
የምኖረው አሜሪካ ነው። አርብ ዕለት በከነቲከት ስቴት፣ ኒውታውን በምትባል ከተማ፤ ሳንዲ ሁክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ፤ ፳ የስድስትና የሰባት ዓመት የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሕፃናትና ስድስት መምህርቶቻቸው በትምህርት ቤታቸው ተገደሉ። የተገደሉት የእናቱን መሣሪያዎች አንግቶ፤ መጀመሪያ እናቱን ከተኛችበት ገድሎ፣ የትምህርት ቤቱን መጠበቂያ ጥሶ በገባ የሃያ ዓመት ጎረምሣ ደጋግሞ በረፈረፈባቸው ጥይቶች ነበር። አሜሪካ ከላይ እስከ ታች በዚህ ኢሰብዓዊ ተግባር ተርገበገበች። ከዩጋንዳ ለሐዘኑ መልዕክትና ማስታወሻ ተላከ። ከቦዝንያ፣ ከአውስትራሊያ፣ በጠቅላላው ከዓለም ዙሪያ የሀዘን መግለጫዎች ጎረፉ። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በቦታው በመገኘት የስነ ሥርዓቱ ተካፋይ ሆነው፤ የሀገሪቱን አጠቃላይ የሀዘን ትብብር ለሙታን ወላጆችና ለከተማው ነዋሪዎች አቀረቡ። እኔም የዚሁ ሀገር ነዋሪ ሆኜ ጉዳዩን በቅርብ ስከታተል፤ ሀዘኑ አጥንቴ ገባ። የሁለት ልጆች አባትም በመሆኔ፤ ውስጤ ተርገበገበ። ሁለተኛዋ ልጄ በሟቾቹ ተመሣሣይ ዕድሜ ያለች በመሆኗ፤ ሀዘኑን አቀረበብኝ። በሀዘኔ መካከል አዕምሮዬ አጥረ ሰፊ ነውና የሀገሬን ድቅድቅ የፖለቲካ ጨለማ ጥሶ መንከራተት ያዘ።
ጎንደር ከተማ መላኩ ተፈራ የጨፈጨፋቸው ለሰላማዊ ሠልፍ የወጡ ወጣቶች፤ ከፊቴ ተደቀኑ። በዓለም የሠራተኞች ቀን መከበሪያ (ሜይ ደይ) ምሽት፤ ፲ ፱ ፻ ፷ ፱ ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ ውስጥ፤ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዕዛዝ ሶስት ሽህ ወጣቶች ሲታረዱ ነበርኩና ልቤ ተንሰፈሰፈ። ወያኔ የሕዝቡን ድምፅ ለመቀማት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ፤ በግንቦት ፲ ፭ ቀን ፲ ፱ ፻ ፺ ፯ ዓመተ ምህረት ማግሥት የገደላቸዉ ፻ ፺ ፪ ወጣቶች አዕምሮን አጣበቡት። አሁን ካጋጠመኝ ሀዘን ጋር ሳመዛዝነው፤ ሁለት የሚዛን ሠፈሮች ጎልተው ወጡ። በኢትዮጵያ፤ በሥልጣን ላይ የሚወጡ፤ ሥልጣናቸውን ለመጠበቅ፤ ያርዳሉ፣ ያስራሉ፣ ያሳድዳሉ፤ እንዳሻቸው ያደርጋሉ። በዚህ ሀገር ደግሞ፤ የሀገሪቱ መሪዎች፤ ሰው ሲሞት፤ የሟቾችን ዕልፈት በመጠቀም፤ ተቀባይነታቸውን ለማሳደግ፤ በቀብራቸው ስነ ሥርዓት በአካል በመገኘት አብረው የሕዝቡን ሀዘን ይካፈላሉ።
ይኼ እንዴት ነው? የኢትዮጵያዊ ሕይወት በሚዛኑ ሲቀመጥ ሚዛኑ ስለሚቀል ነው? ለምን? መላኩ ተፈራ፣ መለሰ ዜናዊ፣ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የግል ሕይወታቸውን ለማሣመር፤ ለሥልጣን ባላቸው ጥማት፤ “እኔ ብቻ ነኝ ትክክለኛው።” “ለሀገሪቱ እኔ አውቃለሁ።” “የምነግራችሁን ስሙ፤ የማዛችሁን ፊፅሙ።” እያሉ በሽዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን፣ ወጣቶችን፣ በመካከለኛ ዕድሜ ያሉትንና አዛውንትን ማረዳቸው ምን ይባላል? ይህ ከፖለቲካ አመለካከት በላይ ነው። ሌሎችን ገዳዮች ቀርቶ፤ እኔም ሰብዕናዬ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ኢትዮጵያዊ ከመሆኔ በላይ፤ ሰው ነኝ። ሰው በመሆኔም፤ ይህ አሜሪካ ውስጥ፤ በትንሽ ከተማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የተደረገው አረመኔያዊ ተግባር፤ ዓይኔን በእንባ ልቤን በስስት ሞላው። ይኼ እንዳይደገም እፈልጋለሁ። ከሞላ ጎደል አሜሪካዊያን በሙሉ ይኼ እንዳይደገም ይፈልጋሉ። ከሞላ ጎደል በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች፤ ይኼ እንዳይደገም ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ የደርግና የወያኔ ዘመን እንዳይደገም እፈልጋለሁ። ወያኔ ግን አሁንም አለ። ግድያውን፣ ማሠሩን፣ ማሳደዱን እየገፋበት ነው። ሰብዕናችንን የምናከብር ሁሉ፤ በቃ ልንል ይገባል። ወያኔ መወገድ አለበት።
ለሥልጣን ጥማት የተደረጉት ጦርነቶች ለምጥ፤ ሀገራችንን አጥለቅልቋታል። ለምጡ እያገረሸ፤ ተጨማሪ በደሎች ተጨማሪ ጦርነችን እያስከተሉ፤ የተከተሉት ጦርነቶች አዳዲስ ጠባሳዎችን እየፈጠሩ፤ ማለቂያ የሌለው እሽክርክሪት ውስጥ ገብተን እየዳከርን ነው። ለትናንቱ ግፍ፤ ዛሬና ነገ በዱቤ ተይዘው፤ አንገታቸውን ሰብረው እዳ ከፋይ ሆነዋል። እስከመቼ?
ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ከኋላው ለማሠለፍ፤ ትግራይን የተለየችና ነፃ መዉጣት ያለባት አድርጎ አቀረበ። ለዚህም ይረዳው ዘንድ “እኛ” እና “ሌሎች” የሚል ፈጠረ። እናም “ወርቃሞቹን ትግሬዎች” ለማሰባሰብ፤ ጠላት አዘጋጀ። “አማራ ገዢ በመሆኑ፤ ትግሬዎች ተበደልን” አለ። ስለዚህ “ጠላታችን አማራ ነው” አለ። በገዥዎችና ተገዥዎች መካከል ያለውን በደል ተመርኩዞ የሚነሳውን ትክክለኛ ሕዝባዊ አመፅ፤ ወያኔ ባነገተው አቆማዳ ጠቅልሎ፤ ደደቢት ውስጥ ቀበረው። ይኼ ያልበገራቸው ጥሩ ኢትዮጵያዊያን አሉ። ትግሬ በመሆናቸው ወያኔን ከመደገፍ ይልቅ፤ ኢትዮጵያዊነታቸው ያየለባቸውና የወያኔን ምንነት ከማንም የበለጠ ያወቁ አሉ። አብዛኞቹ ትግሬዎች ግን፤ በአንድ ምክንያት ወይንም በሌላ፤ የወያኔ ሥርዓት ጠበቃ ሆነዋል። በምንም መንገድ ቢሆን ግን፤ ትግሬዎችን ጠቅልሎ ከወያኔ ጉያ መክተት፤ ፀረ አንድነት ነው። በአንፃሩ ልንገነዘበው የሚገባው፤ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ወይንም ሶማሌ ሆነው፤ ከወያኔ ለሚወረወርላቸው ትራፊ፤ የሀገራቸውን ሕልውና “ገደል ይግባ” ብለው የተሠለፉ ሆድ አደር ወያኔዎች መኖራቸውን ነው።
አንድ ነገር እንደገና በደንብ ግልፅ መሆን አለበት። በኛ ሀገርም ሆነ በሌሎች ሀገሮች፤ በጨቋኝና በተጨቋኞች መካከል ባለው ሀቅ፤ ተፃራሪ የሆኑ አቋሞችን በያዙ ክፍሎች መካከል ትግሎች ተደርገዋል፤ ይደረጋሉም። የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፤ ወደ ፊት የሚመለከተው ወገን፤ ወደ ኋላ የሚመለከተውን ወገን አቸንፎ ይወጣል። ለትክክለኛ ፍትኅ፣ ለእውነት፣ ለእኩልነትና ለአንድነት የቆመ ወገን ያቸንፋል። ይህ በያንዳንዱ ዉጊያ የተመዘገበ አይደለም፤ በማጠቃለያው ጦርነት እንጂ። በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ያለው ትግል፤ ወደ ፊት በሚመለከተው የአንድነት ክፍሉና ወደ ኋላ በሚመለከተው ሀገር በታኙ መካከል ነው። ለሥልጣናቸው ሲሉ ሀገሪቱን ለመበታተን የሚያቀነቅኑት ይቸነፋሉ። የወደ ፊቱ የአንድነት ነው።
ታህሣሥ ፲ ቀን ፳ ፻ ፭ ዓመተ ምህረት
Leave a Reply