በኣስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ኢትዮጵያ ደምቃ ነበር። የለውጥ ጥም ይዟት ትጮህ ነበር። መቼም በየሃገሩ ኣገራዊ ችግሮችን መልክ ኣስይዞ፣ መሪቃል ወይም መፈክር ኣውጥቶ ለውጡን የሚመራውና የለውጥ ሃይል የሆነው ወጣቱ ሲሆን በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁሌም ቀዳሚዎች ናቸው። ታዲያ በዚያ የለውጥ ወራት ጊዜ ከነበረው ኣንዱና ትልቁ ጥያቄ የመሬት ላራሹ ጉዳይ ነበር ኣሉ።
መሬት ላራሹ! መሬት ላራሹ! መሬት ላራሹ!………
ወጣቱ ድምጹን ኣሰማ ። ኣራሹ ማን ነው? ያውጭሰኛውና መሬት የለሹ ዜጋ ነዋ። በጥቂት የመሬት ከበርቴዎች እየተጨቆነ የሚኖረው የሰፊው ድሃ ህዝብ ግፍ ይብቃ፣ ኣዲስ ዘመን መጥቷልና እናንተ የመሬት ከበርቴዎች ሆይ በቃችሁ። ኣራሹ ገበሬ እጣው በሆነችው በዚህች ኣገር ውስጥ፣ የርስቱ ገመድ በወደቀባት በዚህች ምድር ላይ መሬት ይኑረው ነው ጥያቄው። በርግጥ ይህ ጥያቄ በጥሩና ሳይንሳዊ በሆነ ሁኔታ የተቀመጠ ይመስለኛል።
በተለምዶ ያ ትውልድ የምንለው ከንጉሱና ከፊውዳሉ ጋር ሳይሰለች ታገለ። ለገበሬው ኣባቱ ድምጽ ሆነለት። በርግጥ ትግሉ የመሬት ላራሹ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ኣጠቃላይ የኢትዮጵያን ሶሺዩ ፖለቲካ የሚመለከት ሰፊ የለውጥ ትግል ነበር። ይህ ጥያቄ እንደቀጠለ ብዙ ቆየና በ 1966 ዓ.ም ለውጥ ድንገት ፈነዳ። ሲፈነዳ ባልተጠበቀ መንገድ ነበርና ብዙ ለውጥ ፈላጊ ተማሪዎችን ኣላስደሰተም። ወታደር ስላፈነዳው በኣገሪቱ ስጋቶች ኣየሉ። ይሁን እንጂ ደርጉ ስልጣኑን በያዘ በማግስቱ የተማሪውን ጥያቄ “መሬት ላራሹን” እመልሳለሁ ኣለ። የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም ኣንድ ስር ነቀል ኣዋጅ ታወጀ። መሬት የሰፊው ህዝብ ነው ተባለ። በመሰረቱ ይሄ ሰፊው ህዝብ የሚባል ነገር በውስጡ ሌላ ኣነስተኛ ህዝብን ያገለለ ይመስላል። በርግጥም በሶሻሊስቶች ትግል ውስጥ የመደብ ትግል ዋናው ነገር ስለሆነ ታጋዮች ለሰፊው ህዝብ ሲሉ ሊበቀሉት የተነሱት ኣነስተኛ የተባለ መደብ ስላለ ነው። ይህ ግን ኣደገኛ ነው። ትግል ለሁሉም ነጻነት፣ ለዜጎች ሁሉ ሲሆን ነው ክብ ከሆነ ጭቆና የሚወጣው። ይህ ኣዋጅ በወቅቱ ጭቁን ለተባለው መደብ ከፍተኛ ለውጥ ነበር። መሬት የሌላቸውን ባለመሬት ያደረገ፣ ከፊውዳል ጭሰኝነት ያላቀቀ ታሪካዊ ለውጥ ነው።
ይሁን እንጂ ታዲያ የመሬት ላራሹ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ተመለሰ ማለት ኣይቻልም። የመሬት ላራሹ ጥያቄ የገበሬውን የባለቤትነት ጥያቄ የሚመለከት ነው። ደርግ ከፊውዳሉ ነጥቆ ባለቤትነቱን ለህዝብ ነው የሰጠሁት ኣለ። ይሁን እንጂ ህዝብ የመሬት ባለቤት ነው ለማለት በሆነ መንገድ ተደራጅቶ መምጣት ኣለበት። ይህ ግዙፍ ማንነቱ ደግሞ በመንግስት ነው የሚገለጸው። መንግስት ሲስተም ስላለው በተግባር የሆነ ሃብት ባለቤት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በተዘዋዋሪ መሬት የመንግስት ነው እንደማለት ነው የደርግ ኣዋጅ። በርግጥ ይህ የመሬት ባለቤት የሆነው መንግስት ለጭቁኑ ለሰፊው ህዝብ የቆመ በመሆኑ የሃገሪቱን መሬት በገመድ እኩል እኩል ኣካፍሏል። ከዚህ በፊት በፊውዳሉ ስርዓት ውስጡ የበገነው ሰፊ ህዝብ በዚህ ኣዋጅ ለስሜቱ ርካታ ቢያገኝም ሁሉም እኩል እኩል በመካፈሉ ብዙ ድሆችን ቢያደስትም ኣጠቃላይ ኣገራዊ የኢኮኖሚ ተጽእኖው ግን ግራና ቀኝ ኣልተጠናም። የሆነ ሆኖ መሬትን መንግስት ይዞ ኣስራ ሰባት ኣመት ከዘለቅን በሁዋላ ወያኔ መራሹ መንግስት በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ኣዲስ ኣበባን ተቆጣጠረ። ህወሃት ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲባል በረሃ እንደገባ ኣሁንም ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲል መንግስትን እንደተቆጣጠረ ኣዲስ ኣበባ ላይ ገለጸ። ያ የተንጠለጠለው የመሬት ላራሹ ጥያቄ ምን ይሆን ይሆን እየተባለ ሲጠበቅ ይህ መንግስት ደግሞ በህገ-መንግስቱ ላይ እንዲህ ሲል ኣወጀ።
ኣንቀጽ 40
- የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው።
- የኢትዮጵያ ኣርሶ ኣደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው
ይህ ኣዋጅ ከየካቲቱ በምን ይለያል? ካልን መሬት የህዝብ ብቻ ሳይሆን የመንግስትም ሃብት ነው የሚል በመሆኑ ነው። ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ከመነሳቴ በፊት ኤንጂነር ይልቃል ጌትነትና ዶክተር በያን ኣሶባ ለቪኦኤ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ኣዳምጨ ነበር። ሁለቱም መሳጭ የሆነ መልእክት ኣስተላልፈዋል። ኤንጂነር ይልቃል ስለ መሬት ባለቤትነት ሲናገሩ በሚገባ ገልጸውታል። ህወሃት መራሹ መንግስት መሬት የህዝብና የመንግስት ነው ሲለን ከፍ ሲል እንዳልነው በተግባር ህዝብ የመሬት ባለቤት የሚሆነው በመንግስት በኩል ነው። ከደርጉ የተለየ የመሬት ኣዋጅ የለም ለማለት ነው።
ኣንድ ፖሊሲ ወይም ህግ ሲወጣ ከሁሉ በላይ ቶሎ የሚማርከኝ የፍልስፍናው መነሻዎች ወይም መሰረቶች ናቸው። በዚህ በጣም እሳባለሁ። እንዲገባኝም የምፈልገው ያ ነው። መሬት የመንግስትና የህዝብ ነው ብሎ ኣረፍተ ነገር ማራዘሙ ከደርግ የተሻለ የመሬት ህግ ኣለ ኣያስብለውም። ከመነሻው መሬት የህዝብ ነው የሚለው ኣባባል ራሱ ችግር ኣለበት። በመሰረቱ መሬት ኣይደለም የህዝብ መባል ያለበት። ኣገር ነው የህዝብ መባል ያለበት። መሬት ግን የግል ነው መሆን ያለበት። መሬት የዜጎች ነው መሆን ያለበት። ኣገር ነው የወል እንጂ መሬት በዜግነታችን እየተዘረዘረ የሚደርሰን የእግዚኣብሄር ጸጋችን ነው።
ሁለተኛው ሳቢ ጉዳይ ደግሞ በጣም የተለየ ኣስገራሚ የፍልስፍና መሰረት ያለው ጉዳይ ሲሆን የዚህ ህግ የፍልስፍና መሰረት ደግሞ መሸጥና መለወጥ ኣይቻልም የሚለው ነው። እንግዲህ መሸጥ ኣይቻልም ሲባል መንግስትም መሸጥ ኣይችልም ባለ መሬቱም መሸጥ ኣይችልም ማለት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ለምንድነው መሬት ከመሸጥና መለወጥ የኢኮኖሚክ ህግ የወጣው? ምን ግዙፍ ጉዳይ ኢትዮጵያ ኣገኛትና ነው መሬት እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ ያለችው? ብለን የፍልስፍናውን መሰረት እንድንመረምር ያደርገናል። የመንግስት ሰዎች እንደሚሉት ኣንዱ መሬትን መሸጥ መለወጥ እንዳይኖር የተደረገበት ምክንያት በተለይ በሃገራችን የሚበዛው ገበሬ ድሃ ስለሆነ ትንሽ ሲቸግረው መሬቱን እየሸጠ ይሄድና ሁዋላ ላይ ሄዶ ሄዶ ያንን ጥለነው የመጣነውን የፊውዳሉን ስርዓት መልሰን ቁጭ እንላለን ከሚል ስጋት ነው ይላሉ። ስለዚህም ገበሬውን ለመጠበቅና ሄዶ ሄዶ ሊፈጠር የሚችለውን የመሬት ከበርቴ ስርዓት ለመከላከል መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ ሃብት መሆን ኣለበት ይላሉ። በመሰረቱ የፊውዳሉ ስርዓት የሚመለሰው ኣንዳንድ ገበሬዎች ብዙ መሬት እየገዙ የመሬት ሃብታም ስለሚሆኑና ያ የሸጠው ገበሬ የነዚህ የመሬት ሃብታሞች የቀን ሰራተኛ ስለሆነ ኣይደለም። የፊውዳሉ ስርዓት ሊመለስ የሚችልበት እድል የለም። ከሁሉ በላይ ግን ሃብታም እየሆኑ የሚመጡ ገበሬዎች ሌሎች መካከለኛ ወይም ዝቅተኛ ሃብት ያላቸውን ገበሬዎች በእርሻ መሬቶቻቸው ላይ ማሰራት መጀመራቸው የካፒታሊስት ስርዓት መገለጫ ነው። ዋናው መንግስት መጠንቀቅ ያለበት የጉልበት ዋጋን ፍትሃዊነት ማጤንና ሰባዊ መብትን ማስከበር መቻል ነው። ፍትህ ባለበት የካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ የሚኖር የሃብት መበላለጥ ላገር ጎጂ ኣይደለም። በፊውዳሉ ስርዓት ጊዜ ፊውዳሉ ጭሰኛውን እንደፈለገ ያደርገዋል። ድሃው የህግ ከለላ የለውም። ፊውዳሉ ከህግም በላይ ነው። ኣሁን ግን የመሬት ከበርቴ ቢፈጠር ይህ ከበርቴ ከህግ በላይ እንዳይሆን መንግስት ኣለ። የሚቀጥራቸውን ሰራተኞች ተገቢ የጉልበት ዋጋ እንዲከፍል ይገደዳል፣ እንዲያከብራቸው ይገደዳል:: በመሆኑም የመሬት ሃብታም ማፍራት ወደ ፊውዳል ስርዓት ኢትዮጵያን ኣይመልስም። ከፍ ሲል እንዳልኩት የህግ የበላይነት ስለሚኖርና መንግስትም ህግን የማስከበር ሃለፊነት ስላለበት ይህ ኣይፈጠርም።
ሌላው በጣም ጉልህ ችግር ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ ናቸው። በኢኮኖሚክስ ውስጥ መግዛትና መሸጥ ዋና ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ከሌሉ ገበያ የለም ማለት ነው። ገበያ ከሌለ ደግሞ እድገትን ማሰብ ኣይቻልም። ፈጠራን ማሰብ ኣይቻልም። መሬት ለሽያጭ ኣይቀርብም ማለት ዲማንድ ኣይታሰብም ማለት ነው። ገበሬው እርሻን የማስፋፋት ፍላጎቱ ይገደባል ኣይታሰብም ማለት ነው። ግብዓቶችን ተጠቅሞ በዚያች ኣንድ ሄክታር መሬት ላይ ካመረተ በሁዋላ ምርቱ ጥሞት ሁለት ሄክታር ባደርገው የበለጠ ምርት ኣገኛለሁ ብሎ እንዳያስብ ተገድቧል ማለት ነው። በገበሬውና በገበሬው መካከል መሸጥና መለወጥ ኣይኖርም ማለት ገበያን ከገበሬው ህይወት ማውጣት ነው። በኣንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ዲማንድና ኣቅርቦትን የሚገድብ ህግ ማውጣት ኢኮኖሚ እያዳይንቀሳቀስ ሰንክሎ መያዝ ማለት ኣይደለምን?። የኢትዮጵያ መሬት ከመግዛትና ከመሸጥ ህግ ሲገነጠል በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ በእርሻ ላይ በጣም ጥገኛ በሆነ ኣገር ላይ ከፍተኛ የሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ ተጽእኖ ያመጣል። ኣንዱ የዚህ ፍልስፍና ግዙፍ ችግር የግብርናውን ኢኮኖሚ የረጋ ውሃ ማድረግ (economic stagnation መፍጠር) ነው። ድንበር ነው እንጂ መሸጥ የሌለበት መሬት በዜጎች መሃል የመሸጥና የመግዛቱ ሂደት መጦፍ ነው ያለበት። መሬት በገበያ ላይ ሲውል ነው ግብርናው የሚያድገው።
ገበሬው የመሸጥና የመግዛት መብቱ ሲነፈግ ኣንዱ የሚያመጣው ሌላ ችግር ገበሬውን “ቢዝነስ ማይንድድ” እንዳይሆን ያደርገዋል። ከብሮች ያርቀዋል። ይህ ደግሞ በሃገር ደረጃ ሲታይ ተጽእኖው በጣም ጉልህ ነው። በግብርናው ኣካባቢ ለሚታየው ሰፊ ችግር ኣንዱ ትልቁ ተጽእኖ ፈጣሪ ጉዳይ ይህ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የመሆኑ ጉዳይ ካመጣቸው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተጽእኖዎች መካከል ኣንዱ ገበሬውን የንግድ ሰው ኣለማድረጉ ነው። ከዚህም የተነሳ እንደሚታወቀው ኣብዛኛው የዋናዋና ሰብሎች ኣምራች የሆነው ገበሬ በየዓመቱ ምርት የሚያመርተው ለራሱ ነው። ለዓመት ቀለቡ ነው የሚያመርተው። ከራሱ ያለፈ ሰፊ ራእይ እንዳይኖረው ተገድቧል። በዚያች በያዛት በኣማካይ ኣንድ ሄክታር ኣካባቢ መሬት ላይ ትንሽ ባቄላ ለሹሮው፣ ትንሽ ስንዴ ለዳቦው፣ ትንሽ ገብስ ለጠላው ወዘተ ያመርታል። እነዚህን ሲያመርት እያሰበ የሚያመርተው የራሱን የኣመት ቀለብና በልግ ወይ መኸር ሲመጣ የሚያስፈልገውን ዘር ነው። ወደ ከተማ ሄዶ ትንሽ እህሎች የሚሸጠው እንደ ጨው፣ ስኳር፣ ጋዝ የመሳሰሉትን እሱ የማያመርታቸውን ጉዳዮች ለመግዛት ሲያስብ ነው። የከተማው ነዋሪም የሚኖረው በነዚህ ምርቶች ገበሬው እየተነቃቃ በሚሸጠው እህል ነው። ከዛ ውጭ ገበሬው ሁለገብ የእርሻ ስራን ስለሚያካሂድ ኣነሰም በዛም ፍላጎቱን ከጓዳው፣ ከጓሮው ነው የሚያገኘው። ይህም ኣንዱ የገበሬውን የቢዝነስ ሰው ኣለመሆን የሚያሳይ ነው። ገበሬው በመሸጥና በመግዛት ሂደት ውስጥ ኣክቲቭ ሆኖ ኣይታይም። በኣንጻሩ በበለጸጉ ኣገራት የምናየው ደግሞ ገበሬው የሚያመርተው ለራሱ ቀለብ ኣይደለም። ለቢዝነስ ነው። ገበያ እያጠና በሰፊው እያመረተ ያቀርባል። ገንዘብ ባገኘ ቁጥር እየተነቃቃ፣ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን እየተጠቀመ ምርቱን ከፍ እያደረገ ይነግዳል። ይሄ ነው እድገትን የሚያመጣው። በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት የግል ቢሆን ኣንዱ ጥቅሙ ኣንዳንድ ትጉ ገበሬዎች የመሬት ይዞታቸውን ባሰፉ ቁጥር ገበያ ማሰብ ይጀምራሉ። “ቢዝነስ ማይንድድ” ያልነው ጉዳይ ይመጣል። ለመሸጥ፣ ብዙ ብር ለማግኘት ስለሚነቃቁ ምርታቸውን ያሳድጋሉ። የገበያ ዲማንድ እያጠኑ በዚያ ላይ ተመስርተው ምርት ያመርታሉ። ይህ ጉዳይ ደግሞ ምርት እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ ገበሬውን ያነቃውና ግብርናው ዘና ብሎ ቢዝነስ ውስጥ ይገባል። እነዚያ ያቺን መሬታቸውን የሸጡ ሰዎች ደግሞ ተጠቃለው ከተማ ይገባሉ ማለት ኣይደለም። ምን ኣልባትም ከኣንድ የእርሻ ስራ ወደ ሌላ የእርሻ ስራ ሊዘዋወሩ ይችላሉ። ኣንድ ገበሬ እርሻውን ትቶ የወተት ላሞች ገዛዝቶ በዘመናዊ መንገድ እያረባ በዚህ ብቻ ለመኖር ሊመርጥ ይችላል። ወይም በኣንዳንድ ሃብታም ገበሬዎች እርሻ ላይ ተቀጥሮ ከዚያ የሚያገኘው የጉልበት ዋጋ ገቢ በዚያች ኣንድ ሄክታር መሬት ላይ ኣርሶ ከሚያገኘው ገቢ ሊበልጥበት ይችላል። ብዙ ምርጫ ይሰጠዋል ማለት ነው። ሌላው ደግሞ ዜጎች በዚህ ዓለም ላይ ኣለኝ የኔ ነው ሊሉት ከሚገባ ሃብት መካከል መሬት ኣንዱ መሆን ኣለበት። በተለይ ገበሬው የባለቤትነት መብቱ ሲነካ በኣለም ላይ ኣለኝ ሊለው የሚገባውን ሊመካበት የሚገባውን የተፈጥሮ ጸጋ መውሰድ ማለት በመሆኑ ትልቅ የመብት ጥያቄ ኣለበት።
በኣሁኑ ጊዜ ከኣዲስ ኣበባ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ገበሬዎች ሲፈናቀሉ ኣንዱ የታየው ችግር እነዚህ ገበሬዎች መሬቱ የነሱ ዓይደለምና ሲፈናቀሉ በመሬት ዋጋ መደራደር ኣይችሉም። የተወሰኑ ኣመታት ምርቶቻቸው ተሰልቶ ነው ትንሽ ገንዘብ የሚሰጣቸው። ያ ገንዘብ ደግሞ ቀሪ ህይወታቸውን ኣይለውጥም ብቻ ሳይሆን የተወሰኑ ኣመታት እንኳን ኣይገፋላቸውም። ኣንዱ መሰረታዊ ችግር ይሄ ሆኖ ሳለ በተጨማሪ ከተማዋ ስትስፋፋ እነዚህን ሰዎችም ወደ ሆዷ ማቀፍ ኣለባት። ሰባዊነት በጎደለው መንገድ በኣማካይ ስድስት ቤተሰብ ያለውን ኣንድ ገበሬ ትንሽ ብር ሰጥቶ የሄድክበት ሂድ ማለት በጣም ወንጀል ነው። ከተማዋ ስትስፋፋ የምታቅፈው መሬቱን ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም መሆን ኣለበት። የከተማ ነዋሪ ኣድርጋ መዝግባ፣ ቤትና ቦታቸውን ሰጥታ ለቀሪ ህይወታቸው የሚችሉትን ስራ ሰጥታ ከተማዋ ብትስፋፋ ቅሬታ ኣይነሳም ነበር። ዋናው ጉዳይ ግን ከፍ ሲል እንዳልነው በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ከፍተኛ የፍልስፍና ችግር በመኖሩ ነው ኣሁን በተግባር ችግሮች ኣፍጠው እንዲወጡ ያደረገው። በኣጠቃላይ ግን በግብርናው ኣካባቢ ያለውን ትልቅ ችግር ስናይ በዓለም ታሪክ ረጅም ጊዜ የወሰደው የኢትዮጵያ የመሬት ላራሹ ጥያቄ ላለፉት ሃምሳ ኣመታት ያልተመለሰ ኣሁንም ያልተመለሰ ያደርገዋልና የመሬት ላራሹ ጥያቄ በኣዲስ መልክ ሊነሳ ይገባዋል። በርግጥ መሬት ለኣራሹ ሲባል ለገበሬው ብቻ ሳይሆን ከተሜውም የመሬት ባለቤትነቱን ሊያገኝ ይገባዋል። መንግስት መሬት ኣይሸጥም ይልና ራሱ ግን በሊዝ መልክ የከተማ መሬትን እየቸበቸበ ከፍተኛ ገቢን ያገኛል። ዜጎች ቤታቸውን ሊሸጡ ሲሉ ጣራና ግድግዳው ተተምኖ እንጂ መሬት መሸጥ ኣትችሉም እየተባለ ላልሆነ ህገ ወጥ ስራ ይዳርጋሉ::
ህወሃት መራሹ መንግስት ኣንዱ ከፍተኛ የሆነ ገቢ የሚያገኝበት የሀብቱ ምንጭ የከተማ መሬት ሊዝ ነው። በሌላ በኩል ገበሬው የእርሻ መሬት ባለቤትነት መብቱን ተነጥቆ ሳለ መንግስት ኣገር የሚያክሉ ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬቶችን ለመሬት ተቀራማቾች በርካሽ ይሰጣል። በኣንድ በኩል የፊውዳሉ ስርዓት እንዳይፈጠር እሰጋለሁ እያለ ገበሬውን ኣስሮ ይዞ በሌላ በኩል ደግሞ ቤልጂየምን የሚያህል መሬት ለመሬት ቅርምት ተዳርጓል።
ወደ ገበሬው የመሬት ይዞታ ጉዳይ ስንመለስ ህገ-መንግስቱ መሸጥ መለወጥ ይከለክልና መንግስት በሌላ በኩል ማከራየትንና ማውረስን ይፈቅዳል። ማውረስ እየተቻለ ኣይሸጥም። ማከራየት እየተቻለ ኣይለወጥም ይባላል። ገበሬው የሚያርሰውን እርሻ እስከ መቼ እንደሚያስተዳድር የጊዜ ገደብ የለውም። ማውረስም ይችላል። ነገር ግን መሸጥ ኣይችልም። ይህ ኣሰራር ገበሬውን ከገንዘብ ከማራቁ ሌላ በጣም ኣምታች የሆነ ህግ ነው። ግዙፍ የሆነው ሃብታችን እንዲህ ግልጽነት በጎደላቸውና በትክክለኛ የፍልስፍና መሰረት ላይ ባልቆሙ ህጎችና ፖሊሲዎች ላይ ሲመሰረት የሚያመጣው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ግዙፍ ነው። በመሆኑም ኣዲሱ ትውልድ ይህን የመሬት ጥያቄ እንደገና ኣንስቶ ሊታገልለት ይገባል። ያሳዝናል የመሬት ላራሹ ጥያቄ ዛሬም በኣምሳ ኣመቱ ኣልተመለሰም። የመሬት ፖሊሲዎቻችን በውነት በጣም በከፋ ችግር ላይ ያሉ ስለሆነ ህዝቡ ከመልካም ኣስተዳደር ጎን ለጎን ኣንድ ዋና የትግል ጥያቄ ኣድርጎ ሊያቀርብ የሚገባው ጉዳይም ነው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም የቀድሞ ወንድሞቻቸው ያነሱትን ይህን የገበሬውን መሰረታዊ ችግር ኣንስተው ሊታገሉለትና የሃምሳ ዓመቱን ትግል በድል ሊቋጩት ይገባል።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
geletawzeleke@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply