“Injustice anywhere is a threat to justice everywhere” Martin Luther King Jr.
ላለፉት ሦስት ሳምንታት አወዛጋቢውን የአዲሰ አበባ ማስተር ፕላን እቅድና የትግበራ ዝግጅት በመቃወም በአገራችን የተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥ የተቀሰቀሰው የተማሪዎች ተቃውሞ እያደር ወደ ሕዝባዊ ቁጣና አመጽ እየተቀይረ መምጣቱን በግልጽ እየተመለከትን ነው፡፡ አድሮ ጥሬ የሆነው የወያኔ አገዛዝ ሥርዓትምየተነሱትን ጥያቄዎች በወቅቱና ስልጡን በሆነ መልኩ ከመፍታት ይልቅ ላለፉት 24 አመታት እንደሚያደርገው ሁሉ ዛሬም የኃይል እርምጃ በመውሰድበአስሮች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል፣ በርካቶችን ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት አድርሶባቸዋል፣ ቀላል ግምት የማይሰጠው የህዝብ ንብረትም እየወደመ ይገኛል፡፡ የህዝባዊ ተቃውሞው መንስዔ ተማሪዎቹ ያነሱትና በተቀረው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ ብዥታን የፈጠረው የአዲሰ አበባ ከተማየማስፋፊያ እቅድ ቢሆንም እያደር ግን መልኩን ቀይሮ ሥርዓቱ ለበርካታ አመታት ሊመልሳቸው ያልቻሉና በመላ አገሪቱ የተንሰራፋውንአፈና እና መሰረታዊ የፍትሕ፣ የሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲጥያቄዎችን የሚያንጸባርቅ እየሆነ ነው፡፡
ከቅርብ ቀናቶች ወዲህ እየታየ ያለው ሕዝባዊ ቁጣና ንቅናቄ በክልሉ ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሁሉ እያካተተ መምጣቱን እያስተዋልን ነው፡፡ ከገበሬው አንሶቶ አዛውንቶች፣ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ መምህራንና በተለያዩ የስራ መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የትምህርት ተቋማትና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ተቃውሞ ውስጥ እየተሳተፉ መሆናቸውን እየተከታተል ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የወያኔ ሥርዓት ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ አንስቶ ሰፊ የሆነና ከሳምንታት በላይ የቆየ ሕዝባዊ ተቃውሞ ስመለከት ይህ ሦስተኛው ነው፡፡ የመጀመሪያው እጅግ ብዙ የተወራለትና በእንጭጩ የተጨናገፈው የግንቦት 1997 ዓ›ም› ምርጫን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣ ነው፡፡በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው‘ድምጻችን ይሰማ’ በሚል ላለፉት ሶስት አመታት የታየው እጅግ ስልጡንና ሰላማዊ የሆነው የሙስሊሙ ማሕበረሰብ የመብት ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎችሥርዓቱን በተወሰነ ደረጃ ከማሸበርና እንቅልፍ ከመንሳት ባለፈ የማስገደድ አቅም ስላልነበራቸውወያኔ የሚፈጽመውንየመብት ጥሰት፤ እስር፣ ድብደባ፣ ግድያና የሃሰት ውንጀላአላስቆመውም፡፡ የሥርዓቱን ብልግና እና ጭካኔ ግን በደንብ ያጋለጡ ንቅናቄዎችናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው ሰፊ የሆነ ሕዝባዊ ንቅናቄ አሁን በመካሄድ ላይ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ቁጣ ነው፡፡
የ1997ቱ ሕዝባዊ ቁጣ በመላ አገሪቱ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያቀፈና ያለምንም የዘር፣ የኃይማኖት፣ የጽዎታና ሌሎች ልዩነቶችን መነሻ ሳያደረግ በፍትሕ፣ በነጻነትና በዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ዙሪያ ያተኮረ ሰፊ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ሁለተኛው ንቅናቄ መሰረቱ የመብትና የፍትሕ ጥያቄዎች ቢሆኑም አንድን የኃይማኖት ክፍል ‘እስልምናን’ ማዕከል ያደረገ ንቅናቄ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ይሁንና በውስጡ የዘር፣ የጽዎታና ሌሎች ልዩነቶችን አሸንፎ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ያቀፈ ነበር፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው የሕዝብ እንቅስቃሴ ደግሞ ምንም እንኳን የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅቶች አጋርነታቸውን እየገለፁ ቢሆንም አሁን ባለበት ደረጃ የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ማዕከል ያደረገ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡እነዚህ ሁለት በኃማኖትና በጎሳ የተወሰኑት ሕዝባዊ የፍትሕና የነጻነት ጥያቄዎችና ንቅናቄዎችለምን ወደ አገር አቀፍ ንቅናቄነትእንዳላደጉ ወይምየማደግ ምልክት እንዳላሳዩ፣ ለምንስ ቀሪው የኅብረተሰብ ክፍል ሌሎቹ ወገኖቹ የሚያነሱትን የመብት ጥያቄ በጥርጣሬና የጎሪጥ ከማየት ባለፍ አጋርነቱን በተግባር ሊገልጽ አልቻለም? ለምን ልብ ለልብ ተራራቅን? በዛች አገር ውስጥ ማን በፍትሕ እጦት እየማቀቀና እየተሰቃየ ማንስ ደልቶትና ተረጋግቶ በሰላም መኖር ይችላል?ይህ አይነቱ የሕዝብ ክፍፍልስ ከምን መነጨ? ማንንስ ነው እየጠቀመ ያለው? እንደ አንድ አገር ሕዝብ የአንዳችን ሕመም እንደምንስ ለሌሎቻችንን ላይሰማን ቻለ ወይም ለምን እንዳልተሰማን ለማስመሰል እንሞክራለን? ከተሰማንስ ምን አደረግን? ምንስ ማድርግ እንችል ነበር? የሚሉና ሌሎች አግባብነት ያላቸውንጥያቄዎች ማንሳትና በግልጽ መወያየት፤ ለችግሮቹም የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ቁጭ ብሎ በሰለጠነ መልኩና በቅን ልቦና መነጋገርና መደማመጥ ካቃተንና ይህን ማድረግ ተራራ የመግፋት ያህል ከብዶ ከተሰማንከተጫነን የረዥም ጊዜ መከራ፣ ስቃይ፣ ድህነት፣ አፈና እና አንባገነናዊው ሥርዓት መቼና በምን ሁኔታ ልንገላገለ እንችላለን?
ለእነዚህ ችግሮች መንስዔዎች ናቸው ከምላቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ጥቂቶቹን ልጥቀስ፡-
- ለሃያ አራት አመታት በወያኔና መሰል ድርጅቶች ሲዘራ የቆየው ዘርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገው የጥላቻ ቅስቀሳና የቅራኔንመርዝ ሲረጭ የነበረው የዘር ፖለቲካ ፍሬ አፍርቶ በግላጭ መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ለዚህም በየጊዜው በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የተከሰቱትንናአሁንም እየተከሰቱ ያሉት፤ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፉ የጎሣና የኃይማኖት ግጭቶችን በዋነኝነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
- በእረዥም ጊዜ ታሪካችን ውስጥ የተፈጸሙ ክስተቶችን፣ አስነዋሪ ተግባራትንና ቅራኔ ሊፈጥሩና ሊያስፋፉ የሚችሉ ግድፈቶችን መዞ በማውጣት እሱኑ እያጦዙና እያራገቡ የፖለቲካ ትርፋቸውን የሚያሰሉ፤ ወይም በታሪክ ሂደት ውስጥ በአንድ ወይም በሌላውየኅብረተሰብ ክፍል ላይ የተፈጸሙ በደሎችንና የግፍ ተግባራትን እንዳልተፈጸሙ በመካድ ወይም የሌሎችን በደልችላ በማለትና ተገቢውን እውቅና በመንሳት ቅራኔዎችን የሚያሰፉ ግለሰቦች፣ ምሁር ተብዮዎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች የተጠመዱበትን እኩይ አስተሳሰብ በሕዝቡም ዘንድ እንዲሰርጽ በማድረግ ቂምና ጥላቻን ያረገዘና ለበቀል የተዘጋጀ የኅብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር መደረጉንማስተዋል ይቻላል፡፡
- በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ የመረጃ መረቦችም ተደጋግመው የሚሰራጩት ጭፍን እና የጅምላ ፍረጃዎችም በህብረተሰቡ ውስጥ አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠርና እንዲሰጋ በማድረግ ወያኔ በሕዝቡ አበሮነት ላይ የፈጠረውን ስንጥቅ እንዲሰፋና ገደል እንዲሆን አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥረዋል፡፡
- በዘር መድሎና ክፍፍል ላይ የተመሰረተው የአገዛዝ ሥርዓቱ የሥልጣን መዋቅር በሃያዎቹ አመታት ውስጥ ያፈራቸው የዛሬዎቹ ወጣቶች፤ በከፍተኛ የትምርት ተቋማቶች ውስጥ ያሉትን እና ባለፉት አሥር አመታት ውስጥ ተመርቀው በሥራ ገበታ ላይ የሚገኙትን አምራች ኃይሎች የዘር ፖለቲካው ሰለባዎች ለመሆናቸው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን ድባብ ጠጋ ብሎ ማየት በቂ ነው፡፡ እነዛ ማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ያገባኛል በሚሉና በኢትዮጵያዊነት ስሜት ያለምንም የዘር ልዩነት በጋራ ድምጻቸውን በሚያሰሙ ተማሪዎች ይናወጡ የነበሩት የትምርት ተቋማት ዛሬ በጎሣና በጎጥ ተቧድነው እርስ በእርሳቸው በሚቧቀሱና በሚወነጃጀሉ ተማሪዎች ተሞልተዋል፡፡ በአንድ የትምህርተ ተቋም ውስጥ፤ ከዛም አልፎ በአንድ ክፍል ውስጥ አብረው የሚያድሩና በአንድ ክፍል ቁጭ ብለው የሚማሩ ተማሪዎች እርስ በርስ እየተፈራሩ፤ ነገር ግን በቋንቋ ብቻ ከሚመሳሰላቸው ጋር ተቧድነው እርስ በርስ ሲደባደቡና የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሌላውን ሲያጠቁና ሲያገሉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ ትልቅ አገራዊ ኪሳራ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ በአንቦና በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህም የተቋሞቹን መክሸፍ ብቻ ሳይሆን የሚያሳየው እነዚህ ወጣት ተማሪዎች የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢዎች እንደመሆናቸውመጠን ወያኔ የዛሬዋን ብቻ ሳይሆን የነገዋንም ኢትዮጵያን ለማክሸፍና ለማጨለም ተግቶ እየሰራ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡
ወደ ተነሳሁበት ዋና ነጥብ ልመለስና ወያኔ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ በቅርብ ጊዜ ከታዩት ሦስት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች መካከል የመጨረሻዎቹ ሁለቱ፤ ማለትም ‘ድምጻችን ይሰማ!’ በሚል መሪ መፈክር የተካሄደው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃዉሞና አሁን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣና ንቅናቄዎች በግልጽ የሚያሳዩት በትምህርት ተቋማት ውስጥ ተወስኖ የቆየውና ስር የሰደደውየእርስ በእርስ መፈራራትና የክፍፍል ወረርሽኝ በሕዝብም ውስጥ ሰርጾ መግባቱን ነው የሚያመላክቱት፡፡
የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መሰረታዊ የመብትና የነጻነት ጥያቄዎቹን በማንሳቱ ምክንያት መሪዎቹ ሲታሰሩበት፣ አባላቶቹ በገፍ ሲታሰሩ፣ ሲደበደቡና የስቃይ ሰለባ ሲሆኑ ከጥቂት አርቆ አሳቢና አስተዋይ የሆኑ የሌላ እምነት ተከታይ ግለሰቦችና በውጭ የሚኖሩ ጥቂት የኃይማኖት አባቶች በስተቀር በተቋም ደረጃም ሆነ በግል ተሰባስበውምበእነዚህ ወገኖችላይ የደረሰውን የመብት ጥሰት የተቃወሙ፣ ያወገዙና ያነሱትም መሰረታዊ የሆኑ የመብት ጥያቄዎች በጡንቻ ሳይሆን በሕግ አግባብ ሊመለስላቸው ይገባል ብለውለፍትሕ ሲባል ከጎናቸው የቆሙ ወይም ድምጻቸውን ያሰሙ የሌላ ኃይማኖታዊ ተቋማቶች አላየሁም፡፡ ከዚያ ይልቅ በወያኔ ሚዲያዎች የሚሰራጩትን ፕሮፓጋንዳዎችና ቅስቀሳዎች፤ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች በአክራሪዎች የተሰነዘሩ ጥቃቶችን እያጣቀሱ የአገዛዙን የአፈና እርምጃ ተገቢነት አፋቸውን ሞልተው ይደግፉ የነበሩ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ይህን በግልጽ ማስቀመጥ የሚያስፈልገው ሕዝብን ለማቃረን ሳይሆን የገባንበትን አዘቅት በቅጡ እንድናየው ለማሳሰብ ነው፡፡ እንዳበደ ውሻ ያገኘውን ሁሉ የሚናከሰው ወያኔ ብዙም ሳይቆይ የዋልድባን ገዳም ሲያተራምስና መነኮሳትን ሲያስር፣ ሲያዋርድና ሲደበድብ ከጥቂት እንዲሁ ለህሊናቸው ያደሩ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አባላት በቀር በአብዛኛው የሙስሊሙና የሌላው እምነት ተከታይ ዘንድ የነበረው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ለነገሩ የወያኔ የዘር ፖለቲካ በደንብ ስር ሰዶ የተንሰራፋባትና የደቆሳት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞችምሳይቀሩበዋልድባ ገዳም ለተፈጸመውም ሆነበአዲሰ አበባ የጳጳሳቱ መኖሪያ ቤቶች በሌሊት በጠገቡ ጎረምሳ ደህንነቶች እየተሰበረ ሲደበደቡና ሲዋረዱ ድምጹን ያሰማ አልነበረም፡፡ የፍርሃት ቆፈኑና ጥበቱ የእምነት ተቋማትንም ሳይቀር ያደቀቃቸው መሆኑን እነዚህ የአደባባይ ኩነቶች በደንብ ያሳያሉ፡፡ በዚህ እረገድ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ በኩል የሚታየው ዘርና ቋንቋ የተሸገረው አብሮነት ያዝልቀው እንጂ በጥሩ ምሳሌነት ሲወሳ የሚኖር ነው፡፡
ሲፊዋን አገራቸውን ኢትዮጵያን እንዲረሱ ተደርገውና የተወለዱበትን ክልል ወይም የመጡበትን ጎጥ ወይም የዘር ምንጫቸው የሚገኝበትን ስፍራ ወይም በቋንቋ አሰፋፈራቸው የተካለለውን ሥፍራ ብቻ አገራቸው አድርገው እንዲያስቡና በዚህም ተወስነው ሌላውን ክፍል ባዳ ወይም ጠላት አድርገው እንዲያስቡ ተደርጎ ጭንቅላታቸው የተቀረጸው የዛሬዎቹ ወጣቶችና ‘የከፍተኛ’ ተቋማት ተማሪዎች የሚያነሱዋቸው የመብትም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች የመንደር ወንዝ የማይሻገሩ፣ ከቀበሌኛነትያልዘለሉ ወይም በጎሣ፣ በሚናገሩት ቋንቋ ወይም በሚወግኑት ኃይማኖት ዙሪያ የታጠሩና የተወሰኑ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡ እነዚህን የመብት ጥያቄዎች ማንሳቱ ተገቢ መሆኑ ጥያቄውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ መብትም ነው፡፡ ይሁንና ሁሉም እሱ ከመጣበት ክልል ወይም የዘር መስመር ውጪ ባለችዋ ኢትዮጵያና ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ በደሎች፣ የመብት ጥሰቶች፣ አገራዊ ጉዳዮችና ሌሎች ችግሮች አይመለከቱኝም ብሎ አይኑን ከጨፈነ እና ጆሮውን ከደፈነ፤ እሱምሲጠቃና ሲበደል የሌላው አካባቢ ተወላጅ ይህንኑ አይነት ስሜት ካንጸባረቀ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እያከተመላቸው ነው ማለት ነው፡፡
የአፋር አርብቶ አደር ከቅዮው ሲሳደድና በታጣቂዎች ሲዋከብ፣ የኦጋዴን ሕዝብ በርሃብና በጥይት ሲቆላ፣ የጋንቤላ ገበሬ ከአካባቢው እየተፈናቀለ መሬቱ ለውጪ ቱጃሮች ተቸብችቦ በየጫካው ሲበተንና ሲሰቃይ፣ የአማራ ገበሬ ለዘመናት ያፈራውን ቅሪቱን ተዘርፎና ንብረቱበእሳት ጋይቶ ለዘመናት ከኖረበት ስፍራና ካለመው መሬት ላይ ቁራጭ ጨርቁን እንዳጣፋ አገር አይደለም እየተባለ ሲሳደድና ሚስትና ሴት ለጆቹ አይኑ እያየ ሲደፈሩበት፣ የትግራይ ገበሬ ስርአቱን ካልደገፍክ እየተባለ ሲዋከብ፣ የእርዳታ እህል ሲነፈግና በስሙ እየተነገደበት እሱ ግን ሚስትና ልጆቹን ይዞ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ፈሶ ለልመና ሲዳረግ፣ የኦሮሞ ገበሬዎች ለም መሬታቸውን እየተነጠቁ ለዘመኑ ከበርቴዎችና ለውጭ ባለሃብቶችእየተቸበቸበ እነሱ ከነቤተሰቦቻቸውየነጣቂዎቹ አገልጋይ እንዲሆኑ ለባርነት ሲገፉ፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ግፉዋን ላይ የሚፈጸሙ በደሎች የማይቆረቁሩት፣ እንቅልፍ የማይነሱት ትውልድና የህብረተሰብ ክፍል ሊፈጠር የሚችለው ከላይ በጠቀስኳቸው ችግሮች ነው፡፡
ዛሬ የኦሮሞ ተማሪዎች በየትምህርት ተቋማቱና በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃዎች ሳይቀር ይመለከተናል ባሉትጉዳይ ላይ ወደ አደባባይ ብቻቸውን የወጡት፤ ከዛም አልፎ ጠግቦ ባላደረ አንጀታቸው በሥርዓቱ ቅልብ ታጣቂዎች ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩ፣ ሲሰቃዩና በግፍ በየአደባባዩ ሲገደሉ የሌላው ኢትዮጵያዊ ዝምታ የገባንበትን አዘቅት አመላካች ነው፡፡ ይህ በህዝብ መካከል ለክፉ ቀን እንኳን አብሮ በአጋርነት የመቆምና አንዱ ለአንዱ ደጀን የመሆን የቆየ ባህልና ማህበራዊ ትስስር ተቦርቡሮ ተቦርቡሮ ሊበጠስ አንድ ሃሙስ የቀረው በሚመስል ደረጃ ላይ መገኘቱ አሳሳቢ ነው፡፡ ይሁንና እስካሁን የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተሳስረው የሚገኙት በርካታና ደንዳና ክሮች አሁንም እንዳያያዙን ስላሉ እነሱን ማጥበቅ የግድ ይላል፡፡ ለዚህም የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ትስስርና አብሮነት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ‘በድመጻችን ይሰማ’ ትግል ውስጥ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጎራጌ፣ ትግሬ፣ ከንባታ፣ ሃድያ፣ ወዘተ… ሳይል ሁሉም የእስልምና እምነት ተከታዮች በአንድ ላይ እየተሳሰቡና እየተደጋገፉ ለዲናቸው ሲቆሙ አይተናል፡፡
ይህን ሕዝብን አስተሳስረው የያዙ ክሮችን ለማሳሳት ወይም ለመበጣጠስ የሚተጋው ታዲያ ወያኔ ብቻ አይደለም፡፡ በያደባባዩ እራሳቸውን የሕዝብ ተወካይ አድርገው በማቅረብ የቅራኔን መርዝ የሚተፉ የፖለቲካ ድርጅቶችና አንዳንድ ስክነት የራቃቸው ግለሰቦችምየሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ኃይሎች በሕዝቡ መካከል ያሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን የፖለቲካ ግብ ማሳለጫቸው እያደረጉ ታሪካዊ ትስስር ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች እያናቆሩ ዝናን ሊያተርፉና ድጋፍ ሊያሰባስቡ ሲጥሩ የሚታዩ ግለሰቦችን ሕዝቡ ሊገስጻቻው ይገባል፡፡ ሥልጡን ሕዝብ ካሳለፈው መጥፎም ይሁን ጥሩ የታሪክ ሂደት ውስጥ ለዛሬ ሕይወቱ የሚጠቅሙትን ነገሮች በይቅርታ መንፈስ፣ በእውቀትና በሳይንሳዊ ምርምሮች ተደግፎ እያነጸ የአብሮነት ጉዞውን እጅ ለእጅ ተያይዞ ያሰምራል፡፡ በእኩልነት መንፈስም አንገቱን ቀና አድርጎ ብሩህ የሆነ ነገን ያልማል እንጂ ከመቶ አመት በፊት የነበሩ የታሪክ ግድፈቶችን እየመዘዘ የዛሬና የነገውን ትውልድ የአብሮነት ተስፋ አያጨልምም፡፡ በመካከላችን የተፈጠሩት ገደሎች እርስ በእርስ እንዳንደማመጥና ተደጋግፈን እንዳንቆም፤ በተናጠል በሚያጠቃን ሥርዓትም ዘንድ ኮስሰን እንድንታይ እያደረገን ነውና ገደሉን ልናጠበው ይገባል፡፡የፍትሕ ጥያቄ ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ ኃይማኖት ወይም ክልል አይገድቡትም፡፡ በማንም ሰው ላይ ይሁን በየትም ስፍራ የሚፈጽም ግፍና የፍትሕ መታጣት ሌላውን የሰው ዘር ሁሉ ሊቆረቁረውና እንቅልፍ ሊነሳው ይገባል፡፡ለዛም ነው በአፓርታይድ ዘመን መላው አለም ከደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች ጎን ቆሞ ለፍትሕና ለሰው ልጆች እኩልነት የታገለው፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን የአንባገነናዊ ሥርዓቶች አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ አድርገን ለማስቀረት፡-
- ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በየጊዜው የሚነሱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችንና ቁጣዎችን በሰከነ መልኩ እየመዘነ ብሔራዊ ነጻነትን ሊያጎናጽፈን ወደሚችልበት አቅጣጫ እንዲያመራ የበኩላችንን ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ‘እኔ’ ብለን ካጠርነው ጠባብ ምልከታ ውስጥ አራሳችንን አውጥተን ለፍትሕና ለነጻነት የሚደረጉ ሕዝባዊ እምቢተኝነቶችንስንደግፍና አጋር ስንሆን ነው፡፡
- ከላይ በዝርዘር ያነሳዋቸውን በሕዝቡ መካከል የተፈጠሩ ክፍፍሎች፣ ቅራኔዎችና እርስ በእርስ የመፈራራት ስሜቶች ለማጥፋትና ትግሉን በአገር ደረጃ ለመምራት የሚያስችል የድርጊት ግብረ ኃይል ለማቋቋም የሚያስችሉ የውይይት መድረኮችምበተቃዋሚ ፓርቲዎችና በተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎች በኩሉ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
- በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተጀመረው ሕዝባዊ ቁጣ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ የሶስት እዮሽ ግጭት እንዳይሆን፤ ማለትም በመንግስትና በሕዝብ፤ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ተደጋግመው የተከሰቱትን አይነት ቅራኔዎችና የጎሳ ግጭቶች እንዳያስከትል ጉዳዮ የሚመለከታችው አካላት ሁሉ ከወዲሁ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
- በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያንም በወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው የመብት ጥሰት፣ ግድያና አፈና ለመቃወምና ትግሉንም አገራዊ አቅጣጫ ለማዝያዝ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡
- ለበርካታ አመታት ይህን አይነት ሕዝባዊ ንቅናቄ የሚፈጠርበትን አንዳች ተአምር ወይም አጋጣሚ አድፍጠው ሲጠባበቁ የቆዩና ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት የጀመራቸውን ንቅናቄ በመጥለፍና አቅጣጫ በማሳት ለከፋፋይና ጠባብ ለሆነው የፖለቲካ አጀንዳቸው ማሳኪያነት ሊያውሉት የሚፈልጉ፤ እንዲሁም አገርንና ሕዝብን ለዳግም ደም አፋሳሽ እልቂት ሊዳርጉ ወደሚችሉ አቅጣጫዎች ትግሉን ሊገፉት የሚፈልጉ ኃይሎችን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የወያኔ አንድ አካል አድርጎ በመቁጠር ሊታገላቸውና ሊያስቆማቸው ይገባል፡፡
ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልልና በጎንደር በተቀሰቀሱት ግጭቶች ለተገደሉ ወገኖቻችን ቤተሰቦች ሁሉ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡
ፍትህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
ከብራስልስ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Wondemagne says
Excellent!