“አንቺ እማማ ኢትዮጵያ አንቺ እናት ዓለም”
ሎሬትሽ እያቆላመጠ ይነግርሽ እንደነበር በቀለም፤
እወቂበት ከእንግዲህ አብጂለት ፍቱን መላ፣
የሚሞትልሽ እንጂ የሚገልሽ ላይበላ፤
ህዋሳትሽ ይንቀሳቀስ ሰሜን-ደቡብ ምዕራብ-ምስራቅ፣
የአለላ ተምሳሌቱ የሕዝቦችሽ ህብረት ይድመቅ፤
ብድግ በይ ተራመጂ በእንፉቅቅ መዳኽሽ ያብቃ፣
የውብ ህይወት አዲስ ምዕራፍ በግዛትሽ ይገንባ!
እናት አገር ባለታሪክ ተነሽ ቤትሽን አጽጂ፣
የተዝረከረከውን በፕሮፓጋንዳ ፈንጂ፣
በተከፈተው ጉድጓድ ይግባ ጠራርገሽ አስወግጂ።
ዳግም እንዳትረቺም ባባይ-ጠንቋይ ጋጋታ፣
እጆችሽን ከምር ዘርጊ ወደ ፈጠረሽ ጌታ፣
አምላክሽ ካንቺው ነውና የእስላም የክርስቲያኑ፣
ፍጠኚ ታሪክ ይከወን ሳያልፍብሽ ዘመኑ።
‘ዳዊቶችሽ’ በጠጠር ‘ጎልያድን‘ ሲፋለሙ፣
የዝናሽን ውድ ዕሴት ሰንደቅሽን ሲሸከሙ፣
አግዢያቸው በተፈጥሮሽ፣ እስኪ ለእኩይ ማድላት ያብቃ፣
ለዘላለም-ዓለም ክብርሽ እንዲሆኑ ዋስ ጠበቃ፤
ለምስኪኖች ዜጎችሽ አንቺን ብለው ካንቺው ላሉት፣
ለክብራቸው፣ ለማዕረግሽ.. በደማቸው ለሚዋጁት፣
እስኪ መላ! እናት ሀገር! ተዓምር ስሪ አምላክ ይርዳሽ፣
ጸበል ይረጭ መላው ምድርሽ የድል ጽዋ ያጎናጽፍሽ!
እንደ ጨው ዘር ተበትነው በምድረ-ዓለም የባከኑ፣
አሉሽና ውድ ልጆች ባንቺው ፍቅር የተካኑ፣
እቅፍሽን ዘርግተሽ ሰብስቢያቸው ባንድ ላይ፣
ከወንዛቸው ቀላቅያቸው ላገር ዕድገት ላገር ሲሣይ።
ባዲስ ራዕይ መልካም ውጥን በፋኖስሽ ብርሃን ፈለግ፣
ጀግኖችሽን ከየሥፍራው አድነሽ በመፈለግ፣
አሰማሪ ለነጻነት፣… ለልጆችሽ ልዕልና፣
ላንድነትሽ ህያው ክብር ለትውልድሽ ህልውና።
እናት አገር የሁላችን
ዞሮ መግቢያ ቤታችን፣
እኩልነት፣ ፍትህ፣ ርትዕ.. የተፈጥሮ መብቶች አውራ፣
የነጻነት ብርሃን ቀንዲል በግዛትሽ ደምቆ ያብራ!
በልጆችሽ አኩሪ ገድል ህልውናሽ ተጠብቆ፣
ለዘልዓለም ዓለም ኑሪ! ህያው ክብርሽ ባለም ደምቆ።
Leave a Reply