በኢትዮጵያ የግማሽ ምዕተዓመት የፖለቲካዊ ለውጥ ንቅናቄ ታሪክ የመሬት ጥያቄ ዋነኛውና አብዮትን ማሳካት የሚችል ጉልበት ያለው የህዝብ ብሶት መገለጫ መሆኑ የማያሻማ ነው፡፡ ፍውዳላዊውን የሰለሞናዊ ስርወ መንግሰት ንጉሳዊ ስርዓት ግብዓተ መሬት ካፈጠኑት አብይ የሕዝባዊ ብሶትና ምሬት መገለጫ የለውጥ ንቅናቄ መርሆች መኸል “መሬት ለአራሹ” የተሰኘው የተማሪዎች ንቅናቄ መርህ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡
በንጉሳዊው የፊውዳል ስርዓት የንጉሱ ጋሻ ዣግሬዎች ማለትም መኳንንቱ እና መሳፍንቱ መላውን የሀገሪቱ ሰፊ የገጠር እርሻ መሬት በባለቤትነት (በባላባትነት) ተቀራምተው፤ ባለርስት በመባል ድኸውን ገበሬ ጭሰኛ በማድረግ ጉልበቱንና ምርቱን እየበዘበዙ ለዘመናት ህልውናውን እየፈተኑ፣ ኑሮውን ከድጥ ወደ ማጥ እየገፉ ጭቆናንና በደልን አንሰራፈተው ቢቆዩም የጭሰኛው ገበሬ ልጆች የሆኑት የለውጥ ፋኖ ያነገቡ ተማሪዎች “መሬት ለአራሹ” በተሰኘ መርህ ባፋፋሙት የአብዮት ንቅናቄ ሰርዓቱ ለማክተም ተገዷል፤ ምንም እንኳ ይህ አብዮት ፍሬ ያላፈራና በጥቂት ወቶአደሮች የግል አምባገነናዊ ባህርይ ምክንያት የአብዮቱ ባለቤት ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዘብ የተቀማና እስከዛሬም ያልተመለሰ ቢሆንም የ“መሬት” ጥያቄ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ግን ምን ያህል አቅም እንዳለው ለመገንዘብ ይረዳል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬም በህዝብ መሬት ላይ አዛዡ ናዛዡ አኔ ነኝ ብሎ አዋጅ ባስነገረ አንዲሁም የመሬት ባለሙሉ መብት አርሱ ብቻ አንደሆነ የሚያትት ፖሊሲ በቀረፀ ገዢ ቡድን ነው የምትተዳደረው፤ ዛሬ ላይ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ስለሚኖርበት፣ ስለሚያርስበት፣ ሞቶ ስለሚቀበርበት የቀዬ መንደሩ መሬት ዋሰትና የለውም፤ ገዢው ቡድን በፈለገ ጊዜ የእርሻውን መሬት ወደ ኢንዱስትሪ ዞን ፣ የመኖሪያውን መንደር ወደ ንግድ ማዕከል ሕንፃ መገንቢያነት የመለወጥ ስልጣን ባለቤት ነው፤ መሬትን ሽጦና ለውጦ ትርፍን አጋብሶ ማደርም ለገዢው ብቻ የተፈቀደ መብት ነው፡፡
ለአርሶ ኗሪው የሀገሬ 85% ህዝብ የእርሻው መሬትና እስትንፋሱ፤ የስጋና ነብስን የመሰለ ጋብቻ የመሰረቱ ናቸው፤ ይህ ማለት ደግሞ ለመኖር ያርሳል፣ ለማረስ ደግሞ የሚታረስ መሬት ይሻል ማለት ነው፤ እናም የሚያርስበትን መሬት ማንም ሊያሳጠው፤ በፈለገም ጊዜ ሊነጥቀው አይገባም!! አርሶ የሚበላበትን የእርሻ መሬት መንጠቅ አስትንፋሱን ከስጋው ከመለየት የሚተናነስም አይደለም፤ ለምስኪኑ የኢትዮጵያ ገበሬ ማረስ እና መተንፈስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡
የክርስትናው ቅዱስ መፅሐፍ ከክርሰቶስ ልደት በፊት በእስራኤል ህዝብ ላይ ነግሰው የነበሩ ነገስታትን ታሪክ በሚተርክበት መፅሐፈ ነገስት በተሰኘው ንዑስ መፅሐፍ የመጀመሪያ ክፍል በምዕራፍ ፳ ከቁጥር ፩ አስከ ፳፱ ላይ አንድ ታሪክ ያስነብበናል፤ ጊዜው በሰማሪያ ላይ አክዓብ የተባለ ንጉስ የነገሰበት ዘመን ሲሆን በዚህ ንጉስ መኖሪያ አጠገብ የወይን ቦታ (መሬት) ያለው ናቡቴ የተሰኘ ምስኪን ሰው ነበረ፤ ንጉሱ አክዓብም የናቡቴን የወይን ቦታ ለራሱ ሊያደርግ ወደደና “ይህ የወይን ቦታህ በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ስፍራ አደርገው ዘንድ ስጠኝ አኔም በርሱ ፈንታ የተሻለ የወይን ቦታ ልስጥህ የምትወድም ቢሆንና ከተሻለህ ግምቱን ገንዘብ ልስጥህ” ብሎ ናቡቴን ተናገረው፤ ናቡቴ ግን የአባቶቹን ርስት ይሰጠው ዘንድ ፈቃደኛ አንዳይደለ ለንጉስ አክዓብ መለሰለት፤ ንጉሱም አጅግ ተበሳጨ፣ ተናደደም፤ ሚስቱ ኤልዛቤልም ይህን ብስጭቱንና ንዴቱን ተመልክታ የሚፈልውን ማግኘት ካልቻለ የንግስናው ፋይዳ ምን አንደሆነ ጠየቀቸው፣ በክፉ ምክርም ልቡን መርዛ ናቡቴን ገድሎ የወይኑን ስፍራ ያለከልካይ ሊወርስ አንደሚቻለው ተስፋ ሰጠችው፤ አንደእርሷም ክፉ አሳብ ናቡቴ በሐሰት ምስክር በግፍ ተገደለ፣ አክዓብም የናቡቴን የወይን ቦታ ይወርስ ዘንድ ወደ ስፍራው ወረደ ነገር ግን ምስኪኑ ናቡቴ ለርስቱ በግፍ ቢገደልም ንጉሱ አክዓብ የወይን ስፍራውን አይወርስም፡፡
የአሻውን ይፈፅም ዘንድ ከልካይ የሌለበት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ገዢ ቡድንም አክዓብ በመኖሪያ ስፍራው አጠገብ የነበረውን የምስኪኑ ናቡቴን የወይን ስፍራ በተመለከተበት ዓይን የመንበረ መንግሰቱ መቀመጫ በሆነቸው አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ አርሶ አደሮችን መሬት ከምስራቅና ምዕራብ እንዲሁም ከሰሜንና ደቡብ አየ፣ ተመለከተ፤ በተመለከተውም ነገር ምን ያህል ሊጠቀምበት፣ እልፍ አእላፍ ትርፍም ሊያጋብስበት አንደሚችል አስቦ ጥቅሙን አሰላ፤ በስሌቱም ውጤት አጅግ ሐሴት አደረገ፤ ለሐሴቱም ስኬት በኤልዛቤል ክፉ ምክር አምሳል ያዘጋጀውን የአዲስ አበባና የአሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን (ዕቅድ) የሚል ሴራ ይዞ ቀረበ፡፡
ናቡቴ የንጉስ አክዓብን ህልውና የሚፈትን ጥያቄ ውድቅ አንዳደረገ ሁሉ፤ ምስኪኑ የአዲስአበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ገበሬና ልጆቹም ይህን ከመኖሪያቸው መንደርና ከእርሻቸው መሬት የሚያፈናቅል፤ ህልውናቸውንም አደጋ ላይ የሚጥል ሸረኛ ፕላን (ዕቅድ) እንደማይቀበሉ አደባባይ ወተው ተቃወሙ፤ ኤልዛቤላዊው ስርዓትም ናቡቴያውያን የመሬት ባለመብቶችን የህይወት ዋጋ አስከፍሎ አሳቡን ለማሳካት ብዙ ቢጥርም፤ አክዓብ ከናቡቴ ደም መፍሰስ በኃላ የወይን ስፍራውን ሊወርስ ወርዶ አንዳልተሳካለት ሁሉ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሐን ዜጎችና ተማሪዎችን ውድ የሕይወት ዋጋ ካስከፈለ የእምቢተኝነት ፅናት በኃላ የኢትዮጵያ ገዢ ቡድንም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን የኦሮሚያ ምስኪን ገበሬዎች የመኖሪያና የእርሻ መሬት ሊወርስ አልተቻለውም!! አይቻለውምም!!(leጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ በተለይ የተላከ)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
gud says
Religion mixed with politics .
Poor mix
gud says
Every thing is about striking a balance .
Development vs human right
Trust vs suspicion
Love vs hate etc
I support the master plan as long as it is implemented fairly .