ባለፈው እሁድ ትንሽ ትልቅ፣ ወንድ ሴት፣ ከተሜ ገጠሬ፣ ሳይል የጎንደር ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በነቂስ ወጥቶ ከተማዋን ባጨናነቀ መልኩ የህወሓት አገዛዝ የፈጠረውን የሽብርና የፍርሃት አጥር ሰብሮ በመውጣት የተቃውሞ ድምጹን በሰላማዊ መንገድ አሰምቶ ወደቤቱ ተመልሷል። ምንም እንኳን አገዛዙ የተቃውሞ ሰልፉ እንዳይካሄድ ማናቸውንም እርምጃዎች ቢወስድም፣ ግፍ የበዛበት፣ የቆረጠና የተባበረን ሕዝባዊ ማዕበል የሚመክተው አንዳችም ምድራዊ ኃይል የለምና ከፍተኛ ጨዋነት በተሞላው መልክ ሕዝቡ ተቃውሞውን አሰምቷል። በዕለቱ ካስተጋባቸው መፈክሮች ውስጥ “በኦሮሚያ የሚደረገው የወገኖቻችን ግድያ ይቁም” የሚለው የጎንደር ሕዝብ ምንጊዜም በኢትዮጵያዊነትና በሀገር አንድነት ላይ ያለው የሚታወቀውን ጠንካራ አቋሙን ያሳየበትና የትግል አጋርነቱን በግልጽ ያንጸባረቀበት ነው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የሕዝብ መብቶች እንዲከበሩና የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተብዬው እንዲሰረዝ በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ላሰሙ ኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን አገዛዙ የሰጠው ምላሽ የሕዝብን ቁጣ በኃይል ለማፈን መሞከር ነበር። በዚህም ከአራት መቶ በላይ የሰው ሕይወት ጠፍቷል። የሕዝብን ቁጣ በኃይል መደፍጠጥ እንደማይቻል አገዛዙ የተማረ አለመሆኑን ያለፉት 25 ዓመታት የግፍ አገዝዙ ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል። እስካሁን በተለያዩ አካባቢዎች በተጠቀመበት ነጣጥሎ ማዳከምና መምታት በሚለው የማፈኛ ስልቱ በትላንትና ዕለት በምሥራቅ ሐረርጌ በአወዳይ ከተማ ውስጥ ባካሄደው ጭፍጨፋ በርካታ ዜጎችን ሲያቆስል የስድስት ወገኖቻችንን ሕይወት ማጥፋቱን የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋል። ህወሓት በጎንደር በተካሄደው ሰላማዊ ተቃውሞና ሕዝባዊ ማዕበልን መቋቋም እንደማይችል ምናልባት ተረድቶት ይሆናል የሚለውን ግምት ውድቅ እንዳደረገው እነሆ በአወዳይ ከተማ የፈጸመው ጭፍጨፋ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል። በመሆኑም ይህን ህወሓት የፈጸመውን አረመኔያዊ ድርጊት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አጥብቆ ያወግዛል።
ጆሮ ያለህ ስማ እንዲሉ የህወሓትን አፋኝ፣ ጨፍጫፊ፣ ዘረኛና አምባገነን ቡድን ማስታወስ የምንወደው በዓለም ዙሪያ የነበሩ አምባገነን አገዛዞች ሁሉ በውርደት ከሥልጣን መወገዳቸውን ቢያንስ የመንግሥቱን፣ የሙባረክን፣ የጋዳፊን፣ የሳዳምን…ወ.ዘ.ተ እጣ ፈንታ እንዴት እንደነበረ ነው። ስለዚህ የሥልጣን ምንጭና ባለቤት የሆነውን ሕዝብ መብት
አፍኖና በኃይል ረግጦ ለዘለዓለም መግዛት እንደማይቻል ተረድቶ ሕዝብ ለእልቂት፣ ሀገርም ለበለጠ ጉዳት ከመዳረጓ በፊት መብቱን በሰላም ለጠየቀ ሕዝብ ትክክለኛው ምላሽ እንዲሰጠው ይገባል እንላለን። ይህ ሳይሆን ቢቀርና ህወሓት እስካሁን በተከተለው ጎዳና ከቀጠለ ለሚደርሰው የሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ተጠያቂው ህወሓት ብቻ
መሆኑን ከወዲሁ መግለጽ እንወዳለን። ሕዝቡ የሀገር አንድነቱን ጠብቆ መብቱን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር የሚያደርገውን ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ እንደሚደግፍ በማያሻማ ቋንቋ እየገለጸ፣ በሚችለው ሁሉ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
አንድነቷ የተጠበቀ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሕዝብ ትግል ትመሠረታለች!
ሐምሌ 26 ቀን 2008 ዓ. ም (August 2, 2016)
Tel: 44 7937600756 , +1 9168486790 E-mail : shengo.derbiaber@gmail.com
Leave a Reply