የአንድ አገር ችግሮች የዛሬ ሁኔታዎች የፈጠሩዋቸው ብቻ አይደሉም። እንዳውም የአብዛኞቹ ችግሮች መነሻ መሠረታቸው ዛሬ ሳይሆን፣ ትናንትና ከትናንት ወዲያ ነው። የወቅቱን ችግሮቹ አስቸጋሪና ውስብስም የሚያደርጋቸውም ይኸው ምንጫቸው ካለፉ ትውልዶች ተያይዘው መምጣታቸው ነው። የዛሬውን የአገራችን ፖለቲከኞች አብሮ ለመሥራት ቀርቶ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማሰብ ያቃታቸው የለውጥ አራማጅ ነኝ የሚለው ትውልድ ዘርቶት የሄደው «ኢትዮጵያ አገር አይደለችም፤ እንዳውም የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት፤» የሚለው አስተሳሰብ ተሸካሚ በመሆኑ ነው። በመሆኑም ዛሬ ትውልዱ ለገጠመው ሁለንተናዊ ችግር መፍትሔ ለመሻት ከልቡ ካሰበና ለዚህም ቆርጦ ከተነሳ፣ ያለፉት ትውልዶች የተከተሉትን ሕዝብን በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በማንነት የመከፋፈል አስተሳሰብና አመለካከት አውልቆ መጣልና ኢትዮጵያዊ ማንነትን መቀበል ይጠበቅበታል። ያ ትውልድ በተከተለው «እኔ ያልኩት ብቻ ትክክል ነው»፣ «እነ እገሌን የተከተልክ የአባት ጠላት ነህ»፣ «ይህኛው አመለካከት ወይም ቃላት፣ ከዚህኛው የበለጠ ነው»፣ «ይኸኛው ነገድ ጠላትህ ነው» ከሚሉት አስተሳሰቦች ራሱን ማጽዳት አለበት። ሃይማኖትና ርዕዮተዓለም-ወለድ ከሆኑ የጠላትነት ስሜቶችና አመለካከቶች መራቅ አለበት። ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያ ያሰኙ አባቶቻችን እና እናቶቻችንየተከተሉትን የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ስሜትና እምነት አድሶ መላበስ አለበት። አሁን አገራችን ከገጠሟት ችግሮች መላቀቅ እንድትችል ዓለም ከምትከተለው የአንድነትና የመቀራረብ ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ኢትዮጵያዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ትውልዱ፣ በተለይም ፖለቲከኞቹና ልሂቃኑ ሊጨብጡ ይገባል።
በኢትዮጵያ በተቀናጀ ትግል ትሕነግን* (ወያኔን) ከሥልጣን ለማስወገድ እንዳይቻል ካደረጉ ምክንያቶች ዋንኛው፣ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን የዘለቄታ መፍትሄ ለማምጣት ሳይሆን፣ እንደ ኑሮ የፊት የፊቱን ብቻ መኖራቸው እና ካለፉ ድርጊቶችና ክስተቶች ትምህርት መቅሰም አለመቻላቸውነው። በሌላ አባባል፣ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ሳይሆኑ፣ ሁኔታዎችን የሚከተሉ ናቸው። ካለፉ ስሕተቶች የሚማሩ ሳይሆኑ፣ በስሕተት ላይ ስሕተትን የሚደራርቡ ናቸው። ሂደውበት ውጤት ባላገኙበት ጎዳና ደጋግመው የሚመላለሱ ናቸው። ዛሬ በዐይናቸው ሥር የሚሠራውን ወንጀል ሳይመለከቱ፣ ባልነበሩበትና ስለአፈጻጸሙም ምን ዓይነት ትክክለኛ መረጃ በሌላቸው፣ ባለፉት አገዛዞች «ተፈጸሙ» በሚባሉ ጀሮጠገብ አሉሽ አሉሾች የተጠመዱ ናቸው። ይህ ዓይነት ጉዞ ችግር ፈቺ ሳይሆን፣ ችግር ቀፍቃፊ ነው። አንድነት ፈጣሪ ሳይሆን፣ ልዩነትን አራጋቢ ነው።
የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” የሚለው የዘወትር ፀሎት፣ ትውልዱ የዛሬን ብቻ እንዲያስብ ተጽዕኖ ያሳደረብን ይመስላል። ዓለም ላይ እስካለን እና በተለይም ራስ ወዳድ በሆኑ ሰዎች በተሞላች ዓለም ላይ እስከኖርን ድረስ ግን፣ ከአጭር ጊዜ ሕልምና ምኞት ባሻገር፣ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፈን ያን ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር እያጣጣምን ተግባራዊ ለማድረግ ካልጣርን፣ አገራችን ለገጠሟትና ሊገጥሟት ከሚችሉ ሁለንተናዊ ችግሮች ልንታደጋት አለመቻላችን የምንገኝበት ሁኔታ ያሳያል። ከዚህ መውጫው ብቸኛው አማራጭ ትናንትን መሠረትና እርሾ አድርገን፣ ለዛሬና ለነገ የሚጠቅም ሥራ በዕቅድ መሥራት ስንችል ነው። በዕለት ሁኔታዎች መገፋት፣ ዛሬን እንጂ፣ ነገን አለማሰብ፣ ለዛሬ ከጠቀመ የትናቱን ወርቅ መዳብ ነው ማለት፣ በፖለቲካው መስክ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም የሙያ ዘርፎች ይታያል። ለምሳሌ መኃንዲሶቻችንን እና አርኪቴክቶቻችን እንመልከት፤ የከተሞችን ፕላን ሲያወጡ፣ የዛሬ 50 እና 100 ዓመት የሕዝቡ ብዛት የቱን ያህል እንደሚሆን፣ ምን ዓይነት አገልግሎቶች ሊጨመሩ እንደሚችሉ፣ ከተሞቹ የቱን ያህል ሊሠፉ እንደሚችሉ አስበው ከዚያ ጋር በሚጣጣም መልኩ ሳይሆን፣ የዕለት የዕለቱና የዛሬውን ብቻ አስበው ስለሚሠሩ ከተሞቻችንን በየጊዜው ሲፈርሱና ሲገነቡ ይታያሉ። ይህ አስቦና አቅዶ ያለመሥራት አባዜ በዕድገታችንና በማኅበራዊ ሕዎታችን ላይ ተከታታይነትን በማሳጣት ሁልጊዜ ጀማሪዎች እንድንሆን አድርጎናል።
ለዚህ ዓይነቱ ስሕተት የዳረገንም፣ ልሂቃኖቻችን እና ፖለቲከኞቻችን ትናንትን ያላገናዘበ፤ ነገን ግምት ውስጥ ያላስገባ፣ ለባህላችንና ታሪካችን ተገቢ ትኩረት ያልሰጠ፣ ግብታዊ ውሣኔዎችን ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት ሲወስኑ በመኖራቸው ይኸውና ደሀውን ኢትዮጵያዊ አገር አልባ ካደረገው ሁኔታ ላይ ጥሎት ይገኛል። ይህን በምሳሌ እንይ፤
1. «በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም፤»
ባለፉት የዘመነ ትህነግ (ወያኔ) አገዛዝ ዓመታትበአንድነት ኃይሎች ለአገሪቱ ኅልውና መጠበቅ ጥያቄዎች ሲነሱ «ነፍጠኛ ሊመጣብህ ነው» እየተባለየአንድ ኅብረተሰብ ወገን «መስጊድ» እንደገባች ውሻ ሲካለብ፣ ሲገደልና ሲፈናቀል ብሔርተኛ ፖለቲከኞችና ቆምንለት የሚሉት ነገዶች ምንም ነገር እንዳልተፈጸመ በቸልታ ያዩ እንደነበር እናስታውሳለን። እነሆ! አሁን ደግሞ በተራው ብሔርተኛው በብሔርተኛውና ዘረኛው ወያኔ አገዛዝ ላይአምፆ ሲነሳ፣ «ኦነግ ሊመጣብህ ነው፣ ሊያርድህ ነው፣ ሊያጠፋህ ነው፣» ተብሎ «ዝመቱበት» የሚል ጥሪ ከወያኔ ሠፈር ሲዘመርና ልምጭ ባልያዙ ልጆች ላይ መትረየስ ሲያዘንብ፣ በተመሣሣይ ሁኔታ የአንድነት ጎራውና መሰል የኅብረተሰቡ ክፍል በተራው እንዳለፉት የጥፋቱ ተባባሪ ባይሆንም፣ ዝምታን መርጧል። «በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም» ማለት ይኽ ነው። የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በየተራ ወያኔ ነጣጥሎ ብቻ ሳይሆን፣ አንዱን የሌላው የአባት ደመኛ አድርጎ እየሳለ ርስ በርሳቸው እንዲጠፋፉና በየተራ ቁና ሰፋሪዎች እንዲሆኑ ማድረጉን እያየን ነው። በሁለቱም አመፆች የደሃ ልጅ ደም በከንቱ ፈሰሰ። መቼም መነጋገር እና መደማመጥ የማይፈልጉት ልሂቃን እና ፖለቲከኞች ዛሬም የደሀው ልጆች ደም እንደጎርፍ ሲፈስ እያዩ፣ ነገሮችን ቁጭ ብለው ተወያይተው አዋጭ የሆነ የጋራ ራዕይና ተልዕኮ ይዘው ለመውጣት ሲጥሩ አይታዩም። አሁንም ነገሮችን አቻችለው ወደ ሰላም ከመምጣት ይልቅ፣ «እኔ ያልኩት ብቻ ነው ልክ» በሚል በተለያየ ጎራ እንደቀጠሉ ናቸው። በመሃል ተጠቃሚው ደግሞ ትሕነግ (ወያኔ) እና አጋሮቹ ናቸው። ሌሎቹ እርስ በእርስ ሲጋጩ ትሕነግ በሥልጣን ላይ ቆይቶ የመዝረፍያ ዕድሜውን ያራዝማል። በሌላ በኩል የተቃውሞው ጎራ አንድነትና ኅብረት በማጣቱ የተነሳ፣ ሥሩ የነገለውን፣ ቅርንጫፉ የተኮማተረውንና የሚይዘውና የሚጨብጠው ጠፍቶት እንደገበታ ውኃ የሚዋልለውን ወያኔን የሚገፋው አጥቶ የአጥፍቶ መጥፋት ፖሊሲውን በማን አለብኝነት ሲገፋበት እያዬን ነው።
በቅጡ ሳይደራጁና የተቀናጀ የትግል ሥልት ሳይነድፉ፣ ሕዝብን ለአማጽ ማነሳሳት የቱን ያህል ዋጋ አስከፋይና በሕዝብ ሥነ-ልቦና ላይ ጥሎት የሚያልፈው የተሸናፊነት ስሜት ምን ያህል ጥልቅ መሆኑን ካለፉት ስሕተቶቻችን ተምረን፣ ቀጣዩን አካሄድ መስመር ለማስያዝ ቅድመ-ዝግጅት አለማድረጋችንን ትውልዱ ካለፉት ስሕተቶች ያለመማሩን ነቃሽ ነው። እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በያካባቢው የሚነሱትን ትንንሽ ተቃውሞዎችን ለጊዜው እንተወውና፣ እስቲ በየአሥር ዓመታቱ የተካሄዱትን እና በርካታ የደሀ ልጆች ደም አፍስሰው ያለፉትን የ1997 ዓ.ም. እና የ2008ዓ.ም.ን ሕዝባዊ አመፆች እንመልከት።
ከ1997ዓ.ም.ብሔራዊ ምርጫ በኋላ እንዳስተዋልነው፣ ትሕነግ (ወያኔ) ሥልጣን በምርጫ አልለቅም ብሎ ሕዝባዊ አመጽ መቀስቀሱ ይታወሳል። ያኔ ሁሉም ድርጅቶች ቀድመው መክረው ቢሆን ኖሮ፣ ትሕነግ ዕድሜው ባጠረ ነበረ፤ ሆኖም ግን የውስጥ ባንዳዎችን እነ ልደቱ አያሌውን እንተውና፣ ዶ/ር መራራም ይሁን ዶ/ር በየነ እነኚህ «የድሮ ሥርዓት ሊያመጡብን ነው» ብለው ከትሕነግ ጋር በመወገናቸው ወያኔ ለከፈተውፕሮፓጋንዳ ሠፊ ቦታ እንዲያገኝ ስላደረጉት፣ ምዕራቡና ደቡቡ ኢትዮጵያ ባብዛኛው ቦታ ዝምታን መረጠ። መሃሉ፣ ሰሜኑ እና አብዛኛው ትልልቅ ከተሞች ቢንቀሳቀሱም አጋዥ አልነበረውም። በዚህም ምክንያት ትሕነግ ሁለት የተከፋፈለ ጎራን ስላገኘ አጋጣሚውን ተጠቅሞ አመፁን እንዲኮላሽ አደረገ። የሚያሳዝነው ትንሽ ቆይቶ ስለ መጀመሪያው «ድምፅ ተጭበርብሯል፣ አልተጭበረበረም፣» የሚለው ቀርቶ፣ «ስንት ሰው ሞተ? ስንት ታሰረ?» ወደሚለው ክርክር ተገባ። «የታሰሩት እስረኞች ይለቀቁ» የሚለው ዋናው ጉዳይ ሆኖ ቀረበ። ያኔ ለምን ይሄ ክፍፍል ተፈጠረ? ይህ ዓይነት ክፍፍል ወደፊት እንዳይከሰት ምን ማድረግ አለብን? ትሕነግ ሥልጣኑን እንዲለቅ በምን መልክ ማስገደድ ይቻላል? ተብሎ ሳይመከር፣ አገር አቀፍ ምክክር ሳይደረግና ስምምነት ሳይኖርይህ የሰሞኑ ሠፊ አመጽ ተከሰተ። አለመስማማት አንድ ነገር ነው። ግን ሁሉም ያልተስማማበትንና ለመስማማትም ያላስቻሏቸውን ነገሮች በግልጽ ለሕዝቡ በማሳወቅ፣ ሕዝቡ የችግሩ ብቻ ሳይሆን፣ የመፍትሔውም አካል እንዲሆን ማድረግ ይጠብቅባቸው ነበር። ይህ ሳይሆን፣ በነባራዊ ሁኔታዎች ግፊት ሕዝቡ በራሱ ብሶት አዲስ አመጽ ሲነሳ፣ ግልፅ ባልሆነ መልኩ «አብረን ለመሥራት ተስማምተናል» የሚል ማጭበርበሪያ መግለጫ ማውጣት ለትግሉም ሆነ ለታጋዩ የሚጠቅም አይደለም። የማይስማሙ ከሆነ አይስማሙም፤ ሁሉም ባፈተተው ይቀጥል፤ ሕዝብ «የተሻለ ነው» ላለው ድጋፉን ይስጥ፣ የሕዝብ ድጋፍና አመኔታ ያለው ምንጊዜም አሸናፊ መሆኑ ዕውነት ነው።
በ2008 ዓ.ም.ደግሞ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በመቃወም የኦሮሞ ተወላጆችና «የኦሮሞ ክልል» ተብሎ በተከለለው በሚገኙ የትምህርት ተቋሞች የሚማሩ ተማሪዎች፣ በፖለቲካ ድርጅቶች አነሳሽነት ሕዝባዊ ሊባል የሚችል አመጽ ቀሰቀሱ። ተቃውሞው ካለፉት ሁሉ የተለየና በጣም የተቀናጀ ተቃውም ታይቷል። ነገሩ እሰየው የሚያስብል ነው። ሁሉንም የሚያሰባስብ ቢሆን ኖሮ ደግሞ የበለጠ የተዋጣለት በሆነ ነበር። ምክንያቱም አንድነት ኃይልና ጥንካሬ በመሆኑ፣ ዋናውን የችግራችን አውራ፣ ወያኔን አሽቀንጥሮ ለመጣል ያስችለን ነበርና ነው። ነገር ግን እኔንም ጨምሮ እንደሚሰማኝ አመፁ “ኦሮሚያ” ብለው ከትሕነግ ጋር የከለልነው “የኦሮሞ ብቻ ነው” የሚል ድምዳሜ ያለው አመጽ ስለሆነ እና ለሌላው ኢትዮጵያዊ ሥጋትን አመልካች በመሆኑ፣ በ1997 ዓ.ም. ለአማጽ የተነሳው ሕዝብ የአመጹ ተካፋይነቱን ትቶ በተራውእንቅስቃሴውን በልዩ አትኩሮት መከታተልን መረጠ። ይህ ደግሞ ለወያኔ መልካም አጋጣሚ ፈጠረ። ወያኔ እንኳን ሕዝቡ ራሱ ተከፋፍሎለት፣ ዓላማው መከፋፈል ነውና ሁኔታውን ራሱን በሚጠቅም መልኩ አመፁን ወደማስቆም ደረጃ እየገፋው እንዳለ እናያለን። የሚያሳዝነው ዛሬም የአመጹ ታላቁ ግብ ወያኔን ማስወገድ መሆኑ ይዘነጋና ክርክሩ በታሰሩት እና በሞቱት ሰዎች ቁጥር ማነስና መብዛት፣ እንዲሁም «የሞተው የገሌ ነገድ ነው የገሌ» ወደሚለው እንዳይዞር እሰጋለሁ።
ከዋናው ጉዳይ ወጥተን፣ አመጹ የተነሳበት ጉዳይ ይድበሰበስና የታሰሩት ይፈቱ ወደሚል ክርክር እንዳንዘቅጥ አፈራለሁ። የፍራቻየ ምንጩ፣ በተለያዩቡድኖች ውስጥያሉ ፖለቲከኞች እና ልሂቃኖች ለመደራደር ዝግጁ ሳይሆኑ፣ ዛሬም የራሳቸውን እና የደጋፊዋቻቸውን ድምፅ ብቻ እንደገደል ማሚቶ እየሰሙ ነገሩ ሁሉ ባለህበት ሂድ እየሆነ በማየቴ ነው። ለዘላቂ መፍትሔ የሚሆን አመርቂ ሥራ እስካሁንሲሠራ አላየሁምና። እያንዳንዱ ሕዝባዊ አመጽ ግቡ የደሃ ልጅ ማስጨረስ ሳይሆን፣ የአገርና የሕዝብ ጠላት የሆነውን ወያኔ የጨበጠውን የፖለቲካ ሥልጣን ፈልቅቆ የሕዝብ ማድረግ መሆን አለበት። ከዚህ ባለፈ እንዳለፉት ሁሉ የደሀ ልጆችን አስጨፍጭፎ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ስኩዬር አንድ ተመልሶ ዜሮ ወደ ሆነ የፖለቲካ ጨዋታ ልንወጣ ግድ ይለናል።
ታዲያ መቼ ነው ከጥፋታችን የምንማረው እና አንድነታችን መልሰን የምንጨብጠው? የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውን ዜጎች እስከ መቼ ነው በጠላትነት ፈርጀን የምናቆማቸው? እየጨቆኑን ብቻ ሳይሆን፣ እያጠፉን ያሉትን፣ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው የሚያጠራጥሩ ዘረኞችን እስከ መቼ ነው ተሸክመን የምንኖረው? እንዴትና በምንስ ሁኔታ ነው ወደፊት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት እና በሰላም በአገሩ መኖር የሚቻለው? ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ብዙ ምርምር የሚጠይቁ አይደሉም። የሚጠይቁት የፖለቲከኞቻችንና የልሂቃኑን ቅን ልቦናና ኢትዮጵያዊ ሆኖ ማሰብን ብቻ ነው። ምክንያቱም ሕዝባችን ለዘመናት ድንበር ሳይኖረው፣ ማነህ? የት ትሄዳለህ? ዘርህ ምንድን ነው? ሳይባል ተቀላቅሎ፣ ተዋልዶና ተዋዶ የኖረ ነው። ለዚህ ሕዝብ የቋንቋ ድንበር አበጃለሁ ማለት ውኃና ወተትን ቀላቅየ እለያለሁ እንደማለት ነው። ትንሽ ጊዜ ጣልያን ከኢትዮጵያ ለይቶ የገዛት ድንበር አለኝ የምትለው «ኤርትራ» እንኳን በተነሳው የድንበር ግጭት ስንት ደም እንደፈሰሰ ቤቱ ይቁጠረው። ወደፊትም በአሁኑ ወያኔ-ሠራሽ በሆነው የቋንቋ ድንበር ሕዝባችን እንዲከለል ከፈቀድን የደሃ ልጅ ደም እንደጎርፍ በማያባራ መልኩ የሚፈስ መሆኑን መናገር ክፉ አሳቢነት አይሆንም።
2. «ካልደፈረሰ አይጠራም»
አንዳንድ ድርጅቶች ትብብር፣ ኅብረት፣ ቅንጅት፣ ጥምረት፣ ግንባር፣ ውኅደትና አንድነት የሚሉትን ጽንሰ ሀሳቦች ትርጉምና በእያንዳንዳቸው የግንኙነት ቅርጾች ውስጥ ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ ለይተው ሳያውቁ፣ ስለስምምነትና በአንድነት ስለመሥራት አስፈላጊነት ሲሰብኩ ይሰማሉ። ልንስማማባቸው ስለሚችሉ ጉዳዮች፣ ስለመስማማቱ አስፈላጊነት በግልፅ ንግግር ተደርጎ ሁሉንም አስገዳጅ ወደ ሆነ ውልና ግዴታ ሳይገባ፤ በጣም ወሳኝ በሆኑ አቋሞች ማለትም በመንግሥት ቅርጽ፣ በቋንቋ አጠቃቀም፣ በነገዶች ጥቅምና መብት፣ ስለዕኩልነትና ነፃነት፣ ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖት አጠቃቀም ላይ የወል ስምምነት ሳይኖር፣ በምን መልኩ አገሪቱን ለማስተዳደር እንደሚያስቡ ለተከታዮቻቸውም ለሕዝቡም ሳያሳውቁ «ጨቋኙን አገዛዝ ለመጣል እንተባበር» የሚለው ጥሪ «እባብ ያዬ በልጥ በረየ» ነውና ከትህነግና ከኦነግ ትብብር ትምህርት የወሰድን አይመስልም።
“ጨቋኙም”፤ “ተጨቋኙም” ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ዕውነት ነው። ታዲያ ይህን ዘረኛ አገዛዝ በምን ዓይነት መንገድ አስወግደን፣ ኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሟን፣ ሉዐላዊነቷን፣ ታሪኳን፣ ባህሏን፣ የነፃነትና ተጋድሎዋን ሊያስጠብቅና ሊያስከብር በሚችል መልካም አስተዳደር እና አብሮ መኖር የሚቻልበት ሁኔታ ምክክር ተደርጎ ከጋራ ስምምነት ላይ ሳይደረስ፣ በጋራ እንታገላለን ማለት «ተጨፈኑ ላሞኛችሁ» ዓይነት ጥሪ ነው የሚመስለው። ነገዳቸውን እንደ አንድ ሠራዊት አሰልፈው፣ ባንድ ጠቅላይ አዛዥ እንዲመራ ያደረጉ ወገኖች፣ ያልተደራጁትንና የተበታተኑትን «የሥልጣን መወጣጫ እርካብ ሁኑን፣ የናንተን ዕጣ ፈንታ ኋላ እንወስናለን» የሚሉ ወገኖች «ከወያኔና ከኦነግ ትብብር» ትምህርት ያልቀሰሙ የዋሆች ይመስላሉ። የሰው ልጅ ሊሞኝ ወይም ሊታለል የሚችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ሰው ካንድ ጊዜ በላይ ከተታለለ ሰው ሳይሆን ከብት ነው። በዚህ ጉዳይ ዐማራው ከበቂ በላይ ተሞኝቷል። የተተኪውን ማንነትና ምንነት በውል ሳያውቅና ሳይደራጅ፣ «ደርግ ይውደቅ እንጂ የፈለገው ይሁን» ለሚሉ ብልጣብልጦች ተበልጦ ችግሩ ከእሣት ወደ እረመጥ ኑሮ፣ ከመቸገር አልፎ መኖሪያ ቦታ የማጣት፣ የመኖሪያ ቦታ ከማጣት እንደሰው የመቆጠር መብት ካጣበትና በሕይዎት የመኖር ሰብአዊ መብቱን ከተገፈፈበት ደረጃ ላይ ደርሶ እያየን ነው። ስለሆነም አስቀድሞ ግቡና ዓላማው ላልታወቀ የ«እንተባበር»ና የ«አንድ እንሁን» ጥሪ፣ ዐማራው ለጥሪው ያለው አቋም አዎንታዊ ቢሆንም፣ ነገን አሻግሮ ማየት የሚችልበት የአኗኗርና የአስተዳደር ሁኔታ ምን መልክ እንዳለው ሳያውቅ፣ ሂደቱን በአንክሮ ከመከታተል ውጪ የጥሪው ግንባር ቀደም ተሰላፊ ሊሆን ያለፉት ድርጊቶች የሚጋብዙት አለመሆናቸው በቅጡ ሊታወቁ ይገባል። «ግድ የለም፣ ሰላም ይመጣል፣» በሚል «ልጆቻችሁን በሰላም ታሳድጋላችሁ» ተብሎ ገበሬው የተሻለ ነገር የሚመጣ አስመስለው ለባሰ እልቂት የተዳረገው የአማራ ህዝብ ምን ያህል ከዚህ በኋላ ነፃ እናወጣሃለን የሚሉትን ድርጅቶች በጥርጣሬ ዓይን እንደሚመለከታቸው ማስታወስ ተገቢ ነው።
አገር አጥፊው የኤህነግ (ሻዕቢያ) ቡድን በአንድነት ኃይሉ መከፋፈል፣ በምዕራባዊያን የቆየ ሤራ ተዳክሞ፣ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ መገንጠሏ የዘመናችን አሳፋሪው ድርጊት መሆኑ ዕውነት ነው።ይህን አሳፋሪ ድርጊት እንደ ጀግንነት በመቁጠር፣ «ኤህነግን (ሻዕቢያን) አትንኩብን»፣ «ጥፋቱን አታንሱብን» የሚሉ ፖለቲከኞች በጣም ይገርሙኛል። «የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም» እና የኢትዮጵያ ችግር በተነሳ ቁጥር ሻዕቢያ መነሳቱ የማይቀር መሆኑን እነዚህ ፖለቲከኞች ሊያውቁት ይገባል። የችግሮቻችን ቋጠሮ ሁሉ ኤህነግ ነውና! የትህነግ (ወያኔ) ፈጣሪ ማን ሆኖ፣ ኤህነግ (ሻዕቢያ) ለኢትዮጵያ፣ ከሁሉም በላይ ለዐማራ ቅን ነገር ያስባል ብሎ ማንያምናል?
አሁን ሌላ ብዙ የቤት ሥራ ስላለብን፣ ቅድሚያ የምንሰጣቸው ባይሆኑም፣ ይሄንን የቤት ሥራ እንዲኖረን ያደረገን ሻዕቢያነውና፣ አሁንም ሆነ ነገ፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ሰላም ሆና ማየት ከማይፈልጉት መካከል፣ እንደ ግብፅ ወይንም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሻዕቢያ አንዱና ቀንደኛ ጠላታችን መሆናቸውን ዐማራ ነኝ የሚለው ሁሉ ማወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። ዐማራ የሆኑ የቀድሞ ወታደሮችን ለይተው መረሸናቸውን፤ «ዐማራ ነው ለዚህ ሁሉ ጦርነት ተጠያቂ» ብለው ባንዳ አማራዎችን አስመልምለው ይቅርታ ማስጠየቃቸውን ወዘተ ዐማራ ነን የምንል ሁሉ እንደማንረሳ ለኅሊናችን ቃል ልንገባ ይገባል። ለዘር ጥፋትና ለዘር ጽዳት የዳረገን አውራ ጠላታችን ኤህነግ (ሻዕቢያ) ነው።
ሌላው ሰዎችን ለማሞኘት ከሚደረጉጥረቶች መካከል አንዱ፣ ሰሞኑን “ኦሮሞ ክልል” ተብሎ የተከለለው ክልል «የኦሮሞ ብቻ ነው» ከሚሉ ጋር ተሰለፉ የሚሉ የዋሆች መበራከት ነው። እሺ የተነሳሁበትም ስለሆነ እና ተነጋግረን መፍትሄ መፈለግ አለብን ብዬ ስለማምን አዎን ከሁሉም ፖለቲከኞች ጋር መነጋገር አለብን። ነገር ግን ጃዋር ትናንት “Ethiopia out of Oromia”፤ “ኢትዮጵያ ከ”ኦሮሚያ” ትውጣ” እንዳላለ ማስተባበያ እንኳን ሳይሰጥ፣ የሀሳብ ለውጥ ሳያደርግ፣ ይህንም በይፋ ሳያሳውቅ፣ እርሱና መሰሎቹ ለሚመሩት አመጽ «ኢትዮጵያዊያን በትግላችን ውስጥ ተቀላቀሉ ብለዋልና እንተባበር» እያሉ አታሞ የሚመቱ ቡድኖችና ግለሰቦች «ተጨፈኑ እናሞኛችሁ» የሚሉ ዓይነቶች ሆነው ታይተውኛል። በተመሳሳይ ወንጀለኛው ሌንጮ ለታም ድሮውኑ በዐማራ ደም የተጨማለቀው እጁን በንስሃ ሳያጸዳና ይቅርታም ሳይጠይቅ፣ እንዲሁ የአገራችን አውራ ችግር የሆነው ሕገ-መንግሥት «እኔ ያልኩት ትንሽ ማስተካከያ ተደርጎበት ነው የፀደቀው» እያለ ስላሰመረው የአፓርታይድ ክልል ሳይጠየቅ፣ ሌሎች ባልተወከሉበት «ጸደቀ» የተባለውን ሕገመንግሥት «መሻር አለበት» ሳይል፣ ያንኑ ተቀብለን ትህነግን (ወያኔን) ብቻ አጣጥሉን ለሚለው ጥሪው ምን ዓይነት ኅሊና ያለው ሰው አቤት ሊለው ይችላል? እንዴትስ ሌላው እንዲቀበል ይጠብቃሉ? ሳይበደሉ በደላችሁን ብለው የትህነግ እጄታና ዛብ ሆነው የጥፋት ዘመቻ ከከፈቱብን ቡድኖች ጋር «በደላችሁን በሆዳችሁ ይዛችሁ፣ ችግሩንንና በደሉን ረስታችሁ፣ የነሌንጮ ለታንጥሪ ተቀበሉ» የሚሉን ወገኖች «በቁስላችሁ ላይ ጨው እንነስንስበት» ያሉንን ያህል የሚሰማን መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። ሕዝባችንግን የሚበጀውን ከማወቅ አልፎ ጨዋና አስተዋይ ከመሆኑ የተነሳ፣ ድርጊቱን በጥንቃቄ ከመከታተል ውጭ የጥፋቱ ተባባሪ አልሆነም። ያውም ኦሮሞዎቹ «አስነሳነውና መራነው» በሚሉት አመጽ ዋና ተጎጂ ሆኖ እያለ፣ የዛሬውንም የትናንቱንም ድርጊቶች እያወቀ፣ በኦሮሞ ስም የተደራጁ ድርጅቶች ከትህነግ ጋር ወግነው የገደሉት፣ ያሠሩት፣ የዘረፉት፣ ካገር ያባረሩትን ቂም ሳይዝ፣ የትናንቱ ወዳጃቸው ወያኔ በነርሱ ላይ የጥፋት እጁን ሲያነሳ፣ ዐማራው ተባባሪ ሆኖ አለመቆሙ የታላቅነቱ ምልክት ነው። ዐማራው አርቆ ተመልካች፣ ለትውልድና ለነገ የሚያስብ መሆኑ ከዚህ የተሻላ ማሳያ የለም።
3. «ጉድ አንድ ሰሞን ነው» አልለቅ አለን!!!
እስቲ በቅርብ አመታት ብቻ በተለይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ያነሳቸውንና ጉድ አንድ ሰሞን ነው የሚባለው አይነት ነገር ሆኖ ደግመን የማናነሳቸውን ሁኔታዎች እንመልከት።
በመጀመሪያ ከላይ እንዳልኩት ስንቶች ሕይወታቸውን እስኪያጡ ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሳይወከል በቋንቋ መስፈርትነት ብቻ የተሰመረ የድንብሮች አከላል አይሠራም ተብሎ ተጮኸ። የሚያሳዝነው፣ ያንን ባደባባይ የተቃወሙ ሰዎችና ድርጅቶች «ይሄ ማለት እኮ በቃ ካንዱ ወዳንዱ “ክልል” ስንሄድ ፓስፖርት አምጡ ልንባል ነው፣» ያሉ ሰዎች ጭምር ምንም እንዳልተናገሩ የተቃወሙትንና የተፉትን መልሶ እንደመዋጥ በሚያስቆጥር መልኩ፣ “አማራ ክልል”፤“ኦሮሞ ክልል”፤“ትግሬ ክልል” ወዘተ እያሉ ሲጠሩና ሲጽፉ እናያለን። ይህያሳዝናል፤ ያስተዛዝባልም። ልቡና ይስጣቸው ከማለት ውጪ ምን ማለትስ ይቻላል?ወደ ትፋቱ የሚመለስ ውሻ እንጂ፣ ሰው አለመሆኑ ይታወቃል።
ስለኤርትራና ስለ ሻቢዕቢያ ስንት እንዳልተባለ፤ ጠላትነታቸውን ያደረሱብንን በደል በግልፅ ያየነውን ደጋግመው እንዳልነገሩን ሁሉ፣ “ኤርትራ” የተባለችው የኢትዮጵያ ግዛት/አካል መገንጠልዋ አልበቃ ብሎ፣ በኢትዮጵያ ላይ ስንት ሸፍጥ እንደተሠራ እያወቅን፤ የድርጅቱን መሪ ሲያሞካሹልን፤ ትግላቸው ትክክል እንደነበር ሌላም ሌላም ሲነገረን መስማት ያማል። ኤህነግ (ሻዕቢያ) እና ትህነግ (ወያኔ) ዛሬ የሰረቁትን ሲከፋፈሉ ቢጣሉም፣ የአንድ ሳንቲም ግልባጭ መሆናቸውን እያወቅን፣ ኤህነግ የትህነግ ፈጣሪ እንደሆነ እያወቅን፣ በቅሎ ወለደች፤ ሸንበቆ አፈራ፤ ዝንብ ማር ጋገረች እያሉ ያወሩናል። እንግዲህ እነሱስ እሺ ኅሊናቸውን ይሳቱ፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን አያስተውልም ብለው ላሞኝህ ማለታቸው ግን ትልቅ ስሕተት ነው። ጠላቶቻችንን እናውቃለን፤ በቅደም ተከተልም አንደኛ ሁለተኛ ሶስተኛ እያልን ማን እንደሆኑ በደንብ እናውቃለን እና ልታሞኙን ብትሞክሩ ሞኞቹ እናንተ እንጂ፣ እኛ ለዳግም ሞኝነት አልተዘጋጀንምና አትልፉ ልንላችሁ እንወዳለን። ከንቱ ልፋታችሁ ያሳዝነናል!
እስቲ ደሞ ወደ «እስረኞች ይፈቱልን» ጩኸት ልመለስ። ይሄንን በተመለከተማ የታሰሩትን ሳስብ ያመኛል። ልቤ ይደማል። ትህነግም ድክመታችንን ስለሚያውቅ በየቀኑ አዲስ የቤት ሥራ እየሰጠ፣ በፊት የነበሩ አንገብጋቢ እና ወሳኝ ጉዳዮችንያስረሳናል። እስቲ እነ እስክንድር ነጋን፣ እነ አንዱአለም አራጌን ወይንም ሌሎች በእስር ቤት ያሉ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞች አስቡዋቸው። አንድ ሰሞን ይፈቱ! ይፈቱ! የሚል ጩኸት ነበር። ይህ ጩኸት ሲበረክት ትህነግ ሌላ አጀንዳ ሰጠን። እኛም የጨበጥነውን ለቀን፣ አዲስ በተሰጠን ሌላ አጀንዳ እንጮኻለን። እንደዚህ እያለ የጨበጥነውን እየለቀቅን፣ ትህነግ በሚሰጠን አጀንዳ ላይ ለፍሬ ያልበቃ ጩኸት ስንጮህ ይኸውና 25 ዓመታት ተቆጠረ። መቼ ነው በራሳችን አጀንዳ መጮህና ለፍሬ የምናበቃው? መቼ ነው የቀደመውንና የአሁኑን አቀናጅተን በአንድ ላይ መጮህና መታገል የምንጀመረው? እስቲ «አንዳርጋቸው ፅጌ ይፈታ» በሚል አንድ ሰሞን በዓለም ዙሪያ የነበረውን አስቡትና አሁን ደግሞ ስሙም የተረሳ በሚመስል መልኩ የይፈታው ጩኸት ደብዛው በመጥፋት ላይ ነው። ይህ የሚያሳየው ፖለቲከኞቻችን የራሳቸው አጀንዳ የሌላቸው፣ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ሳይሆኑ፣ ሁኔታዎች የሚገዙዋቸው፣ አልፎ አልፎምወረት የተጠናወታቸው ይመስላል። ሕዝቡም ለእሱ ብለው ሕይዎታቸውን የሰዉትን ብቻ ሳይሆን፣ በሕይዎት በእስር እየማቀቁ ያሉትንም ዘንግቶ የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን ብቻ በማንሳት ዘላቂ ነገር ሳያመጣ ንፁሃንን እያስበላ ማለፍን ባህሉ እያደረገው መምጣቱን የሚሳይ ነው። እንዲህ የተዘነጉ ክስተቶችን እና በከንቱ ደማቸው ፈሶ የቀረውን ኢትዮጵያዊያን ዘርዝሬ አልጨርሰውም። ሆኖም ግን ምንም የተቀናጀ ነገር እንደሌለን ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው። ይህን አባባል ኦስካር ዴቭስ እንዲህ ይገልጸዋል፤
“While in prison, your greater fear is being forgotten by those whom you have fought for and gave up your own freedom to defend their right” by Oscar Daves.
ሌላው ቢቀር አሁን በረሃብ እየተጠበሱና እያለቁ ስላሉ ወገኖቻችን እንኳን ለራባቸው ልንደርስ፣ ችግራቸውን ለማሰማት የተባበረ ጥረት ስናደርግ አይታይም። በቃ እነ ትህነግ በየጊዜው ትኩስ ዜና እየፈጠሩልን ስለ አዲስ ክስተቱ ብቻ እየተወዛገብን በፊት የተከሰተውን አሁን ካለው ሁኔታ ጋር አገናኝቶ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ማሰብ ተስኖናል። ይሄ ነገር ሳይቀየር፣ አገር ሰላም ሆና እኩልነት የሰፈነባት ሀገር ይኖረናል ማለት ዘበት ነው። ሰከን ባለ አእምሮ አስበን፤ የተቀናጀ ዘላቂ መፍትሄ ሰንቀን ትህነግን (ወያኔን) ለማውረድ ቁርጠኛ አቋም ይዘን በተደራጀ መልክ መንቀሳቀስ ካልጀመርን በስተቀር፤ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አውራ ጠላት የሆነው ትህነግ (ወያኔ)፣ ለረጅም ጊዜ የተውጠነጠነ ድክመታችንን ግምት ውስጥ ያስገባ እቅድ አንግቦ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፣ እየፈራነው ያለው የአገራችን ከመኖር ወደ አለመኖር የቁልቁለት ጉዞ እኛው ራሳችን እያፋጠነው መሆኑመታወቅ አለበት።
4. «የነቶሎቶሎ ቤት ግርግዳው ሰንበሌጥ»
ሁላችንም እንደምንገነዘበው፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ኢሕአፓ ከፍተኛ የሆነውን ሕዝብ ስሜት ተቆጣጥሮ እንደነበር እናስታውሳለን። ለድል ግን ሲበቃ አላየንም። ለዚህም ያበቃው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በሚመለከት የጠራና በሐቅ ላይ የተመሠረት ዓላማ አለመያዝ፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ መሆኑንና ኢትዮጵያን እንደአገር ሳይሆን፣ «የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት» ብሎ ማመኑና በእስር ላይ የሚገኙት ነገዶች ባፈተታቸው መንገድ የታሰሩበትን ቤት አፍርሰው የየራሳቸውን ጎጆ እንዲቀልሱ የሰጠው ዕውቅና አንዱና ዋናው ነው። ከዚህ በተጨማሪ በቂ የትጥቅ ትግል አራማጅ ኃይል ሳያዘጋጅ፤ አመራሩ ወጥ አመለካከት ሳይገነባ፣ በጨበጣ የፖለቲካ ሥልጣን ለመጨበጥ የወሰደው የከተማ ውስጥ ትጥቅ ትግል «ጠላቴ ናቸው» ባላቸው ኃይሎች የተሰነዘረበትን የመልስ ምት መመከት አለመቻሉ እንደሆነ ይታወቃል። በአጠቃላይ ሁለንተናዊ አቅም ሳይገነባ፣ «በቶሎ ጥይትተኩሳችሁ አሳዩን ወይንም ልንተኩስ ነው፣ ዝግጅት ጨርሰናል ባጭር ጊዜ ውስጥ ሥልጣን እንረከባለን» የሚል ተስፋን በወጣቱ ኅሊና ውሰጥ በክራር በተቀነባበረ ቅስቀሳ በማሰራጨት፣ ያሉትን አምኖ በርሃ ለገባው ወጣትና ጎልማስ ያሉትን ሆነው አለመገኘት፣ ለድርጅቱ በትግል ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ ሐቅ ነው። ድርጅቶች መወጣት የማይችሉትን ቃል መግባት እና ያን ቃልሳይፈጽሙ መቅረት በሕዝቡ ሥነልቦና ውስጥ በቀላሉ ሊሽር የማይችል የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊከት መቻሉን፣ ሕዝባችን የሚገኝበት ተበታትኖ ለጠላት ምት የተጋለጠበት ሁኔታ ያሳያል።
እስቲ ግንቦት 7ን አስቡት። «በቃ 6 ወር ነው፣ ዓመት ነው፣ ተደራጅተናል ወያኔን እንጥላለን» ሲሉን አመታት አለፉ። «ይሄንን ያህል ሠራዊት አሰልጥነን፣ ዝግጅት ጨርሰናል፣ ውጊያ ጀምረናል» እያሉ በተቆጣጠሩት ራዲዮና ቴሌቪዥን ይነግሩናል። በተጨባጭ ግን የምናየው አለን የሚሉት «ሠራዊት» ከነመሪው ለትህነግ(ወያኔ) እጁን ሲሰጥ ነው። የዚህ ሁሉ ውድቀት ምክንያቱ እታገላለሁ የሚለው ኃይል በተቀናጀና በተጠና፣ የአብዛኛውን ለውጥ ፈላጊ ፍላጎትን እምነት ያማከለ ሥራ አለመሠራት ውጤት ነው። አስቦ፣ ጊዜ ወስዶ፣ ተጨንቆና ተማክሮ ከመስራት ይልቅ፣ የይድረስ ይድረስ፣ በአቋራጭ ለድል ለመብቃት በተወሰኑ ሰዎች ፍላጎት ላይ በመንጠልጠል ርቆ የተሰቀለውን ዳቦ ያለመሰላል ለማውረድ ስለምንጣደፍ ነው። ድርጅቶች እንደዚህ ወደተጣደፈ ተግባር የሚገቡትም ወደው እንዳልሆነ ይታወቃል። ደጋፊዎቻቸው እንዲህ እንዲሠሩ ይገፋፉዋቸዋል። የሕዝቡንና የደጋፊዎቻቸውን ስሜት ለመጠበቅ ሲሉ፣ የማይችሉትን ቃል በመግባት፣ ለጊዜውም ቢሆን ደጋፊዎቻቸን ከጎናቸው ለማሰለፍ ለተወሰነ ወቅት ጫጫታ ከጎናቸው ያቆማሉ። ይህ ደግሞ ለትህነግ የመከፋፈል ዓላማ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር «ተቃዋሚ ነኝ» ያለውን ራሱን በራሱ እያናካሱ እንዲገዙ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ምክንያቱም ድርጅቱ ሳይጠናከር፣ በስሜት ብቻ የተቀላቀሉትን ለይቶ ለማጥቃት ይመቻልና ነው። እስቲ ወደ ኋላ ዞር ብለን እናስብ፤ በዕውነት ከምር አስቡት፤በግልጽ መሬት ይዞ፣ እዚህ ቦታ ውጊያ አካሄደ ሳንባል፣ ኃይል እጠቀማለው ስላለ ብቻ፣ የግንቦት 7 አሸባሪ አባላት ተብለው ስንቶቹ የአሸባሪ ታፔላ ተለጥፎባቸው ተገደሉ? ለዕድሜ ልክ እስር ቤት ተዳረጉ። ስለዚህ ምናለ፣ መጀመሪያ ሕዝቡን አንድ ባይሆን እንኳን፣ አብዛኛውን የሚያቀራርብ ሃሳብ ላይ ተመሥርቶና ተመክሮ ወደሚያስማው ሃሳብ የማይመጡትም በግልጽ አቋማቸውን አሳውቀው በራሳቸው መንገድ እንዲጓዙ መፍቀድ። በአብዛኛው የሚያሰባስበውን ሀሳብ የሚያራምዱ የትግሉ ተመክሮ፣ የዓላማ ጽናት፣ ሐቀኝነትና ታታሪነት ያላቸውን ሰዎች ወደፊት አውጥቶ፣ ቀሪው በነርሱ ዙሪያ እንዲሰባሰብና የሚችለውን እንደአቅሙና ችሎታው ለትግሉ አስተዋጽዖ የሚያደርግበትን ስልት ነድፎ መንቀሳቀስ ይደር የሚባል መሆን የለበትም ባይ ነኝ። ይገባኛል፣ ለትህነግ (ወያኔ) አንድም ቀን መጨመር የኢትዮጵያን ጥፋት ከድጡ ወደማጡ እንደሚያስኬድ፤ ግን በችኮላ የተጓዝንባቸው ጉዞዎች ለፍሬ ስላላበቁን ፣ ቸኩለንም የምናመጣው ለውጥ ይኖራል ተብሎ ስለማይጠበቅ፣ ካለፉት ስሕተቶቻችን ትምህርት ቀስመን፣ ችግሮቻችን አበጥረን አውቀን፣ ለመፍትሔዎቹ በጋራ የምንሠራበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል እላለሁ።
የችኩሎችን ምሳሌ ላስረዳ። ዶ/ር ፍሥሓ እሸቱ ወደ ፖለቲካው መድረክ ዘው ብለው ገብተው፣ በ6 ወር ውስጥ መንግስት መለወጥ ይቻላል ብለው፣ አጀብ! አጀብ! ተባለ። ከዚያም ጊዜው ሲያልፍ ምን ላይ እንዳሉ ባላውቅም ድምፃቸው ጠፋ። ዐወጋን የሚባሉ ዐማራዎች ተደራጅተው ወያኔ ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው ተብሎ ፕሮፓጋንዳ ተናፈሰ፣ ኢሣትም አራገበው፤ ወዲያው ተለቃቅመው ተያዙ መሰል ወሬያቸው ጠፋ። አርበኞች ግንባር ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ ነው ተባልን። አሁን ግን ስለነሱ ጥቃት ማድረስ ብዙም አንሰማም። ሌላም ሌላም ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። መቼ ነው ሰከን ብለን ሕዝባዊ መሠረት ያለው፣ በብሔርተኝነት እስከመገንጠል የሚያምኑትንም ይሁን፣ ብሔር ተጠርቶም ይሁን፣ ሳይጠራ፣ ባንድነት እንኑር የሚሉትን ሁሉንም ድርጅቶች አሰባስቦ፣ ሁሉንም ባያስደስት እንኳን፣ ጠርዝ የያዙትን ወደመሀል ስቦ፣ አብዛኛውን አስማምቶ ማኖር የሚችል የፖለቲካ አስተሳሰብ መጨበጥና ከዚህ በመለስ ያሉትን፤ ልዩነቶች በሂደት ደረጃ በደረጃ ለሁሉም አስማሚ የሆነ የጋራ መፍትሔ በማመንጨት፣ ልዩነቶቻችን ምን እንደሆኑ፣ ለሕዝብ አሳውቀን ሕዝቡ ራሱሊዳኘን ወደሚችልበት የፖለቲካ አስተሳሰብ መግባት የምንችለው?ይህ ለእኔ የምናፍቀው ጉዳይ ነው።
እዚህ ጋር የግል ሀሳቤን እና የታዘብኩትን ልጨምር። በኢትዮጵያዊነት በጽኑ አምናለሁ፤ ሁላችንም እኩል የሆንባት ሀገር እንድትኖረን እመኛለሁ። ሆኖም፣ ሁሉ በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑት የዐማራውን በትህነግ (ወያኔ) መበደል የማይቀበሉና ይህን ገሸሽ እያደረጉ ሌሎችን ለማስደሰት የሚጥሩና በዐማራው ደምና ጥፋት ኢትዮጵያ እንድትገነባ የሚያደርጉትን እቃወማለሁ። በተመሳሳይ መልኩ የብሔር ድርጅቶች «መብታችን ይከበር» ሲሉ የሌሎችንም መብት እነርሱ ማክበር ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው። «ባህላችን ይከበር፣» ብለው መልሰው የዐማራን ባህል ወስደው ዐማራውን አዲስ ባህል እንዲሰጡት አልፈቅድም። «ድሮ ሳንፈልግ በአማርኛ ተናገርን» ብለው፣ ዛሬ ዐማራውን በግድ የራሱ ያልሆነ ቋንቋ እንዲናገር ሲያስገድዱት ማየት አልፈቅድም። ስለሆነም በኢትዮጵያዊነት የተደራጁት ዐማራን ካገለሉ፣ በብሔር የተደራጁትም ዐማራውን በአውራ ጠላትነት ፈርጀውኅልውናውን ከተፈታተኑት፤ ዐማራው ራሱን እንደ ዐማራ አደራጅቶ፣ ቢቻል ከሌላው ጋር ዕኩል ሆኖ አብሮ የመኖር መብቱን ማስከበር፤ ካልተቻለ ደግሞ ጠባቦቹ ዐማራን ለማጥፋት በያዙት መንገድ ከቀጠሉ፣ዐማራውም ራሱን በዐማራነት አደራጅቶ ከሚፈጸምበት ጥቃት መከላከል ተገዶ የሚገባበት መንገድ በመሆኑ ማንም ይህን ሊከለክለው አይገባም ባይነኝ። ምክንያቱም እንደ ሲቪክ ድርጅት ዐማራውን አንቅቶ በአንድነት ጎራ ሥር ያሉትን ዐማሮች፣የዐማራ መብቶች እንደተነጠቁና እንደተገፈፉ ተረድቶ፣ ባለበት ድርጅት ልክ የሌላው ኢትዮጵያዊ መብት ሲከበር የዐማራውም መብት መከበር እንዳለበት ጠንክረው እንዲሠሩ ማስተማርና ማንቃት ይችላል። ነገሩ ገፍቶ ደግሞ ብሔርተኞቹም ከገነኑ፣ ዐማራው ወገኖቹን አሰባስቦ፣ «መጀመሪያ ዐማራን ላድን» የሚሉ የዐማራ ፖለቲካ ድርጅቶች ከውስጡ ይወለዳሉ። በዚህም ምክንያት ሞረሽ የዐማራ ድርጅት የሚባል መቋቋሙን ከሚደግፉ አንዱ ነኝ። ይህም በእኔ አመለካከት አንድ ሕዝብ እጅህን አጣጥፈህ ሞትን በፀጋ ተቀበል የሚል የሃይማኖትም ሆነ የሌላ ሕግ ስለሌለ የሚደገፍ ነው። ይህ ዐማራ እንደ ዐማራ ብቻውን ሌሎችን የሚገጥመው ግን፣ የመጀመሪያው አማራጭ በአብሮነትና በዕኩልነት እንኑር የሚለው ሰሚ ካጣ ነው። ዐማራውን ጠላታችን ነው ብለው ያመኑና ለዚሁ ተግባር ነገዳቸውን በዙሪያቸው ያደራጁ ቡድኖች፣ ሲያጠፉት፣ ሌላው ኢትዮጵያዊ እንደ ዜጋ ከጥፋት ሊያድነው ካልቻለና ከጎኑ ካልቆመ፣ ዐማራው ዝም ብሎ ጥፋትን መቀበል የለበትም። ከጥፋት ራሱን መከላከል ተፈጥሮአዊ መብቱ ነውና ማንም ሊከለክለው የሚችል አይሆንም።
በአገራችን የፖለቲካ ጉዞ ያስተዋልኩትሌላ አንድ ነገር አለ። «ለምን ተብሎ፣ እንዴትስ ተደርጎ የዐማራ ድርጅት ይቋቋማል?» የሚሉ ወገኖች አሉ። ይህን ጥያቄአቸውን ወደ ሌሎች ሲያዞሩት አይታዩም። ትግሬው፣ ኦሮሞም፣ ጉራጌው፣ ሶማሌው፣ አፋሩ፣ ወዘተ በነገዱ ተደራጅቷል። «እነዚህ ለምን ተደራጁ?» ተብሎ ሲጠየቅ አይሰማም። ዐማራ ጊዜ ወስዶ፣ አስቦና ሁኔታዎችን ገምግሞ «ነገዱን ከፈጽሞ ጥፋት ለመከላከል ያለው ብቸኛና ተገዶ የገባበት መንገድ ተደራጅቶ ራሱን ከጥፋት መከላከል ነው፤» ብሎ ዝግጅት ሲጀምር ለምን? እንዴት? የሚሉ ድምፆች ከዚህም ከዚያም ይደመጣሉ። እነዚህ ድምፆች ዐማራውን እንዲጠፋ ተያይዞም ኢትዮጵያ እንድትጠፋ ምኞት ያላቸው ድምፆች እንጂ፣ ለዐማራው ማንነትና ለኢትዮጵያዊነት ዳብሮ መቀጠል ከሚመኙ ወገኖች እንዳልሆኑ መገንዘብ አይገድም።
በሌላ በኩል «የዐማራው መደራጀት ተገቢ ነው፣በሀሳብ እንደግፈዋለን ወይንም አንቃወምም»የሚሉ ድምፆች ቢኖሩም፣ ጠጋ ብለው የመደራጀቱ ሂደት ተፋጥኖ በነገዱ ላይ ተጨማሪ ጥፋት ሳይጠፋ፣ የኢትዮጵያዊነት አያያዥ ክሮች ሳይበጠሱ ሁኔታዎችን ወደ ነበሩበት ጤናማ ሕይዎት ለመመለስ ለሚደረገው ትግል ምንም አይነት አስተዋፅኦ ሲያደርጉ አይታዩም። በተለያየ ምክንያት ከዳር ሆነው ሲመለከቱ ነው የሚታዩት። ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርት ድርጅቱ ተመሥርቶ 3 ዓመት ከተጓዘ በኋ፣ አንዳንድ ሰዎች «እንዴት ናችሁ? ምን እየሠራችሁ ነው? ለተጎጂው ዐማራ ምን አደረጋችሁ?» የሚሉ ድምፆችን ያሰማሉ። እነርሱ ግን «እኛ ምን አደረግን? ከእኛ ምን ይጠበቃል?» ብለው ራሳቸውን አልጠየቁም። ይህን ቢጠይቁ ምን እንደተሠራና ምን እንደቀረ መልሱን ራሳቸው ያገኙት ነበር። ሞረሽ ወገኔ በዚህ የሦስት ዓመት ጉዞው ማንም ሊሠሩ ይችላሉ ብሎ ሊያምን ቀርቶ ሊያስባቸው የማይችሉ መሠረታዊ የመረጃ ማሰባሰብ፣ የማደራጀትና ዐማራውን የማንቃት ሥራዎች ሠርቷል። የሞረሽ ምሥክሩ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን፣ ተግባር ስለሆነ ተግባሩ ኅያው ሆኖ የሚቀጥልበት መሠረቱ ተጥሏል። በዚህ ረገድ ሞረሽ ወገኔን የመሠረቱና በሂደት የተቀላቀሉ ወገኖች «ለወገን ችግር ፈጥኖ ደራሹ ወገን ነው» የሚለውን አባባል በተግባር ያሳዩ በመሆኑ በነገዱ ታሪክ ውስጥ የጎላ ቦታ የሚይዙ እንደሚሆን መጠራጠር አይቻልም።
እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ድራሻ ሳይወጣ፣ ሌሎችን «ምን ሠራችሁ?» ብሎ መጠየቅ አግባብነቱ ባይታየኝም፣ ምንም ሳያደርጉ «የታለ ሞረሽ? ምን ሠራ?» ብሎ ድርጅቱን ማጣጣል እና አማራ በአማራነቱ መደራጀቱ ጥቅም እንደሌለው ማሰብ፣ ዐማራውን ለጠላቶቹ የጥፋት እልቂት ተመቻችቶ ጥፋቱን በፀጋ እንዲቀበል የጥፋት መልክተኛ ከመሆን ውጭ የሚታይ በጎ አመለካከት አይደለም። ይሄ እኮ ነው ችግራችን። ምንም ሣንሠራ ለውጥ እንፈልጋለን። ሰዎች በአቅማቸው የሠሩትን ማመስገን ሳይሆን፣ ያልሠሩትን ማብጠልጠል እንሻለን። ስለዚህም በቃ ፖለቲካ ድርጅቶች ካቅማቸው በላይ እንዲህ ልናደርግ ነው እንዲሉ ያስገድዳቸዋል። «አይነጋ መስልዋት ከቋት ምን አለች» እንዲሉ ይሄኛውን አጣጥለው አዲስ የሚመጡትም አዲስ ድርጅት ቢያቋቁሙም ለዘላቂ መፍትሄ እስካልሠሩ ልፋታቸው እንዳለፉት ሁሉ ከንቱ ሆኖ እንደሚቀር መናገር መጥፎ ምልኪ አሳቢነት አይሆንም። እናም ያልዘሩት ማጨድ አይቻልምና ዘርተን ለማጨድ እንጣር!
5. በለስ ከቀናው ጋር ተስማምቶ የድርሻን ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንጂ ግልጽአቋም አለመያዝ፣
ከላይ በተወሰነ መልኩ ለማንሳት እንደሞከርኩት፣ ዋናው ችግራችን በውስጣችን ስለግላቸው ስብዕና ወይንም ስለጥቅማቸው ብቻ እንጂ፣ ስለኅብረተሰቡ ወይንም ለሀገሪቱ የማያስቡ ብዙ ሰዎች በፖለቲካው መድረክ ውስጥ መኖራቸው ነው። ይህንስል ራሴን ነፃ ለማድረግ አልፈልግም። የራሴን የግል ዓላማ ለማሳካት እስካሁን በግል ሕይዎቴ ዙሪያ ብቻ ስለተጠመድኩ፣ ለወገኔ ማበርከት የሚገባኝን እንዳላበረከትኩ ይሰማኛል። «አንተስ?» የሚል ጥያቄ ከመጠየቄ በፊት ግዴታ የን አለመወጣቴን እንደማውቅ ተረዱልኝ።
ዋናው ግንበቃ! ጣልያን ሲመጣ በባንዳነት፣ ሲወጣም በውስጥ አርበኝነት በሚሉ ስሞች ሌሎች ዕውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች በከፈሉት የሕይዎት፣ የአጥንትና የደም ዋጋ ምቾታቸውን ያስጠበቁ ብዙ ባንዳዎች እንደነበሩ ሁሉ፣ ዛሬም በዚህ ዘመን ውስጥ በከፋና በሠፋ መልኩ አሉ። ወደፊትም ይኖራሉ። ኅብረተሰብ እንደ ወራጅ ውኃ ነውና ይህ የሚቋረጥ አይሆንም። ማቋራጫው ዕውነተኛ ታሪክን ለትውልድ በማስተማር ባንዶቹ እንዳለፈውና እንዳሁኑ የቀረው ቢቀር «እንምራችሁ» እንዳይሉን የእያንዳንዱን ፖለቲከኛ ማንነት ማወቅ ተገቢ ነው እላለሁ። ያለፈውን ታሪካችን አሳዛኝ የሚያደርገው ባንዳዎቹ በሥልጣን ማማ ላይ ተቀምጠው ልጆቻቸውን በራሳቸው አምሳል ከመቅረጽ አልፈው፣ ይህን ውርስ በትምህርት ዘመናዊነት እንዲላበስ አድርገው የባንዳዎቹ ልጆች ዛሬ የት እንዳሉ የምናውቀው ነው።
የአርበኞቹ ልጆች ወላጆቻቸው ያስተማሩዋቸውያገር ፍቅር፣ አርበኝነት እንጂ፣ ዘመናዊ ትምህርት የሚያስተምሩበት አጋጣሚውም ዕድሉም ስላልነበራቸው የአርበኝነቱንና የአገር ፍቅሩ ብቻ በልባቸው ቀረ። የዘመናዊ ትምህርቱ ባይተዋሮች በመሆናቸው፤ይኸውና በባንዳ ልጆች ከመገዛት አልፈው፣ አባቶቻቸው ሞተው ያስጠበቋትን አገር ከማጣት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በዚህም ምክንያት ዛሬ ሀገሪቱ የምትመራው በባንዳ ልጆች ነው። በተቃዋሚው ጎራም ያሉት ብዙዎቹ የባንዳ ልጆች ናቸው። ሁለቱም ስለ ግለሰብ ስብዕናቸው ወይንም ስለሚያካብቱት ሀብት እንጂ፣ ስለ ኅብረተሰቡ ሲጨነቁ አይታዩም። አሁንም እየታየ ያለው የደሀን ልጅ አስገድለው የነርሱንና የልጆቻቸውን ሕይዎት የተደላደለ ለማድረግነው።
ለዚህም ነው «ቶሎ ተኩሶ ቶሎ ለውጥ አምጡ፣ አለበለዚያ ካለው ጋር እንሠራለን» የሚሉን። «ቶሎ ተኩስ» የሚሉት ደግሞ በሚገርም ሁኔታ እንኳንስ ጥይት ሊተኩስ የሚችል የሰው ኃይልቀርቶ፣ በሰማይ ሊንሳፈፍ የሚችል ባሉን (ፊኛ) ያዘጋጁ አይደሉም። ለዚህምነው ግልጽ የሆነ አቋም ሳይያዝ፣ የማይቀላቀሉ ዘይት እና ውኃ «ትህነግን ብቻ እንጣል እንጂ፣ እኛ እንስማማለን» የሚሉን። አትሳሳት ወገኔ እንዲህ ያለ የችኮላ አካሄድ አይሠራም። ይህ ትልቅ ማጭበርበር እና በሌላ ሰው ደም የሥልጣን ባለቤቶች ለመሆን የሚፈልጉ የባንዳዎች ሀሳብ ነው። መስማማት አንድነት ያስፈልጋል፣ አዎ! ያስፈልጋል። ግን በደፈናው ስምምነትና አንድነት የለም። የአንድነቱና የስምምነቱ መሠረታዊ ጉዳዮች በግልጽ ለሕዝብ ይፋ መሆን አለበት። አንድነቱና ስምምነቱ የኢትዮጵያን አገራዊነትና አንድነትመሠረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል። አገር ለማፍረስና ለመበታተን ስምምነት አያሻም። አገር ለማፍረስ የሚያሻው እንደ ትህነግ (ወያኔ) ጉልበት ብቻ ነው።
6.ከኔ ሀሳብ ውጪ ያላ ሀሳብ ላሣር ነው፣
እንደምናውቀው ከሶሻሊዝም አብዮት የተጠናወተን ከፉ ልክፍት፣ «ከኔ ሀሳብ ውጪ ያለ ሁሉ መጥፎ ነው። ያን የሚያራምድ ሁሉ ጠላቴ ነው» የሚለው ነው።«ከእኔ የተለየ ሀሳብ የሚያቀነቅነውን ሰው ወይም ቡድን ላጥፋው» ከሚለው አስተሳሰብ እስካልተላቀቅን ድረስ፣ ዲሞክራሲ፣ መቻቻል፣ መከባበር፣ መደማመጥ፣ ልዩነቶችን አውቆና ተቀብሎ የአንድነቱ ምሰሶዎች የማድረግ አመለካከት እስካልቀረጽን ድረስ፣ አብሮ መኖር የሚባል ነገር አይታሰብም። በእርግጥ በኢኮኖሚ ዕቅዳቸው ምክንያት ግራ ዘመም፤ ቀኝ ዘመም፣ መሀል፣ አጥባቂ ፣ ለዘብተኛ ወዘተ ተባብለው በመሠረታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ግን ተስማምቶ መኖር የተለመደና ዴሞክራሲያዊ ነው። ምክንያቱም ይህየሕዝቡን መብት የሚነካና የሚጫን ሳይሆን፣ ልዩነታቸው የተመሠረተው በቋንቋ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መርሕ ላይ ነው። አንደኛው ወገን፣ «አንዷን ጥንታዊ ሀገር በብሔር ከፋፍለን፣ አንድ የነበረን ሕዝብ ልዩነቱን በምን መልኩ ልናጠበውና የመጨረሻ ዕልባት ልንሰጠው በማንችልበት የብጥብጥና የመጋደል አዙሪት ውስጥ አስገብተን፣ ከኢኮኖሚ ውጪ በሰዎች ኅሊና ውስጥ ያለ ስስ ስሜትን በማዳበር አብሮ መኖርን እስከ ወዲያኛው የማይቀበለው ትክክል ነው» ሲል፣ ሌላው ደግሞ «የለም፣ በብሔር ድንበር ሳይከፋፈል፣ የሁሉም መብት ተከብሮ፣ በጋራ የምንኖርበት አገር ይኑረን፣» የሚል ነው። እነኚህ ሀሳቦች ፈጽሞ የማይስማሙ ሀሳቦች ስለሆኑ፣ ሁለቱ ሀሳቦች አብረው እንዲኖሩ ማድረግ ከባድ ነገር ነው። እንደዚህም ሆኖ ሳለ ግን፣ ሁሉም ሀሳቡን አንጥሮ አውጥቶ፣ አንዱ አስተሳሰብ የሌላውን ሥጋት በምን መልኩ እንደሚመልስ በግልጽ አስቀምጦ፣ ልንመራበትና አብሮ ሊያኖረን የሚችለውን ቀመር ሕዝብ እንዲወስንበት ማድረግ ብልኅነት ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ ድምፅ መገዛትም ነው። ይህ ደግሞ «ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ነው፤ ባለሥልጣኖች የሕዝብ ወኪሎችና እንደራሴዎች ናቸው፣» የሚለውን የዲሞክራሲ መርሕ የሚያራምድ በመሆኑ አስማሚ ነው። ችግሩ አንዱ የሌላውን ሀሳብ ማዳመጥ አይፈልግም፤ ሕዝቡ እንዲወስን ሳይሆን፣ እርሱ የፈለገውን በጉልበት በሥራ ላይ እንዲውል የመፈለጉ ጉዳይ የፖለቲከኞቻችን ያልተለወጥ ቅኝት መሆን ነው።
ሌላኛው ትዝብቴ ደሞ ከላይ እንዳነሳሁት ኢትዮጵያው ውስጥ በብሔር እና በሀገር ደረጃ ያለው አደረጃጀት በተመለከተ የሚሰጡ አስተያየቶች ይለያያሉ። የልዩነቱ መሠረት ጉልበት ከሆነ አላውቅም። ለምሳሌ ትግሬ ወይንም ኦሮሞ ወዘተ በኢትዮጵያዊነት ሲሰባሰብ እሰየው ይባላል፣ ይበረታታልም። ትግሬ ወይንም ኦሮሞ በብሔር ሲደራጁ ጉልበት አላቸው፣ ተደራጅተዋል በሚል እንደሆነ አላውቅም ሀሳባቸውን በግልጽ ከመቃወም እንቆጠብና፣ በነገድ መደራጀታቸው የሚያስከትለውን ችግር ከማስረዳት ይልቅ፣ እነሱን ወደ ማባበል እንዞራለን። ዐማራ ሲደራጅ ግን፣ ራሱ ዐማራን ጨምሮ፣ ያለው ተቃውሞ ለየት ያለ ነው። ሲጀመር ዐማራ «በኢትዮጵያዊነት ልደራጅ» ሲል «የድሮ ሥርዓት ናፋቂ» ይባላል። ከዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ለመውጣትና ዘሩን ከጥፋት ለመከላከል፣ «እንግዲህ ምን ላድርግ? በዚህም በዚያም ቦታ ካሳጣችሁኝ፣ እንደ ዐማራ ልደራጅ» ሲል፣ አንዱ «ዐማራ የለም» ይላል። ሌላው ደግሞ «እንዴት ዐማራ ይጠባል? ቢያልቅም፣ ከጥፋት የሚያድነው ቢያጣም፣ በዐማራነት ከሚደራጅ ጭራሹኑ ቢጠፋ ይሻለዋል» ይላል። እንግዲህ ያለውን አመለካከት ልዩነት አስቡት። በዚህ ብቻ አያበቃም። ራሳቸው ዐማራዎቹ በአንድነት ጎራ ሥር ያሉት እና አሁን አሁን እያቆጠቆጡ የመጡት «ዐማራ በዐማራነት መደራጀት አለበት» ከሚሉት ከዋና ጠላቶቻቸው ይልቅ የእርስ በእርስ ጠላትነታቸው ገኖ የሚወጣበት ይበልጣል። ይሄም «እኔ ካልኩት ሀሳብ ውጪ ሌላው ሁሉ ስሕተት ነው፣ የተለየ ሀሳብ ያላቸው መጥፋት አለባቸው» ከሚለው የቆየ አስተሳሰብ የሚቀዳ መሆኑ ጥርጥር የለውም።
መሆን የነበረበት፣ ሌሎች ስሕተትም ይሁኑ ልክ፣በብሔርም ሆነ በአንድነት ድርጅት ውስጥ ተወካይ እንዳላቸው እና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የብሔራቸውን መብት እንደሚያስከብሩ ሁሉ፣ ዐማራውም በአንድነት ድርጅት ውስጥም ይሁን በዐማራነት የተደራጁትን በሚያስማማቸው፣ «ዐማራን ከጥፋት መታደግ» በሚለው አብረው እየሠሩ ልዩነታቸውን ለሕዝቡ እየገለጹ በሂደት የትኛው ድርጅት እንደሚስማማው ሕዝቡ እየመዘነ የራሱን ውሳኔ እንዲሰጥ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበር ያለባቸው። አይደለም፣ የዐማራ የፖለቲካ ድርጅትይቅርና! ሕዝብን ለማሰባሰብ እና ለመርዳት የተቋቋመ የሲቪክ ድርጅትን «የዐማራ ሲሆን አንቀበልም» ማለት የቱን ያህል እኛ ካልነው ውጪ ለመስማት ችግር እንዳለብን ያሳያል። ሜጫና ቱለማን ያልተቃወመ ሰው ወይንም ድርጅትለምን እና እንዴት ሞረሽን ይቃወማል? ኦነግን ያውም እጁ በደም የተጨማለቀን ድርጅት ያልተቃወመ ገና አየር ላይ ያለ ቤተ-አማራን ድርጅት እንዴት ያጥላላል? እስቲ ነገሮችን ሰፋ አድርገን እንይ? አንድን የፖለቲካ ሃሳብ መቃወም መብታችን ነው ግን ከተቃወምንም ሁሉንም እንጂ፣ የአንዱን ነገድ ድርጅቶች ብቻ ለይተን አንቃወም። ሰው መጥቶ አይንካህ እንጂ፣ የፈለገውን ሀሳብ ያራምድ። ድንበር ተሻግሮ ከነካህ መልስ ምት ያስፈልጋል። መደራጀትህም ለዛ ነው። ግን መቻቻልና መደማመጥ ከሌላ የትም አይደረስም።
መፍትሔው
በሀገሪቱ አሉ የተባሉ የፖለቲካ፤ የሲቪክ፤ የሃይማኖት ድርጅቶች ተሰባስበው የሁሉንም ሀሳብ አዳምጠው፤ እያንዳንዱ ለሚለው ሀሳብ ማጠናከሪያውን መረጃ አቅርቦ፤ እንዲሁም ላቀረበው ሀሳብ በመረጃ የተደገፈ የተቃውሞ ሀሳቦችን አዳምጦ፤ ሁሉንም እንኳን ባያስደስት አብዛኛውን በተወሰነ መልኩ አስማምቶ፣ በሰላምና በእኩልነት የምንኖርባትን ሀገር እንድትኖረን ለነገ ሳይባል ዛሬ ማካሄድ ግድ የሚለን ይመስለኛል። እዚህ ጋር የሚቀርበው መፍትሔበሀገሪቱ ትልቁን ቁጥር የሚይዙትን ዐማራን እና ኦሮሞን የሚያቀራርብ ሀሳብ ማቅረብ የግድ ነው።ነገር ግን ይህሀሳብ በፍፁም ቁጥራቸው አነስተኛ በሆኑት ሌሎች ነገዶች ላይም ይሁን የተቀላቀሉ ነገዶች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚኖረውና መብቶቻቸውን የሚያስከብር መሆኑን ከወዲሁ እርግጠኛ መሆን አለበት። ከምንም በላይ ለችግራችን ሁሉ መነሻ የሆነው አንድን የኢትዮጵያ አካባቢ ለአንድ ብሔር ሰጥቶ የተቀሩትን በዛ አካባቢ 2ኛ ዜጋ ያደረገው በባንቱስታን ሥልት የተዘረጋውን የብሔር አከላለልና የዚሁ መሠረት የሆነው ሕገመንግሥትመናድ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። የሁሉም ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ ተከብሮ የሚኖርባት ሃገር እንዲኖረን ማድረግ ያስፈልጋል። (ልብ በሉ ይህ መብት ዐማራንም ይጨምራል። አዲስ በቻይና ልብስ አዲስ ባህላዊ አለባበስ ለዐማራው መስጠት መቆም አለበት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ባህል ይከበር እስካልን ድረስ)። ሕዝቡ በድምፅ ብልጫ እስከወሰነ ድረስ በሀገሪቱ ሁለትና ከዚያም በላይብሔራዊ ቋንቋ ቢኖር መበልጸግን እንጂ፣ መደህየትን ስለማያመለክት ክፋት አለው ብየ አላምንም። ለጉዳዩ ግን ባለቤቱ ሕዝቡ ዓላማውና ግቡ ተብራርቶ ቀርቦለት ጥቅሙንና ጉዳቱን መዝኖ በድምፁ የሚወስነው መሆን ይኖርበታል።
«ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልምና» እኔ ሀሳቤን አካፍያለሁ። በደፈናው ሰውን ማብጠልጠል ሳይሆን፣ ሀሳብን በሀሳብ በመሞገት የተሻለ የምትሉትን ሀሳብ እያቀረባችሁ የሕዝባችንን የመከራ ቀናት ለማሳጠር እንሥራ። መፍትሔውን በተመለከተ ብዙ ዝርዝር ሀሳቦች የምላቸውን ወደፊት ይዤ እቀርባለሁ።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይታረቃት!!!
ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!!!
*በስነፅሁፍ ህግ መሰረት በአማርኛ ስፅፍ አማርኛ ቋንቋ ብቻ መጠቀም ስላለብኝ ትህነግ (የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር) የሚለውን እንጂ በትግርኛ የሆነውን ህወሃት (ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ) የሚለውን አልጠቀምም። በተለምዶ ወያኔ ስለሚባሉ አልፎ አልፎ እጠቀማለው። ሻዕቢያም እንዲሁ በአማርኛ ሲሆን ኤህነግ ነው። በእንግሊዝኛ ሲሆን TPLF, EPLF ወዘተ ተብሎ ይፃፋል። በአማርኛ ሲሆን ኦነግ የምል ሲሆን በኦሮምኛ ከፃፍኩ/ከተናገርኩ አባኦ (አደ ቢሊሱማ ኦሮሞ) ብዬ ነው።
አበበ ተድላ (abetedla2011@gmail.com)
ታህሳስ 2008
አማረ መኮን ን says
የጽሑፉ ፍሬ ነገር፤ አሁን ሃገራችን ያለችበትን ሁኔታ የሚያመላክት ነው። ሆኖም ግን ሃገሪቷ ያጋጠማትን ችግር በጋራ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት
የሚያቃልል/የሚያጎድፍ ዓይነት መስሎ ይታያል።ትችት ማቅረቡ ላይ ችግር ያለ አይመስለኝም፤ሆኖም ግን፤ከዚህ ችግር እራስን ነጻ አውጥቶ ሌላውን
ብቻ መተቸት ትክክል አይመስለኝም። አነሰም በዛ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን።
Abdissa says
You said I can accept the nation as a nation but you reject the nation’s region, you know why Amhara peoples couldn’t organized as a nation? The reason is Amhara living everywhere in the country and amhara people believe more beneficial as long as Ethiopia exists but this doesn’t work for others like Oromos because oromos have their own land and resources to live while they can make a border demarcation which means not secession ! To create solidarity between Oromo and Amhara people, Amhara intellectuals must accept and respect the real Oromo people interest on the other hand you know how much Oromo people respect others and live with them for many years without insulting and undermining others people.