
በአለፉት ወራት የኦሮሞ ወጣች የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በሚል ፈሊጥ በአካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን በማፈናቀል ከትውልድ ትውልድ የቆየውን የተረጋጋ ኑሯቸውን የሚያዛባ ፕላን በመቃወም ያነሱት ጥያቄ ከወጣቶቹ አልፎ ራሱን ገበሬውን የሚያካትት፣ ከመሬት ጥያቄ አልፎ የዴሞክራሲን ጥያቄ ወደሚያነሳና ድርጅታችን በሙሉ ልብ ወደሚደግፈው ሰፊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ሲቀየር እየታዘብን ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በወልቃይት ጠገዴና በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች ህዝብ የመብትና የህልውና መከበርን ጥያቄዎች እያነሳ ባካሄዳቸው ትግሎች አገዛዙ ተወጥሮ ተይዟል፡፡ ይህንን ይፋና ሰፊ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቋቋም የወያኔ /ኢህአዴግ አመራር በተለመደው የጅምላ አፈናና ሽብር ተሰማርቶ በመቶ የሚቆጠሩ ንጹህ ዜጎችን ህይወት ቀስፏል፡፡ በሽህ የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎችን ለእስር ዳርጓል፡፡ ይህ አፈናና ግፍ ሊገታው ያልቻለውን ህዝባዊ ትግል ለማፈን ደግሞ ለሃገራችን ችግሮች መንስኤ ያላቸውን የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙሰኝነትን በማውሳት በነዚህ መስኮች በኢህአዴግ በራሱ ላይ የሚንጸባረቁትን ችግሮች ጠቅሶ ከነዚህ አንጻር የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣ ለነዚህም ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ከህዝቡ ጋር ለመወያየት አቅጃለሁ ብሎ ይህንን ሂደት ለመጀመር ቅድሚያ ለሃገሪቱ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች በመስጠት እነሱ ጋር ውይይት መጀመሩ በሰፊው ተወስቷል፡፡
የሃገራችን ውስብስብ ችግሮች ያገቡናል የሚሉ ሃይሎች በሙሉ በሚሳተፉባቸው ውይይቶች ይፈቱ የሚለው ሃሳብ በእኛም ሆነ በማንም ዴሞክራት የሚደገፍ ነባር አቋም በመሆኑ በመርህ ደረጃ በዚህ ጉዳይ ላይ ተቃውሞ አይኖረንም፡፡ ግን ደግሞ ይህ አቋማችን ሃቀኛና ፍሬያማ ወይይት ምን መሆን አለበት ከሚለው ጥያቄ ተነስተን ከዚህ አንጻር የኢህአዴግን ሂደት ከመመርመርና ግድፈቶቹን ከመጠቆም፣ ከዚያም በዚህ ጉዳይ መወሰድ የሚገባቸውን አርምጃዎች ለህዝባችን አቅርበን ለነሱ ከመታገል የሚገታን አይደለም፡፡
የኢህአዴግ መንግስት የሃገሪቱን ችግሮች በውይይት እፈታለሁ በማለት የተለያዩ ሃይሎችን ሲጋብዝ ከሁሉ መጀመሪያ ልንለው የምንፈልገው አንድ ነገር አለ፡፡ በእርግጥ የሃገራችንን ችግሮች እንፍታ ከተባለ ምንም አይነት ውይይት የማያስፈልገው በአለፉት 25 አመታት በሁሉም የሃገራችን ዴሞክራቶች ሲነሳ የቆየው በግፍ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች መሪዎች ወዘተ ይፈቱ የሚለው ጥያቄ አለ፡፡ ከዚህም አልፎ ለችግሮቻችን መፍትሄ ከተባለ ባልተቋረጠ ወከባ ውስጥ ከሚገኙትና በህዝብ ፊት መፍትሄዎቻችውን እያቀረቡ በመታገል ላይ ካሉት ተቃዋሚዎች፣ ከሲቪኩ ማህበረሰብ ተወካዮችና ሌሎች የሃገሪቱ ጉዳይ ያባናል ከሚሉ ሃይሎች ጋር ውይይት ብቻ ሳይሆን በሃሳባቸውና በኢህአዴግ አካሄዶች መሃከል ስላሉት ልዩነነቶች በህዝብ ፊት ይፋ የሆኑ ክርክሮች ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ አንጻር ሲታይ የኢህአዴግ አካሄድ እንደሚጠበቀው ‘ሁሉን አቀፍ’ መሆን ሲገባው የሃገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ሆን ብሎ ያገለለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከፖለቲካ ሃይሎች ጋር ተካሄደ የተባለው ውይይት ‘የጋራ ምክር ቤት’ የተባለው ስብስብ አባላት ከሆኑ ድርጅቶች ጋር ብቻ ነው፡፡ የዚህ ምክር ቤት አባላት ከኢህአዴግ በሚለገስላቸው ድጎማ የሚተዳደሩ፣ በህዝብ ፊት ምንም ተአማኒነት የሌላቸው ተለጣፊ ድርጅቶች ሲሆኑ በሃገሪቱ አሉ የሚባሉት ተቃዋሚ ድርጅቶች – ማለትም መኢአድ፣ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ የሉበትም፡፡ በመሆኑም እነዚህ ድርጅቶች በውይይቱ አልተሳፉም፡፡ ከዚህም በመነሳት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢኒጂንር ይልቃል ‘የተካሄደው ውይይት ለገዥው ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ስራ ከመስራት የዘለለ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡’ በማለት ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡትን አስተያየት የሃገራችን ዴሞክራቶች በሙሉ የሚጋሩት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ከዚህ ስንነሳ ፍሬያማና ለሃገራችን ውስብስብ ችግሮች መፍትሄ የሚያመጣው አካሄድ ምን እንደሚሆን በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ሃቀኛና ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ከተባለ የተወሰኑ ምሁራንንና ተለጣፊ የፖለቲካ መሪዎችን ለየብቻና ‘በዝግ ችሎት’ ማነጋገር የትም የማያደርስ አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የመንግስት ተወካዮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች (ገበሬ፣ ሰራተኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሃገር ሽማግሎች ወዘተ) በጋራ የሚሰበሰቡበት፣ በህዝብ ፊት ስለሃገሪቱ ችግሮች የሚወያዩበትና ሃገራችን አሁን ካለችበት ቀውስ ወጥታ ዴሞክራሲና ብሄራዊ እርቅ የሰፈነበት የተረጋጋ ህብረተሰብ ስለሚመሰረትበት ሁኔታ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚያቀርቡበት ኢህአዴግም የሚሳተፍበት ሰፊ መድረክ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በዚህ ሰፊ መድረክ ሳቢያ ስምምነት የሚደረስባቸው ነጥቦች በእርግጥም በተግባር መተርጎማቸውን የሚከታተል በዚሁ መድረክ የሚሰየም አካል ያስፈልጋል፡፡
እንዲህ አይነቱ ሰፊ ሃገራዊ አጀንዳ ያነገበ ሃገር አቀፍ ጉባኤ እንዲደረግ መጀመሪያ በህዝባዊ ትግል የኢህአዴግ አገዛዝ ከያዘው የጥፋት ሂደት ተገትቶ ለሃቀኛና ፍሬያማ ብሄራዊ ውይይተት መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በመለስ ምንም ዘላቂ የሆነ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ አሁን በኦሮምያ፣ በጎንደርና በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች በመካሄድ ላያ ያሉትና መኢሶን ሙሉ በሙሉ የሚደግፋቸው ትግሎች ሳያሰልሱ መቀጠላቸው ብቻ አይበቃም፡፡ በሃገራችን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ብሶታቸውንና ጥያቄዎቻቸውን እያነገቡ ከትግሉ መደባለቅና ሰፊ የህዝባዊ ትግል ማእበል ለመቀስቀስ መተባበር ይኖርባቸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ሂደታችን አሁን እንደሚታየው ከኦሮሞ ወጣቶች፣ ከወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ወዘተ ጋር የትግል አንድነት በመግለጽና ለነዚህ ትግሎች ድጋፍ በማሳየት መወሰን የለበትም፡፡ እርግጥ በዚህ መልክ የትግል አጋርነት ማሳየት ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ የአማራው፣ የትግራዩ፣ የጉራጌው ወዘተ ወጣት የኦሮሞ ወገኖቹን ትግል ደግፎ፣ የኦሮሞ ወጣቶች ደግሞ በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የማንነት ጥያቄ አንግቦ የሚያካሂደውን ትግል በይፋ ደግፈው ቢወጡ፣ በጋምቤላና በሌሎች የሃገራችን አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሲከሰቱ፣ አማራው ለዝንት አለም ከኖረበት አካባቢ አገርህ አይደለም እየተባለ ሃብት ንብረቱን ተዘርፎ እንዲባረር ሲገደድ ወጣቶች በሙሉ በአንድ ድምጽ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙ፤ የወያኔ አገዛዝ ከሁሉም በላይ የሚፈራውንና በስውር ደባና በይፋ የሚዋጋውን የህዝቦች ወንድማማችነት መንፈስ ለማጎልበት የሚረዳ ስለሆነ እሰየው የሚያሰኝና ሊበረታታ የሚገባው አካሄድ ይሆናል ማለት ነው።
ነገር ግን ትግሉ ይስፋፋ፣ ይጠንክር ስንል አንድ ጥያቄ አንስተን መመለስ ይኖርብናል፡፡ የኦሮሞ ወጣቶችን ትግል የሚደግፈው ወጣት የራሱ ብሶትና ጥያቄ የለውም ወይ ? በእርግጥ አለው፡፡ በመሆኑም እነሱን መደገፍ ማለት ውጤታማ የሚሆነው በዚች ሚልዮኖች ስፍር ቀጥር በሌላቸውና እጅግ የተሰበጣጠሩ የመብትና የህልውና ቀውስ ወስጥ በወደቁባት ሃገራችን እነዚህ የተሰበጣጠሩ ሃይሎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ከኦሮሞ ወጣቶች ትግል አርአያነት በመቅሰምም ሁሉም የየራሳቸውን ችግሮችና ብሶቶች እያነገቡ ሲታገሉ እንደሆነ ግልጽ ይመስለናል፡፡ በዚህ መልክ ሁሉም ብሶቱን አንግቦ ይንቀሳቀስ ሲባል ይህ ትግል ሁላችንም የምንመኘውን ፍሬ እንዲሰጥ ከተፈለገ ተቀነባብሮና ተደጋግፎ በአንድ ሰፊና ሁሉን አቀፍ የሆነ የጋራ አጀንዳ ዙሪያ መታገሉ ወሳኝ ይሆናል፡፡ የጋራ አጀንዳ ማንገብ ማለት ደግሞ ለነዚህ ሁሉ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው በሃገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሲመሰረት መሆኑን በመገንዘብ በትግል ላይ ያለው ህዝብ የስርአት ለውጥ በሚለው የፖለቲካ አጀንዳ ዙሪያ በአንድ አቅጣጫ መግፋት ማለት ነው፡፡
ይህ ትግል አይቀሬ በሚሆኑት የወያኔ /ኢህአዴግ ጅምላ የአፈናና የሽብር እርምጃዎች፣ እንደዚሁም የትግሉ መሪዎች ብሎ በሚፈርጃቸው ዜጎች ላይ በሚወስዳቸው እርምጃዎች አመራር አልባ ሆኖ እንዳይዝረከረክና እንዳይከስም ከፈለግን ከጅምላ አፈናና ከአመራሮች መታሰር ባሻገር ሊቀጥል የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርብናል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ በትግል ላይ ያሉት ሚልዮኖች የመጣ ቢመጣ የወያኔ ጸረ ህዝብ እርምጃዎች ከአእምሯቸው ሊፍቁት የማይችሉት የትግል አጀንዳ መጨበጥ ይኖርባቸዋል፡፡ በአጭሩ ትግሉ የኢህአዴግ አመራር በህዝብ ትግል ተገዶ ለሚጠራ ‘ሃገር አቀፍ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጉባኤ’ መሆን ይኖርበታል የምንለው ለዚህ ነው፡፡
በትግል ላይ ያሉ ሃቀኛ ዴሞክራቶችና አገር ወዳድ ሃይሎች ይህንን የትግል አጀንዳ ለህዝብ ከማስጨበጥ ባሻገር ከወዲሁ የዚህን አገር አቀፍ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጉባኤ ምንነት፣ የሚጠብቁትን ተግባራትና በሃገራችን የዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ ሂደት እልባት እስከሚያገኝበት ወቅት ድረስ የዚህ ሂደት ሮድ ማፕ ወይም ቅደም ተከተሎች ምን እንደሚሆኑ በጋራ ተወያይተው መንደፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ከዚህም በመነሳት በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ ያላሰለሱ ቅስቀሳዎች በማካሄድ ትግሉ ከየት ወዴትና እንዴት በሚሉት ጥያቄዎች አኳያ ህዝባችን በጣም ግልጽ የሆነ ስእል እንዲኖረው ማድረግ ከወቅቱ አንገብጋቢ ተግባራት አንዱና እንዲያውም ዋናው ነው ብለን እናምናለን፡፡
መላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)
መጋቢት 2008
Leave a Reply