ኢትዮጵያ በአፍሪካና አለም ታሪክ አኩሪ ስም ይዛ የኖረች ታላቅ ሀገር ናት። ልጆቿ ጎሳና ቋንቋ ሳይለያቸው ለሃገራቸውና ለክብራቸው በቆራጥነት በከፈሉት የጋራ መስዋእትነት ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአህጉራቸው ህዝብ ጭምር ክብር ያጎናፀፉ ጀግኖች መሆናቸውን ያስመሰከሩባት የአበሻ ምድር ናት። ኢትዮጵያ በሽታ ድህነትና ማይምነት ሳይበግረው የውጪ ጠላትን ያንበረከከ ጀግና ህዝብ ያላት ታምረኛ ሃገር ናት። ኢትዮጵያ የራሳቸውን ያገር አንድነት በሚያስደንቅ ወኔ ህይወታቸውን በመገበር ለአፍሪካ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው አለኝታነታቸውን ያረጋገጡ ኩሩ ህዝብ ሃገር ናት። ኢትዮጵያ ከራሷም አልፋ ላለም ሰላምና ደህንነት የታገለችና በጥቁር ህዝብ አኩሪ ታሪክ ተምሳሌነቷ ለትውልድ ልእልና ያጎናጸፈች የጀግና ህዝብ ምድር ናት።
እንዳለመታደል ሆኖ ያቺ ስመገናና ሃገር ያች በህዝ ያገር ፍቅር ወኔና ጀግንነት አለምን እፁብ ድንቅ ያሰኘች ሃገር ያች ከራሷ አልፋ ለአፍሪካና ለአለም ህዝቦች ጠበቃ የነበረች ሃገር ዛሬ ራሷ በወጉ። መቆም አቅቷት ይልቁንም ህልውናዋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ስትንገዳገድ ማየት የገናና ታሪኳ ባለቤት የሆነውን ህዝቧን አንገት የሚያስደፋ አሳዛኝ ሁኔታ ሆኗል። በሚያስደንቅ ህብረት ችግሩን ችግር አድርጎና መከራውን ችሎ ኢትዮጵያ የምትባል የክብር ሃገር የፈጠረ ህዝብ ዛሬ ፍቅርን በጠብ፣ ወንድማማችነትን በደመኝነት፣ ሃገራዊ ክብርን በውርደት ለመለወጥ የወሰነ በሚያስመስል አሳሳቢ የታሪክ አጋጣሚ ላይ ይገኛል። ቋንቋና ጎሳ ሳይቆጥሩ ለአንድ የጋራ ሃገራቸው ክብር፣ ለህዝባቸው ልእልና ደማቸውን በአንድ ጅረት ያፈሰሱና አጥንታቸውን በጋራ የከሰከሱ የዛች ታላቅ ሃገር ልጆች ዛሬ መደማመጥ ተስኗቸው እና ከኮሳና ከፖለቲካ እምነት በላይ፥ ሃገር፥ የምትባል አንድ የክብር መርከብ መኖሯን ሳያስተውሉ በክብር የተረከቧትን ውድ እናታቸውን የውርደት አፈር ሊያለብሷት ሲታገሉ ማየት እጅግ ታላቅ የህሊና ህመም ነው። የቋንቋ የሃይማኖትና ጎሳ አጥር ሳይለያቸው ባንድነት ሞተው ያገርና ህዝብ ክብር ያስጠበቁ የነዚያ ጀግኖች ልጆች ዛሬ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ከበው በመነጋገር የሃገራቸውን አኩሪ ታሪክ ከማስቀጠልና የአባቶቻቸውን አደራ ከማስከበር ይልቅ የጀግኖችን የክብር ስጦታ በውርደት ለመለወጥ መወሰናቸው ለምን እንደሆነ ለማንም ሊገባ የማይችል እንቆቅልሽ ነው።
አሁን ግን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ቀልብ ገዝተው ይህን እንቆቅልሽ በመፍታት ሃገራቸውን ከውርደት ህዝቧንም ከመከራ ለማዳን ቆርጠው መነሳት አለባቸው። ዛሬ ማንኛውም ግለሰብና ቡድን አባቶቹ ለክብሩና ለእናት ሃገሩ የከፈሉትን ህይወት ብቻ ሳይሆን ራሱም ላለፉት 40 አመታት ያህል ያፈሰሰውን ደም አላማ ቆም ብሎ የሚያስብበት ወሳን ወቅት ላይ ነው። ባለፉት 40 አመታት ሁሉም ላገር ይበጃል ባለው ጎራ ተሰልፎ የከፈለውን መስዋኢትነት መመርመርና የመጨረሻ ግቡን ማስተዋል ይኖርበታል። ሁሉም በየጎራው ያፈሰሰው ደም የከሰከሰው አጥንት መንገዱ ይለያይ እንጂ ኢትዮጵያ የምትባል የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አንባ ለመፍጠር እንደነበረ ማረጋገጥ አለበት። ግለሰቦችና ቡድኖች ወደኋላ መለስ ብለው የእስከዛሬ የታሪክና የትግል ጉዟቸውን ሲመረምሩ ዛሬ ኢትዮጵያ የምተገኝበት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ አቅደው ያለመነሳታቸውን ይረዳሉ። ይህም እጅግ የሚያሳዝናቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
ሆኖም ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የታሪክ ምእራፍ ታሪክን ብትዝታ ለማሰብና ለመቆጨት ጊዜ የሚሰጥ አይደለም። ወዲያውም ቁምነገሩ አሁን ሃገሪቱ የገጠማትን ችግር መፍታት እንጂ እነማን ምን አደረጉ በሚል ትርጉም አልባ ጥያቄ ላይ መቆዘሙ አይደለም። አሁን ወቅቱ ሃገሪቱ ለገጠማት ችግር ተጨባጭ መፍትሄ ለማግኘት ሁሉም በጋራ አዲስ ሰላማዊ እስትራትጂ የሚቀይስበት ወቅት ነው። መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ሃይሎች ዛሬ የምንገኝበት ወቅት በሰለጠነ አስተሳሰብ አዲስ ስልት በትብብር የምንቀይስበት ጊዜ መሆኑን በማጤን ላዲስ መፍትሄ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ሃይሎች የእስከዛሬ ትግል እውነተኛና የመጨረሻ ግብ ያገርና ህዝብ ጥቅም ከሆነ ይህን የጋራ ግብ ለማሳካት የሚተባበሩበት ጊዜ አሁን ነው። ኢትዮፕያንና ህዝቧን የሚወድ ግለሰብም ሆነ ቡድን ሃገሩንና ህዝቡን ከውርደት እና እልቂት የሚያድንበት ወሳኝ ወቅት አሁን ነው።
መንግስት ባለፉት 24 አመታት ሃገሪቱን ይበጃል ባለው መንገድ ለመምራትና ስኬት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህም ሂደት በተለይ በኤኮኖሚው ዘርፍ ተጠቃሽ ስኬት መገኘቱ የሚካድ አይደለም። በፖለቲካውም ዘርፍ ቢሆን በሃገሪቱ የፖለቲካ ባህል አዲስ የሆነ የመድብለፓርቲና የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት ተሞክሯል። እንዲያም ሆኖ የተቃውሞ ፖለቲካውና አካሄዱ ውዝግብና ግጭት የበዛበት ሆኖ ይታያል። የንፁሃን ዜጎች ህይወትም የሚጠፋበት ግጭት መከሰቱ እጅግ አሳዛንና አሳሳቢ ነው። ይባስ ብሎ የሰላማዊ ተቃውሞውን ወደ ትጥቅ ትግል የለወጡ ሃይሎችም ተፈጥረዋል። ባገር ውስጥ የሚካሄደው ሰላማዊ ተቃውሞም ቢሆን ጤናማ አይደለም። የዚህ ድምር ውጤት የህዝብ ሰላምና ፀጥታ መታወክና መደፍረስ ሆኗል። አስፈላጊ ያልሆኑ ግጭቶችን በማስወገድ ሁኔታውን ለማስተካከልና ጤናማ የፖለቲካ ድባብ ተፈጥሮ ሰላም ባስተማማኝ እንዲሰፍን ለማድረግ ከየትኛውም ሃይል በበለጠ መንግስት ሃላፊነት ወስዶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ጉዳይ ከመንግስት በላይ ቀዳሚ ሚና ሊኖረው የሚችል ወገን የለም። መንግስት ያገርና ህዝብ መሪ እንደመሆኑ የሃገሪቱ የፖለቲካ አቅጣጫ መልክ እንዲይዝ የማድረግ አቅሙም ሆነ ሃላፊነቱ ይፈቅድለታል። ስለሆነም በሰከነና በሆደሰፊነት ነገሩን በማጤን በሁሉም አካላት መካከል ሰላም ተፈጥሮ በወንድማማችነትና መፈቃቀድ መንፈስ በችግሩ ላይ መነጋገር የሚቻልበትን መድረክ መፍጠር ይኖርበታል። በዚህ ጥረቱ አገርአቀፍና አለማቀፍ ሰላም ወዳድ ሃይሎች ሁሉ ከጎኑ እንደሚቆሙ ጥርጥር የለውም። የአፍሪካ ሰላም ድርድርና እርቅ ተቋምም ከሌሎች መሰል አላማ ካላቸው ገለልተኛ ወገኖች ጋር በመተባበር በዚህ ጉዳይ ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በታላቅ አክብሮት ይገልፃል።
የፖለቲካ ቡድኖችና ሃይሎችም ሁሉ የእስከዛሬ ትግላቸው እና መስዋእትነታቸው ፍሬ አፍርቶ በየበኩላቸው የሚገባቸውን የታሪክ ክብር እና ሞገስ ማግኘት የሚሹ ከሆነ ሃገራቸው ዛሬ ከምተገኝበት አስጨናቂ ፈተና ሊያወጣት በሚችል አዲስ ሰላማዊ መንገድ ላይ መስማማት አለባቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ የምትፈልገውና ከጭንቅ የሚያወጣት ብቸኛው መንገድ ሰላምና ፍቅር ብቻ ነው።
የእርስ በእርስ እልቂት ላገር ጠቅሞ አያውቅም። በጦርነት ድሞክራሲና ብልፅግናን ማምጣት አይቻልም። የመጠፋፋት ፖለቲካ ጎዳ እንጂ ህዝብ የሚፈልጋትን ኢትዮጵያ መፍጠር አላስቻለም። የጉልበት ትግል የጥፋት እንጂ የእድገት መንገድ አልሆነም።
ዛሬ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አዲስ ታሪክ ሊሰራ መዘጋጀት አለበት። በጦርነትና ጉልበት ያጣናትን ኢትዮጵያ በሰላምና ፍቅር መድረክ ዳግም ልንፈልጋት አሁን ጊዜው የግድ ብሏል። አስተዋይ ህሊና ያለው ግለሰብም ሆነ ቡድን የኢትዮፕናዊያንን ነባርና ዘላቂ ችግር መፍቻው ትክክለኛውና አማራጭ የሌለው መንገድ ሰላምና እርቅ ብቻ መሆኑን ማመን አለበት። በዚህ ታሪካዊ ወቅት ሰላም፣ እርቅ፣ ድርድርና ውይይት የማይቀበል ወገን ኢትዮጵያ ለዘላለም እንድትጠፋ የወሰነ ወገን ብቻ መሆን አለበት። በዚህ ፈታኝ ወቅት የሰላምን መንገድ የሚጠላ ወገን ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።
ሰላም ፈላጊነት አሸናፊነት ነው። ሰላም ወዳድነት የሃገር ወዳድነት መገለጫ ነው። ሰላም ወዳድነት አስተዋይነት ነው። ሰላም ወዳድነት ጀግንነት ነው። ሰላም ወዳድነት ስልጡንነት ነው። እናም ኢትዮጵያን ሁሉ ልዩነታቸውን ወደጎን በመተው ለህልውናዋና ለህዝቧ ደህንነት እና ለዘላቂ ሰላም በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ከበው በድፍረት የሚመክሩበት ጊዜ አሁን ነው። የታሪክ ቁርሾዎችን ጥለው ዳግም ወደጦርነት ላይገቡ በመማማል በልዩነት ደምቀው ሃገራቸውን በፍቅር መገንባት እንደሚችሉ ለአለም አዲስ ታሪክ ሰርተው ማሳየት አለባቸው። ኢትዮጵያዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸው የሚያሳዩበት አጋጣሚ አሁን ነው። መቼም ኢትዮጵያዊያን በግትርነትና በእልህ ይህን የታሪክ አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተው ሃገራቸውን ለውድቀት ህዝብንም ለውርደት ወደሚዳርግ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን መመለሻ ወደሌለው ገደል ለመክተት ይወስናሉ ብለን አናምንም።
በመሆኑም የአፍሪካ ሰላም ድርድና እርቅ ተቋም የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በመመርመርና የችግሩ መፍቻ መንገድ ሰላም ብቻ መሆኑን በማመን ለኢትዮጵያ መንግስትና ለተቃዋሚ ሃይሎች ሁሉ የሚከተለውን ጥሪ ያስተላልፋል።
- መንግስትና በየጎራው የተሰለፉ ተቃዋሚ ሃይሎች ሁሉ ለኢትዮጵያ ነባራዊና ወቅታዊ ችግር መፍትሄ ሰላማዊ መንገድ መሆኑን እንድቀበሉ
- ባገር ውስጥም ሆነ በየድንበሩ የሚካሄዱ ግጭቶች ባስቸኳይ እንድቆሙ
- የኢትዮጵያ መንግስት የሃገሪቱን ችግር ለመፍታት ሲል በሆደሰፊነት ባስተዋይነት መንፈስ በሰላምና እርቅ ጉዳይ ላይ ያለውን ግልፅ አቋም በይፋ እንድገልፅ
- ለኢትዮጵያ ችግር ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት በሰላምና እርቅ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ አካላት ሁሉ ግንባር በመፍጠርና ሃይላቸውን በማስተባበር በጋራ የሚሰሩበትን መንገድ ባስቸኳይ እንዲቀይሱ እያሳሰብን የአፍሪካ ሰላም ድርድርና እርቅ ተቋም በዚህ ጉዳይ ከሚሰሩ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ለመስራት ዛሬ ነገ ሳይል ባፋጣኝ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን ይገልፃል
ለዚህም መንግስት፣ አገርአቀፍና አለማቀፍ ሰላም ወዳድ ሃይሎች ሁሉ ጉዳዩን በቅንነት እና በቆራጥነት በመመልከት ለሰላም ጥረቱ ስኬት እንዲተባበሩ ተቋሙ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ታህሳስ 13 ቀን 2008 አም
የአፍሪካ ሰላምድርድርና እርቅ ተቋም
ዋሽንግተን ዲሲ ዩናይትድ ስቴትስ
African peace mediation Institution
afripmri@gmail.com
Leave a Reply