በ2001ዓም ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህ” በሚል ርዕስ የጻፉት ድንቅ ጽሁፍ የያዘው መልዕክት በዚህ አዲስ ዓመትም ትልቅ ትርጉም ያለው ሆኖ ስላገኘነው “ያለ ምንም ደም አዲስ ዓመትን” በማለት ርዕስ ሰጥተነው እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ በርዕሱ ላይ ላካሄድነው መጠነኛ ለውጥ ኃላፊነቱን እንወስዳለን፡፡
የሰሞኑ መልካም ምኞች የሚመስል ስሜት የምንለዋወጠው “እንኳን አደረሰሽ (አደረሰህ)” በመባባል ነው። ከየት ተነስተን ወዴት እንደደረስን ግን አናውቅም። ምኞቱ የሚገልጸው ሁላችንም በአንድነት ወደተሻለ ደረጃ መሸጋገራችንን ይመስላል፤ እውነቱ ግን ሁላችንም በአንድነት ቁልቁል ወርደናል።
“… ጋሼ ማረኝ ማረኝ፤ ጋሼ ማረኝ ማረኝ
ዶሮ ብር አወጣች እኔን ሥጋ አማረኝ! …”
ተብሎ የተዘፈነበት ጊዜ መቶ ዓመት ሊሆነው ነው፤ ዛሬ እኛ ምን ብለን ልንዘፍን ይቃጣናል?
ለእኔ “ያለምንም ደም” የሚለው የደርግ መዝሙር ተስማሚ ሆኖልኛል። አንድ ዶሮ መቶ ብር፣ አንድ ኪሎ ቅቤ መቶ ብር፣ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ስድስት ብር፣ አንድ እንጀራ ሁለት ብር ተኩል፣ አንድ እንቁላል አንድ ብር ከሃምሳ ሲሆን፣ የማገዶውንና የውሀውን ትተን (ውሀ ከዘይት መወዳደር ጀምሮአል፤ በአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ወደ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ብር ግድም ከፍያለሁ!) አንድ ድስት የዶሮ ወጥ ምን ያህል ሊያወጣ ነው እንግዲህ እንኳን አደረሳችሁ ማለት መልካም ምኞት ነው ወይስ እርግማን? ብዙ ሰው ከ2000 ወደ 2001 የተላለፈው “ያለምንም ደም” ውሀውም ተወዶበት ነው። ለመሆኑ ለሚሌኒየም ግርግርና ከበሮ ምን ያህል ገንዘብ ወጥቶ ይሆን? ቂል አትበሉኝና የወጣው ገንዘብ ለእያንዳንዱ ገበሬ ለዓመት በዓሉ ሃምሳ ብር ቢታደል የሚያስፈልገው ወጪ 500,000,000 ብቻ ነው፤ ጥድቁ ቀርቶ ሆነና …
የደላቸው ሰዎች በምድረ ኢትዮጵያ የሉም ማለት አይለም። እነሱ አዲሱን ዓመትሲቀበሉ ግቢያቸውን ደም በደም አርጥበውታል፤ የዶሮውንም፣ የበጉንም፣ የፍየሉንም፣ የሰንጋውንም ደም ደሀው አላየም። ሀብታሞቹ ለርኩሳን መንፈሶች ገብረውልን የምሳቸውን ሰጥተው ባይገላግሉን በቅዥት እናልቅ ነበር! ሀብታሞች ርኩሳን መንፈሶችን መክተውልናል። ለአዲስ ዓመት ትልቁ ነገር ደም ማፍሰሱ ነው እንጂ ሥጋ መብላቱ አይደለም። ማን ነበር …
“… እኔ ስበላ አይተህ ደስ ይበልህ እንጂ
ያንተ መከጀልስ ለምንም አይበጅ፤ …” ያለው?
ዛሬ መከጀልም ቅንጦት እየሆነ ነው። “ደሀ በሕልሙ ቅቤ ባይጠጣ” ይባል ነበር – ዱሮ። ዛሬ ሕልም ማለም ቀርቷል፤ ዛሬ ሕልሙ ወደ ቅዠት ተለውጦአል። የዘንድሮው ቅዠት ክፋቱ እስቲተኙ አይጠብቅም፤ የሚያስለፈልፈው ደሀውን ብቻም አይደለም፤ በእውንም በጥጋብም ያቃዣል። “ኢኮኖሚው እያደገ ነው፤ የህዝቡ ኑሮ እየተሻሻለ ነው” እያሉ በጠኔ ለሚሰቃዩት መንገር ቅዠት አይደለም?
እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ለዕንቁጣጣሽ ዶሮ ማረድ ያልቻለ ደሀ አይቼ አላውቅም። በሠፈሬ የተካንሁት እኔ ብቻ ስለነበርሁ፣ ለዶሮ አራጅነት በየቤቱ እጠራ ነበርና በደንብ አውቃለሁ። ደሀው የሚቸገረው የዶሮውን መልክ መረጣ ላይ ነበር። ገብስማ፣ ጥቁር፣ ወይም ዛጎልማ ወይም ሌላ ነበር ትልቁ ችግር። ዛሬ ችግሩ ሌላ ሆነ፤ ዕንቁጣጣሽን የምንቀበለው ያለ ምንም ደም ሆነ። ሃያኛውን ምዕተ-ዓመት ስንቀበል ደሀው ዶሮ ማረድ ይችል እንደነበረ አትጠራጠሩ። ሃያ አንደኛውን ምዕተ-ዓመት ስንቀበል ዶሮ ማረድ ያለመቻላችን ዕድገት መሆኑ ነው? የመቶ ዓመት ዕድገት ለዕንቁጣጣሽ ዶሮ ማጣት!
ደሀነትን ማጠፋት ሲባል ግራ ይገባኝ ነበር፤ ለካስ ያውም ከተገኘ በአምስት ብር ደረቅ ሽሮ፣ የሦስት ብር እንጀራ ለእንቁጣጣሽ መብላት ነው! ማን ነው ይህንን ለደሀው የመረጠለት? ደሀነቱ እንኳን ደሀውን እኔንም ክፉኛ ተሰማኝ። ለዶሮ መግዣ እያልሁ ለዓመት በዓል ትንሽ ገንዘብ የምሰጣቸው ሰዎች ነበሩ። በአቅሜ ያስለመድኋቸው ገንዘብ ዛሬ የዶሮዋን አንድ ክንፍ አይገዛም። ታዲያ እኔ አልደኸየሁም? ዱሮ ለዶሮም፣ ለቅቤም የምሰጠው ዛሬ ለዶሮ ብቻ የሚበቃ ሲሆን አልደኸየሁም? ተያይዘን ነው እየደኸየን ያለነው፤ በደርግ ዘመን አንድ ሰሞን የአምቦ ውሀና ክብሪት ጠፋና ህዝብ ተንጫጫ። በራዲዮና በቴሌቪዥን የተሰጠው መልስ “አድኃርያን ለውስኪ መበረዣና፣ ለሲጃራ ማቀጣጠያ ቢቸግራቸው ሰማይ የተደፋባቸው መሰላቸው” የሚል ነበር። ራዲዮኑንና ቴሌቭዥኑን ሲቆጣጠሩት ማሰብ ይቸግራል መሰለኝ።
እንዲያውም ሌላ ሃሳብ መጣብኝ። አድባሮቹ፣ ቆሌዎቹ፣ ምናምንቴዎቹ የሰው ደም ለምደው እንዳይሆን፤ ያለ ምንም ደም የሰውንም ደም ጨምሮ ከሆነ በዚሁ ይለፍልን፤ ሌላ ምን እንላለን።
Leave a Reply