
የሰላማዊ ትግል ተግባራዊነትና ስኬት መለኪያው ምንድን ነው? በዚህ ልጀምር ጽሑፌን። በርግጥ መጀመር ያለበት፤ ሰላማዊ ትግል ምንድን ነው? የት ተተገበረ? እንዴት ተተገበረ? ከትጥቅ አመጹ በምን ተሽሎ ይገኛል? እዚህ ሰላማዊ ትግል፤ እዚያ ግን የትጥቅ ትግል የሚባለው እንዴት ነው? በሚሉት ነበር። ነገር ግን፤ አንባቢዬ በትክክል እንደሚረዱት፤ አሁን የያዝነው፤ በተጨባጩ በሀገራችን ባለው የፖለቲካ ሀቅ፤ ምን ላይ ነው ያለነው? ምን ማድረጉ ለትክክለኛው ሕዝባዊ ድል አመርቂ ውጤት ያስገኝልናል? ከሚለው በመነሳት ነው። እንግዲህ መሠረታዊው መነሻ፤ አሁን ያለንበት የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ ነው፤ ማለት ነው። እዚህ ላይ ነው እኔ፤ ሽንጤን ገትሬ፤ “ሰላማዊ ትግሉ ያቸንፋል!” በማለት የቆምኩት። እናም ላስረዳ!
ገዥው ወገንተኛ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፣ ከሕዝቡ ተነጥሎ ቆሟል። ሀገራችንን የሚገዛት እንደ ወራሪ ኃይል ሆኖ፤ ፍጹም ፀረ-ኢትዮጵያዊነትን በአደባባይ እየተነፈሰ ነው። ሕዝቡ መሮት በተነሳበት በአሁኑ ሰዓት፤ ዘመናዊ መሣሪያ እስካፍንጫው ታጥቆ፤ በራሱ ምርጥ ሰዎች መንግሥታዊና ግላዊ መዋቅሮች ሰግስጎ፤ የሕዝቡን መነሳሳት በአረመኔነት ለመቅጨት፤ ላይ ታች ይሯሯጣል። ለጋ ወጣቶችን በወገንተኛ ሰበካው በመበረዝ፤ በመዋቅሩ ሰካክቶ አስገብቶ፤ አዲስ ኢትዮጵያዊያን ለመፍጠር እየጣደፈ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም፤ አሰላለፉን አሳምሮ፤ ለዴሞክራሲ አቀንቃኞች ዴሞክራት በመምሰል፤ ለልማት ጎትጓቾች የልማት አራማጅ በመምሰል፤ እንደ ሁኔታው ፊቱን እየኳኳለ ቀርቧል። ካንድ ወዳጄ ጋር ስንጫወት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር እኮ ውስጡ በስብሷል ለሚለው መልስ፤ ከሚያውቀው የድሮ አባባል መዥርጎ አውጣና፤ “ታዲያ ተወው እንጂ፤ እዚያው ትል ይፍጠር!” አለኝ። ትግሉን የሚወስነው፤ የኛ የታጋዮቹ ሁኔታ እንጂ፤ የምንታገለው አካል አይደለም። ያማ ለሕልውናው የማያደርገው ነገር የለም። እናም በገዥው ማንነትና ተግባር፤ ትግሉ አይወሰንም። ትግሉ የሚወሰነው፤ ይሄን የገዥውን ማንነትና ተግባር በማጤን፤ ታጋዮች በሚያደርጉት ዝግጅትና በሚወስዱት እርምጃ ነው።
የሰላማዊ ትግሉን አስመልክቶ የሚቀርቡት መቃወሚያ መደምደሚያዎች የሚከተሉት ናቸው።
የመጀመሪያው፤ “የሰላማዊ ትግል በሮች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል!” የሚለው ነው። እንዴ! የሰላማዊ ትግል በሮች ሙሉ ለሙሉ ይዘጋሉ ወይ? ይሄ ምን ማለት ነው። ይህ ለኔ የሚያመለክተው፤ የሰላማዊ ትግሉን ምንነት ከመረዳት ጉድለት መኖሩን ነው። ሰላማዊ ትግል እኮ፤ መስመር ተደርጎ፤ “ከዚህ በፊት ሰላማዊ ትግል፤ ከዚህ በኋላ ሰላማዊ ትግሉ አበቃለት፤ ዛሬ በሩ ተከፍቷል፣ ትናንት በሩ ተዘግቷል እና የትጥቅ ትግል ይጀምራል።” የሚባልበት ክስተት አይደለም። መቼም ይሄን በሚመለከት በተደጋጋሚ የጻፍኩበት ስለሆነ፤ መልሼ አልደርትበትም። የምርጫ ትዕይንቱ መዘጋት፤ የሰላማዊ ትግሉ በር መዘጋት አይደለም። የገዥው ክፍል እንደ እስስት ቆዳው መቀያየሩም እንኳ፤ የሰላማዊ ትግሉን ሂደት አይወስነውም። የሰላሙን ትግል የጀመሩት ሰላማዊ ታጋዮች ናቸው። የትም ሀገር ሆነ በማንኛውም ታሪካዊ ወቅት፤ ሰላማዊ ትግል አድርጉና ቀይሩኝ ብሎ የፈቀደ አምባገነን መንግሥት የለም። ሊያደርገውም የሚፈልግ ሆነ የሚሞክር የለም። በምርጫም አስወግዱኝ ብሎ በሩን ከፍቶ የሚያስተናግድ አምባገነን መንግሥት አልተፈጠረም። በምርጫ የሚያምንና ያን የሚያደርግ፤ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ነው። ያን መንግሥት ለመቀየር ደግሞ፤ ሰላማዊ ትግል አይደረግም። ውድድር ማድረግ ብቻ ነው። ኑሮ ግድ ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስቃይ ውስጥ ሲከተው፤ መንግሥት የሕዝቡ አገልጋይ መሆኑ ቀርቶ ሕዝቡ የመንግሥቱ አገልጋይ እንዲሆን ሲደረግ፣ መንግሥቱ ጠባብ፣ ወገንተኛና አምባገነን ሲሆን፣ ታጋዮች እምቢ ብለው ተነሱ። በሰላም የመታገሉን ፈቃድ ከማንም አላገኙም። ፈቃጁም ሆነ ሰራዡ ታጋዮቹ ናቸው። የሰላማዊ ትግሉንም በር የሚዘጉት፤ ሰላማዊ ታጋዮች፤ አሁን ግባችንን መትተናል፤ ካሁን በኋላ ሰላማዊ ትግሉ አበቃ ብለው፤ እጃቸውን ሲያነሱ ብቻ ነው። በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ቀን ከሌት የሚሰቃዩት ኢትዮጵያዊያን ይሄን አላሉም፤ አይሉምም፤ ስቃያቸው እስካላቆመ ድረስ!
ሁለተኛው ደግሞ፤ የገዢውን ቡድን የአድራጊ ፈጣሪነት ሚና አግዝፈው፤ በሁሉም ቦታ አለ፣ ሕዝቡን አስሮ ይዟል፣ አንድ ለአምስት በመጠርነፍ መፈናፈኛ አሳጥቷል፣ በምንም መንገድ ለሰላማዊ ትግሉ ቀዳዳ አይሠጥም የሚባለው ነው። በተጨማሪ ደግሞ፤ እኒህ ገዥዎች በዚሁ ያለፉበት ስለሆኑ፤ “ማንኛውንም የአደረጃጀት ሂደት ስለሚያውቁት፤ ከሕዝቡ ቀድመው ሁሉን ያውቁታል!” እናም “በምንም ዓይነት መንገድ ከዚህ መንግሥት ውጪ መደራጀትና ማደግ አይቻልም!” የሚባለው ነው። እንዴ! ሕዝቡኮ ከገዢው ቡድን ይበልጣል፣ ይበዛል፣ ይልቃል፣ ያውቃል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ዕድሜውን ሊያራዝም የሚችለው፤ ሕዝቡን በማሰቃየት፣ በማግለል፣ በማሰር፣ ካገር በማባረር፣ በጣም ጥቂቶቹን ከአብዛኛው በማስበለጥና ወገንተኛ በመሆን ነው። ይህ ደግሞ ከሞላ ጎደል ኢትዮጵያዊያንን በያሉበት በድሏል፣ አስቆጥቷል፣ አነሳስቷል። ስለዚህ፤ በምንም መንገድ ቢሆን፤ የአምባገነኑ ወገንተኛ ገዢ ቡድን ማንኛውም ጥረት፤ ከሕዝቡ የኑሮ ስቃይ እውቀት አይበልጥም። ሕዝቡ እየተፈተነ ያለው፤ በመሞትና በመኖር መካከል ነው። ሌላ ምርጫ የለውም። በየዕለቱ በአምባገነኑ ቡድን በሚደርስበት በደል ዙሪያ በሚደረጉ አመጾች፤ ሕዝቡ አቸናፊ ይሆናል። ሌላው የድርጅቶች ድርሻ ነው።
ሶስተኛው ደግሞ፤ “አሜሪካ፣ አውሮፓና ቻይና ስለሚደግፉት፤ በምንም መንገድ፤ በሰላማዊ ትግል ገዢው ቡድን አይወድቅም!” የሚለው ነው። እንዴ! መቼ ነው ለውጭ ሀገር መንግሥታት፤ እጃችንን አራግበን፤ ያውላችሁ እንደወደዳችሁ ብለን፤ የሀገራችንን የትግል ሂደት ወሳኝነት ቦታ የሠጠናቸው? እኛው ሠጪና ነሺ ከሆን ደግሞ፤ በጃችን ያለውን ወሳኝነት፤ እንዴት አድርገን ነው የነሱ ነው የምንለው! ትናንት በኤርትራ ጉዳይ፤ እኒሁ ምዕራባዊያን፤ ከጣሊያን ጋር አብረው መቆማቸውን ረሳን እንዴ! ቻይና እኮ ከማንም የባሰች አፋኝ ሀገር ናት! ከሷ ምን ይጠበቃል! የኛን የኛ እናደርገው።
አራተኛው ደግሞ፤ “ሕዝቡ አንድ አይደለም። ሕዝቡ አልተነሳም። ሕዝቡ ባልተነሳበት ወቅት፤ ሰላማዊ ትግሉ አይሠራም።” የሚለው ነው። እንዴ! ደግሞ በሕዝቡ ማሳበብ ጀመርን! ሀቁንማ መቀበል ያስፈልጋል። ደግሞስ ሕዝቡ ለሰላማዊ ትግሉ ካልተነሳ፤ እንዴት ብሎ ነው ለትጥቅ አመጹ የሚነሳው? ሕዝቡ ከድርጅቶች ደጋግሞ ቀድሞ ተገኝቷል። አሁንም ከድርሻው በላይ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው። ከዚህ በላይ ሕዝቡ ምን ያድርግ? የፖለቲካ ድርጅቶች ማድረግ ካለባቸው በላይ ጋዜጠኞች ፍዳቸውን እያዩ አይደለም! ሕዝቡ ለምን ሠረታችሁ ተጠቀማችሁ በመባል ንብረታቸው እየተነጠቀ አይደለም? ይሄን ሕግ አላከበራችሁም፣ ዓይናችሁ አላማረንም አየተባሉ አየተጎሳቆሉ አይደለም? ሕዝቡ ያለድርጅትና ያለመሪ ሀገሩን ነፃ የሚያወጣ ከሆነ፤ የታጋዮች አስፈላጊነት የቱ ላይ ነው? ሕዝቡንስ አንድ ለማድረግ፤ በአንድነት ትግል ማካሄዱ አይበጅም!
እውነቱን እንቀበል! የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ከሁሉ በላይ የሚፈራው ነገር ቢኖር፤ የሕዝቡን አንድነት ነው። የሕዝቡን ሰላማዊ አመጽ ነው። ታጋዮች ሕዝቡን እንዳያገኙ ያላደረገውና የማያደርገው ነገር የለም። በዚህ መንግሥት እምነት፤ ታጋዮችን ከሕዝቡ ነጥሎ በማሰር፣ በማባረርና በመግደል፤ ሰላማዊ ትግሉን የሚገታ መስሎት ተያይዞታል። ነገር ግን፤ ሰላማዊ ትግሉን የሚያራምዱት የሕዝቡ አካል ናቸው። አንዱ ሲታሰር በሕዝቡና በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መካከል ባለው ቅራኔ የተጸነሱ፣ በሕዝቡ ብሶት የተፈለፈሉ፤ ሌሎች በብዛት እየተከተሉት፤ የበለጠ ውጥረት ውስጥ ከተውታል። ሰላማዊ ትግሉም የመብራት አጥፊና አልሚ ቁልፍ የሚቆጣጠረው፤ አንዴ የሚበራ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚያጠፋ አምፖል አይደለም። ምንነቱ በሆነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ባህርይ የተቀረጸ የሕዝብ አመጽ ነው። ሰላማዊ ትግሉ ከሕዝቡ ብሶት ጋር የተቆራኘ ክስተት ነው።
ይልቅስ በሰላማዊ ትግሉ ዙርያ አመርቂ የሆነ ውጤት ለማምጣት፤ በአንድነት አብረን እንነሳ። በሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ የሚታዩ፤ ከፋፋይ የሆኑ፤ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ይሄን ማስወገጃው በአንድነት መነሳቱና፤ አሁኑኑ በገዥው መንግሥት ላይ ጫና ማድረጉ ነው። የየራሳችን ፓርቲዎች ከምንል፤ የአንድነት እንቅስቃሴ እንበል። ማለቱ ብቻ ሳይሆን ደግሞ፤ በሕዝብ ፊት የሚታይ የአንድነት ጥረት እናድርግ።
የሰላማዊ ትግሉ በአንድ ድርጅት ብቻ የሚመራ ነው። የሰላማዊ ትግሉ ትኩረቱ፤ ያለውን ሥርዓት ለመለወጥና ትክክለኛ የሕዝቡ ተወካይ መንግሥት የሚኖበትን ሂደት ለመፍጠር ነው። የምንታገልላቸው ዕሴቶቻችን፤ የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር፣ የሕግ የበላይንት መስፈንና የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ናቸው። በነዚህ መሠረታዊ መታገያ ዕሴቶቻችን ዙሪያ፤ በውጭ ሀገር ያለነው ኢትዮጵያዊያን ብንሰባሰብ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ሰላማዊ ትግል ትልቅ ብርታት እንሠጣለን። አስተዋጽዖችንም ትርጉም ይኖረዋል። ተከታዩም አስተማማኝ ይሆናል። አዎ! ላለፉት ከሃያ በላይ ዓመታት የትብብሩን ጥሪ ስናስተጋባና አንዲትም እርምጃ ወደፊት ሳንሄድ ኖረናል። ይህ ግን የትብብሩን አስፈላጊነት በምንም መንገድ አይቀይረውም። ጥረታችንን በተስተካከል መንገድ ማካሂያድና ጥበብ በተሞላበት መንገድ መምራት ነው። አሁን በአንድ ተነስቶ መታገሉ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው። ያ ካልሆነ፤ ትግሉ የእሬያ ታጥቦ ጭቃነት ነው። አንድነቱን ገሃድ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ያለ ክፍል መኖሩን ተገንዝቤያለሁ። በርቱ እላለሁ።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
እሁድ፤ ሐምሌ ፳፮ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት ( 08/02/2015 )
_________________________________________________
የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፬ – ሁለተኛው ጉዳይ)
በአንድነት ተሰባሰበን እስካልታገልን ድረስ፤ ትግሉ ሕዝባዊ አይደለም፤ ድሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አይሆንም።
በክፍል ፬ የመጀመሪያው ጉዳይ ላይ፤ ከየት እንጀምር የሚለውን በአጠቃላይ ቃኝቸዋለሁ። በዚህ በሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ፤ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያዊያን ድረገጾች እየተመላለስኩ እንድጽፍ ያደረገኝን፤ በአንድነት ተሰባስበን መታገሉን አጎላዋለሁ።በአንድነት ተሰባሰበን እስካልታገልን ድረስ፤ ትግሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አይደለም። በዚህ ትግል የሚገኘው ድልም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድል አይሆንም። “ብቻ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ይውደቅ እንጂ!” የሚለው ጭፍን እምነት፤ የወደፊቷን ኢትዮጵያና የፖለቲካ ሀ – ሁ ን ያላገነዘበ ነው። ይህ “የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ከባርነት ለመውጣት የሚያደርገው የነፃነት ትግል ነው!” በማለት በተደጋጋሚ አስምሬያለሁ። ታጋዩም መሪውም ሕዝቡ ካልሆነ፤ የነፃነት ትግል አልተያዘም። ዋናው ትኩረታችን በዚህና በዚህ ላይ ብቻ ካልሆነ፤ የሽቅድድም ጉዳይ ይዘናል ማለት ነው። በምንም ዓይነት ይሁን በምንም፤ ማንም ድርጅት ለብቻው የሚያደርገው ትግል፤ የወገንተኛውን አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ተክቶ፤ ራሱ ገዢ ለመሆን እንጂ፤ የሕዝቡን የነፃነት ጥማት ከግቡ ለማድረስ አይደለም።
ባለፉት አርባ ዓመታት፤ የሚቀጥለው መንግሥት የተሻለ ይሆናል እያልን፤ ከነበረው የባሰ እየመጣ፤ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከመቼውም በከፋ ደረጃ ወደታች እየዘቀጠ፤ መቀጠላችን ሀቅ ነው። አሁንም እያንዳንዱ ድርጅት የያዘው፤ ገዥውን ድርጅት በሌላው ለመተካት ከሆነ፤ ትግሉ የተተኪው ድርጅት እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አይደለም። በርግጥ ማንም ድርጅት ሊመሠረትና፤ ለተመሠረተበትና በመርኀ-ግብሩ ላሠፈረው ዓላማ ሊታገል ይችላል። ያንን ማንም ሊያቆመው አይችልም። ያ ትግል ግን፤ የዚያ ድርጅት ትግል ብቻ መሆኑ፤ መታወቅ አለበት።
በአሁኑ ሰዓት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነፃነቱ የሚያደርገውን ትግል አብሮ በአንድነት ከጎኑ መቆም፤ ድሉ የራሱ የሕዝቡ እንዲሆንና ይህን ሊያደናቅፍ የሚነሳውን መቃወም፤ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ታጋይ ግዴታ ነው። በሀገርና በድርጅት መካከል ያለውን ልዩነት የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም። ይህን በድፍን መናገር እችላለሁ። ታዲያ ለሀገር የሚደረግ ትግልና ለድርጅት የሚደረግ ትግል፤ የተለያዩ መሆናቸውን መረዳቱ ከዚሁ ይመነጫል። ድርጅቶች በሙሉ፤ የትግላቸውን ሂደት በትክክል ለመምራት፤ የተግባር ቅደም ተከተላቸውን ማወቅ አለባቸው። እናም አሁን የሀገር ነፃነት በተያዘበት ትግል፤ የድርጅቶች የራሳቸው ብቻ የሆነ ጉዳይ፤ ወደኋላ መጎተት አለበት። ደግሞ ድርጅት የሚመለክ ጣዖት አይደለም። ድርጅት መሣሪያ ነው። መሣሪያ ደግሞ፤ እንደ መገልገያነቱ፤ በወቅቱና በቦታው አስፈላጊ የሆነው ብቻ ነው የሚነገበው። ዛፍ ለመቁረጥ ዶማ፤ መሬት ለመቆፈር መዶሻ ተይዞ አይወጣም። ሀገርን ነፃ ለማውጣት፤ ሀገር አቀፍ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነው የሚያስፈልገው።
በርግጥ ይህ በአንድ ጊዜ ሊቆቹ በጠረንጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የሚወስኑት ጉዳይ አይደለም። በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ የደረሰባቸውን በደል በመቃወም፤ በተለያየ መንገድ፤ በተለያየ ወቅት፤ የተለያዩ ታጋዮች፤ የተለያዩ ድርጅቶችን መሥርተው ትግል ጀምረዋል። ይህ በተጨባጭ ያለና የማይካድ ሀቅ ነው። አሁን እኒህ ሁሉ ድርጅቶች፤ ዋናው ሀገራዊ ነፃነት መሆኑን ያውቃሉ። ታዲያ ለሀገራዊ ነፃነቱ፤ በብዛት ሕዝቡ በአንድነት የሚሰባሰብበት፤ አንድነት ያለውና በሀገራዊ ነፃነቱ ላይ ያተኮረ ንቅናቄ መመሥረቱን፤ ቅድሚያ ሊሠጡት ይገባል። ቅድሚያ ለዚህ ሠጥተው፤ በአንድነት ለመታገል፤ የየድርጅት ግላዊ ዓላማቸውን፤ ለሀገር ነፃነት መሰዋዕት ማድረግ አለባቸው።
አንዳንድ ድርጅቶች በያዙት መንገድ ለመግፋት የሚያቀርቡት መመከቻ፤ “ሌሎችን ቁጭ ብዬ አልጠብቅም። ቢመጡ ይምጡ፤ እኔ ግን መቀጠል አለብኝ! እኔን ብቻ እመኑኝ። ሌሎቹ አይረቡም!” ነው። ሌሎች ደግሞ፤ “ሁሉም በመረጠው ቢታገል፤ እኛ ምን አገባን! ዝም እንበል!” ይላሉ። እንዲሁም ሌሎች፤ “ለምን ተቃዋሚን እንቃወማለን?” በማለት የሚነቅፉ አሉ። ይህ ትግል የሀገር ነፃነት ትግል ነው። ይህ ትግል የሀገራችንን የኢትዮጵያን ሕልውናና የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያንን የወደፊት ወሳኝ ነው። የሚቀጥለውን መንግሥት አቋቋሚ ኃይል ነው። ስለዚህ፤ ማንኛውም የትግል ድርጅት የሚወስደው ዕርምጃ፤ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያንን ያገባናል። በትግሉ ዙሪያ ያሉትን ጠቅጥቆ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን በሙሉ ለትግል አስነሳለሁ ማለት፤ ማፌዝ ነው። የሁላችን የሆነውን የሀገራችንን የነፃነት ትግል በአንድነት ማድረጉ፤ አማራጭ የሌለው ስለሆነ፤ ከያዝነው ተግባር ይልቅ፤ በአንድነት ለመነሳታችን ቅድሚያ መሥጠቱ፤ ለትግሉና ለድሉ ስኬት፤ አስተማማኝ ነው።
ታጋዮችን በሙሉ የግድ ወደ አንድ እንድንሰባሰብ የሚያደርገን ምንድን ነው? መጀመሪያ የምንታገልላቸው ዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች የጋራ ናቸው። ኢትዮጵያዊያን፤ ከወገንተኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነፃ ለመውጣት በሚታገሉበት ወቅት፤ በኢትዮጵያዊነታችን፤ አብረን የትግሉ አካል ለመሆን ነው። በሀገራችን ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያዊያን አንድ ነን። ትግሉ በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ አገዛዝን፣ ብዙዎችን ያገለለውንና በጥቂቶች የሚመራን አስተዳደር ለማስወገድ ነው። ትግሉ የውጪ ሀገር ባለሀብቶች፣ ቡድኖች፣ ሆኑ መንግሥታት፤ በሀገራችን ጉዳይ ጣልቃ ገብነታቸው መክኖ፤ የራሳችን ነፃ መንግሥት እንዲኖረን ነው። ሀገራችን አንድ ናት። ዳር ደንበሯን እንጠብቃለን። ትግሉ ሁሉን ያካተተ፣ የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ መብት የሚጠብቅ፣ የሕግ የበላይነት በሀገራችን በኢትዮጵያ የሚያሰፍንና የሕዝቡን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ነው። እናም ትግሉ ሰላም፣ ብሔራዊ ነፃነትና፤ ዴሞክራሲን ለመትከል ነው። ይህ አንድ ትግል ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፤ ሁላችንም የምንፈልገው፤ ትግሉ ተሳክቶ ድሉ አስተማማኝ እንዲሆንና የወደፊቷ ኢትዮጵያ፤ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ በእኩልነት ተሳታፊ የምንሆንባት ለማድረግ፤ የወሳኝነት ሚና ለመጫወት ነው።
ከላይ እንዳሰመርኩበት በአሁኑ ስዓት የተለያዩ የትግል ድርጅቶች መኖራቸውና፤ በተለያዩ የትግል መስኮች የተሰማሩ ታጋዮች መኖራቸው ግልጽ ነው። የዚህ ነባር መሠረታዊ እውነታ፤ አሁን መለወጥ አለበት። የትግሉ ባለቤትና ታጋዩ ሕዝቡ ነው። እናም ዋናው ትኩረት መደረግ ያለበት፤ ሕዝቡ በአንድነት ተስልፎ እንዲያምጽ መንገዱን መጥረግ ነው። ለዚህም በሕዝቡ መካከል ተገኝቶ፤ የሕዝቡን በደል አብሮ መካፈል ነው። የሕዝቡን ብሶት ማንሳት ነው። በዚህም ከሕዝቡ ጎን ሆኖ፤ ሕዝቡን መከተልና መምራት ነው። ታዲያ መሠረታዊ ተግባር መሆን ያለበት፤ በሕዝቡ መካከል ተገኝቶ፤ ሕዝቡን መቀስቀሱ ነው። ይህ ትግል፤ የገዥውን ወገንተኛ አምባገነን መንግሥት ነጥሎ የሚያወጣና ተግባሩን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ይህ ትግል፤ የገዥውን ወገንተኛ አምባገነን ገዥ መንግሥት ሩጫና አስመሳይነት የሚያከሽፍ ነው። ይህ ትግል፤ የአልገዛም ባይነትን ስሜት የሚያበረታታ ነው። ይህ ትግል፤ የታጋዩን መዋቅር የሚያሰፋ ነው። ይህ ትግል የወደፊቱን መጪ ብሩህ እውነታ የሚያስተጋባ ነው። እናም ይህ ትግል በአንድ ኢትዮጵያዊ የነፃነት ንቅናቄ ሥር ተደራጅቶ የሚካሄድ መሆን አለበት።
በአንድነት ተደራጅተን ስንታገል፣ የሕዝቡ የነፃነት ፍላጎት ሲግል፣ ሕዝቡ በየቦታው እምቢተኝነቱን ሲያቀጣጥል፤ ለገዥው ወገንተኛ አምባገነን መንግሥት፤ ሁለት ምርጫ ብቻ ከፊቱ ይደቀናሉ። እኒህ ወሳኝ የሆኑ ምርጫዎች፤ የገዥውን ቡድን ዕድሜ፣ የሕዝቡን አጸፋ አመላለስና፣ የወደፊቱን የሀገራችን ሕልውና ይወስናሉ። የመጀመሪያው የሕዝቡን ጥንካሬ በመመልከት፤ ለሕዝቡ እምቢተኝነት ተገዝቶ፤ የሕዝቡን ፍላጎት ለሟሟላት ተገዥ መሆን ነው። ሁለተኛው፤ በእብሪት ተሞልቶና “እኔ ገዢ ነኝ፤ እኔ ብቻ ያልኩት መፈጸም አለበት!” በማለት፤ ጉልበቱን ተጠቅሞ የሕዝቡን እምቢተኝነት በጭካኔ ለመቅጨት፤ ሠይፉን ከአፎቱ መምዘዝ ነው። የመጀመሪያው እንደሂደቱ የሚመለስ ሲሆን፤ የተለመደው የአምባገነኖች መጨረሻ እንዳስገነዘበን ግን፤ የሁለተኛውን ምርጫ ነው መጠበቅ ያለብን። ያኔ የሕዝቡ የአጸፋ መልስ፤ የገዥው በእብሪት ጉልበት መከላከልና የበላይነቱን ለመጠበቅ የሚያደርገው ሩጫ፤ የወደፊቱን ይወስናል። ለሕዝቡ ያኔ የሕልውና ግዴታ ቦታውን ይወስዳል። በአንድ ተደራጅተንና ጠንክረን ስንገኝ፤ በመኖርና ባለመኖር መካከል ለሚቀመጥ ሕልውና፤ በማናቸውም መንገድ መኖርን በመምረጥ መቆማችን፤ አጠያያቂ አይደለም። ከወዲሁ በመተንበይ፤ አፈጻጸሙ እንዲህ ወይንም እንዲያ ይሆናል ባንልም፤ በሂደቱ፤ ይሄ ጠንካራ የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ፤ ትክክለኛ መልስ በመሥጠትና አስፈላጊውን የትግል መንገድ መርጦ በመሄድ፤ ድሉ የሕዝቡ እንደሚሆን፤ ጥርጥር ሊኖረን አይገባም።
አዎ ዛሬ በሀገራችን የሕግ የበላይነት የለም። የጉልበት ግዛት ሠፍኗል። ወንጀል መሥራት ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኘትና ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት፤ ያስወነጅላል። በሰላም ሠርቶ ማደር ያስወነጅላል። ለሀገርና ለወደፊቱ መቆርቆር ያስወነጅላል። እናም ሕዝቡ ይኼስ በዛ ብሎ ተነስቷል። ሕዝቡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ቆሟል። አንድ ኢትዮጵያዊነት ነው ያለው። እናም ሕዝቡ በአንድነት ነው የሚታገለው። ለድርጅት ሳይሆን ለኢትዮጵያዊነቱ ነው የሚታገለው። የትግል አንድነቱ እስከተፈጠረ ድረስ፤ በጊዜው ስለሚደረገው ትግልም ሆነ ስለአካሂያዱ አሁን መዘርዘሩ ዋጋ የለውም። እስኪ መጀመሪያ የትግል አንድነቱን እንፍጠር። የድርጅቶች ሁሉ የቅድሚያ ተግባር፤ አንድነት መፍጠሩ ይሁን።
የመጨረሻውን ከየት እንጀምር? የሂደቱን ዝርዝር በሚቀጥለው አቀርባለሁ።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ሰኞ፤ ሐምሌ ፳ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት ( 7/27/2015 )
_________________________________________________
(ክፍል ፬) – አሁን ካለንበት ወደፊት ለመሄድ ከየት እንጀምር? (የመጀመሪያው ጉዳይ)
አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለችበት የፖለቲካ ሀቅና የታጋዩ ክፍል በቆመበት መሬት፤ በር የሚያንኳኳና ደረስኩ የሚል ጥሪ መጥቷል። ትግሉን አብረን ማድረግ አለብን! እያለ። በያለንበት እንተባበር! እያለ። መቼም ይሄን የማይል ሕይወት የለም። ሁላችን እንፈልገዋለን። ሁላችን ትክክለኛና መሆን ያለበት ግዴታ ነው እንላለን። ሌላ አማራጭ እንደሌለ እናምናለን። ታዲያ ከየት እንጀምር? በክፍል አንድ፤ በአሁኑ ሰዓት የሰላማዊ ትግሉ በኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ገልጫለሁ። በክፍል ሁለት ደግሞ፤ ስለሰላማዊ ትግሉ ያለንን ግንዛቤ አሳይቻለሁ። በክፍል ሶስት፤ ከዚህ ቀደም የሰላማዊ ትግል ካካሄያዱ ሌሎች ሀገሮች የምንማረውን ዘርዝሬያለሁ። በዚህ በአራተኛው ክፍል፤ ሶስት ጉዳዮች ያሉት ዘገባ አለኝ። የመጀመሪያው ጉዳይ፣ አሁን ካለንበት ወደፊት ለመሄድ ከየት እንጀምር? የሚለውን ራሱን በመመርመር፤ አጠቃላይ ሂደቱን እነድፋለሁ። ተከታትለው በሚወጡት የሁለተኛውና የሶስተኛው ጉዳዮች፤ በተጨባጭ በዝርዝር ማድረግ ያለብንን እዘረዝራለሁ።
ወደፊት ለመሄድ፤ መጀመሪያ ያለንበትን የፖለቲካ ሀቅ በትክክል ማወቅ፤ ግድ ይላል። ያለንበትን በትክክል ማወቁ፤ ለምናደርገው ጉዞ ትክል ማጠንጠኛው ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ከባርነት ለመውጣት የሚያደርገው የነፃነት ትግል ነው። ታጋዩም መሪውም ሕዝቡ ነው። ለዚህ የምንስማማባቸውን አስፍረን፣ ማድረግ ያለብንን ለይተን አቅርበን፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ሕያውነት ገሀድ የማድረጉ ኃላፊነት የኛ ነው።
ለሁሉም እስኪ በመጀመሪያ የምንስማማባቸውን መሠረታዊ የሆኑ ዋና ሀገራዊ ሀቆች ላስፍር፤
፩ኛ. በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ገዢ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን፤ እንደ ጠላት ወራሪ የሚገዛ ቡድን ነው፤ እናም ይህ መንግሥት መወገድ አለበት። ይህ መንግሥት ሕገወጥ ነው። ይህ መንግሥት አድሎዓዊ ነው። ይህ መንግሥት አምባገነን ነው። ሀገራችንን ወደ አደገኛ አዘቅት እየወሰዳት ነው። አስተዳደሩ በሙስናና በዘረኝነት የተወጠረ ነው። ረሃብና ድህነት እንደ ጥላ አብረውን የሚጓዙ ወዳጆቻችን በሆኑበት ሀቅ፣ ስደትና ከሀገር የነፍስ አውጭኝ ሩጫ በነገሡበት ሀቅ፣ ጥቂቶች ከምርጥ ዘር የመጡ ሁሉን በሚቆጣጠሩበት ሀቅ፣ ወጣቱ በሱሰኛ እጽዋት በተመረዘበትና ሥራ ባጣበት ሀቅ፣ ኢትዮጵያዊ መንግሥት አለ ብሎ መናገር፤ የሀገርን ትርጉም አላዋቂነትን ያሳያል። እናም ይሄን ለምናውቅ፤ ይህ መንግሥት መወገድ አለበት።
፪ኛ. ይህ መንግሥት መወገድ ያለበት፤ በጠቅላላ በሕዝቡ ተሳታፊነት በተካሄደ ትግል ብቻ ነው። ሕዝቡ የድሉ ባለቤት የሚሆነው፤ ሕዝቡ በሙሉ “የኔ” ብሎ በአንድነት፣ ሀገራዊ ነፃነትን ባነገበ አንድ ድርጅት ሥር ታግሎ፤ ነፃ ሲሆን ብቻ ነው። ሀገራዊ ነፃነት፤ በሕዝቡ አንድነት ብቻ እንጂ፤ በድርጅቶች ጋጋት አይካሄድም። እናም በምንችለው ሁሉ ጥረታችን መሆን ያለበት፤ ይሄን የሕዝቡን በአንድነት የትግል መነሳሳት እውን ማድረግ ነው። በጭፍን ይሄን መንግሥት እንጣል ብቻ ማለት፤ የአንድነት ሀገራዊ ትግልን ባህሪይ አለመረዳትን ያሳያል። እናም ሕዝባዊ ትግሉ በአንድ ድርጅት ሥር መካሄዱ የግድ ነው። ሕዝቡን ተክቶ የሚታገል ፓርቲ የለም። በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመጠቀው የተማረው ወጣት አንስቶ፤ በቁጥር በብዙ ሚሊዮን እጥፍ ከሚበልጡትና የቴክኖሎጂን ጭላንጭል ሊያዩ ቀርቶ፤ የዕለት ምግባቸውን ከየት እንደሚያገኙ እስከ ጣጠራቸው የገጠር ዘመዶቻችን ድረስ፤ የዚህ ትግል ባለጉዳዮች ነን። ይሄን በተስተካከለ መንገድ እንዲሄድ ማድረግ እንችላለን። ዕውቀቱ፣ ልምዱና ችሎታው አለን። እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊ ነን የምንል ሁሉ፤ የዚህ ትግል ባለጉዳዮች ነን። ጥረት ማድረግ አለብን። በሌሎች ጫንቃ ላይ ልንንጠላጠል፣ ወይንም ሌሎችን አዝለን የድሉን ፍሬ ልንበላ አንችልም።
፫ኛ. የሚቀጥለው መንግሥት ሲመሠረት፤ ሁሉን አቀፍና ጊዜያዊ መሆን አለበት። ላንዴም ለመጨረሻ ጊዜም ከጦርነት እሽክርክሪት ወጥተን፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ መንግሥት እንዲኖረን፤ ከድል በኋላ መቋቋም ያለበት፤ የሽግግር መንግሥት ነው። ይህ የሽግግር መንግሥት፤ በትግሉ ላይ ከተሰማሩት የተውጣጣ ሆኖ፤ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት፤ ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ፤ ከሕዝቡ በትክክል በመሰብሰብ፤ ያዘጋጅና ያቀርባል። በዚህ ወቅት ብዙ ሌሎች ጉዳዮች ይከናወናሉ። በተወሰነ ጊዜ የሚካሄድ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያዘጋጃል። ትክክለኛ ምርጫ ያካሂዳል። ለተመረጠው ክፍል ሥልጣኑን ያስረክባል።
እንግዲህ ይህ አሁን ላለንበት የትግል ሁኔታ፤ በሀራችን ላይ ያለና መሠረታዊ የሆነ፤ ሁላችን የምንስማማበት፤ የፖለቲካ ግንዛቤ ነው። እዚህ ላይ ልዩነት ካለ፤ ወደፊት መቀጠል አይቻልም። የትግሉ ባለቤት ከሆነው፤ ከሕዝቡ ጋር፤ እየታገለ ካለውና ለወደፊት ከሚቀላቀለው ጋር አብሮ ተደራጅቶ ለትግል መሰለፍ፤ ግዴታ ነው። ለየግላችን ድርጅት ፈጥረን፣ በራሳችን ድርጅት ሥር ብቻ በመሰባሰብና፣ ከሌሎች በየራሳቸው ድርጅቶች ከተሰባሰቡት ጋር በመተባበር ለመታገል መሞከር፤ መሠረታዊ የሆነውን የሀገር ጉዳይ፤ ከድርጅት በታች አድርጎ ማስቀመጥ ነው። በርግጥ በሁሉም ጉዳዮች ላይ፤ በግለስብም ሆነ በቡድን፤ አንድ አቋም ሊኖረንና ልንስማማ አንችልም። በዚህ ምንም ዓይነት ብዥታ ሊኖረን አይገባም። ሀገራችንን ከወገንተኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነፃ ለማውጣት፤ መታገያችን በሆኑ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግን፤ የግድ መስማማት አለብን። መሠረታዊ የሆኑት መታገያ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ምንድን ናቸው? መሠረታዊ የሆኑት መታገያ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን፤ ከላይ በቁጥር ፩፣ ፪ትና ፫ ከሰፈሩትና ከምንስማማባቸው የፖለቲካ ሀቆች ይመነጫሉ።
፩ኛ. በኢትዮጵያ ሀገራችን፤ ኢትዮጵያዊነታችንን አምነን የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን፤ በዚሁ በኢትዮጵያዊነታችን፤ አንድነታችንን እናንጠብቃለን። ኢትዮጵያዊያን አንድ ነን። በማንኛውም መንገድ ኢትዮጵያዊ ሆነን ስንገኝ፤ ያ ኢትዮጵያዊነታችን አንድና አንድ ብቻ መሆኑን እናስከብራለን። የተለየ ቦታ ያለው ኢትዮጵያዊነት አይኖርም።
፪ኛ. የሀገራችን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረን፤ በግዛቷ ስፋት ውስጥ፤ ሁሉም መሬቷ ለኢትዮጵያዊያን እንዲውል አድርገን፣ አንድነቷን እንጠብቃለን።
፫ኛ. እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ በሀገራችን የፖለቲካ ጉዳይ ስንሳተፍ፤ በግል ኢትዮጵያዊነታችን ላይ ከመነጨ መብት ነው። የያንዳንዳችን የግለሰብ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብትን፤ ያለማዛነፍ እናከብራለን።
፬ኛ. በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እናደርጋለን። በሕግ ፊት የበላይና የበታች አይኖርም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ በሕግ ፊት እኩል እንዲሆን እናደርጋለን።
፭ኛ. የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነትን እናስከብራለን። ምን ጊዜም ቢሆን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ፤ ሕዝቡ የመንግሥቱ ባለቤት እንጂ፤ መንግሥቱ የሕዝቡ ባለቤት የሚሆንበት ክስተት ያቆማል። የሕዝቡን የበላይነት እናከብራለን።
ከላይ የተዘረዘሩት አምስቱ መታገያ ሀገራዊ ዕሴቶቻችን ናቸው። እኒህ ግድግዳና ማገር ሆነው፤ ቤቱን የሚሸከሙ ናቸው። ጣራው ከላይ ይደረባል። ምርጉና ልሰናው ይከተላል። በነዚህ ዕሴቶቻችን ላይ መጨመር ይቻላል። ተጨማሪዎቹ ግን፤ ጊዜን ጠብቀው፤ ለነዚህ አምስት ዋና መታገያ ዕሴቶቻችን ተገዝተው ሲቀርቡ ነው ተቀባይነት የሚኖራቸው።
እንግዲህ እንደዚህ የተበታተነ ትግል በያዝንበት ወቅት፤ ለስምምነቱም ሆነ ለመለያየቱ መድረካችን አደባባዩ ሆኗል። በሚስጥርና በጓዳ የሚደረግ ስምምነትም ሆነ ልዩነት፤ አድሮ የራሱ አዛባ እየጠፈጠፈ፤ ብትንትናችንን ያወጣዋል። እናም ባደባባይ ይሁን መስማማታችን። ለሕዝብ የሚደረግ የሕዝብ ጉዳይ፤ ግልጽነት ግዴታው ነው። ከማን ይደበቃል። በማን ጀርባ ይንሾካሾካሉ? አይቻልም።
ትግሉ ተደራጅተው ለሚታገሉት ብቻ የተሠጠ፤ የግል ኃላፊነታቸው አይደለም። ይህ ሀገራዊ ትግላችን፤ “እኔ ስላልተደራጀሁ አያገባኝም!” ወይንም “ተጠያቂ አልሆንበትም!” ብዬ ላመልጠው አልችልም። ኢትዮጵያዊነቴን ካልካድኩ በስተቀር! እናም፤ ግለሰብ እና በድርጅት ያሉ የድርጅት አባላት እኩል ተጠያቂነት አለብን። ስለዚህ ጥረቱ ከሁላችን መሆን አለበት። ራስን ነፃ ለማውጣት፤ “ድርጅቶች እኮ አይረቡም!” “እነሱ መድረኩን አጣበው ይዘውታል!” እና ሌሎች ይኼን የመሳሰሉ ማምለጫ አባባሎች ተበልተዋል። አይሠሩም። መታገል ያለባት መሆኗን የተረዳች እህት፤ በግለሰብ ያለባትን ኃላፊነት ለመወጣት፤ ማድረግ ያለባትን የምትወስነው ራሷ እንጂ፤ ያሉ ወይንም የሌሉ ድርጅቶች አይደሉም። የድርጅቶች መኖር ወይንም አለመኖር፤ የአንድን ግለሰብ የትግል ፍላጎት፤ አያስሩም። ካልወደዳቸው፤ ሌላ መንገድ እንዲፈልግ ያስገድዱታል።
በተጨማሪም፤ ሌሎቹ አይረቡም በማለት የሚቀርበው ያለመስማማት መንገድ የትም አያደርስም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ባንድ አቆራኝቶ ለማታገል የተነሳ ድርጅት ሆነ ግለሰብ፤ “ይሄ አንዲያ ነው!” ወይንም “ያቺ አንዲህ ነች!” “ያ ድርጅት እንዲያ ነው!” ወይንም “እነሱኮ . . .!” በማለት ላለመተባበር ማምለጫ ማበጀት፤ ኃላፊነት የጎደለው አካሄያድ ነው። ደግሞስ ለምን በሁሉ ነገር ከሚስማሙን ጋር ብቻ እንሠራለን ብለን እንነሳለን? ይሄ እኮ የሀገር ጉዳይ ነው! እንኳንስ በትግሉ የተሰማሩት ቀርቶ፤ ገና የገዠው ክፍል አባላት፤ ትግሉ ሲግልና መፈርጠጥ ሲጀምሩ፤ አቅፈን ከጉያችን እናሰልፋቸዋለን። የያዝነው ሀገራዊ ትግል ነው! ቁርሾ መወጫ ጨዋታ አይደለም።
ሰሞኑን በግብታዊነት ድርጅቶችን ለማስተባበር ጀምሬ ነበር። በርግጥ ትልቁ ስህተት ከኔ ነበር። ወደፊት እንዳሰብኩት አልሄደም። ከዚህ ጠቃሚ ተመክሮ ወስጃለሁ። በሂደቱ ብዙ ታጋዮች ድጋፍ አድርገውልኝ፤ እንዴት ሊተባበሩኝ እንደሚችሉ ሃሳብ ሠጥተውኛል። አብረውኝ ቆመዋል። አብረን ወደፊት እንሄዳለን። በጣም አመሰግናቸዋለሁ። የጊዜውን አጣዳፊነት፣ የአደጋዉን አስጊነትና የሁኔታውን አመቺነት ብቻ አንግቤ፤ ከእውነታው ይልቅ ፍላጎቴን አስቀድሜ ያደረግሁት ሩጫ፤ ፍሬ ሳይይዝ ቀረ። አምናለሁ፤ ይህ በአንድነት ተሳባስበን የመታገሉ ግዴታ፤ አብሮን አለ። የትል አልሄደም፤ አይሄድምም። ከኔ በፊት ሌሎች ጥረውበታል። አሁንም ሌሎች በሚችሉት እየጣሩ ነው። ጊዜ ይወስዳል። በትግሉ ብዙ የቆዩ አሉ። በትግሉ ብዙ የተማሩ አሉ። በትግሉ በተለያየ መንገድ፤ የተለያየ ግብ ይዘው የቀረቡ አሉ። እናም እኒህን ሁሉ በአንድ ማሰባሰቡ ቀላል አይደለም። ከተጨባጩ የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ በላይ፤ አስቸጋሪና ተጎታች የሚሆነው፤ በትግሉ ዙሪያ ያሉትን ወደ አንድ እንዲመጡ መለማመጡ፣ ማባበሉ፣ ማንቆለጳጰሱ፣ ማስጎምጀቱ፣ ማጓጓቱና መጎተቱ ነው። ከዚህ በተሻለ መንገድ አሁንም ሳላርፍ እቀጥላለሁ።
በተለያዩ ታጋይ ድርጅቶች ሥር ያሉት አባላት መረዳት ያለባቸው፤ በድርጅታቸው ሥር ያከናወኑት ሁሉ፤ እያንዳንዱ ድርጅት የፈጸመው በጎ ተግባር፣ ያከናወናቸው ትክክለኛ ጀብዱዎች፣ ጉድለት የታየባቸው ተመክሮዎችና በትግሉ የተሰዉ ጓዶቻቸው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ያደረጉት ስለሆነ፤ የየግል ድርጅቶች ታሪክ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አካል በመሆኑ፤ የየድርጅቶቻቸው ስም ቢቀየር፣ ድርጅቶቹ ቢፈርሱ፤ ይህ ታሪክ ቋሚ ሆኖ ይኖራል። እናም በአንድ እንሰለፍ ስንል፤ ይሄን ታሪክ ወደ አንድ አጠቃለን እናመጣዋለን እንጂ፤ ማንም ሊሠርዘው አይችልም። ትግሉ አንድ ነው። የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ትግል ነው። አሁን የያዝነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልና ታሪክ እንጂ፤ የድርጅቶች ትግል ወይም የድርጅቶች ታሪክ አይደለም። ከወራሪው የፋሽስቱ ጣልያን ጋር ተጋፍጠው የተሰለፉትን አርበኞቻችን፤ በአብቹ ተሰለፉ በበላይ ዘለቀ፤ አርበኞቻችን ብለን እናነሳቸዋለን እንጂ፤ የአብቹ አርበኞች ወይንም የበላይ ዘለቀ አርበኞች አንላቸውም። አሁን ያሉት ድርጅቶች መሠረታቸው፤ የአባሎቻቸው ቁጥር ብዛት፣ ያላቸው ታሪክ፣ ያካበቱት ንብረት ወይንም የመሪዎቻቸው ማንነት ሳይሆን፤ መርኀ-ግብራቸውና ርዕዩተዓለማቸው ነው። ያ ደግሞ ትርጉም የሚኖረው፤ ሕዝቡ የመምረጥ መብት ኖሮት፤ ከዚህኛው ያኛው ይሻላል ብሎ የሚያማርጥበት ወቅት ሲመጣ ነው።
ሁለተኛውን ጉዳይ በሚቀጥለው ጽሑፌ አቀርባለሁ።
ከታላቅ ምስጋና ጋር
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
አርብ፤ ሐምሌ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት (7/17/2015)
_________________________________________________
(ክፍል ፫)
የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል አራማጆች፤ ከሌሎች ሰላማዊ ትግል አራማጆች የምንማረው
በክፍል አንድ፤ የሰላማዊ ትግሉ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ገልጫለሁ። በክፍል ሁለት ደግሞ፤ ስለሰላማዊ ትግሉ ያለንን ግንዛቤ አሳይቻለሁ። በዚሁ በሶስተኛው ክፍል ላይ፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሰላማዊ ትግል፤ ከሌሎች ከዚህ ቀደም የሰላማዊ ትግል ካካሄያዱ ሀገሮች የምንማረውን ተመክሮ እዘረዝራለሁ። ሰላማዊ ትግሉ፤ ዕለት በዕለት በገዥው ወገንተኛ አምባገነን ገዥ መንግሥት ፊት ኑሯቸውን በመምራት፤ በመንግሥታዊ መዋቅሩ ከተሰገሰጉት ካድሬዎች ጋር የሚላተሙ ኢትዮጵያዊያን፤ ትኩረታቸው ውስን ሆኖ፤ በጠባብ ጥያቄያቸው ዙሪያ ተጠምደው፤ በትምህርት ቤታቸው፣ በገበያ አዳራሻቸው፣ በእርሻ መስካቸው፣ በመሥሪያ ቤታቸው፣ በሚሠሩበት ፋብሪካ፣ በቀበሌያቸው፣ በገበሬ ማህበራቸው፣ ወታደሮች ለግዳጅ በተሰማሩበት ቦታ፤ ለኒሁ ውስን ጥያቄዎች መልስ ፍለጋ ሲሯሯጡ፤ በቦታው ተገኝቶ እኒህን ጥያቄዎቻቸውን ሀገራዊ ይዘት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። እኒህን ውስን የአካባቢ ጥያቄዎች፤ በሀገራዊ ራዕዩ ቦታ ሠጥቶ፤ መታገያ ዕሴቶች ሆነው፤ ሕዝባዊ መነሳሳት እንዲከተል ማድረግ ነው። የገዥው ክፍል እንዲህ ባለ በጉልበት የመግዛት ሂደት ሲሰማራ፣ ድህነት በሀገራችን በነገሠበት ወቅት፣ ሙስና በገዥው ክፍል ውስጥ ባህል ሆኖ ሲደራ፣ አድልዖ የዕድገት መሰላል በሆነበት አስተዳደር፣ ሕዝቡን በመርገጥ ግፉን ሲያበዛ፤ ሕዝቡ እምቢ ብሎ በሰላማዊ መንገድ ማመጹ፤ የሕልውና ጉዳይ ነው። ለዚህም ሕዝቡ እምቢተኛነትን ይዟል። ትክክለኛ ላልሆነ አሠራር ተባባሪ አልሆንም ብሏል። ሰላማዊ በሆነ እምቢተኝነት፤ የኅብረተሰቡን የፖለቲካም ሆነ የማንኛውም የአስተዳደር በደል ምንጭ አጥፍቶ፤ ትክክለኛ የሆነ ሥርዓት ለማምጣት ተነስቷል። እኒህ ሰላማዊ ታጋዮች፤ ሕዝቡን በማስተማር፣ ከፍተኛ ሕዝባዊ መዋቅር በመዘርጋትና ሕዝቡን በማነሳሳት፤ አጠቃላይ መሬት አንቀጥቃጭ ንቅናቄ ለማስከተል ቆርጠው ተነስተዋል። ታዲያ ከሌሎች የሰላማዊ ትግል ካካሄያዱ ሀገሮች፤ ምን ተመክሮ እንቀስማለን። ይህን ለመመለስ ነው ይህ ጽሑፍ የሚጥረው።
ሰላማዊ ትግል፤ በአመጽ ያለውን ገዥ ክፍል ለማስወገድ በመሰለፍና፤ ያለውን እንዳለ ተቀብሎ በመኖር መካከል ያለ የሕዝብ ይሄስ በቃ የማለት እርምጃ ነው። ያለውን ተቀብሎ ባለው ሥርዓት ሥር ለመኖር መወሰን አንድ ነገር ነው። ባንጻሩ ደግሞ፤ ያለውን ሥርዓት አውግዞ፤ ያንን ለመለወጥ ነፍጥ አንግቦ መነሳት ሌላው ነገር ነው። በመካከል ያለው ሰላማዊ ትግሉ ነው። ይህን ትግል፤ ከሕንድ እስከ አሜሪካ፣ ከፖላንድ እስከ ጓቴማላ፣ ከደቡብ አፍሪቃ እስከ በርማ፣ ከፊሊፒንስ እስከ ጀርመን፣ ከቻይና እስከ ቼዝ ድረስ፤ ታጋዮች አካሂደውታል። በርግጥ በቻይናና በበርማ ግፈኛ የሆኑ አምባገነን ገዥዎች፤ አረመኔነት በተመላበት መንገድ፤ የሕዝቡን አመጽ ለጊዜው አዘግይተውታል። እኛ፤ ከተሳኩትም ሆነ ካልተሳኩት የምንማረው አለ።
መሠረታዊ የሰላማዊ ትግሉ ማሽከርከሪያ፤ የገዥውን ክፍል ውስጣዊ ችግሮች በማባባስ፤ ቅራኔውና ውጥረቱ በታጋዩ ክፍልና በገዥው ክፍል መሆኑ ቀርቶ፤ በገዥው ውስጥ እንዲካረር በማድረግ፤ ግልብ ሆኖ እንዲፈረካከት መቦርቦር ነው። ጋንዲና ማርቲን ሉተር ኪንግ፤ የሰላማዊ ትግሉ አራማጆችና ባለስኬቶች ነበሩ። ከነዚህ አዛውንት ሰላማዊ ታጋዮች ብዙ የምንማረው ትምህርት አለ። ዋናው ቁምነገር፤ የነዚህን ግዙፍ ሰላማዊ ታጋዮች ግብር በማጥናት፤ ለኛ ሀገር ተስማሚ በሆነ መንገድ፤ ተመክሯቸውን መጠቀም ነው። እኛ በያዝነው ትግል፤ ዋና ገዥ ፍልስፍናችን ምንድን ነው? ሀገራችን ያለችበት አስጊ ሁኔታ የሚቀየረው፤ ሁላችን ታጋይና ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተሰልፈን፤ በአንድ ራዕይና በአንድ ድርጅት ስንታገል ነው። ታግለን ደግሞ መመሥረት ያለበት፤ ሁላችንም የሚወክል የሽግግር መንግሥት ነው። ሰላማዊ ትግሉ፤ ያላማራጭ ባሁን ሰዓት ላለንበት የፖለቲካ ሀቅ፤ ብቸኛ መንገዱ ነው። ለምን?
አንድ ማዕከል ያለው ትግል ባገራችን በሌለበት ሁኔታ፤ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሞሉባት ኢትዮጵያ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በትውልድ ሐረግ፣ በንብረት ብዛት፣ በአካባቢ ብልጽግናና በመሳሰሉት መለያያ መንገዶች ያለን መሆናችን አንዱ ምክንያት ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለይም የትውልድ ዘር ቆጠራ ላይ የተመሠረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የተስፋፉበት፣ የተለያዩ የትግል መስኮችና ግቦች የፖለቲካውን ምኅዳር ያጣበቡበት ሀቅ ሌላው ምክንያት ነው። አምባገነኑ ወገንተኛ ገዥ ተወግዶ፤ የነገዋ ኢትዮጵያ የሁላችን እንድትሆን አስተማማኝ የሆነ የትግል ስልት ማስፈለጉ፤ ሌላው ምክንያት ነው። ብዙ ታጋይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ትግሉ፤ ለሌላው ሳይሆን ለራሳቸው ሲሉ መምጣታቸው፤ አስፈላጊና ወሳኝ ነው። ይህ ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው። ባሁኑ ሰዓት፤ በገዥው ቡድን መካከል፤ መለስ ዜናዊን የመሰለ፤ ሁሉን ሥልጣን ጠቅልሎ በጁ የጨበጠ አንድ አምባገነን በሌለበት ወቅትና፤ እያንዳንዳቸው የራሳቸውን ወገን ለማጠናከር በሚሯሯጡበት ሰዓት፤ በመካከላቸው ያለውን ክፍተት ለማስፋትና ጥርጣሬ እንዲገባባቸው ለማድረግ፤ ግፊት ከሕዝቡ ያስፈልጋል። ሰላማዊ ትግሉ ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ፤ ለዚህ የገዥው ተጨባጭ እውነታ፤ አጣዳፊና ተግባራዊ መደረግ ያለበት ግዴታ ነው። ባሁኑ ሰዓት በታጠቀ ኃይል ከመፈረካከታቸው ይልቅ፤ በመካከላቸው በሚፈጠረው ቅራኔና ሽኩቻ፤ የበለጠ መዳከማቸው አመኔታ አለው። እናም ይሄን ለማባባስ አንድ የሚያደርጋቸውን ሳይሆን የሚሰነጣጥቃቸውን መምረጥ አለብን። እናም ሰላማዊ ትግሉ ይሄን ለማድረግ ይረዳናል። የሱማሌና የዩጎዝላቪያ ሀቅ፤ በላያችን ላይ ከብዶ ሊያንዣብብ ያስፈልጋል።
በርግጥ ሰላማዊ ትግሉን መምረጥ ማለት፤ የማህተማ ጋንዲን ወይንም የማርቲን ሉተር ኪንግን ተግባር በቀጥታ መቅዳት ማለት አይደለም። የኛ ሀገር የፖለቲካ ሁኔታና ያለው ተጨባጭ ሀቅ ገዥ ነው። ለጋንዲና ለማርቲን የሃይማኖት መሠረት ዋና ትክላቸው ነበር። በርግጥ ኢትዮጵያዊያን፤ ሃይማኖተኞች ነን። በክርስትያንም ሆን በእስልምና ተከታዮች ዘንድ፤ ለሌሎች ጠበቃ ሆኖ መቆምና ግፍን መቃወም ባህላችን ነው። ሰላምታ አለዋወጣችን እንኳ፤ አንገታችንን ዝቅ አድርገን በመድፋት፤ ሰላምታ ከምንለዋወጠው ሰው ራሳችንን አሳንሰን ነው። አስደጋጭ ሁኔታ ሰፈጠር፤ ለፀሎት ወደ ቤተ ክርስትያንና ወደ መስጂድ መሮጣችን እውቅ ነው። አብሮ ለጸሎት ወደ ቤተ እመነት መሄድና አብሮ መጸለይ የተለመደ ነው። እንግዲህ ይህ ብዙ የሚያመሳስለን ሁኔታ መኖሩን ይመሰክራል። ለነሱ ዋናው እምነታቸው፤ ገዥውን ክፍል ተገዥ ለማድረግ ሳይሆን፤ ሁሉም እኩል የሚሆንበት የወደፊት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ይሄ በቅኝ ግዛት ትማቅቅ ለነበረችው ሕንድ፤ ምን ያህል እንደሠራ ማየቱ ቸግሮኛል። እንግሊዞች ወጥተው ሕንዶች የራሳቸው መንግሥት እንዲመሠርቱ የታገለው ጋንዲ፣ ይሄን መስበኩ ለኔ ገርሞኛል። ባንጻሩ ማርቲን ምርጫ አልነበረውም። ኔልሰን ማንዴላም ቢሆን ምርጫ ስላልነበረው፤ በአውሮፓውያንና አሜሪካውያን፤ ለውጡ ዘምዶቻቸውን እንደማይጎዳና ጥቁሮቹን ባሉበት የድህነት ሰቆቃ እንዲማቅቁ መደረጉን ተገዶ ተቀብሏል። ወራሪንና እንደወራሪ የሚገዛን ቡድን፤ አስተናግዶ እኩል ለማድረግ፤ የሀገራችን ሀቅ አያመችም።
ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶች አሉ። ሰላማዊ ትግሉ መማርና መመራመርን መጠየቁን ያምኑበት ነበር። ለነሱ እውነተኛ እውቀት ማለት፤ በቦታው በተጨባጭ ያለውን ሀቅ ተገንዝቦ፤ ሂደቱን በማስላት፤ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በማካተት፤ ወደ መሠረታዊ ዋና ግቡ መጓዝ ማለት ነበር። ደጋግሞ ስለሰላማዊ ትግሉ ምንነት መስበክና ማስተማር የመሪዎቹ ኃላፊነት መሆኑን አስምረውበታል። የሰላማዊ ትግሉ በተግባር ላይ ስለመዋሉ እውነተኛነት፤ ጽኑ እምነትና ቆራጥነት ግድ ነበሩ። በጋጠ ወጦችና በገዥው ታጣቂዎች ለደረሰባቸው ጉጥጫና ግፍ፤ የአካል፣ የመንፈስና የንብረት ጥቃት፤ መልሳቸው ግልጽ ነበር። “ያነገትኩት እውነት፤ ክቡርና ጠንካራ ስለሆነ፤ ውሎ አድሮ፤ አቸናፊ ነኝ!” ነበር። የዚህ ትግል መሪዎች፤ የአእምሮ ነፃነት ያላቸውና ለግል ተጠቃሚነት ቦታ ያልሠጡ መሆን አለባቸው ብለዋል። በሰላማዊ ትግል የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎት ማሟላት፤ ትክክለኛ ተግባር ነው ብለው አምነዋል። ከማንኛውም ቦታ የሚመጡ የተለያዩ ሃሳቦችን ለማዳመጥና ለማመዛዘን ፈቃደኞች ነበሩ። የሰላማዊ ትግሉ ሂደት፤ ለኅብረተሰቡ ኑሮ፤ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ነው። እናም ከትግሉ ስኬት በኋላም አገልጋይ የሚሆኑ ባህሪና ጥበቦችን በሥልጠናና በተግባራዊ ልምድ ማዳበር ይጠቅማል። ለሚከተለው ሰላምና ብልጽግና፤ በተለይም ከጦርነት እሽክርክሪት ለመውጣት መሠረት ነው። እብሪትና ድንቁርና፤ ጦር ወደ መምዘዝና ካንተ መቼ አንሼ ወደሚል ያመራሉ።
የሕዝቡ የነፃነት ፍላጎት አይሎ፤ በየቦታው እምቢተኝነቱን ሲያሰማ፤ የገዥው ወገንተኛ አምባገነን መንግሥት ሁለት ምርጫ ብቻ ከፊቱ ይደቀናሉ። እኒህ ወሳኝ የሆኑ ምርጫዎች፤ የገዥውን ቡድን አረመኔያዊ ግፍ፣ የሕዝቡን አጸፋ አመላለስና የወደፊቱን የሀገራችን ሕልውና ይወስናሉ። የመጀመሪያው ለሕዝቡ እምቢተኝነት ተገዝቶ፤ የሕዝቡን ፍላጎት ለሟሟላት እሽ ማለት ነው። ሁለተኛው፤ በእብሪት ተሞልቶና እኔ ገዢ ነኝ፤ እኔ ብቻ ያልኩት መፈጸም አለበት በማለት፤ ጉልበቱን ተጠቅሞ የሕዝቡን እምቢተኝነት በጭካኔ ለመቅጨት ሠይፉን ከአፎቱ መምዘዝ ነው። የመጀመሪያው እንደሂደቱ የሚመለስ ሲሆን፤ የአምባገነኖች መጨረሻ እንዳስገነዘበን ግን፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች፤ የሁለተኛው ምርጫ ነው የተለመደው። የሕዝቡ የአጸፋ መልስ፤ የገዥውን የእብሪት ጉልበት መቋቋምና የበላይነቱን መውሰድ ይጋብዛል። ያኔ የሕልውና ግዴታ ቦታውን ይወስዳል። በመኖርና ባለመኖር መካከል የሚቀመጥ መርጫ፤ በማናቸውም መንገድ መኖርን ይዞ መነሳቱ፤ አጠያያቂ አይደለም።
በአራተኛው ክፍል፤ ከየት እንጀምር የሚለውን ተግባራዊ ጉዳይ ይዞ ይቀርባል።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ረቡዕ፤ ሰኔ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህቱረት ( 6/17/2015 )
_________________________________________________
(ክፍል ፪)
በክፍል አንድ፤ የሰላማዊ ትግሉ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ገልጫለሁ። በዚሁ ላይ፤ የሰላማዊ ትግሉ ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር ያለውን ልዩነት አሳይቻለሁ። በተጨማሪ ደግሞ፤ የሰላማዊ ትግሉ የሚካሄደው በአንድ የሕዝባዊ ንቅናቄ ድርጅት ሥር ብቻ መሆኑንና፤ አማራጭና ተለዋጭ እንደሌለው አስምሬበታለሁ። በሂደቱ መሰባሰቢያ የሆኑትን ሀገር አቀፍ የትግል ዕሴቶች አስቀምጫለሁ። በዚህ ክፍል ሁለት ደግሞ፤ ስለተሳሳተው የሰላማዊ ትግሉ ግንዛቤያችን አስረዳለሁ። ባጠቃላይ፤ የሰላም ትግሉ ከትጥቅ ትግሉ አኳያ ለምን እንደሚመረጥ በግልጽ አሰፍራለሁ። በማጉላትም በአሁኑ ሰዓት፤ የሰላማዊ ትግሉ አማራጭ የሌለው ብቸኛ የትግል መንገዳችን መሆን እንዳለበት አመላክታለሁ።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ስለሚካሄደው ሰላማዊ ትግሉ ያለን ግንዛቤ ጉድለት አለው። አንዳንዶቻችን፤ ገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ስለሚያስር፣ ስለሚገድል፣ ከሀገር ስለሚያሳድድ የሰላማዊ ትግሉ አይሠራም እንላለን። ሌሎቻችን ደግሞ፣ በምንም መንገድ፤ ገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ወዶ ሥልጣኑን ስለማይለቅ፤ በምርጫ መሳተፉ ዋጋ የለውም፤ ስለዚህ የትጥቅ ትግሉ ብቻ ነው የሚያዋጣ፤ በማለት ሰላማዊ ትግሉን እናዋድቃለን። ይህ በመሠረቱ በሀገራችን ያለውን አስከፊ የፖለቲካ ሁኔታ ከመመልከትና ይህ የገዥ ቡድን ላንዴም ለሁሌም እንዲወገድ ከመፈለግ የተነሳ መሆኑ ግልጽ ነው። ችግሩ ግን ፍላጎት የታሪክን ሞተር አያሽከረክርም። ተጨባጩ የሀገራችን እውነታና ያንን ለመለወጥ በቦታው የዋለው ተግባር፤ ሂደቱን ይነዳዋል።
ትግሉ በአምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ነው። ትግሉ ሀቅ ነው። ትግሉ አንድ ነው። በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በኢትዮጵያ ካለው ሰላማዊ ትግል ባሻገር ያለውን በማካሄድ ላይ ያሉት፤ አንድም የዚህ ወይንም የዚያ አካባቢ ነፃ አውጪ ግንባር ናቸው፤ አለያም ይህ ወይንም ያ ድርጅት ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ አሰባስቦ በአንድ ያሰለፈ ሕዝባዊ ድርጅትም ሆነ ጦር የለም። ስለዚህ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ወገን፤ የገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በሌላ ወገን የተሰለፈበት ትግል አልተያዘም። እናም ይህ እስካልሆነ ደረስ፤ ትግሉ የሕዝቡ አይደለም ማለት ነው። በርግጥ ሁሉም ድርጅቶች የሕዝብ ነን ማለታችውና ለሕዝብ ነው የምንታገልው ማለታቸው አይቀርም። ከሆነ ለምን በአንድ አይሰባሰቡም? ይህ የሕዝቡ የነፃነት ትግል የማይሆነው፤ የሚታገሉት ለራሳቸው ጠባብ የግል የድርጅታቸው ዓላማና ግብ ስለሆነ ነው። በራሳቸው ጠባቡ የድርጅት ፍላጎትና በሕዝቡ ፍላጎት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። አለያማ ሁሉም የሕዝቡን ፍላጎት እንከተላለን ካሉ፤ በአንድ ይሆኑ ነበር። እንግዲህ በዚህ ጠባብ የድርጅት መነፅር ሁሉንም ነገር ስለሚመለከቱ፤ የድርጅቶች መፍትሔ ከዚሁ ይመነጫል።
የነሱን ድርጅት የበላይ አድርጎ የማያስቀምጥ ሂደት ሁሉ፤ “ትክክል” አይደለም። ለዚህ ነው ሰላማዊ ትግሉን የሚኮንኑት። በትክክለኛ መንገድ መኮነንም ተገቢ ይሆናል። ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ መኮነን ግን ተገቢ አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ፤ ገዥውን ክፍል ለማስወገድ የሚደረግ ንቅናቄ እንጂ፤ ገዥውን ለመተካት የሚደረግ ሩጫ አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ፤ ያለው የገዢ ቡድን መወገድ አለበት ብሎ የተነሳ ሕዝብ፤ የሚወስደው የፖለቲካ እርምጃ ነው። ማንኛውም የትግሉ እንቅስቃሴ፤ በመሳተፍ ተወዳድሮ ለማቸነፍ ሳይሆን፤ የውድድሩን መድረክ፤ ሕዝቡን ለመድረሻና ለመቀስቀሻ ለመጠቀም ነው። ሰላማዊ ትግል ሽርሽር አይደለም። መስዋዕትነት ይከፈልበታል። የኛ ታጋዮች እየከፈሉበት ነው። ሳሙዔል አወቀ ከፍተኛውን መስዋዕት ከፍሏል። ሌሎች ቀድመዉታል፤ ሌሎችም ይከተሉታል። ለዚህ ነው ይህ ገዥ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መወገድ ያለበት። እና “ምርጫ ተወዳደረን እንድንጥለው ካልፈቀደልን፤ ሰላማዊ ትግሉ አበቃለት!” ማለት፤ ሰላማዊ ትግልን አለማወቅ ሳይሆን፤ ሆን ብሎ ማደናገር ነው። ሰላማዊ ትግል፤ በምርጫ ለማቸነፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ይደለም። በምንም መንገድ በምርጫ የሚቸነፍና ወዶ ሥልጣኑን የሚለቅ አምባገነን ጠላት የለም።
እኔ የሰላማዊ ትግሉን የምቀበለው፤ ፍጹማዊ ከሆነ ከትጥቅ ትግሉ ይበልጣል ከሚል ውሳኔ ተነስቼ አይደለም። በምንም መንገድ ትጥቅ ትግልን አልኮንንም። በአሁኑ የኢትዮጵያ የትግል አሰላለፍ፤ የቅንጣት ታክል ማመነታታት ሳይኖረኝ፤ የሰላማዊ ትግሉ ያላማራጭ ብቸኛ መንገዳችን መሆን አለበት እላለሁ። ለምን? አሁን አንድ የሆነ የትግል ማዕከል የለንም። እያንዳንዱ ድርጅት፤ ለድርጅቱ ግብ የሚታገልበት ሀቅ ነው ያለው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለግሉ ታግሎ ሥልጣን ጨብጧል። የያንዳንዱ ድርጅት ትግል፤ ያንን ለመተካት ነው። ውጪሰው ኢትዮጵያዊ ታጋዮች ደግሞ፤ አንድነት ከመመስረት ይልቅ፤ በመከፋፈልና እርስ በርስ በመነካከስ፤ ቁጥራቸው የበዙ ድርጅቶችን መሥርተን፤ በሕዝቡ ትግልና ድል ላይ ልናደርግ የምንችለው አስተዋፅዖ አመንምነነዋል። ዋናውን ጉዳይ ትተን በጠባብ ዕይታችን ታፍነን፤ ሩቅ ማየት አቅቶን ዓይናችን ስለጨፈን፤ የትግሉ ባቡር ጓዙን ጠቅልሎ ጥሎን እየሄደ ነው። እርስ በርስ መነኳኮሩ ጥሞናል። ከዕለት ዕለት መበጣጠስና መቀናነሱ አልቆረቆረንም።
አሁንም ባለንበት ስናዘግም፤ ትግሉ እኛን ታግሎናል። ይልቁንም ከኛ ተከትለው የትግሉን ችቦ የሚያበሩት ታጋዮች፤ መልሰው መላልሰው እንደኛው በተለመዱት፤ ሀገር ወይስ ድርጅት፣ የሰላማዊ ትግል ወይስ የትጥቅ ትግል፣ ከውጭ መደራጀት ወይስ በሀገር ቤት መንቀሳቀስ፣ ከኤርትራ መነሳት ወይስ ኤርትራን በጠላትነት የትግሉ አካል ማድረግ፣ በየግል ድርጅቶች መታገል ወይስ የትግል ማዕከል መፍጠር፤ በሚሉ አንድ ቦታ ላይ በማይደመደሙ ንትርኮች እንዳይጠመዱ ያሰጋል። ከዚህ ወጥተውና የእስከዛሬውን ትግል መርምረው፤ ትምህርት በመውሰድ፤ የአንድነት ትግል የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማስተካከል አለብን። ይኼን የማቀርበው፤ በትግሉ ሳይሆን፤ አሁን በውጭ ባለነው ታጋዮች ያለኝ እምነት እየመነመነ በመሆኑ ነው።
ሰላማዊ ትግል፤ ለሚታገሉለት ሕዝብና ሀገር፤ ለኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ፤ የመጨረሻ ከፍተኛውን ቦታ በመሥጠት፤ ከግለሰብ የኔነት ጋር የተያያዙትን በሙሉ፤ የግል ጥቅም ሆነ የድርጅት ግብ ወደ ኋላ ገፍቶ፤ ቅድሚያ ለወገንና ለሀገር የሚሠጡበት ትግል ነው። ትግሉ፤ ገዥውን ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አምባገነን መንግሥትን ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ የሚከተለውን ሥርዓት ወሳኝ የሆነ ነው። ትግላችን ከፍተኛ ጥንካሬን ይጠይቃል። ትግላችን ወሰን የለሽ ትዕግስትን ይጠይቃል። ሞትን መናቅን ይጠይቃል። ይህ ሰላማዊ ትግል፤ የሕዝቡ ትግል ነው። ሰላማዊ ትግል፤ ታጋዮች በሕዝቡ መካከል ተገኝተው፣ የአካባቢው አካል ሆነው፣ የአካባቢው ብሶት የራሳቸው ብሶት ሆኖ፣ ከተባሰው ጎን ተሰልፈው፣ ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚያካሂዱት ትግል ነው። የድርጅቶች ትግል አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ በሕዝቡ የሚደረግ ነው። ሰላማዊ ትግሉ ሁሉን አስተባባሪ ነው። የማንም የግል ድርጅት ንቅናቄ አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ ደጋፊው ብዙ ነው። ሰላማዊ ትግል የተወሰነ አባልነትን ብቻ ያነገበ የአንድ ክፍል ጥረት አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ዘንዳ ድጋፍና ተቀባይነትን ይሻል። በዚህ ዓይን ስንመለከተው ነው፤ የኛን አስተዋፅዖ ትርጉም የምናበጅለት።
የትጥቅ ትግሉ ተገቢ ቦታና ጊዜ አለው። አሁን ባለንበት ሀቅ፤ አንድ ማዕከል በሌለበት ሁኔታ፤ እያንዳንዱ ድርጅት ለራሱ መርኀ-ግብርና ግብ በቢታገልበት እውነታ፤ የታጠቀው ጦር የድርጅቶች መሣሪያ በሆነበት ጊዜ፤ የትጥቅ ትግሉ በጣም አደገኛ ነው። ሀገራችንን ወደ መበጣጠስ ያመራታል። በተለይም አብዛኛዎቹ የታጠቁት የነፃ አውጪ ግንባሮች መሆናቸው፤ አደጋዉን ያበዛዋል። እናም የሰላማዊ ትግሉ በጥረታችን አንድ ማዕከል አበጅቶ፤ ትግሉን እንድንቀጥልና ለድሉ እንድናበረክት ይጠራናል። ለሰላማዊ ትግሉ ቆርጠን እንነሳ። በሂደት አንድ ማዕከል ሲፈጠር፤ ሂደቱ ራሱ የሚያስከትለውን አዲስ ክስተት ከዚህ ሆኖ መገመት ከባድ ነው። በወቅቱ ግን ሂደቱን ተከትሎ እምነታችን መቀየር እንዳለበት ጥርጥር የለኝም።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ረቡዕ፤ ሰኔ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህቱረት (6/17/2015)
_________________________________________________
የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፩)
ኢትዮጵያዊያን፤ ተከታታይ አምባገነን መሪዎችን ከነአገልጋዮቻቸው ለማስወገድና የሕዝቡን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ትግል፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ነው። በ ፲፱፻፷፮ ዓመተ ምህረት ሕዝቡ የተነሳባቸው የመብትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም። ይኼው ሃምሳ ዓመት አለፈው። ይባስ ብሎ ሕዝቡን የመንግሥት አገልጋይ አድርጎ የሚጠቀም ጠባብ አምባገነን ገዢ፤ በሀገራችን ነግሷል። ይኼን መንግሥት ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ማዕከል የለውም። በሀገር ቤት ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚንቀሳቀሱት የሰላማዊ ታጋዮች እና ከሀገር ውጪ ያሉ ታገዮች፤ በመካከላቸው የትግል ቅንጅት የለም። በሀገር ቤት ያሉት የሚያደርጉት ትግል፤ ምስጋና ለወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ አምባገነን መንግሥት ምስጋና ይግባውና፤ መልክ እየያዘ ነው። የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የአንድነት ፓርቲና የሰማያዊ ፓርቲ ታጋዮች ወደ አንድ መሰባሰባቸው፤ የትግሉን ማዕከል ለማበጀት የማዕዘን ድንጋዩን ጥሏል።
ሰላማዊ ትግል ካለው መንግሥት ዓይን የተሰወረ ተግባር የለውም። ለአቸናፊንቱ ያለው እምነት የተመረኮዘው፤ የጨበጠው እውነትና ያነገተው የሕዝብ እዮታ ነው። እውነት ምን ጊዜም አቸናፊ ሆኖ ይወጣል። የሕዝብ እዮታ ደግሞ፤ ይዘገይ እንደሆን እንጂ፤ አቸናፊ ሆኖ መውጣቱ አያጠራጥርም። ምንም እንኳ የገዥው ክፍል፤ በዕለት በዕለት በሥር በሥሩ እየተከታተለ ሰላማዊ ታጋዮችን ሊያመክን ቢሞክርም፤ ምንጫቸው የገዥው በደል የደረሰበት ሕዝብ ነውና አይደርቅም። እኒህ በሰላም ለመታገል ቆርጠው የተነሱ ታጋዮቻችን የሚያደርጉትን ትግል፤ እነሱም ሆነ ከነሱ ውጪ ያለነው ሌሎች ታጋዮችና ሰላማዊው ሰው፤ ስለሚያደርጉት ሆነ ማድረግ ስላለባቸው እንቅስቃሴ ያለን ግንዛቤ፤ አንድ አይደለም። የሰላማዊ ትግልን ምንነት፣ ጠቃሚ ግንዛቤና ዝርዝር መርኅ፤ ከመጽሐፍትና ከድረገፆች ማግኘት ይቻላል። ያ መሠረታዊና ለመነሻው መረጃ ነው። እናም እንደ ማንኛውም ኅብረተሰባዊ ክስተት ሁሉ፤ በሚተገበርበት ቦታ፤ ያካባቢውን ተጨባጭ እውነታና የትግል ተመክሮ ከዝርዝር ውስጥ አስገብቶ፤ ያካባቢው የተለዬ ሁኔታ አስተካክሎት፤ ለሂደቱና ስኬቱ ዋነኛ የሆኑ ወሳኝ ሁኔታዎችን በትክክል ካልተረዳን፤ ድፍኑ የሰላማዊ ትግል ግንዛቤ፤ ተንሳፋፊ ነው። ከዚህ በመነሳት፤ በኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግልን ግንዛቤ በግልጽ በመተንተን፤ ሰላማዊ ትግሉ እንዴት ነው? የሚለውን መልሼ፤ አንድ ተመሳሳይ ግንዛቤ ላይ እንድንደርስ፤ በዚህ ጽሑፍ አሳያለሁ።
በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ ሰላማዊ ትግል፤ በሀገራችን ያለውን ሕግና ስነ-ሥርዓት በትክክል አምነውበት፤ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ሁኔታዎች መሟላትና መኖር ተቀብሎ፤ መንግሥታዊ ሥልጣኑን በምርጫ ተወዳድሮ በማቸነፍ፤ ገዥውን ፓርቲ ለመተካትና ያለውን ሥርዓት ለማስቀጠል የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አይደለም። ሰላማዊ ትግል የተወዳዳሪ ወይም የተፎካካሪ ፓርቲዎች መንገድ አይደለም። የተፎካካሪ ወይም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች፤ ያለውን ሥርዓት ትክክለኛነት ከጥያቄ ውስጥ አይስገቡም። ከገዥው ክፍል ያላቸው ልዩነት፤ ውስንና የአስተዳዳር ዘይቤ ላይ ያተኮረ ነው። ሰላማዊ ትግል፤ መሠረታዊ የሆነ ሀገራዊ የአስተዳዳር ፍልስፍናና ተግባር፤ ከዚህም ተነስቶ የአስተዳዳር መመሪያውን አፈጻጸሙ ላይ ልዩነት ያቀርባል። ሰላማዊ ታጋዮች፤ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ብቻ ሳይሆን፤ ተዘግቷል ብለው ያምናሉ። ሰላማዊ ትግሉ፤ ገዥውን ክፍል ለማስወገድ የሚደረግ ንቅናቄ ነው። ለመተካት የሚደረግ ሩጫ አይደለም።
ሰላማዊ ትግሉ፤ ሁለት ተፃራሪ የሆኑ ተግባራት ባንድ ላይ የሚከናወኑበት ሂደት ነው። የመጀመሪያው እንደ ፖለቲካ አካል ለመንቀሳቀስ፤ የሀገሪቱ ሕግና ደንብ በሚያዘው መሠረት፤ ተመዝግበው ሕጋዊ የሆነ እንቅስቃሴያቸውን ማካሄድ ነው። ይህ፤ የማይወዱትን ግዴታ እንዲቀበሉ ያስገድዳቸዋል። እናም መከተል ያለባቸው መንገድና ማድረግ ያለባቸው ግዴታ አለ። እንደ የፖለቲካ አካል በምርጫ ቦርዱ መመዝገብ፣ ተወዳዳሪዎችን ማዘጋጀትና ማቅረብ፣ መወዳደር የመሳሰሉት ናቸው።
ሁለተኛውና የሕልውናቸው መሠረታዊ ዓምድ፤ ሰላማዊ ከሚለው ማንነታቸውን ገላጭ ቃል ቀጥሎ ያለው ትግሉ ነው። ይህ እምቢተኝነታቸው ነው። ይህ ነው ትግሉ። ሕዝቡ ዕለት በዕለት በየቦታው የሚደርስበትን በደል አብረው ተካፋይ ስለሆኑ፤ ተበዳዩን ወገን በማሰለፍ፤ በእምቢተኝነት ለአቤቱታ ይነሳሉ። መልስ እንደማያገኙ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን፤ በሂደቱ፤ እያንዳንዱን የሕዝብ በደል፤ ሀገራዊ መልክና ይዘት በመሥጠት፤ ሕዝቡን ለእምቢተኝነት ይቀሰቅሱበታል። የበደሎችን ተዛማጅነት ያሳዩበታል። የመወዳደር ግዴታቸውንና በዚህ አጋጣሚ የሚፈጠሩ መድረኮችን፤ ለዚሁ ተግባር ያውሏቸዋል። ተወዳድረው ለማቸነፍ ሳይሆን፤ የውድድሩን ሂደት ሕዝቡን ለመድረሻና ለመቀስቀሻ ይጠቀሙበታል። አምባገነኑን ገዥ ክፍል ለማጋለጫ ይጥእቀሙበታል። መወዳደራቸው የመጀመሪያውን ግዴታቸውን ሲያሟላላቸው፤ ተወዳድረው የማቸነፍ በሩ እንደተዘጋ ያውቃሉና፤ ሂደቱን ለመቀስቀሻ ሲጠቀሙበት፤ ሁለቱንም ግዴታዎቻቸውን አሟሉ ማለት ነው።
ይህ ነው በተወዳዳሪ ድርጅቶችና በሰላማዊ ታጋዮች መካከል ያለው አንዱ ልዩነት። በመሠረታዊ ማንነታቸው ላይ ያለው ሌላው ወሳኝ ልዩነት፤ ተወዳዳሪ ድርጅቶች ከአንድ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰላማዊ ትግሉን የሚያራምዱ ታጋዮች ግን፤ አንድ እና አንድ ድርጅት ብቻ ነው የሚኖራቸው። ካንድ ከበዙ የሰላማዊ ትግሉን ሂደት አበላሽተውታል። ለምን?
ሰላማዊ ትግል፤ ያለው የገዢ ቡድን መወገድ አለበት ብሎ የተነሳ ሕዝብ፤ የሚወስደው የፖለቲካ እርምጃ ነው። በዚህ እምነት ዙሪያ የሚሰባሰቡ፤ ውስን በሆነ የመታገያ ዕሴቶች የተባበሩና ከዚያ ውጪ፤ የተለያዬ አመለካከት ያላቸው ናቸው። በአሁኗ ኢትዮጵያ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል፤ አስራ ሁለት መሠረታዊ የትግል ዕሴቶችን ያቅፋል።
፩ኛ. ያለው አስተዳደር፤ ጠባብ፣ ወገንተኛና አምባገነን ነው።
፪ኛ. በሀገራችን ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተረግጧል።
፫ኛ. የገዥው ክፍል እውነተኛ የሕዝብ ተወካይ አይደለም።
፬ኛ. ይህ ሥርዓት ሲወገድ፤ የሚከተለው ሥርዓት፤ ዴሞክራሲያዊና ኢትዮጵያዊ ይሆናል።
፭ኛ. ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ትግል፤ በሽግግር መንግሥት ሂደት ሥር ያልፋል።
፮ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅት፤ የሀገራችን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ይረቀቃልና ይጸድቃል።
፯ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፤ የግለሰብ ዴሞክራሲያ መብቶች ይከበራሉ።
፰ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ መንግሥቱ፤ በሀገራችን የሕግ የበላይነት ይሰፍናል።
፱ኛ. በሕገ-መንግሥቱ፤ እያንዳንዳችን በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ የምንሳተፍበት የፖለቲካ ምኅዳር ይዘረጋል።
፲ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ይጠበቃል።
፲፩ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፣ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ይከበራል፤ ሀገሪቱ ለኢትዮጵያዊያን ትሆናለች።
፲፪ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅት፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረታዊ የሆኑ ተቋማት ይቋቋማሉ።
የሚሉት ናቸው።
በነዚህ ዙሪያ የሚሰባሰቡት የፓርቲ አባልት አይደሉም። በነዚህ የትግል ዕሴቶች ዙሪያ የሚሰባሰቡት፤ መላ የተበደሉና ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ከነዚህ የትግል ዕሴቶች ሌላ ይዞ ሊንቀሳቀስ የሚችል፤ የገዥውን ክፍል ለውጥ የሚሻ አይኖርም። ሌላ አጀንዳ ያለው ካለ፤ የትጋዩ ክፍል አካልም ወገንም አይደለም። ይህ ወደ ሽግግር መንግሥት የሚወስደው ጎዳና፤ አንድ ነው። ከዚያ በኋላ የሚከተለው እንዲህ ነው።
ታጋዩ ክፍል፤ ሕዝቡ የትግሉ ባለቤት፣ መሪና የድሉ ባለቤት መሆኑን አምኖ ይቀበላል። ስለዚህ የሕዝቡ ድርሻ የሆነውን፤ በሽግግሩ ጊዜና ከሽግግሩ በኋላ፤ ሕዝቡ የሚወስነው ይሆናል። ከዚያ በፊት ለሚደረገው ትግል፤ ታጋዩን በሙሉ በአንድነት ማሰባሰብና፤ ትግሉ በአምባገነኑ ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በሕዝቡ መካከል ብቻ መሆኑን ተረድተን፤ አንድ ትግል አንድ ኢትዮጵያዊ ራዕይ ይዘን የምንፋለምበት መሆን አለበት።
ሰላማዊ ትግሉ በኢትዮጵያ የአሁን ተጨባጭ የፖለቲካ ሀቅና ከትጥቅ ትግል ተለይቶ የተሻለ አማራጭ የሚሆንበትን ምክንያትና ሌሎች ትንታናዎቼን በሚቀጥሉት ክፍሎች አቀርባለሁ።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ረቡዕ፤ ሰኔ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህቱረት ( 6/17/2015 )
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply