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ሳይሆን፣ ፍልስፍና፣ የሳይንስ ምርምር፣ ማቲማቲክና ሎጂክ ተቀዳሚ ቦታን በመውሰድ ለአውሮፓው ስልጣኔ በር መክፈት እንደቻሉ መታወቅ አለበት። በሌላ አነጋገር በአውሮፓው የስልጣኔ ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነትን መቀዳጅት የቻለው ከአስራ ስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ፣ በተለይም ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህ በመነሳት እንደ ጀርመን የመሳሰሉ በዕድገት ወደ ኋላ የቀሩና ወደ ህብረ-ብሄር (Nation-State) ያልተሸጋገሩ አገሮች በመጀመሪያ ቅድሚያ የሰጡት ለጥበብና ለሳይንስ ነው። የፕረሺያው ንጉስ ታላቁ ፍሪድርሽ አገራቸውን ከኋላ-ቀርነት ለማውጣት ሲሯሯጡ፣ ትግል ሲያደርጉና ፈላስፋዎችንም ምክር ሲጠይቁ እነ ቮልቴር የለገሷቸው ምክር በጥበብና በሳይንስ ላይ እንዲያተኩሩ ነበር። በዚህ አማካይነት ብቻ ዕውነተኛ ስልጣኔን መቀዳጀት እንደሚቻልና ህዝባዊ መተሳሰር እንደሚመጣ ግልጽ ነበር። ከዚህ በኋላ የተነሱት የጀርመኑ ክላሲኮች ያተኮሩትም ይህንን መንገድ በመከተልና፣ በተለይም በግሪኩ ስልጣኔ ላይ በማትኮርና ይህንን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነበር። ስለሆነም እንደነ ጎተና ቪንከልማን የመሳሰሉት ሌሎች ቀደም ብለው የሄዱ የአንዳንድ የአውሮፓን፣ በተለይም የኢጣሊያንን የከተማ አገነባብና የህንፃ ስራዎች ከተመለቱ በኋላ የደረሱበት ድምዳሜ የግሪኩ ስልጣኔና፣ በዚያ ላይ የተመሰረተው የኢጣሊያኑ የተሃድሶ አብዮት ትክክለኛው የህብረተሰብ ዕድገትና የስልጣኔ መንገዶች እንደነበሩ በመገንዘብ ነው።
በዚህም ላይ አጥብቀው በመስራትና በአገዛዞች ላይ ግፊት በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ችለዋል ማለት ይቻላል። በዚህ አማካይነት ብቻም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሳይንሳዊ ግኝቶችና የቴክኖሎጂ መሰረቶች መጣል እንደሚቻል ከፍተኛ ግንዛቤ ነበር። ሰፋና ዕውነተኛ ዕውቀት ላይ በመመስረት ብቻ የሰው ልጅ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንደሚጎናጸፍና ህብረተሰብአዊ ስምምነትን ማምጣት እንደሚቻል በአጠቃላይ ሲታይ ለአውሮፓ ምሁራን፣ በተለይም ኋላ ላይ ለተነሱት የጀርመን ፈላስፋዎች እንዲሁም የጥበብና የሳይንስ ሰዎች ግልጽ ነበር። በፍልስፍና፣ በሳይንስና በጥበብ ላይ ብቻ ርብርቦሽና ትግል ሲደረግ ብቻ የሰው ልጅ ከአውሬ ባህርይው በመላቀቅ የሰለጠነ ስራ መስራት እንደሚቻል መገንዘብ የተቻለው። ስለሆነም በአውሮፓ ምድር ውስጥ፣ በተለይም በፈላስፋዎችና በሳይንቲስቶች ዘንድ ትግል ሲባል ከጭንቅላት ጋር መታገልና፣ የተፈጥሮንና የህዋን ህግ በመረዳት የሰለጠነ ስርዓት መገንባት ሲሆን፣ አንዱን ተቀናቃኝ ወይም ጨቋኝ የሚባልን ኃይል በመጣል ብቻ ዕውነተኛ ነፃነት እንደማይገኝ የታመነበት መሰረታዊ ሃሳብ ነበር።
ከዚህ በላይ ለማሳየት የሞከርኩት ትግል ሲባል ስሜታዊ ሳይሆንና ከአንድ አገዛዝ ጋር ፍጥጫ ውስጥ በመግባት ወደ ድል ማምራት እንደማይቻል ሲሆን፣ ትግል ማለት የተፈጥሮናን የህዋን ህግ በመረዳትና አርቆ አሳቢነትን፣ ዲያሌክቲክናና እንዱሁም ልዩ ልዩ በጭንቅላት ውስጥ ያሉ ለማሰብና ለመመራመር የሚያግዙ የጭንቅላት ክፍሎች በመጠቀምና ለተግባር የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን በመስራት አንድ ህዝብ የስልጣኔ ባለቤት ሊሆን እንደሚችል ነው። ትግል ሲባል ከሳይንስ፣ ከፍልስፍናና ከሎጂክ ውጭ ሊደረግ እንደማይችልና፣ እነዚህን ያላሰቀደመ የትግል ዘዴ አንድ አገዛዝ ከስልጣን ላይ ቢወገድም እንኳ አንድ ህዝብ በምንም ዐይነት የስልጣኔ ባለቤት ለመሆን እንደማይችል ነው።
ይህ ማለት ግን ይህ ዐይነቱ የትግል ዘዴ በራሱ ብቻ በቂ ነው ማለት አይደለም። በአንዳንድ የታሪክ ወቅት የገዢ መደቦች ወደ ፍጹም እልክነትና የስልጣኔ እንቅፋትነት በመሆን አንድን ህበረተሰብ ትርምስ ውስጥ እንደሚከቱትና በውዝግብ ዓለም ውስጥ እንዲኖር የሚያደርጉበት ጊዜ ይኖራል። በተለይም የተሳሳተ ዕውቀት በሚስፋፋበት ጊዜና ይህም ስርዓቱን በሚያቅፍበት ጊዜ አንድ ስርዓት ህዝባዊ ነፃነትን ከማስፈን ይልቅ ወደ በዝባዥነትና ወደ ጦርነት የሚያመራበት ጊዜ አለ። ስለሆነም ልክ በአራተኛው ክፍል-ዘመን ከክርስቶስ መወለድ በፊት በግሪኩ ስልጣኔ ዘመን በአውሮፓ ምድር ውስጥም ከአስራ ሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ኤምፕሪስሲቶች ወይም በክስተት ላይ የሚያተኩሩ ፈላስፋዎች በመነሳት የአውሮፓውን ዕድገት መልክ እንደቀየሩትና ለአዲስ ዐይነት የኃይል አሰላለፍ መሰረት እንደጣሉና የሰው ልጅም በተፈጥሮ ላይ ለየት ያለ ግንዛቤ እንዲያድርበት ማድረጋቸው የማይታበል ሀቅ ነው።
በተለይም በእንግሊዝ አገር ብቅ ያሉት ኤምፔሪሲስቶች የሚባሉ ፈላስፋዎች የእነ ፕላቶንን የአርቆ አስተዋይነት ፍልፍና አሽንቀጥረው በመጣል በጊዜው ብቅ ላሉ አዲስ የገዢ መደቦች ሊያገልግሉ የሚችሉና ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ተበዥባዥ ማድረግ የሚችሉ ልዩ ዐይነት የሳይንስ ፈለግ ያስፋፋሉ። በካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ማደግና በኢንዱስትሪ አብዮት አማካይነት የተነሳ አዲስ ኃይል አሰላለፍ ሲፈጠር፣ የሰውም ልጅ ኑር መቃውስና ገበሬውም ከመሬቱ መፈናቀል ይጀምራል። ይህ አዲሱ የኃይል አሰላለፍና የኢኮኖሚ ስርዓት መሬትንና ሌሎች ሀብቶች በጥቂት የህብረተሰብ ክፍልል ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ በማድረግ ለህብረተሰባዊ ግጭት በሩን ይከፍታል። በጊዜውም የነበሩት የተወሰኑ ተመራማሪዎች ይህን አዲስ የህብረተሰብ ኃይል አሰላለፍና የኢኮኖሚ ስርዓት የበላይነት ሊያረጋግጥ የሚችልና ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደረግ እንደ ህግ የበላይነት (The Rule of Law) የመሰለውንና ሌሎችንም ዕውቀቶች ማዳበርና ማስፋፋት ቻሉ። ይህ ዐይነቱ ስርዓትና ዕውቀትን ማዛባትና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በሚጠቅም መልክ ሆኖ መዘጋጀት ለመደባዊ ክፍፍልና ለድህነት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። የኢንዱስትሪ አብዮትና እያደገ የመጣው ካፒታሊዝም ትርፍን ዋናው የስርዓቱ መሰረታዊ ጥያቄና ዓላማ በማድረግ በሰራተኛው ላይና በተፈጥሮ ላይ ግፊት ማድረግ ጀመረ።
ይህንን የተመለክቱ ሮማንቲክስ የሚባሉ ተመራማሪዎች የኢንዱስትሪ አብዮትን አስቀያሚ ጎን በማሳየትና የተፈጥሮን ምንነት በመረዳት በሰው ልጅና በተፈጥሮ መሀከል ሚዛናዊነትና መተሳሰብ መኖር እንዳለበት ያመለክታሉ። በተለይም በጀርመን ምድር ብቅ ያሉ ፈላስፋዎች የእንግሊዙን መንገድ በመቃወም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሚዛናዊ ዕድገትና ዕውነተኛ የሆነ፣ በኢኮኖሚ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ ሁሉንም ያካተተ የሲቪል ሀብረተሰብ መመስረት እንዳለበት ይታገላሉ። ስለሆነም ዕድገት ሲባል ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ባህርይ መኖር እንዳለበትና፣ የሰው ልጅም በአፈጣጠሩ ግለሰብአዊ ሳይሆን ማህበራዊ እንደሆነና በዚህም አማካይነት ብቻ የራሱን ምንነት መግለጽና መኖር እንደሚችል ያስተምራሉ።
ከዚህ በመነሳትና የኢንዱስትሪ አብዮት እያየለና በብዙ አውሮፓ አገሮች ተቀባይነትን ሲያገኝና ከኢኮኖሚ ከዕድገት ባሻገር የህዝቡን ኑሮ ሲያቃውስና በከፍተኛ ደረጃ ተበዝባዥ አድርጎ ወደ አስቀያሚ ኑሮ ሲጥለው የተመለከቱ እንደነ ሄግል፣ በኋላ ደግሞ ማርክስና ኤንግልስ ከፍተኛ ምርምርና ጥናት በማካሄድ አንድ ህዝብ በአንደዚህ ዐይነቱ ዕድገት ሊጓዝ እንደማይችልና፣ የግዴታ የሶሻሊዝም መመስረትን አስፈላጊነት ማሳየት ይችላሉ። ይህም ማለት ሮማንቲኮችም ሆነ በኋላ እነ ማርክስ ትግላቸውን ሲጀምሩ ዝም ብለው በጥላቻ ላይ በመመርኮዝ ሳይሆን የብዙ ዐመታት ጥናት፣ ምርምርና ክርክር ካደረጉ በኋላ ነው ወደዚህ ዐይነቱ መደምደሚያ ላይ መድረስ የቻሉት። በጊዜው የነበረው በጣም አሰቃቂና አስቀያሚ ኑሮ ከነበራቸው የንቃተ-ሁኔታ ጋር መጣጣም እንዳማይችልና የሰውም ልጅ ዕጣ በዚህ መወሰን እንዳማይችል በመገንዘብ ነው የኮሙኒስትን ማኒፌስቶና በኋላ ደግሞ የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ህግና እንቅስቃሴ ማሳየት የሚችል ዳስ ካፒታልን መደረስ የተቻለው። ሮማንቲኮችም ሆነ በኋላ ላይ ሄገልስና ማርክስ የፈለሰፉት የትግል ዘዴ በመሰረቱ አዲስ ነገር ሳይሆን፣ በተለይም የኢኮኖሚ ዕኩልነትና ህብረተሰብአዊ ሚዛናዊነት በግሪኩ ስልጣኔ ዘመንም በሶክራተስና በፕላቶ እንዲሁም ደግሞ በአርስቲቶለስ ለውይይት የቀረበና ማስተማሪያ ነበር። የአገዛዞችም መሰረት ስነ-ምግባርና ሞራላዊ መሆን እንዳለበት ያስተምሩና በዚህ አማካይነትም ህብረተሰብአዊ ሚዛናዊነት መምጣት አንደሚችል ይሰብኩ ነበር ።
በኋላም በአስራ ሶስተኛውና በአስራ አራተኛው ክፍለ-ዘመን በተገለጸላቸው ቀሳውስት አማካይነት የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ ዕኩልነት ጉዳይ እየተነሳ ክርክር የሚደረግበት ነበር። በሌላ አነጋገር አንዳንድ የእኛ አገር ጥራዝ ነጠቆች እንደሚሉት እነ ማርክስ እብዶች ስለሆኑ ሳይሆን ይህንን ትግላቸውንና ምርምራቸውን የጀመሩትና ይሰብኩ የነበረው፣ በጊዜው የነበረው እጅግ አሰቃቂ ሁኔታና መፈናቀል ስለታያቸውና ይኖሩበትም ስለነበር ነው። እንደኛው ምሁራን የእግዚአብሄር ዕጣ ነው ብለው በመቀበል ወይም ደግሞ የተፈጥሮ ህግ ነው በማለት እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ ሳይሆን፣ የችግሩን ምንጭ በመረዳት በአዲስ መልክ ለተፈጠረው ሁኒታ አዲስ መልስ ለመስጠት ነበር ትግላቸውን የጀመሩት። እነ ማርክስ ጦርነትን የሰበኩበትና ደም መፋሰስም እንዳለበት ያስተማሩበት አንድም ቦታ ላይ አይገኝም። ይሁንና ግና አንድ አገዛዝ መረን የለቀቀና ህዝብን የሚያሰቃይና የሚጨቁን ከሆነ እነ ማርክስ ብቻ ሳይሆኑ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የነበሩ የተገለጸላቸው ቀሳውስትም የኃይልን ምንነትና አስፈላጊነት ያነሱ እንደነበር የታወቀ ጉዳይ ነው። በእነሱም ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ ያለ አገዛዝ ዝም ብሎ የራሱን ህግ በማውጣት ህዝብን በማሰቃየት ፍዳ ውስጥ መክተት እንደሌለበት በመረዳት ነው። ስለሆነም መነሺያቸው የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ሲሆን፣ አንድ ሰው የአንድ አገር መሪ ስለሆነ የራሱ የሆነ ልዩ ህግ ሊኖረው እንደማይችልና፣ ህዝብን ማተረማመስ እንደማይችል ነው። ዋናው መሰረታቸው ግን ዕውቀትና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ነበር ማለት ይቻላል። በአጭሩ በአውሮፓ የትግል ታሪክ ውስጥ ዕውቀትን ለመፈለግ የተለያየ አካሄድ ቢኖርም የትግል ዋናው መሰረት ጭንቅላትን ከማደስ፣ ከማነፅና በዲያሌክቲክ አማካይነት ጥያቄን በጥያቄ መልክ በማንሳትና በመጠየቅ ወደ ተቀራራቢ መልስ ለመምጣት ሙከራ ማድረግ ነበር።
እንደ ዛሬው ሁኔታ በአመጽ ላይ ያተኮረና፣ ዕውቀትም ሲባል ለአንድ የገዢ መደብ መሳሪያ በመሆን የተወሳሰብ የጦር መሳሪያ በመስራት ህዝባዊ ዕልቂት ለማድረስ አልነበረም። የዛሪው ዐይነቱ ዕውቀት ከጥንታዊው የሚለየው ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኮኖሚ በካፒታሊዝም ሎጂክ ውስጥ በመውደቅ የሰውን ልጅ ነፃነት ተቀናቃኞች መሆናቸው ሲሆን፣ ጥንታዊው የሳይንስ ተመራማሪዎች ዕምነት ግን የሰውን ልጅ ከጨለማ ኑሮ ለማውጣትና በተፈጥሮ ላይ የተወሰነ ቁጥጥር እንዲኖረው ማድረግ ሲሆን፣ አካሄዳቸው በምንም ዐይነት የሰውን ልጅ መጨቆኛ መሳሪያ ለማድረግ አልነበረም። ይህንን ፍርሃት ጎተ (Goethe) ፋውስት ሁለት በሚለው የቲያትር ድርሰቱ ውስጥ በደንብ ይገልጸዋል። ማለትም ቴክኖሎጂና ሳይንስ በኢኮኖሚ ቁጥጥር ስር በመውደቃቸው የሰው ልጅ ዕውነተኛ ነፃነትን ለመቀዳጀት የማይችልበት ሁኔታ እንደተፈጠረ ነው የሚያመለክተው።
ከዚህ አጠር መጠን ብሎ ከቀረበ የትግል ትርጉም በመነሳት በአገራችን ምድር ለዲሞክራሲ ሲባል የተካሄደውን እልክ አስጨራሽ ትግል የተሳሳተ አካሄድ ከሞላ ጎደል እንመልከት። በአገራችን ምድር ውስጥ በአለፉት ስድሳ ዓመታት የተካሄደው ትግል የሚባለው ነገር ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ እንዲሁም ሎጂካዊ መሰረት አለው ወይ? ብለን ለመመርመር እንሞክር። ይህንን ማጤኑ ወይም መመርመሩና መረዳቱ ዛሬ ላለንበት የተመሰቃቀለ ሁኔታ ተቀራራቢ መልስ ሊሰጠን ይችላል ብየ እገምታለሁ።
በአገራችን ምድር የትግል ትርጉምና ለዲሞክራሲ የተደረገው ትግል!
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የረዢም ጊዜ ታሪክ ቢኖራትም ይህ ታሪክ ግን ከተወሰኑ ግኝቶች ያለፈና ለሳይንስ፣ ለሎጂክና ለፍልስፍና ምርምር የሚያገለግል አልነበረም። ዕውቀት የሚባለው ነገር አብዛኛውን ጊዜ ከቤተክርስቲያንና ከቀሳውስት ውጭ አልፎ የሚሄድ ባለመሆኑኗ ለጥያቄና ለምርምር የሚያመች ስላልነበር ሰፋ ላለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሩን ሊከፍት አልቻለም። ስለሆነም የህዝቡ ኑሮ ተሃድሶ በማግኘትና በመሻሻል ሃሳቡ ሾሎ የተፈጥሮንና የህዋን ህግ በመረዳትና በመመራመር የሳይንስ ባለቤት ሊሆን አልቻለም። የፊዩዳሉ ስርዓት ሲስፋፋና ከሃይማኖት ጋር ሲጣመር ይህ በራሱ ለምሁራዊና ለዕድገት ዕንቅፋት በመሆን በአገራችን ምድር ውስጥ በተለይም ከሶሎሞናዊ አገዛዝ ጀምሮ በከተማዎች ግንባታ፣ በዕደ-ጥበብና በንግድ የሚገለጽ ዕድገትና እንቅስቃሴ ባለመታየቱ ህዝቡ ተፈጥሮ የሚሰጠውን ከመጠቀም አልፎ በምርምር አማካይነት አዳዲስ መሳሪያዎችን በመስራትና ልዩ ልዩ ምርቶችን በማምረት ኑሮውን ማሻሻል አልቻለም። ከዚህ ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሳል ከሆነው ከግሪኩ ስልጣኔና በኋላም ከሬናሳንስን ዕውቀት ጋር ለመተዋወቅ ባለመቻሉ በአጠቃላይ ሲታይ የህዝቡ ኑሮ ተፈጥሮአዊና ከመሬት ጋር ብቻ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ሰፊው ህዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነውን ውስጣዊ የማሰብ ኃይል ለመጠቀም ባለመቻሉ በተፈጥሮ ላይ የበላይነትን በመቀዳጀት በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን እያወጣ በመለወጥና አዳዲስ መሳሪያዎች በመስራት ህብርተሰብአዊ ለውጥን ሊጎናጸፍ አልቻለም።
እንደዚህ ዐይነቱ በተፈጥሮ ላይ ብቻ የመመካት የአኗኗር ስልትና፣ ዕድሉን ከሃይማኖት ጋር ማገናኘት የተፈጥሮ አደጋና በየጊዜው የሚከሰቱ በሽታዎች ሰለባ ሊያደርገው በቃ። የአገራችንን ዕድገት ኋላ መጓተት የተገነዘቡ እንደነ አፄ ቴዎድሮ የመሳሰሉ መሪዎች አንዳንድ ሙከራ ቢያደርጉም ውስጥ ለውስጥ በሚካሄደው ፊዩዳላዊ አሻጥርነትና ዕምቢተኝነት የአፄው ቴዎድሮስ አገዛዝ በመደላደል የአሰባቸውን የዘመናዊነት ስራዎች ሊሰራ አልቻለም። የአገዛዙም የማህበራዊ መሰረት (Social Base) በተገለጸላቸውና በፈላስፎች የተመረኮዘ ስላልነበር የንጉሱን የዘመናዊነት ጥም የሚረዳ የህብረተስብ ክፍል አልነበረም። የኢትዮጵያ መሳፍንት እንደ አውሮፓ ፊዩዳሎችና መሳፍንቶች የአኗኗር ስልታቸውን ለመለወጥ የተዘጋጁ ስላልነበሩና የነበረው ስርዓትም ግፊት ስለማያደርግባቸው አካባቢያቸውን የሚንከባከቡና ከተማዎችንና መንደሮችን የሚገነቡ አልነበሩም። ተግባራቸውና ትግላቸው ይበልጥ በጦርነትና ላይ ያተኮረና ዝርፊያም የተሞላበት ስለነበር ህብረተሰብአዊ መደላደል እንዳይኖርና ከውስጥ የስራ-ክፍፍል እንዳይዳብር አግደዋል ማለት ይቻላል። ይህ ዕምቢተኝነትና በየአካባቢው የዕድገት እንቅስቃሴ መታየት አለመቻልና ሁልግዜ ለስልጣን ብቻ ፍክክር ማድረግና ጦርነት መክፈት የህዝቡን አትኩሮና የአኗኗር ስልት ውስን ሊያደርገው በቅቷል። በዚህም ምክንያት ኑሮው መሻሻል የማይታይበትና አዳዲስ አስተሳሰቦችም የማይፈልቁበት የአኗኗር ስልት ነበር። ከዚህም በላይ አፄ ቴዎድሮስ ከውጭ ኢንጅነሮችንና ቴክኖሎጂን ለማስመጣት ያደረጉት ጥረት በእንግሊዝ አሻጥርነት ባለመሳካቱ አፄው ሳይወዱ በግድ ወደ እልከነት አመሩ።
አፄ ምኒልክ ከአደዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ለማድረግና ወደ ተጠቃለለ አስተዳደር ያደረጉት ሙከራ አንድ እርምጃ ወደፊት ቢሆንም በነበረው ምሁራዊ ድክመትና አልቦ የህብረተሰብ መሰረት የዘመናዊነት ሙከራው ቴክኖሎጂያዊ ዕምርታንና ምርምርን አላስከተለም። ይህ ጉዳይ አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ከያዙም በኋላም ብዙ የሄደ ባለመሆኑ ዕውቀት የሚባለው ነገር ከአካዳሚ አልፎ በከተማዎች ዕድገት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በጥበብና በልዩ ልዩ ውብ ስራዎች የሚገለጽ አልነበረም። እንዲያውም አፄ ኃይለስላሴ ጣሊያን ያንኮታከተውን የፊዩዳል ስርዓት በመመለስና በገንዘብ አማካይነት የሚገለጽ የንግድና አልፎ አልፎ በቀላል የኢንዱስትሪ ተከላ አማካይነት ሳያውቁት ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊና የሳይኮሎጂካል ክስተት እንዲፈጠር በማድረግ ለአመጽ የሚጋብዝ ሁኔታ ፈጥረው ሄደዋል ማለት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለት ጊዜ ከጣሊያን የተሰነዘረበትን የወረራ ጦርነት መክቶ ቢመልስም፣ የቻይናው የኮሙኒስት መሪና ነፃ አውጭው ሊቀ መንበር ማኦ ሴቱንግ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሁለተኛ ጊዜ በፋሺስቱ ጣሊያን የተከፈተበትን ጦርነት በቆራጠኝነት ተዋግቶ ድልን ቢቀዳጅም ህዝቡ ብቃት ያለው አመራር ባለማግኘቱ ከድል በኋላ ተመልሶ የእንግሊዝና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጉያ ስር በመውደቅ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይቀዳጅ ተደረገ፤ ወደ ድህነትና ወደ ጥገኝነትም እንዲያመራ ተገደደ። ውስጣዊ ኃይል የሌለው የኢንዱስትሪ ተከላና የህብረተሰብ አወቃቀር ቀናቸውን ለሚጠባበቁና የአገራችንን ህልውና ለሚፈታተኑ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ሁኔታውን አመቻችቶ ሰጠ። ስለሆነም በፍጆታ ምርት ላይ ብቻ የአተኮረው፡ ስፋትነትና ጥልቅነት የሌለው እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት ያልነበረው ጠባብ የገበያ ኢኮኖሚ ለአዲስ ዐይነት ሀብረተሰባዊ ቀውስ በሩን ከፈተ። ከዚህም በላይ፣ ቀስ በቀስ ከሳይንስ፣ ከቴክኖሎጂና ከከተማዎች ዕድገት ጋር እየተገናዘበ መዋቀር ያልቻለው ቢሮክራሲያዊ ስርዓትና የወታደር ተቋም የአገዛዙን ጥቅም ከመጠበቅ አልፎ የሚሄድ አልነበረም። ስለሆነም ማንኛውንም ህዝባዊ ብሶት በእንጭጩ ለመቅጨት ሲባል የተዘጋጀ አመጽን የሚያስቀድም ኃይል ነበር የሚያስመስለው። እንደሌሎች የተሃድሶ አብዮት ባልተካሄደባቸውና ሰፊ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በማይታይባቸው በብዙ የአፍሪካ፣ የማዕከላዊና የላቲን አሜሪካ አገሮች ያለው ዐይነት ችግርም በአገራችን ምድር እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ መታየቱ አልቀረም።
ካለምንም የጭንቅላት ተሃድሶና ዲሞክራሲያዊ ኢንስቲቱሽን ጋር እየተነፃፀረ ያልሰጠነው ወታደራዊ፣ የፖሊሲና የፀጥታ ኃይል በአሜሪካንና በእንግሊዝ አመለካከት በመሰልጠኑና የርዕዮተ-ዓለም ተፅዕኖም ስለነበረበት በመሰረቱ የዕድገት ተቀናቃኝ ነበር። ይህ ዐይነቱ ይበልጥ አመጽን ያስቀደመ ወታደራዊ አስለጣጠን ዘዴ ከፊዩዳሉ ርዕዮተ-ዓለም ጋር በሚዋሃድበት ጊዜ እንዳየነው ውጤቱ በቀይና በነጭ ሽብር ዘመን እንደተካሄደው ዐይነት ርህራሄ የጎደለው ጭፍጨፋን ነው የሚያካሂደው። አስተሳሰቡን ሊቆጣጠር የማይችል በመሆኑም የቅንጣትም ያህል ሳያስብ የወሰዳቸው ጨካኝ እርምጃዎች ለብዙ መቶ ሺህ ወጣቶች መሞት ምክንያት ሊሆን በቅቷል። በአብዮቱ ወቅት የተገኙ ድሎች በሙሉ በዚህ በአሜሪካን ርዕዮተ-ዓለም በሰለጠነና ከፊዩዳሊዝም ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ባልተላቀቀና ሀቀኝነትን ሳይሆን ተንኮለኝነትን መመሪያው ያደረገውና ብሄራዊ ባህርይ የሌለው የሲቪል ቢሮክራሲና ንዑስ ከበርቴ ሁኔታውን ተጠቅመው በወጣቱና በተራማጁ ላይ እንዳለ በመነሳት ዛሬ ላለው ሁኔታ አመቹ ሁኔታ ፈጠሩ። አገራችንን የምሁር አልባ በማድረግ ዛሬ ላልነበት አሳፋሪና አስከፊ ሁኔታ ሊዳርጉን በቁ።
በመሆኑም በአገራቸን ምድር በትግል ስም የተካሄደውን ትርምስና እስከዛሬ ድረስ ልንላቀቅ ያልቻልነውን አስተሳሰሰብ መረዳት የምንችለው የተመሰቃቀሉ ግን ደግሞ ዕድገትንና ስልጣኔን የሚቀናቀኑ ሁኔታዎችና የኃይል አሰላለፎችን ከቁጥር ውስጥ ያስገባን እንደሆን ብቻ ነው። በግራና በሶሻሊዝም ስም የሚወነጀለውን የተማሪውን እንቅስቃሴና የትግል ዘይቤና መተላለቅ መረዳት የምንችለውም በአገራችን ምድር ውስጥ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ፊዩዳላዊ አሰተሳሰበና የእምቢተኝነት እልክ ይህ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሃድሶን፣ ሳይንስንና ቴክኖሎጂንም ማስፋፋት ሳይሆን የተወሰነ የፍጆታ አጠቃቀም ሁኔታን ማስፋፋት ከተያያዘው በተለይም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር ማያያዝ የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። ካለበለዚያ ሳያወጡና ሳያወርዱ እንዲያው ዝም ተብሎ የሚሰነዘሩ ክሶች ኢ-ሳይንሳዊ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የነገሮችን ሂደት በደንብ እንዳንገነዘብና በአዲስ መንፈስ ተነሳስተን አዲስና የበለጸገች ኢትዮጵያን እንዳንገነባ ያግዱናል።
በፍልስፍና፣ በሶስዮሎጂና በሳይኮሎጂ መነጽር እየተመረመሩ ለንባብ የማይቀርቡ ጽሁፎችና ተራ ውንጀላዎች ዕውነትን ከውሸት ነጥለን ማየት እንዳንችል ያደርጉናል። ከዚህ ስንነሳ፣ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ የኃይል አሰላለፍና ዕውቀትን በአዲስ መልክ ማደራጀትና ማስፋፋት፣ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ኤሊቶችም ይህንን ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ በየአገሮች ውስጥ አዲስ ዐይነት ህብረተሰብአዊ የኃይል አሰላለፍና የህሊና አወቃቀር እንዲፈጠር እንዳደረግና ይህ በራሱ ለዕውነተኛ ዕድገትና ስልጣኔ እንቅፋት እንደሆነ መረዳቱ ዛሬ ላለንበት ህብረተሰባዊ ውዝግብና ድህነትና ራሱን የቻለ ምክንያት ሆኖ እንደሚታይ መረዳቱ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛም ። ነገሮችን በደንብ ተገንዝበን እንደሆነ በአብዛኛው የላቲን፣ የማዕከለኛው አሜሪካ፣ በአሺያና በአፍሪካ አገሮች ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አንድም ቦታ የተዋጣለትና የተስተካከለ ስርዓት መገንባት ያልተቻለው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተፈጠረውና በተስፋፋው የኃይል አሰላለፍ፣ ህብረተሰብአዊ አደረጃጀትና የተሳሳተ ዕውቀት መስፋፋት ጋር የተያያዘ መሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም።
ይህም በመሆኑ የኮሙኒስት ርዕዮተ-ዓለም ባልተስፋፋቸው እንደ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ቺሌ፣ ኤልሳባዶርና ፓራጓዋይ እንዲህም አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በስድሳኛውና በሰባኛው እንዲሁም በሰማኒያኛው ዓመተ ምህረት ስልጣን የጨበጡትና ለብዙ መቶ ሺህ ህዝብ መሞት፣ ወደ እስር ቤት መወርወርና መሰደድ ምክንያት የሆኑት ፋሺስታዊ ስርዓቶች ከኩሙኒዝም ጋር የተያያዙና የሚደገፉ ሳይሆን፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በጠቅላላው የምዕራቡ ዓለም ይደገፉ የነበሩና ጥብቅም ግኑኝነት የነበራቸው ነበሩ። አብዛኛዎቹ የሲቪልና የሚሊታሪ ቢሮክራቶች የሰለጠኑት ከምዕራቡ በመጣ ርዕዮተ-ዓለም እንጂ በሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም አልነበረም። ስለዚህም ክስ በሚቀርብበት ጊዜ የታሪክን ሂደትና የየአገሮችን የኃይል አሰላለፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያያዘውንና የሚደጋገፈውን የአገዛዝ ሰንሰለት መመርመሩ ዛሬ ያለንበትን የተተራመሰና የተወናበደ ሁኔታ እንድንረዳ ያደርገናል። በመሆኑም ምሁርና ታጋይ ነኝ ባይ ሁሉ ወደ አንዳች ፍርድና ድምደማ ከመድረሱ በፊት የተማረ አስከሆነ ድረስ የህብረተሰብ ዕድገትን ታሪክና የኃይል አሰላለፍ፣ እንዲሁም አንዳንድ አገሮች ታሪክን ለምን ለመስራት እንዳልቻሉና የተዋጣለት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ ህብረ-ብሄር መገንባት እንዳልቻሉ ተመራምሮና አጥንቶ ማቅረቡ ታሪካዊና የሞራል ግዴታ ነው።
ያም ሆነ ይህ የተማሪው እንቅስቃሴ የትግል ፍልስፍና የጊዜው ሁኔታ ነፀብራቅ ወይም ጊዜው የወለደው ነው ማለት ይቻላል። የተማሪው እንቅስቃሴ በጊዜው ከተዋወቃቸው ሊትሬቸሮች አልፎ ባለመሄዱና ትግልና ድልን በዚያው መነጽር ማየት መቻሉ የሚያስደንቅ ባይሆንም፣ በሌላ በኩል ግን በሌሎች አገሮች ያልታየ መተራረድ ውስጥ መግባቱ ራሱን የቻለ ምርምር ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህ ጉዳይ ከዚህ ጸሀፊ አቅም በላይ የሆነና ቦታውም የሚፈቅድ ስላይደለ ሌሎች የበኩላቸውን ምርምር ቢያድርጉ ለአገራችን ችግር ግንዛቤ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ። ይሁንና ግን በጊዜው የተነሱት የዲሞክራሲ ጥያቄዎችና የመሬት ላራሹ ጉድይ ትክክል አይደሉም ማለት ኢትዮጵያ በድሮ መልኳ ትቀጥል፣ መሻሻል አይስፈልጋትም እንደማለት ይቆጠራል። በተጨማሪም በአብዮቱ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ የትግል ምዕራፍ ውስጥ መግባት እንደቻለና ነፃነትም እንደተቀዳጀና በራሱ ላይም መተማመን አንደጀመረ የማይካድ ሀቅ ነው።
በመሆኑም በጊዜው የነበሩ አንዳንድ የተገለጸላቸው ምሁራን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጨለማ ስርዓት እንዲላቀቅና ብርሃንን አንዲጎናጸፍ ለማድረግ የበኩላቸውን ከፍተኛ ጥረትና አስተዋፅዖ ለማድረጋቸው የሚያጠራጥር አይመስለኝም። ይሁንና ግን የተወሰነው ኤሊት የህብረተሰብአችንን አወቃቀር በደንብ ባለመገንዘቡና ከውጭ የሚሸረበውን ሴራ ለማጤን ባለመቻሉ በእልከኝነትና በስሜት ብቻ በመገፋት ለብዙ መቶ ሺህ ወጣት መሞትና የአንድ ትውልድ ምሁር ተሟጦ እንዲያልቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል ማለት ይቻላል። ቀድሞውን ዲሞክራሲያ ኑሮ ጋር መለማመድ፣ መቻቻልና መደማመጥ የሚለውን ከጭንቅላቱ ጋር ማዋሃድ ባለመቻሉ በጥቂቶች ስህተትና እልከኝነት የተነሳ የብዙ መቶ ሺህ ወጣትና የአንድ ትውልድ ምሁራን ህይወት እንዲጠፋ ተደረገ። በዚያን ጊዜ በተሰራ ስህተት፣ ከዚያ በኋላ አንድ የወጣለት ምሁር ማፍራት አልተቻለም። ለማንኛውም በጊዜው የነበረውን ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ትግል የተደረገውን ሙከራና ክሽፍት መረዳት የምንችለው በስሜትና በጥላቻ በመነሳሳት ሳይሆን በሳይንስና በዲያሌክቲክ መነጽር ሁኔታውን ስንገመግም ብቻ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በነፃነትና የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን ሲባል የተካሄዱትና የሚካሄዱት ትግሎች በሙሉ የመጨረሻ መጨረሻ ለህዝባዊ ዕልቂትና ለድህነት የዳረጉን ሳይንሳዊውን የትግል ዘዴ፣ አርቆ አሳቢነትንና በዚህ አማካይነት የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የሚያስችላቸውን መንገድ ለመከተል ባለመቻላችው ነው። የየብሄረሰብ ነፃ አውጭዎችም ራሳቸው የህብረተሰብአችን የማቴሪያልና የህሊና አወቃቀር ውጤቶች በመሆናቸው አርቀው በማሰብ ለአጠቃላይ ዕድገትና ህብረተሰብአዊ መተሳሰር መነሳት ያልቻሉት በዚህም ምክንያት ነው። በብሄረሰብ ደረጃ ብቻ በመደራጀት ነፃነትን የሚቀዳጁ የመሰላቸው ጥቂት የየብሄረሰቡ ኤሊቶች የትግልን ትርጉም የተረዱት ከሳይንስ ውጭ በማድረግና ሙሉ በሙሉ በአመጽ ላይ ብቻ እንዲመረኮዝ በማሰባቸው ነው። ዓላማቸውንም ለመድረስ ሲሉ የአገራችንን አንድነትና ዕድገት ከሚፃረሩ አደገኛ ኃይሎች ጋር መሰለፋቸው ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥ ደግሞ ህዝባዊ ዕልቂት እንዲመጣ የማያደርጉት ነገር አልነበረም። የትግላቸውም ዓላማ ሌላውን የኢትዮጵያ ግዛት በማተረማመስ የራሳቸውን ነፃነት ብለው የተረጎሙትን መቀዳጀት ነበር ።
ይህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ ሂደታቸውና አስተሳሰባቸው ግን የተመኙትንና የፈለጉትን ነፃነት እንዲቀዳጁ በፍጹም አላስቻላቸውም። ዛሬ ኤርትራ ውስጥ የሰፈነውን ፋሺስታዊ አገዛዝና የወጣቶች እልቂትና መሰደድ፣ እንዲሁም አገዛዙ አሁንም ቢሆን ከጦርነት ዓለም አለመላቀቁ የሚያረጋግጠው የቱን ያህል ቂም-በቀለኝነትና እልከኝነት ከጭንቅላቱ ጋር ተዋህደው እንደሚያሰቃዩት ነው። ፍልስፍናውም በዚህ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የተረከባቸውን ከተማዎችና ኢንስቲቱሽኖች በስነ-ስርዓት ማስተዳደር አቅቶት እያፈራረሰና ህዝቡን ወደ ድህነት እየመራው እንደሆነ ሁኔታዎች ያረጋግጣሉ። ይሁንና በኤርትራዊነትና በጥላቻ እንዲሁም በአጉል ኩራት ጭንቅላቱ የታወረው የተወሰነው ኤርትራዊ ወጣት የአቶ ኢሳያስ መንግስት የሚሰራው ትክክል እንደሆነና ነፃነትም የሰፈነ እንደሆነ ለማሳመን በመሞከር ላይ ነው። የሚገርመው ነገር ብዙ ኤርትራውያን እዚህ አውሮፓ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነበት አገር እየኖሩ ለምን ያሉበትንና የሚኖሩበትን ሁኔታ ከአገራቸው ሁኔታ ጋር ማወዳደር እንደማይችሉ ነው?
በመሆኑም በሁላችንም ዘንድ ያለው መደናበርና ግራ መጋባት ህብረተሰብና ህብረ-ብሄር የሚባሉትን መሰረተ-ሃሳቦች ከጭንቅላታችን ጋር ለማዋሃድና ወደዚህ ለመድረስ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ማድረግ የሚገቡንን ነገሮች ለማወቅ ባለመቻላችን ወይም ባለመፈላጋችን የተነሳ ሁላችንም ወደ ቡድናዊ ስሜት በማምራት በተለይም በአብዮቱ ወቅት ድርጅቶችን በማምለክ ዛሬ ላለው ትርምስና ዓላማ-ቢስነት መንገዱን አመቻችቶ ሰጥቶናል ማለት ይቻላል። ወደ ብሄረሰብ ትግልና ወደ ድርጅት ምስረታና በዚህ አማካይነት ትግል ማካሄድና ድልን መጎናፀፍ ይቻላል የሚለው አጉል ፈሊጥ በጭንቅላታችን ወስጥ በመቀረጹ ትልቁን የአገርና የህብረተሰብ ምስረታና አገነባብ ዘዴ እንድንዘነጋ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን አገራችን ለውጭ ኃይሎች ወረራ እንድታመች መንገዱን ሁሉ አዘጋጅተናል ማለት ይቻላል። ጠቅላላው የትግላችንን ትርጉምና በተለይም ደግሞ የተወሰነው የተማሪው እንቅስቃሴ ክንፍና የተለያዩ ብሄረሰቦች ችግር ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረተ-ሃሳቦች ካለመረዳት የተነሳ በመሃከላችን በፈጠርነው ትርምስና የርስ በርስ ፍጥጫ የቱን ያህል የውጭ ጠላትን እንደጋበዝንና በዘለዓለም ድህነት ውስጥ መኖር የተገደድን መሆናችንን አለመረዳታችን ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደኛ ያሉ ደካማና ግራ የተጋቡ አገሮችን በትርምስ ዓለም ውስጥ እንድንኖር የተደገሰልንን ድግስ ዞር ብለን ለማየት ያለመቻላችን የቱን ያህል የአስተሳሰብ ችግርና ዓለም አቀፋዊውን ሁኔታ መረዳት እንደተሳነና እንደሚሳነን ነው። እንዲያው ታጋይ ቢሞት ትግል አይሞትም እያልን አሁንም ቢሆን ብዙ ወጣቶችን በማሳሳት የምናደርገው ቅስቀሳ የቱን ያህል ሚናችንና የህብረተሰብን ትርጉም ያለተረዳን መሆናችንን ነው። ይሁንና ግን እዚህና እዚያ በመራወጣችን የታገልንና ለህዝባችንም አንድ ነገር ያደረግንለትና የምናደርግለት ይመስለናል። እዚህ ላይ ነው ትልቁ ትራጄዲ!!
እስካሁን ድረስ ያለብን ችግር እያንዳንዳችን ድርጊታችንን ለመመርመር ፕላቶን እንደሚለን ጭንቅላታችንን ወደ ውስጥ ማንበብ አለመቻላችን ነው። እያንዳንዳችን የምንሰራው ትክክል ስለሚመስለንና እዚህና እዚያም በራሳችን ዓለም እየተሽከረከርን ስለምንኖር አስተሳሰባችንና ድርጊታችንን መመርመር በፍጹም አልቻልንም። በማስፈራራት፣ በመሽሎክሎክና በተንኮል መንፈስ የምናካሂደው አጉል ትግል አሁንም ቢሆን ለማሰብና ለመመራመር እንዲሁም በግልጽ ለመከራከር የሚያመች አይደለም። ይህ ዐይነቱም አስተሳሰብ የትግል ዘዴ ሆኖ በመታየቱ ሁሉም በመፋራት ዓለም ውስጥ ያለ ነው የሚመስለው። በአለፉት ስላሳ ዐመታት እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ የምንቀሳቀስም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ራስን ለመጠየቅና በመመርመር ከዚህም በመነሳት በአዲስ ቲዎሪና ሳይንስ ትግላችንን እንደገና ሀ ብለን ለመጀመር ከፍተኛ ዕድል ነበረን። እዚህ በምዕራቡ ዓለምና አሜሪካ ውስጥ አየኖርን ዕድሉን መጠቀም ባለመቻላችን አሁንም ቢሆን በድሮው ዓለም ውስጥ ነው የምንኖር የሚመሰለው። አብዛኛዎቻችን ለመታረምና ራስን ለማረም ዝግጁ አይደለንም። ሌሎቻችን ደግሞ ለምን ዐይነት ህብረተሰብ እንደምንታገል በቅጡ የተገነዘብን አይመስለኝም። እንዲያው ብቻ ትግል ትግል እያልን እዚህና እዚያ እንሯሯጣለን።
ያም ሆነ ይህ፣ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በአውሮፓ የትግል ታሪክ ውስጥ ትግል ሲባል ተፈጥሮንና ህዋን መቃኝተና ህጋቸውን አጥንቶ በምድር ላይ ገነትን መመስረት ነው። ለዚህ ደግሞ ፍልስፍና መሰረት ሲሆና፣ በፍልስፍና አማካይነት ብቻ ነው ወደ ሳይንስና ወደ ቴክኖሎጂ ማምራት የሚቻለው። ሰብአዊነት በመባል በግሪኩ የስልጣኔ ዘመን የተጀመረው እንቅስቃሴ ዋና ዓላማው የሰውን ልጅ ከአውሬ ባህርይው በማላቀቅ ምድራዊት ገነትን በመመስረት በመፈቃቀር እንዲኖር ነው። የሰብአዊነት ዋናው መሰረቱም ዕውቀት ሲሆን፣ በዚህ አማካይነት የተፈጥሮንና የኮስሞስን ህግ መረዳትና አዳዲስ መሳሪያዎችን በመስራት በተፈጥሮ ላይ የተወሰነ ቁጥጥርን ለመቀዳጀት ነው። በእኔ ግምትና ዛሬ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና በአገራቸንም ያለውን ትርምስና ድህነት ስመለከትና ስመረምር ይህንን ሎጂካዊ ሂደት ያልተከተለ ህብረተሰብ የግዴታ መዘበራረቅንና አመጸኝነትን ነው የሚያስከትለው። ይህ ሁኔታ ደግሞ የግዴታ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ እንዲያደርግ በመገፋፋት ለአካባቢ መዛባትና ለተለያዩ አትክልቶችና ዛፎች መውደም ምክንያት ይሆናል። ተፈጥሮ እንክብካቤ የሚያስፈልጋት መሆኑ ቀርቶ ወደ ተራ ተበዝባዥነት በመቀየርና በኢኮኖሚስ ስሌት በመታየት የአንድ አገር ህዝብ ህይወት አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ይገደዳል።
ታሪክ እንዳይሰራና ተረጋግቶ እንዳይኖር ይረገማል። ስለሆነም በአገራችን ምድር ትግል ሲጀመር የተገላቢጦሽና በኋላ ደግሞ በአብዮቱ ዘመን በሰው ህይወት ላያ ያነጻጸረ ሁኔታ የተፈጠረው ይህንን ሳይንሳዊ መንገድ ባለመከተላችን ብቻ ነው። በአገራችን ምድር ለዲሞክራያዊ መብቶች መከበር የተደረገው ትግል ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ተሃድሶ ያልነበረውና፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ማንነቱን በመረዳትና የተፈጥሮን ህግ በመገንዘብ ወደ አዲስ ስልጣኔ የሚያመራው ሳይሆን፣ ትግል ሲባል በማሸነፍና በመሸነፍ መሃከል የሚገለጽ በመሆኑና ሌላውን በዝግታና በጥሞና በማሳመን ሳይሆን፣ ታምናለህ አታምንም የሚለውን አጉል አካሂድ በማስቀደማችንና በቂም-በቀለኝነት በመገፋፋታችን ርስ በርስ ለመፋጀት ሁኔታውን ለማመቻቸት በቃን። በአጠቃላይ ሲታይ ይህ ጉዳይ ለህብረተሰብአዊ ትርምስ ሁኔታዎችን ያመቻቸና በዚያው ውስጥ የተፈጠሩ አዳዲስ ኃይሎች ወደ አመጽ በማምራት አገራችን ወደ አጠቃላይ ጦርነት ውስጥ እንድትወድቅ ተደረገ።
ከዚህ ስንነሳ በተለይም በአለፉት 23 ዐመታት በአገራችን ምድር የተከሰተውንና የተፈጠረውን አዲስ ሁኔታ መረዳት የምንችለው ዲያሌክቲክን ወይም ሳይንሳዊ መንገድን የምርምር ዘዴ ማድረግ የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። የአገራችንን ሁኔታ፣ የህብረተሰብአችንና የአገዛዙን የህሊና አወቃቀር በደንብ መረዳት ካልቻልን ደግሞ ትግል ትግል እያልን በየቦታው የምናካሂደው ጩኸት የመጨረሻ መጨረሻ አዎንታዊ ውጤት ሊኖረው አይችልም። ስለሆነም ያለፈውን ታሪክ ብቻ ሳይሆን መገምገም ያለብን ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት የተካሄደውንም ትግል መመርመሩ ለዛሬው ችግራችን የተቀራረበ መፍትሄ መስጠት ይቻላል ብዬ አምናለሁ።
የተቃውሞ ፖለቲካ ትርጉምና የተቃዋሚው የትግል ዘዴ!
በመጀመሪያ ደረጃ ስለትግል በምናወራበት ወይም ትግልን አስመልክተን ስለዲሞክራሲና ስለነፃነት አስፈላጊነት ስንታገልና ስንጽፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእኛ ውክልና አልሰጠንም። ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ በስሟ የሚንቀሳቀስ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ድርጅት የግል ሀብት አይደለችም። እስከሚገባኝ ድረስ ትግል ስንጀመር አንደኛ በፈቃደኝነት (Volentaristic) ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሞራልና ምሁራዊ ግዴታ ስላለብን የየበኩላችንን አስተዋፅዖ ማድረግ አለብን ከሚለው ዕምነት በመነሳት ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ በተለይም የፖለቲካ ስልጣን እንይዛለን ብለው የሚታገሉ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች በራሳቸው ውስጣዊ ፍላጎት በመነሳትና በታሪክ ማህደርም ስማቸው እንዲመዘገብ የሚፈልጉ ካለምንም ፕሪንስፕልና ቁርጥ ዓላማ የሚታገሉና ሰፊውን ህዝብ የሚያሳስቱ እንዳሉ መታወቅ አለበት። ይህም ማለት ሁሉም ስለትግል በሚያወራበት ጊዜ ለአንድ ዓላማና በአንድ ርዕይ ወይም ፍልስፍና በመመራት ሳይሆን የሚታገለው ወይም አገዛዙን የሚቃወመው፣ እንደ ንቃተ-ህሊናውና ዕውቀቱ የተለያየ የትግል ስልትና ዓላማ በመጠቀም ነው የሚታገለው።
በሌላ ወገን ደግሞ አብዛኛዎቻችን ማለት ይቻላል ብዙም ሳናወጣና ሳናወርድ በስሜት በመገፋፋትና በአንዳንዶች ንግግርና ዝና በመሳብ ትግል የሚባለው ወዴት እንደሚወስደን የማናውቀው ውስጥ ገብተን ራሳችንን የምናሰቃይ አለን። የነፃነትን ትርጉም በደንብ ሳንረዳና ውስጣዊ ነፃነት ሳይሰማን የሌላውን ንግግር በማሰተጋባት የምንታግል የሚመስለንና ሌላ አመለካከት ካለው ጋር የማንግባባ ወይም የምናኮርፍ አለን። ትግል የሚባለውን ፈሊጥ ስንጀምር አብዛኛዎቻችን ለትግል የሚያመች በቂ ኢንፎርሜሽንና ዕውቀት ይኑረን አይኑረን የመረመርንና የምንመረምር አይመስለኝም። እስከምገምተው ድረስ እኔም ራሴም ብሆን ትግል ስጀምር በቂ ኢንፎርሚሽን ኖሮኝ ወይም አውቄ ሳይሆን ወደ ትግል ዓለም ውስጥ ዘልዬ የገባሁት በሁኔታው በመገፋፋት ብቻ ነው። በትግል ታሪክ ውስጥ የተማርኩት ነገር ቢኖር ትግል ሲባል እንዲያው በጭፍን፣ በእልከኝነት፣ በደመ-ነፍስ፣ በቂም-በቀልነትና በአጉል ተንኮል የሚካሄድ ሳይሆን የማያቋርጥ ጥረትንና ጥንቃቄን የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት ነው። በመሆኑም ትግል ሲባል በተቻለ መጠን አንዱን የሚያቀርብ ሌላውን የሚያገል ሳይሆን ለጠቅላላው ህብረተሰብ መቆምና የተሳሳተውን ደግሞ በጠላትነት በመፈረጅ መነሳሳት ሳይሆን በማስተማር ለቀና ነገር እንዲሰለፍ፣ ካለበለዚያ ደግሞ የራሱን ኑር እንዲኖር መመከር ነው።
በሌላ አነገጋር ትግል ዕውቀትን ያሰቀደመ መሆን ሲገባው ዋና ዓላማውም በተለይም በድህነት ዓለም ለሚሰቃይ ህዝብ ከጨለማ አውጥቶ የቀን ብርሃንን እንዲያይ ማድረግ ነው። ከዚህም በላይ ስለትግል ሲወራ ለናት አገር መቆምና የተከበረችና የበለጸገች አገር ለመገንባት መታገል ማለት ነው። በመሆኑም ትግል ሲባል በሳይንስ መነጽር እስካልተፈተነና ለአንዳንድ ግለሰቦችና ለድርጅቶች ብቻ የሚጣል ከሆነ እንደ የካቲቱ አብዮት በዚያው መልክ ባይሆን እንኳ በሌላ መልክ ትርምስ ውስጥ መግባታችን የማይቀር ነው። ልክ እንደሌሎች የነፃነት ትግል ከተካሄደባቸው አገሮችና አሁንም ቢሆን ዕውነተኛውን ነፃነት እንዳልተቀዳጁ አገሮች የኛም አገር ዕጣ ከስድሳና ከሰባ ዓመት በኋላ አለመሻሳል ይሆናል። ስለሆነም ስለትግል በምናወራበት ጊዜ ግልጽ ማድረግ ያሉብን አያሌ ነገሮች አሉ ማለት ነው። ትግልን ከድርጅትና ከግለሰብ ባሻገር ማየት አለብን። ትግል ሳይንሳዊ፣ ፍልስፍናዊና የቲዎሪ መሰረት ያለውና፣ ማንኛውም ሁኔታና ድርጊት በሳይንስና በዲያሌክቲክ መነጽር መመርመር እንዳለበት መገንዘብ አለብን።
ከዚህ በመነሳት ተቃውሞ የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ በመጠኑም ቢሆን እንመርምር። በተለይም የተቃውሞን ትርጉም በሚመለከት ባለፉት 23 ዐመታት ከፍተኛ መደነባበርና የአስተሳሰብ ግድፈት ይታያል። በአንድ አገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች የተቃዋሚ ፖለቲካ እንካሂዳለን ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? መቃወም ማለት ምን ማለት ነው? የተቃዋሚ ፖለቲካ በየአራት ዐመቱ በሚደረግ የምርጫ ውድድር ብቻና አንዳንድ ጊዜ ድምጽን በማሰማትና የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት በመፍጠርና የይድረሱልን ጩኸት በማሰማት የሚገለጽ ነው ወይ? ወይስ ልዩ ዐይነት ትርጉም አለው? በእኔ ዕምነት አንድ የፖለቲካ ድርጅት የተቃውሞ ፖለቲካ አካሄዳለው ሲል የሚያካሂደው የተቃውሞ ፖለቲካ ካለበት ሁኔታ የሚነሳና የህዝቡን ፍላጎት ያካተተና የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት። አንድ የፖለቲካ ድርጅት የተቃውሞ ፖለቲካ አካሂዳለው ሲል የራሱን ፍላጎት ለማንፀባርቅና በጭንቅላቱ ውስጥ የቀረጸውን ስዕል በህዝብ ላይ ለመጫን ሳይሆን በሳይንስ የተፈተነ ዛላቂ መፍትሄ በማቅረብ የተከበረችና የበለጸገች አገር ለመገንባት ነው።
አንድ ድርጅት ይህንን ወይም ያኛውን ርዕዮተ-ዓለም ከመከተሉና ፕሮግራምም ከመንደፉ በፊት በምሁር እንቅስቃሴ ውስጥ ማለፍና በትግልም የተፈተነ እንዲሁም ህዝብን ያስተማረና ማስተማር የሚችል መሆን አለበት። ይህ ተቀዳሚው ተግባር ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ተቃዋሚ ነኝ ሲል አንድ ስልጣንን የጨበጠ ኃይል የሚያካሂደው ጠቅላላው ፖሊሲ ህበረተሰብአዊ ባህርይ የለውም፣ ለህዝቡ ሀብት የሚፈጥር አይደለም፣ አንድን ህዝብ ከድህነት የሚያላቅቀው አይደለም፣ የስይንስና የቴክኖሎጂ ባላቤት ሊያደርገው አይችልም፣ ባህላዊና ህብረተሰብአዊ ትስስርን አያመጣም፣ ብሄራዊ ነፃነትን ያስደፍራል፣ የውጭ ኃይል ታዛዥ በመሆን አንድ ህዝብ በትርምስና በጦርነት ውስጥ እንዲኖር … ወዘተ ያደርጋል ብሎ በመገመትና በማሰብ ነው። ይህም ማለት አንድ ስልጣንን የጨበጠ አገዛዝ አንድን ህዝብ አደጋ ላይ የሚጥለው ከሆነና በዘለዓለማዊ ድህነት ውስጥ እንዲኖር የሚያደርገው ከሆነ ተቃዋሚ ፖለቲካ አካሂዳለው የሚለው የፖለቲካ ድርጅት አገርን በተለያዩ መንገዶች ከሚያጠፋ ጋር በመቀመጥ ሊደራደር አይችልም ማለት ነው። በመሆኑም የአንድ ፖለቲካ ድርጅት የተቃውሞ ፖለቲካ ጭፍን አካሄድ መከተል ሳይሆን አንድ ስልጣንን የጨበጠ አገዛዝ አገርን የሚያፈራርስና ህዝብን የሚያተረማምስ ፖለቲካ ለምን እንደሚከተልና ርዕዮተ-ዓለሙና ጠቅላላው ፖሊሲ ምን እንደሆነ በመመርመር አማርጭና ፍቱን መፍትሄ ማቅረብ አለበት። ይህንን ሳያደርግ የፖለቲካ ድርጅት መስርቻለሁ፣ የተቃውሞ ፖለቲካ ነው የማካሂደው ኑ ተከተሎኝ እያለ እዚህና እዚያ ቢራወጥና ተደማጭነትን ለማግኝት ቢችል እንደዚህ ዐይነቱ ድርጅት ስልጣን በሚይዝበት ጊዜ የተሻለ ነገር ማምጣት በፍጹ አይችልም ማለት ነው። ዓላማውም መሰረታዊ የሆነ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ማምጣት ሳይሆን በስልጣን ላይ ቁጥጥ በማለት የራሱን ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ነው የሚታገለው።
ከዚህ ስንነሳ በአለፉት 23 ዐመታት የወያኔን ፖለቲካ አንቃወማለን፣ አገራችንን “ማዳን” አለብን ብለው እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ግለሰቦች ተፈጥረዋል። አብዛኛዎቹ የሊበራል ዲሞክራሲን ርዕዮተ-ዓለም እናራምዳለን ሲሉ፣ እንዳንዶቹ ደግሞ የሶሻል ዲሞክራቲክና አሁን ደግሞ የማዕከለኛ ቀኝ (Center Right) ፖለቲካ ነው ፍልስፍናችን፣ በዚህም መሰረት ነው የኢትዮጵያን ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለማዋቀር የምንፈልገው ብለው አገዛዙን እንደሚቃወሙ የሚነግሩን አሉ። ይሁንና ግን እነዚህ የተለያየ ርዕይ የሚመስል በይዘት ግን ተመሳሳይ የሆነ ፖለቲካ የሚያራምዱ ድርጅቶች ሁሉ ፍልስፍናቸው ምን እንደሆነና የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር እንዴት እንደሚፈቱና ጠንካራ አገርስ እንዴት እንደሚገነቡ ሲያስረዱን አይታይም፤ በጽሁፍም ተንትነው ያቀረቡት ነገር የለም። ሁሉም ድርጅቶች ግን ለአገዛዙ አማራጭ እንደሆኑና የተሻለም ፖለቲካ የሚያካሂዱ ለመሆናቸው የምዕራቡን ዓለምና አሜሪካንን ለማሳመን የማያደርጉት ጥረት የለም። አንዳዶቹ እየተጋበዙ ስለአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ገለጻ ሲሰጡ፣ ሌሎች ደግሞ ስኮላርሺፕ እየተሰጣቸው የወደፊት የአገሪቱ መሪዎች እንደሚሆኑ እየታጩና በመጠባበቅም ላይ ይገኛሉ።
ይሁንና ግን እነዚህ የተለያየ ስም ይዘው የሚታገሉ ድርጅቶች ሁሉ እዚያው በዚያው ደግሞ ርስ በርሱ የሚጋጭ ፖለቲካ ሲያካሂዱ ይታያል። ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእነዚህ ድርጅቶች በሙሉ የውክልና መብት አልሰጣቸውም። የምዕራቡ መንግስታት ጋም ሄዳችሁ ተማጠኑልኝ አላለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ከእነዚህም ሆነ ከምሁሩ የሚፈልገው ነገር በሳይንስና በፍልስፍናና ላይ የተመረኮዘ ፖለቲካ እንዲካሄድለትና አገራችንም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ከውርደት ተላቃ የተከበረችና ጠንካራ አገር እንድትሆን ብቻ ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘው የውጭ ኃይል ተላላኪና ጦርነትን አራማጅ ኃይል በአገራችን ምድር ስልጣንን እንዳይጨብጥና የድህነቱን ዘመን እንዳያራዝምበት ነው። በአገር ቤት ውስጥም ሆነ በውጭ የኢትዮጵያን ህዝብ እንወክላለን ብለው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ባሻገር ሌሎች ደግሞ ከእንቅልፋቸው የባነኑ ይመስል ሰላሳና አርባ ዐመታት የተደላደለ ኑሮ ከኖሩ በኋላ ምንም ዐይነት የፖለቲካ ባዮግራፊ ሳይኖራቸው ወያኔን እንቃወማለን በማለት እዚህና እዚያ በመሯሯጥ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣት የሚያሳስቱ አሉ። አሁንም ነፍሳችን አለ እየተንቀሳቀስን ነን የሚሉ ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ ወያኔን እንዳለ ከመጥላትና አንዳንድ ነገሮችን ከመቃውም በስተቀር የወያኔን አነሳስና፣ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረጋቸውንና የሚያደርጋቸውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመመርመርና ይህ ከውጭው ዓለም ጋር የተያያዘና የአሜሪካኖች ፕሮጀክት መሆኑን ሲያስተምሩን አይታይም።
ስለሆነም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሙሉ ወያኔ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር ያካሄዳቸውንና የሚያካሄዳቸውን ፖሊሲዎች በሙሉ የውጭው ኃይል ምንም እጁ የለበትም፤ ስለሆነም እኛ በምዕራቡ ላይ የዲፕሎማሲ ጭነት በማድረግ እንመልሰውና የምንፈልገውን ነገር አናካሄዳለን የሚል አጉል የፖለቲካ ስሌትን የሚከተሉ እንጂ አዲስና ጠንካራን ኢትዮጵያን እንዲሁም ከአሜሪካን ቁጥጥር ውጭ የሆነ ዘላቂነት ያለው የሰላም ፖለቲካ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ለውይይት አቅርበው ሁላችንም እንድንመካከርበትና እንድንከራከር አላደርጉም፤ ሲያደርጉም አይታይም። ይህ ዐይነቱ ግልጽነት የሌለውና በሳይንስና በቲዎሪ ያልተመረመረና ያልተደገፈ የተቃዋሚው ኃይል ፖለቲካ መደነባበርንና ተስፋ ማስቆጠርን ከማስከተሉ በስተቀር ወያኔን ለመፈታተንና ለመጋፍጥ የሚያስችል ፖለቲካ አይደለም። ይህም የሚያሳየው ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት ዘንድ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የዓለምን የፖለቲካ አወቃቀር የመረዳት ችግር እንዳለና፣ አብዛኛዎቹም ድርጅት ነን ባዮች የጥናት መመራመሪያ ኢንስቲቱሽንና በደንብ የተደራጀና የተዋቀረ የፖለቲካ መሰረት እንደሌላቸው ነው። ይህ ሁኔታ ወያኔን እንደፈለገው አገራችንን እንዲያፈራርስ ሲረዳው፣ የምዕራቡ ኃይል ደግሞ አማራጭ የለም በማለት አገዛዙን በመደገፍ በጥፋት ፖለቲካው እንዲገፋፋበት እየረዳው ነው።
ለመሆኑ የምዕራቡ ኃይል አሜሪካንንም ጨምሮ የኢትዮጵያን ብልጽግናና ጥንካሬ እንዲሁም አንድነት ይሻሉ ወይ? በታሪክ ውስጥ እንደታየውና፣ በተለይም ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ ቢያንስ ከሁለት መቶ ዐመት ጀምሮ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተብለው በሚጠሩና በምዕራቡ መሀከል ያለው ግኑኝነት የሎሌና የጌታ ግኑኝነት ነው። የሶስተኛው ዓለም አገሮች ጥሬ-ሀብት አቅራቢ ሆነው እዚያው በዚያው እየተንደፋደፉ መቅረት አለባቸው። ይህንን የተረዱ እንደ ጃፓንና ቻይና ከዚህ የኢምፔሪያሊስት ሰንሰለት ውስጥ ለመላቀቅና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የማያቋርጥና ቆራጥ ትግል ማካሄድ ነበረባቸው። ቻይናውያን ከጃፓን ነፃ ወጥተው የራሳችንን መንገድ እንክተላለን ሲሉ ይህንን የኢምፔሪያሊዝም ሰንሰለት በመበጣጠስ ነበር ቀሰ በቀስ አገራቸውን መገንባት የቻሉት። ተመልሰው የኢምፔሪያሊዝም ጉያ ስር በመግባት አይደለም አገራችንን እንገነባለን ብለው የነሱት። እየወደቁና እየተነሱም ቢሆን በራሳቸው ጥረትና ውስጣዊ ጽናት ዛሬ ወደ ኃያለ-መንግስትነት ለማምራት በቅተዋል።
ቆራጥና የበሰለ ትግል ማካሄድ ያልቻሉና ምሁራዊ ድክመት ያላቸውና የምዕራቡን ዓለም እንደ አምላክ የሚያመልኩ እንደ ኢትዮጵያ የመሰሉ አገሮች ደግሞ እዚያው በዚያው ተንደፋድፈው እንዲቀሩ ተገደዋል። እጣቸው ድህነት፣ ለማኝነትና የብሄራዊ ውርደት ሆኗል። በመሆኑም የምዕራቡ ዓለምና አሜሪካም ጭምር ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ብሄራዊ ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ የሚያስችላቸውን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከምዕራቡ ዓለም ማግኘት ይችላሉ፣ የምዕራቡ ዓለም የጠነከረች ኢትዮጵያን ይፍለጋል የሚለው አሰተሳሰብ ከፍተኛ የፖለቲካ ጅልነት ብቻ ሳይሆን ትጥቅ የሚያስፈታና በዘለዓለም ድህንተ ውስጥ እንድንኖር የሚያደርገን ነው። በዓለም የፖለቲካ ታሪክና በህብረ-ብሄር ምስረታ ሂደት ውስጥ ያልታየ ነገር ነው። ይህ እጅግ አደገኛ አስተሳሰብ ከአገራችን ምድር እስካልጠፋ ድረስና፣ አንዳንድ አሳሳስች ምሁራን በጋጋታ ጽሁፋቸው እንዲገፉበት የምናግዛቸው ከሆነ እኛም በበኩላችን ወያኔ የሚያደርገውን ጥፋት በሌላ መልክ እናካሄዳለን ማለት ነው።
ከላይኛው ሀተታዬ ስነሳ፣ ያለፉትን የሃያ ሶስት ዓመታት የተቃዋሚውን ትግልና -ትግል እንበለውና- የህዝባችንን ብሶት ለተመለከተ መገንዘብ የምንችለው ትግሉ የኢትዮጵያን ነበራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቅና የአገዛዙን ባህርይና ከውጭው ዓለም ጋር ያለውን መተሳሰር ያላገናዘበ ወይም መመልከት የማይችል ነው ብል የምሳሳት አይመስለኝም። የአገዛዙን አመጣጥና የስልጣን አያያዝ ከሞላ ጎደል ከዚህ ቀደም ‹‹ከአምባገነን ባሻገር …›› በሚለው ጽሁፍ ውስጥ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በዚህ ላይ አልመለስበትም። ለማሳሰብ የምፈልገው ግን በዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ በተለይም አገዛዙ ባላፉት 23 ዓመታት የተከተለውን የኢኮኖሚና አጠቃላይ ትርምስ የፖለቲካ ሂደት ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በፖለቲካ ሳይንስ መነጽር የመረቃ ትንተና መስጠት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የሚካሄደው ትግል ስልጣንን ከመጨበጥ ወይም በስልጣን ውስጥ ከመካተት ተሻግሮ የሚሄዳ አይደለም። በመሆኑም ይህ ዐይነቱ ግራ የተጋባና ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው የተቃውሞ ፖለቲካ በአገራችን ምድርም ሆነ በዲያስፖራው ዘንድ የአስተሳሰብ ጥራት እንዳይኖር አግዷል ማለት ይቻላል። የብዙ ተቃዋሚ ፖለቲካኛ ባዮች ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥና ካለምንም ጥረት መታወቅ በመቻላቸው የፖለቲካን ትግል የተረዱትና የሚረዱት እንደ አንድ ትልቅ ህብረተሰብአዊና የነፃነት እንዲሁም የስልጣኔ ፕሮጀክት ሳይሆን ከራሳቸው ዝናና መታወቅ ጋር በማማያዝና ስልጣን ለመውጣት ብቻ ነው። ስለሆነም አገር ቤት ስለሰፈነው ተጨባጭ ሁኔታና ይህ ጉዳይ ከውጭው ዓለም ጋር በመተሳሰር የድህነትና የኋላ-ቀርነት ዋናው ምክንያት ስለመሆኑ የሚነግሩንና የሚያሰተምሩን አንዳችም ነገር የለም። እንዲያውም አገዛዙን የሚመለከቱት ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ከመጉደሉ በስተቀር እንደ ኖርማል አገዛዝ አደርገው ነው። ትልቁ ስህተት እዚህ ላይ ነው።
እንዳየነውና የኢትዮጵያም ህዝብ ባለፉት 23 ዐመታት እንደኖረበት ወያኔ ጨካኝ የሆነ አገዛዝ፣ ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ እሴት የሌለው፣ ባህልን አፍራሽ፣ ለሰው ልጅ ደንታ የሌለውና ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት ምን እንደሆነ ያልገባው፣ ፍቅር የሌለው፣ ጥበብንና ሳይንስን እንዲሁም ቴክኖሎጂን የሚጠላ፣ አገርን የሚሸጥና የሚያፈራርስ ኃይል ነው። በመሆኑም እሱ ያካሄዳቸውና የሚያካሂዳቸው አገር አፍራሽ ፕሮጀክቶችን በሙሉ ትክክል ናቸው ብሎ የሚገምትና፣ የኢትዮጵያም ህዝብ ማርና ወተት እየበላና እየጠጣ በገነት ዓለም ውስጥ እንደሚኖር አድርጎ ነው ለማሳመን የሚሞክረው። በሱ ዕምነትና ፍልስፍና ህዝብን ከቤቱ ማፈናቀልና ቆሻሻ ቦታ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ እንደ ዕድገት ነው የሚቆጠረው። ወያኔ የሰው ልጅ ሊኖር የሚገባውን ባህርይ የጎደለው ብቻ ሳይሆን ባለፉት 23 ዐመታት የሽሩሩና በህብረተሰብ ውስጥ የመካተት ሂደት ምንም የተማረው ነገር የለም። ራሱንም የሚቆጥረው የህብረተሰቡ አካል ሳይሆን እንደ እንግዳና የራሱን ምኞትና ፍላጎት እንደፈለገው ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱን እጅግ አደገኛ አገዛዝና አስተሳሰብ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ እለውጣለሁ ማለት ዘበት ነው። እዚህ ላይ ነው የአንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ነን ባዮች ችግር። አሁንም ቢሆን በምርጫ ማመንና አገዛዙ እነሱ እንደሚሉት የዓለም አቀፍ ስታንደርድን ካሟላ ለምርጫ ውድድር እንደሚቀርቡ ነው የሚሰብኩት። ይህም የሚያመለክተው የቱን ያህል ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የአገዛዙን ህሊናዊ-አወቃቀር አለመረዳቱ ብቻ ሳይሆን ለመሰረታዊ ለውጥም የተዘጋጀ አለመሆኑን ነው።
ከዓለም አቀፍ የፖለቲካ ትንተና አንፃር ስነሳ የዛሬውን የወያኔን አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስን ህብረተሰብአዊ አወቃቀር በመነሳት አይደለም ምንነቱንና አወቃቀሩን መረዳት የምችለው። መረዳት የምንችለው ዓለም አቀፋዊውን የአገዛዝ ሰንሰለትና ከዚያ ጋር የተያያዙ የኢኮኖሚና ፖሊሲዎችንና ፓለቲካዊ እርምጃዎችን ማገናዘብ ስንችል ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር የወያኔ አገዛዝ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስና የራሱ ፍልስፍናን ርዕይ ያለው፣ እንዲሁም ደግሞ በራሱ ጥረት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት ተግባራዊ የሚያደርግ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣኔ አንዳይመጣ ከላይ የተቀመጠ ፕሮጀክትና ህዝብን የሚያተራምስ ነው። እዚህ ላይ ነው ሁኔታውን መረዳት የሚዳግተው።
ያለፉትን 23 ዓመታት ፀር-ምሁራዊ ትግል ስመለከትና ስመረምር በተቃዋሚ ስም እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሰው ኃይል ይህንን ሁኔታ ለመረዳት አለመቻሉና 90 ሚሊዮን ምስኪን ህዝብን ሲያሳስት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በአብዮቱ ዘመን በግራና በሶሻሊዝም ስም የተካሄደው ዕልቂት ተራማጅ ነበርኩ የሚለውንና ተራማጅ ያለሆነውን ሁሉ ከሞላ ጎደል ግልጽ በላሆነ የትግል መድረክ ላይ አሰልፍፏቸዋል ማለት ይቻላል። ሁሉም አንድ ዐይነት ቋንቋ የሚናገሩ ነው የሚመስለው። አንድም ሰው ደፍሮ በአብዮቱ ዘመን የተሰራውን ስህተት በሳይንስ መነፅር በመመርመር ሲያሰረዳና አዲስ የትግል ዘዴ መቀየስ እንደሚያስፈልግ ሲያስተምር አይታይም ። ሁሉም ወደ ገበያ ኢኮኖሚና ወደ ሊበራል ዲሞክራሲ ስርዓት የሚያመራ ነው የሚመስለው። በመሆኑም 23 ዓመታት ያህል በነፃ-ገበያ ስም በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና በዚህ አማካይነት የተፈጠረውን ድህነትና ህብረተሰብአዊ ትርምስ ለመመርመር የቃጣና የሚቃጣ የለም። የተቃዋሚው የትግል ዘዴ የኢትዮጵያን ህዝብ መሰረታዊ ችግር ሳይረዳ ትግል የሚያካሂድ ነው የሚመስለው። በመሆኑም አንዳቸውም ተቃዋሚ ኃይል ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ስርዓት ነው የሰፈነው ብሎ ቢጠየቅ ሊመልስ የሚችል ያለ አይመስለኝም። በሽታችንንና የበሽታችንን ዋና ምክንት ካለወቀን ደግሞ እንዴት እንደምንታገልና እንዴትስ ስትራቴጂ እንደምንቀይስ ግራ ይገባኛል። ስለዚህም ተጨባጭ ሁኔታዎችን እስካልተረዳን ድረስ ትግልችን የተደነባበረና እንደየሁኔታው አየተለዋወጠ ግራ የሚያጋባ ይሆናል ማለት ነው። ፕሪንሲፕልና ዓላማ የሌለው ይሆናል።
ስለዚህም የሚደረገው ትግል በሰላማዊና ሰላማዊ ባልሆነ መሀከል መምረጥና መፈላሰፍ ሳይሆን በአገራችን ምድር ውስጥ የሰፈነውን ሁኔታ ከሁሉም አኳያ መመርመርና ወደ ውጭ አውቶ መከራከር ያስፈልጋል። ከላይ እንዳልኩት ኢትዮጵያ የየድርጅቶችና የየግለሰቦች የግል ሀብት ስላልሆነች ሞራላዊ፣ ህብረተሰብአዊና የታሪክ ግዴታ አለብን የምንል ሁሉ የኢትዮጵያንና የዓለምን ሁኔታ አንስተን መወያየትና መከራክር፣ ከዚያም በመነሳት ሊያሰራንና መፍትሄ ሊሆን ይችላል ብለን ወደምንገምተው ህብረተሰባዊ ፕሮጀክት ማምራት አለብን። ከዚህ ስነሳ የአገራችንን ሁኔታ አንስቶ በየመድረኩና በየሚዲያዎች የሚሰጠው ትንተናና ገለፃ ሀቁን እንድነረዳና ወደምንፈልገው መንገድ የሚውሰደን አይደለም። ትምህርታዊና ሃሳባችን እንድንሰበስብ የሚረዳን አይደለም። ለመጻፍና ድምጻችንን ለማሰማት ብለን ስለማንጽፍ በእርግጥ ለአገራችን የምናስብ ከሆነ ከአደናጋሪ አቀራረብና ተጨባጭ ሁኔታን መንፀባረቅ ከማይችል የአጻጻፍ ዘዴ መላቀቅ አለብን።
ከትግል ጀምሮ እስከ ህዳሴ ግድብና ስለ ኢኮኖሚ ጉዳይ የሚቀርቡ ጽሁፎች ልክ አገራችን በጤናማ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ነው። የጽሁፎቹን ይዘት በደንብ ለተመለከተ የኢትዮጵያን ህዝብ በአማካይ ቦታ ያሰቀመጠና ብሄራዊ ፕሮጀክት ያላቸው አቀራረቦች አይደሉም። ይህንን አስመልክቶ ሰሞኑን በገበያ ኢኮኖሚ ስምና የገንዘብምን ቅነሳ (Devaluation) አስመለክቶ የሚቀርበው ትንተና መስል አቀራረብ ልክ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝቦች በመልካም አስተዳደር ውስጥ እንዳሉ፣ ግን ደግሞ የሚያስፈልጋቸው አንዳንድ እርማቶች እንደሆነ ነው። በተለይም የኢኮኖሚ ፖሊሲውን ከኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ የሚያሰቅቅ ኑሮና አገር መፈራረስ ነጥሎ መፃፉ የቱን ያህል የምሁር ድክመት እንዳለ ነው የሚያመልክተው። ይህ ዐይነቱ ከዚህም ከዚያም ሳይታሰብና ሁኔታዎችን ሳያገናዝብ የሚቀርብ ጽሁፍ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ ያደናግራል። ውሸትን ከዕውነት እንዳንለይ ያደርገናል። ዝም ብሎ የሚጻፍ ነገር እንደሌለ ሁሉ ስለኢኮኖሚም ሆነ ስለሌላ ነገር የሚጽፉ በምን ዐይነት ፍልስፍናና የአሰራር ስልት እንዲሁም ሳይንስ ላይ ተደግፈው እንደሚዝፉና መፍትሄውም ምን እንደሆነ ቢያስረዱን ክፋት የለውም። ካለበለዚያ እንክርዳዱን ከስንዴው የማንለይበትና የምንድነጋገርበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ይህ ዐይነቱ ብቅ ጥልቅ የሚል የትግል አካሄድና አልፎ አልፎ የሚቀርብ ጽሁፍ ውዝንብር መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን ወደ ዕውነተኛ ነፃነትና ጠንካራ አገር እንዳንመሰርት እንቅፋት እየሆነብን ነው። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ወያኔ ብቻ አይደለም የስልጣኔው እንቅፋት። ወያኔ የምናየው የስልጣኔና የጠንካራ አገር ግንባታ ዋናው ጠላት ሲሆን፣ የማይታየው ጠላት ደግሞ እዚህና እዚያ በገበያ ስም የሚምለውና የሰውን ደስተኛ ኑሮ በነፃ ገበያ ስር ለመገደብ የሚሞክረው ነው። የብዙዎቻችንም ችግር ይህንን የተደናበረ ሁኔታ በሳይንስ መነጽር ለመመርመር ያለመቻልና ፍላጎትም ያለመኖር ነው። ትግል ፍላጎትን ይሻል። ትግል ሞራላዊና ስነ-ምግባራዊ መሆን አለበት። በሳይንስና በፍልስፍና ላየ የተመረኮዘ መሆን አለበት። የመጨረሻ መጨረሻም ጠንካራና የተከበረች አገር፣ እንዲሁም ህዝቦቿ በደስተኛ ዓለም ውስጥ የሚኖሩባት አገር ለመመስረት የሚያስችለን መሆን አለበት። ስለሆነም ትግል ከውስጣዊ ፍላጎት ጋር የተያያዘና ዕውነተኛ ነፃነትን የሚያጎናጽፍ መሆን አለበት። በእርግጥም ግለሰባዊ ነፃነትን ከህብረተሰብአዊ ኃላፊነት ጋር የሚያጣምርና ታሪክን ሊያሰራ የሚችል መሆን አለበት። ስለሆነም ትግል ካለጥረትናን ዕውነተኛውን መንገድ ከመፈለግ ውጭ ሊታይ አይችልም። ከዚህ በመነሳት ለምንድነው የምንታገለው? ምንስ ዐይነት ህብረተሰብ ያስፈልገናል? የሚለውን ለመመርመር አንሞክር።
ለምንድነው የምንታገለው? ምንስ ዐይነት ህብረተሰብ ነው የምንመኘው?
በመሰረቱ ለራሳችንም ሆነ ለህብረተሳባችን እንታገላለን ስንል የመጨረሻ መጨረሻ አንድ ዐይነት ውጤት ላይ ለመድረስ ነው። ለስቃይ እታገላለሁ ብሎ የሚነሳ የለም። አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ትግል ስናካሂድ የመጨረሻ መጨረሻ ደስታን ለመጎናጽፍ ነው። ይሁንና ግን በአንዳንድ አሳሳች ሰዎችና በራሳችንም ጥረት ካለማድረግ የተነሳ በመጀመሪያ ላይ ይታይ የነበረው የትግል ሆይ ሆይና ደስታ ወደ ስቃይነትና ወደ መበጣበጥ ያመራናል። የየካቲቱን አብዮት እንደምሳሌ መውሰድ እንችላለን። ተፈልጎ ወደዚያ ዐይነቱ ብጥብጥ ውስጥ የተገባ ሳይሆን በአንዳንድ ሰዎች አሳሳችነትና ራሳችንም ትግል ስንል ከመጀመሪያውኑ ለመመርመር ጥረት ባለማድረጋችን ብቻ ነው።
በፍልስፍና ዓለም ውስጥና በተግባርም እንደታየው የፈላስፋዎችና የሳይንቲስቶች ትግልና ዋና ዓላማ የነበረው የሰውን ልጅ ወደ ደስታ ዓለም ውስጥ ለማሸጋገርና እንደ ወንድማማችና እንደእህትማማች አብረው እንዲኖሩ ነው። ለህብረተሰብ የሚደረግ ትግልም በአንድ አገር ገነትን ከመመስረትና ህብረተሰብአዊ ስምምነትን ከማምጣት ውጭ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ትክክለኛ ፍልስፍናና ሳይንሳዊ መንገድን መከተል ያስፈልጋል። የለም የነፃ ገበያ ብቻ ነው አንድን ህዝብ ደስተኛና ተስማምቶ እንዲኖር የሚያደርገው የሚለው እጅግ አሳሳች አቀራረብ አደገኛ ብቻ ሳይሆን የሰልጣኔውን ጥማችንን ለሺህ ዐመት እንዲራዘም ያደርገዋል። ይሁንና ግን በዕቅድ ላይ የተመሰረተና ግለሰብአዊ ተሳትፎነት ያለው የአገር ውስጥ ከበርቴ ማደግና በኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ መሳተፍ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ለዚህ ጸሀፊ ግልጽና የማያወላውል አቋሙ ነው።
ትግላችንም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደየችሎታው የሚሳተፍበትና በመንግስትም የሚደገፍበት አጠቃላይ የሆነ ብሄራዊ ፕሮጀክት መሆን ይገባዋል። በዚህ ዐይነት ብሄራዊ ፕሮጀክት ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚና ሰፋ ያለ የስራ ክፍፍል ቦታ እንደሚኖራቸውና አስፈላጊም እንደሆኑ ግልጽ መሆን አለበት። በሌላ ወገን ግን አገራችንን ሙሉ በሙሉ ለገበያ ተዋናዮች መልቀቅ አለብን፣ የውጭ ኢንቬስተሮችም መጥተው እንደፈለጉ ይዋኙ፣ በዚህም አማካይነት የስራ መስክ ይከፈታል የሚለው በሳይንስና በህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተረጋገጠ አይደለም። ለአጠቃላዩ የኢኮኖሚ ዕድገትና የህብረተሰብ ግንባታ የሚያመች አይደለም። እንዲያውም የተደራጀና ስርዓት ያለው የገበያ ኢኮኖሚ እንዳንመሰርት የሚያግደን ይሆናል።
እንድሚታወቀው በህብርተስብና በፍልስፍና የትግል ታሪክ ውስጥ ኢኮኖሚክና ሶሻል ጀስቲስ የሚባሉ ነገሮች አሉ። እነዚህ መሰረተ-ሃሳቦች ኖርማቲቭ ናቸው እንጂ እያንዳንዱ ግለሰብ በተመጣጣኝ ተመሳሳይ የአኗኗር ስልት ይኖረዋል ማለት አይደለም። በብዙዎቻን ዘንድ ያለው ችግር ይህንን የእያንዳንዱን ግለሰብ በስነ-ስርዓት ለመኖር ያለውን ፍላጎት በቅጡ አለመረዳትና ከዚህ በመነሳት አንዳች ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮጀክት ለመፍጠር ወይም በዚህ ዙሪያ ለመታገል ያለመቻል ነው። ስለዚህም ለአገራችን እንታገላለን ስንል 90 ሚሊዮኑን ህዝባችንና አኗኗሩን በጭንቅላታችን ውስጥ ማስቀመጥ አለብን። ስቃዩንና ጥማቱን መረዳት አለብን። ካለበት እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ ሊወጣ የሚችልበትን ሁኔታ ማወጠንጠንና መዘጋጀት አለብን። የአገራችንና የህዝባችን ዕድል በሱና በእኛ እጅ ብቻ እንዳለ መገንዘብ አለብን። የአገራችን ዕድገትና ውድቀት ሊወሰን የሚችለው በእኛ ዕውቀትና ታታሪነት እንዲሁም ደግሞ መሸነፍ መሆኑን መገንዘብና ማወቅ አለበን። በታሪክ ውስጥ ታላላቅና ሰለጠኑ የሚባሉ አገሮች በውጭ ኃይል ቡራኬ የተገኙ አይደለም። በከፍተኛ ምሁራዊ ጥረት፣ በእልከኝነትና በብልህነት ነው። አንድ አገር በኃያል መንግስት ነኝ በሚል ቡራኬ ልትኖርና ዕድሏም ሊወሰን በፍጹም አይችልም። ሊወሰን የሚችለው እኛ ተገዢ የሆን እንደሆን ብቻ ነው። ሽንፈትን ያሳየን እንደሆን ብቻ ነው። ድረሱልን እያልን የጮኽን እንደሆን ብቻ ነው። ፍልስፍናውና የተፈጥሮ ህግ እንደሚያስተምረን እያንዳንዱ ህዝብና አገር ነፃና ኩሩ አገር መገንባት መቻል አለባት። ተፈጥሮአዊ መብቱም ነው። ይህንን መረዳት የማንኛውም ታጋይ ነኝ ባይ ግዴታና በጭንቅላት ውስጥ መቋጠር ያለበት ጉዳይ ነው።
ከዚህ ስንነሳ ከላይ እንዳልኩት ትግል ሲካሄድ ዝም ብሎ መራወጥና መሳሪያ እያነሱ መጫረስ ሳይሆን፣ አንድ ተሰማሚና ደስተኛ ሁኔታን ለመፍጠር ነው። እያንዳንድችን ዘለዓለማችንን ትግል ትግል እያልን ልንኖር አንችልም። በትግል ዓለም ውስጥም መደስትም እንዳለና፣ እያንዳዱ ግለሰብም በተለያየ መልክ ደስታን መቀዳጀት እንደሚሻ መረዳት አለብን። ይሁንና ሁላችንንም የሚያሰተሳሰረንና ሊያሰራን የሚችል መድረክና ህብረተሰብ ለመፍጠር መታገል አለብን። ወደ አንድ ነገር ለመድረስ ሂደቱን ማዋቅ አለብን። ከላይ አንድ ቦታ እንዳልኩት ሎጂክን ያልተከተለና የአንድን ህብረተሰብ ህግ ያላጤነ መቀመቅ ውስጥ እንደሚከተን ሁሉ ትግላችን ሎጂክን የተከተለ መሆን አለበት። ለዚህ ደግም በመሀከላችን የሃሳብ ስምምነት መኖር አለበት። የለም እኔ እንደዚህ ነው የማስበው፣ አቋሜ እንደዚህ ነው ብለን ድርቅ የምንልና የሌላውን ሃሳብና ሎጂካዊ አቀራረብ ለማዳመጥ እስካልፈለግን ድረስ ችግር ፈጣሪዎች ነው የምንሆነው።
ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ በሬናሳንስ ዘመን የነበረውን ትግል ስንመለከት ትግሉ በሃሳብ ዙሪያ የተካሄደ ሲሆን፣ በተቻለ መጠን ኃይልን ሳይበታትኑ ሀቀኛውን መንገድ ፍለጎ ተግባራዊ ማድረግ ነበር። በእርግጥ ከዛሬ ስምንት መቶና ሁለት ሺህ ዐመት በፊት ትግል ሲጀመር ወደ ካፒታሊዝምና ወደ ገበያ ኢኮኖሚ መድረስ አለብን ተብሎ ሳይሆን ትግል የተጀመረው የኮስሞስን ህግ በመረዳት ስምምነትና ስርዓት ያለው ህብረተሰብ ለመመስረት ነበር ዋናው ዓላማው። ማንኛውም ህብረተሰብ የየራሱ ዲይናሚዝም ስላለውና በየኢፖኩ አዳዲስ ሁኔዎች ስለሚከሰቱ ዛሬ የምናየውን የዓለምን ህዝብ ኑሮ የሚወስነውን ግሎባል ካፒታሊዝም ማየትና እንድንኖርበትም ተገደድን።
ወደ አገራችን ተጨባች ሁኔታ ስንመጣ በመሀከላችን፣ ከዚህም ሆነ ከዚያ ብሄረሰብ መጣን በምንለው ዘንድ ከፍተኛ አለመግባባት አለ። የሁላችን ችግር አንድ ሆኖ ሳለ፣ የየራሳችንን ጎጆ ቀልብሰን ማንም እንዳይደርስብን ቤታችንን ዘግተን ለመኖር እንታገለለን። ይህ ዐይነቱ ተናጠልና ትናኝሽ የትግል ዘዴ የመጨረሻ መጨረሻ ሁላችንንም ነው የሚያጠፋን። ቁጭ ብለን ስናጠናና ስንወያይ ከአንድ ምንጭ የተቀዳን ብቻ ሳይሆን ፍላጎታችንና ህልማችንም ተመሳሳይ መሆኑን መረዳት እንችላለን። ጠላት ካለን ጠላትን ድል መምታትና ጠንካራ አገር መመስረት የምንችለው በተናጠል ትግል ሳይሆን ኃይላችንን ስናስተባብር ብቻ ነው። ዓላማችን በቆንጆ ቤት ውስጥ መኖር፣ ንጹህ ውሃ ማግኘት፣ በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ፣ መብራትና ህክምና ማግኘት፣ እንዲሁም ቤተሰብ መስርተን ደስተኛ ኑሮ ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ በተናጠልና በቡድናዊ ስሜት የትም አንደርስም።
የህዝባችንን የረዠም ጊዜ የነፃነት ህልምና መሰረታዊ ፍላጎቱን አሟልተን የተከበረችና ጠንካራ አገር ለመገንባት ከተፈለገ የፖለቲካው ጥያቄ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። የፖለቲካ ጥያቄ ስል ስልጣንን ከወያኔ በአንዳች ነገር በመንጠቅ ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ሳይሆን ሰፊ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ነድፎ ቀስ በቀስ ሰፊውን ህዝብ የስልጣን ባለቤት ማድረግ ወይንም በዲሞክራሲያዊ ክንውን ውስጥ ተሳታፊ በመሆን በማንኛውም የአገር ግንባታ ውስጥ ተሳታፊና ዕውነተኛ ነፃነትም እንዲቀዳጅ ነው ። እስካሁን ድረስ በአገራችንም ሆነ በብዙ አገሮች የፖለቲካን አወቃቀርና ተግባራዊነት ስንመለከት አንድ ዐይነት ስምምነት አለ። ይኸውም ሰፊውን ህዝብ ከፖለቲካ በማግለል ጠቅላላውን የአንድን አገር ህዝብ ዕድል ተመረጥን በሚሉ ጥቂት ኤሊቶችና የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በሚባለው እንዲወሰን ማድረግ እንደ ዋና ፓለቲካ ፈሊጥ ሆኖ ሲተገበር ይታያል። ባለፉት ስድሳ ዐመታት፣ በተለይም ደግሞ ባለፉት 20 ዐመታት እንደ ሞድ ሆኖ በዚህ መልክ የተካሄደው ፖለቲካ በየአገሮች ውስጥ እኩልነትንና ብልጽግናን እንዲሁም ህዝባዊ ስምምነትን ያመጣ ሳይሆን ትርምስን የፈጠረና አንዳንድ አገሮች እንደገና ወደ መፈረካከስና እንደ ህብረ-ብሄር ወደ ማይታዩበት ደረጃ እየወረዱ ያሉበት ሁኔታ ነው። ከዚህ ስንነሳ የፖለቲካን ትርጉም በአዲስ መልክ ልንፈጥረው ባንችል አንኳ የግዴታ ለአገራችን በሚስማማ መልክና ህዝቡን ሊያሳትፍ በሚችል መልክ ለማዋቀር መዘጋጀት ይኖርብናል። ስለዚህም የግዴታ የፖለቲካን ምንነት ከፍልስፍናና ከሳይንስ ጋር ማገናኘት ያለብን ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው ፖለቲካን ለመጀመሪያ ጊዜ ትርጉምና ቦታ የሰጡት የግሪክ ፈላስፎች ናቸው። በእነሱ ዕምነትም የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ፓለቲካዊ እንስሳ ነው። ይህም ማለት ፖለቲካ ለተወሰኑ ስዎች ብቻ የሚለቀቅ ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ ያለን ህዝብ በሙሉ የሚመለከት ነው። በመሆኑም በሶክራተስና በፕላቶ እንዲሁም በአርስቲቶለስ አመለካከትና ፍልስፍና ፖለቲካ ከሞራልና ከስነ-ምግባር ውጭ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ፖለቲካ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ ነው። ፍልስፍናና ሳይንሳዊ የሚያደረገው የሰውን ልጅ ህይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ስለሚመለከትና፣ በምድር ላይም የሰው ልጅ ታሪክን የሚሰራ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። የግሪክን ፍልስፍና መሰረት ያደረጉ የአስራ አራተኛው ክፈለ-ዘመን ፈላስፎችና በኋላም በጀርመን ምድር ብቅ ያሉት ፈላስፋዎች የፖለቲካን ትርጉም የተረዱት ህብረተሰብአዊና የነፃነት ፕሮጀክትነቱን በመረዳት ነው። ስለዚህም ፖለቲካ ሲባል በአርቆ-አስተዋይነት ላይ የተመሰረተ መሆን ሲገባው ዋና ዓላማውም አንድን ህብረተሰብ ከሳይንስ አንፃር በመገምገም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዲቀዳጅ ማድርግ ነው። ስለዚህም ፖለቲካ ሲባል የማቴሪያል ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን መነፈሳዊም (Spiritual) ነው። ይኸም ማለት የሰው ልጅ ከፍተኛ ንቃተ-ህሊናን ሲቀዳጅና ሁልጊዜ ራሱን መጠየቅ ሲችል ህብረተሰቡንም የመቆጣጠር ኃይል ይኖረዋል ማለት ነው። ስለዚህም እንደዚህ ዐይነቱ ፍልስፍናና መንፈስን ያስቀደመ ፖለቲካ በምንም ዐይነት ጦርነትን አያስቀድምም ወይም ደግም ህብረሰብአዊና የአካባቢ ችግር በጦርነት ይፈታል ብሎ አያምንም። እንደምናየው ጦርነት ሁልጊዜ የኢምፔርያሊስቶች ፕሮጀክትና ሀብረተሰቦችን ሰላም መንሻና ተረጋግተው የጠነከረ አገር እንዳይገነቡ ማድረጊያ መሳሪያ ነው።
ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ውስጥ ተግባራዊ መሆን ያለበት ፖለቲካ የግዴታ ህዝቡን የሚያሳትፍና እንዲደራጅና በየአካባቢው የራሱን ችግሮች ዲሞክራሲያው በሆነ መንገድ ሊፈታ የሚያስችለው መሆን አለበት። በማንኛውም ኢኮኖሚያዊ፣ ማሀብራዊና ባህላዊ እንዲሁም ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ላይ የሚያሳትፈው መሆን መቻል አለበት። የውጭንም ፖለቲካ በሚመለከት ከቢሮክራሲያዊ የአሰራር ዘዴ በመላቀቅ ግልጽነት ያለውና ህዝቡ ሊረዳው የሚችል ፖለቲካ መካሄድ አለበት። የዛሬው አገዛዝ ካለምንም ውክልናና ዲሞክራሲያዊ ውይይት አገርን የሚያሸጥ ፖለቲካና የአገርን መሬት ለባዕዳን ጦር መስፈሪያ በመስጠት ከዚያ እየተነሱ ሌላ አገር እንዲደበደብ የማድረጉ ፖለቲካ ተብዬ መወገድ ያለበትና የውጭ ኃይልም በምንም መንገድ በአገራችን የውስጥና የውጭ የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ እንዳይፈተፍት አስፈላጊው እርምጃና ህዝቡን የማስተማር ጉዳይ ተግባራዊ መሆን አለባቸው። በዚህ መልክ ብቻ የኢትዮጵያ ህዝብ አገሩን በአዲስ መንፈስ በመነሳሳት ዲሞክራሲያዊትና የበለጸገች አገር መገንባት ይችላል። ከዚህ ውጭ የሚካሄድ በኤሊት የሚወከል የሚስጥር ፖለቲካ አገራችንን ለዘለዓለም እየተተራመሰች አንድትኖር ያደርጋታል። በዚያው መጠንም የድህነቱ ዘመን ይራዘማል ማለት ነው።
በመሆኑም ጠቅላላውን ፖለቲካ አገር፣ ህብረተሰብና ህብረ-ብሄር የሚሉትን መሰረተ ሃሳቦች በጭንቅላት ውስጥ በማስቀደም እንዴት ጠንካራና በቀላሉ ልትፈረካከስና ለጠላት ኢላማ ለመሆን የማትችል አገር ለመመስረት የሚያስችል ሆኖ መዘጋጀት አለበት። ብሄራዊ ነፃነትን የሚያቀዳጅና እያንዳንዱም ዜጋ በአገሩ ተከብሮና ነፃነት ተሰምቶት እንዲኖር የሚያስችለው መሆን አለበት። በእንደዚህ ዐይነቱ ትልቅ የፖለቲካ ፕሮጀክት ብቻ ነው ህልማችንን ዕውን ለማድረግ የምንችለውና ደስተኝነትንም የምንጎናጸፈው። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን፣ ተፈጥሮን በመቆጣጠርና ጠንካራ አገር መመስረት የምንችለውና ለተከታዩም ትውልድ ጥለን የምናልፈው በሃሳብና በዕውቀት ዙሪያ መሰባሰብ ከቻልንና ለውይይትና ለክርክር ዝግጁ የሆን እንደሆን ብቻ ነው።
መልካም ንባብ!!
fekadubekele@gmx.de
Asfaw Godebo says
Okay