
የኢትዮጵያን ችግር የመፍትሄ መንገድ በሚመለከት “ኢትዮጵያን ለማዳን እንነጋገር” በሚል ርእስ ቀደም ሲል አንድ የሰላም ጥሪ ማቅረባችንን እናስታውሳለን። መልእክቱም ባጭሩ ይህች ታላቅ ሀገር የገጠማት ችግር ሊፈታ የሚችለው በመሪዎቿና በልዩ ልዩ የተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ የራሷ ልጆች ብቻ መሆኑን፤ መፍቻ መንገዱም ውይይትና ንግግር መሆኑን፤ ጊዜውም አሁን መሆኑን የሚያመላክት ነበር። ለዚህም ሁሉም ወገኖች ቢያንስ በችግሩ ላይ ለመነጋገር መስማማት እንዳለባቸው በመጠቆም ለሰላማዊ ውይይት እንዲተባበሩና ሃሳባቸውን እንዲገልፁልን አሳስበንም ነበር።
ጥሪውን የተመለከቱ ድርጅቶችና ግለሰቦች የሰጡንን በጎ ምላሽና ማበረታቻ በምስጋናና በአክብሮት ተቀብለናል፤ ደስ ብሎናልም። የሰላም ውይይት ወደሰላም በር የሚወስድ ጠቃሚ ስልት መሆኑን በማመን ድርጅታችን ላቀረበው የውይይት መድረክ ዝግጅት ሃሳብ በፅሁፍም ሆነ በቃል ድጋፍና በጎ ምላሽ ለሰጣችሁ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን። ወንድምና እህትማማች የሆኑ የኢትዮጵያን ልጆች በሰላም ተነጋግረው ችግራቸውን የመፍታት አቅም እንዳላቸው በማመን የሚገናኙበትን መድረክ ለመፍጠር የጀመርነውን ጉዞ በፅናት እንድንቀጥል ያገኘነው በጎ ምላሽና የትብብር ተስፋ አዲስ ጉልበት የሰጠን ስለሆነ ለስኬቱ ተግተን እንሰራለን።
ኢትዮጵያውያን ዛሬ የገጠማቸውን ችግር በውይይት ለመፍታት ቆርጠው እንዲነሱ ለቀረበው ጥሪ እስካሁን የተሰጠው በጎ ምላሽና የድጋፍ አስተያየት ተስፋ ሰጪ ነው። ይሁን እንጂ ስራው ገና ብዙ ድካም እንደሚጠይቅ መታመን አለበት። ሰላማዊ ውይይት ሃሳቡ ማራኪ የመሆኑን ያህል ዋጋው ውድ ነው። የተለያየ ሃሳብ ያላቸው የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች እንድትኖራቸው የሚናፍቋትንና በፍቅር የሚኖሩባትን የጋራ ሀገር እንደገና ለመፍጠር በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመምከር በአንድ የውይይት ማእድ ቀርበው ሲወያዩ ማየትን ለመሰለ ታላቅ እድል ለመብቃት ወሰን የሌለው መስዋእትነት መክፈል ያስፈልጋል። ድርጅታችን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ምድር ጭምር ሰላምና የህግ የበላይነት ይሰፍኑ ዘንድ የአቅሙን ለመስራት የተነሳው ይህ ታላቅ ግብ የሚጠይቀውን የመስዋእትነት ክብደት በመዘንጋት ሳይሆን የመስዋእትነቱን አስፈላጊነት ጭምር በመቀበል ነው።
ኢትዮጵያውያን ወገኖችም የራሳቸውን ችግር ለመፍታት እስከፈቀዱና ለመተባበር እስከቆረጡ ድረስ የሰላም ጉዞው የቱንም ያህል ዋጋ ቢጠይቅ ለስኬት እንደምንበቃ ጥርጥር የለንም። በዚህ ነጥብ ላይ ለሰላማዊ ድርድር ተስፋ ቆርጠናል ከሚሉ ወገኖች እንለያለን። በመሆኑም ሰላምና ፍትህ ለአፍሪካ ወንድምና እህት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የገጠመውን ጊዚያዊ ፈተና አሸንፎ እንዲወጣ መሪዎቹና ተቃዋሚ ሀይሎች እስካሁን የሄዱበትን ጎዳና ዳግም በማጤን በሆደ ሰፊነትና በሀላፊነት ስሜት ለትውልድ በኩራት የሚተላለፍ ታሪክ እንዲሰሩ ለመርዳት በጀመረው ጥረት ይቀጥላል። ሃሳቡ መልካም የመሰላችሁ ወገኖች ሁሉ በምትችሉት መንገድ ድጋፋችሁ እንዲቀጥል እናሳስባለን።
ለሀገራቸው የየራሳቸው ህልም ያላቸው ግን ደግሞ የአንድ እናት ልጆች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአንድ መድረክ ለሰላም እንዲመክሩ የምናደርገው ጥረት ይሳካ ዘንድ ሁሉም ወገኖች የየበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱና ትብብር እንዲያደርጉ እንጠብቃለን።
የሰላም ውይይት መድረክ አስፈላጊነትና አጣዳፊነት
መንግስትና ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ የሚሳተፉበት የሰላም ውይይት መድረክ ባስቸኳይ መዘጋጀት አለበት የምንልበት አጣዳፊ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።
- ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል የሰላም ምክክር ባጣዳፊ ካልተጀመረ ግጭቱ ተዳፍኖ ከቆየ በኋላ ባልተጠበቀ መንገድ መልኩን ሊለውጥ ይችላል። በመሆኑም ችግሩ ከፍቶ ወደ ብሄር ወይም ጎሳ ግጭት ሳይለወጥ አሁን ባለበት ደረጃ እያለ መፍታት ይቻላል።
- የሰላም ጥረቱ በዘገየ ቁጥር በየስፍራው በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ የሚነሱ አዳዲስ አመለካከቶች አዳዲስ ችግሮችን በመፍጠር ግጭቱን እያባባሱት ስለሆነ ችግር በችግር ላይ እየተደራረበ በየትኛውም መንገድ ለመፍታት በሚከብድ የተወሳሰበ ደረጃ ላይ ሳይደርስ በጊዜ መቆጣጠር አስፈላጊ ስለሆነ ነው።
- የሰላም መፍትሄው በዘገየ ቁጥር አዳዲስ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አዳዲስ የፖለቲካ ሀይሎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ስለሚሆንና ይህም የመፍትሄ ማፈላለጉን ተግባር የበለጠ የሚያከብደው በመሆኑ ነው።
ስለዚህ መንግስትና ተቃዋሚ ሀይሎች ሁሉ የሰላም ውይይት አስፈላጊነትንና አጣዳፊነቱም ጭምር በመገንዘብ በተለይ የሚከተሉትን ሀሳቦች በማጤን የስነልቡና ቁርጠኝነት እንዲያሳዩና ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪያችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን።
- ኢትዮጵያን የገጠማትን ችግር በሰላማዊ ውይይትና ድርድር መፍታት ይቻላል፤ በዚህ መንገድ የሚደረስበትም ስምምነትና መፍትሄ ዘላቂ ስለሚሆን ጠቃሚ ነው። ስለዚህ መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ሀይሎች ለሰላማዊ ውይይትና ድርድር ቁርጠኝነት ማሳየትና ይፋ አቋማቸውን መግለፅ ይኖርባቸዋል። በሰላም ምክክርና ድርድር ጉዳይ ላይ ያላቸውንም አቋም በደብዳቤ 840 1st St NE Washington DC 20002 በኢሜል peaceafrica16@gmail.comቢልኩልንእናመሰግናለን።
- የወቅቱን የኢትዮጵያን ችግር ባስተማማኝና ዘላቂ መንገድ ለመፍታት በተናጠል ከሚወሰድ እርምጃ ይልቅ የጋራ ምክክርና ስምምነት የበለጠ ጠቃሚ እንደሚሆን መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ሀይሎች ሊያምኑበት ይገባል።
- የሰላማዊ ውይይት ፍላጎት የሽንፈት መገለጫ ሳይሆን የብስለትና የስልጣኔ እርምጃ መሆኑን ከልብ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። ለዚህም እልህን ማሸነፍና በሰላምና በሰከነ መንገድ የሚደረግ ውይይት ከመንግስትና ተቃዋሚ ሀይሎች በላይ ለህዝብና ለሀገር የሚበጅ ተግባር መሆኑን ማመንን ይጠይቃል።
- ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታና የገጠማትም ችግር አዲስ አቀራረብና አመለካከት የሚጠይቅ ነው። ስለሆነም መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ሀይሎች የድርጅት መርሃ-ግብርና የፖሊሲ አጥርን በመሻገር ተቀናቃኝን ፊት ለፊት ገጥሞ በመከራከር ረገድ እስካሁን የሄዱትን ርቀት አልፈው ለመጓዝ ሊዘጋጁ ይገባል።
- በሰላምና ድርድር ጉዳይ ላይ የሚሰሩ አካላትም ሆኑ የድርጅታችንን የሰላም ጥረት የሚደግፉ አካላት በሚችሉት መንገድ ሁሉ እንዲረዱና እንዲተባበሩ ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን። በዚህ አጋጣሚ ሃሳባችን ቀና መሆኑን በመመልከት ገንቢ አስተያየት የሰጣችሁንንና ድጋፍ ልታደርጉልን ጥረት እያደረጋችሁ ላላችሁ አካላት ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ሰላምና ፍትህ ለአፍሪካ
ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም
ዋሽንግተን ዲሲ
This is a good idea to create the dream land that is always in our minds.