በየአመቱ የካቲት 12 ቀን ሲደርስ ከማስታውሳቸው የዚህች አገር ባለውለተኞች መካከል ተመስገን ገብሬ አንዱ ነው። ይህ ሰው ሀገሩ ኢትዮጵያ በፋሽስቶች እንዳትወረር ብዙ ትግል አካሂዷል። ከወረራው በኋላም በአርበኝነት ተሰማርቶ የፋሽስቶችን ግብአተ-መሬት ካፋጠኑ የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን መካከል ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ነው። ተመስገን ገብሬ በ1901 ዓ.ም ጐጃም ደብረማርቆስ ከተማ ነው የተወለደ። ታህሳስ 15 ቀን 1941 ዓ.ም በ40 ዓመቱ አረፈ። በትምህርቱ እጅግ ጐበዝ የሚባል በመሆኑ ገና በ15 ዓመቱ የቅኔ መምህር ሆኖ ነበር። በቤተ-ክህነት ትምህርት በዚህ እድሜ የቅኔ መምህር የሆነ ሰው ከተመስገን ሌላ አልተገኘም ይባላል።
ይህ ሰው በ1918 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የዘመናዊ ትምህርቱን በስዊድሽ ሚስዮን ተከታትሎ ጨርሷል። በ1920ዎቹ ውስጥ ጣሊያን ኢትዮጵያን ከመውረሯ በፊት ወረራው ለኢትዮጵያ እንደማይቀር በማወቅ በየአደባባዩ ሕዝብን እየሰበሰበ አንድ እንዲሆንና ጠላትን እንዲመክት ያስተምር ነበር። በአንድነቷ የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመመስረት ብርቱ ትግል አድርጓል።
ተመስገን የኤርትራ ድምፅ የሚሰኝ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅም ነበር። የአልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለስላሴ የቤት ውስጥ መምህርም ነበር። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አጭር ልቦለድ የሚባለው የጉለሌው ሰካራም መጽሐፍም ደራሲ ነው። በአማርኛ ቋንቋ ችሎታውና በአፃፃፍ ቴክኒኩ እጅግ የተዋጣለት ደራሲ መሆኑን ሃያሲያን ይናገራሉ።
ተመስገን ገብሬ በኢጣሊያ ወረራም በፋሽስቶች ሊገደሉ ከሚፈለጉ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነበር። በተለይ ደግሞ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ወርውረው ካቆሰሉት በኋላ ፋሽስቶች 30 ሺ ያህል የሚገመት የአዲስ አበባን ሕዝብ ጨፍጭፈዋል። ጣሊያኖች እነ አብርሀ ደቦጭ ግራዚያኒን ለመግደል ያሴሩት በተመስገን ገብሬ ግፊት ነው ብለው በማመናቸው በዋና ጠላትነት ይፈልጉት ነበር። በዚያን ወቅት ተመስገንም በአጋጣሚ በፋሽስቶች እጅ ይወድቃል። ግን ተመስገን ገብሬ መሆኑን አላወቁም። ስሙን ሸሸጋቸው። እሱንም ሊገድሉት እስር ቤት ባስገቡት ወቅት ጣሊያኖች ኢትዮጵያዊያኖችን ሲጨፈጭፉ በዓይኑ አይቷል። ከዚህም ጭፍጨፋ በተአምር አምልጦ ወደ ሱዳን ይሰደዳል።
ተመስገን ገብሬ ይህን የየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የተደረገውን ጭፍጨፋ እና በአጠቃላይ በርሱ ሕይወት ዙሪያ ያለውን ውጣ ውረድ ሕይወቴ በሚል ርዕስ ፅፎታል። ይህን መጽሀፍ በ2000 ዓ.ም የአርትኦት ስራውን የሰራነውና እንዲታተም ያደረግነው እኔ እና ደረጀ ገብሬ እንዲሁም የተመስገን ገብሬ ልጅ ሲስተር ክብረ ተመስገን መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ እወዳለሁ። ከዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የተወሰነውን ክፍል በመውሰድ በወቅቱ ምን ዓይነት ግፍ እንደተፈፀመ ለማስታወስ እንሞክራለሁ። ተመስገን ጭፍጨፋውን በተመለከተ በወቅቱ ለንደን ለሚገኙት ለጃንሆይም ያየውን ጽፎላቸው ሲያነቡት አልቅሰዋል። ምን ይሆን ለጃንሆይ የፃፈላቸው? ከብዙ በጥቂቱ የሚከተለውን ይመስላል፡-
“ከሦስት ቀን የከተማ ጥፋት በኋላ ከሆለታ የመጡ የፋሽስት አውሬዎች በሚመለሱበት ካሚዮን በኋላው በኩል አቶ አርአያን እግራቸውን ጠርቅመው አሰሯቸው። ካሚዮኑ ሳይጐትታቸው “እኔ ወደ ሰማይ እንድገባ ሰማይ ተከፍቶ ይጠብቀኛል። እየሱስንም በዚያ አየዋለሁ። ደስ ይለኛል። ደስ ይለኛል። ደስ ይለኛል!” የሚለውን የሚሲዮን መዝሙር ዘመሩ። ፋሽስቶቹም የተሻለውን መዝሙር ብትሰማ ይሻልሃል አሏቸውና ዱኪ ዱኪ የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ። ካሚዮኑም ሞተሩን አስነስቶ ሲነዳ ታስረው ቁመው ነበርና ያን ጊዜ ዘግናኝ አወዳደቅ አቶ አርአያ ወደቁ። ካምዮኑም እየፈጠነ ጐተታቸው። ከአዲስ አበባ እስከ ሆለታ አርባ ኪሎ ሜትር ይሆናል። ካምዮኑ ከዚያ ሲደርስ ያ ከካሚዮኑ ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ እንደተንጠለጠለ ነበርና የካሚዮኑ ነጂ ከካሚዮኑ ፈታና ለውሾች ወረወረው።
እኔንም ያለሁበትን ቤት ሰብረው ከዚያ ቤት ያለነውን አውጥተው ከየመንደሩም ሕዝቡን አጠራቅመው ኑረዋል። ከዚያም መሐል ጨመሩን። ስምንት መትረየስ በዙሪያችን ጠምደዋል። በዚያም ቦታ ቁጥራቸው በብዙ የሆኑ ሐበሾችን አስቀድመው ገለዋቸዋል። ሬሣቸውም ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ። እኛንም በዚያ ሊገድሉን ተዘጋጁ። ለመትረየስም ተኩስ እንድንመች ያንዳችንን እጅ ካንዱ ጋር አያይዘው አሰሩን። አሥረውን ወደ መተኰሱ ሳይመለሱ አንድ ታላቅ ሹም መጣ። የርሱም ፖለቲካ ልዩ ነበረ። ፋሽስቶች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሕዝብ መግደል፤ ሕፃናቶችን ከአባትና እናታቸው ጋራ በቤት ዘግቶ ማቃጠል መልካም ብሎ ቢወድ እንኳን እኒያ ቦምብ በቤተ-መንግስቱ ስብሰባ የወረወሩት ሐበሾች ሳይታወቁ እንዲቀሩ አይወድም ነበርና ስለዚህ ካሚዮኖች ይዞ እየዞረ ፋሽስቶች የሚገድሉትን እያስጣለ ወደ እስር ቤት ለምርመራ ይወስድ ኑረዋል። እኛንም እንዲተኮስብን ታሰረን ከቆምንበት ከቅዱሰ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስት ረድፍ ወደላይኛው መንገድ ለመድረስ ስንሄድ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ።
ምራቄ ደረቀ አለ። በካሚዮኑ ወደ እስር ቤት አስወሰደን። ለግዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር። ከማዘጋጃ ቤቱ በር ስንደርስ በአምስት ካምዮን ያጠራቀመንን ሰዎች በዋናው መንገድ እንድንቆም አዘዘን። ዙሪያችንንም ከበው በሳንጃ እየወጉን ጨፍቅ ብለን በመንገዱ ቆምን። ከወደኋላችን ትልቁን የጣሊያን ካሚዮን በላያችን ላይ ነዱብን። አስራ ስምንት ቆስለው አልተጨረሱም፤በሳንጃ ጆሮአቸውን ወጓቸው። በአንድ ጊዜ ማለት አርባ ስምንት ሰዎች ጨፈለቀ። ተካሚዮኑ ወደኋላ ያፈገፈጉትን እሥረኞች ዙሪያውን ሳንጃ መዘው የቆሙት ወጓቸው። እኔም በካምዮኑ ጉልበቴን መታኝ። ያን ግዜ የቆሰልሁት እስከ ዛሬ ለምጥ ይመስላል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስትያን ተቃጥሎ ኑሯል። እንደ ማታ የፀሐይ ጮራ ከምዕራብ በኩል ይታያል። በለሊት ወስደው ከገደሉት በእስር ቤት የቀረው ያንሳል። ነገር ግን በዚህ ለመግደል ሲያወጡ የሚበልጥ በዚያ በር ያገቡ ነበር። በበነጋው ከተደበደበው ሕዝብ ከኪሱ የተገኘውን እየቆጠሩ ለሹሙ አስረከቡ፤ እኔም ከጽሕፈት ቤቱ ፊት ለፊት ነበርሁ።
የደበደቧቸውን የሐበሾችን የጋብቻ ቀለበታቸውን በሲባጐ እንደ መቁጠሪያ ሰክተው ደርድረው በአንገታቸው አግብተው አቀረቡት። አንዱ ቆጥሮ መዝኖም እስኪያስረክብ ሌላው ገና ባንገታቸው ነበር። ንፁህ የሆነውንም ልብስ በካምዮን አምጥተውት ነበርና እየቆጠሩ እስኪረከቡ፤ ገናም ሳይገቡ ገፈዋቸው ኖሯል። ስለዚህም ከጥቂቶች በቀር ሙሉው ልብስ በደም አልተበላሸም። በመሬትም ጣል ጣል እያደረጉ እየቆጠሩ እስኪረከቡ የጥቂቶች ልብሶች ገና እስከ ትኩስ ደም ኑረው ከመሬት መልሰው ሲያነሱዋቸው አፈር እና ግብስባሱን እየያዙት ሲነሱ አየሁ። ይህን ባዬ ጊዜ አንዱ ብድግ ብሎ እንደ እብድ ተነሳ።
“እርሷን አሁን ከመሬት አፈር ይዛ የተነሳችውን ደም እግዚአብሔር አየ፤ ሊፈርድ ነው። ይህ ክፉ ስራችሁ በጭካኔ ሕዝቡን የሰው ሕይወት በማጥፋት ትጫወታላቸሁ። የገደላችኋቸው ወገኖቻችን ቀለበት በሲባጐ ሰክታችሁ መዝናችሁ ወሰዳችሁ። ደማችንን መሬቱ መጠጠው፤ ሬሳውም እንደ ገለባ ተከመረ። ስትገድሉ እግዚአብሔር ሊፈርድባችሁ ነው። ይኸው አሁን የእግዚአብሔር ሚዛን ሞላ። እንግዲህ ኢትዮጵያን ከቶ አትገዙም። እኔንም አሁን ልትገድለኝ ነው” አላቸው። ገናም ነገሩን ሳይጨርስ አምስት ቦምብ ተወረወረ። በአጠገቡ ያሉ ሁሉ ተቆላልፈው ሰማንያ ሰዎች ወደቁ። ካሚዮንም ሬሳውን ለመውሰድ አመጡ። ሬሳውን በአንድ ካሚዮን ከወሰዱ በኋላ ሌሎች ካሚዮኖችም ቁስለኞችን ለመውሰድ አመጡ። በብርቱም የቆሰሉትን እያነሱ ወስደው ከእስር ቤት በር በመትረየስ ተኰስዋቸው። በጥቂት የቆሰሉት ሰዎች ግን ቁስላቸውን አየሸሸጉ እንደ ደህና እየመሰሉ በእስረኛው መሐል ተሸሸጉ። ኢጣሊያኖችም እየበረበሩ ጥቂትም ቆስሎ ቢሆን ልትታከሙ ነው እያሉ እየመረጡ ከበር ገደሏቸው። ቁስል የሌላቸውንም እየነዱ ሲያወጡ “እረ እኛ ጤነኛ ነን አልቆሰልንም” እያሉ ቢጮሁ “አይሆንም ትታከማለህ፤ ቆስላችኋል” ብለው እየጐተቱ አውጥተው ከማዘጋጃ ቤት በር ሲደርሱ የሳንቃውን ቋሚ ዘንግ የሚመስሉትን ብረቶች በሁለት እጃቸው አንቀው ይዘው አልወጣ አሉ። በእንጨት ላይ እያሰለፉ ገደሏቸው።
ቀኑ ብርቱ ፀሐይ ነበር። በዚያ እስር ቤት በማዘጋጃ ቤት ሜዳ ነበርና ብርቱ ክቢያ ተከበን ታላቅ ፍርሃት ነበር። ውሃና መብልም አላገኘንም። በሦስተኛው ቀን ጊዜውም ስድስት ሰዓት ሲሆን አስራ ሰባት ሰዎች በውሃ ጥማቱ ሞቱ። ይህም ቀን ጨለመ። እህልና ውሃ ሳናገኝ ሦስተኛው ቀን ነበርና ገንዘብም አየተቀበሉ በኰዳቸው ጣሊያኖች ለእስረኞች ውሃ መሸጥ ጀመሩ።
ሕይወታችንም በዚህ ስቃይ ውስጥ ታንቃ ስንጨነቅ መሸ፤ እንጂ ለቀን ቀኑ ረጅም ነበር። ከዚያ ረሐብና ውሃ ጥማት እንዲገድሉን መርጠን ነበር። ይህንንም ከልክለውን ሁለት ካሚዮን አምጥተው ከዚህ ወደሚሰፋ እስር ቦታ ሊወስዱን እየቆጠሩ ስሙን እየፃፉ 30ውን አሳፈሩት። እንደተናገርኩት እኔ በጽህፈት ቤቱ በር አጠገብ ስለነበርኩ እስረኛውን እየቆጠሩ እያሳፈሩ መጓዝ የጀመሩ ከወዲያ በኩል ነበርና ስለዚህ የኔ መሄዴ ዘግይቶ ነበር። ብዙ የሚያሳዝን ቁም ነገሮች በመዘግየቴ አየሁ።
ሦስት ሴቶች በወሊድ ተጨንቀው ኖረዋል። ሊወልዱም ቦታ አላገኙምና በእስረኛው ግፊ ተጨፍልቀው ሞተዋል። ሦስቱም ከትንንሽ ህፃናቶቻቸው ጋር ሬሳቸው ወድቆ አየሁት። በውሃ ጥማትና በረሃብ እነርሱም በቦምብ ከገደሉት ከሞተው ሰውና ከሬሳው ብዛት የተነሳ እኒህን በወሊድ የሞቱትን ያስተዋላቸው አልነበረም። እኔንም ሊገድሉኘ ስሜን በሊስት ይዘው ይፈልጉኝ ነበርና ስሜን ፅፈው ሊያሳፍሩኝ ሲሉ ሌላ ስም ነገርኳቸው። በካሚዮንም እስረኛውን ወደወሰዱበት ስፍራ አጓዙን። በመንገድም የካሚዮኑ መብራት በሚወድቅበት እንመለከት ነበር። መንገዱ ሁሉ ሬሳ ተሞልቶ ነበር። በገደሏቸው በሐበሾች ሬሳ ተሞልቶ ነበር። ዝም ብለው በላዩ ይነዱበት ነበር። በሬሳው ብቻ አይደለም። ነገር ግን ሬሳውን ደግሞ በካሚዮናቸው በጨፈለቁት ወቅት በሰው ሬሳ መንገዱ ተበላሽቶ ያስጸይፍ ነበር። ከመንገዱም ዳር የወደቁትን ሬሶች የካሚዮኑ ብርሃን በወደቀባቸው ጊዜ ድመቶች ጐንጫቸውን ነክሰው ጺማቸውን እያራገፉ ሲበሏቸው አየሁ።
ካሚዮኑ ከእስር ቤቱ በር ፊት በር በሚባለው በደረሰ ጊዜ ከካሚዮን እንድንወርድ አደረጉን። በኋላ በኩል ከነበሩት መጀመሪያ የወረዱትን ቦምብ ወርውረው ገደሏቸው። የቀረነው አንወርድም ብለን ራሳችንን በውስጥ በሸሸግን ጊዜ በኋላ በኩል ነጂው በሚቀመጥበት በኩል መትረየስ አምጥተው አስገብተው ተኩሰውብን ሞላዎችን ገደሏቸው። የቀረነው እየዘለልን ከካሚዮን ወረድን። ለጥይቱ ፈርተው በኋላ በኩል ሸሽተው ነበርና የወረደም የለም። የእስር ቤቱ በር ክፍት ስለነበር እየፈጠንን ሩጠን ተጨመርን። ሌሊቱንም ሁሉ እስረኛውን እያጋዙት ሲጨምሩት አደሩ።
ይህም ቦታ ጠፍ ሁኖ የኖረ ነበረና ሳማና ልት የሚባለው ምንስ ወራቱ መጋቢት ቢሆን ቅጠሉ ለምልሞ ነበር። በታላቅ ረሃብና ውሃ ጥማት የተጨነቀው እስረኛ ያንን መራራ ቅጠል በላ። ሲጠጣ ይህን ቅጠል ያሳደሩ ስሩን እየገፈፉ በሉ። እኔም ምን የሚበላ ነገር ይህ ፍጥረት አገኘ? ባገኘው ህይወት ነው ብዬ ወደሚያላምጡት ሰዎች ሔድሁ። የሚያውቀኝ ሰው አገኘሁና ከዚያ ስር ቆፍሮ ሰጠኘ። እኔም ወስጄ ለባልንጀሮቼ አካፈልኋቸው፤ለውሃ ጥማት ይህን ማላመጥ መድሃኒት ነው ብሎ ነግሮኝ ነበርና ለውሃ ጥማት መድሃኒት ነው ብዬ ነገርኋቸው። ከፊላችንም መራራ እንደሚጣፍጥ ይህን እያላመጥን እስከ አራት ሰዓት ቆየን።
ዛሬ ቀኑ አሁድ ነበር። የተያዝንበትም አርብ በስምንት ሰዓት ነበር። ከዚያ እስከ ዛሬ እህል የሚባል እንኳን ለመብል ማግኘት ቀርቶ ያየን የለም። ፀሐይ በዚህ ቀን ሲተኩስ ሰው ሁሉ ልቡሱን እያወለቀ በራሱ ላይ ተከናነበው። በዚህም መከናነብ የፀሐይ ትኩሳት ሲበርድ ውሃውን ጥማት መከላከል የሚችሉ መስሏቸው ነበር። ከሌላው እስር ቤት በቀር በዚህ እስር ቤት ውስጥ የነበረው አስረኛ እነሱ ጣሊያኖች እንደገመቱት 18 ሺ ነበር። ከረሐቡና ከጥማቱ የተነሳ እስረኛውም ሁሉ መናገር አይችልም ነበር። ነፍሱ ገና አለቀው እያለች ነው እንጂ ሁሉም ደክሞ ይጠራሞት ነበር። ለመተንፈስ እስከማይችል ድረስ ያ ትልቁ ሰፊ ሜዳ ጠቦ ነበር።
አንዱ እየተጋፋ መጣ። ጠርሙስ በእጁ ነበር። ፊቱ ክስመት ገብቶ ነበር። ከአጠገባችን ቆሞ ሊናገረን ፈለገ። ገና ከንፈሩን ማላቀቅ ግን አፈልቻለም። ከውሃ ጥማት የተነሳ ረድኤት በማፈልግ ዓይን በሚያሳዝን ተኩሮ ወደ እኛ ተመለከተ። በታላቅ ችግር በውሃ ጥማት የተያያዘውን ከንፈር አላቀቀው። ደካማ በሆነ ድምፅ “እባካችሁ! እባካችሁ!” ሲል ሰማነው። ነገሩን የሚለውን አጥርተን አልሰማነውም ነበርና ልንሰማው እንድንችል ወደ እኛ በጣም ቀረበ። እ…ባካችሁ ከእናንተ ጭብጦ የሌላችሁ ሽንቱን በዚህ ጠርሙስ ይስጠኝ ወንድሞቼ ሁለቱ በውሃ ጥማት ሞቱ፤ እኔም ልሞት ነኝ፤ እባክዎ ጭብጦ ባይኖርዎ ሽንትዎን እባክዎ ጌታ ይስጡኝ” ብሎ ልመናውን ወደ አቶ ገብረመድህን አወቀ አበረታው። አቶ ገብረመድህን አወቀም “እኔም አንዳንተ ነኝ። ውሃ ከጠጣሁ ሦስተኛ ቀኔ ነው። ከዬት ሽንት አመጣለሁ?” እኛንም አልፎ እየዞረ ሲለምን አልቆየም። እስከ መጨረሻው ደክሞት ነበር። መናገርም አቃተው። አንድ ድንጋይም በአጠገባችን ተንተርሶ ጥቂት ግዜ ተጋድሞ በሕይወቱ ቆየ። በመጨረሻም ግን እንደ እንቅልፍ በሞት ያችን ድንጋይ እንደተንተራሰ አሸለበ።
በዚህ ቀን በውሃ ጥማት ከመቶ በላይ እሰረኛ ከጥዋት እስከ ሰባት ሰዓት ሞቱ። ሬሳቸውንም ካሚዮኖች መጥተው ወሰዱት። በዚህ ጊዜ የእስር ቤቱ ሹም ቲሊንቲ ሎዊጂ ኮርቦ የሚባለው በዚያ እስር ውስጥ ገብቶ የተጠሙትን ነፍሳቸው አልላቀቅ ያላቸውን አይቷቸው ኑሯል። በኰዳው ውሀ ይዞ መጣ። ቲሊንቲም የኮዳውን ውሃ ለእስረኛው መሸጡን ሰማን። ገንዘብም ይዤ ሄድሁ። የሚሸጠው እሱ ብቻ ስለሆነ ካጠገቡ መድረስ አይቻልም። የተጠማው ብዙ ሕዝብ ውሃ ለማግኘት ዙሪያውን ከቦት ይጋፋ ነበር። ገዥውም ፋታ አያገኝም ነበር። በቀኝ እጁ ሽጉጡን አውጥቶ፤ በግራ እጁ በተጠማው ሰው በአፉ ውስጥ ትንሽ ጠብ ያደርግለታል። የኢጣሊያ አንድ ኰዳ ሁለት ጠርሙስ ተኩል ይይዛል። ቲሊንቲ አንዱን ኰዳ ውሃ ለሃያ አምስት ሰው አስጠጥቶ ሃያ አምስት ብር ለአንድ ኮዳ ተከፈለው። የአቶ ስለሺ አሽከርም በጣም ተጠምቶ ነበር። አንድ ብር በቲሊንቲ ግራ እጅ አኖረ። እሱም ከኰዳው አጠጣው። ቲሊንቲም ውሃውን አቀረበና በአፉ አፈሰሰበት። ጠጪውም ስላልረካ ኮዳውን ቲሊንቲን ቀልጥፎ ሲያቃናው በሁለት እጁ ከአፉ አስጠግቶ ያዘው። ቲሊንቱም ሽጉጡን በዓይኑ መሐል ተኮሰበት። ሳይውጠው ገና በጉንጩ የነበረው ሲወድቅ በአፉ ፈሰሰ። ቲሊንቲም ደጋግሞ ተኩሶ ጨረሰው። እርሱን በተኰሰው ጊዜ አሳልፎ ክንዱን ያንዱን ሰው አቁስሎት ስለነበር የቆሰለው ብር እንኳ ቢሰጠው እንዲሁ ያለ ዋጋ አጠጣው።
ይህንም በውሃ ጥማት የሆነውን ታላቅ እልቂት እንዲቀር ውሃ በሸራ ቧንቧ ኢጣሊያኖች ከታሰርንበት ድረስ አስገብተው በ120 በርሜል ሞሉልን። እኒያ ሁለት ሹማምንቶች ማርሻሎና ቲሊኒቲ ሎዊጂ ኮርቦ እስረኛውን እያካፈሉ ከዚያ ወዲህ ያለው ይጠጣ እያሉ ሲከላከሉ አንድ ግዜ እስረኛው እንደ ናዳ ተንዶ ጥሷቸው ሄደና ውሃም የቻለውን ያህል ይጠጣ አለ። በርሜሉንም ገና ያላየው ነበር። እነርሱም በዚህ ግፊት እኒህ ውሃ ሲሸጡ የዋሉ ሹማምንቶች ተድጠው ሞተው ኑረዋል። የሹማምንቶቻቸውን ሞት ስላወቁ ሰው ላይ ቦምብ ይወረውሩበት ጀመር። በበርሜሎች ዙሪያ ሬሳው ተከመረ። በቦምብ የተመቱት የጥቂቶችም ሬሳ በበርሜሎች ውሃ ውስጥ ገባ። ደማቸው ተቀላቀለበት፤ ሰውም ከላያቸው ላይ ሳይፀየፍ ይጠጣ ነበር። ልብሶቸውንም በበርሜሉ ውሃ እየነከሩ አምጥተው የተነከረውን ልብስ እንደ ጡት ጠቡት። በደከሙት ባልጀሮች አፍም እየጨመቁላቸው ቤዛ ሆኑ። ከተወረወረብንም ቦምብ ብዛት የተነሳ የሞተው ሬሳ በበርሜሎች ዙሪያ ተቆልሎ ነበርና ሰው ቢሄድም ሬሳው ወደ በርሜሉ እንደማያደርሰው አወቀ፤ ከመሄድም ታገሰ።
ሦስት መትረየስ አግብተው ጠምደው ተኮሱብን። ውሃ ለእስረኛ ሲሸጡ ውለው እግዜር ፈርዶባቸው የተዳጡትንም የሹማምነቶቻቸውን በቀል ተበቀሉን። አምስት ካሚዮን አመላልሰው አንድ ሺ አምስት መቶ የሚያህል እስረኛ ሞተ። ሬሳውንም በካሚዮን እስኪያወጡ ድረስ ፈፅሞ ጨለመ።
በኢጣሊያ ፋሽስት የተያዘ ሳይገደል በህይወት ፊት ምንድን ነው? መብልና ውሃ የሰጡን ሹማምንቶች ወደ ቤታቸው በተመለሱ ጊዜ ቁጣቸውን አድሰው በዙሪያው በውድሞው ያሉ ፋሽስቶች በሰው ህይወት ሊጫወቱ ቦምብ ይወረውሩብን ጀመረ። ግን የቁጣ ምክንያት አልነበራቸውም። በዙሪያው ከሚወረወር ቦምብ ለመሸሽ የማይደረስበት መሃከለኛውን ቦታ ለመያዝ እርስ በርሳችን ተጨናንቆ ተጋፍቶ ቆሞ ሳለ በዙሪያ ዳር የሚወረወሩት ቦምቦች ከመሀል አወራወራቸው ሊያደርሳቸው ስለማይችል በዳር በኩል ዙሪያውን ያሉትን ጨፈጨፏቸው። የቀረውም ከመሀል ሆኖ ለቦምብ ውርውራ ስለአቃታቸው መትረየሱን ለመሀል ጠምደው ተኮሱብን። ከጥይት ለመዳን የፈለገ ሲተኛ የቆመው ህዝብ ጨፈለቀው። የቆመውን መትረየስ ጠረገው። የቆሰለና ያልቆሰለ የሞተና ደህነኛ እስኪጠባ ድረስ ተቆላልፎ አደረ። ሰኞ በበነጋው ሌላ ሹም መጥቶ ደህናውንና የቆሰለውን በአንድ በኩል ለየው፤ የሞተውን ሬሳ ግን በካሚዮን ማጓዝ ጀመረ።
ግን በዚያ ማታ በቦምብ የገደሏቸውን ሬሳውን ሳይወስዱ ስለቀሩ ወደ በሩ ሲል ወዳለው ማዕዘን አንድ ሴት እስከ ልጇ የታሰረች በቦምብ ተመታ ሞታ ኑሯል። ልጇ ደህና ነበረ። የእናቱንም ሬሳ ሌሊትን ሁሉ በደረቷ ላይ ተሰቅሎ ገና በሕይወት እንዳለች ሁሉ ይጠባት ነበር። እስረኞችም ምንስ በእንዲህ ያለ ጭንቅ ተይዘው፤ በውሃ ረገድ ባይረዳዱ የዚህ ሕፃን ስቃይ ልባቸውን አንቀሳቀሰው። ይህን ሕፃን አንስተው ትናንት በግፍ ልጇ ለተዳጠባት ሴት እባክሽ አጥቢው ብለው ሰጧት። ያችም ሴት ለልጇ ምትክ እንዳገኘች ደስ ብሏት አልተቀበለችም። እንዲያውም ወርውራ ጣለችው። ነገ ኢጣሊያኖች በቦምብ ለሚገድሉት ለማሳደግ አላጠባም። ለመትረየስና ለሳንጃም አላሳዳግም ብላ ወረወረችው። በዚያ ብርቱ ፀሐይ ተንጋሎ ወድቆ ብርቱ ለቅሶ አለቀሰ። እኔም አንስቼ እናቱ ሬሳ ላይ አስቀመጥኩት። እናቱንም እንዳገኘ ሁሉ ደስ ብሎት ለቅሶውንም አቆመ። ወዲያውም በካሚዎን ሬሳውን መውሰድ ጀመሩ። የዚህን ህፃን እናቱ በካሚዎን ሬሳዋን ፋሽስቶች ወስደው ሲያገቡ አንዱ ኦፊሰር የሆነ ፋሽስት ይህን ህፃን ታቅፎ በእውነት ሲያለቅስ አየነው።
እነዚህ የካቶሊክ ካህናት የሃይማኖት ወገናቸውን ሁሉ አስፈትተው ይዘው ሄዱ። የዛኑ ለት ማታውኑ የቀረነውን እስረኞች በካምዮን ጭነው ወደ ሆለታ ወሰዱን። እዛም ስንደርስ በጫካው አውርደው ተኮሱብን። እኔም አጠገቤ ያለው ሰው ተመቶ ሲወድቅ አብሬው ወደቅሁ። ጣሊያኖችም ጨርሰናቸዋል ብለው ትተውን ሄዱ።
እኔም ካምዮኑ መሄዱን አረጋግጨ በሆዴ እየተንፏቀቅሁ ከዛ እሬሳ መሃል ወጥቼ በጨረቃ ብርሃን ወደ እትቴ በዛብሽ ቤት ሄድኩ። እዛም እንደደረስሁ በምክር ወደ ጐጃም እንዴት እንደምደርስ አሰላን፤ እርስዋም ልብሷን አለበሰችኝና ሻሽዋንም አስራልኝ ማሰሮ አሳዝላኝ በጨረቃ ብርሃን ጉዞየን ወደ ጐጃም አቀናሁ። የማውቀው የአባይን በረሃ በለሊት እየተጓዝሁ በቀን እየተደበቅሁ እማርቆስ ገባሁ። እዛም እናቴንና እህቴን በሌላ መንደር አገኘኋቸው።
እናቴ “በቤቱ በምበላበት ገበታ ዙሪያውን ልጆቼና አባቴ ከበው ይቀመጡ ነበር። ዛሬ ግን በዚያው ገበታ ዙሪያና በዚያው ቤት ብቻየን እቀመጣለሁ። ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ እንደ ቀመሰው መራራ ውኃ፤ ሕይወቴ ሁሉ መራራ ሆነ። ሕይወቴ ሁሉ እንዲህ ለኃዘን ከሆነ ለምን ሰው ሆንሁኝ?” አለች።
እናቴን በእንዲህ ያለ ኃዘን ባየሁ ጊዜ ከቶ የተራበው ሰውነቴ እጅግ መብል ሊወስድ አልቻለም። በባቢሎን ወንዝ ዳር ተቀምጠው እሥራኤል ጽዮንን እያሰቡ ያለቅሱ እንደ ነበር ልንበላ በከበብነው ገበታ ዙሪያ ፈረንጆች የገደሏዋቸውን አያቴንና አራቱን ወንድሞቼን እያሰበች እናቴ አለቀሰች። እናቴ ገና ከአንድ ወር በፊት በገበታ ዙሪያ አብረዋት ይከቡ የነበሩትን ልጆቿን ፈረንጆቸ ሲገድሉባት ይቀመጡበት የነበረውን ቦታ ባዶውን ስታይ በአጭር ጊዜ እንዴት ልትረሳቸው ይሆንላታል? ይቀመጡበት የነበረው የገበታው ዙሪያና ይተኙበት የነበረው ክፍል ባዶነት እንደ ሐውልት ቁሞ ነበር። ወደ መብል ስትቀመጥ ባዶ የሆነውን ዙሪያ ወደመኝታ ቤት ስትሔድ ባዶውን አልጋ ማየት ለእናቴ እጅግ ኅዘን ነበር። ስለዚህም እናቴ ያን ቤት ትታ ሌላ ቤት ተከራይታ ነበር። እንዲሁ የእናቴ ዕንባ በጐንጮችዋ ላይ ሲወርድ ባየሁ ጊዜ ነጮች ያፈሰሱትን የወንድሞቸን ደም ያህል የቀረበውን መብል ቆጠርሁ፤ ለመብላትም ፈቃዴ ተዘጋ፤ ምንም እንኳ ተርቤ ብሰነብት።
ከዚሀ በኋላ የቀረበው ሁሉ መብል ተነሣ። እኔ ከነጮች እንድሸሽ አጎቴ የሰጠኝን ፈረስ አቀረበልኝ። ጠጉሬ የከተማ ሰው ቁርጥ ነበርና እንደ ውጭ ባላገር እንድመስል እኅቴ እያበላለጠች ስትቆርጥልኝ አዘገየችኝ። ገና ከተዘንቦው በኩል ስትቆርጥልኝ አያሌ የነጭ ወታደሮች ቤቱን ከበቡት። እናቴ ከድንጋጤ የተነሣ አእምሮዋ ሳይቀር ጠፋባት፤ አጎቴና እኅቴ ከቤት ወጥተው ነገሩ ምንድን ነው? ብለው ጠየቋቸው። ብርጋዴሩ የያዘውን ሊስት አየና… እፈልጋለሁ አለ። በጣም ያስደንቅ ነበር። በሊስት የተያያዘው ስም በፍፁም የእኔ ስም ነው። ግን ያባቱ ስም አሥራት ይባል ነበር። የእኔ አባት ስም ሌላ .. ነበር። እህቴም የሚፈልጉትን ሰው ቤቱን እንደ ተሳሳቱ ነገረቻቸው። ብራጋዴሩ ሊስቱን እንደገና አየና ከአጎቱ ጋር ይኖራል እንጂ ለእርሱ ቤት የለውም ብሎ ነገራት። አዎን ያ ሰው ደግሞ ከአጎቱ ጋር ይኖር ነበርና አዎን ከአጎቱ ጋር ነው ብላ ነገረችው፤ ወታደሮቹም ሔደው ያንን ቤት ከበቡት። መንደረተኛውን ሁሉ እንዳይወጣና እንዳይገባ ከለከሉ። ያን ለመያዝ ከዚያም ጫጫታ ሆነ። በዚህ ጊዜ ለማምለጥ ቅጽበት ጊዜ አገኘሁ። ኮርቻ ለመጫንና ለመለጎም ጊዜ አልነበረም፤ በፈረሱ ያለ ኮርቻ ያለ ልጓም ተቀመጥሁና ጋለብሁ። ጠጉሬን ግማሹን ተቆርጨ ግማሹን ሳልቆረጥ አመለጥሁ። ይህም ዛሬ ተረት ይመስላል።
ሕይወቴ ከነጮች በማምለጥ ለሩጫና ለሽሽት ብቻ ሆነ። በፊቴም ሁሉ ተስፋና መጽናኛ የለም፤ ዙሪያውም ሁሉ ከሌሊት የባሰ ጨለማ ሆነብኝ። በሀገራችን እያባረሩ ለሚያድኑን ለነጮች የምታበራይቱ ፀሐይ ግን በሃገራችን ሰማይ ታበራ ነበር። ስለዚህም ለሚያዳኑን ለእነርሱ የሚያምረው የበጋ ብርሃን ለምታደነው ለእኔ የክረምት ጨለማ ነበር። በዚያ ጊዜ አእምሮው ጮሌ የሆነ ዕውር ከእኔ የተሻለ ነበር። ወዴት እንደምሸሽ ከቶ አላውቅም ነበር። ወዴት እንድጋልብ ሳላውቅ ፈረሱን ወደ ቀጥታው እንዲጋልብ ለቀቅሁት። በማዶው በኩል በተራራው ግርጌ ተፋጥኜ ካለፍሁ በኋላ አርባ ማይል እንደ ተጓዝሁ ከራዕዩ እንደ ተመለሰ ሰው ሆንሁ። ለጥቁር ሕዝብ በሰላም የተሰማራበትን ነጮቹ በማደን የማያባርሩበትን አዲሱን ክበብ አየሁ። አዲስ ምድርና አዲስ ሰማይ ያህል መሰለኝ። በዚያም ጠባቂ የሌለው በግ ጥቁሩ ሕዝብ ተሰማርተዋል። ጠባቂው በእንግሊዝ አገር ነው። ቀበሮው ከዚህ አስቀድሞ አልገባም ነበር። የዘር ወራት ነበርና ሁሉም ደርሶ ነበር። ያን ሃገር ነበረና የዘራውን ሊበላ በተስፋ ይዘራ ነበር። ገና ነጮች ሃገሩን አልወረሩትም ነበርና በመስኩ ከብቱ ተሰማርቶ ነበር። እናቶች በቤታቸው ናቸው። ሕፃናቶችም በመንደራቸው አንደ ማለዳ ወፎች እየተንጫጩ ይጫወታሉ። በግ ጠባቂው በጎችን ይመለከታል። ከብቶችን የማያረባው ዘላን ከብቶችን ይከተላል። ወደ መንደራቸው ጠባቂዎች ከመንጋዎቻቸው ጋር ይጓዛሉ። ወርቅ የሚመስለው የፀሐይ ጮራ በተራራዎች ላይ ተዘርግቷል። ገበሬዎች በሚያርሱበት ቦታ ጅራፍ ብቻ ይጮሃል። የኤውሮፓ ማሰልጠኛ ቦንብና መድፍ መትረየስ ድምፅ አይሰማም። በነጮች ወራሪ የሣር ክዳን አንድ ጎጆ የተቃጠለ አመድ የለምና ንፋሱም አመድ አያበንም። በወንዙ ዳር የተተከሉ ለጋ ሸንበቆዎች በወታደር አልተጣሱም። ገና ንፋሱ ያወዛውዛቸዋል። ባላገሮች በሃገራቸው ላይ በፍፁም ፀጥታ ይኖራሉ። እንዲህ ያለ ጥቁር ሕዝብ ከሰላሙ ጋር የሚኖርበት አዲስ አገር አገኘሁ። የሰላም የሰላም የሰላም ሃገር። ነጮች ወራሪዎች አልረገጥዋትም፤ በድንገት ግን አደጋ ጥሎ ለመወረር ገና ሳያዩዋቸው በሚስጥር መግባት ጀምረዋል። በቤቴ ለመኖር የነበረኝ ሰላም በነጮች ከተቀጠቀጠ ሁለት ዓመት ያህል ሆኖ ነበርና በሀገራቸው በሰላም እንዲሁ የሚኖሩትን ሰዎች በማየቴ ካለፈው ዓመት በፊት እንዴት በሰላም ከበቴ እኖር እንደነበር አሳሰበኝ። በሰሩት ቤት መኖር! ሰማይ ቢከፈት ከዚህ የበለጠ ስጦታ በምድር ሊዘንብ በቻለ። ሕዝብ በሀገር ውስጥ በሰላም መኖር ሕፃናትን በሰላም ማሳደግ፣ ቤተሰብን መርዳት ከዚህም ጋራ በሰሩት ቤት በሰላም መኖር! ከዚህ የበለጠ የበረከት ፍሬ መሬት ልትሰጥ ትችላለችን? ሰው በሕይወቱ የሚመኘውና ሊኖረው የሚፈልገው ይህ ብቻ ነው። የነጮች ወራሪዎች በረገጧት ሃገር ሁሉ ለሕያው ነፍስ የሚያስፈልገው የሰላም ኑሮ የለም ነበር። ከወራሪዎች ድንግል በነበረችው ከዚህች አውራጃ ሃገር በደረስሁ ጊዜ አዲስ ሌላ አለም ያየሁ ያህል መሰለኝ። ያልታደለችው ኢትዮጵያ በእርግጥ ሰፊ ሃገር ናት። ወራሪዎችም ባንድ ጊዜ በሙሉዋ ሊጎርሷት አልቻሉም ነበርና በየከተማ አጠገብ ያሉትን ሃገሮች በቦምብ በመርዝና ቤቶችን በማቃጠል ያልታደለውን ፍጥረት ገና ያመነዥኩ ነበር። በተራራዎችና በአፋፎች የኢጣልያኖች መድፎች እንደ ክረምት ነጎድጓድ ይጮሃሉ። ባለ ከብቶች ከከብታቸው ጋር የሚኖርባቸው ጠፍጣፋ ሃገሮች በጉም እንደሚጋረዱ የተራራ እግሮች በመርዝ ጢስ ታፍነዋል። ከዓመት አራት ግዜ ፍሬዋን ትሰጥ የነበረች ሃገር ያለ አዝመራ ሆነች። ለመታጨድ የደረሱ አዝመራዎችን የሰለጠኑት ነጮች በእሳት ቦምብ ሲያቃጥሉት፤ ዝሆኖች አንበሶች አንደሚኖሩባት በረሃ የገበሬዎች አዝመራ ተቃጠለ። ቅጠልያ የሆነችው ሃገር ከቃጠሎው የተነሣ እንደ ነብር ቆዳ ዝንጉርጉር ሆነች። ከጠፍጣፋው ሃገር ሸሽተው በተራራ ሰዎቸ ተሰማሩ። የተሰማሩበት ጫካ ሳይቀር ተቃጠለ፤ ከነጮች የሥልጣኔ ቦምብና መርዝ የሚሸሹ የአፍሪካ ሕፃናቶች ለሊት ሲባንኑ መርዝ! መርዝ! መርዝ! እያሉ በዕንቅልፋቸው እየጮሁ ያለቅሱ ነበር። በዚህም ሁሉ ያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ለመቁረጥ ብቻ ሆነ። (ምንጭ: ሰንደቅ)
sirak says
the front page picture was city of Keren in Eritrea.
it was in late 1960.i was there.
sincerely
sirak stiphanos tesfasilasie