የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከአርብ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለመሬት አስተዳደር ተቋማት፣ ለመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን እንዲሁም ለ11ዱም ክፍለ ከተሞች ባስተላለፈው ሰርኩላር፣ የመሬት እና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዳይሰጡ ውሳኔ አስተላልፏል።
ካቢኔው ዕግዱን ያስተላለፈው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረታቸውን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያደርጉ ለማስቻል ሲሆን አንዳንድ ስግብግብ ግለሰቦች ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር በመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ በመገንዘቡም ጭምር ነው ተብሏል።
በዚህም ምክንያት ማንኛውም የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ የታገደ ሲሆን ስድስቱም የመሬት ነክ ተቋማት፣ 11ዱም ክፍለ ከተሞች እንዲሁም የመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን የመሬት አገልግሎቶችን እንዳይሰጡ ወሳኔ መተላለፉን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክሬተሪ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። (አዲ አበባ መስተዳድር)
Leave a Reply