
ከሠላሳ ሰባት ዓመት በፊት የተካሄደው የሞስኮ ኦሊምፒክ ሲነሣ ቀድሞ የሚመጣው የሚወሳው ረዥም ርቀት ሯጩ ምሩፅ ይፍጠር ነው፡፡ የድል ቁርጠኝነት የተሞላበት አሯሯጡ የመላው ዓለምን ምናብ ሰንጎ መያዙ አይረሳም፡፡
በሞስኮ ኦሊምፒክ በሁለቱ ርቀቶች በ5,000 ሜተርና በ10,000 ሜትር ለተቀናቃኞቹ ዕድል ሳይሰጥ ተፈትልኮ የሮጠበትና ያሸነፈበት መንገድ ‹‹ይፍጠር ዘ ሺፍተር›› (ማርሽ ለዋጩ ምሩፅ – አካለ ማርሹ ምሩፅ) የተባለበትን ዳግም ያረጋገጠበት ነበር፡፡ በሞስኮ ድሉ ከተመሰጡና አርአያ ከሆነላቸው መካከል በወቅቱ የሰባት ዓመት ልጅ የነበረው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ውድድሩን በትራንዚተር ሬዲዮ ጆሮውን ደቅኖ ሲከታተል አንድ ቀን የርሱን ዱካ እንደሚከተል አልሞ ነበር፡፡
ኢትዮጵያን የኦሊምፒክ ብርሃን ከዘጠና ሦስት ዓመት በፊት የዳሰሰው በፓሪስ ኦሊምፒክ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንንና የክብር ተከታዮቻቸው በታደሙበት ቢሆንም፣ መወዳደር የጀመረችው ግን ከስድሳ ዓመት በፊት ሜልቦርን ላይ ነበር፡፡ የኦሊምፒክ የድል ጮራ የበራውም በሮም ኦሊምፒክ አበበ ቢቂላ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ ነው፡፡ ከአበበ ቢቂላ ጋር ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ የኢትዮጵያ የምንጊዜም የረዥም ርቀት ዝነኞች ሆነው ተከስተዋል፡፡
ፋና ወጊው አበበ ቢቂላ የኦሊምፒክ ማራቶንን በ1952 ዓ.ም. (1960) እና 1957 ዓ.ም. (1964) ኦሊምፒኮች ድል ሲመታ፣ ምሩፅ ግን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ ያሰጠውን አስደናቂ ድርብ ድል በሞስኮ በ1972 ዓ.ም. (1980) ተቀዳጅቷል፡፡
የሞስኮ ኦሊምፒክ የምሩፅ አስደናቂው ድርብ ድል እስከሚከሰትበት ድረስ የሚዲያ መድረኩን ተቆጣጥረውት የነበሩት ሁለት እንግሊዛውያን የ1,500 ሜትርና የ800 ሜትር ባለድሎቹ ሰባስቲያን ኮ እና ስቲቭ ኦቬት ነበሩ፡፡ በአስደናቂ አሯሯጡና በልዩ ችሎታው ማርሽ ቀይሮ ያሳየው ብልጫ ሩጫውን ሕይወት ሰጠው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 1972 ዓ.ም. በተካሄደው የ10 ሺሕ ፍጻሜ ከምሩፅ ይፍጠር ጋር አብረው የተሰለፉ መሐመድ ከድርና ቶሎሳ ቆቱ በሁለት ኦሊምፒክ የበላይ የነበረችው ፊንላንድ በሻምፒዮኑ ላሲ ሸረን መሪነት ካርሎ ማኒንካን ይዞ የታየው የ25 ዙር ታክቲካዊ ትግል የተቋጨው፣ ውድድሩ ሊያበቃ 300 ሜትር ሲቀረው ምልዓተ ኃይሉን ተጠቅሞ ባፈተለከው ምሩፅ ይፍጠር ድል አድራጊነት ነበር፡፡ ምሩፅ የመጨረሻውን 200 ሜትር በ26.8 ሰከንድ በመሮጥ መስመሩን በጥሶ ያለፈው በ27 ደቂቃ 42.69 ሰከንድ ነበር፡፡ ማኒንካ ብር፣ መሐመድ ነሐስ ሲያገኙ ቶሎሳና ቬረን ተከታዮቹን ቦታ ይዘው ፈጽመዋል፡፡
ይህ በሁለቱ በኢትዮጵያና በፊንላንድ መካከል የነበረውን ፉክክር ለማየት በወቅቱ የፊንላንድ ፕሬዚዳንት የነበሩት በስፍራው መገኘታቸው ይታወሳል፡፡ በ5,000 ሜትርም ምሩፅ የመጨረሻውን 200 ሜትር በ27.2 ሰከንድ በማለፍ ድሉን ያጣጣመው በ13፡20.91 ሲሆን፣ ያስከተላቸውም ታንዛኒያውን ሱሌይማን ንያምቡና ፊንላንዳዊውን ማኒካን ነበር፡፡
ምሩፅ ስለ ሞስኮ ድሉ ከ12 ዓመት በፊት ላናገረው የኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ድረ ገጽ እንዳወጋው፣ ያኔ ከአሠልጣኞቻቸው ጋር የተነጋገሩት ርሱም የተለማመደው በሁለቱም ርቀቶች 300 ሜትር ሲቀር አፈትልኮ ለመሮጥ ነበር፡፡ ‹‹አምስት ዙር እንደቀረው የተቀናቃኞቼን እንቅስቃሴና ትርታ ማዳመጥ ጀመርሁ፤ ውጥረት የሚሰፍነው ደወሉ ሲደወል በመሆኑና አቅማቸውን አሰባስበው ከመነሳታቸው በፊት 300 ሜትር ሲቀር ማምለጥ እንዳለብኝ ወሰንሁ፤ ድሉንም ጨበጥኩ፡፡››
የምሩፅ ይፍጠር የሩጫ ጉዞ
መስከረም 1961 ዓ.ም. አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴን የያዘው የሜክሲኮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ተሳታፊ አትሌቶች የመጨረሻ ጉዟቸውን ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ከማድረጋቸው በፊት ለልምምድ ያረፉት አስመራ ከተማ ነበር፡፡ በአስመራ ንግሥተ ሳባ ስታዲየም ልምምድ ሲያደርጉ የተመለከተው የከተማዋ ነዋሪ ምሩፅ ይፍጠር ለወደፊት ሕይወቱ በር ከፋች አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ በልምምድ ሩጫ ውድድርም ከነማሞ ወልዴ ጋር ተወዳድሮ መጨረሻ ቢወጣም አሯሯጡንና አቅሙን ያስተዋሉት አሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ በአየር ኃይል ስፖርት መምሪያ እንዲያዝና ልምምድ እንዲያደርግ አደረጉ፡፡ ቅጥሩንም ፈጸመ፡፡ ለ20 ዓመታት በአየር ኃይል ሲያገለግል እስከ ሻምበልነት ደርሷል፡፡
በአዲስ አበባው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም፣ ንብ የሚባለውን የአየር ኃይል ስፖርት ክለብን እየወከለ በብሔራዊ ሻምፒዮናና በጦር ኃይሎች ውድድር ውጤታማ መሆን የጀመረው ምሩፅ፣ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል ውድድሩ በ1962 ዓ.ም. በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታንዛኒያ ውስጥ በ1,500 ሜትር ከኦሊምፒክ ባለወርቁ ኬፕቾግ ኬይኖ ጋር ተወዳድሮ ሦስተኛ የወጣበት ውድድሩ ነበር፡፡
በ1963 ዓ.ም. በአሜሪካ በተካሄደው የአፍሮ አሜሪካን ውድድር በ10 ሺሕ ወርቅ፣ በ5 ሺሕ ሜትር ብር ሜዳሊያ በማግኘት ድሉን አሐዱ ብሎ ጀምሯል፡፡
የመጀመሪያው የኦሊምፒክ መድረኩ በሆነው 20ኛው ኦሊምፒያድ በሙኒክ ሲካሄድ ምሩፅ በ5 ሺሕና በ10 ሺሕ ሜትር ለመወዳደር ነበር ወደ ሥፍራው ያመራው፡፡ በ10 ሺሕ ሜትር በማጣሪያው አንደኛ ወጥቶ በፍጻሜው ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያን አግኝቷል፡፡ በ5 ሺሕ ሜትር ማጣሪያ ‹‹አሠልጣኞቹ በፈጠሩት ችግር›› ምክንያት በጊዜ ባለመድረሱ የተነሳ ሳይወዳደር በመቅረቱ ሌላ ሜዳሊያ የማግኘት ዕድሉ ተጨናግፎበታል፡፡
በ1965 ዓ.ም. በሌጎስ (ናይጄሪያ) በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በ10 ሺሕ ወርቅ በ5 ሺሕ ብር አሸንፏል፡፡ በዚያው ዓመት ከሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ከተውጣጡት መካከል የኢትዮጵያ ስፖርት ኮከብ አትሌት ተብሎ የተመረጠው ምሩፅ፣ በ1968 ዓ.ም. በሞንትሪያል (ካናዳ) በተካሄደው 21ኛው ኦሊምፒያድ ያለ ጥርጥር በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ሁለት ወርቅ ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስፖርታዊ ግንኙነት የነበራት ኒውዚላንድ ከሞንትሪያል ኦሊምፒክ ባለመታገዷ ምክንያት አፍሪካውያን አንካፈልም በማለታቸው ሳይወዳደር ተመልሷል፡፡
በሙኒክ ኦሊምፒክ ምሩፅን ያሸነፈው ፊንላንዳዊው ላሲ ቨረን ዳግመኛ ድሉን ምሩፅ በሌለበት አጣጣመ፡፡
ምሩፅ የኦሊምፒክ ወርቅ ሕልሙን ያሳካው በ1972 ዓ.ም. ሞስኮ ባስተናገደችው 22ኛ ኦሊምፒያድ ሲሆን በሁለቱም ርቀቶች ወርቁን ያጠለቀው ፊንላንዳዊውን ላሲ ቨረንን ድል በመምታት ነበር፡፡
በሞስኮ ኦሊምፒክ ሲሮጥ ዕድሜው የገፋው (በፓስፖርት ዕድሜው 36 ዓመቱ በተለያዩ ሚዲያዎች እስከ 42 የሚያደርሱት) ምሩፅ፣ በ1969 ዓ.ም. እና በ1971 ዓ.ም. በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫዎች አፍሪካን በመወከል አራት ወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ ተወዳዳሪዎቹን በቀደመበት ርቀት ያህል በሞስኮ አልደገመውም፡፡ ዕድሜው ገፍቷልና፡፡
በሁለቱ የዓለም ዋንጫዎች በ5,000 ሜትር ውድድሩ ሊያበቃ 500 ሜትር ሲቀር፣ በ10 ሺሕ 600 ሜትር ሲቀር ነበር ማርሽ ቀይሮ በማፈትለክ ያሸነፈው፡፡ በሞስኮ ኦሊምፒክ ግን በሁለቱ ርቀቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው 200 ሜትርና 300 ሜትር ሲቀረው ነበር፣ ማርሽ ቀይሮ ድል የመታው፡፡ ምሩፅ በ1971 ዓ.ም. በዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ ለመካፈል የበቃው የመጀመሪያው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዳካር (ሴኔጋል) ሲካሄድ ሁለት ወርቅ (በ5 ሺሕና 10 ሺሕ) በማግኘቱ ነበር፡፡
ምሩፅ 1971 ዓ.ም. ወርቃማ ዓመቱ ነበር፡፡ እጅግ የገነነበት ታላቅ ክብርንም የተቀዳጀበት፡፡ በዚያው ዓመት በቼኮዝሎቫኪያ በተዘጋጀው የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ዘጠኝ አትሌቶች ሲመረጡ አንዱ ምሩፅ ሲሆን፣ ‹‹የኮከቦች ኮከብ›› ተብሎ መመረጡ በተዘጋጀው የተሸላሚዎች መድረክ ራሱ ከመሀል በከፍታ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ የወርቅ ጫማም ተሸላሚ ነበር፡፡ ምሩፅ ድርብ ድሎቹን በዳካር፣ በሞስኮና ሞንትሪያል በተደረጉ አህጉራዊና ዓለማዊ ውድድሮች ስድስት ወርቅ ይዞ አዲስ አበባ በደረሰ ጊዜ ጋዜጠኛ ኃይሉ ልመንህ እንዲህ ገጥሞለት ነበር፡፡
“አብዮቱ ፈካ አበባው አማረ
ያለም ሻምፒዮና በምሩፅ ሠመረ፡፡
ሞስኮ ላይ ቀደመ ዳካር ላይ ድል መታ
ሞንትሪያል ደገመ እንዳመሉ ረታ
ዓለም ይሁን አለ ድሉን ተቀበለ
እየደጋገመ ምሩፅ ምሩፅ አለ፡፡”
የመጀመሪያ ዓለም ዋንጫ በዱዞልዶርፍ (ምዕራብ ጀርመን) ሲካሄድ አፍሪካን ወክሎ ለመሳተፍ የበቃው የቅርብ ተቀናቃኙን ኬንያዊውን የዓለም ሪከርድ ባለቤት ሔንሪ ሮኖን በመርታት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት (በወቅቱ ኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ) ሻምበል ምሩፅ በቅድመ ሞስኮ ኦሊምፒክ ባገኛቸው አህጉራዊና ኢንተርናሽናል ድሎች ኢትዮጵያን ለታላቅ ግርማ ሞገስ በማብቃት ለፈጸመው አኩሪ ተግባር አምስተኛው የአብዮት በዓል ሲከበር፣ ‹‹የጥቁር ዓባይ ኒሻን››ን ከርዕሰ ብሔሩ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እጅ መቀበሉ ይታወሳል፡፡
በ1,500 ሜትር መወዳደር የጀመረው ምሩፅ 5 ሺሕና 10 ሺሕ መደበኛ ውድድሮቹ ቢሆኑም በጎዳና ላይ ሩጫዎችም ተደጋጋሚ ድሎች ማግኘቱ አይሳትም፡፡
በተለይ በተከታታይ ዓመታት ድል የተጎናፀፈበት የፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን ውድድር ለዓለም ክብረ ወሰን የበቃበት ነበር፡፡ ጥር 29 ቀን 1969 ዓ.ም. በፖርቶ ሪኮ ኮዓሞ የ21 ኪሎ ሜትር (ግማሽ ማራቶን) ውድድር ምሩፅና መሐመድ ከድር ተከታትለው ሲያሸንፉ ምሩፅ የገባበት 1 ሰዓት 02 ደቂቃ 57 ሰከንድ ያለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡
በ1972 በፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን አሸንፎ እንደተመለሰ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም “የማተኩረው በሞስኮ ኦሊምፒክ ስለሆነ በፖርቶ ሪኮው ድሌ አልኮራም” ማለቱ አይዘነጋም፡፡
በሞስኮ ኦሊምፒክ ለሦስተኛ ጊዜ ድሉን ለማጣጣም ቋምጦ የነበረው ፊንላንዳዊ ላሲ ቬረን በሞስኮ አየሩ ጥሩ ከሆነ እንደሚያሸንፍ መናገሩን ተከትሎ ምሩፅ በሰጠው አፀፋ “ሐሩርም ይሁን በረዶ እኔ ከማሸነፍ የሚገታኝ አንዳች ኃይል የለም” ማለቱ ልበ ሙሉነቱን ያሳየበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ከሞስኮ ኦሊምፒክ ድሉ በኋላ ጥንታዊ ኦሊምፒክ በተመሠረተባት ግሪክ ለኦሊምፒያዊ ሽልማት ከተመረጡ አምስት አትሌቶች ቀዳሚ ሆኖ የኦሊምፒክ ሎሬት አክሊልን ከርዕሰ ብሔሩ የተቀበለው ምሩፅ ይፍጠር ነበር፡፡
በዓለም ገናና ለሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ለሞሮኮው ሰዒድ አዊታና ለሌሎችም አርአያ የሆነው ምሩፅ፣ ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር በ1973 ዓ.ም. በምዕራብ ጀርመን ባደን ባደን ጉባኤውን ሲያካሂድ የዓለም አትሌቶችን ከወከሉ አትሌቶች አንዱ ርሱ ነበር፡፡ ሌላኛው ተወካይ እንግሊዛዊው ያሁኑ የኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት የያኔው የሞስኮ ኦሊምፒክ የ1,500 ሜትር ባለድል ሰባስቲያን ኮ ነበር፡፡
ጀንበሯ ስትጠልቅ
ከሁለት አሠርታት ወዲህ በአብዛኛው መቀመጫውን በካናዳ አድርጎ የነበረው ምሩፅ፣ ከዓመት ወዲህ ባደረበት ጽኑ የሳምባ ሕመም ምክንያት ሕክምናውን እየተከታተለ ቢቆይም፣ ከሐሙስ ታኅሣስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ወዲህ መሻገር አልቻለም፡፡ በቶሮንቶ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ሕይወቱ ማለፉ በካናዳ ለቤተሰቡ ቅርብ የሆነው አድናቂና ወዳጁ አቶ ታምሩ ተስፋዬ በስልክ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ዜና ዕረፍቱን ተከትሎ ቤተሰቡ በካናዳ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም ጥልቅ ሐዘናቸውን ከገለጹት ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር መገናኘቱንና አስክሬኑን በክብር ወደ አገሩ ለመመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
“ምሩፅ አገሬ ወስዳችሁ ነው የምትቀብሩኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታዬ ነው” ይል እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ታምሩ፣ በገና በዓል ምክንያት መሥሪያ ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ሒደቱን ማፋጠን ባለመቻሉ ሰነዶቹ ተሟልተው እንዳበቁ በቀናት ውስጥ አስክሬኑ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓጓዝ ተናግረዋል፡፡
የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር በክብር ለማስፈጸም በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተሰየመ ኮሚቴ መኖሩንና የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሪዎች ኃይሌ ገብረሥላሴና ገብረ እግዚአብሔር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በአዲስ አበባ የሚገኘው ልጁ ቢንያም ምሩፅ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስክሬኑን ለማጓጓዝ መጠየቁን ያወሳው ቢንያም፣ ለምሩፅ የጀግና ሽኝት እንደሚደረግለት እምነቱ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ያ ስመ ገናና “ይፍጠር ዘ ሺፍተር”፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ከካናዳ ሆኖ በባዕድ መንግሥት እየታገዘ በነበረበት ሰዓት ምሩፅ፣ እጅግ ውድና በገንዘብ የማይተመኑት ሽልማቶቹ በጨረታ ተሸጠው ለሕክምና እንዲውሉ ሲጠየቅ “ሽልማቶቼ የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፤ ለሽያጭ አይታሰቡም” ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ከአባቱ አቶ ይፍጠር ተክለሃይማትና ከእናቱ ወ/ሮ ለተገብርኤል ገብረአረጋዊ ጥቅምት 5 ቀን 1937 ዓ.ም. በትግራይ፣ ዓዲግራት የተወለደውና በ72 ዓመቱ ያረፈው ምሩፅ ይፍጠር የሰባት ልጆች አባት ነበር፡፡
የምሩፅ ይፍጠር ዓበይት ድሎች | |||
ኢትዮጵያን በመወከል | |||
ሜዳሊያ | እ.ኤ.አ. | ኦሊምፒክ ጨዋታዎች | |
ወርቅ | 1980 | ሞስኮ | 5,000 ሜትር |
ወርቅ | 1980 | ሞስኮ | 10,000 ሜትር |
ነሐሰ | 1972 | ሙኒክ | 10,000 ሜትር |
መላ አፍሪካ ጨዋታዎች | |||
ወርቅ | 1973 | ሌጎስ | 10,000 ሜትር |
ብር | 1973 | ሌጎስ | 5,000 ሜትር |
አፍሪካን በመወከል | |||
የአይኤኤፍ ዓለም ዋንጫ (የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ) | |||
ወርቅ | 1977 | ዱዘልዶርፍ | 5,000 ሜትር |
ወርቅ | 1977 | ዱዘልዶርፍ | 10,000 ሜትር |
ወርቅ | 1979 | ሞንትሪያል | 5,000 ሜትር |
ወርቅ | 1979 | ሞንትሪያል | 10,000 ሜትር |
Leave a Reply