ትግርኛ ቋንቋም ያደናብር ጀመረ እንዴ! ዛሬ (ጥር 6) በፌስቡክ ላይ እንዳየሁት አንዲት ሴት ወገብዋን በነጠላዋ አስራ ትግርኛ የማያውቀውንም የሚቀሰቅስ ንግግር ስታደርግ ነበረ፤ የተናገረችው ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ነው፤ የሕዝቡን ቀልብ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራው ነበር ለማለት አያስቸግርም፤ አንዳንድ ትግርኛ ተናጋሪዎች “ጀግና” እያሉ በወያኔ ላይ የተቃውሞ ንግግር ማድረጉዋን ሲገልጹ አንዳንዶቹ የቋንቋው ባለቤቶች ደግሞ በጣም እየተናደዱ የሴትዮዋ ንግግር የተቃውሞ ሳይሆን የድጋፍ ንግግር ነበር እያሉ ይሞግታሉ፤ የትግርኛ ተናጋሪዎች ተቃውሞንና ድጋፍን ለመለየት ችግር አለባቸው ከማለቴ በፊት ከዚህ በፊት እኔ በትግራይ ሕዝብ ምክንያት የታማሁበትን እንደሚያስታውሰኝ መግለጹ ተገቢ ይመስለኛል፤ የወያኔ ግልጽ ተጽእኖ የትግራይ ሕዝብ በሙሉ በሀሳብ እንዳይለያይ ነው፤ ወያኔ በትግራይ ችጋር የለም ካለ፣ ማንም ትግርኛ ተናጋሪ አጠገቡ በችጋር የሚያቃስት ሰው ቢኖርም የተባለውን መድገምና በትግራይ ችጋር የለም ማለትን መድገም አለበት፤ እንዲህ እያሉ እውነት ከትግርኛ ቋንቋ አይጠፋም ወይ?
ብዙ ሰዎች የተገነዘቡ አይመስለኝም እንጂ ችግሩ ቋንቋን (ማለት ትግርኛን) የትግርኛ ተናጋሪዎች ሞኖፖሊ (የብቻቸው) የማድረግ ጥረት ያለ ቢመስልም፣ ዋናውና ትልቁ አደጋ ሀሳብንም ቀለም እየቀቡ የሚቀበሉትንና የማይቀበሉትን ለመለየት መሞከሩ ነው፡፡
ይቺ ሴት በትግራይም ጉዳይ ይሁን በኢትዮጵያ ጉዳይ አስተያየት የራስዋን አስተያየት ሰጥታለች፤ ትርፋማ የሚሆነው ምን አለች? ምን አስተያየት አቀረበች? ነው እንጂ ወያኔን ተቃውማለች፤ የለም፣ አልተቃወመችም፣ የሚል ነበር፤ መቃወምም፣ መደገፍም መብትዋ መሆኑን ተቀብለን ከተቃውሞዋ ምን እንማራለን? ከድጋፍዋስ ምን እንማራለን? ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ (ለትግራይ የሚበጀው ለኢትዮጵያም ይበጃል፡፡)
ወያኔዎች፡– እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ የእውነትን መስቀል ተሸክመው ከትግራይ ብቅ የሚሉ ሰዎች ነበሩ፤ አሉ፤ ይመጣሉ!!! ገብረ መድኅንን፣ አስገደን ከነልጆቹ፣ አብርሃን … እስከዘላለሙ አንረሳቸውም፡፡
(ምንጭ: መስፍን ወልደ ማርያም ብሎግ)
ጥር 2008
Leave a Reply