አቶ ዠ ለዩናይትድ ኔሽንስ ዋና ጸሃፊነት ውድድር ተመዝግበው ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው። ፍላየር እያደሉ ነው። ፍላየሩ ላይ የዌብ ሳይት፣ ኢሜይል አድራሻ፣ እንዲሁም የትምህርትና የሥራ ልምዳቸው ተደርድሯል። የዌብ ሳይታቸው www.z.com ይነበባል። የሥራ ልምዳቸውና የትምህርት ደረጃቸው ደግሞ እንደሚከተለው፣
የሥራ ልምድ፣
በዩናይትድ ኔሽንስ ኢትዮጵያን ወክሎ መቀመጥ ከሃምሌ 2007 ጀምሮ
የባህል ሚኒስቴር፣ ሚኒስትር ዴኤታ ከመጋቢት 2007 እስከ ሃምሌ 2007
የማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ የቅርንጫፍ ዳሬክተር ከግንቦት 2007 እስከ ሃምሌ 2007
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል ከምርጫ 2005 ጀምሮ
የኢሃዲግ ፍቅር ቴአትር ቤት አርቲስቲክ ዳሬክተር ከየካቲት 2007 እስከ መጋቢት 2007
አዎን፣ አቶ ዠ እንደሮኬት ተተኩሰው ሚኒስቴር ዴኤታ ደርሰዋል።
የትምህርት ደረጃ፣
ዶክትሬት (PhD)
ከ Fastlane University 2007
አዎን፣ አቶ ዠ እንዴት እንደሆነ ሳያውቁት ዶክትሬት ተጭኖባቸዋል። አብሮአቸው የህዝብ ምክርቤት የሚቀመጥ የሌላ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነው ሃሳቡን ያቀረበላቸው። “በመላላክ ተማሩ” በማለት። “ጊዜ አይወስድም እኮ!” ጨመረበት። በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ዶክትሬቱ ተላከላቸው፣ በፖስታ። ከዚያም ባማረ ፍሬም ተደርጎ ቢሮአቸው ውስጥ ግድግዳ ላይ ተሰቀለ። አቶ ዠ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያን፣ የባችለርና የማስተርስ ድግሪ ፕሮግራምን “ትሪፕል” መተው፣ ዶክትሬት ተጫነባቸው። አልከበዳቸውም። ወረቀቱ ቢሮአቸው ባጌጠ ፍሬም ተከንፎ የተሰቀለ ሰሞን ቀና ብለው እንኳን አይተውት አያቁም። ያፈሩት ይመሥል። የኋላ የኋላ ግን በድፍረትና በ“የኔ ነው” ባይነት በኩራት ይመለከቱታል። አንዳንድ “ቀናተኞች” ግን የኼ ድግሪ “የወፍጮ ድግሪ ነው፣ ውሃ አያነሳም!” በማለት ቢተችዋቸውም ይመኩበታል። “የወፍጮ ድግሪ፣ የሙቀጫ ድግሪ፣ ድግሪ ድግሪ ነው” ይላሉ ለራሳቸው፣ “ዶ/ር” ዠ።
******************************
አቶ ዠ በዩናይትድ ኔሽንስ ኢትዮጵያን ወክለው መቀመጥ ከጀመሩ 47 ቀናት እንዳለፉ ዩናይትድ ኔሽንስ አዲስ ዋና ጸሃፊ የሚመርጥበት ጊዜ ደረሰ። በነዚህ 47 ቀናት አቶ ዠ “seasoned diplomat” ሆንኩ ብለው አሰቡ። “Seasoned Diplomat” የሚለውን ሃረግ የሰሙት ጎናቸው ከሚቀመጠው የዩጋንዳ ተወካይ ነው። Seasoned Diplomat መሆናቸውን ለሚጠየቁት ጥያቄ ሁሉ ቀጥተኛ መልስ ባለመሥጠት አረጋገጡ። ለምሳሌ፣
“የሰሜን ኮርያን የኒኩልየር መሳሪያ ፕሮግራምና ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ካላት ትብብር ጋር በማነጻጸር እንዴት ይመለከቱታል?” ተብለው ሲጠየቁ፣
መልሳቸው፣
“In fact ነገሩ ሎድድ ነው። It is complicated፣ የተወሳሰበ ነው።” ብለው ይጀምሩና ኢህአዲግ ልማታዊ መንግሥት ሥለመሆኑ ይነግሩሃል።
“ታዲያ ልማታዊ ከሆናችሁ ለምን ህዝባችሁን በተደጋጋሚ ረሃብ ያጠቃዋል?” ብለህ ተከታታይ ጥያቄ ጣል ብታደርግ
“In fact ነገሩ የተወሳሰበ ነው። ትኩረታችን የብረታብረት፣ የስኳር እንዱስትሪና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ነው” ይሉሃል።
“ቤት መሥራት ጥሩ ነው። ታዲያ በብዛት ቤት የምትሰሩ ከሆነ ለምንድነው ታዲያ የቤት ችግር በጣም አንገብጋቢ የሆነው? የቤት ኪራይ ዋጋስ ጣራ ሰንጥቆ ሰማይ የደረሰው?” ብለህ መጠየቅ አትፈልግም። ምክንያቱም መልሱ “complicated፣ የተወሳሰበ” ይሆናልና። ስለዚህ ቀለል ያለ ጥያቄ ነው ብለህ አስበህ፣ ቀጥተኛ መልስ አገኛለሁ ብለህ አስበህ፣
“ቁርስዎን ምን በሉ?” ብለህ ብትጠይቃቸው መልሳቸው የሚጀምረው፣
“In fact ነገሩ ሎድድ ነው. . .” በሚለው ሃረግ ነው። Seasoned Diplomat!
****************************
አቶ ዠ “Seasoned Diplomat” ሆንኩ ብለው አሰበው አላቆሙም። ለዩናይትድ ኔሽንስ ዋና ጸሃፊነት እመጥናለሁ ብለው አሰቡኛ ለመወዳደር ወሰኑ። እና አቶ ዠ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን በዕረፍት ሰዓት ኒው ዮርክ ባለው የዩናይትድ ኔሽንስ ህንጻ በየቢሮውና በየኮሪደሩ እየተዘዋወሩ ውስጥ ውስጡን ጀምረዋል። የአፍሪካ ሃገራት ተወካዮች ጋ እየተዘዋወሩ ሃሳባቸውንና ምኞታቸውን በመግለጽ ድጋፍ እንዲለግሱዋቸው ተማጽነዋል። የዩጋንዳውን ተወካይ ኮሪደር ላይ አግኝተው ሃሳባቸውን ሲያዋዩት “of course Mr. Z (ዚ)” ብሎ ሳቀ። ባቅራቢያው ያልፍ የነበረው የዛምቢያው ተወካይም “whatever he does, I will too, እሱ የሚያደርገውን እኔም አደርጋለሁ” አለ፣ የድጋፍ ሳቅ እየሳቀ፣ ምን እንደሆነ፣ ምን እንደተነጋገሩ ሳይሰማ።
****************************
አለፍ ብሎ ደግሞ የአረብ ሃገራት ተወካዮች ተሰብስበው ቆመው እየጮሁ ያወጋሉ። ይደግፉኛል ብለው ባይተማመኑም “ግፋ ቢል እምቢ ነው። ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” አሉ አቶ ዠ ለራሳቸው። “ካለመጠየቅም የዩኤን ጸሃፊነት ይቀራል” ብለው ፍላየራቸውን ይዘው ተጠጓቸውና ማስረዳት ጀመሩ።
“how do you say your name? ስሞትን በትክክል እንዴት ያነቡታል?“ሲል አንዱ ጠየቀ። ዠ ማለት ከብዶታል።
“ዠ” አሉ አቶ ዠ።
“ጀ” አለ አረቡ። ‘የለም ዠ ነው’ ሲሉ አሰቡ አቶ ዠ። “አረቦች ለካ ዠ ማለት አይችሉም። ዠበናችን ጀበና፣ ዣንጥላችን ጃንጥላ የሆኑት በነሱ ምክንያት ነው፣ አረብኛ ወደኛ ሃገር በመሰደዱ ነው” ብሎ አንዱ ባህል ሚኒስቴር ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርቦ የሰሙት ትዝ አላቸው።
“you can call me Z፣ ዘ በለኝ።” አሉ ፈገግ ብለው።
“Z like Zebra. . .?” አለ አረቡ እየሳቀ። ”ምናባቱ እንደ ሜዳ አሀያ ያዥጎረጉረኛል?“ሲሉ አሰቡ አቶ ዠ በሆዳቸው። ሆኖም ግን የሆድን በሆድ አድርጎ መስማማት ሳይሻል አይቀርም. . . “ካለመስማማትም ደጃዝማችነት ይቀራል” ተብሎ ይሆን?
“or Z like Zero” አለ ሌላው አረብ።
“Z like Zoro” መለሱ አቶ ዠ. . . እና ሳቁ። የላቲን አሜሪካውን ዝነኛ፣ ለድሆች የቆመ ሽፍታ በማስታወስ።
“Z like Zoro” ሁሉም ተቀባበሉና ሳቁ። የሳቸውን መመረጥ እንደሚደግፉ ሁሉም ተስማሙ። አቶ ዠ ተሰናብተው ሄዱ። አለፍ ካማለታቸው፣
“መጁኑን” የሚል ቃልና ሳቅ ሰሙ። ለእሳቸው የተወረወረ ቃል ይሆን? ቃል አልተነፈሱም። ”ዝም ካለማለትም ደጃዝማችነት ይቀራል“ ተብሎ ይሆን?
*****************************
ከዚያ ቀጥሎ ከምሥራቅ አውሮፓ የመጡ ተወካዮች አንድ ቦታ ተሰብስበው አዩና ቀርበው ሃሳባቸውን አሥረዱ። ሥማቸውን ተናገሩ። ገረማቸው። በትክክል ሥማቸውን ሚሮኮ የሚባለው የክሮኤሽያ ተወካይ አሳምሮ ጠራው።
“ዠ አይደለም? ምን ችግር አለው፣ ቀላል ነው። እኛም እኮ ዠ የሚል ፊደል አለን።” አቶ ዠ ተደሰቱ። ከምሥራቅ አውሮፓ የመጡት ተወካዮች የሳቸውን መመረጥ እንደግፋለንም አንደግፍምም አላሉም። መልካም ዕድል ብቻ ተመኙላቸው።
*****************************
አቶ ዠ ይህንን ቅስቀሳ አካሄደው ከጨረሱ በኋላ ወደ ከተማ አቀኑ። አቶ ዠ ለዩናይትድ ኔሽንስ ዋና ጸሃፊነት ያስፈልጋል ብለው ያሰቡትን አይነት አለባበስ ለሟሟላት ወደ ልብስ መገብየት አቀኑ። እናም አንድ ትልቅ የገበያ አዳራሽ ገብተው ከሱቅ ወደሱቅ እየተዘዋወሩ ልብስ ማማረጥ ያዙ. . .
“አንተ ሌባ” የሚል ድምጽ ሲሰሙ ኮት እየለኩ ነበር።
“አንተን ነው፣ አንተ አጭበርባሪ” ደገመው ሰውየው። ሌሎችም ተከተሉት።
አቶ ዠ ሽምቅቅ ብለው ከኮቱ ውስጥ ሙልጭ ብለው ወለቁ። የሚገቡበት ጠፋቸው። ለካስ የሳቸውን ለዩናይትድ ኔሽንስ ዋናጸሃፊነት መወዳደር ሰምተው ውድድራቸውን የሚቃወሙ ነበሩ።
“ገና በህግ ትጠየቃለሁ፣ አንተ አጭበርባሪ መፈከር ጸሃፊ! ሥራ መሥራት መፈክር መጻፍ መሰለህ? ‘ሙያ በልብ ነው። በመፈክር አይደለም!’ የሚሉ ሰዎች ሥልጣን ሲይዙ እንዳንተ ያለው አጭበርባሪ በወሬ አዳሪ በህግ ይጠየቃል”
****************************
አቶ ዠ ተወራጩ። ላብ በላብ ሆነዋል።
“ተነሳ እንጂ! ቡና ፈልቷል፣ ቁርስም ተሰርቷል” ባለቤታቸው ወ/ሮ ዘ ነበሩ።
“ምነው ላብ በላብ ሆንክ? ህልም፣ ራዕይ ነው?”
“ቅ’ዠ’ት ነው . . . ተይኝ ባክሽ ቅ’ዠ’ት ነው. . .” አቶ ዠ እየተጎተቱ ካልጋቸው ውስጥ ወጡ።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply